ግንቦት ሃያ ምንድነው?

በበሪሁን ተሻለ

ግንቦት 20 ፍዳ ያስቆጠረው ወታደራዊ አገዛዝ ያከተመበት ታላቅ ዕለት ነው፡፡ ወታደራዊ አምባገነንነት እንዳይሆን የፈረሰበትና ፈላጭ ቆራጮች እምቧጮ የሆኑበት ቀን ነው፡፡ በጊዜ ንብረትና ቤተሰብ አሽሽተው ያመለጡ ቢያመልጡም፣ አንዳንዶቹ ሊሸሹ ሞክረው የነበሩ ባልደረቦቻቸውን እሥር ቤት ከርችመው ጣሊያን ኤምባሲ ቢገቡም፣ ቀሪዎቹ መላ ሳያበጁ ቢነጋባቸውም፣ የወታደራዊ ኃይላቸው፣ የፀጥታ መረባቸውና ፓርቲያቸው ተበጣጥሶ ማኅተሙ የተመታበት ደረሰኙ የተቆረጠበት ቀን ነው፡፡

ግንባት 20 ይህን ያህል እርግጥ ነው፡፡ ይህን ያህል እውነት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ግን የለውም፡፡ ከዚህ በላይም አይደለም፡፡ እንደገና የተወለድንበት፣ ዴሞክራሲያችን ተመርቆ የተከፈተበት፣ ወርቃማው የፍትህ ዘመን የጀመረበት፣ ኢትዮጵያ መሪዎቿን ፈቅዳና መርጣ የሰየመችበት፣ የአገሪቷ ፖለቲካ ጠርቶ ትግሉ ወደ ሰከነና ወደ ሠለጠነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ግብግብ የተሸጋገረበት ዕለት ነው ማለት እውነትም ልክም አይደለም፡፡ ይህንን እንኳን ያኔ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ይቅርና ዛሬም ከ25 ዓመት በኋላ ለማለት አልታደልንም፡፡

እንኳን ያኔ ዛሬም ያልኩበትን ምክንያት ላስረዳ፡፡ እንኳን ያኔ ካልኩበት ልጀምር፡፡ ሁለተኛውን ቆየት ብዬ እመለስበታለሁ፡፡ ግንቦት 20 ሌላ ምንም ቅፅል፣ የማጌጫና የመዋቢያ ነገር ሳይጨመርበት፣ የሕዝብ ግንኙነትም ሆነ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ሳያስፈልገው፣ በገዛ ራሱ ምክንያት ታላቅ ቀን ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተባለው ወታደራዊው አገዛዝ ያከተመበት ቀን ነው፡፡ ‹‹አሁን ደርግ አለ!?›› ያሉ መሪዎችና መላው መዋቅራቸው የተፈረካከሰበትና የተደረመሰበት ቀን ነው፡፡ አይሆኑ ሆኖ አፈር ድቤ በገባው በወታደራዊው አገዛዝ ምትክ ሥልጣን የያዘው ኢሕአዴግ ራሱ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለትጥቅ ትግሉ በተደራጀበት ይዘትና መልኩ ነው፡፡

የኢሕአዴግ ጊዜያዊ መንግሥት ሥልጣኑን ያዘ እንጂ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሕዝባዊ መንግሥት አልተቋቋመም፣ ሊቋቋምም አይችልም፡፡ ከኢሕአዴግ ጊዜያዊ መንግሥት በኋላ የሽግግር መንግሥት የተቋቋመውና ያስፈለገውም በደርግ ፍርስራሽ ላይ ወዲያውኑ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት፣ ምርጫ ማለት ስለማይቻል ነው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የታዩ ተመሳሳይ ልምዶችና የተቋቋሙ አሠራሮች እንደመሰከሩት፣ አንድ ነባር መንግሥት በአመፅ (በትጥቅ ትግል) ከወደቀ በኋላ፣ የመሣሪያም ሆነ ሌላ ዓይነት ትግል ሲያደርጉ የቆዩ ተቃዋሚ ኃይሎች በሙሉ በፖለቲካው መድረክ ላይ እንዲወጡና የሽግግሩን ወቅት ተግባራት አብረው እንዲያከናውኑ የሚደረግበት የሽግግር ሥርዓት ይዘረጋል፡፡ የሽግግሩ ወቅት ተግባርም ሁሉም የሚስማሙበትን መነሻ ዴሞክራሲያዊ መሠረቶችን መጣልና በዚህ አማካይነትም ሕገ መንግሥታዊ ጉባዔ መጥራት ነው፡፡

ሽግግሩ ተገቢው ሥራ ሁሉ ተሠርቶ፣ ተቃዋሚዎች ሁሉ ተሳትፈውና ተንቀሳቅሰው፣ በሕዝብ ውስጥና በሕዝብ ፊት ታማኝነትን አግኝተው፣ ተወዳጅነት አበጅተው አንዱ ብቻውን ወይም ከሌሎች ጋር የሥልጣን ባለአደራ ሆኖ እንዲወጣ መሰናዶ የተደረገበት ስለመሆኑ ሌላ ጉዳይ ሆኖ፣ የሽግግሩ ዘመን ራሱ ከሞላ ጎደል አራት ዓመት ወስዷል፡፡ ይህም የሽግግር ወቅቱ ቻርተር ከወሰነው ከመጨረሻውና ከጣሪያው ከሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ በላይ ነው፡፡

