‹‹ብዝኃነትን ያከበረች አገር - ኢትዮጵያ!››

ዕውን አሁን ይኼ እውነት ነው?!

በበሪሁን ተሻለ

የዘንድሮው የዓለም የፕሬስ ቀን የኢትዮጵያ አከባበር የጥንት የጠዋቱንና የተለመደውን የአንደበት ወግ እንኳን ያላሟላ ከክብረ በዓላዊና ከሥነ ሥርዓታዊ ግርግሩ እንኳን የጎደለው፣ ፋሲካ (ትንሳዔ) በታላቅ ኃይሉ ጎድን ብሎ ‹‹ድምፁን›› ካጠፋው ከሜይዴይ በዓል በላይ መታወስ ያልቻለ ሆኖ ውሏል፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን እንደሚገባው አለመከበሩ የሚገቡትን ጥያቄዎች አንግቦና አስተጋብቶ የራሱንና የአገርን ‹‹እንዴት ሰነበች?›› የዘገባ፣ የግምገማና የሒሳብ ማወራረድ ሥራ አለመሥራቱ ተጠያቂ፣ የበዓሉን አከባበር ለብቻው አግኝቶ የመራውና የተቆጣጣረው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሊሆን አይችልም፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዓላማና ተግባር ‹‹በመንግሥት ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ሥርዓት ውስጥ›› የመንግሥትን የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ መሥራት ነው፡፡ ለጊዜያዊ ሥራ ለሚመጡትም ሆነ ተቀማጭነታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ለሆነ የውጭ አገር ዜና ወኪሎች ፈቃድ መስጠት ከሚለው ከተቋቋመበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ (ታኅሳስ 2001) ያለብልኃት ከተሰጠው ከዚህ ሥልጣን በስተቀር፣ ሌላ ምንም ዓይነት ሚዲያ ነክ የሬጉላቶሪ ኃላፊነት የሌለው ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ የመንግሥት ጽምፅ ነው፡፡ የመንግሥት ቃል አቀባይ ነው፡፡ የመንግሥት አፈ ቀላጤ ነው፡፡ የመንግሥት ኢንፎርሜሽን ጠቅላይ መምርያ ነው፡፡ የመንግሥት ገጽታ ግንባታ ዋና ኃላፊ ነው፡፡ የመንግሥት ልዩ ልዩ የኅትመት፣ የኦዲዮና የቪዲዮ ምርቶች አምራች ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሚዲያው ተጠቃሚ ነው፡፡ የሚዲያው የመንግሥት ኢንፎርሜሽን ዋነኛ ምንጭ ነው፡፡

የፕሬሱ ሚና በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው የማንም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት መብት መድረክ ሆኖ ማገልገል ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነት የደራ ገበያ ሆኖ ማገልገል ነው፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ከሌሎች መካከል ‹‹የመንግሥት ቃል አቀባይነት ሥራዎችን ጨምሮ የኢንፎርሜሽን ዋነኛ ምንጭ በመሆን ማገልገል፣ የመንግሥት መልዕክቶች መቅረጽና በልዩ ልዩ መንገዶች ማሠራጨት፣ በአገራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የመንግሥትን አቋም መግለጽ፤›› ነው፡፡ በዚህ መካከል ሁለቱም ሥራ ላይና መንገድ ላይ ይገናኛሉ እንጂ አንድ አይደሉም፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት (ፕሬስ ሴክሬተሪ፣ ወዘተ) ሚዲያ አይደለም፡፡ ሚዲያም (የመንግሥት ሚዲያም ጭምር) የመንግሥት አፈ ቀላጤ (ቃል አቀባይ) አይደለም፡፡ አይሆንም፣ አይገባምም፡፡

ሲጀመር የመንግሥት ቃል አቀባይና አወዳሽ እንደሆነ ተቃኝቶ የመንግሥት ባለሟልና አገልጋይ ሆኖ በሕዝብ ላይ የተሠራ ኃይል ሆኖ የተፈጠረው የጋዜጠኛነት ሙያ መጀመርያ ይህንን አውቆ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ቁርጥ አቋም ወስዶ የገዛ ራሱንና የመንግሥትን፣ የሚዲያውን ሥራና የመንግሥት ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሥልጣንና ተግባር ነጣጥሎና ለያይቶ ግንኙነታቸውን አልወሰነም፡፡

