‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ብድር ለመስጠት የሚያስችለን ፕሮጀክት ከተፈጠረ የሚለቀቀው ብድር ከፍተኛ መሆኑ አይቀሬ ነው››

ጂን ኪሚያኪ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ዋና ተወካይ

ጂን ኪሚያኪ በኢትዮጵያ የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ዋና ተወካይ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ወቅት የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤንና በቅርቡ ለጃይካ ዓለም አቀፍ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንትነት የተሾሙትን ኃላፊ በመቀበል አስተናግደዋል፡፡ ጃይካ የጃፓን መንግሥትን በመወከል በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት፣ የውኃ አቅርቦት፣ የጤና ትምህርት፣ የግብርና ልማት እንዲሁም የሰው ኃይል መስኮች ላይ ድጋፍ በመስጠት እየሠራ ይገኛል፡፡ ይሁንና ጃፓን ከሌሎች አገሮች አኳያ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው ድጋፍ ውስጥ የሚጎድል አንድ ጉዳይ እንዳለ የሚገልጹት ኪሚያኪ፣ ይኼውም አገሪቱ ከጃፓን ርካሽ ወይም ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰብበትና በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር ሳታገኝ መቆየቷ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ከጃፓን ለመበደር የሚያስችላት ብቃት ቢኖራትም እስካሁን ብድር ለማግኘት ሳትችል ቆይታለች፡፡ ለዚህ አንደኛው ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው አሠራር እንደሆነ የሚናገሩት ዋና ተወካዩ ኪሚያኪ፣ የጃፓን መንግሥት የብድር ፕሮጀክቶችን ለማፅደቅ በሚወስድበት የጊዜ ገደብና የኢትዮጵያ መንግሥት ብድሩን ለማግኘት በሚፈልግበት ጊዜ መካከል ያለው ክፍተት ዋናው ጋሬጣ ሆኖ መቆየቱን ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ግን ወደፊት በሁለቱ አገሮች መካከል በሚደረግ ስምምነት ተፈትቶ ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለመንገድ ግንባታና ለትራንስፖርት ዘርፍ ብድር ለማመቻቸት የጃፓን መንግሥት ፍላጎት እንዳለው ኪሚያኪ አብራርተዋል፡፡ በ0.01 በመቶ ወለድ፣ በአርባ ዓመታት የመክፈያ ዘመንና በአሥር ዓመት የዕፎይታ ጊዜ የሚታሰብ የብድር አቅርቦት ለማመቻቸት መንግሥታቸው ፍላጎት ማሳየቱን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም በጃፓን ዕርዳታ አሰጣጥ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ ምልክትና በመሳሰሉት ላይ ስለሚሠሩ ሥራዎች ጂን ኪሚያኪን ብርሃኑ ፈቃደ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለመጀመር ያህል የቀደሙት የቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ልማት ኮንፈረንስ (ቲካድ) ስብሰባዎች ምን ውጤት አስገኝተው አልፈዋል?