‹‹ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት›› ፀድቆ በዚህ መሠረት ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ›› እስኪቋቋምና አዋጅ ቁጥር 2/1982 እንደደነገገው ሪፐብሊኩ ተመሥርቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ሥልጣን ከሽግግሩ መንግሥት ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. እስከተካበት ጊዜ ድረስ የፈጀ ሽግግር ነው፡፡ ስለዚህም ግንቦት 20ን ከተገለጸውና ከሚገባው ታላቅነት በላይ ዕለቱ በተከበረ ቁጥር፣ የመከበሩም ድግግሞሽ በቀጠለ ቁጥር፣ ይብስ እያገረሸበት እንደሚባለው ‹‹ከየትኛውም በዓል›› ታላቅ ‹‹የቀናት ሁሉ አውራ››፣ የብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ጥያቄ መልስ ያገኘበት፣ ወዘተ ወይም ‹‹ተዓምራት›› የተፈጸመበት ቀን አይደለም፡፡

ተደጋግሞ እንደተገለጸው ወታደራዊው አገዛዝ ያከተመበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ ፈላጭ ቆራጮች እምቧጮ የሆኑበት፣ ወታደራዊ ኃይላቸው፣ የፀጥታ መረባቸውና ፓርቲያቸው የተበጣጠሰበት ቀን ነው፡፡ በሽግግር ዘመኑ ውስጥም ሆነ ከዚያ ወዲህ እስካሁን ያሉ ይህንኑ ቀን እግረ መንገዳቸውን የሚያወሱ፣ ኦፊሴል ሰነዶችም የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው፡፡ የሽግግሩ ወቅት ቻርተር ራሱ በአዋጅ ‹‹ኢትዮጵያን ለአሥራ ሰባት ዓመታት ሲገዛ የቆየው የወታደራዊው አምባገነን መንግሥት መገርሰስ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩንና መንግሥቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደ አዲስ ለመገንባት የሚችልበትን ዕድል የከፈተ ታሪካዊ ወቅት፤›› ነው ይለዋል፡፡

ቻርተሩ ‹‹ወታደራዊው አምባገነን መንግሥት የቀድሞዎቹ መንግሥታት ተቀጥያ እንደመሆኑ መጠን፣ ውድቀቱ የጭቆናንና የአፈናን ዘመን ማክተም በማመልከት ነፃነት የእኩልነት መብቶችና የሁሉም ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት መርሆዎች፣ የፖለቲካ የኢኮኖሚ የማኅበራዊ ሕይወት ምሰሶዎች የሚሆኑበትን አዲስ ምዕራፍ በመክፈት የኢትዮጵያን ሕዝቦች ከዘመናት የጭቆናና የኋላቀርነት ቀንበር አውጥቶ ደኅንነታቸው የሚጠበቅበትን ሁኔታ ለመፍጠር አስተዋጽኦ የሚያበረክት…›› ነው ሲልም በቃ አለቀ ደቀቀ፣ ከዚህ በኋላ ምን ትፈልጋለህ? ማለቱ አይደለም፡፡ በ1984 ዓ.ም. በሙሉ የተወሰዱት የሕግ ማውጣት ዕርምጃዎች ከሞላ ጎደል እንዳሉ ግንቦት 20 ለከፈተው አዲስ ምዕራፍ መነሻ የሆኑ መደላድሎችን በየሥፍራቸውና በየብቻቸው የማስቀመጥ መከራዎችን የሚመለከቱ ነበሩ፡፡

ይልቁንም የመሣሪያውና የትጥቅ ትግሉ አብቅቶ ዋነኛውና ምትክ የሌለው የሰላማዊና የሕጋዊ ትግሉ ምዕራፍ በመከፈቱ፣ ይህም የማንንም የኢሕአዴግን ጨምሮ፣ የሁሉንም ኃይሎች ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መለወጥ፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር ይዞ መገኘት የመሰለ፣ ማንም አስቀድሞ የማያውቀው፣ ያልለመደውና ሊለማመደውም ያልቻለ ፈተና በመጋረጡ ተከታዩ የሕጋዊውና የሰላማዊው ትግል ምዕራፍና ጉዞ ይበልጥ እያስቸገረ መጣ፡፡ በተለይ ኢሕአዴግ ራሱ እዚህ ላይ ብዙ ተቸገረ፡፡ ለሐሳቦቹ አሸናፊነት፣ ማለትም ሐሳቦቹ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ በአብዛኛው ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ከሌሎች ሐሳቦች ጋር ከመታገል ይልቅ በጦርነቱ አሸናፊነት መጎናፀፉን፣ በተለይም የረባና የሚያሠጋ የፖለቲካ ኃይል አለመኖሩን የገዛ ራሱ ብቸኛ ትክክለኛነት ማስረጃ አድርጎ ተቀበለ፡፡

