ፓትሪክ ሉሙምባ በጣና ፎረም ሲታወሱ

ፓትሪክ ሉሙምባ የሚለው ስም ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ብቅ ያለው እ.ኤ.አ. በ1960 ነው፡፡ የአሁኗ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከቤልጂየም ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ባደረገችው ትግል ሉሙምባ ቁልፍ መሪ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1960 ሉሙምባ በ35 ዓመታቸው በአገሪቱ ታሪክ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ የመጀመሪያ መሪ ሆነዋል፡፡ በዚህ የአፍሪካ የነፃነት ዓመት እየባለ በሚጠራ ዓመት ሉሙምባ ያቀረቡት ጥያቄ ለየት ያለ ነበር፡፡ ኮንጎ የምትፈልገው ሙሉ ነፃነት ነው ሲሉ ሞግተዋል፡፡ የተቀሩት አዳዲስ ነፃ አገሮች መሪዎች የቀድሞ ቅኝ ገዢዎቻቸውን ተዘዋዋሪ ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ ችለው የሚያልፉ የነበረ ሲሆን፣ ሉሙምባ ግን ብቻቸውን ባላቸው ኃይል ሁሉ የማንኛውም ሦስተኛ ወገን በተለይ የቤልጂየምን ጣልቃ ገብነት ለመቋቋም ሞክረዋል፡፡

ጊዜውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ዓይነት ከዚህ ቀደም ያልታየ የአፍሪካዊ ተቃውሞ በትክክልም እንደሚገመተው ሕይወታቸውን በእጅግ አሳዛኝ ሁኔታ አጥተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ጥር 17 ቀን 1961 በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡ ይህ ሳይበቃ ሰውነታቸው በኬሚካል እንዲቀልጥ ተደርጓል፡፡ ይህ ሰቅጣጭ ግድያ በቤልጂየምና በአሜሪካ መንግሥት የተቀነባበረ ሲሆን፣ በኮንጓዊያን ተባባሪነት ፍፃሜ አግኝቷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ‹‹እ.ኤ.አ. በ1999 በሉሙምባ ሕይወት ላይ ዘጋቢ ፊልም ተሠርቶ ነበር፡፡ በፊልሙ በኮንጎ የፖሊስ መኮንን የነበሩት ቤልጂየማዊው ጀራርድ ሱዌቴ እንስሳ እንኳን የማይሠራውን ነገር ሉሙምባ ላይ አድርገናል በማለት ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን አንድ ጥይትና ሁለት ጥርሶችን በማሳየት የሉሙምባ ሰውነት ሲቀልጥ ያተረፍኩት ነው በማለት በጉራ ሲናገሩ ይታያሉ፤›› በማለት በሉሙምባ ላይ የተፈጸመውን ግፍ አስታውሰዋል፡፡

ቤልጂየማዊው ጸሐፊ ሉዶ ዲዊተ ይህን ግድያ ‹የ20ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ አስፈላጊው ግድያ› ይሉታል፡፡ የግድያው ታሪካዊ አስፈላጊነት በተለያዩ ምክንያቶች የሚገለጽ ሲሆን፣ ግድያው ሲፈጸም የነበረው ዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታ፣ በኮንጎ ፖለቲካ ላይ ያሳረፈው ተፅዕኖና እንደ መሪ ሉሙምባ ያላቸው አጠቃላይ ውርስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እነዚህ ጉዳዮች በቅርቡ በባህር ዳር ከተማ የተጠናቀቀው የጣና ከፍተኛ እርከን የአፍሪካ የደኅንነት ፎረም በሉሙምባ የአመራር ዘይቤና በአፍሪካ ስላለው ተፅዕኖ ሲመክር በተሳታፊዎች ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡ የዘንድሮው ዓመታዊው የጣና ፎረም የመለስ ዜናዊ የተከታታይ ሌክቸሮች መድረክ እንዲወያይበት የተመረጠው ርዕስ፣ ‹‹አመራር በአፍሪካ ውስጥ፣ በፓትሪስ ሉሙምባ ትሩፋት ላይ የሐሳብ ልውውጥ›› የሚል ነው፡፡ የመድረኩ መሪና በአሜሪካ የዊድሮው ዊልሰን ማዕከል የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶ/ር ሞንዴ ሙያንግዋ፣ አፍሪካ ሙሉ አቅሟን ለመጠቀምና ለራሷ ያስቀመጠችውን ራዕይ ለማሳካት የአመራር ጥራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹በአፍሪካ መሠረታዊ የሆነ የአመራር ክፍተት አለ፡፡ ይህ መድረክ ደግሞ በአፍሪካ መሪዎች ላይ ሐሳብ ለመለዋወጥና ትምህርት ለመቅሰም ዕድል ይሰጠናል፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በአቶ መለስ ዜናዊ፣ በኔልሰን ማንዴላና በክዋሜ ንክሩማህ ትሩፋቶች ላይ መድረኩ ውይይቶችን አዘጋጅቷል፡፡

