ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት

አዲሱ የብአዴን የትምክህተኝነትና የጠባብነት መታገያ

 
ስንቶች ተኮላሽተው ከአረንቋው ዘቀጡ

ስንቶች ተቸንፈው ከጎዳናው ወጡ

ጥቂቶች ቆራጦች ያልተንበረከክነው

ነገ እልፍ እንሆናለን ታሪክ ምስክር ነው

የፋሽስቶች እብሪት ድንፋታው ሳይገታን

የከሳሾች ሴራ አፈናው ሳይረታን

ግራ አድርባይ መስመር ሳያንበረክከን

ጨለምተኛ እምነቶች ከቶም ሳይበግሩን

ንፁህ ደማችን ፈለግ ብርሃን ሆኖን

ብሩህ አዲስ ዓለም በትግል እናያለን

የከፋ የከረፋ መአት ይውረድብን

ልክ የለሽ መከራ እንቅፋት ይግጠመን

የፋሽስቶች ነዲድ ነበልባሉ ይግረፈን

በትግል በእምቢታ በአመጽ እንጠራለን

በንፁህ ደማችን ችቦ እናበራለን፡፡

ይህ ‘ያልተንበረከክነው’ የሚል ርዕስ ያለው ግጥም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ታጋዮችንና ደጋፊዎችን ለማበረታታት ቁልፍ ሚና እንደተጫወተ የፓርቲው ታሪክ ይጠቁማል፡፡ በአቶ ህላዊ ዮሴፍ ተጽፎ ከመሰከረም 19 ቀን 1975 ዓ.ም. ጀምሮ የኢሕዴን/ብአዴን መዝሙር ሆኖ እስካሁንም ያገለግላል፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በትግል ሥልትና በአመለካከት ልዩነት የተነጠሉ ታጋዮች በ1973 ዓ.ም. የመሠረቱት ኢሕዴን፣ በደርግ ላይ ከሌሎች ትግል ላይ ከነበሩ ኃይሎች ጋር በመተባበር ድል ከተቀዳጀ በኋላ በ1986 ዓ.ም. ከኅብረ ብሔራዊ ድርጅት ወደ ብሔራዊ ድርጅት በመሸጋገር ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ወደመሆን አመራ፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዋና መቀመጫ ባህር ዳር ከኅዳር 7 ቀን እስከ ኅዳር 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ የኢሕዴን/ብአዴን 35ኛ ዓመት ልደት ተከብሯል፡፡ የበዓሉ አካል ከሆኑት በርካታ እንቅስቃሴዎች አንዱ ‘ያልተንበረከክነው’ ግጥምን የያዘና የኢሕዴን መሥራች ታጋዮችን ምሥል የያዘ ቢል ቦርድ በከተማው እንብርት ላይ እንዲቆም ማድረግ ነው፡፡ በበዓሉ የውይይት መድረኮች፣ የጥበብ ዝግጅቶች፣ የሥዕል ኤግዚቢሽንና የተለያዩ የቪዲዮ ምሥሎችን የሚያሳዩ ትዕይንቶች ተካተው ነበር፡፡

ኅዳር 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ጠዋት ላይ የሙሉ ዓለም የኪነ ጥበብ ማዕከል አርቲስቶች የብአዴንን ታሪክ በሙዚቃዊ ድራማ አቅርበዋል፡፡ በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ የቀረበው ቴአትር ታዳሚውን አዝናንቷል፡፡ ቴአትሩ በዋነኛነት የያዘው ጭብጥ የአማራ ሕዝቦች እንደ ሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁሉ ያለፉ ሥርዓቶች ሰለባ እንደነበሩ፣ ብአዴን በትጥቅ ትግሉ ጊዜም ሆነ ከድል በኋላ የአማራ ሕዝቦች ድጋፍ እንዳልተለየው፣ ብአዴን ከ1983 ዓ.ም. በኋላ በክልሉ በርካታ ለውጦችን ቢያመጣም የሚቀረው ሥራ የበለጠ እንደሆነ፣ የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሳያንስና ሳይበልጥ በእኩልነትና በመፈቃቀድ እስከኖረ ድረስ ብቻ፣ የኢትዮጵያን ሰላምና ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚቻል ያካትታል፡፡

