ጋብቻን ከሦስተኛ ወገን የመጠበቅ ፈተና

በዘመነ አስተርዕዮ ከተለመዱት ወጎችና ልማዶች ውስጥ መተጫጨትና ጋብቻ የተለመደ ነው፡፡ ወርሃ ጥር የሙሽሮች ወር ሲባልም እሰማለሁ፡፡ ቃና ዘገሊላን መሠረት አድርጎ በዚህ ወቅት የሚደረጉ ጋብቻዎች በፈጣሪ እንደሚባረኩ የፀና እምነት ያለ ይመስላል፡፡ በቃና ዘገሊላ ኢየሱስ ክርስቶስ በሠርግ ተገኝቶ ያለቀውን ወይን እንዳበረከተው ጋብቻው በዚህ ወራት ሲፈጸም በረከት ይኖረዋል በሚልም ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ሰሞን ከታደምኳቸው የጋብቻ ሥርዓቶች አብዛኛዎቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ኃይለ ቃልም በጥሪ ካርዳቸው ላይ መያዛቸውን አስተውያለሁ፡፡ ‹‹ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፡፡›› ‹‹እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየውም፡፡›› ከተለመዱት ጥቅሶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ጥቅሱን ደጋግሜ ሳነበው ስለደነቀኝ ለዛሬው ጽሑፍ ዋና ጭብጥ አድርጌዋለሁ፡፡

ጋብቻው ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ ጥቅሱ የተለመደ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ትርጓሜውን ለሃይማኖት አባቶች ትቼ ኃይለ ቃሉን በግርድፉ ስረዳው ከተነሳሁበት ርዕስ ጋር ተገናኘልኝ፡፡ ወንድና ሴት ጋብቻ ሲመሠርቱ ከእናትና ከአባታቸው መለየታቸው በይፋ ነው፡፡ ሰው በማግባቱና ለሚስቱ ወይም ለባሏ በማድላቷ ቤተሰቦቹን/ቤተሰቦቿን ተወ፣ ካደ አያስብልም፡፡ ከአባትና እናት በመለየት ባል ከሚስቱ ጋር ጠንካራ ጥምረትን ይመሠርታል ነው፡፡ ይህንን ጥምረት ሌሎች ሰዎች ሊያከብሩት እንደሚገባ፣ ጋብቻውን ለተጋቢዎቹ መተው እንደሚያስፈልግ ቀላል የሚመስል ግን ጠንካራ መልዕክትን የሚያስተላልፍ ነው፡፡

ከሕግ አስተምህሮ አንፃር ከተዋዋይ ወገኖች ውጭ ያሉ ሰዎች ሦስተኛ ወገኖች ይባላሉ፡፡ ከጋብቻ አንፃር ከባልና ከሚስት ውጭ ያሉት ሰዎች ሦስተኛ ወገኖች ናቸው፡፡ ልጅ፣ አባት፣ እናት፣ ወንድም፣ እህት፣ ጓደኛ፣ መንግሥት ለተጋቢዎቹ ሦስተኛ ወገኖች ናቸው፡፡ በቤተሰብ ሕጉ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ጋብቻ ለመመሥረት መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በዋናነት የሚፀና ጋብቻ ተፈጸመ የሚባለው ተጋቢዎቹ ለመጋባት ነፃና ሙሉ ፈቃዳቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ዕድሜያቸውም 18 እና ከዚያ በላይ ሞልቷቸው ከሆነ ነው፡፡ በሕጉ በተከለከሉ የሥጋና የጋብቻ ዝምድና ደረጃዎችም መጋባት የተከለከለ ነው፡፡ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች እስከተሟሉ ድረስ ሦስተኛ ወገኖች ጋብቻውን ሊቃወሙት አይችሉም፡፡ ሴቲቱ ተጠልፋ ካገባች፣ ያለዕድሜ ከተዳረች፣ የቅርብ ዘመዷን ካገባች ግን እንኳን እናት አባት መንግሥት፣ ያገባኛል የሚል ሦስተኛ ወገን ሁሉ ጋብቻው እንዳይፈጸም ሊቃወም፣ ከተፈጸመም በጽሕፈት ቤት እንዲፈርስ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩልም ካየነው ሕጉ ያስቀመጣቸው መሥፈርቶች በጋብቻ ያለአግባብ ጣልቃ የሚገቡ ሦስተኛ ወገኖችንም ተፅዕኖ የሚያስቀር ወይም የሚቀንስ ነው፡፡ ዕድሜው አካለ መጠን የደረሰ/የደረሰች በሙሉ ፈቃድ ማንን በምን መልኩ ለማግባት እንደፈለገ በነፃ ለመወሰን ስለሚችል የሦስተኛ ወገንን ተፅዕኖ ይቋቋማል የሚል ግምት አለ፡፡ እከሊትን አግባ፣ እከሌን አታግባ፣ ይህን አድርግ፣ ያንን አታድርግ.. በሚል ተፅዕኖ ለማድረግ ለሚደፍር ቤተሰብ ጆሮ የለንም ለማለት በሚያስችል ዕድሜ ማግባትን ሕጉ አስገዳጅ አድርጓል፡፡

