‹‹[ክፍተቶች] ለኔ መልካም አጋጣሚዎች ናቸው›› ሳምራዊት ፍቅሩ የሶፍትዌር ኢንጂነር

ሳምራዊት ፍቅሩ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ ነው፡፡ ትምህርቷን እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ያጠናቀቀችውም አሰላ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ፣ በ2002 ዓ.ም. በማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ ትምህርት ተምራለች፡፡ የኮሌጅ ትምህርቷን በ2004 ዓ.ም. እንዳጠናቀቀች የምትናገረው ሳምራዊት፣ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች፡፡

ከትምህርቷ ጐን ለጐንም በሁለት የሥራ መስኮች ተሰማርታ ትሠራ ነበር፡፡ በአንድ ኩባንያ ውስጥ ሲስተም አናሊስት እንዲሁም በሙዚቃ ድርጅት ውስጥ ሴልስ ማኔጀር ሆና ታገለግል ነበር፡፡

‹‹ሙዚቃ ቤት በሴልስ ሙያ መሥራቴ ብዙ ጥቅም ሰጥቶኛል፡፡ አንድ አልበም ለመሸጥ የማሳመን ኃላፊነት ነበረብኝ፡፡ ይህም በቀላሉ ከሰው ጋር መግባባት እንድችል አድርጐኛል፡፡ በዚህም ጥሩ ልምድ አግኝቻለሁኝ›› የምትለው ወጣቷ፣ በትምህርት የቀሰመችውን ሙያ አገልግሎት ላይ ታውለው ዘንድ ጥሩ አጋጣሚም እንደፈጠረላት ትናገራለች፡፡  

በሙዚቃ ቤት ቆይታዋ ካስተዋለቻቸው ችግሮች መካከል ሸልፍ ላይ የቀረቡት አልበሞች ተሸጠው ሲያልቁ መልሶ ለመተካት መቸገር አንዱ ነበር፡፡ ደንበኞች በሚጠይቁት መጠን አልበሞች ለማቅረብ በማከማቻ ክፍላቸው ምን ያህል እንደቀረ የሚያውቁበት አሠራርም አልነበራቸውም፡፡ አልበሙ ይኖራል በሚል ግምት ደንበኞቻቸው ጥቂት እንዲጠብቁ ብዙ ጊዜም ያግባቧቸዋል፡፡ ማከማቻው ክፍል ሲገባ ግን ዕውነታው ሌላ ይሆናል፡፡ ያሰቡትም ሳይሳካ ይቀርና ደንበኞቻቸውን ይቅርታ ጠይቀው ይልኳቸው ነበር፡፡ ይህም ‹‹ደንበኞቻችንን ያርቅ ነበር›› የምትለው ሳምራዊት፣ በማከማቻ ክፍሉ ምን ያህል አልበሞች እንዳሉ የሚጠቁም (Point of Sales) የተባለ ሶፍትዌር ሠራች፡፡ በ6,000 ብር የሸጠችው ሲሆን፣ የመጀመሪያ ሥራዋ እንደመሆኑ ዋጋው እንዳላሳሰባት ትናገራለች፡፡ በእነዚህ ሥራዎች ጥቂት ካገለገለች በኋላ ሙያዋን ያጠናክራሉ ብላ ባሰበቻቸው የሥራ መስኮች ተሰማርታለች፡፡

የራሷን ድርጅት ከፍቶ የመሥራት ፍላጐት ስለነበራት ተረጋግታ አልተቀመጠችም፡፡ ህልሟን ዕውን ለማድረግም ብዙ ትሞክር ነበር፡፡ በጥረቷም እ.ኤ.አ. በ2010 የውጭ የሥራ ዕድል አገኘች፡፡ ሥራው በኤስኤምኤስ የሚሠራ ሎተሪ ሶፍትዌር ማዘጋጀት ነበር፡፡ በወር 700 ዶላር እየተከፈላት ለሰባት ወር ሠርታለች፡፡

ሥራው አልቆ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰችም የራሷን ሥራ መሥራት የምትችልበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ዕርምጃዋን አንድ ብላ ጀመረች፡፡ በከተማው ውስጥ በመዘዋወር ችግሮችን ማፈላለግ ጀመረች፡፡ ‹‹ችግሮች ለእኔ መልካም አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ያየሁትን ችግር የሚቀርፍ ፕሮግራም እሠራለሁኝ›› ትላለች፡፡ ባደረገችው እንቅስቃሴም ጥረቷን የሚጠይቁ ችግሮች ያጋጥማት ጀመረ፡፡ የተለያዩ የድረ ገፅ ፕሮግራሞችን በአገር ውስጥና ከባህር ማዶ ባገኘችው ዕድል መሥራት ጀመረች፡፡