‹‹ፓትሪክ ሉሙምባ የሚለው ስም በአኅጉሩ ከጫፍ እስከ ጫፍ በተለያዩ ትውልዶች ሲስተጋባ የኖረው ሰውዬው በቆሙለት ዓላማና እንደ መሪ ምልክት በመሆናቸው ነው፡፡ ከሉሙምባ አመራር ምን እንማራለን? ኮንጎን እንዴት ነው የመሯት? ከሌሎች የአፍሪካ መሪዎች ጋር የነበራቸው ግንኙነት ምን ይመስላል? ከቀድሞ ቅኝ ገዢዎችና ከሌሎች የዓለም አገሮች ጋር እንዴት ነው ይሠሩ የነበረው?›› በማለትም ዶ/ር ሙያንግዋ አክለዋል፡፡

በፈረንሳይ ፓሪስ ስኩል ኦፍ አድቫንስ ስተዲስ ኤንድ ሶሻል ሳይንስስ ዳይሬክተር ኮንጓዊው ፕሮፌሰር ኤሊኪያ ቦኮሎ የሉሙምባን አጭር የሕይወት ታሪክ፣ ሰብዕናቸውንና ትሩፋቶቻቸውን በተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን የመድረኩ አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች ሉሙምባ በማን፣ ለምንና እንዴት ገደሉ የሚለውን ለማወቅ ያላቸውን ፍላጎት አንፀባርቀዋል፡፡

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ፣ ‹‹እ.ኤ.አ. በ1960 ብዙ የአፍሪካ አገሮች ነፃነታቸውን አግኝተዋል፡፡ ከሞላ ጎደል መሪዎቻቸው አብዮተኛ ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነዚህ መሪዎች አልተገደሉም፡፡ ታዲያ ሉሙምባ ብቻቸውን ለምን ተገደሉ? ለዚህ ጥያቄ እስካሁን ምላሽ ያገኘን አልመሰለኝም፤›› ብለዋል፡፡

ከኮንጎ ጋር ከነበራት ግንኙነትና ካላት ፍላጎት አኳያ የሉሙምባ ግድያ በአብዛኛው ከቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ቤልጂየም ጋር ይያያዛል፡፡ ቤልጂየም ለ80 ዓመታት ኮንጎን ስትገዛ የተፈጥሮ ሀብቷን ከመዝረፍ ባሻገር የአገሪቱን ነባር ነዋሪዎች ለግፍና ለስቃይ ዳርጋለች፡፡

ሉሙምባ ስለ ‹‹ነፃነትና ሙሉ በሙሉ ራስን ስለመቻል›› ደጋግመው ሲያነሱ፣ ቤልጂየም ለኮንጎ ነፃነት የሰጠችውን ግማሽ ልብ ድጋፍና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟን የማስጠበቅ ዕቅዷን እያጣቀሱ ነው፡፡ በንግግራቸውም ቤልጂየም የኮንጎን ሀብት እንዴት እንደዘረፈችና ነዋሪዎቿንም ለማያባራ ስቃይ እንደዳረገች በማንሳት ይኮንኗት ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ወደተገደሉበት ቦታ በአውሮፕላን የወሰዳቸውና ሲገደሉም የተኩስ ትዕዛዙን የሰጡት ቤልጂየማውያን መሆናቸው አይገርምም፡፡

በሉሙምባ ግድያ ተሳትፈዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ወይም የሚታመኑ አገሮች ኮንጎ ላይ ልዩ ጥቅም ያላቸው ሲሆን፣ ሉሙምባ ደግሞ ይህንን ለማስቀረት ቁርጠኛ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ በጃፓን ሒሮሽማና ናጋሳኪ የጣለቻቸው አውዳሚ ቦምቦች የተሠሩበት ዩራኒየም የተገኘው ከኮንጎ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ሉሙምባ የኮንጎ ሀብት ጥቅም ላይ የሚውለው የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል መሆን አለበት ማለታቸው ከምዕራባውያን ፍላጎት ጋር የተጣጠመ አልሆነም፡፡ ይህን ሐሳብ ለማኮላሸት ቤልጂየምንና የተመድን ጽሕፈት ቤት ተጠቅማዋል፣ ኮንጓዊ የሉሙምባ ባላንጣዎችን ድጋፍ ገዝተዋል፣ ገዳዮችን ቀጥረዋል፡፡