ሚዲያው ስለፕሬስ ነፃነት ቀን አከባበር የዘንድሮውም ሆነ ሌላ ድምቀትና ይዘት ከመነጋገሩ በፊት፣ መጀመርያ ሚዲያ ወይም ፕሬስ ማለት ምን ማለት ነው? ፕሬስ ማለት የትኛው ነው? (የትኛውስ ፕሬስ አይደለም)? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ በሚዲያውና በሚዲያው ተቆጣጣሪ የሥልጣን አካላት መካከል ያለውን ግንኙነት መረዳት፣ የወሰን ክልሉንና ዳር ድንበሩን ማበጀት አለበት፡፡

የዘንድሮውን የፕሬስ ነፃነት በዓል ቀን በአንፃራዊነት ከሌሎች ያለፉት ዓመታት ይበልጥ ያደበዘዘውም፣ ከምንም በላይ ባለቤቶቹ ራሳቸው (በሥራ ላይ ያሉት የፕሬስ ተቋማት) እጅ ሰጥተው፣ ታክተው አልገኝም ያሉበት መሆኑ ጭምር ይመስላል፡፡ ይህ በዕለቱ በሥፍራው የመገኘትን (ያለመገኘትን) ጉዳይ ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ አነሰም በዛም፣ ከፋም ለማም ለምልክትም ያህል ቢሆን የሚላወሱት ፕሬሶች ዕለቱን የአንድ ቀን ክብረ በዓል ብቻ አድርገው ሳይቆጥሩ፣ ዓመቱን በሙሉ የገዛ ራሳቸውና የፕሬስ ተቋሞቻቸው የደኅንነትና የጤንነት ምርመራ ጉዳይ አድርገው ሲያሰላስሉትና ሲሰናዱበት የቆዩበት ማድረግ ነበረባቸው፡፡ የሚያዚያ 25 የፕሬስ ነፃነት በዓል ውሎ ያስመዘገበው አንዱ ጉድለት ይኸው ነው፡፡

የግዳቸውን ያሉትና አሉ የሚባሉት የሙያ ማኅበራትም ለነፃ ሚዲያና ለሚዲያ ነፃነት የሚያደርጉትን ትግል ማስመዘንና ማስመዝገብ ቀርቶ፣ ስለመኖራቸውና ስለህልውናቸው ከወሬ በቀር የሚያስረዳላቸው አንድም ነገር የሌላቸው ናቸው፡፡ እጅግ በጣም የሚገርመው የፈዘዘ ሚና ካላቸው ከሚዲያ ተቋማቱ፣ ከባለሀብቱና ከጋዜጠኞቹ ውጪ ያሉትኛ ‹‹ደንበኛ›› በባደረጋቸው የመንግሥት ሚዲያና በእንዲህ ያለም ስብሰባ ንቁ ተሳታፊ ሆነው የሚታዩት የዩኒቨርሲቲዎቻችን፣ የጋዜጠኝነት ትምህርት መምህራንና ምሁራን ናቸው፡፡

ከፕሬስ ነፃነት ጋር የተያያዘውን የዩኒቨርሲቲዎችን የጋዜጠኝነት የትምህርት ከፍልና የዚህን የትምህርት ክፍል ምሁራንና መምህራን ጥብቅ እና ወሳኝ ሚና ለጊዜው እንተወው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ሲባል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ራሱ የአካዳሚ ነፃነት፣ አዲስ ነገርንና እውነትን የመፈለግና የመነጋገር እንቅስቃሴ ዋና መፍለቅለቂያ መሆን የሚገባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ የጋዜጠኝነት የትምህርት ተቋማትም ይኸው ይመለከታቸዋል፡፡ ማሰብን፣ ማስተዋልን፣ መረጃን በፈርጅ በፈርጅ መለየትንና ማዛመድን፣ መተንተንን፣ መፈተሽንና ንጥረ ሐሳብ አርቅቆ ማቅረብን የሚማሩበትና የሚያስተምሩበት መድረክ ነው ሲባል እንሰማለን፡፡

ኦፊሴል መድረክ ላይ ተሰይመው ከዚህ ተቋም መጡ የሚባሉትን ስናይ ግን ስለፕሬስ ነፃነት መማር ቀርቶ ስለአካዴሚ ነፃነት ህልውና እንጠራጠራለን፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይህንን ክህሎት አከርካሪያቸው ያደረጉ መናገርና መነጋገር የሚፍለቀለቅባቸው ቦታዎች ስለመሆናቸው እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡

የዘንድሮውን የፕሬስ ነፃነት ቀን እዚያው ሆቴሉ ቅጥር ውስጥና አዳራሹ ውስጥ ልዩና አስገራሚ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ‹‹የሚዲያ ብዝኃነትን ያከበረች አገር ኢትዮጵያ!›› የሚለው መፈክር ነው፡፡ ዕውን ኢትዮጵያ የሚዲያ ብዝሃነት ያከበረች አገር-ናት ወይ? ወዘተ ወደሚሉት ጥያቄዎች በቀጥታ ወይም እግረመንገዳችንን ከመግባታችን በፊት ይህን ለቋንቋችንም ለሕይወታችንም አዲስ የሆነው የብዝኃነትን የራሱን የቃሉንና የጽንሰ ሐሳቡን ትርጉም ለማየት እንሞክር፡፡

ኢትዮጵያ በጣም መጠነ ሰፊና የዳበረ ሕይወታዊ ሀብት ስብጥር የሚገኝበትና በዓለም ላይ ይህን መሰል ፀጋ ካላቸው አካባቢዎች አንዷ ናት፡፡ የኢትዮጵያ የዕፅዋት፣ የእንስሳትና የጥቃቅን ህዋሳት ክምችትና ስብጥር የኢትዮጵያ ሕይወታዊ ሀብት ነው፡፡ ለሕዝቦቿ ጥቅምና ብልጽግና የሚውል ከፍተኛ ፀጋዋ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዥጉርጉርነት ግን በተፈጥሮ ሀብቷ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሆድ ከዚህ የበለጠ ሰፊና ዥንጉርጉር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቋንቋው፣ በባህሉ፣ በሃይማኖቱ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአስተሳሰቡ ልዩ ልዩ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሕዝብም የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ይባላል፡፡ ‹‹ሕዝብ›› ጥቅል ብዛትን ‹‹ሕዝቦች›› ዓይነት ብዙነትን ይገልጻሉ፡፡ (በነገራችን ላይ አንዱ ‹‹የነፍጠኛ›› ሌላው የዴሞክራት ወይም የብሔርተኛ መለያ ሆነው አሁን ሲያገለግሉ የምናያቸው እነዚህ ቃላት፣ የብዝኃነታችን ዕውቅና እንኳን ገና ጭንጋፍ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው)

ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያየ መልክና ልክ ዓይነተ ብዙ ነው፡፡ ዥንጉርጉር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች አገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩት ቋንቋዎች ብዙ ናቸው፡፡ የሐሳብ ልዩነት ደግሞ ከዚህ በላይ የሰፋ ነው፡፡

ኢትዮጵያን በአንድ ሃይማኖትና በአንድ ቋንቋ ውስጥ አንድ የማድረግ የተከታታይ መንግሥታት ፖሊሲ አገሪቷን የእልቂት፣ የረሃብና የፍዳ አገር አድርጓት አልፏል፡፡ የቋንቋንና የሃይማኖትን እኩልነት የአገር ሕግና ወግ ለማድረግ ጅምሩ ተይዟል፡፡ ገና ብዙም ይቀረናል፡፡ በአስተሳሰብ ብዝኃነት ረገድ ግን ገና የተነካ ነገር የለም፡፡ እንዲያውም ሁሉም ነገር አድሮ ጥሬ እየሆነ በመምጣቱ፣ በሌሎች ብዝኃነት ላይ የታየውን ጅምር የሚፈታተን አደገኛ ከመሆን አይመለስም፡፡

በጥቅል ብዛቱ ሕዝብ፣ በዓይነት ብዙነቱ ሕዝቦች የሚባለው ሕዝብ በአስተሳሰቡ ደግሞ ልዩ ልዩ ነው፡፡ እንደ ሃይማኖት፣ እንደ ብሔረሰብና እንደ ባህል እንኳን በስያሜ በቁጥር የሚታወቅ መለያ የለውም፡፡ የሕዝብ ውስጥ አስተሳሰብ ልዩ ልዩና ብዙ፣ የማይጣጣምና የማይገጥምም ነው፡፡ እንዲህ ማለት ግን ክፉ ነው፣ አደገኛ ነው ማለት አይደለም፡፡ አደገኛ የሚሆነው ሲታፈን ነው፡፡ መብላላት ሲያቅተው ነው፡፡ ለፍላጎቶቻቸውና ለዓላማቸው ዓርማ አበጅተው የፖለቲካም ሆነ የሕዝባዊ ድርጅትነት ቀለም ቀብተው የሚነቃነቁ ድርጅቶች ሲጠፉ ወይም ገደብ ሲደረግባቸው ነው፡፡