ኪሚያኪ፡- የቲካድ ስብሰባ መካሄድ የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1993 ነበር፡፡ በአፍሪካውያን የወደፊት ጉዞ ላይ ዓለም ጨለምተኛ በነበረበት ወይም ‹‹አፍሮ ፔሲሚዝም›› በሚባለው ወቅት ነበር የስብሰባው ጅማሮ፡፡ በመሆኑም ቲካድ ባለብዙ ፈርጅ መድረኮች እንዲፈጠሩ፣ ስለአፍሪካ የልማት እሴቶች መወያየት የሚቻልባቸው ሒደቶችን ለመፍጠር የታሰበበት ነበር፡፡ በዚህ ላይ በየአምስት ዓመቱ ባለፈርጀ ብዙ የዓለም ኤጀንሲዎች፣ የአፍሪካ መሪዎችና የሚመለከታቸው ሁሉ በጃፓን እየተገናኙ ይመክሩ ነበር፡፡ በቅርቡ በኬንያ ከሚካሄደው የቲካድ ስብሰባ ጀምሮ ግን በየሦስት ዓመቱ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ በኬንያው ስብሰባ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ በተለይም በሰላምና መረጋጋት በአጽንኦት በድኅረ ግጭት የግንባታ ሥራዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ የሚያስችል ውይይት ትኩረት ይሰጥበታል፡፡ ስለአየር ንብረት ለውጥም ውይይት ይደረጋል፡፡ በመሠረቱ ቲካድ ስለእንዲህ ያሉ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት በአፍሪካ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ውይይት እንዲያደርጉባቸው ሒደቶችን ለማመቻቸት የሚተጋ ነው፡፡ በጠቅላላው የአገሮች ተወካዮች፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎችና የጃፓን መንግሥት በጋራ ስለአፍሪካ የሚወያዩበት መድረክ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካ የሩዝ ልማት ጥምረት፣ የካይዘን ሥርዓትና ሌሎችም መሰል ፕሮግራሞች እንዲተገበሩ የሚደግፍ ጉባዔ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምንም እንኳ ቲካድ ላለፉት ሁለት አሥርት ሲካሄድ ቢቆይም ብዙም ውጤታማ ሥራ አላከናወነም ተብሎ ይተቻል፡፡ በአፍሪካ መገለል ጉዳይ ላይ ተቆርቋሪ ሆኖ በመቅረቱ ነው? ወይስ በእውነትም በአፍሪካ አወንታዊ ለውጥ እንዲታይ የሚሠራ ነው?

ኪሚያኪ፡- እንደ እውነቱ በአፍሪካ አወንታዊ ለውጥ መፍጠር እንፈልጋለን፡፡ ሆኖም አንድ አገር ብቻውን በተናጠል ሁሉንም ሊያከናውን ግን አይቻለውም፡፡ ስለዚህም ትስስሮችን እንዲሁም የዕውቀት ልውውጦችና በጋራ መማማር በአፍሪካውያን መካከል እንዲፈጠር እየጣርን ነው፡፡ ለእኔ ገንዘብ መስጠት ጠቃሚ ቢሆንም ተጨባጭነት ያላቸው አሠራሮችን መፍጠር ግን ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኬንያ በአፍሪካ ሲካሄድ የመጀመሪያው የሆነውን ጉባዔ ለማሰናዳት ዝግጅት እያካሄደች ትገኛለች፡፡ ባለፈው በጃፓን በተካሄድ የቲካድ ስብሰባ ወቅት የጃፓን መንግሥት ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለአፍሪካ ለመስጠት ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ይሁንና እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ ገንዘቡ ወደ አፍሪካውያኑ እንዳልመጣ ነው የሚነገረው፡፡ 

ኪሚያኪ፡- በየጊዜው በሚኒስትሮች ደረጃ የሚካሄድ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን የሚገመገም ኮንፈረንስ እናካሂዳለን፡፡ አንደኛው የቲካድ ጉባዔ ተካሂዶ ቀጣዩ ከመጀመሩ በፊት የአፈጻጸም ሪፖርት ይፋ ይደረጋል፡፡ በዚህ ሪፖርት ውስጥ ምን ያህል ቃል እንደተገባና ምን ያህሉ ቃል በገባው መሠረት እንደተለቀቀ መመልከት ይቻላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 ቃል የተገባው ገንዘብ እስከ 2018 ላለው ጊዜ የሚውል ነው፡፡ በ2013 ቃል የተገባው ገንዘብ እስካሁን አልተለቀቀም፡፡ ይህንን ጨምሮ ምናልባት አዳዲስ የገንዘብ አሐዞች በመጪው ቲካድ ጉባዔ ወቅት ይፋ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በኬንያው የቲካድ ስብሰባ የሚጠበቀው ውጤት ምንድነው?