የሉሙምባ አገዳደል የተወሳሳበ እንደሆነ የሚቀበሉት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር ዋና የሕግ አማካሪ አቶ መርሐጽድቅ መኮንን፣ ሉሙምባ የቀዝቃዛው ጦርነት ፍጥጫ ሰለባ እንደሆኑ ያምናሉ፡፡

ይህ የቤልጂየም የደኅንነት አገልግሎት ባልደረባ የነበሩት የኮሎኔል ሉዊ ባርሊየም አቋም ነው፡፡ የሉሙምባን ሕይወት በሚተርከው ዘጋቢ ፊልም፣ ‹‹ሉሙምባ የተሳሳተ መንገድ መርጠዋል፡፡ ከሞላ ጎደል ኮሙዩኒስት ነበሩ፡፡ ከምዕራባውያን ይልቅ ሩሲያን መርጠዋል፤›› ብለዋል፡፡ ሉሙምባ ኮሙዩኒስት ስለመሆናቸው ሲጠየቁ፣ ‹‹እኔ በጭራሽ ኮሙዩኒስት አይደለሁም፡፡ መቼም ኮሙዩኒስት ልሆን አልችልም፡፡ እኔ በቀላሉ ብሔርተኛ መሪ ነኝ፤›› የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡

ሉሙምባ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ወዲያው በተለያዩ ምክንያቶች ኮንጎን ለፖለቲካዊ ቀውስ ዳርገዋታል፡፡ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት፣ በፅኑ መሠረት ላይ ያልቆመው ጥምር መንግሥት፣ የተገንጣይ ክልሎች አመፅ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቀውሱ መጀመርያ ላይ ሉሙምባ የአሜሪካን ዕርዳታ ጠይቀው ነበር፡፡ ምላሹ ግን አሉታዊ ነበር፡፡

በርካታ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ወደ ኋላ ላይ ግን ከሩሲያ ወይም ሶቪየት ኅብረት ዕርዳታ ለመጠየቅ ተገደዋል፡፡ እየተጠናከረ የመጣውን የካታንጋ የመገንጠል እንቅስቃሴ በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተመድ ኃይሎች አልተባበር ሲሏቸው፣ ሉሙምባ በጥያቄያቸው መሠረት ጥቂት አውሮፕላኖችን ከሩሲያ አግኝተዋል፡፡ ነገር ግን ቀጥለው የሩሲያ ወታደሮች ኮንጎ እንዲገቡ ሲጠይቁ ብዙዎች በራሳቸው ላይ የሞት ፍርድ አሳለፉ ብለዋቸዋል፡፡ በወቅቱ የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኪታ ክሩስቼቭ ሩሲያ ለሉሙምባ መንግሥት ወታደሮችን ለመላክ እያሰበች እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አሜሪካ ሉሙምባን ለማጥፋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በሙሉ ኃይሏ ተቀላቅላለች፡፡ ከሉሙምባ ሕልፈተ ሕይወት በኋላ ሩሲያና ኮንጎ ለነበራቸው የአጭር ጊዜ ግንኙነት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የተቋቋመው ፓትሪስ ሉሙምባ ዩኒቨርሲቲ በሩሲያ ከሚገኙ ግዙፍ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ነው፡፡

ፓን አፍሪካኒስቱ ሉሙምባ

ሉሙምባ ከተቀዳሚ የፓን አፍሪካኒስት መሪዎች አንዱ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1958 በጋና አክራ ለመጀመርያ ጊዜ የተካሄደውን የመላው አፍሪካ ሕዝቦች ኮንፈረንስ ሲሳተፉ ከሌሎች የአፍሪካ ብሔርተኛ መሪዎች ጋር የተዋወቁ ሲሆን፣ ኮንፈረንሱ ያቋቋመው ቋሚ ኮሚቴ አባልም ነበሩ፡፡ ሉሙምባ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ስለአፍሪካ አንድነት ሰብከዋል፡፡

የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች እ.ኤ.አ. ከ1960 በኋላ ነፃነት መስጠቱን አጠናክረው ቢቀጥሉም፣ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ መፍጠርን የማቆም ዕቅድ ግን አልነበራቸውም፡፡ የመድረኩ አንድ ተሳታፊ ‹‹በዚህ የተነሳ እውነተኛና ትክክለኛ ነፃነት መጠየቅ ከመጀመርያው መቀመቅ የሚከት ነው፡፡ ሉሙምባ ያደረጉት ይህንን ነው፤›› ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ በኮንጎ ጉዳይ የተለያዩ መጻሕፍት የጻፉት አዳም ሆሻቻይልድ፣ ‹‹የሉሙምባ መገደል ከአፍሪካ ነፃነት አንፃር ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡ በ1950ዎቹ አፍሪካን ነፃ የማድረግ ንቅናቄ ነበር፡፡ ንቅናቄው ትልቅ የተስፋ አየርን ያነፈሰ ነበር፡፡ የአፍሪካ ሕዝቦች እውነተኛ ነፃነት እንደሚያገኙ ጠብቀው ነበር፡፡ የአገራቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ሙሉ ቁጥጥር በማድረግ ዕጣ ፈንታቸውን ራሳቸው እንደሚወስኑ እምነት ነበራቸው፡፡ የሉሙምባ መገደል ያረጋገጠው ይህ ላይሆን እንደሚችል ነው፡፡ ቤልጂየምና ሌሎች ቅኝ ገዢዎች ነፃነቱን ቢሰጡም የነበረው የቢዝነስ ፍላጎት ግን እንዲረበሽ አይፈልጉም ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ለሉሙምባ የኢኮኖሚ ነፃነትን ያካተተ እውነተኛ ነፃነት የአፍሪካ ሕዝቦችን ለተሻለ ኑሮ ያበቃል፣ የአፍሪካ ህዳሴን ለማረጋገጥና እውነተኛ የአፍሪካ አንድነት ለመገንባት አኅጉሪቱ ከሀብቱ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ወሳኝ እንደሆነ ይወተውቱ ነበር፡፡ ለአፍሪካ ዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ ትኩረት ካልተሰጠ የአፍሪካ አንድነት ህልም ከአፍ ዘሎ ወደ ተግባር ሊያመራ አይችልም ሱሉም ይከራከሩ ነበር፡፡

ለዚህም ነው ከሌሎች የነፃነት መሪዎች በተቃራኒ የኮንጎ ዜጎች በአፍሪካዊነታቸው እንዲኮሩ በተደጋጋሚ ይጠይቁ የነበረው፡፡ በተቀረው አፍሪካ አዳዲሶቹ መሪዎች እንደ ቀድሞ ቅኝ ገዢዎቻቸው በመምሰል ዜጎችን በተገዥነት መንፈስ ያዩ ነበር፡፡ ፓን አፍሪካኒስቱ ሉሙምባ ሌሎች ነፃ ያልወጡ ግዛቶች ነፃ እንዲሆኑ ሊሰጥ ስለሚገባው ዕርዳታም ይናገሩ ነበር፡፡ ከውጭ የሚመጣ ርዕዮተ ዓለምን የሚቃወሙት ሉሙምባ፣ የሶቭየት ኅብረት ሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለምንም አፍሪካዊ ያልሆነ ይሉት ነበር፡፡ ከዚህ ይልቅ ወደ አፍሪካ እሴቶች የመመለስን ጠቀሜታ ያስተጋቡ ነበር፡፡

ለብዙ ተንታኞች ሉሙምባ ለያኔዋ አፍሪካ የነፃነትና የወንድማማችነት ህልም ድምፅ ነበሩ፡፡ ከዚህ አንፃር የአፍሪካ አገሮች ሉሙምባን ለማዳን ጥረት ማድረግ አልነበረባቸውም ወይ ሲሉ የመድረኩ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል፡፡ ለነገሩ አገራቸው ወደ ቀውስ ባመራች ወቅት እ.ኤ.አ. በሐምሌ 1960 ነፃ የአፍሪካ አገሮች በኪንሻሳ (ያኔ ሊዮፖልድቪል ትባል ነበር) እንዲገኙና ኅብረት ፈጥረው እንድተባበሯቸው ጥሪ አድርገው ነበር፡፡ ነገር ግን የውኃ ሽታ ሆነው ቀሩ፡፡