ፕሬስ ደግሞ ይህን ለመሰለው፣ ለተለያየውና ዥንጉርጉርነቱ ጭምር ቅጥ አምባሩ ለጠፋው የሰው አመለካከት ልክና መልክ ይሰጣል፡፡ ከሁሉም በላይ  ደግሞ ብሶት አለመመርቀዙን ያረጋግጣል፡፡ የሕዝብ አስተሳሰብ፣ ፍላጎትና ዓላማ አደባባይ የሚወጣው ግን በአንድ ወይም በተወሰኑ ‹‹ባለአደራ›› የሬዲዮ ጣቢያዎችና ጋዜጦች ብቻ አይደለም፡፡ የመጀመርያው የብዝኃነት መነሻ ብዙ ሚዲያ መኖር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬም ሲበዛ የዚህ ደሃ ናት፡፡

ይህ ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› ነው ሲባል እስኪታክተን ሰምተናል፡፡ ያታከተን ግን የኢትዮጵያ ድምፅ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ድምፅ የሚያስተናግድ ብዙና ዝርዝር ሚዲያ ኖሮ አያውቅም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሬዲዮና የቴሌቪዥን ድርጅቱ ስም ከተቀየረ በኋላ ራሱን ‹‹የብዝኃነት›› ድምፅ አድርጎ ሰይሟል፡፡ በየዕለቱም ዜና አንባቢዎቹ ይህ የብዝኃነት ድምፅ ነው እያሉ ሲያገሱብን እናያለን፡፡

መጀመርያ ነገር ኢቲቪ ይህን ለመሆን ያበቃኝን የፐብሊክ ሚዲያነት (ብሮድካስትነት) ለውጥ አግኝቻለሁ ከሚለው ውሸት እንነሳ፡፡ ኢቲቪ ወይም ኢቢሲ ዛሬም በሕግ ጭምር የመንግሥት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ራሱ ‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል፤›› ሲል ደነገገ፡፡ ሚዲያው የመንግሥት ነው አለ፡፡ በእንግሊዝኛም የ(State) ሚዲያ ነው ያለው፡፡ በ1987 ዓ.ም. በሽግግሩ ዘመን የወጣው የሬዲዮና የቴሌቪዥን፣ የፕሬስ ድርጅትና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ራሱ ድርጅቶችን የጠራቸው በስማቸው ነው፡፡ የመንግሥት ናቸው ብሎ ነው፡፡

ፐብሊክ ብሮድካስት ማለት የመጣው ከ1999 ዓ.ም. በኋላ ለዚያውም በእንግሊዝኛ ቋንቋ በብሮድካስት ሕጉ ነው፡፡ የብሮድካስት ሕጉ የአማርኛ ስያሜ ግን የብሮድካስት አገልግሎት ዓይነቶችን የመንግሥት፣ የንግድና የማኅበረሰብ ማለቱን አልተወም፡፡ አዋጁና ሕጉ በአማርኛ የመንግሥት በእንግሊዝኛ የፐብሊክ ያለውን፣ በአማርኛ የሕዝብ ብሎ መተርጎምና በዚያ መጥራት የተጀመረው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን በመመርያ ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ ፐብሊክ ማለት የሕዝብ ማለት ነው ብሎ ከተረጎመና የአዋጁን ስህተት ‹‹ካረመ›› በኋላ ነው፡፡

ብልኃት እንኳን የጠፋው የስያሜው ጉዳይ አስተዛዛቢነት እንዳለ ሆኖ አንድ የመንግሥት አፈ ቀላጤ የነበረ ሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ጣቢያ የፐብሊክ ለማድረግ ከአዋጅ በላይ የትራንስፎርሜሽን ሒደት ያስፈልገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ግን ይህንን አላደረገም፣ አልሆነም፡፡

የኢቢሲ አስተዳደር አሁንም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነው፡፡ በገዛ ራሱ ፈቃድ የሚተዳደርና ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29(5) የደነገገው ዛሬም ገና የሚታሰብ አይደለም፡፡ ኢቲቪ ምንም ሆነ ምን ግን እንኳን ብዝኃነትን የሚያነሳውን አንድ የወሬ ጭብጥ ሌላኛውን ገጽታ እንኳን ማስተናገድ የማይችል፣ ይህንንም ስላደረገ ወይም ስላላደረገ የሚወቀስና የሚከሰስ የጥፋት መለኪያ የወጣለት፣ የተጠያቂነት ግዴታ ያለበት ድርጅት አይደለም፡፡ የኢቲቪ የዜናና የኢንፎርሜሽን ይዘት በመንግሥት አጀንዳ አምሳል የሚቀረጽ ነው፡፡

በአጠቃላይ የመንግሥት ጋዜጠኛ ሥራ ራሱ ከመንግሥት አገልጋይነት (ባለሟልነት) ከመንግሥት ቃል አቀባይነትና አወዳሽነት ገና አልወጣም፡፡