በተመሳሳይ ቀን ከሰዓት በኋላ በሙሉ ዓለም አዳራሽ የቀድሞ የኢሕዴን ታጋዮች ከአሁኑ የብአዴን አመራሮች ጋር በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉም ፕሮግራም ተይዞ ነበር፡፡ ለውይይቱ መነሻ እንዲሆን አቶ ጌታቸው ጀንበሬ የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን አፈጻጸምና የሁለተኛውን ዕቅድ አቅርበው ነበር፡፡ የቀድሞ ታጋዮች አቶ ጌታቸው ማብራሪያቸውን በሚያቀርቡበት ሰዓትም ሆነ ሌሎች ባለሥልጣናት ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ በጥሞና ከመስማት ይልቅ፣ አብዛኛዎቹ ከዚህ ቀደም የተገናኙት ብአዴን 30ኛ ዓመቱን ባከበረበት ወቅት ስለነበር ናፍቆታቸውን ለመወጣት መረጃ በመለዋወጥ ላይ ነበሩ፡፡ ውይይቱም ሲጀመር አልፎ አልፎ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያሉትን ጨምሮ የመልካም አስተዳደር ዕጦት በክልሉ መስፈኑን ያመላከቱ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ጊዜ የታጋዮቹ የተለያዩ መብቶች ጡረታን ጨምሮ እንዳልተከበሩና ከባድ መስዋዕትነት ከፍለው ያለፉ ታጋዮች ቤተሰቦችም ችግር ላይ እንደሆኑ በመዘርዘር ነው የጨረሱት፡፡

ከቀድሞ ታጋዮች አንዱ የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ዮሴፍ ረታ የቀድሞ የኢሕዴን/ብአዴን ታጋዮች ማኅበር ተመሥርቶ ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘ በመሆኑ፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል፡፡ የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንንና የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ማኅበሩን፣ ታጋዮቹንና ቤተሰባቸውን ለማገዝ ቃል ገብተዋል፡፡ በተመሳሳይ መድረክ ‘የኢሕዴን/ብአዴን ታሪክ 1973 - 2008’ በሚል ርዕስ በብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀ መጽሐፍም ተመርቋል፡፡

የበዓሉ አከባበርና ድርቁ

ኢሕዴን/ብአዴን 35ኛ ዓመቱን ያከበረበት ወቅት አማራ ክልልን ጨምሮ አገሪቱ በድርቅ እየተሰቃየች በመሆኑ በፓርቲው ላይ የተለያዩ ትችቶች ተሰንዝረዋል፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ድርጊቱን አፄ ኃይለ ሥላሴና ደርግ በ1966 እና በ1977 ዓ.ም. ድርቅ ጊዜ ካሳዩት ግዴለሽነት ጋር ሁሉ አነፃፅረውታል፡፡

በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች 30 ሚሊዮን ብር የለገሰው ብአዴን በበዓል አከባበሩ ወቅት ስለድርቁ ችግሮች በግልጽ ሽፋን መስጠቱ፣ በእርግጥም ድርቅ ስለመከሰቱ ጭምር ከካዱት የቀደሙት ገዥዎች ለየት ያደርገዋል የሚሉ አሉ፡፡ ብአዴን በዓሉን ለማክበር ምን ያህል እንዳወጣ ከመግለጽ ቢቆጠብም፣ አብዛኛዎቹ የበዓሉ እንቅስቃሴዎች በፌሽታና በጭፈራ ሳይሆን በአዳራሽ ውስጥ በሚያልቁ ውይይቶች በመሆኑ ብዙ ገንዘብ እንዳልወጣ ግን አስታውቋል፡፡

የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኮንን ብአዴን የ35ኛ ዓመት በዓሉን በድምቀት ለማክበር ሦስት ምክንያቶች እንዳነሳሱት አመልክተዋል፡፡ አንደኛ የሕዝቡን የመስዋዕትነትና አኩሪ የትግል ታሪክ ለማስታወስና ለማሰብ፣ ሁለተኛ የትግሉ ታሪክና እሴቶችን የልማት ኃይሎች በተለይ ወጣቱ ትውልድ እንዲያውቋቸውና አሟልተው እንዲይዟቸው በማሰብ፣ ሦስተኛ ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ሁሉም የልማት ኃይሎች ግንዛቤ፣ ግልጽነትና ተነሳሽነትን ሰንቀው ወደላቀ ተግባር እንዲሰማሩ ለማበረታታት ተልዕኮ ይዞ መከበሩን አብራርተዋል፡፡

አቶ ዓለምነው በዓሉ በድግስና በፈንጠዝያ ሳይሆን ትምህርታዊ ተሞክሮ ለመቅሰምና ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁነትን የመሰነቅ ዓላማና ግቦች አስቀምጦ ተግባራዊ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹የአየር ለውጥ መዛባትን ተከትሎ የተከሰተውን የድርቅ አደጋ በቀጣይነት መመከት የሚያስችል የአረንጓዴ ልማት የሚያግዙ በኅዳር 11 ስም የተሰየሙ በ1,170 ቀበሌዎች የደን ልማት ማዕከሎች እንዲከለሉና እንዲለሙ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል፤›› ብለዋል፡፡

የብአዴን ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፣ ብአዴን ውጤታማ ሊሆን የቻለው ትናንትም ሆነ ዛሬ የጠራ የፖለቲካ መስመር በመያዝ፣ ከሕዝብ በመወገኑና በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በመመራት ሕዝቡን አሠልፎ በመዝለቁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ድርቁን በተመለከተም ብአዴን በአንድ በኩል ከዚህ ቀደም የተጀመረውን ውኃን ማዕከል ያደረገ የተፈጥሮ ሀብት ልማት በማጠናከር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለድርቅ የተጋለጡ ወገኖችና የእንስሳት ሀብቶቻቸው ለጉዳት እንዳይጋለጡ በመከላከል፣ ችግሩን ለመፍታት ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ባለፉት የልማት ዓመታት በገነባነው አገራዊ የመቋቋም ብቃት በመታገዝ የዚህ ችግር የአጭር ጊዜም ሆነ የዘላቂ አሉታዊ ተፅዕኖ ትንሽ እንዲሆን ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡ ድርቁ በሕዝባችን ላይ ጉልህ ጉዳት በተለይም ደግሞ ሰብዓዊ መቅሰፍትና ረሃብ በማያስከትል መንገድ እንደምንፈታው ደግሞ እምነታችን የፀና ነው፤›› በማለት በዓሉ የድርቅ ችግሩን የዘነጋ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡

የበዓሉ የክብር እንግዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም በተመሳሳይ በድርቁ ተጎጂ የሆኑ ዜጎችን ለመታደግ፣ በእስካሁኑ የልማት ስኬት አማካይነት ችግሩን በራሱ ለመቋቋም መንግሥት አስፈላጊውን ርብርብ እያደረገ እንደሆነና ይህንን ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት

ከብአዴን 35ኛ ዓመት በዓል እንቅስቃሴዎች መካከል በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ላይ ኅዳር 10 ቀን በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ የተደረገው የፓናል ውይይት አንዱ ነው፡፡ ውይይቱ በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ በረከት ስምኦንና በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ህላዌ ዮሴፍ የተመራ ሲሆን፣ ባልተለመደ ሁኔታ ንቁ ተሳትፎ የተደረገበትና ለፓናሊስቶቹ ሞጋች የሆኑ ጥያቄዎች ከመድረክ የቀረቡበትም ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ብሩክ ከበደ ከሬዲዮ ፋና እንዲሁም ጋዜጠኛ ሰጠኝ እንግዳው ከአማራ መገናኛ ብዙኃን በተለያዩ መድረኮች በአማራ ብሔርተኝነት ላይ የተነሱ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