ኢትዮጵያ መንግሥት ምንጊዜም በበዳይነትና በጨቋኝነት የሚታወቅበት አገር ሆና ኖራለች፡፡ ይህንን ደርግን የገረሰሰው ኢሕአዴግ ያውቃል፡፡ መንግሥት በዚህ ዓይነት ደመኛነቱ እንጂ በምንም ቀና ነገር በማይታወቅበት አገር አዲስ ምዕራፍ ይከፈታል፡፡ በተለይም ደግሞ የዴሞክራሲ ዘመን ይነግሳል ብሎ ስለተነሳ፣ ቃል ኪዳን ስለገባና ተስፋ ስለሰጠ ብቻ ማንም ወገን ታማኝነት እንደማያገኝ ለኢሕአዴግ በጭራሽ ግልጽ አልነበረም፡፡ እንዲያውም የደርግ መገርሰስ የኢሕአዴግ ድል ማድረግ የትጥቅ ትግሉ እንጂ የትግሉ ማክተሚያ አይደለም፣ ትግሉ ይቀጥላል፣ አዲሱ ዓይነት ትግል ደግሞ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ነው ብሎ ከማንም በላይ በመፈክር የጮኸው ኢሕአዴግ፣ ያለ ተቃዋሚ ሥራውን ማካሄድ አለመቻሉን የሴራና የተንኮል ጉዳይ አድርጎ ወሰደ፡፡ እኛና እነሱ፣ የወገን ጦርና የጠላት ወገን ማለት ተጀመረ፡፡ በሐሳብ መለያየት ግንቦት 20 ላይ እና ከዚያ ወዲህም ሞት ሆኖ ተፈረጀ፡፡ የተለየ ሐሳብና አቋም ያላቸው ሰዎችና የፖለቲካ ኃይሎች የሚያራምዱት አቋም ትክክለኛ ሆነም አልሆነም፣ በፖለቲካው ሒደት ውስጥ ልክ እንደ ኢሕአዴግ እንደ ራሱ የተነሱበት ምክንያት፣ ጥቅምና ሥፍራ እንዳላቸው በበጎ ዓይን ማየት ጠፋ፡፡ ግንቦት 20 አዲስ ዕድል ማምጣቱና ሌላ ምዕራፍ መከፈቱ ዕውን ቢሆንም፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ የጀመረበት ዕለት፣ የቀናት ሁሉ አውራ፣ ከየትኛውም በዓል የበለጠ በዓል፣ ከዕለታት ሁሉ የተባረከ ዕለት ማለት ግን በጣም አስተዛዛቢ ነው፡፡

ከሁሉም የበለጠ የሚገርመው ደግሞ ኢሕአዴግ ‹‹ከቀኖቹ ሁሉ የተባረከ›› ነው የሚለውን ግንቦት 20 ማክበር የጀመረው ዕለቱን በአገር የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀን አዋጅ ውስጥ ሳያካትትና ሳይደነባ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ግንቦት 20ን የሕዝብ በዓል ለማድረግ፣ እንዲሁም መስከረም ሁለትን ከዚህ የሕዝብ በዓላት ዝርዝር ውስጥ ለመሰረዝ አስቀድሞ ቢያቅተው ወይም ሳይመቸው ቢቀር እንኳን አምስተኛውን የግንቦት 20ን ቀን በሕግ የታወቀ ማድረግ ይችል ነበር፡፡ የዚህ ምክንያት ከየካቲት 1988 ዓ.ም. ጀምሮ በፀና የሕዝብ በዓላት ማሻሻያ አዋጅ የድል ቀንን ከመጋቢት 28 ቀን ወደ ሚያዝያ 27 ቀን እንዲዞር በሕግ የተደነገገ በመሆኑ ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን እነሆ የግንቦት 20 ቀን 25ኛው የብር ኢዮቤልዩ የሚከበረው ዕለቱ በሕግ በሕዝብ በዓላት ቀን ውስጥ ሳይመዘገብ ነው፡፡

ከዋናው መሠረታዊ የመርሆና የአፈጻጸም ችግር በተጨማሪ በሕግ ያለመደንገጉ ስያሜ ላይ ያስከተለው ውዥንብር የሚናቅ አይደለም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያሳትመውን አጀንዳ ጨምሮ ብዙዎቹ ዕለቱን የሚያውቁት ‹‹ኢሕአዴግ ደርግን ያስወገደበት›› ብለው ነው፡፡ የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የዘንድሮ በዓል ዘገባ ደግሞ ዕለቱን የድል ቀን ይለዋል፡፡ የድል ቀን ማለት በኢትዮጵያ ሚያዝያ 27 ቀን ነው፡፡ በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጀትና በስዊዘርላንድ የሌሎች ዓለም አቀፋዊ ድርጀቶች የኢትዮጵያ ቋሚ ሚሲዮን ደግሞ የዘንድሮን የግንቦት 20 በዓል ምክንያት አድርጎ በድረ ገጹ ያወጣው መግለጫ ዕለቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀን ሲል ይሰይመዋል፡፡ ‹‹ብሔራዊ ቀን››!

በዚያ ስም ተጠርቶም አያውቅም እንጂ አሁን ደግሞ ከነጭራሹ ይህንኑ ስያሜ ያለዕውቀት ተገፏል እንጂ፣ አዲስ አበባ ግንቦት 20 የሚባል መንገድ ሰይማ ነበር፡፡ በእርግጥ ግንቦት 20 ታሪካዊ ቀን ነው፡፡ ጦርነቱ የቆመበት ወይም የተፈጸመበት ቀን ነው፡፡ በአብዛኛውና ከሞላ ጎደል ሁሉም የሚስማማበት ከፊል ኦፊሴላዊ ስሙ እንደሚገልጸው ‹‹ኢሕአዴግ ደርግን ያስወገደበት›› ቀን ነው፡፡

ግንቦት 20ን ታሪካዊ ቀን የሚያደርገው ግን ደርግን ማስወገድና ኢሕአዴግን ሥልጣን ላይ ማውጣት በራሱ የመጨረሻው ግብ ስለሆነ አይደለም፡፡ ደርግ እርግማን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የወደቀ መርግና መርገምትም ነበር፡፡ ከጦርነት ተላቅቆ የተረጋጋ ኑሮ ለናፈቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከደርግ መገላገል ራሱን የቻለ ዕፎይታና ግብ ነበር፡፡ የመጨረሻ ግብ ግን እሱ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚያ በኋላ በተገኘው ሰላም ውስጥ መነሻ የዴሞክራሲ ሁኔታዎችን አመቻችቶ አገርን እንደገና የማደራጀት፣ የማበጀትና የሕዝብን ከሕዝብ፣ የሕዝብን ከመንግሥት ግንኙነት እንደገና አዋድዶ የመገንባት ታላቅ ሥራ አለ፡፡ ግንቦት 20 ይህ ሁሉ የሆነበት ወይም ይህ ስለመሆኑ የተረጋገጠ ዋስትና ያገኘበት አይደለም፡፡