ዕውን ኢትዮጵያ የሚዲያ ብዝኃነትን ያከበረች አገር ስለመሆኗ ዋና መለኪያውና መመዘኛው ግን፣ አንድ የመንግሥት የሬዲዮ (የቴሌቪዥን) ወይም የግል የፕሬስ ተቋም ብቸኛ በተናጠል አይደለም፡፡ የዚህ መመልከቻ መስታወት ኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነው አጠቃላይ የፖለቲካ ምኅዳር ነው፡፡

አገራችን ዛሬም የተለያዩ ሐሳቦችን በጤናማነት መቀበል ያልተለመደባት አገር ናት፡፡ በጽንፍ ከማሰብ ገና አልወጣንም፡፡ በጭፍን ጥላቻና ተቃውሞ ውስጥ መባከናችን አልቀረም፡፡ የፖለቲካ ቡድኖች በጠላትነት መፈራረጃቸው መሟሸሽ ቀርቶ ነውር አልተባለም፡፡ በተፃራሪነት መተያየት፣ ልዩነቶችን የማይታረቁ አድርጎ መፈረጅ ዛሬም የአገር ወግና ባህል ነው፡፡ በወዳጅና በጠላት ማዕዘኖች ውስጥ ማሰብ፣ በእንዲህ ዓይነቱ ሁለት ተቃራኒ ማዕዘኖች የታጠረ አስተሳሰብ ውስጥ መውደቅ፣ በሁሉም ወገን የመሰከርነውን ሁሉ አደጋ አሳይቶናል፡፡ ተቃውሞና ትችት እንፈራለን፡፡ ተቃውሞና ትችት ወይም የተለየ ሐሳብ ሲመጣ ይህ ጠላቶቻችን የሚሉት ነው፡፡ ሌላ ስውር ዓላማ ያለው ወገን ነው፡፡ ድርጅታችንን ለአደጋ የሚያጋልጥ ፉክክር ነው ወደሚል ጥርጣሬና ውንጀላ እንሮጣለን፡፡ እኔ ወይም የእኔ ወገን በጎ ነገሮች አሉት ብሎ ከመናገርና ከመከራከር ይልቅ፣ ተቃራኒዬ ጠላቴ እኩይ ባህርይ አለው ማለት የተካንበት የጨዋታ ሕግ ነው፡፡ እኔ ብቻ ልክ እንጂ ሁለታችንም ተሳስተን ወይም ተስቶን ቢሆንስ? ትክክለኛው ነገር ከሁለታችን ውጪ ቢኖርስ? ብሎ ነገርና እውነቱን ፍለጋ አልፈጠረብንም፡፡ መልካሙና መጥፎው በሁለታችን በኩል አንድ ላይ ተሰናስሎ እንዳለስ የሚል ያልተዘጋ አመለካከት ጨርሶ አናውቅም፡፡ አንዱ የሌላውን ጥሩ ቢናገር ትልቅ ፖለቲካዊ ሽንፈት ነው፡፡ ወይም ነውር ነው፡፡

‹‹የአገር ፍቅር ያለው›› እና የሌለው፣ ሕዝባዊና ፀረ ሕዝብ፣ ወዘተ የሚሉ ጥንድ ተቃራኒ ጥጐች ይዘን፣ ሁሉን ነገር በወዳጅና በጠላት ዓይን በሚሰፍር አመለካከት የተቀየደ ህሊና ይዘን ከልዩ ልዩ አቋሞችና አመለካከቶች ጋር አብሮ በሰላም ለመኖር አንመችም፣ አንችልም፡፡ ያለጠላትነት፣ ወዳጅ ጠላት ሳይባባሉ ልዩ ልዩ አመለካከቶች አደባባይ የሚወጡበት፣ የሚከራከሩበትና ለአገራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ልማት የሚተጋገዙበት፣ በጎና ትክክለኛ ድባብ በመፍጠር ፋንታ አንድን አመለካከት ብቻ ከዳር እስከ ዳር ለማስፈን እየጣሩ ‹‹ልዩነት ውበታችን›› ነው ማለት ለማንም አይበጅም፡፡ በአንድ ፓርቲና በመስመሩ የመመራት ጉዳይም ከሐሳቦች ጋር ውድድር ገጥሞ ሐሳብን በሐሳብ፣ አመለካከትን በአመለካከት የመርታትና ሰፊ ተቀባይነት የማግኘት፣ ይህንንም በሕዝብ ነፃ ድምፅ የማረጋገጥ እንጂ ሌላውን የለም ብሎ ክዶ እኔ ብቻ ልክ በሚል ወፍራም ዳፍንት ተይዞ አቋምን በአጠባና በአፈና እየጫኑ አይደለም፡፡