ከብአዴን 35ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ጎልቶ የወጣው የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ምንነት ላይ ማብራሪያ የሰጡት አቶ በረከት ስምኦን ናቸው፡፡ ‹‹በልዩ ልዩ ማኅረሰቦቻችን መካከል ያለው ግንኙነት የሚገዛበት ዴሞክራሲያዊ የአሠራር መርህ ነው፤›› በማለት የፅንሰ ሐሳቡን ማዕከላዊ ጭብጥ የገለጹት አቶ በረከት፣ ይህን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ ኢትዮጵያዊነትንና ብሔራዊ ማንነትን ማክበርና የሁሉንም ሕዝቦች የመሥራትና የመልማት መብትን በፍትሐዊነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም  አመልክተዋል፡፡

ብዙ ሕዝቦች ባሉበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትን በጤናማ አስተሳሰብ በመምራት በመካከላቸው ፍቅር፣ መከባበርና መተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡ ግንኙነቱ ጤናማ ባልሆነ አስተሳሰብ በሚመራበት ጊዜ ግጭት መከሰቱ እንደማይቀር ያመለከቱት አቶ በረከት፣ በኢትዮጵያ የተማከለ አስተዳደር ከተመሠረተበት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ በማኅበረሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የተመላበት፣ ግጭት የጠነከረበት፣ በዚህም ምክንያት አገሪቱ ሰላም ያጣችበት እንደነበር ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

አሠራሩ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስላለው ፋይዳም ሲያብራሩ፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በክልሉ ያሉትን የትምክህተኝነትና የጠባብነት ችግር ለመዋጋት ቁልፍ መሣሪያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ብአዴን አማራ የሚባል ብሔር የለም የሚሉ ኃይሎችን ሞግቷል፡፡ ብአዴን አማራ የሚባል የራሱ ቋንቋና ታሪክ ያለው ትልቅ ሕዝብ አለ ብሎ ተቀብሏል፡፡ አማራ ለዘመናት ልማት ተነፍጎት የቆየ ሕዝብ ነው፡፡ ክልሉ በብአዴን መልማት ጀምሯል፡፡ አማራዎች በመረጡት ቦታ ሠርተው የመኖር መብታቸውን የማስከበር ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በእኩልነትና በመከባበር እንዲኖሩ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ከሌሎች ብሔሮች ጋር ያለው ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆን ተጥሯል፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ የአገው፣ የእምራ፣ የኦሮሚያ፣ የቅማንትና የአርጎባ ማኅበረሰቦች አሉ፡፡ እነዚህ ማኅበረሰቦች ከአማራው የማይተናነስ፣ ከአማራው የማይበልጥ መብት ያላቸው መሆኑን ተቀብሎ ለማስተናገድ ጥረት ተደርጓል፤›› ሲሉም በክልሉ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ለማስፈን የተሠሩትን ተግባራት ጠቃቅሰዋል፡፡

‘የብአዴን ጉዞ ቁልቁለት ነው ከፍታ?’

ብአዴን ከኅብረ ብሔራዊው ኢሕዴን መምጣቱ ዝቅ አያደርገውም ወይ በሚል የቀረበው ጥያቄ የመወያያ ርዕስ ነበር፡፡ አቶ በረከትም ሆኑ አቶ ህላዌ ሽግግሩ ከፍታ እንጂ ቁልቁለት እንደልሆነ አፅንኦት ሰጥተው አስረድተዋል፡፡ በተለይ አቶ በረከት ብአዴን የተነሳበት የኅብረ ብሔራዊ አጀንዳ መልኩን ቀየረ እንጂ ውድቅ እንዳልተደረገ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ኢሕዴን ወደ ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን ወደተለየ ኅብረ ብሔራዊ ድርጅትነትም ነው የተቀየረው፡፡ ሁለት ዓይነት ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀቶች አሉ፡፡ አንደኛው ኢሕዴን ከ1973 ዓ.ም. እስከ 1986 ዓ.ም. ወይም ኢሕአፓ ከ1967 ዓ.ም. እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ የነበራቸው አደረጃጀት ነው፡፡ ይኼ ከተለያዩ ብሔሮች ግለሰቦችን እየመለመሉ አባል በማድረግ የሚገለጽ ነው፡፡ ሁለተኛው የአደረጃጀት መልክ አሁን ኢሕአዴግ የሚከተለው ዓይነት ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ነው፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ይሁንና የማታ ማታ ኢሕዴን ወደ ብአዴን እንዲቀየር ሁለት ምክንያቶች እንዳስገደዱት አቶ በረከት ገልጸዋል፡፡ አንደኛው ምክንያት ብዙዎቹ በኢሕዴን ውስጥ የነበሩ ታጋዮች ብሔራዊ ድርጅት ለማቋቋም የሚያስችል የብቃት ደረጃ ላይ ደርሰው መልቀቃቸው ነው፡፡ ‹‹ይኼ ለብአዴንም ሆነ ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕድገት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሁሉም ሕዝቦች መብት የተከበረባት አገር መሆኗ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የአማራ ሕዝብም መብቱ ተከብሮ ለልማት፣ ለዴሞክራሲና ለሰላም መብቃት ስላለበት ኢሕዴን ወደ ብአዴን ተሸጋግሯል፤›› ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ህላዌ በበኩላቸው፣ ‹‹ፖለቲከኞች ነንና የወቅቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ ነባራዊ ሁኔታ በሚያዘው የትግል ሥልትና የአደረጃጀት ቅርፅ ውስጥ ነው የገባነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