ጋብቻ ከተመሠረተ በኋላም በባልና ሚስት ከሚጣሉ የተወሰኑ ግዴታዎች ውጭ አብዛኛዎቹ ባል ለሚስት፣ ሚስት ለባል ሊፈጽሙት የሚገባ ነው፡፡ በቤተሰብ ሕጉ ጋብቻ በተጋቢዎች ግላዊ ግንኙነት ላይ ስለሚኖረው ውጤት በሚል በአንቀጽ 49-56 የተዘረዘሩት የተጋቢዎቹ የእርስ በርስ ግዴታዎች ናቸው፡፡ ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው የመከባበር፣ የመተጋገዝ፣ የመደጋገፍ፣ በቤተሰብ አመራር በእኩል የመሳተፍ፣ አብረው የመኖር፣ በጋራ የመኖሪያ ሥፍራን የመወሰን እንዲሁም ባል ለሚስቱ፣ ሚስት ለባልዋ ታማኝ የመሆን ግዴታ አለባቸው፡፡ እነዚህ ግዴታዎች በጣም ግላዊና ባልና ሚስት ያለማንም ተፅዕኖ ሊፈጽሙዋቸው የሚገቡ ግዴታዎች ናቸው፡፡ ከንብረት አንፃርም ባልና ሚስት የጋራ ግዴታዎች ያሏቸው መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የቤተሰብ ሕጉ ከእነዚህ ዋና ግዴታዎች ውጭ የተወሰኑ ግዴታዎች ባልና ሚስት ለልጆቻቸውና ለቤተዘመዶቻቸው ጋር የተያያዙ ግዴታዎችን ይደነግጋል፡፡ ልጆቻቸውን በጋራ የማሳደግ፣ ሞግዚትና አሳዳጊ የመሆኑ፤ የሥጋና የጋብቻ ዘመዶቻቸውን በሕጉ አግባብ ቀለብ የመቁረጥ ግዴታ ለተጋቢዎቹ ጥሏል፡፡ ከእነዚህ ልዩ ሁኔታዎች ውጭ ሦስተኛ ወገኖች ከትዳሩ ጥቅም ሊያገኙ ወይም ተጋቢዎቹ ላይ ግዴታ ሊጥሉ የሚችሉበት የሕግ አግባብ የለም፡፡

ተግባሩ ግን ከሕጉ መንፈስ እጅጉን የራቀ ነው፡፡ ጋብቻ የሁለት ጥንዶች ግንኙነት ብቻ አይደለም፡፡ ሦስተኛ ወገኖች በተለይም የባልና የሚስት ዘመዶች በበጎም በክፉም ተፅዕኖ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ወቅት ለሚጋቡ ጥንዶች ትምህርት እንዲሆን ጋብቻን አሉታዊ በሆነ መልኩ ተፅዕኖ የሚያደርጉ/ጣልቃ የሚገቡትን ልምድ ለማየትና ፈተናውን ለማስቀረት የሚኖሩትን አማራጮች ለመጠቆም እንሞክራለን፡፡

 