በዚህ በያዝነው ግንባት ወር ውስጥ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚታዩት የግንቦት 20 ነክ ፕሮግራምና የፕሮግራም ማስታወቂያዎች የሚያስታውሱት አንድ ዓብይ ጉዳይ፣ የደርግ መውደቅና የኢሕአዴግ ሥልጣን መያዝ ከትግል ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሰናበት ማለት እንዳልሆነ፣ ይልቁንም አዲስና ያልነበረ ሰላማዊ ትግል መጀመሩ የተበሰረበት ጊዜ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ!›› ዝነኛ የሆነውና በሰፊው የታወቀው የኔ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሳግ እያስቸገራቸውና እንባ እየተናነቃቸው መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ ሲሉ፣ የትጥቅ ትግል አበቃ ከዚህ በኋላም ምክንያት የለውም ብለው እንጂ ትግል አበቃ ብለው አይደለም፡፡ አላሉምም፡፡ እንዲያውም ትግሉ በሰላማዊ መልኩ እንደ አዲስ ጀመረ ብለው መርቀው ከፈቱት፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሚነሳው ጥያቄ ኢሕአዴግ ራሱ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት ተለወጠ ወይ? እሱና ሌሎችም አካላትና ድርጅቶች ይኸው ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መለወጥ የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር መያዝ ቻሉ ወይ? ወይስ ከተለመደው የጦርነት ሥልትና ቋንቋ መውጣት ቸገራቸው ወይ? የሚለው ነበር፡፡

ይህ ከሆነና እንዲህ ከተባለ ግንቦት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. 25 ዓመት ይሞላናል፡፡ አሁንም የጠላትነት ፖለቲካ ቀስፎ ይዞናል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የጠላትነት ፖለቲካን ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በየበኩላቸው ሲነቅፉት እንሰማለን፡፡ ሆኖም ግን ከአፍ አልፈው በመካከላቸው ያለውን ገደል ለመናድ ጥረት ሲያደርጉ፣ ይህም የሚጠይቀውን ዕይታና አመለካከት ሲያስተናግዱ አናይም፡፡ ስለሆነም ሁለቱም በተለያዩ የአገር ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን ላይ ቢወጣ፣ በተራው ተቃዋሚ ሆኖ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ከመቆየት ነፃነቱ ይልቅ በቀል ሲከተለው እያየ፣ ይህ እንዳይመጣ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ አባዜ ውስጥ ተወጥሯል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የአቻ ለአቻ ግምገማ ሥርዓት የኢትዮጵያን ጉዳይ በመረመረበት ወቅት አስረግጦ ያስታወቀው፣ አፍረጥርጦ የገለጸው፣ አስቀድሞ ፈርቶ የተናገረው ይህንኑ ጉዳይ ነበር፡፡ ከተቃዋሚ/ተቃዋሚዎች ጋር እንዲህ ያለ የአንደራረስም ፖለቲካ መፍጠር ተቃዋሚ የሚሆኑበትን ቀን መርገምን ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ ተቃዋሚ እንዳይሆኑ መሥራትን ያስከትላል ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡

ተቃዋሚዎችም ወደ በቀል ከሚወስድ ምሬት ካለመላቀቃቸውም በላይ የመጠማመዱ ዋና ተጎጂዎች ናቸው፡፡ የራሳቸውን የውስጠ-ድርጅት ዴሞክራሲ ጉድለትና አሉባልታ ተገን ያደረገ ሥውር ሸርና ደባ በአንጃ እየከፋፈለ እንደቆራረጣቸው፣ እንዳነታረካቸውና እንዳነከታቸው ይገኛሉ፡፡ እነሱም ይህ የገዢው ፓርቲ ሥራ ነው ከማለት ባሻገር መጠቃቃትን ለማዳከምና ለመከላከል የሚመቹ አጋጣሚዎችን አልተጠቀሙባቸውም፡፡

ተቃዋሚዎች የሌሉ ያህል በሆነበት፣ ገዢው ፓርቲም ሁሉን ነገር ለራሱ ሥልጣን መሣሪያ ከማድረግና ከእኔ ያልገጠመ ፖለቲካ የጠላት ነው ከማለት ባልተላቀቀበት በዚህ ሁኔታ፣ የተለያየ ሐሳብ አንሰማም አይሰማም፡፡ ከአሮጌው ሥርዓት መምጣት ጋር አንድ ያደረገ ‹‹ማብራሪያ››፣ ሕዝብ ይተላለቃል ወደ መገነጣጠል እንሄዳለን ማስፈራሪያ የአገር ኦፊሴል ሚዲያ ዋና አጀንዳ ይሆናል፡፡ የዚህ ሁሉ ዋና ጉዳት ተጎጂና ሰለባ ደግሞ አገርና ሕዝብ ነው፡፡