‘አማራውስ በሌላው ብሔር ይከበራል?’

ብአዴንና የአማራ ሕዝብ ሌሎች ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እንዲያከብሩ እየሠራ ያለው ሥራ ጠቃሚ ቢሆንም፣ ሌሎችስ ብአዴንንና የአማራ ሕዝብን እንዲያከብሩት ምን እየተሠራ ነው? የሚል ጥያቄም ከመድረክ ተወርውሮ ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ ምናልባትም ብአዴን 35ኛ ዓመቱን ማክበር ከጀመረ ጀምሮ በአንዳንድ ወገኖች የብአዴን ታሪክና የአማራ ሕዝብ ታሪክ ላይ የማጥላላት ዘመቻ በመከፈቱ የተነሳ ይመስላል፡፡ ለአብነትም ያህል ኢሕዴን/ብአዴን ደርግን ለመደምሰስ በተደረገው የትጥቅ ትግል ያደረገው አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም የሚል አስተያየት በማኅበራዊ ሚዲያ መስተጋባቱን ልብ ይሏል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ ቁልፍ መሣሪያ በመሆኑ ከአንድ ብሔር ጋር የተያያዘ ሳይሆን የገዥው ፓርቲም አመለካከት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ በረከት፣ አመለካከቱን የማለምለም ሥራ የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ኃላፊነት ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ከክልል ክልል የተለያየ የሚያደርገው ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚኖር ግን ገልጸዋል፡፡

ትምክህተኝነትና ጠባብነት ከአማራ ብሔር ጋር ብቻ የተያያዘ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም ይኼ የአመለካከት ችግር በሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም በተለያየ ገጽታ የሚገለጽ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ሌሎቹ የራሳቸውን ልዩ ሁኔታ በየደረጃው የሚገልጹት ቢሆንም፣ በአማራ ክልል ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ማረጋገጥ ፋይዳው ለሌሎችም እንደሚተርፍ አብራርተዋል፡፡ ‹‹የአማራ ብሔር በብሔር ላይ ሁለት ዓይነት አመለካከት አለው፡፡ የአማራ አርሶ አደር ብሔርተኝነት የራሱን መሬት ማልማት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ የሌለውን መሬት የመጥለፍ ፍላጎት የለውም፡፡ የተወሰነው በፊት ገዥ የነበረው አማራ ደግሞ ወደሌላ አካባቢ ሄዶ መሬት መውሰድና መውረር ይፈልጋል፡፡ ኢሕዴን/ብአዴን የቆመው ለአርሶ አደሩ ብሔርተኝነት ነው፤ › ብለዋል፡፡