ግንቦት 20ን እንኳንስ ሃያ አምስት ጊዜ፣ እንኳንስ ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ ይቅርና ለመጀመርያ ጊዜ ያኔ በ1984 ዓ.ም. በተከበረበት ጊዜ ነገር ዓለሙ ሁሉ ከእጅ ማምለጡ፣ ከመንገድ መውጣቱ፣ ታጥቦ ጭቃ መሆኑ በአደባባይና በይፋ እየታየ እየተጋለጠ ነበር፡፡

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሁሌም በየካቲት ወር የሕወሓት የልደት በዓል የኢትዮጵያ ሕዝብም ልደት ነው የሚል ሀተታ እንደሚያሰማን ሁሉ ግንቦት 20ም የዴሞክራሲ ጮራ የታየበት፣ የዴሞክራሲ ፀሐይ የበራበትና እንዲያውም በግዳጅ የማይከበር የሕዝብ በዓል ተብሎ ተሞካሸ፡፡ ደርግ ከውልደት እስከ ሞቱ ተነሳ፡፡ ከመታሰቢያ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና የስፖርት ውድድር አልፎ ግንቦት 20 በአብዮት አደባባይም ተከበረ፡፡ የሕወሓት ኢሕዴንን ታጋዮች የጎማ ሰንደል ጫማ ያጠለቀ፣ እርግብ በኢሠፓ ዓርማና በብረት ቆብ ላይ ቆማ በሚያሳይ የጨርቅ ሥዕል ግርጌው በተጌጠው የእነ መንግሥቱ ሰገነት ላይ መለስ ዜናዊና ታምራት ላይኔ በወርቃማ ወንበሮች ላይ ተቀምጠው ታዩ፡፡ ሰሜን ኮሪያ ለደርግ የፀደቀችበት የፕላስቲክ አበባ ዳግም ተነስቶ እየተውለበለበ፣ ነፃ መፈክርና ስሜት የሌለበት በድን ሠልፍ በሠገነቱ ሥር አለፈ፡፡

ልክ በዚያኑ ወቅት ኦነግና ኢሕአዴግ ለ‹‹ፍጥጫው ጦርነት›› ከዝግጅት በላይ አልፈው ፍልሚያ ላይ ነበሩ፡፡ ከ‹‹ብሔራዊ ነፃነት ንቅናቄዎች፣ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችና ከታዋቂ ግለሰቦች ተወጣጥቶ ከ87 በማይበልጡ አባላት›› የተመሠረተው የሽግግሩ መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ባለ 32 መቀመጫ ኢሕአዴግ ነው፡፡ ባለአሥሩ ደግሞ ኦነግ ነው፡፡ ሁኔታዎች በፈቀዱበት ሁሉ የብሔራዊ፣ የክልላዊና የወረዳ ምክር ቤቶች ምርጫ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ይከናወናል የተባለው ምርጫ ቀጠሮ የተያዘው ለሰኔ 14 ቀን 1984 ዓ.ም. ነው፡፡ የምክር ቤቱን ወንበር/በርጩማ በመቃመስና እውነተኛ ሥልጣንን በመካፈል መካከል ያለው ልዩነት የተምታታበት ይህ የሥልጣን አካል፣ ዋነኛ ተወዳዳሪና ተገዳዳሪ አባላትም ኢሕአዴግና ኦነግ ነበሩ፡፡

እነዚህ ሁለቱ ኢሕአዴግና ኦነግ እየተሳሳቁ፣ እየተኳረፉና እየታረቁ የሚገዛገዙበት ጊዜ አልቆ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን መሸነቋቆጥም መጥቷል፡፡ መንግሥታዊ ሚዲያው ሳይቀር መጎሻሸሚያ መሣሪያ ሆነ፡፡ መጪው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ አይሆንም ይሆናል የሚለው በመንግሥቱ ውስጥ ያሉ ቡድኖች መከራከሪያ እስከመሆን ደረሰ፡፡ ምርጫው ለሰላም የቆመና ያልቆመ ወገን መለያ ተደርጎም ተሰየመ፡፡ በኦነግና በኢሕአዴግ መካከል በዜና በመግለጫና በግል አስተያየት መልክ የሚካሄደው መጎሻሸም ወደ የከፋ መዘራጠጥ ተሸጋገረ፡፡ በዚህ መካከል የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃንም የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ አሉና ከኢሕአዴግ ሬዲዮ ጋር ሆነው ኦነግን ማላመጥ ገቡ፡፡ የኦነግ ሬዲዮ ቋንቋም መራር እየሆነ መጣ፡፡ ሰኔ 10 ቀን 1984 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ክፍል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ኦነግ ለሰኔ 14 ለተቀጠረው ምርጫ የሚያበቃ ዝግጅት ስለሌለ፣ ጽሕፈት ቤቶቹ የተዘጉና አባላቱና ደጋፊዎቹ የተሠሩ ስለሆነ በምርጫው እንደማይሳተፍ ገለጸ፡፡ እነ መአሕድና ኢዳግ ተደረቡ፡፡ ኦነግ የወጣበት የምርጫ ዝግጀት በአጥጋቢ ሁኔታ እየካሄደ ነው መባሉ ቀጥሎ ሳለ፣ ሰኔ 13 ቀን የምርጫ ኮሚሽኑ በሰጠው መግለጫ መሠረት ከዚያ በፊት ምርጫ እንደማይካሄድባቸው ተለይተው ከታወቁት የአፋር፣ የሶማሌና የሐረሪ ክልል በተጨማሪ ከቀሪዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች በፖለቲካና በፀጥታ ምክንያት፣ እንዲሁም ሰነዶችና አስመራጮች በወቅቱ ሊሟሉ ባመቻላቸው ከ26,000 ጣቢያዎች ውስጥ ወደ ስድስት ሺሕ የምርጫ ጣቢያዎች ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የማይከናወንባቸው መሆኑንና የምርጫ ጊዜያቸውም መራዘሙን አስታወቀ፡፡ ኦነግም በምርጫው ማግሥት ከሽግግር መንግሥቱ ወጣ፡፡ በሱ ቤት የሽግግር መንግሥቱን አፍርሷል፡፡ ከምክር ቤቱና ከካቢኔው ውስጥ አባላቱን አግልሎ በነፃነት ትግሉ የሚገፋ መሆኑኑ ይፋ ገልጾ ሠራዊቱን አነቃንቋል፡፡