ለምሳሌ ስለምርጫ እንነጋገር፡፡ በምዕራብና ምርጫ በሚካሄድባቸው አገሮች እንደሚታየው ወግ አጥባቂም ሆነ ሶሻሊስት ሥልጣን ላይ ቢወጣ የአገርና የሕዝብ የተረጋጋ ጉዞ ያለመናጋት ይቀጥላል፡፡ ይህ ለእኛ ሩቅ ነው፡፡ እጅግ በጣም ሩቅ ነው፡፡ ምርጫ እየተካሄደ ኢሕአዴግ ሁሉንም ምርጫዎች አሸንፎ የመንግሥት ሥልጣን ይዟል፣ ይዞ ቆይቷል፡፡ ኢሕአዴግ የመንግሥትን ሥልጣን መጀመርያ የተረከበው ግን በምርጫ አይደለም፡፡

አሁን የመሠረትነው ሥርዓት መንግሥትነት በምርጫና በአማራጭ ፓርቲ የሚቀየርበት ሥርዓት ነው ብለናል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥትነት በምርጫና በአማራጭ ፓርቲ የሚቀየር ስለመሆኑ ግን እምነት የሚያሳድር ነገር የለም፡፡ እንዲያውም ይህን ራሱ ማለት ከአፍ እላፊ በላይ በሀራጥቃነት (Heresy) የሚያስጠይቅ የሚመስል አስደንጋጭ ነገር ነው፡፡ የተገለጸው ጉዳይና ሁኔታ ስለመኖሩ እምነት የሚያሳድር ነገር የለም ያልንበት ምክንያት ከፓርቲዎች ይጀምራል፡፡ በአማራጭነት ኢሕአዴግን በምርጫ የሚፈታተን ብርቱ ፓርቲ የለም፡፡ አሉ የሚባሉት ተቃዋሚዎች እንዳሉ ተባብረው ቢመጡ እንኳ ከወገናዊነት ነፃ የሆነ (ከሚዲያው ወገናዊነት ጭምር) የምርጫ ውድድር ሜዳ የመገኘቱ ጉዳይ ሌላ ፈተና ነው፡፡ በምርጫ ማሸነፍ ከዕለታት አንድ ቀን ቢቀና እንኳ ትርምስም ሆነ አፍርሶ መገንባት ሳይኖር ጉዞ ስለመቀጠሉ መተማመን አይቻልም፡፡ ገዢው ፓርቲ እኔ ነኝ ያሸነፍኩት ብሎ በጉልበት የማይቀማበት፣ ወይም አሸናፊ ነኝ ባለ ወገንና አልለቅም ባለ ወገን መካከል ሕዝብ ተከፋፍሎ ቀውስ ውስጥ የማይገባበትና እስካሁን የተለፋበት የልማት ሥራ ለውድመት የማይጋለጥበት ሁኔታ ገና አልተደላደለም፡፡ ሌላም ጣጣ አለ፡፡ ነባሩ ገዢ እንደምንም ወርዶ ተቃዋሚው ሥልጣን መያዝ ቢችል እንኳ የነባሩን ገዢ ቡድናዊ አሻራና ቁጥርጥር ለማፅዳት ሲል መንግሥታዊ አውታሮችን ማበራየቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህንን ችግር አይቀሬ የሚያደርገው ከቡድናዊ ወገናዊነት ነፃ የሆኑ አውታሮችን (የመንግሥት ሚዲያውን ጨምሮ) የመገንባቱ ተግባር አለመከናወኑ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ስብስብና ተቃዋሚዎች በጠላትነት የፖለቲካ ወጥመድ ውስጥ እስከተሰነከሉ ድረስም ይህን ተግባር መወጣት (ማለትም ከቡድናዊ ወገናዊነት ነፃ የሆኑ አውታሮችን መገንባት) አይቻልም፡፡ ገና ሲጀመር የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ በየአገሩ የምርጫ አካላት፣ የመከላከያና የፖሊስ ተቋማት በማንኛውም ፓርቲ ተቀጽላነት ውስጥ የማይወድቁበትን ሁኔታ ማልማት አስፈላጊነት የሚመከረው በመድኅንነትም የሚታዘዘው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

