ፊርማና ዓይነ ስውርነት

ሰዎች በዕለት ተዕለት ኑሮአቸው ግብይት ሲፈጽሙ ውል ውስጥ ይገባሉ፡፡ ውል በቃል፣ በድርጊትና በጽሑፍ ሊከናወን መቻሉ ደግሞ በዕለት የምንገባቸውን ውሎች ቁጥር ይጨምራል፡፡ ውሉ በጽሑፍ እንዲሆን ሕጉ ሲያስገድድ ወይም ተዋዋይ ወገኖች በጽሑፍ እንዲሆን ሲስማሙ ሊፈጸሙ የሚገባቸው የአጻጻፍ ሥርዓቶች /Formality Requirements/ በሕጉ ተቀምጠዋል፡፡ ውል በጽሑፍ እንዲደረግ ግዴታ ሲኖር ልዩ በሆነ አሠራር ተገልጾ በውሉ ግዴታ ያለባቸው ሰዎች ሁሉ መፈረም አለባቸው፡፡ በሁለት ምስክሮችም ፊት ካልተረጋገጠ አይጸናም፡፡ አንዳንድ ውሎች ሲሆኑ ደግሞ ውሉ በውል አዋዋይ ሹም ፊት ካልተፈጸመ ወይም ካልተመዘገበ በሕግ ፊት ዋጋ አይኖረውም፡፡ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚቋቋሙ የመያዣ፣ ባለቤትነትን የማስተላለፍ፣ የአላባ መብቶች ወዘተ. ይህን የማረጋገጥና የምዝገባ /Authentication and Registration/ ሥርዓት እንዲያሟሉ ሕጉ ግዴታ ከሚጥልባቸው ውስጥ ይመደባሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሁሉንም የአጻጻፍ ሥርዓቶች ለመመልከት ሐሳብ የለም፡፡ የምንመለከተው ፊርማን የተመለከቱ ደንቦችን ሲሆን፣ በተለይ ዓይነ ስውራንና መሐይምናን ውል ላይ ሲፈርሙ ሊከተሉት ስለሚገባው ሥርዓት ነው፡፡ በተግባር ዓይነ ስውራን ብዙ ውሎች ውስጥ ይገባሉ፤ ባንክ ገንዘብ ያስቀምጣሉ፤ የመኖሪያና የንግድ ቤት ይገዛሉ፤ ይሸጣሉ፤ ብድር ይወስዳሉ፤ ወዘተ. ዓይነ ስውራን እነዚህን ውሎች ሲፈጽሙ ፈቃዳቸውን በፊርማቸው ያረጋግጣሉ፡፡ ፊርማዎቻቸው ግን በሕግ ፊት ተቀባይነት የሚያገኙበትን ሁኔታ መመልከት አግባብ ይሆናል፡፡

 