አዲስ ምዕራፍ የከፈተው የደርግ መውደቅ፣ እንዳልሆነ መሆን የጀመረው ገና የመጀመርያ ገጹ ላይና አንደኛው የግንቦት 20 በዓል አካባቢ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመርያው የምርጫ ዕድልና አጋጣሚ የሦስት ወራት የቻርተር ቀጠሮውን ማክበር ቀርቶ በዓመቱም በግንቦት 20 ድል ላይ የሚገነባ ዕርምጃ አላስመሰከረም፡፡ ይልቁንም ከሽግግር መንግሥት መሥራች አባል ድርጅቶች ውስጥ ኦነግ በምርጫና በሕግ ሳይሆን በኩርፊያና በቁጣ ወጣ፡፡ ኢሕአዴግ የመጀመርያውን የግንቦት 20 በዓል አዲስ አበባ አብዮት አደባባይ ባከበረ ማግሥት፣ ሰንበት ብሎ በሐብሮ አውራጃ ገለምሶ ላይ አካባቢውን ከደርግ ነፃ ያወጣሁበት ብሎ የሻዕቢያና የኢሕአዴግ ተወካይ በተገኙበት የ‹‹ድል ቀን›› ያከበረው ኦነግ፣ ከሽግግሩ መንግሥት የወጣው ከኢትዮጵያ ‹‹የሰላምና የዴሞክራሲ ኃይሎች›› ውስጥ የወጣው ሌላ የድል ቀን ሳያከብር ነው፡፡ በዚያው በ1984 ዓ.ም. ውስጥ ነው፡፡ የኦነግ በዚህ ሁኔታ መውጣትም አገራችንን ብዙ ጎድቷታል፡፡

የኦነግ መውጣት አገሪቷን ጎድቷታል የምንለው ኦነግ ጥሩ ድርጅት፣ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ስለሆነ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳት ኦነግ መውጣቱ ሳይሆን አወጣጡ ነወ፡፡ ጥፋቱ ደግሞ የኢሕአዴግ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የሥልጣን ተቃዋሚውን፣ የእሱን ሥልጣን የሚጋፋውን በማቃለል የቅርብ ጥቅም ታውሮ፣ ለኦነግ ከምርጫና ከሽግግር መንግሥት መውጣት ሰበብ ሆነ፡፡ በልብወለድ የቅኝ ግዛት ጥያቄና በጎሰኛ ጥላቻ የታወረውንና በግፍ የተጨማለቀውን ኦነግን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ፊት ወደማያዳግም የፖለቲካ ግብዓተ መሬቱ ከመሄድ አተረፈው፡፡ ለኃፍረተ ፖለቲካው መከለያ ሰጠው፡፡ ሕዝብ ራሱን ኢሕአዴግን እንዲፀየፈው እንዲሸሸው ሲያደርግ ኦነግና ሌሎች ርባና ቢስ ምናልባትም አደገኛ ተቀናቃኞችን ግን ሳይለፉ ጭፍን ድጋፍ ለማግኘት እንዲችሉ አገዛቸው፡፡ ኦነግና የቅኝ ጥያቄው እነሆ አሁንም ድረስ የኢትዮጵየ ሕዝቦች ትግል ችግር ሆኖ እንዲቀጥል አደረገ፡፡ ለራሱም ለኢሕአዴግም ቢሆን ለያኔው ዕዳ ያቀለለ መሰለው እንጂ፣ በሥልጣን እስካለ ድረስ የማይላቀቀውን ጠላት አገግሞና ጠንክሮ እየሞተና እየተነሳ፣ እየተፈረካከሰና ተመልስ ተሠራሁ እያለ እንዲመለስ፣ እንዲመላለስ መርቆ ሰደደው፡፡

ግንቦት 20 እንደገና የተወለድንበት፣ ዴሞክራሲያችን ተመርቆ የተከፈተበት፣ ወርቃማው የፍትሕ ዘመን የተጀመረበት፣ ኢትዮጵያ መሪዎቿን ወድዳና ፈቅዳ መርጣ የሰየመችበት፣ የአገሪቱ ፖለቲካ ጠርቶ ትግሉ ወደ ሰከነና ወደ ሠለጠነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ግብግብ የተሸጋገረበት ዕለት ነው ማለት እንኳን ያኔ ከ25 ዓመት በፊት ዛሬም ጭምር ትክክል አይደለም፡፡ ይህንን ከቃላት በላይ ተጨባጭና ነባራዊው ኑሯችን ይናገረዋል፡፡