ተግባራዊ ተሞክሮ

አሁን አሁን በአገራችን የጋብቻውን ያህል ፍቺው እየበረከተ መጥቷል፡፡ ጠበቃ አበበ አሳመረ በሙያቸው ካጋጠማቸው፣ በዕለት ተዕለት የኅብረተሰቡ ኑሮና ከተለያዩ ጽሑፎች ተረድቼው ጻፍኩት ባሉት ‹‹የባልና ሚስት አለመግባባትና የፍቺ ምክንያቶች›› መጽሐፍ ምክንያቶቹን በስፋት ይተነትናሉ፡፡ ከተነሳንበት በጋብቻ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት አንፃር ጸሐፊው ያነሱትን ለማሳያነት በአጭሩ እንቃኝ፡፡ ጠበቃ አበበ አሳመረ አምስት ዓይነት ባልና ሚስትን ለፍቺ የሚዳርጉ የቤተሰብ ተፅዕኖችን ያብራራሉ፡፡ የመጀመሪያው ለወላጅ ቤተሰብ በሚሰጥ ትኩረት የተነሳ የሚመጣ አለመግባባት ነው፡፡ ጸሐፊው በተለይ ሴቶች ለቤተሰባቸው ያላቸው ትኩረት ከትዳርም በኋላ ቀጣይነት ስለሚኖረው ከትዳሩ ጎን ለጎን ትኩረታቸውን የወላጅ ቤተሰባቸው ነገር ይስበዋል ይላሉ፡፡ ገንዘብ ከመርዳት ውጭ ለቤተሰብ በሚሰጥ ትኩረት የተነሳ የሚበጠበጥ ትዳር መኖሩን የሚገልጹት ጸሐፊው፣ ለወላጅ ቤተሰብ የሚሰጥ ትኩረት ለራስ ቤተሰብ ከሚሰጥ ትኩረት ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን ማድረግና ከትዳር አጋርም ጋር በሚገባ እየተመካከሩ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ጸሐፊው የጠቀሱት ሁለተኛው ዓይነት ተፅዕኖ የቤተሰብና የሌሎች ሰዎች ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ ጸሐፊው በመኖሪያ አካባቢ ምርጫ፣ በልጅ አወላለድ፣ በመማር ጉዳይ፣ በአኗኗር ሥርዓት ወዘተ. ከጋብቻም በኋላ በባልና ሚስት ሕይወት ጣልቃ የሚገቡ ሰዎች ለፍቺ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ካጋጠማቸው ተሞክሮ አንዱን ሲገልጹ ‹‹ከእናቱና ከአባቱ ቃል አይወጣም፤ ተራ የቤተሰባችን ጉዳይ ሳይቀር ከእነሱ ጋር ካልተመካከረ አይወሰንም፡፡ እንደ አጋጣሚ ተነጋግረን የወሰነው ነገር ካለም ቤተሰቦቹን ካማከረ በኋላ ሐሳቡን ይቀይራል፡፡ የትዳርህ ጉዳይ በራስህ ተመካክረህ የምትወስነው ጉዳይ ነው፤ በእኛ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ የራሱ ቤተሰቦች እየኖሩልን መኖር አልፈልግም፤ በቃኝ፤›› በሚል ጣልቃ ገብነቱ ለፍቺ ምክንያት ሆኗል ይላሉ፡፡ ጸሐፊው የባልና የሚስት ግንኙነት ራሱን የቻለ የግል ጉዳይ መሆኑን በማስመር ከተጋቢዎች አቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር ወይም በጋራ ተመካክረው የቤተሰብ አስተያየት እንደሚያስፈልጋቸው ካላመኑበት በቀር የቤተሰብ አስተያየት በየውሳኔዎቻቸው ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ መፍቀድም ሆነ ዕድል መስጠት እንደሌለባቸው ይመክራሉ፡፡

ሦስተኛው ለጥቅም ሲባል በቤተሰብ ወይም በሌላ ሰው የሚደረግ የፍቺ ጉትጎታና ጫና ነው፡፡ በባልና ሚስት መካከል የሚፈጠር አለመግባባት ለግል ጥቅም መጠቀሚያ ለማድረግ ሲባል በቤተሰብ አባላት፣ በጓደኛ፣ በድብቅ ፍቅረኛ ወዘተ. የሚደረግ ግፊት እንደሚያጋጥም ጠበቃ አበበ አስማረ በመጽሐፋቸው ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ያበቃኝ ‹‹እሱ ነው›› እያለች በቁጭት ስሜት ያወራችኝን ሴት ‹‹እሱ ማነው?›› ብዬ ስጠይቃት ይላሉ ጸሐፊው፣ በድብቅ የያዘችው ወንድ ጓደኛዋ እንደሆነ ነገረችኝ፡፡ ጸሐፊው በመጽሐፋቸው እንደገለጹት ይህ ሰው ከተፋታች በኋላ የምታገኘውን ንብረት እያሰበ ባሏን እንድትፈታ ከፍተኛ ግፊት ያደርግባት ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ባሏን የሆነ ቦታ ከሴት ጋር እንዳየው እያደገ በርካታ የፈጠራ ታሪኮችን እየነገራት በባሏ ላይ ልቧ እንዲሸፍት ያደርጋታል፡፡ ፍቺ ከፈጸመች በኋላ ይህ ሰው የእሷን መኪና ማሽከርከር ጀመረ፡፡ የእሷን መኪና ይዞ ከሌሎች ሴቶች ጋር ሲማግጥ በተደጋጋሚ ስላወቀች ተጣሉ፡፡ በመጨረሻም ሁለቱም ሞቱ፡፡