የኮንጎ ትልቅ ዕጦት

የሉሙምባ ሰብዕና በኮንጎ የታጠረ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው ሕይወታቸው በመጥፋቱ አፍሪካ ያለቀሰችው፡፡ መሞታቸው በመላው አፍሪካ ተቃውሞ አቀጣጥሏል፡፡ የሉሙምባ መገደል ለብሔራዊ አንድነት፣ ለኢኮኖሚ ነፃነትና ለፓን አፍሪካዊ ወንድማማችነት፣ ለኮንጓዊያን ነፃነትና ብልፅግና መሰናክል መሆኑ አልቀረም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ለኮንጎ ብሔራዊ አንድነት እንደ ሉሙምባ የሚታገል ሌላ መሪ በአገሪቱ ባለፉት 55 ዓመታት አልታየም፡፡ ሉሙምባ ብሔራዊ ኅብረትን ለማምጣት አገሪቱን በብሔርና በክልል መከፋፈል አያስፈልግም ይሉ ነበር፡፡ ሉሙምባ ያለ ጊዜያቸው ካረፉ በኋላ ኮንጎ የተለያዩ አጀንዳዎች ያነገቡ ኃይሎች የሚተላለቁባት የጦር አውድማ ሆናለች፡፡

እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 1960 ኮንጎ የነፃነት በዓሏን ስታከብር ሉሙምባ ንግግር እንድያደርጉ ፕሮግራም አልተያዘም ነበር፡፡ ይሁንና የቤልጅየሙ ንጉሥ ቦድዋን ያደረጉት ፈር የለቀቀ ንግግር ምላሽ እንዲሰጡ አስገደዳቸው፡፡ ‹‹ነፃነታችን በቤልጂየም ድንጋጌ የተፈጸመ ቢሆንም ዛሬ ግን ከቤልጂም ጋር ወዳጅና እኩል ደረጃ ያለን ሉዓላዊ አገር ነን፡፡ ለራሱ ክብር ያለው ማንኛውም ኮንጓዊ የነፃነት ትግል ያደረግነው ለማሸነፍ መሆኑን መርሳት የለበትም፡፡ ጥቁር በመሆናችን ብቻ ለግዳጅ ሥራ፣ ለስድብና ለድብደባ እንዳረግ ነበር፡፡ አሁን የኮንጎ ሪፐብሊክ ታውጇል፡፡ መሬታችን አሁን ለልጆቻችን የተገባ ነው፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ በማስፈን መሬታችን የአገሪቱን ልጆች ተጠቃሚ እንዲያደርግ እንሠራለን፤›› ሲሉ የቤልጂየም ሥራ ኮንጎን በጎ ከማድረግ የዘለለ አልነበረም ላሉት ንጉሥ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የሉሙምባ ሰብዕና እንደዚህ ነው፡፡ ድርጊታቸው ሕይወታቸውን ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም የኮንጎ ዜጎች ለራሳቸው የተሻለ ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ ዳዊት ሆነው ከጓሊያዷ ቢልጂየም ጋር ለመዋጋት ቁርጠኛ ነበሩ፡፡ በርካታ ሰዎች ይህ ንግግር በራስ ላይ የሞት ፍርድ እንደመወሰን ይወሰዳል ብለው ነበር፡፡

ማንም በቀላሉ ሊገነዘብ እንደሚችለው ይህ አቋም ቤልጂየምንም ሆነ ሌላ ምዕራባዊ ኃይልን ሊያስደስት አይችልም፡፡ ለዚህም ይመስላል የሉሙምባ መንግሥት ከየአቅጣጫው ተግዳሮቶች ይገጥሙት የጀመረው ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው፡፡ ከአምስት ቀናት በኋላ በጦር ኃይሉ ውስጥ አመፅ ተቀሰቀሰ፡፡ በኃይሉ ውስጥ ያሉ ጥቂት ኮንጓዊያን የቤልጂየም አመራሮች እንዲነሱ በመጠየቃቸው የተነሳ አመፅ ነበር፡፡ የሚገርመው ሉሙምባ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ኮንጓዊ ሳይሆኑ ቤልጂየማዊ መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት ከነፃነት በኋላም ኃላፊነታቸውን የመልቀቅ ዕቅድ አልነበራቸውም፡፡