ፊርማ

ፊርማ አንድ ሰው በሕግ የሚገደድባቸውን ሰነዶች ይዘት ስለማወቁና ስለመፍቀዱ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው፡፡ ማንም ሰው ፊርማውን ያስቀመጠበትን ሰነድ ይዘት ያውቃል ተብሎ ግምት ይወሰዳል፡፡ ሕጋችን ወጥነት ቢጎድለውም ፊርማን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በየአዋጆቹ ይደነግጋል፡፡ በዚህ ረገድ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ስለውል የተደነገጉት ደንቦች፣ ኑዛዜን የተመለከቱ ድንጋጌዎች፣ በንግድ ሕጉ የሚተላለፉ የገንዘብ ሰነዶችን /ቼክ፣ የሐዋላ ወረቀት፣ የተስፋ ሰነድ፣ ወዘተ./ የተመለከቱ ድንጋጌዎችና ሌሎች አዋጆች /ለምሳሌ፣ የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ/ ፊርማን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ይዘዋል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 1728 ‹‹ፊርማ›› በሚል ርዕስ ‹‹ፊርማ በውሉ ተገዳጅ በሆነው ሰው እጅ መጻፍ ይገባዋል፡፡ ለመፈረም የማይችል ሰው በጽሕፈት ፊርማው ፋንታ የጣት ምልክት መተካት ይችላል፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ሕጉ ፊርማ በጽሑፍ መልክና በእጅ ሊፈረም እንደሚገባ ደንግጓል፡፡ መጻፍ የማይችል ግን በጣት ሊፈርም ይችላል፡፡ የሕጉ ድንጋጌ የተወሰደበት የስዊዝ የግዴታ ሕግ ላይ ማብራሪያ የጻፉ የሕግ ምሁራን በጣት መፈረም ሰፋ አድርጎ ሊተረጎም እንደሚገባና በእጅና በእግር ጣትም ሆነ በአፍ መፈረምን እንደሚያካተት ጽፈዋል፡፡ ሆኖም እንደ ቺቺኖቪች አገላለጽ ከጣት ፊርማ ወይም ምልክት ውጭ በመሣሪያ መፈርም /Signature by tool/ ሕጉ መከልከሉን ጽፈዋል፡፡ ድንጋጌው የተወሰደበት የስዊዝ የግዴታ ሕግ ግን በልዩ ሁኔታ በመሣሪያ እንዲፈረም ይፈቅዳል፡፡ ድንጋጌው “A signature appended with a tool would qualify only in situations accepted by custom and traditions, and when it is necessary to sign valuable documents which are particularly put in circulation in large numbers” ስለሚል ብዙ ግብይት ባላቸው ድርጅቶች ሰነዶችን በጣት መፈረም አድካሚ ስለሚሆን በልማድ የሚፈቀድበትን ሁኔታ አመላክቷል፡፡ የእኛ ሕግ ተመሳሳይ ድንጋጌ ባይኖረውም በተግባር በመሣሪያ በመታገዝ መፈረም የተለመደ ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቴክኖሎጂ የሕጎቻችንንም ይዘት የለወጠው ይመስላል፡፡ ንግድ ሰዎች በአካል ሳይገናኙ ሊፈጸም የመቻሉ ነገር ወይም አገልግሎቶችን ፈጣንና ተደራሽ ከማድረግም አንፃር በቴክኖሎጂ የታገዙ ፊርማዎች በተወሰኑ ጉዳዮች በሕግ ተፈቅደዋል፡፡ በዚህ ረገድ የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003 የኤሌክትሮኒክ ፊርማን የፈቀደ ሲሆን፣ በአዋጁ ፍርድ ቤቶችም ፊርማውን በማስረጃነት እንዲቀበሉ ያስገድዳል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2/11/ ‹‹የኤሌክትሮኒክ ፊርማ›› ማለት ‹‹መልዕክቱ ከያዘው መረጃ ጋር በተያያዘ፣ የፈራሚውን ትክክለኛነትና ማንነት ለመለየትና በመልዕክቱ የተካተተው መረጃ በፈራሚው የፀደቀ ወይም ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ለማረጋገጥ ጥቅም ላይ የሚውል ከመረጃ መልዕክቱ ጋር የተቆራኘ ወይም ከመልዕክቱ ጋር ምክንያታዊ በሆነ አኳኋን የተያያዘ የኤሌክትሮኒክ መልክ ያለው መረጃ ነው፤›› በሚል ተተርጉሟል፡፡ በሌላ ሕግ ወይም ልማዳዊ አሠራር በሌላ አኳኋን ቢደነገግም የኤሌክትሮኒክ ፊርማ በፍርድ ቤት ተቀባይነት ያለው መሆኑን አዋጁ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ አዋጁ በቅርብ ጊዜ የወጣ በመሆኑና ባንኮች ሙሉ በመሉ በክፍያ ሥርዓቱ መጠቀም ባለመጀመራቸው በተግባር የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን የመፈተሻው ጊዜ ገና ይመስላል፡፡