ኪሚያኪ፡- ቲካድ ፈንድ ለመስጠት ወይም ገንዘብ ለማሰባሰብ ቃል የሚገባበት ኮንፈረንስ አይደለም፡፡ በስብሰባው የጋራ መግባባት የሚያስገኙ የተለያዩ ሐሳቦች ልውውጥ እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ ስለጉባዔው አጀንዳዎች ምንነትና ይዘት ላይ ውይይቶች በመካሄድ ላይ በመሆናቸው ሥራው ገና በሒደት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ሆኖም ቁልፍ ተብለው ከሚታሰቡት ነጥቦች ውስጥ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ወይም የአፍሪካ ኢንዱስትሪ ልማት አንዱ ነው፡፡ ማኅበራዊ መረጋጋትና አይበገሬነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችም ይነሳሉ፡፡ ወጣቶችና ሴቶች በዚህ ረገድ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችሉ ነጥቦችም መነጋገሪያ ይሆናሉ፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎችም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሲሆኑ፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት፣ ኢንቨስትመንት እንዲሁም መሠረተ ልማትም ቸል የማይባሉ ናቸው፡፡ እነዚህ እንግዲህ ውይይት ይደረግባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ አንኳር ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለኢትዮጵያ እንነጋገር፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አኳያ ሲነፃፀር ከጃፓን የልማት ድጋፎች ተጠቃሚነቷ ምን ያህል ነው?

ኪሚያኪ፡- ጃፓን ከምትሰጠው የልማት ድጋፍ አኳያ ኢትዮጵያ በጣም ወሳኝ አገር ነች፡፡ ከአሥሩ ዋና ዋና የልማት ድጋፍ ተቀባይ አገሮች አንዷ ነች፡፡ ጃፓን በየትኛውም የልማት ተግባራት ውስጥ ለኢትዮጵያ ቅድሚያ ትሰጣለች፡፡ በመሠረተ ልማት ግንባታ እንደ መንገድና ድልድይ ሥራዎች ላይ ለአገሪቱ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ በግብርና ልማት፣ በውኃ አቅርቦት፣ በትምህርትና በጤና መስኮች ላይ እንሳተፋለን፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ጉልበትን መሠረት ያደረገ የኢንዱስትሪ ልማት ላይ በተመረኮዘ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት በምታደርገው እንቅስቃሴ ሞዴል ሆናለች፡፡ ለእኔ ኢትዮጵያ በሚሰጠው የልማት ድጋፍ ተጠቃሚ የሆነች አገር ነች፡፡  ይህም ሆኖ ግን በድጋፍ እንቅስቃሴያችን ውስጥ ደካማ ነጥብ ነው ብዬ የማስበው በጃፓን የመገበያያ ገንዘብ የን ላይ መሠረት ያደረገ የብድር አቅርቦት እስካሁን እንዲኖር አለማመቻቸታችንን ነው፡፡ በየን ብድር የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች በአብዛኛው የረጅም ጊዜና በዝቅተኛ የወለድ ዕዳ ፋይናንስ የሚደረጉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ከጃፓን ብድር ለማግኘት መሥፈርቱን የምታሟላ አገር ብትሆንም እስካሁን ብድር ሳታገኝ ቆይታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ብድር እንዲለቀቅ ለማድረግ ቅድሚያ ከሰጠናቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ስድስተኛው ዙር የቲካድ ጉባዔ ከመጠናቀቁ በፊት ብድር የሚያገኙ የተወሰኑ ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ብድሩን ለመስጠት መሟላት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ተደራድራችሁ ስምምነት ላይ ደርሳችኋል እንበል፡፡ ምን ያህል ገንዘብ ለአገሪቱ ይለቀቅላታል ተብሎ ይጠበቃል?