ሉሙምባ ማንኛውንም ዓይነት የውጭ ጣልቃ ገብነትን ስለሚቃወሙ ለውጥ ለማምጣት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ለአብነትም የጦር ኃይሉ ጄኔራል ጀንሰንስ በ24 ሰዓታት ውስጥ ኮንጎን ለቀው እንዲወጡ አዘዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ሜጀር ቪክቶር ሉንዱላን ዋና አዛዥ ማድረጋቸውንና ጆሴፍ ሞቡቱን ደግሞ ወደ ኮሎኔልነት ማሳደጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የኮንጎ የጦር ኃይል የኮንጓዊያን ነው፤›› ሲሉም ተናግረው ነበር፡፡

በመቀጠልም በካታንጋና በደቡብ ካሳይ ግዛቶች ተገንጣይ ቡድኖች አመፁ፡፡ ለሌሎች በርካታ ከተሞች ደግሞ የአመፅ እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ፡፡ ሉሙምባ እነዚህ እንቅስቃሴዎች በቤልጂየም  የተቀናበሩና ዓላማቸውም የእሳቸውን አመራር ማሳጣት እንደሆነ ይናገሩ ነበር፡፡ ግጭቶቹ አገሪቱን ወደ ብጥብጥና አለመረጋጋት እንድታመራ ማድረግ ጀመሩ፡፡

ቤልጂየም ሁኔታውን ለማረጋጋት የራሷን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለማድረግ ሐሳብ አቀረበች፡፡ ሉሙምባ በግልጽ ቢቃወሙትም ቤልጂየም ዜጎቼን ለመከላከል ነው በማለት ወታደሮቹን ላከች፡፡ ይሁንና የሉሙምባ ዋነኛ ተቀናቃኝና የካታንጋን የመገንጠል እንቅስቃሴ ለሚመሩት ሞይስ ካፔንዳ ሾምቤ ድጋፍ ለመስጠት ያለመ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ፡፡ በዚህ ቅር የተሰኙት ሉሙምባ የቤልጂየምን አምባሳደር ከአገር እንዲወጡ አድርገው ነበር፡፡

ሉሙምባ ለተመድ ይግባኝ በማለት ቤልጂየሞች እንዲወጡላቸው ጠየቁ፡፡ የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች በጥያቄው መሠረት ወደ ኮንጎ ቢገቡም፣ ለሉሙምባ እጅግ አጣዳፊ የነበረውን ካታንጋን የመቆጣጠር ሥራ ሊሠሩላቸው አልቻሉም፡፡ የቤልጂየም ወታደሮችን ከኮንጎ ማስወጣት አልተቻለም፡፡

የሉሙምባ ወታደሮች በተለያዩ አላስፈላጊ ግድያዎችና የመብት ረገጣዎች ላይ መሳተፋቸውም ሁኔታዎችን ይበልጥ አወሳሰባቸው፡፡ ድርጊቱን ሉሙምባ በይፋ ቢያወግዙም በርካቶች ተጠያቂ አድርገው ይከሷቸው ነበር፡፡ ኮሎኔል ሞቡቱን የመሳሰሉ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎች የመከላከያ ሚኒስትር ጭምር የነበሩትን ሉሙምባን መታዘዝ አቆሙ፡፡

እነዚህን እጅግ የተወሳሰቡ ችግሮች በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እያስተናገደ ያለውን መንግሥት የሚመሩት ሉሙምባ ለችግሮቹ መፍትሔ ለመፈለግ እየተጣጣሩ ባሉበት ጊዜ፣ ፕሬዚዳንት ካሳቩቡ ከሥልጣናቸው መነሳታቸውን አወጁ፡፡

ይህ ሳይበቃ በራሳቸው በሉሙምባ ያደጉት ኮሎኔል ጆሴፍ ሞቡቱ ፕሬዚዳንት ካሳቩቡና ሉሙምባ እንደተነሱ ገለጹ፡፡ ሞቡቱ በአሜሪካ መንግሥት ይረዱ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ሉሙምባ በቤት ውስጥ እስር ነበሩ፡፡ ኪንሻሳ ከሚገኘው ቤታቸው በ2,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኪሳንጋኒ (ያኔ ስታንሊቪል ትባል ነበር) ደጋፊዎቻቸው አማራጭ መንግሥት መሥርተው ነበር፡፡ ይህ መንግሥት በወቅቱ የሶቪየት ኅብረትንና የቻይናን ዕውቅና አግኝቶ እንደነበር ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ ሉሙምባ ይህን ኃይል ለመቀላቀል በድብቅ ጉዞ ላይ እያሉ ነው በአሜሪካና በቤልጂየም መንግሥታት በተቀጠሩ ጠላቶቻቸው ተይዘው በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት፡፡