የዓይነ ስውራን ፊርማ

ዓይነ ስውራን በጽሑፍ የተደረገ ግብይትን ወይም ውልን ይዘት ስለማያውቁት ለፊርማቸው ሕግ የተለየ ሥርዓት ያስቀምጣል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1728/3/ ‹‹የዓይነ ስውራን ወይም የመሀይምናን ፊርማ የጣት ምልክት ፊርማ የእነሱ ፊርማ መሆኑን ውል አዋዋይ ሹም ወይም አንድ ፍርድ ጸሐፊ ወይም አንድ ዳኛ በሥራቸው ላይ ሆነው ያረጋገጧቸው ካልሆነ አያስገድዳቸውም፤›› በማለት ደንግጓል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ ለመረዳት እንደሚቻለው ዓይነ ስውራን በጣታቸው በሚፈርሙት ውል እንዲገደዱ ፊርማቸው በውል አዋዋይ ሹም ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ድንጋጌው ዓይነ ስውራን ሆነው በጽሑፍ የሚፈርሙ ሰዎችን የሚመለከት ስለመሆኑ አለመሆኑ አከራካሪ ነው፡፡ በአንድ በኩል ድንጋጌው ‹‹የዓይነ ስውራን የጣት ምልክት ፊርማ›› ስለሚል የዓይነ ስውራን ጽሑፍ ፊርማን በውል አዋዋይ ሹም ፊት እንዲረጋገጥ የሚጠይቅ አይመስልም፡፡ በሌላ በኩል ግን ዓይነ ስውራን በመርህ ደረጃ የሚጽፉትና የሚያውቁት የብሬል ጽሑፍ እንጂ የእጅ ጽሑፍ ባለመሆኑ፣ ፊርማውንም ወጥነት ባለው ሁኔታ ተመሳሳይ ማድረግ አለመቻሉ የሚያመጣውን ተግባራዊ ክፍተት ግንዛቤ ውስጥ ካስገባን ሁሉም የዓይነ ስውራን ፊርማ በውል አዋዋይ ሹም ፊት ሊረጋገጥ እንደሚገባ እንገነዘባለን፡፡ በተግባር በባንኮች አካባቢ አንዳንድ ዓይነ ስውራን መጻፍ ስለምችል ያለማንም እርዳታ በጽሑፍ ፊርማዬ ሒሳቤን ላንቀሳቅስ የሚል ሙግት በየዕለቱ ያሰማሉ፡፡ የስዊዝ ሕግ ላይ ማብራሪያ የጻፉ የሕግ ባለሙያዎች ዓይነ ስውራን በእጅ ጽሑፍም ሆነ በጣት ሲፈርሙ በውል አዋዋይ ሹም እንዲፀድቅ ግዴታ መጣሉን ያብራራሉ፡፡ ሌላው በውል አዋዋይ ሹም ፊት ያልተረጋገጠ የዓይነ ስውራን ፊርማን መቃወም የሚችሉት ዓይነ ስውራኑ የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ የፊርማ ጉዳይ ከፎርም ባለፈ ፈቃድ ከመስጠት ወይም ካለመስጠት ጋር ስለሚያያዝ በፊርማው ተጎዳሁ የሚለው ዓይነ ስውር ውል አዋዋይ ፊት ያልተፈረመውን ውል የመቀበል ወይም እንዲፈርስ የመጠየቅ ምርጫ አለው፡፡

ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ ‹‹የውል ሕግ መሠረታዊ ሐሳቦች›› በሚለው መጽሐፋቸው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1728/3/ አፈጻጸም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠ ውሳኔ በመተንተን ያስረዳሉ፡፡ በመዝገብ ቁጥር 141/81 በተሰጠው ውሳኔ መልስ ሰጪ የነበረው ሰው ከአመልካቿ ጋር ባደረግሁት ውል አጠራቅሜ አስቀምጫለሁ ያለውን ቆዳና ሌጦ ልታስረክበኝ በብር 24,588.00 ተዋውለን ገንዘብ ፈርማ ወስዳለች፡፡ ስለዚህ በውሉ መሠረት ቆዳና ሌጦውን ታስረክበኝ፤ አለበለዚያም የወሰደችውን ገንዘብ ከነወለዱ ትክፈለኝ በማለት በሥር ፍርድ ቤት ክስ መሠረተ፡፡ አመልካች በበኩሏ እኔ መሀይም በመሆኔ ቀደም ሲል ለሸጥኩለት ቆዳና ሌጦ ፋክቱር ነው በማለት በባዶ ወረቀት ላይ ነው ያስፈረመኝ፤ ገንዘቡን አልወሰድኩም፤ መሀይም በመሆኔ ውሉ በውል አዋዋይ ሹም ፊት የተደረገ ስላልሆነ አልገደድበትም፤ በሰነዱ ላይ በእማኝነት የፈረሙ ሰዎች ቀርበው ይመስክሩልኝ፤ ፊርማውም ይመርመርልኝ የሚል ክርክር አቀረበች፡፡

የከፍተኛውና የጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ሰነዱ በአመልካቿ ለመፈረሙ በባለሙያ ምርመራ እንዲረጋገጥ ካደረጉ በኋላ አመልካች ነጋዴ በመሆንዋ በባዶ ወረቀት ላይ ትፈርማለች ማለት አይቻልም፡፡ ካደረገችውም የሆነ ይሆን ብላ ነው በማለት ፈረዱባት፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ደግሞ ሁለት ጭብጦችን ይዞ በውል ረገድ ለፎርም መሠረቱ ሕግ ወይም ስምምነት መሆኑን፣ ከመሀይማን ወይም ዓይነ ስውራን ጋር የሚደረጉ ውሎች ሁሉ በጽሑፍ እንዲደረጉ ሕጉ የሚያዝ መሆኑን፣ መሀይምነትም ሆነ ዓይነ ስውርነት ከውል ፎርም አኳያ የተሰጠው ልዩ ስፍራ አለመኖሩን፣ ነገር ግን ውሉ በጽሑፍ እንዲሆን ከተደረገ ፊርማው በውል አዋዋይ ፊት መፈረም እንዳለበት፣ ይህ ሁኔታ በሌለበት ጊዜ በፊርማቸው እገደዳለሁ የማለቱና ያለማለቱ ምርጫ የዚሁ ሰው መሆኑን ተንትኗል፡፡ በሌላ በኩል የአመልካች ነጋዴ መሆን ሕጉ በመሀይምነት ያደረገላትን ጥበቃ የማያላላው መሆኑን፤ ጥበቃው የተያያዘው ከመሀይምነት ወይም ከዓይነ ስውርነት ጋር ብቻ እንጂ ከተሰማሩበት የሥራ መስክ ጋር አለመሆኑን በመዘርዘር አመልካች በሰነዱ ልትገደድ አይገባም በማለት የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ ሰብሮታል፡፡ ተመሳሳይ ሌሎች የቅርብ ውሳኔዎች ባይኖሩም ከዚህ ውሳኔ የተወሰኑ ነጥቦችን መረዳት ይቻላል፡፡ ቀዳሚው በጽሑፍ እንዲደረጉ ግዴታ ያልተጣለባቸው ውሎች ላይ ቢሆንም የዓይነ ስውራን ፊርማ በውል አዋዋይ ሹም ፊት ሊረጋገጡ ይገባል፡፡ ሁለተኛው ዓይነ ስውራን በጽሑፍም ሆነ በጣት ሲፈርሙ ፊርማቸው በውል አዋዋይ ሹም መጽደቅ ይኖርበታል፡፡ ሌላው ይህ ሥርዓት አለመፈጸሙን መቃወም የሚችለው ዓይነ ስውሩ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1728/3/ የተፈጻሚነት ወሰን