ኪሚያኪ፡- እንግዲህ ምን ያህል የገንዘብ መጠን መለቀቅ እንዳለበት ገና አልወሰንም፡፡

ሪፖርተር፡- መንገዶችና ድልድዮች እንዲሁም መሰል መሠረተ ልማቶች ከጃፓን በተገኘ ገንዘብ ኢትዮጵያ ውስጥ መገንባታቸው እውነት ነው፡፡ ይህም ቢባል ግን ጃፓን ለሌሎች አገሮች ከምትሰጠው የልማትና የገንዘብ ድጋፍ አንፃር ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ድጋፍ አነስተኛ ሆኖ ይታያል፡፡

ኪሚያኪ፡- ድጋፍ በምንሰጥበት ወቅት ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን እናካትታለን፡፡ የቴክኒክ፣ የዕርዳታና ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰብበት ብድር ለአገሮች ድጋፍ የምንሰጥባቸው ክፍሎች ናቸው፡፡ የብድር መጠኑ ትልቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብድር ለመስጠት የሚያስችለን ፕሮጀክት ከተፈጠረ የሚለቀቀው ብድር በጣም ትልቅ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታዲያ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ብድር ሊያስገኙ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ለማቅረብ ገና ብቁ አይደለችም እያሉ ነው ማለት ነው?

ኪሚያኪ፡- ኢትዮጵያ ብድር ለማግኘት ብቁ ነች፡፡ ከጃፓን ብድር ለማግኘትም ተገቢዋ አገር ነች፡፡ ትልቁ ፈተናችን ግን በብድር አሰጣጥ ወቅት ያሉት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ነው፡፡ የምናስከፍለው የወለድ መጠን 0.01 በመቶ ሲሆን፣ በጣም ዝቅተኛው ነው፡፡ የብድር መክፈያው ጊዜም 40 ዓመት ሆኖ የመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት የዕፎይታ ጊዜያት ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት ብድር የመሸከም አቅምንና የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለመደገፍ የሚያስቸለው ጥሩ ዕድል እንደሆነ አስባለሁ፡፡ በግሌ ግን መንግሥት ፋይናንሱ በአፋጣኝና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲለቀቅለት የሚጠባበቅ ይመስለኛል፡፡ ይህ ግን እኛ ለምንከተለው የዝግጅት ሒደት ተስማሚ አካሄድ አይደለም፡፡ ይህ ምናልባት ፈተና ከሆኑብን ነገሮች አንዱ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ብድሩን ለማፅደቅ የሚጠይቀው ጊዜ ምን ያህል ነው?

ኪሚያኪ፡- ገና ሀ ተብሎ ከባዶ የሚጀምር ከሆነ ስምምነት ለማድረግ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ፕሮጀክቱን ለመተግበር ተጨማሪ ጊዜ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚጀመር የብድር ፕሮጀክት ለማቅረብ ይፈልጋል፡፡ ልዩነቱ ይህ ነው፡፡ እንደምገነዘበው ፕሮጀክቱን በአግባቡ ካቀድነውና የጊዜ ልዩነቱን በአግባቡ አስልተን ፋይናንሱን ማቅረብ የምችልበት ዕድል  ከተፈጠረ፣ ጥሩ የብድር መጠን ማግኘት የሚችሉ ፕሮጀክቶችን መቅረፅ እንችላለን፡፡ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር መነጋገር ይኖርብናል፡፡  

ሪፖርተር፡- የትኞቹ ፕሮጀክቶች ናቸው የጃፓንን ብድር የማግኘት ዕድሉ ያላቸው?

ኪሚያኪ፡- በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ይመደባል፡፡ በሁለተኛነት የመንገዶች ግንባታና የትራንስፖርት ዘርፍ ለጃፓን ብድር ለማግኘት ብቁ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአነስተኛ መጠን የሚንቀሳቀሱ የሴቶች የንግድ ሥራ መስኮችን የመደገፍ ሐሳብ አለን፡፡ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ይህንን ፕሮጀክት ለማስጀመር እናስባለን፡፡ ሥራው በቅርቡ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም አገሮች ድጋፍ የሚሰጡባቸው የተለያዩ አካሄዶች አሉ፡፡ ጃፓን ለኢትዮጵያ ወይም ለሌላው አገር የምትሰጠው ድጋፍ ከሌላው ልዩ የሚሆንባቸው ሁለት ወይም ሦስት ነጥቦችን ሊጠቅሱልን ይችላሉ?