ከምታገኘው የወር ደመወዝ በመቆጠብም ህልሟን ዕውን ማድረግ ቻለች፡፡ ጐተራ ወንጌላዊት አካባቢ ሀይብሪድ የተሰኘ የራሷን የሶፍትዌር ኩባንያ ከጥቂት ጊዜያት በፊት አቋቋመች፡፡

በከፈተችው ጠባብ ቢሮ ውስጥ ረዳት አልነበራትም፡፡ ሁሉንም ሥራ የምትወጣው በራሷ ነበር፡፡ ቢሮዋን እንደከፈተችም በቆዳ ፋብሪካዎች ውስጥ የተመለከተችውን ችግር የሚቀርፍ ፕሮግራም ሠራች፡፡

እንደ እሷ ገለጻ፣ በፋብሪካዎቹ ያየችው ችግር ብዙ ገንዘብ የሚያሳጣቸው ነበር፡፡ ‹‹በፋብሪካዎቹ አብዛኛው ሥራ የሚሠራው በማሽን ነው፡፡ ማሽኖቹም በዓመት የተወሰኑ ጊዜያት ውስጥ ጥገና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ነገር ግን ጥገና የሚደረግላቸው ሲበላሹ ብቻ ነው፡፡ ጥገናቸውን ጨርሰው አገልግሎት መስጠት እስኪጀምሩ ድረስም ድርጅቱ ብዙ ገንዘብ ያጣል›› በማለት የሠራችው ፕሮግራም ማሽኑ ጥገና ሲያስፈልገው ቀደም ብሎ የሚያስጠነቅቅና ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ ከኪሣራም ነፃ የሚያደርጋቸው እንደነበር ትናገራለች፡፡

ነገር ግን የሥራ ውጤቷን ለፋብሪካዎቹ ብታሳይም በጐ ምላሽ አላገኘችም፡፡ አምነው ሊቀበሏት አልቻሉም፡፡ ‹‹ብዙዎቹ ቢወዱትም ዕውን ሥራውን ያቀልልናል የሚለውን ማመን አልቻሉም፡፡ በነፃ እንዲጠቀሙት ሐሳብ ባቀርብላቸውም በጅ ብሎ የተቀበለኝ አልነበረም›› ትላለች፡፡ ሥራዋ ተቀባይነት ባያገኝም ተስፋ አላስቆረጣትም፡፡ ሌላ አማራጮቿን መሞከር ነበረባት፡፡ ከዚህ ቀደም በባህር ማዶ ሠርታው የነበረውን የኤስኤምኤስ ሎተሪ ፕሮጀክት አጠናክራ ቀጠለች፡፡

ይሁን እንጂ እንደ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅት ምርቷን ብታቀርብም በሎተሪ ሥራ የመሥራት ዕድሉ ያላቸው ሌሎች ተቋማት ነበሩ፡፡ በመሆኑም አጋጣሚውን እንደ ገቢ ማግኛ ዘዴ መጠቀም ለሚችል አንድ በከተማው ለሚገኝ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም አቀረበች፡፡

ፕሮግራሙን የወደደው ተቋሙም ወደሥራ ለመቀየር ፈቃዶችን በማውጣት ላይ ሳለ ለዓባይ ግድብ ተመሳሳይ ፕሮግራም የተጀመረበት ወቅት በመሆኑ ወደ ሥራው ለመግባት የሚያስችለውን ፈቃድ ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍም ተገደደች፡፡    