አራተኛው ለወላጅ ቤተሰብ በሚደረግ ድጋፍ ምክንያት አለመግባባት ተከስቶ ትዳር ሊፈታ ይችላል፡፡ ጸሐፊው በትዳር ውስጥ ገደብ የሌለው የወላጅ ቤተሰብን የመደገፍ ጉዳይ ወይም ድብቅ ድጋፍ ላለመግባባት ምክንያት እንደሚሆን እውነተኛ ውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊን ተሞክሮ በማንሳት እንደዚህ ይገልጹታል፡፡ ‹‹ቤተሰብ ለመጠየቅ አዲስ አበባ ስሄድ፣ የእኔ ዘመዶች ባለቤቴ ለቤተሰቦቿ የገዛችውን ቤት አሳዩኝ፡፡ በፍጹም መታገስ ስላልቻልኩ ደወልኩላትና ሰደብኳት፡፡ የሰጠችኝ መልስ የድካሜ ዋጋ ነው፤ የፈለከውን መሆን ትችላለህ የሚል ነበር፡፡ ከዚያም ስመለስ ጓደኛዬ ቤት አረፍኩ፤ በዚያው ተለያይተን ቀረን፡፡››

ጸሐፊው በመጨረሻ የሚገልጹት በቤተሰብ ግፊት የሚፈጸም ጋብቻን ሲሆን፣ ግፊቱ ላለመግባባት ዋና ምክንያት የሚሆነው በአብዛኛው ባልየው ሀብታም ነው፣ በጣም የተማረ ነው፣ ውጭ አገር ይወስድሻል ወዘተ. በሚሉ ምክንያቶችና ሚስት እንድታገባውና ካገባችውም በኋላ በትዳሩ ውስጥ እንድትቆይ ግፊት ሲደረግ ነው ይላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ በስፋት ሕይወታቸው  በተከሰተባቸው ሴቶች በየመጽሔቱ የምናነበው ጉዳዩ በመሆኑ ጸሐፊው ያነሷቸውን ተግባራዊ ተሞክሮ ከማንሳት ልቆጠብ፡፡ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ከዚህም የሰፋ ቢሆንም ለማሳያ ይህ በቂ ነው፡፡

ችግሩን ማን ይቅረፈው?    

በጋብቻ ላይ ያለአግባብ ጣልቃ የሚገቡ የሦስተኛ ወገኖች ጉዳዩ በዋናነት የተግባር/የአኗኗር ጉዳይ እንደመሆኑ ሊፈቱት ወይም ሊቀንሱት የሚችሉት ተጋቢዎቹና ሕግን የሚተረጉሙ አካላት ናቸው፡፡ ሕጉ ጋብቻ አካለመጠን ባደረሱና በነፃ ፈቃዳቸው ለመኖር በተስማሙ ተቃራኒ ጾታዎች እንዲመሠረት በመፍቀድ የሦስተኛ ወገንን ጣልቃ ገብነት ከልክሏል፡፡ ሦስተኛ ወገኖች ተጋቢዎቹ አውቀው ወይም ተዘናግተው ያለአግባብ ጣልቃ እንዲገቡ ካልፈቀዱላቸው በቀር ሕጉን ጠቅሰው በጋብቻ ውስጥ እጃቸውን ለማስገባት የሚችሉበት ሁኔታ የለም፡፡ ከዚህ አንፃር ሦስተኛ ወገኖች ጋብቻን እንዳያፈርሱ ዕድል መንሳት ከተጋቢዎች ይጠበቃል፡፡ ተጋቢዎቹ ከተግባቡ፣ ከተመካከሩና ከተከባበሩ ሦስተኛ ወገን ትዳር ለማፍረስ ቦታ አይኖረውም፡፡ ሁለቱም ተጋቢዎች ጠንካራ ባይሆኑ እንኳን ጠንካራ የሆነው ደካማውን ሊያግዘውና ትዳራቸውን ሊጠብቁት ይገባል፡፡ ጋብቻ ማኅበራዊ ተቋም እንደመሆኑ ምሰሶዎቹ ተጋቢዎች በብስለትና በሰከነ አዕምሮ ካልጠበቁት ሌላ አካል የተሻለ አይጠብቀውም፡፡