ኪሚያኪ፡- እንግሊዞችን ካየህ በፈጠራና በልማት መስኮች ላይ አዳዲስ ሐሳቦችን በማመንጨቱ ረገድ ንቁዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል እ.ኤ.አ. በ2000 ውጤት ተኮር ዕርዳታ የሚባል ሐሳብ ይዘው ብቅ በማለት የበጀት ድጋፍ ላይ ያተኮረ ሥርዓት አስተዋውቀዋል፡፡ ይህ ለእንግሊዞች ጥሩ ውጤት ሊሰጥ ይችላል፡፡ እንደሚገባኝ ከሆነ በመሠረቱ የእንግሊዞች አካሄድ የፖሊሲ ማዕቀፍ በመፍጠርና በጀት ላይ መሠረት ያደረገ ሥርዓት በመፍጠር አፈጻጸምን ለመቆጣጠር የሚያልም አካሄድ ነው፡፡ የእኛ አካሄድ ግን የተለየ ነው፡፡ በመጠኑም ቢሆን ቀደምታዊነት ወይም ቀኝ ዘመምነት ያጠቃዋል፡፡ ነገር ግን በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ውስጥ በነበረን ተሞክሮ ላይ መሠረት የሚያደርግ ነው፡፡ ተጨባጭና ተግባር ላይ የተመረኮዙ ሞዴሎችን በመፍጠርና እነሱን በማስፋፋት ትልልቅ የፋይናንሰ ድጋፎችን በካፒታል ዕርዳታ ወይም በብድር መልክ ድጋፍ በማድረግ መሬት ላይ የሚታይ ለውጥ ለመፍጠር የቻልንባቸው አካሄዶች ናቸው፡፡ በአብዛኛው በሰው ሀብት ልማት ላይ የሚመረኮዝ ድጋፍ ነው የምናደርገው፡፡ ጃፓናውያን ባለሙያዎችንና ቴክኒሻኖችን ድጋፍ ወደምንሰጣቸው አገሮች እንልካለን፡፡ ከአገሮቹ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የምንሰጣቸውን ቴክኖሎጂዎች አሻሽለን እንደ አገሩ ሁኔታ ተስማሚ በማድረግ እናቀርባለን፡፡ አቀራረባችን በአብዛኛው ተግባር ተኮር ነው፡፡ እንግሊዞች በአብዛኛው በፖሊሲ ደረጃ ያተኮረ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡ በመሆኑም የእንግሊዝ አቀራረብ ማዕቀፍ ተኮር ሲሆን፣ የእኛ ግን ግብዓት ተኮር የሚባለውን አካሄድ የሚከተል ነው፡፡ በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ውስጥ የነበረን ተሞክሮ ላይ በእጅጉ እንተማመናለን፡፡ ይህ ተሞክሮ በአፍሪካም ተግባራዊነት እንደሚኖረው እምነት አለን፡፡ ምናልባትም በእኛና በምዕራባውያኑ ለጋሾች መካከል መመጋገብ ሊኖር እንደሚችል እናስባለን፡፡  

ሪፖርተር፡- የጃፓን መንግሥት በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ ያተኮረ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የጃፓን ባለሙያዎችም ወደዚህ በመምጣት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ሲያማክሩና በምክክር መድረኮችም ላይ ሲሳተፉ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ሒደት ወደፊትም ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል?

ኪሚያኪ፡- የምክክር መድረኩ ወደፊት ስለመቀጠሉ ጉዳይ እስካሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት አላደረግንም፡፡ ፍላጎታችን ግን የምክክር መድረኩ እንዲቀጥል ማድረግ ነው፡፡ በደቡብ ምሥራቅ እስያ የነበረን ተሞክሮ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ተግባራዊ መሆን የሚችል ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፖሊሲን መቅረፅና የሰው ሀብት ልማትን በካይዘን አማካይነት ማጎልበት ብሎም መሠረተ ልማትን የማስፋፋት ጥረቶች የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሲታከልበት በጣም ወሳኝ የሆነ ሥራ በመሆኑ፣ በዚህ አገር ውስጥ አብዝተን ልንሠራበት የምንፈልገው መስክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከውጭ የሚመጣ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልጋት ዕሙን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ተሞክሮቻችሁን ሲጠቅሱ የልማታዊ መንግሥት ንድፈ ሐሳብን በማቀንቀን ጃፓን ተጠቃሽ አገር ሆና ትገኛለች፡፡ በእስያ እንደሠራው ሁሉ በአፍሪካም የልማታዊ መንግሥት አካሄድ የሚሳካ ይመስልዎታል? አፍሪካ ከግሉ ዘርፍ ይልቅ ጠንካራ የመንግሥት ሚናን እያሰፈነች በመሄድ ልማትን የምታሰፍን አኅጉር ልትሆን ትችላለች ብለው ያስባሉ?

