ጭልፊት

ጭልፊት በኢትዮጵያ ተረትና ምሳሌ ውስጥ ትታወቃለች፡፡ በመዝገበ ቃላዊ ፍቺዋ ዶሮን፣ ሥጋና ዓሣ የምትነጥቅ አሞራ፣ በሐምሌና በነሐሴ ወራት የማትታይ ይላታል፡፡ ጭልፊቶች በኢትዮጵያ አብዛኛው አካባቢ ይታያሉ፡፡ እርድ በሚፈፀምባቸው ቦታዎች፣ ዓሣ በሚሰገርባቸው ሐይቆችና ሜዳማ ቦታዎች አይጠፉም፡፡ በየአውራጎዳናው የተጣሉ ጥንቦችን ለማንሳትም የሚቀድማቸው የለም፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ወፎች የኪስ መጽሐፍ›› እንደሚገልጸው፣ ሁለገብ ጭልፊት (Black Kite) ሙሉ አካላቸው ጥቁር ቡናማ ቀለም ያለው አዳኝ ወፎች ናቸው፡፡