ለዓይነ ስውራን ጥበቃ የሚያደርገው የዚህ ድንጋጌ የተፈጻሚነት ወሰን በተግባር አከራካሪ ነው፡፡ በተለይ በባንኮች አካባቢ ዓይነ ስውራን የባንክ አገልግሎት /ብድርና የባንክ ሒሳብ መክፈትና ማንቀሳቀስ/ ጋር በተያያዘ አሠራሩና ሕጉ ልዩነት ይታይበታል፡፡ በዚህ ምክንያት የተወሰኑ አካላት ድንጋጌውን አስፋፍቶ የመተርጎም፣ የተወሰኑ ደግሞ በጠባቡ በመተርጎም ስለተፈጻሚነቱ ይከራከራሉ፡፡ ከኑዛዜና ቼክ ጋር በተያያዘም የሚነሱ ክርክሮች ስለሚታዩ የተወሰኑትን እንመልከት፡፡

ልዩ ልዩ ውሎች

የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1728/3/ ስለ ውል በጠቅላላው በሚደነግገው የሕጉ ክፍል ስለሚወድቅ ተፈጻሚነቱ ለውል ጉዳዮች ነው፡፡ ስለዚህ ዓይነ ስውራን የሚመሠርቱዋቸው የሽያጭ፣ የብድር፣ የስጦታ፣ ወዘተ. ውሎች ላይ የሚያሰፍሩት ፊርማ በውል አዋዋይ ሹም ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ እነዚህ ውሎች የተለየ የፎርም ቅርጽ እንዲከተሉ በሕጉ ባይመለከትም፣ ዓይነ ስውራን ሲፈርሟቸው በውል አዋዋይ ሹም ፊት ሊሆን ይገባል፡፡ በተግባር የተለየ አቋም የሚያንፀባርቁ የሕግ ባለሙያዎች አይጠፉም፡፡ አንዳንዶች ስለ ልዩ ውል የሚደነግጉት የፍትሐ ብሔር ሕጉ ክፍሎች የዓይነ ስውራን ፊርማ በሕግ ተቀባይነትን ስለሚያገኝበት ሁኔታ ባልደነገጉበት ሁኔታ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1728/3/ ተፈጻሚ ማድረግ ተገቢ አይሆንም ሊሉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም በጠቅላላው የሕጉ ክፍል ስለፊርማ የተደነገገው ደንብ በልዩ ክፍሉ የተለየ ተቃራኒ ድንጋጌ እስካልሰፈረ ድረስ ተፈጻሚ ሊሆን ይገባል፡፡ የሕጉ ልዩ ክፍል ስለፊርማ የገለጸው ነገር አለመኖር የሕጉን የጠቅላላ ክፍል የአጻጻፍ ሥርዓት መቀበሉ እንደሆነ ማሰብ ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር ማንኛውም ውል ላይ ዓይነ ስውራን የሚያሰፍሩት ውል በውል አዋዋይ ሹም ካልተረጋገጠ አያስገድዳቸውም ብለን ለመደምደም ያስችለናል፡፡ ፊርማው የፎርም ቅቡልነት /Validity/ መሥፈርት ባይሆንም እንኳ የፈቃድ አሰጣጥ ማረጋገጫ ነው፡፡