ኪሚያኪ፡- ለዚህ እኮ ነው በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የኢንዱስትሪ ልማት ሒደት የምንደግፈው፡፡ የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም በአፍሪካ ሊተገበር መቻሉ እርግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም የግሉ ዘርፍ ደካማ ሆኖ የሚገኝበት ወቅት ነው፡፡ ደካማ መሠረተ ልማት ያለበት አኅጉር ነው፡፡ የመንግሥት ጠንካራነት የጎላው የግሉ ዘርፍ ደካማ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ይህ ባደጉትና በማደግ ላይ ባሉት አገሮች መካከል የሚታየው ቁልፍ ልዩነት ነው፡፡ በታዳጊ አገሮች ውስጥ መንግሥት በግሉ ዘርፍ ላይ የበላይ የሚሆነው የጥቂቶችን የሞኖፖል ልዕልና ለማስቀረት ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ውስጥ የግሉ ዘርፍ መሠረተ ልማትን እንዲገነባ የሚያስችል አቅም ስለሌለው እሱ ላይ መተማመን አይቻልም፡፡  በምዕራቡ ዓለም ሞዴል መሠረት የግሉ ዘርፍ ያለው አቅም ፈጠራዎችን ለማጎልበትና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትን ለማስፈን የሚያስችል ነው፡፡ መንግሥታት የግሉ ዘርፍ የሚያመነጫቸውን ፈጠራዎች ለማመንጨት አቅሙም ዕውቀቱም የላቸውም፡፡ በታዳጊ አገሮች ውስጥ መንግሥታት በዘመኑ ካሉት ቴክኖሎጂዎች ጋር በመቀራረብ ሌሎች የደረሱበት ደረጃ ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በጥንቃቄ ለመማር የሚያስችሉ ሞዴሎችም ይገኛሉ፡፡ ይህ ሲሆን፣ ግን ሌሎች ላይ ለመድረስ የሚኬድበትንና ግንባር ቀደም አገሮች የሚገኙበትን አካሄድ ማደባለቅ አይኖርብንም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ግንባር ቀደም በሆኑት አገሮች ላይ ለመድረስ ምን ያህል ጊዜ ይፈጅባቸዋል?

