ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኒውዮርክ

መቀመጫውን በኒውዮርክ አሜሪካ ያደገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ 70ኛ መደበኛ ስብሰባውን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ያካሄደው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ፣ የዚህ ዓመት ዋነኛ አጀንዳ የሆነው ድኅረ 2015 ዓለም አቀፍ የልማት አጀንዳ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ዘንድሮ የተጠናቀቀው የሚሌንየሙ የልማት ግቦች በመባል የሚታወቀውን ፕሮግራሙ ይተካል ተብሎ የሚታመንበት ዘላቂ የልማት ፕሮግራም በይፋ የሚያፀድቅበት ጉባዔ ይሆናል፡፡

በዚሁ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኒውዮርክ ላይ ተገኝተው በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ፣ ከጠቅላላ ጉባዔው ጎን ለጎን አንዳንድ ወሳኝ የጎንዮሽ ስብሰባዎችን ላይ በመምራት፣ ንግግር በማድረግና በመወያየት ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በተጨማሪ የግብፅ ፕሬዚዳንት አቡዱልፈታህ አልሲሲን ጨምሮ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፋይዳ ካላቸው አገሮች መሪዎችም ጋር የሁለትዮሽ ምክክር ላይ በማድረግ ላይ መጠመዳቸውን ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ቡድን 77

ከጠቅላላ ጉባዔው ጎን ለጎን የሚካሄደው አንዱና በተለይ ለደቡብ ደሃ አገሮች ትብብር መሠረት የሚጥለው የቡድን 77 አገሮች 39ኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መደበኛና ስብሰባ ዋነኛ ሲሆን፣ ድርጅቱ በመልማት ላይ የሚገኙ 77 አገሮች እ.ኤ.አ. በ1964 የመሠረቱት ነበር፡፡ ቡድን 77 ስሙ እንደተጠበቀ ቢቆይም፣ በአሁኑ ወቅት 134 በመልማት ላይ የሚገኙ የደቡብ አገሮች አባል የሆኑበትና በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ውስጥ በቁጥር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አገሮች በማቀፍ ግንባር ቀደም ድርጅት ነው፡፡ የደቡብ አገሮች የጋራ ጉዳዮችንና አጀንዳዎችን በመቅረፅና በመግፋትም ይታወቃል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን መካከል የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ፣ በዚሁ የጎንዮሽ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የኢትዮጵያን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ ቡድኑ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ የታሰቡትን ዓላማዎች በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ባይችልም፣ እጅግ በጣም ወሳኝ የሆኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ታዳጊ አገሮችን በሚጠቅም አኳኋን እንዲወሰኑና መልክ እንዲይዙ በማድረግ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለጠቅላላ ጉባዔው የሚቀርበው ‹‹የዘላቂ ልማት›› አጀንዳ እንዲፀድቅና ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ኮንፈረንስ ላይ በተደረገ ውሳኔ መሠረት፣ ወደ ትግበራ የሚገባበትና በቂ ፋይናንስ የሚገኝበት ጉዳይ ላይ ታዳጊ አገሮች የጋራ አቋም ይወስዱ ዘንድ ጥሪ አድርጓል፡፡

የሰላም ማስከበር

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ልዑክ ድረ ገጽ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የሰላም ማስከበር ጉባዔ ያዘጋጀች ሲሆን፣ ጠቅላይ ማኒስትር ኃይለ ማርያም የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ኢትዮጵያ በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. መጨረሻ አፍሪካ ለተለያዩ ቀውሶች ፈጣን ምላሽ መስጠት የምትችልበት አጀንዳ በአዲስ አበባ መካሄዱን አስመልክተው፣ ውይይት የተደረገባቸውን አንኳር ጉዳዮችና ከዚሁ አኅጉራዊ ጉባዔ የተገኘው ውጤትና ተሞክሮ በሪፖርት መልክ አቅርበዋል፡፡ ሰላም በማስከበር ሒደት በተለይ በአፍሪካ የተገኙ መልካም ውጤቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያና በአሜሪካ የጋራ አዘጋጅነት የተዘጋጀ ይኸው ስብሰባ በአዲስ አበባ በተካሄደው የመጀመርያ ጉባዔ ላይ ተመርኩዞ የተከናወነ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በተለይ በአፍሪካ የኅብረቱ አባል አገሮች ከአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል (African Standing force) ዓላማዎች ጋር በተጓዳኝ ለመሳካት የሚያስችል፣ የእያንዳንዱን አገር የተናጠል ጥንካሬን ከፍ ማድረግና ለሚፈጠሩ ቀውሶች በጋራ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የተቀናጀ አቅም መፍጠር አማራጭ የለውም ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡

ሶማሊያ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት በተለያዩ መንግሥታትና አካላት አድናቆት የተቸራት ሲሆን፣ ድርጅቱ በሶማሊያ ላይ ባካሄደው ከፍተኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዋና ተሳታፊ ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ በሶማሊያ አልሸባብን ለመጠራረግ የተከፈለውን መስዋዕትነትና በአካባቢው ስለሚታየው የፖለቲካና የደኅንነት ወቅታዊ ሁኔታና መሻሻል በተመለከተ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ‹‹አንድ ዓመት ይቀረዋል›› ያሉት፣ ‹‹ሶማሊያ ራዕይ 2016›› ፕሮግራም ያለበትን ሁኔታ፣ በዚሁ ራዕይ የተካተቱ ዕቅዶች ምን ደረጃ ላይ መሆናቸው መገምገም እንደሚያስፈልግና በአካባቢው የተጀመረው ጥረት ወደኋላ እንዳይመለስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማድረግ ያለበትን ድጋፍም አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ግምገማ፣ የፌዴራል ሥርዓቱን አወቃቀር መወሰንና የዴሞክራሲያዊ ግንባታ ሒደት የመሳሰሉ ሦስቱ የራዕዩ ዋና ዋና አንኳር ጉዳዮች ምን ደረጃ እንዳሉም ለተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡ በሶማሊያ ተቋማትን ለመገንባት የተደረገውን እንቅስቃሴም አድንቀዋል፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ባቀረቡት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ከተመድም በፊት የነበረው የመንግሥታቱ ድርጅት (League of Nations) ጀምሮ የዓለም ኅብረትና የጋራ ደኅንነት አጀንዳን ዓላማ የምታምን በመሆኗ፣ የተመድ መሥራች አባል መሆኗ ኩራት እንደሚሰማት አስረድተው ድርጅቱ ግን 21ኛውን ክፍለ ዘመን በሚመጥን ደረጃ አገልግሎት መስጠት ገና ይቀረዋል በማለት ምክንያቶችን ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ 70ኛ ዓመቱን ሲያከብር ዓለምና የዓለም ሁኔታ እጅግ መቀየሩን ገልጸው፣ ይህንን የቴክኖሎጂና የፖለቲካ ለውጥ መሠረት በማድረግ ድርጅቱ ራሱን እንዲያበቃና ማሻሻያ እንዲያደርግ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፣ በተለይ የድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት አሳታፊ እንዲሆን ቀደም ሲል የተደረገው ስምምነትና የተደረሰው ውሳኔ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪያቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ዘላቂ ልማት ለማምጣት የተደረሰውን ስምምነት አድንቀው፣ በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ተጨባጭ ስምምነት እንዲደረስ ተመድ ሚናውን እንዲጫወት ጠይቀዋል፡፡ በዚሁ ዓመት በፈረንሣይ (ፓሪስ) የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ ወሳኝ ጉባዔ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

የተጠናቀቀው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከካርቦን ልቀት ነፃና ሙሉ በሙሉ አረንጓዴ ልማት መሆኑን ለአብነት ጠቅሰው፣ ዓለም የገጠሟትን የአየር ንብረት መዛባት ችግር በመመልከት የሁሉንም አባል አገሮች ትብብር እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

ከግብፅ ፕሬዚዳንት ጋር

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከተለያዩ አገሮች መሪዎች ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው እየተዘገበ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ተገናኝተው በታላቁ የዓባይ ግድብ፣ በአየር ለውጥና በጉዳይ ላይ አስመልክተው በቅርቡ በፓሪስ ሊካሄድ ስለታሰበው ጉባዔ መመካከራቸው ተሰምቷል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የዓባይ ውኃ አጠቃቀምና የታላቁ የህዳሴ ግድብ በተመለከተ አንድ የጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ሁለቱም መሪዎች የመከሩት ዝርዝር ነገር ምን ላይ ያጠነጠነ እንደሆነ አልታወቀም፡፡ ነገር ግን የተቋረጠው የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ እንዲቀጥል ተስማምተዋል፡፡

ሁለቱም መሪዎች ኒውዮርክ ተገናኝተው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው እየተነገረ ባለበት ወቅት፣ ከትናንት በስትያ አንድ የግብፅ ልዑክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ብርሃነ ገብረ ክርስቶስን አግኝቶ ባነጋገረበት ወቅት ግብፅ በተመድ የፀጥታ ምክር ቤት አባል ለመሆን ጥረት እያደረገች መሆኑን፣ ኢትዮጵያም ድጋፏን እንድትሰጥ መጠየቁ ታውቋል፡፡ በይፋ ባይገለጽም ፕሬዚዳንት አልሲሲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት፣ ይኼ የድጋፍ ጥያቄ አንዱ አጀንዳ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከተለያዩ አገሮች መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው እየተዘገበ ሲሆን፣ በተለይ ከተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን ጋር በአንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ታውቋል፡፡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ዋና ጸሐፊው፣ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ያደረገችውን ጥረት አድንቀው፣ በተለይ በሱዳን ያለውን ቀውስ ለመፍታት የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ በምትቀጥልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸው እየተነገረ ነው፡፡ እንዲሁም ውይይቱ ሶማሊያንና የአየር ንብረት ለውጥን ያካተተ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