ያቀረበቻቸው ፕሮጀክቶች በልዩ ልዩ ምክንያቶች በሥራ ላይ ሳይውሉ ቢቀሩም ጥረቷን አላቋረጠችም፡፡ ይልቁንም ባላት የኤስኤምኤስ ልምድም ሌላ ፕሮግራም ለመሥራት ተነሳች፡፡ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ታክሲ ማግኘት የሚችሉበትን ፕሮግራም ለማዘጋጀት እንቅስቃሴም ጀመረች፡፡ ‹‹በመጀመሪያ ምን ያህል የታክሲ ችግር አለ? የምንሠራው ፕሮግራም ምን ያህል ችግሩን ያቀለዋል? የሚሉትን ጥያቄዎች አጠናሁኝ፡፡ ከዚያም ከሕግ አኳያ የሚኖሩትን ኃላፊነቶችና ፈቃድ አወጣሁ›› በማለት ከዓመት በፊት ሥርዓቱን መዘርጋት እንደጀመረች ትናገራለች፡፡

አጠቃላይ ሒደቱን ጨርሶ ለአገልግሎት ለማብቃት አራት ወራት ፈጅቶባታል፡፡ በዚህኛው ሥራዋ መልካም ውጤት ማስመዝገብ እንደቻለችም ትናገራለች፡፡ ተጠቃሚውና የታክሲ ሹፌሮች በአሠራሩ ደስተኛ ሆነው አብረዋት መሥራት የጀመሩት ወዲያው ግልጋሎቱን እንደጀመረች ነበር፡፡ በዚህ ሥርዓት የሚታቀፉ የላዳ ታክሲዎች ሲሆኑ በድንገተኛ ገጠመኞች ዕርዳታ ለሚሹ ሰዎች ሥርዓቱ ትልቅ ዕፎይታ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ‹‹አደጋ ሲያጋጥም፣ ሕመም ሲኖር፣ ፈጥነው በመድረስ አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡ የደኅንነት ጥያቄን በሚመለከትም ታክሲዎቹ የተመዘገቡ በመሆናቸው ከሥጋት ነፃ ናቸው›› ትላለች፡፡

እንደ እሷ ገለጻ፣ አገልግሎቱን ለማግኘት ሁለት የመልዕክት ማስተላለፊያ የስልክ መስመሮችን መጠቀም ግድ ነው፡፡ አንደኛው 8202 ሲሆን፣ ደንበኞች የሚጠቀሙበት የመልዕክት ማስተላለፊያ መስመር ነው፡፡ ሌላው 8812 አሽከርካሪዎች የሚመዘገቡበት ነው፡፡ አሠራሩን በተመለከተም ‹‹ደንበኞች በ8202 መስመር ላይ ያሉበትን ቦታ መልዕክት ይልካሉ፡፡ ያሉበት አካባቢ ከሚገኙ ተሽከርካሪዎች መካከልም ለአንዱ መልዕክት ይተላለፍለታል፡፡ ደንበኛውንና ተሽከርካሪውን ለማገናኘትም የደንበኛው የስልክ ቁጥር ለአሽከርካሪው ይላካል›› በማለት በአንድ አገልግሎት እስከ ስምንት ብር እንደምታገኝ ትናገራለች፡፡ ክፍያውን ከቴሌ የምታገኝ ሲሆን ሒደቱ በሰባት ደቂቃ ውስጥ እንደሚያልቅ ገልጻለች፡፡

ቀስ በቀስ አገልግሎቱን የማስፋፋት ዕቅድ አላት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ከአንድ በላይ የሆኑ ደንበኞች በኮንትራት ታክሲ ወጪውን በጋራ ከፍለው አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት የሚያስችላቸውን አሠራር ለመዘርጋት እንቅስቃሴ ጀምራለች፡፡ በተጨማሪም የትራንስፖርት እጥረት ባጋጠማቸው ቦታዎች ላይ የከተማ ባሶችን በአፋጣኝ ማቅረብ የሚቻልበትን አሠራርም ለመዘርጋት ደፋ ቀና እያለች እንደሆነ ተናግራለች፡፡

በከተማ ውስጥ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር የመቅረፍ ዓላማ እንዳላት የምትናገረው ሣምራዊት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ተገቢውን አገልግሎት ማድረስ የሚችሉ ተሽከርካሪዎችን ብቻ እንደምታስተናግድ ትናገራለች፡፡ ሥነ ምግባር የተላበሱ አሽከርካሪዎችን ለማፍራት ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን እንደምትሰጣቸው ገልጻለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት ትሠራበት የነበረውን ቢሮ ወደ ጉርድ ሾላ በማዛወር ላይ ስለምትገኝ፣ የመልዕክት ማስተላለፊያ መስመሮቹ ለተወሰኑ ቀናት አገልግሎት እንደማይሰጡም ገልጻለች፡፡