ኪሚያኪ፡- ጃፓንን ካየህ በፍጥነት ያደገችና በአሁኑ ወቅትም የግንባር ቀደምትነት ቦታዋን የያዘች አገር ነች፡፡ ስለዚህ ሌሎች የደረሱበት ደረጃ ላይ የመድረስ ሒደት ጃፓንን የሚመለከት አይሆንም፡፡ አይሠራምም፡፡ ይሁንና ሌሎች የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ የሚያስበውን የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ይዞ ወደ ግንባር ቀደምት አገሮች ተርታ ለመምጣት አንዳንድ ጊዜ ከባድ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡ ሌሎች ከደረሱበት ለመድረስ ያስቻለን ጥሩ የስኬት ተሞክሮ አለን፡፡ በጣም ፈጣን ወይም አዝጋሚ ለውጥ መፍጠር ሊያስፈልገን የሚችልበት ሒደት ይኖራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጃፓን ባለበት የቆመ የኢኮኖሚ ዕድገት ችግር ውስጥ ገብታለች፡፡ ኢኮኖሚው ማደግ አልቻለም፡፡ በእኔ አፈታት ይህ የሆነው ጃፓን በጣም ባህላዊና ጠንካራ የማኅበረሰብ ትስስር የሰፈነባት አገር በመሆኗ ነው፡፡ የዕድሜ ልክ ለውጥ ላይ የሚያጠነጥን ሥርዓት ስለምንከተል፣ ይህም በራሱ ማኅበረሰብ ላይ ብቻ ታማኝነቱን በማፅናቱ ያመጣው ችግር ነው፡፡ እንደ አሜሪካ ያሉ ኃይለኛና ፈጣን ለውጥ የሚያመጣ ማኅበረሰብ ላይ የተመረኮዙ አገሮች በየጊዜው አዳዲስ ሰዎችን በመቀበል፣ አዳዲስ ፈጠራዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በማመንጨት ንቁ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ጃፓን ግን እንደ እነዚህ አይደለችም፡፡ ታዳጊ አገሮች ግን በርካታ ጥሩ ሞዴሎችን ከእስያ አሊያም ከምዕራቡ ዓለም በመውሰድ መማር የሚችሉባቸው ዕድሎች አሏቸው፡፡ እዚህ ላይ ቁልፉ ነጥብ አንዱ ከሌላው መማሩ ላይ ነው፡፡ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ፣ የግሉ ዘርፍም ከመንግሥት ለመማር መጣር አለባቸው፡፡ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ምክክርን የምናበረታታው አንዱ ከሌላው እንዲማርና እንዲያውቅ ለማስቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሌሎች አገሮች ለመማር በጣም ንቁ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጃይካ ‹‹ሻምፒዮን ምርቶች›› የተሰኘ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ እያካሄደ ይገኛል፡፡ ዋና ዓላማውም የባለቤትነት መብታቸው የተከበረላቸው ብራንድ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የኢትዮጵያ ቆዳ ውጤቶችን ብራንድ እንዲሆኑና ለዓለም ገበያ እንዲበቁ የማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ እንዴት እየተጓዘ ነው?

ኪሚያኪ፡- ኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ያህል በረሃብ የተነሳ አሉታዊ ምሥል ይዛ ቆይታለች፡፡ ሆኖም አገሪቱ ጥራት ያላቸው ምርቶችን ለማምረት የሚያስችላት ትልቅ አቅም አላት፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያሉ ምርቶች ውድ በሆኑ የዓለም ገበያዎች ላይ መውጣት እንዲችሉ እንፈልጋለን፡፡ ለመጀመር ያህል ትኩረታችንን በጃፓን ውድ ገበያዎች ላይ አድርገናል፡፡ በቅርቡ በጃፓን የተደረገ ጥናት የሚያሳየው የቆዳ ውጤቶች ትልቅ የገበያ ዕድል እንዳላቸው ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ የደጋ ቆዳ ውጤቶችን የሚያስተዋውቅ ብራንድ በመፍጠር የንግድ መለያ ምልክት እንዲሆን አድርገናል፡፡ ከፍተኛ ጥራት ያለው የኢትዮጵያ የደጋማው አካባቢ ቆዳ ‹‹ኢትዮጵያን ኃይላንድ ሃይ ኳሊቲ ሌዘር›› በሚል ስያሜ በጃፓን አገር እንዲመዘገብና የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ጥበቃ የተደረገለት ምርት በመሆን፣ በጃፓን ገበያዎች እንዲቀርብ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በኢትዮጵያም የንግድ ስያሜው እንዲመዘገብና የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት እንዲመዘግበው ሒደቶችን እያጠናቀቅን ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በባለቤትነት የሚካሄደው በኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር በኩል ነው፡፡ ማንኛውም የማኅበሩ አባል ተገቢውን ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያሟላ ምርት ማቅረብ እስከቻለ ድረስ ከዚህ ንግድ ምልክቱ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምርቱን ብራንድ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር ጥራትን የማሻሻል ሥራዎች ላይም ትኩረት እናደርጋለን፡፡ እስካሁን ይህ አካሄድ ውጤታማ በመሆኑ እንገፋበታለን ብለናል፡፡ ከቆዳ ባሻገር ቡናም ተመሳሳይ ዕድል ሊያገኝ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ቅድሚያ ግን ዋና ዋና የሆኑ ጉዳዮችን መመልከቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የጃፓን ኢንቨስተሮችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ትልቅ ጉጉት አድሮበታል፡፡ በጃፓኖች ፍላጎት ላይ የተመሠረተና ለእነሱ ብቻ የሚውል የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት የሚያስችል ቦታም አቅርቧል፡፡ በዚህ ረገድ የጃፓን ኢንቨስተሮች ምላሽ ምን ይመስላል?