መሪዎቻችንን ወድደን፣ ፈቅደንና መርጠን የምንሰይም ስለመሆናችን በቅድሚያ እናንሳ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የ1984 ዓ.ም. እና መሰል ምርጫዎች ሳይቆጠሩ እነሆ አምስት ጠቅላላ ምርጫዎች አይተናል፡፡ በእነዚህ ምርጫዎች ሁሉ በተይም በፌዴራል ደረጃ አሸናፊው ኢሕአዴግ ነው፡፡ እስከ ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ማለትም እስከ 29ኛው የግንቦት 20 በዓል ድረስ በሥልጣን የሚቆየውም ኢሕአዴግ ነው፡፡ በ2007 ዓ.ም. ምርጫ መሠረት፡፡ የሚያስገርመውና ጥያቄ የሚያስነሳው እንዴት አንድ ፓርቲ አገሪቱ ያስተናገደቻቸውን አምስት ምርጫዎች በሙሉና በተከታታይ ያሸንፋል? አይደለም፡፡ በጭራሽ፡፡ ፓርቲዎች በዝተው ተባዝተው አማራጮች ሰፍተው ከእነዚህ መካከል በተከታትይ እስካሁን፣ ወደፊትም የሚታየንን ያህል የሚያሸንፈው አንድ ፓርቲ ብቻ ቢሆን ነውር የለውም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን በተካሄዱት ምርጫዎች አሸናፊ የሆነው ፓርቲ አንድ ብቻ መሆኑ የሚያስጠላው ያ ፓርቲ ኢሕአዴግ በመሆኑም አይደለም፡፡ ምርጫም አማራጭም ስለሌለ ነው፡፡ የሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ስላልተግባቡ ነው፡፡

ኢሕአዴግ በነፃ ተደራጅቶና በምርጫ ተወዳድሮ ሥልጣን የመያዝ መብት በኢትዮጵያ ስለመረጋገጡ ቢሰብክም፣ ሁኔታው ጨርሶ የተለየ ነው፡፡ መጀመርያ ነገር የመደራጀት መብቱና ነፃነቱ የሌለ ያህል ነው፡፡ የለምም፡፡ አሁን ያሉትና የቀሩት የፖለቲካ ድርጅቶች የሕዝብ ትርታ የመሆን ወግ የሚሞካክራቸው አይደሉም፡፡ የበረዶ ወቅት ሲመጣ አንቀላፍተው ከርመው ፀሐይ ስትወጣ ብቅ የሚሉ ፍጡራንን ይመስል ምርጫ ሲደርስ ብቅ፣ ምርጫ ሲያልፍ ስውር የሚሉትንና የሚደረጉትን (የሚያደርጋቸውን) ፓርቲዎች ይዞ እንኳን ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አማራጭ ሊገኝ ራሳቸውንም ማቆየት አይችሉም፡፡ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ ሲጀመር አንስቶ ገዥ የሆነውና አሁንም በገዢነቱ የቀጠለው ፓርቲ ኢሕአዴግም ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪ ተለውጦ፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር ይዞ መገኘት በጭራሽ አልቻለም፡፡ ከነበረውና አሥራ ሰባት ዓመት ሙሉ ከተካነበት የጦርነት ሥልት መሸጋገር ባለመቻሉ ገና አንድ ተብሎ ሳይጀመር በተማረው ኃይልና ክፍል ላይ ጥቃትና ጥላቻ ሰነዘረ፡፡ የፖለቲካ ልዕልና ማግኛ መንገዱን አበላሸ፡፡ ዘጋ፡፡ ከሕዝቡ ጋር ሊኖረው የሚፈልገውን የፖለቲካ አግባብ ለመፍጠር የሚያስችለውን አንዱን ዋና መንገድ ገና ከመጀመርያው ጥርቅም አድርጎ በመዝጋቱ፣ በፖለቲካው መስክ የተከላካይነት ሚና ውስጥ ተሰንቅሮ እስካሁንም እዚያው ነው፡፡

ተቃዋሚዎች የሌሉ ያህል በሆኑበት፣ ገዢው ፓርቲም ሁሉን ነገር ለራሱ ሥልጣን መሣሪያ በሚያደርግበት፣ ከእኔ ያልገጠመ ፖለቲካ የአገር ጠላት ነው በሚልበት በዚህ ሁኔታ ግንቦት 20 የብዙኃን ፓርቲዎች መፍለቂያ፣ ወዘተ የሚባለው አይገባም፡፡ ይልቁንም ያማል፡፡ ዕውን ኢትዮጵያ ውስጥ አማራጭ ፓርቲዎች አሉ? በአማራጭነት ኢሕአዴግን በምርጫ የሚፈታተኑ ብርቱ ፓርቲ የለንም፡፡ ያለመኖራቸውም ምክንያት በራሳቸው ድክመት ላይ ብቻ የሚመካኝ አይደለም፡፡ ፓርቲዎችም ኖረው፣ አሉ የሚባሉ ተቃዋሚዎች እንዳሉ ተባብረው እንደ ግንቦት 97 ቢመጡ እንኳ ‹‹ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ወገናዊነት ነፃ የሆነ የምርጫ ውድድር ሜዳ የመገኘቱ ነገር ሌላ ፈተና ነው፡፡