ጋብቻን በሦስተኛ ወገኖች ጣልቃ ገብነትና ተንኮል እንዳይፈርሰ የሚጠብቀው ሌላው አካል ፍርድ ቤት ነው፡፡ ተጋቢዎቹ ችግራቸውን መፍታት አቅቷቸው የፍች ጉዳይ ፍርድ ቤት ከደረሰ ዳኞች የጋብቻን ማኅበራዊ ተቋምነት መነሻ በማድረግ የፍቺ ጉዳዩን በጥንቃቄና በብልሃት ሊመረምሩት ይገባል፡፡ የቤተሰብ ሕጉ ፍቺን ልቅ ቢያደርገውም፣ ጋብቻን በስምምነት ለማፍረስ መብት ቢሰጥም፣ ያለበቂ ምክንያት መፍታት ቢቻልም ሕጉ ዳኞች ባልና ሚስቱን እንዲያስታርቁ፣ እንዲያሸማግሉና ከፍቺ መልስ መፍትሔ እንዲሰጡ ያስገድዳቸዋል፡፡ ጋብቻ በፍቺ ሊፈርስ የሚችለው በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 76 ይደነግጋል፡፡ እነዚህም ባልና ሚስት በስምምነት ለመፍታት ሲወስኑና ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱ በአንድነት ጋብቻቸው በፍቺ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ሲያቀርቡ ነው፡፡ በሁለቱም ዓይነት የፍቺ ጥያቄዎች ሕጉ ለዳኞች የሚሰጠው መመርያ የጋብቻን ማኅበራዊ ተቋምነት ጠብቀው ተጋቢዎቹ ከጊዜያዊ ስሜት ወጥተው እንዲስማሙ ማስቻል ነው፡፡