ሉሙምባ ከተገደሉ በኋላ የኮንጎ ጉዞ የተሻለ አልሆነም፡፡ እንደ ሞቡቱና ካቢላ የመሳሰሉ በአንድ ወቅት የሉሙምባ አድናቂ የነበሩ መሪዎች በምዕራባውያን ድጋፍ ራሳቸውን አበልፅገው፣ ለበርካታ ሚሊዮን ኮንጓዊያን ግን የስቃይ ምንጭ ሆነው ቀጠሉ፡፡ በተለይ የሞቡቱ አሰቃቂ የ32 ዓመታት አገዛዝ ያስከተለው ተፅዕኖ አሁንም በኮንጎ በጉልህ ይታያል፡፡ የሚያስደንቀው ጉዳይ ሞቡቱ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ሉሙምባን ብሔራዊ ጀግና ብለው መሰየማቸው ነው፡፡

ሉሙምባ በርካታ በሌሎች መሪዎች ላይ የሌሉ ባህርያትና ብቃቶች ያሉዋቸው ቢሆኑም፣ የራሳቸው ክፍተቶችም አሏቸው፡፡ አንዳንድ ስህተቶችም ዋጋ አስከፍለዋቸዋል፡፡ በ35 ዓመታቸው ለከፍተኛ ኃላፊነት መብቃታቸው በራሱ ትልቅ ተግዳሮት ነበር፡፡ የፖስታ ቤት ሠራተኛና አካውንታንት የነበሩት ሉሙምባ ለኃላፊነታቸው የሚመጥን የትምህርት ደረጃና የሥራ ልምድ ነበራቸው ማለት አዳጋች ነው፡፡

የጣና ፎረም አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች ግን የአካባቢያቸውን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በአግባቡ አለመገንዘባቸው ትልቁ ድክመታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከተቀናቃኞቻቸው ጋርም የተሳለጠ ግንኙነት ለመፍጠር ያደረጉት ውስን ጥረት ሌላው ድክመታቸው ነው፡፡ በተለይ ከካታንጋው አለቃ ሞይስ ሾምቤ ጋር ስምምነት አለማድረጋቸው ትልቅ ክፍተት መፍጠሩ ታይቷል፡፡

ሉሙምባ በተቺዎቻቸው የማመቻቸትና የመቻቻል ባህሪ የላቸውም ይባላሉ፡፡ አንድ ሐሳብ እንዲያሸንፍና ገዢ እንድሆን እንጂ መሀል ላይ ስምምነት እንዲደረግ ፍላጎት አልነበራቸውም ተብለው ይተቻሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ጠላቶቻቸው ጋር አብረው የማይሄዱ በርካታ ፖሊሲዎች የነበሯቸው፡፡

ግርማ ሞገስ የነበራቸው ወጣቱ የኮንጎ መሪ ካረፉ እነሆ 55 ዓመታት ሞሉ፡፡ በሥልጣን ላይ በነበሩባቸው ጥቂት ወራት ያሳዩት በርካታ ውብ ቃላትን እንጂ ድርጊቶችን አይደለም፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ መሪዎች በተለየ ምንም ነገር እንዳይሠሩ በተቀናጀ መንገድ ገደብ ተደርጎባቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ህልማቸው ወረቀት ላይ እንጂ በመሬት ላይ አይታይም፡፡ ቢያንስ ግን አቅማቸውና ሁኔታዎች የፈቀደላቸውን ያህል ሞክረዋል፡፡ የሉሙምባ ትልቁ ጩኸት የነበረው የአፍሪካ የኢኮኖሚ ነፃነት አሁንም ከዋና አጀንዳነት አልተነሳም፡፡ እንደ ዶ/ር ቴድሮስ ገለጻ የሉሙምባ የመጨረሻ ቃላት እነዚህ ናቸው፡፡ ‹‹በደስታ ጊዜም ሆነ በደስታ አልባ ጊዜያት አጠገባችሁ ነኝ፡፡ ይህችን አገር ከውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ለማላቀቅ አብረን ታግለናል፤›› ይህ አሁንም አፍሪካን ጤነኛ ካልሆነ የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመለየት የሚያስፈልግ መንፈስ ነው፡፡