በምርጫ ማሸነፍ ድንገት ቢሳካ? ትርምስም ሆነ አፍርሶ መገንባት ሳይኖር የተረጋጋ ሕይወት የሚቀጥል ስለመሆኑ ግንቦት 20 መተማመኛ ሰጥቶናል? ገዢው ፓርቲ እኔ ነኝ ያሸነፍኩ ብሎ በጉልበት የማይቀማበት ወይም አሸናፊ ነኝ ባለ ወገንና አልለቅም ባለ ወገን መካከል ሕዝብ ተከፋፍሎ ቀውስ ውስጥ የማይገባበት፣ የተለፋበት የልማት ሥራ ለውድመት የማይጋለጥበትን ሁኔታ ያደላደለ ግንቦት 20 እናውቃለን ወይ? የ25 ዓመቱ ትግል እንኳን መልስ መስጠት አደባባይ አውጥቶ ያልጠየቃቸው በርካታ መሠረታዊና አሳሳቢ ጥያቄዎች አሉ፡፡ አንድ የአገር ግንባታ ጉዳይ እናንሳ፡፡ ለነገሩና ለምሳሌ ያህልም ሕጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ጠንካራ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ አላት እንበል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ከፖለቲካ ሌላ ሌላ ኃይል የላቸውም፡፡ ሊኖራቸውም አይገባም፡፡ ሕግን ቢደፍሩና በጉልበት ሥልጣን እንይዛለን ለማለት ቢሞክሩ የሕግና የፀጥታው አካል ይከለክላቸዋል፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ ሕግን ልተላለፍ ቢል በሕግ መከላከል ይቻላል? የመከላከያ ኃይልን ለመንግሥት ግልበጣ መገልገል መፈቀድ እንደሌለበት ሁሉ፣ ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት አደጋ ላይ ነው በማለት የጨነቀው ገዥ የሚያከናውነውን ሕገወጥነት ነቅቶ መጠበቅና ማቆም የሚያስችል ሥርዓት አለን? ግንቦት 20 የዓምደ መንግሥት (State) እና የመስተዳድር ልዩነትን በወጉ ፈልቅቆ አውጥቷል? እጅግ በጣም ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡

አሜሪካን በምሳሌነት እንመልከት፡፡ የዴሞክራቲክ ፓርቲና የሪፐብሊካን ፓርቲ ከዓውደ መንግሥቱ ጋር ምንም ዓይነት ልዩ ትስስር የላቸውም፡፡ ሥልጣን የያዘው የትኛውም ፓርቲ ቢሆን እንዲህ ያለ ልዩ ትስስር በማበጀትና ባለማበጀት ምክንያት ተጠቃሚም ተጐጂም የሚሆኑበት ሁኔታ የለም፡፡ ሁለቱም በሕግና በምርጫ ወጪና ወራጅ በመሆን ረገድ አይበላለጡም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ገዥውን ፓርቲ በዚህ ዓይነት መመዘኛ ከተቃዋሚዎች ጋር እኩል አድርጎ ማስቀመጥ በፍፁም አይቻልም፡፡ እኛ አገር ሥልጣን የያዘ ፓርቲ መንግሥት (State) የሆነ ያህል ነው፡፡

አፄ ኃይለ ሥላሴ ለማይከሰስና ከሰማይ ለተሰጠ ፍፁማዊ ገዥነት መሣሪያ የሆነ አውታረ መንግሥት ገነቡ፡፡ የደርጉ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የራሱን ተመላኪነትና ተቆጣጣሪነት በኢሠፓና በደኅንነት መረቡ አማካይነት በኅብረተተሰቡ ላይ አዋቀረ፡፡ ኢሕእዴግ መጥቶም በግል/በፓርቲ አምሳል የመቅረፅ ታሪክን አላስቆመም፡፡ እንዲያውም ቀጠለበት፡፡ ገና ወደ ሥልጣን እንደመጣ የቅልበሳ አደጋ በማይኖርበት አኳኋን የነበረውን የአገዛዝ (የደኅንነት የጦር አውታር) አፍርሶ የራሱን ታጋዮች አከርካሪ ያደረገ ግንባታ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያካሄደው ለውጥ፣ ከፓርቲ ነፃ የሆነ መንግሥታዊ የአገዛዝ አውታርን ተጨባጭ እንዳያደርግ ሰንክሎ ይዞታል፡፡

በ1984 ዓ.ም. በጥር ወር የወጣው የማዕከላዊ የሽግግር መንግሥት የአገር መከላከያ ሠራዊት ሥምሪትና የፖሊስ ኃይል ማቋቋሚያ አዋጅ፣ ‹‹የአገሪቱን የመከላከያ ሠራዊት በዘለቄታ ማቋቋም ወደፊት በሕዝብ የሚመረጠው መንግሥት ኃላፊነት፤›› ነው ቢልም፣ ለሽግግሩ ዘመን የማዕከላዊ መንግሥት የአገር መከላከያ ሠራዊት ሆኖ እንዲያገለግል የተወሰነለት የኢሕአዴግ ሠራዊት ግዳጁን በዚያው በሽግግሩ ዘመን አላበቃም፡፡ ዛሬም የአገሪቱ መከላከያና ደኅንነት ከኢሕአዴግ ጋር የተሳሰረ አመጣጡን እንደያዘ ነው፡፡