የባንክ ሒሳብ መክፈትና ማንቀሳቀስ

ስለ ባንክ ሥራዎች በተደነገገው የንግድ ሕጉ ክፍል ባንኮች ከሚሰጡአቸው አገልግሎቶች ውስጥ ቁጥር 896 እስከ 902 የሚገኘው ገንዘብ በአደራ ማስቀመጥ ይገኛል፡፡ ከድንጋጌዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ የባንክ አገልግሎት ውል እንደመሆኑ መጠን በተዋዋዮች ሙሉና ነፃ ፈቃድ በስምምነት የሚፈጸም ነው፡፡ በንግድ ሕጉ እንዲህ ዓይነት ውሎች በጽሑፍ እንዲደረጉ የተቀመጠ የሕግ ግዴታ ባይኖርም በተግባር ባንኮች በጽሑፍ የሚያደርጉት ነው፡፡ የባንክ ሒሳብ ሲከፈትም ሆነ ሲንቀሳቀስ የሒሳብ ባለቤቱ ፊርማ የሚያስፈልግ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ባንኮች የሒሳብ ባለቤቱ የፊርማ ናሙና ካልሰጠና ሒሳቡንም ሲያንቀሳቅስ ከናሙናው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ፊርማ ካላስቀመጠ ገንዘቡን ለመጠቀም አይችልም፡፡ የዓይነ ስውራን ፊርማን በተመለከተ የንግድ ሕጉ የሚለው ነገር አለመኖሩ በፊርማው ሥርዓት ላይ የተለያየ አመለካከት እንዲኖር ይጋብዛል፡፡ በዚህ ረገድ አንዳንዶች የባንክ ሒሳብን የሚገዛው የንግድ ሕጉ የሚለው ነገር ከሌለ በግለሰቡና በባንኩ መካከል በሚኖረው ስምምነት በባንኩ መመርያ መሠረት እልባት እንደሚያገኝ ይገልጻሉ፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ባንኮች ዓይነ ስውራን ሒሳብ ሲከፍቱ የጣት ምልክት ናሙናቸውን ያስቀምጣሉ፤ ማንነታቸውን የሚለይ ፎቶግራፍ ያያይዙና የቅርብ ሰዎቻቸውን ካመጡ ተነቦለቸው አብሯቸው በመጣ ሰው ፊርማ ሒሳብ ከፍተው እንዲያንቀሳቅሱ ይፈቅዱላቸዋል እንጂ የዓይነ ስውራኑ ፊርማ በውል አዋዋይ ሹም ፊት አይረጋገጥም፡፡

 

ሌላው አቋም ግን የባንክ ሒሳብ መክፈትና ማንቀሳቀስ በውል የሚፈጸም በመሆኑ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1728/3/ በሚደነግገው መሠረት ፊርማቸው በውል አዋዋይ ሹም ፊት ካልተረጋገጠ አያስገድዳቸውም የሚል ነው፡፡ ይህ አቋም ለዓይነ ስውራን ጥበቃ ካስፈለገበት የሕጉ አላማ አንፃር ከተመለከትነው ለዓይነ ስውራን ጠቃሚ ይመስላል፡፡ ገንዘብ በአደራ የማስቀመጥ ውል በጽሑፍ እንዲደረግ የሕግ ግዴታ ባይኖርም በተግባር ተዋዋዮቹ በጽሑፍ ስለሚያደርጉት ስለፊርማ የተደነገጉት የፍትሐ ብሔር ሕጉ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ ክርክር ሕጉን መሠረት ያደረገና ሕጉ ለዓይነ ስውራን ለመስጠት የፈለገው ጥበቃ ስለሚያሳልጥ ቅቡልነት አለው፡፡ ሆኖም በተግባር ዓይነ ስውራንን ያለመጥቀም ውጤት ሊኖረው ይችላል፡፡ ዓይነ ስውራን የባንክ ሒሳብ ሲከፍቱ፣ ሲያስገቡ፣ ሲያወጡ፣ ወዘተ. በየቀኑ ወይም በየሰዓቱ ውል አዋዋይ ሹም ፊት እንዲሄዱ ካስገደድናቸው፤ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ፤ ፈጣን አገልግሎትም አያገኙም፤ ባንኮችም ቢሆን ይህንኑ በመፍራት ዓይነ ስውራን ደንበኞች ሒሳብ እንዲከፍቱ ላያበረታቱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ረገድ ባንኮች በተግባር እየተጠቀሙበት ያለው አሠራር ዓይነ ስውራን ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሎአቸዋል፡፡ ዓይነ ስውራን በሌላ ሰው ፊርማ እንዲያንቀሳቅሱ መፍቀድ የሕግ መሠረት ባይኖረውም በባንኮች የዳበረ ልምድ በመሆኑ ቸል ሊባል አይችልም፡፡ ለዚህ ጉዳይ ገዥ የሚሆነው ሕጉ ወይም የዳበረው ልምድ? የሚለው ነጥብ ግን ሰበር ችሎት አስገዳጅ ትርጓሜ ባልሰጠበት ሁኔታ በእርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል፡፡ ሰበር ችሎቱ በአንዳንድ ጉዳዮች የሕጉን ጥሬ ትርጉም፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ እውነታው በመመልከት የዳበረ አሠራርና ልምድን መሠረት ያደረገ ፍርድ ሲሰጥ ስለሚስተዋል እንደየሁኔታው የሁለቱም ዘንግ ክርክሮች ተቀባይነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡

ኑዛዜና ቼክ

 

ኑዛዜና ቼክ ፊርማን መሠረት የሚያደርጉ የሕግ ተግባራት ናቸው፡፡ በግልጽ የሚደረግ ኑዛዜ /የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 891/ እና በተናዛዡ ጽሑፍ የሚደረግ ኑዛዜ /894/ የተናዛዡን የጽሑፍ ወይም የጣት ፊርማ ካልያዙ ፈራሽ ይሆናሉ፡፡ ቼክንም በተመለከተ ቼኩ ላይ ቼኩን ያወጣው ሰው ፊርማ ከሌለ ሰነዱ እንደቼክ አይቆጠርም፡፡ /የንግድ ሕግ ቁጥር 827 እና 828/፡፡ ከዚህ በመነሳት ኑዛዜና ቼክ ቅቡልነታቸው ፊርማን መሠረት ያደረገ በመሆኑ የዓይነ ስውራኑ ፊርማ እንዴት እንደሚከወን መጠየቁ ተገቢ ነው፡፡

ዓይነ ስውራኑ ኑዛዜ ሲፈጽሙ በውል አዋዋይ ሹም ፊት ሊያደርጉ ይገባል ወይም አይገባም የሚለው ነጥብ ለተወሰኑ ጊዜያት አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ፍርድ ቤቶችንም የተለያየ አቋም ሲያንፀባርቁ ቆይተዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 50917 የካቲት 25 ቀን 2003 ዓ.ም. አስገዳጅ ፍርድ ከሰጠ በኋላ ግን ክርክሩ እልባት ያገኘ ይመስላል፡፡ በዚህ ጉዳይ አመልካች ሟች ዓይነ ስውር በመሆናቸው ያደረጉት ኑዛዜ በውል አዋዋይ ሹም ስላልተረጋገጠ ፈራሽ ሊሆን ይገባል የሚል ክርክር አቅርበዋል፡፡ ተጠሪ ደግሞ ዓይነ ስውር የሚያደርገው ኑዛዜ በውል አዋዋይ ፊት ይደረግ የሚል ሕግ ባለመኖሩና የውል ሕግ ድንጋጌ ለኑዛዜ ተፈጻሚ ስለማይሆን ፈራሽ ሊሆን አይገባም ሲል ተከራክረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሟች ዓይነ ስውር እንደመሆናቸው መጠን የኑዛዜ ሰነዱን በእገዛ የፈረሙ በመሆኑ፣ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 340 መሠረት ፈራሽ ሊሆን ይገባል ብሎ ፈረደ፡፡ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ደግሞ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 340 ዓይነ ስውራን ድጋፍ ሊጠይቁ እንደሚችሉ እንጅ በአዋዋይ ፊት ያልተደረገ ኑዛዜ ፈራሽ ነው ብሎ በአስገዳጅነት ባለማስቀመጡ፤ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1728ም ተፈጻሚነቱ ውሎች ላይ እንጂ ኑዛዜን አይመለከትም በማለት የሥር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሽሮታል፡፡ የከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት የይግባኝ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ስህተት የለውም ብሏል፡፡ ጉዳዩን በመጨረሻ የተመለከተው የፌደራል ሰበር የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 340ን በስፋት በመተቸት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱን ፍርድ ውድቅ አድርጓል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1728/3/ን በተመለከተ ደግሞ ድንጋጌው ‹‹መሀይማን የጣት ምልክት ፊርማቸውን በአዋዋይ ፊት ማድረግ እንደሚገባ ሲደነግግ ኑዛዜን አስመልክቶ በተቀመጠው በቁጥር 881/3/ ማህይማን የጣት ምልክታቸውን ወዲያውኑ ማስቀመጥ ያለባቸው መሆኑን እንጅ በተለይ በአዋዋይ ፊት እንዲያደርጉ አልደነገገም፤›› በማለት የአመልካችን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡ ፍርዱ መሀይምናንን በተመለከተ የተሰጠ ቢሆንም የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1728 ከኑዛዜ ፎርም አንፃር የተረጎመ በመሆኑ ለዓይነ ስውራንም ረብ አለው፡፡ በዚህ መሠረት ዓይነ ስውራን የሚያደርጉት ኑዛዜ በውል አዋዋይ ፊት ባይደረግም የሕግ ውጤት ይኖረዋል፡፡