ጋብቻ በስምምነት እንዲፈርስ በተጠየቀ ጊዜ በአንቀጽ 78 መሠረት ዳኛው ባልና ሚስቱን በተናጠል ወይም በአንድ ላይ በማስቀረብ ስለጥያቄያቸው እንዲያነጋግር፣ እንዲሁም የመፍታት ሐሳባቸውን እንዲለውጡ የመጠየቅ ግዴታ አለበት፡፡ በተጨማሪም ሐሳባቸውን የማይለውጡ ከሆነ ከሦስት ወራት የማይበልጥ የማሰላሰያ ጊዜ በመወሰን ሊስማሙ፣ ሊያስቡበት፣ ሊመክሩበት የሚያስችላቸውን ጊዜ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ጋብቻው በፍቺ ጥያቄ ፈራሽ እንዲሆን በተጠየቀበትም ጊዜ በአንቀጽ 82 መሠረት ፍርድ ቤቱ ባልና ሚስቱን በተናጠልም ሆነ በአንድነት በማነጋገር አለመግባባቱን በስምምነት ለመፍታት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንዲችሉ ያግባባቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ ካልተሳካም ባልና ሚስቱ ከፍርድ ቤት ውጭ ራሳቸው በመረጧቸው ሽማግሌዎች አማካኝነት ጉዳያቸውን በእርቅ እንዲጨርሱ፣ ካልተሳካም የማሰላሰያ ጊዜ ሦስት ወራት ይህም ሲያበቃ አንድ ተጨማሪ ወር የራሱን ሙከራ እንዲያደርግ ሕጉ ግዴታ ይጥላል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ዳኞች ሕጉን በአግባቡ ከተገነዘቡት ባልና ሚስቱ በሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ምክንያት የተፈጠረባቸውን አለመግባባት በስምምነት ለመፍታት ጥረት የማድረግ ከባድ ግዴታ እንደሚጥልባቸው ነው፡፡ በተግባር ያለው ግን ከሕጉ ይዘትና ከሕግ አውጭው መንፈስ እጅጉን የራቀ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችን ጋብቻ ሳይመከርበት፣ ሳይሸመገልበትና ለማስማማት አዎንታዊ ተጨባጭ ጥረት ሳይደረግ በቀላሉ እንዲፈታ የሚወስኑበት አጋጣሚ በስፋት ይስተዋላል፡፡ ፍቺ ይግባኝ የማይጠየቅበት ከባድ ቁርጠኝነት የሚፈልግ ፍርድ እንደመሆኑ ከፍርድ ቤቶች የሚጠበቀው ጥንቃቄና ጋብቻውን ለማዳን የሚደረግ ጥረት ጠንካራ መሆን እንዳለበት ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በተግባር እንደሚስተዋለው ግን ፍርድ ቤቶች ጋብቻን ሳያድኑት እየቀሩ ከፍቺ በኋላ በሚደረግ የኅብረተሰቡ/የቤተሰብ ጥረት ጋብቻው የሚቀጥልበትን ሁኔታ እናስተውላለን፡፡ አንድ ባልንጀራዬ ያጫወተኝ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ባልና ሚስቱ እርስ በርሳቸው ጽኑ ፍቅር ቢኖራቸውም ሦስተኛ ወገኖች ትዳሩን ረበሹት፡፡ እንዲህ አለሽ፣ እንዲህ አደረገች በሚል ትዳሩን ማፍረስ የሙሉ ጊዜ ሥራቸው አደረጉት፤ እናም ጣልቃ ገቦቹ ተሳክቶላቸው የፍቺ ጥያቄ በፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ጉዳዩ የቀረበላት ወጣት ዳኛ ትዳሩን/ጋብቻውን ለማዳን ምንም ጥረት ሳታደርግ፣ በብርሃን ፍጥነት አፈረሰችው፡፡ የትዳሩ ውጤት የሆኑትንም ልጆች እንደ ዕቃ ለእያንዳንዳቸው አከፋፈለች፡፡ ፍርድ ቤቱ የቆረጠውን ትዳር ግን የሚቀጥል አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ከንብረት ክፍፍል ጋር በተያያዘ ንብረት አጣርተው እንዲያከፋፍሉ የተሾሙ ሽማግሌዎች ተጋቢዎቹ ከንብረት ክፍፍል መልስ ስለግንኙነታቸው እንዲመካከሩና ጋብቻቸውን እንዲጠግኑ መከሯቸው፡፡ በመካከላቸው ምንም ዓይነት የጎላ ልዩነት ያልነበራቸው ባልና ሚስት ለብቻቸው ችግሩን ተወያዩና ፈቱት፡፡ መነሻውም መድረሻውም የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት መሆኑን በማመን የጋብቻ መስኮታቸውን ለጣልቃ ገቦቹ ለመዝጋት ወስነው፤ ተስማሙ ጋብቻውም ተመለሰ፡፡ ፍርድ ቤት ያለጥንቃቄ ያፈረሰውን ጋብቻ፣ ተጋቢዎቹ ራሳቸው በሽማግሌዎቹ አነሳሽነት ወደነበረበት ሁኔታ መለሱት፡፡ ባልንጀራዬ ፍርድ ቤቶቹ በሕግ የተጣለባቸውን የጋብቻን ተቋምነት ከጊዜያዊ የተጋቢዎች የልዩነት ስሜት በላይ እንዳይጠብቁ የሚያደርጋቸውን ምክንያት ለመጠቆም ሞከረ፡፡ የዕድሜ ለጋነት፣ ስለ ጋብቻና ኃላፊነቱ የበሰለ ተግባራዊ ዕውቀት አለመኖር፣ ስልቹነት፣ ከጠበቁት ጋብቻ ይልቅ ለፈረዱት ፍቺ ስታስቲካዊ ቁጥር ብዛት መጨነቅ ወዘተ. የጥቆማው ቅቡል መሆን አለመሆን ሰፊ ጥናት የሚፈልግ ፍርድ ቤቶች ሊያስቡበት የሚገባ ነጥብ ነው፡፡

ወደተነሳንበት ነጥብ እንመለስ በጥር ወር ጋብቻ ለመመሥረት የሚያስቡ ጥንዶች ካልተገባ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ጋብቻቸውን ካልታደጉት ጋብቻ ሁልጊዜ እንደ ጥር ወቅት ላይሆን ይችላል፡፡ ችግሩ የሚቀረፈው በማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት ምክር ቢሆንም፣ ተጋቢዎቹ ከብስለት ጋር ጠንቃቃና ጠንካራ ከሆኑ ለጣልቃ ገብ ቦታ አይኖቸውም፡፡ ችግሩ ከፍቶ ፍርድ ቤት ከደረሰም ዳኞች በሰከነ አዕምሮ ጋብቻውን ለመታደግ ጥረት ማድረግ ሕጋዊም ሞራላዊም ግዴታ አለባቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች የቀረበላቸውን ፍቺ ሁሉ የሚያፀድቁ ከሆነ ግን ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገቦች ሃይባይ አያገኙም፡፡ ‹‹ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፡፡›› የሚለውም ዘላለማዊ ቃል የጣልቃ ገቦችን ጆሮ ያወፍራል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getukow [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