ኪሚያኪ፡- እውነቱን ለመናገር ወደዚህ መምጣት የሚፈልጉ በቂ የጃፓን ኢንቨስተሮችን ማግኘት አልቻልንም፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጃፓን ኢንቨስተሮችን ወደ ኢትዮጵያ ኢንዲመጡ ለማድረግ ሰፊ ጊዜ እንደሚያስፈልገን እናስባለን፡፡ ለጃፓኖች የሚስማማ የኢንዱስትሪ ፓርክ በሁለት ወይም በሦስት ዓመት ውስጥ መገንባት ከቻልን ደህና ቁጥር ያላቸው ኢንቨስተሮችን ማምጣት እንደምንችል አስባለሁ፡፡ እንደ ካምቦዲያና ቬትናም ያሉ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮችን ተሞክሮ በምናይበት ወቅት፣ በአብዛኛው ኢንቨስተሮችን በመሳብ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲያመርቱ የማድረግ ሒደቱ ከአምስት እስከ ስምንት ዓመት የሚፈጅ ሆኖ ይገኛል፡፡ እንዲህ ያለው ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ዕውን እንዲሆን የሚያስችለው የጊዜ ገደብ ከስምንት እስከ አሥር ዓመት ሊሆን እንደሚችል አስቀምጠናል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የጃፓን ኢንቨስተሮች ከዚህ ባጠረ ጊዜ ውስጥ እንዲመጡና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ይፈልጋል፡፡ ይህም ሌላኛው ልንመለከተው የሚገባ ጉዳይ ቢሆንም እየሠራንበት ነው፡፡ ጥራታቸውን የጠበቁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዴት ሊገነቡ እንደሚገባ ምክር በማግኘት ሒደት ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንቨስተሮችን ከጃፓን የማምጣት እንቅስቃሴያችሁ ቢሰምር ምን ያህል ሊመጡ እንደሚችሉ ታስባላችሁ? መምጣት አለባቸው ብላችሁ የያዛችሁት ቁጥር ምን ያህል ነው?

ኪሚያኪ፡- ይህንን በእውነቱ አላውቅም፡፡ ኢንቨስተሮች ልክ እንደ አዕዋፍት ናቸው፡፡ የሚመቻቸውና መስህብ ያለው አካባቢ ሲያገኙ ይመጣሉ፡፡ ይቆያሉ፡፡ በሚጠብቁት ደረጃ ነገሮችን ካላገኙም ጥለው ይሄዳሉ፡፡ በኬንያ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጃፓን ኢንቨስተሮች አሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካም ትልቁን ቁጥር የያዙ ጃፓናውያን ኢንቨስተሮችን ተቀብላለች፡፡ ኢትዮጵያ ግን የተሻለ አቅም አላት፡፡ እርግጥ እዚህ ለሰዎች ብዙ ሥልጠና መስጠት ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ሆኖም ጥራት ያለው የሰው ሀብት አላችሁ፡፡ በዚህ አገር የተገነባውን የመሠረተ ልማት እንዲሁ ልናልፈው አንችልም፡፡ የእኔ ዓላማ ለዚህ አገር የሚሆን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ መንደፍ ነው፡፡ ምናልባት ለአሥር ዓመት የሚሆን፡፡ መንግሥት ይህንን ላይጠብቅ ይችላል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ማየት ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው መስክ ጠንካራ ትሆናለች ብዬ አስባለሁ፡፡