ቼክን በተመለከተ ሕጉ የሚለው ነገር የለም፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉንም ድንጋጌ ለመጠቀም የሚያስችል የሕግ ምክንያት የለም፡፡ ሆኖም ቼክ ተመሳሳይ ፊርማን አይቶ መፈረም ስለሚጠይቅ ዓይነ ስውራን ቼክ በመጻፍ ግብይት የሚፈጽሙበት ሁኔታ የለም፡፡ ጸሐፊው ያነጋገራቸው የባንክ ሠራተኞች ዓይነ ስውራን የሚጽፉት ቼክ እንዳላጋጠማቸውና ቢያጋጥማቸውም ከቼክ አሠራር አንፃር መፍቀዱ አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸውለታል፡፡ በዚህ ረገድ ዓይነ ስውራን የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ተግባር ላይ ሲውል በኤሌክትሮኒክ ፊርማ ከሚጠቀሙ በቀር የሕግ ክፍተቱ ዓይነ ስውራንን በሚጠቅም መልኩ ሊሸፈን የሚችል አይመስልም፡፡

ማጠቃለያ

ሕጉ የዓይነ ስውራንን ጥቅም ለማስጠበቅ ፊርማን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ቀርጿል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1728/3/ ዓይነ ስውራን ፊርማቸውን በውል አዋዋይ ፊት ካላረጋገጡ እንደማያስገድዳቸው በመደንገግ መርሁን አስቀምጧል፡፡ ይህ ድንጋጌ ለማንኛውም ውል ተፈጻሚ መሆኑ ባያጠያይቅም፣ በተግባር ባንኮች በሒሳብ መክፈትና ማንቀሳቀስ ጊዜ ስለማያከብሩት ከሕጉ የተለየ አሠራር ዳብሯል፡፡ አሠራሩ ለዓይነ ስውራን ጠቃሚ ቢሆንም በሕግ /በአዋጅ፣ ደንብ ወይም መመርያ/ያልተደገፈ በመሆኑ አሠራሩ ሁልጊዜም የባንኮችን ጥቅም ስለማስጠበቁ ዋስትና አይሆንም፡፡ በዚህ ረገድ ብሔራዊ ባንክ ጉዳዩን በመመርያ ቢገዛው ወይም ሕጉ ቢሻሻል የተሻለ ይሆናል፡፡ ኑዛዜን በተመለከተ ግን ዓይነ ስውራንም ሆነ መሀይምናን በውል አዋዋይ ፊት መፈረም ስለማይጠበቅባቸው ዓይነ ስውራን ኑዛዜያቸውን በጥንቃቄ ሊፈጽሙ ይገባል፡፡ የቼክ ጉዳይ በብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ አተገባበር መፍትሔ ካላገኘ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካልና የዓይነ ስውራን ማኅበር ሊያስቡበት ይገባል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getukow [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