የጠላትነትና የአንደራረስም ፖለቲካ እንዲጠፋ ጭራሹንም መሠረት እንዳይኖረው የሐሳብና የአመለካከት ልዩነቶቻችንን እውነትም ውበታችን አድርጎ መቀበልና ማስተናገድ አንዱ የጥበብ መጀመርያ ነው፡፡

ግንቦት 20 ወታደራዊ አምባገነንነት እንዳይሆን ሆኖ የፈረሰበትና ፈላጭ ቆራጭነት እምቧጮ የሆነበት ቀን ነው፡፡ የአምባገነኖች ወታደራዊ ኃይል፣ የፀጥታ መረባቸውና ፓርቲያቸውም ተበጣጥሷል፡፡ የአምባገነኖችና የፈላጭ ቆራጮች ከአገር አንድነት ጀርባ የመሸገው፣ እነ ኢሕአፓ ጭምር የዘመሩለት ፀረ ዴሞክራሲያዊ አመለካከትና እንዲሁም ፀረ ወያኔ ፕሮፓጋንዳቸው ግን ጫፉ ሳይነካ ከሞላ ጎደል አሁን ድረስ ሥር ሰዶ የቆየው፣ ኢሕአዴግ በተለያየ አቅሙና አቋሙ ይህንን ነፃና አደባባይ የወጣ ግላጭ የሐሳብ መንሸራሸርያ ገበያ ውስጥ መፋለም ስላልፈቀደ ነው፣ ስላልፈለገ ነው፡፡ ስለሆነም የጠላትነት ፖለቲካን ማፍረስ አልቻልንም፡፡ እንዲያውም አዲስና ዘመናዊ አድርገን ገነባነው፡፡ የገነባነው ፖለቲካ ደግሞ እኔ ብቻ ልክ የሚል የማይበገር ወፍራም ዳፍንት የተጠናወተው ነው፡፡ ተቃራኒ ሐሳብ የማቅረብ የማንኛውንም ሰው ነፃነትን የማያከብር፣ እንዲያውም የተለያየ ተቃራኒ ሐሳብን ጥቅሜ ብሎ ማድመጥ፣ መከራከርና ቅያሜ ሳይዙ፣ ቂም ሳይቋጥሩ መለያየትን አዲስ ባህል አድርጎ ማልማት ሲገባው በዚህ ላይ ያመፀ ፖለቲካ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት የተለያዩ አመለካከቶች ከሆድ ውስጥ ሙሾነት ወጥተው አደባባይ የሚሰጡበት እየተብላሉ፣ እየተናጡና በየፈርጁ እየተዘረዘሩ ባመዛኙ ኑሮና ጥቅም ባገናኛቸው ልክ ተመሳሳይ ፍላጎቶችና ዓላማዎች እየተያያዙ፣ በኅብረተሰቡ መሠረታዊ ሐቆች ላይ የተፈተለ የፖለቲካ አቋም የሚሆኑበት ብዝኃነት የሚያስተናግድ ሥርዓት አልገነባንም፡፡

ይህ ደግሞ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና ነፃነት ላይ ካስከተለው ጉዳት በተጨማሪ፣ በሰብዕና ላይ ወደር የሌለው ድቀት አስከትሏል፡፡ ነፍስና ህሊና በተለይ በመንግሥት ሥራ ላይ የመንግሥትና የአለቃ ንብረት ሆነዋል፡፡ ያመኑበትን ፊት ለፊት ተናግሮ የመኖር ክብር ጠፍቷል፡፡ የዝምታ፣ የምንተዳዬና የማረጥረጥ ኑሮ ሰፍኗል፡፡ የበላይ ትክክል ነው ያለውን ትክክል ማለት፣ ነህ ያለውን ነኝ ማለት የአደባባይ የኑሮ ዘይቤ፣ የዜግነት ግዴታ ሆኗል፡፡ ለሥራ መታመን፣ እውነቱን ተከትሎ መናገርና መተቸት መቀበሪያ፣ የፖለቲካ አባልነትና አጫፋሪነት ማደሪያ ሆኗል፡፡ መሽቆጥቆጥ፣ ማጎብደድ፣ መስማማት ከንግግር አኳያ እንኳን የአለቃንና የፓርቲ መሪን ዓረፍተ ነገር፣ ሐረግና አባባል የተመዘገበ የታማኝነት ምክልትና መግለጫ ማድረግ ፖለቲካዊ ክብርና ሞገስ አግኝቶ ተራብቷል፡፡ እንዲህ ዓይነት ወጥነት በዋጠው አገር ብዝኃነት የለም፣ ብዝኃነት አይከበርም፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