የዚህን ትስስር ስፋትና ጥልቀት በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አይተነዋል፡፡ ተቃዋሚዎች በቀድሞው የሠራዊት አባላት ላይ የተፈጸመውን በደል እያነሱ ሲወቅጡበት፣ ኢሕአዴግ ደግሞ ተቃዋሚዎች ሠራዊት ሊበትኑ ነው ከሚል የውስጥ ቅስቀሳ አልፎ በይፋ መግለጫ የኢሕአዴግን ሠራዊት ነባር የትግል ውለታ የሚቆጥር እያስመሰለ መከላከያ ሠራዊቱ በአመጣጥ፣ በዕይታና በተልዕኮ ከኢሕአዴግ ጋር ያጣበቀ ቅስቀሳ ሲያደርግ ሰማን፡፡ ኢሕአዴግ የከፋ ችግር ቢመጣ የት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል የጠቆመ አጋጣሚ ነው፡፡

ግንቦት 20 ፍዳ ያስቆጠረን ወታደራዊ አገዛዝ ያከተመበት ታላቅ ዕለት ከመሆን በላይ፣ ሌላ ተዓምር አላስመዘገበም የምንልበት ሌላም ምክንያትና ርዕሰ ጉዳይ አለ፡፡ ገዥው ፓርቲ ዕቅድና ፖሊሲውን በንቃት የሚያስፈጽምበት የሰው ኃይል ለማብዛት ያደረገው ትግል፣ የመንግሥታዊ መሥሪያ ቤት አውታሮችን በአባላትና በካድሬዎች እንዲጥለቀለቅ አድርጎታል፡፡ የመንግሥታዊ አካላት ለኢሕአዴግ ማጋደልም በግልጽ የሚታይ እውነት ነው፡፡ የፓርቲውን ዓላማ ነው የማስፈጽመው ማለት ድረስ የዘለቀ አለማፈር አለ፡፡ በዚህ ምክንያት ከኢሕአዴግ የተቀያየመው ጉዞውና እንቅስቃሴው መሰናከል ቢበዛበት፣ የተለሳለሰ ፓርቲ ደግሞ መሰናከሉ ቢቀልለት አይገርምም፡፡

የመንግሥት ሚዲያዎች የገዥውን ፓርቲ ፍላጐት በማገልገል የተጠመዱ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኝነት›› ራሱ ስሙ እንጂ ተግባሩ የለም፡፡ ልማታዊ ጋዜጠኝነት የሚባል ነገር ካለ ይህ ተገነባ፣ ያ ለማ የሚሉ አዳናቂ ፕሮግራሞች ማጉረፍ ማለት አይደለም፡፡ የመልካሙ ሥራ ዜና መሆኑ ሳይረሳ ልማትን፣ መልካም አስተዳደርን፣ ፍትሕንና የሰብዓዊ መብት አያያዝን የሚያጎሳቁሉ የባህል የአሠራርና የተግባር ብልሽቶችን በየትኛውም የመንግሥት ተቋም ውስጥ እያሳደዱ ሁለገብ ልማትን መታደግ ነው፡፡ ይህ በመንግሥት ሚዲያ ውስጥ ተጨባጭ ሊሆን የሚችለው የመንግሥትን (የፓርቲ አይደለም) አቋምና ፖሊሲ ከማክበርና እንቅስቃሴውን ከማሳወቅ ባሻገር፣ ጋዜጠኛው የገዥው ፓርቲ አዘጥዛጭ መሆን ሳያስፈልገው ኅብረተሰቡን እንዲያገለግል ነፃነቱ ሲኖረው ነው፡፡ ጋዜጠኞች ለዚህ ነፃነትና ክብር መታገል ቀርቶ ነፍስና ህሊናቸውን የገበሩ በማረጥረጥ ኑሮ የተዋጡ ሆነዋል፡፡

ብዙ ፓርቲ አለ፣ ምርጫ እየተደረገ ነው እየተባለም እነሆ ለ25 ዓመታት የቀጠለው የኢሕአዴግ አገዛዝ በውስጠ ተፈጥሮው ለአንድ ፓርቲ አስተዳደር የተዋቀረ በመሆኑ ነው ማለት፣ የግንቦት 20ን ዋነኛ ታላቅነት የሚቀንስ አይደለም፡፡

ደርግን መርገምት ያልነው፣ መርግ ያደረግነው፣ የወጋነውና ያስወገድነው በሐሳብ መለያየት ሞት ነው ብሎ በሞት ስለቀጣን ነው፡፡ የፖለቲካ ጠቦች፣ የዕለት ግጭቶች፣ የሕዝብ ቅሬታዎች ሁሉ በጠበንጃ ይፈቱ ስላለ ነው፡፡ ‹‹የኤርትራን ጥያቄ›› መፍታት ስላልቻለ ነው፡፡

በዕለተ ቀኑ ግንቦት 20 የ‹‹ቅኝ ገዥዋ›› ርዕሰ ከተማ ወደ ሆነችው አዲስ አበባ ከትግል አጋሩ ጋር ሰተት ብሎ የገባው ሻዕቢያ የመራውን ‹‹የኤርትራ ጥያቄ›› ዕውን ፈታ ወይ? የኤርትራ ጥያቄ እንደገና ግንቦት 1990 ዓ.ም. መልሶ አላዳገመንም ወይ? አሁንም ድረስ አለ አይደለም ወይ? በኢትዮጵያና በጣሊያን ኤምባሲ፣ በኢትዮጵያና በዚምባብዌ መካከል የተፈጠረውን ሃያ አምስት ዓመት የፈጀ አለመግባባት የሚፈታ ግንቦት 20 የለም ወይ? እነዚህ ሁሉ ለየብቻ መጠየቅና መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ 

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