ትምክህተኝነትም ሆነ ጠባብነት የኪራይ ሰብሳቢነት በሽታ መደበቂያዎች ናቸው ያሉት አቶ በረከት፣ ይህንን ለማዳከም ባለፉት 25 ዓመታት በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም እነዚህ የአመለካከት ችግሮች ስለማንሰራታቸው ምልክቶች እየታዩ ስለመሆኑ ግን አምነዋል፡፡ ‹‹የትምክህት ሐሳባችንን በነፃነት እንግለጽ፣ አትንኩን የማለት ነገር ይታያል፡፡ ይኼንን አመለካከት መጠጊያ የሚያደርጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ አስተሳሰባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ብአዴን የተለየና የተሳሳተ ሐሳብ ያላቸውም ሰዎች ቢሆኑ ሐሳባቸውን ለምን ይገልጻሉ የሚል ብዥታ ኖሯቸው አያውቅም፡፡ ነገር ግን በተገለጸበት ቦታ ይኼንን አመለካከት መታገልና ማስተካከል ደግሞ ግዴታቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎችና አጋር ፓርቲዎች ተወካዮች ለአቶ በረከት አስተያየት ድጋፍ በመስጠት ተመሳሳይ አመለካከት በየብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቡ እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህም አንዱ የሕወሓት ነባር ታጋይና የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ለሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነገር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ለአማራው ሕዝብ የሚቆረቆር የሌላ ደም ሕዝብም አለ፤›› በማለት እኩልነት ተቀብሎ መንቀሳቀስ መከበርን እንደሚያጎናፅፍ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ያለፈው ታሪክ አንድን ሕዝብ የራሱ ዘር ከሌላው ዘር በከፋ መልኩ ሊበድለው እንደሚችል የአማራን ሕዝብ ለአብነት በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በስመ አማራ ገዥዎች የአማራን ሕዝብ አጎሳቁለዋል፡፡ የትምክህት ኃይሎችና የጠባቦች አመለካከት የአማራ ሕዝቦችን አራቁቷል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሚመራው ብአዴን ነው ክልሉን እያለማ ያለው፡፡ አሁን አንድ ብሔር የበላይ የሆነበት ሁኔታ የለም፡፡ የሚፈልግ አካል ቢኖርም ሊሳካለት አይችልም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት ቁልፍ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‘ብአዴን የአማራ ሕዝቦች ስቃይ ይሰማዋል ወይ?’

ሌላው ለውይይት በር የከፈተው ጥያቄ ከክልላቸው ውጭ እየኖሩ ላሉና አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ በደል ለሚደርስባቸው የአማራ ተወላጆች ችግር ብአዴን የሚሰጠው ምላሽ ላይና በክልሉ ስላመጣው ለውጥ የቀረበው ነው፡፡

አቶ በረከት ብአዴን ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን መብት ከማስከበር አኳያ ብአዴን በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን አመልክተዋል፡፡ በተለያዩ ክልሎች ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ አማሮች እንደሚኖሩ ያስታወሱት አቶ በረከት፣ በአብዛኛው ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ተስማምተው ቢኖሩም አልፎ አልፎ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹ዋናው ገጽታ ይኼ ነው፡፡ ችግሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የችግሩ መንስዔ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ሳይጎዱ አማሮች አይጎዱም፡፡ የኢትዮጵያ ዋና መገለጫ ብዝኃነትን በአግባቡ የምታስተናግድ አገር መሆኗ ነው፡፡ የአፈጻጸም ችግርን ከመርህ ነጥለን ማየት አለብን፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ህላዌ በበኩላቸው ብአዴን ለአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ አይደለም በማለት የቀረበው ጥያቄ ከእውነታው ተቃራኒ መሆኑን ሲያስረዱ በጣም ስሜታዊ ሆነው ነበር፡፡ ‹‹በክልሉ የመጣውን ለውጥ እኮ በዓይናችን የምናየው ነው፡፡ ድህነትንና ኋላቀርነትን እያስወገደ ያለው ማነው? የቀድሞ ገዥዎች የትኛውን አካባቢ አለሙ? ለየትኛው አካባቢ የጤና አገልግሎት ሰጡ? መንገድ ሠሩ? እኛ ነን ክልሉን ያለማነው፡፡ ከ300 የማይበልጡ ትምህርት ቤቶችን 8,000 ያደረሰው ብአዴን ነው፡፡ ከዚህ በላይ መጥቀም አለ? ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ ቀበሌዎችን በመንገድ ያገናኘው ማነው? ሰማይን ተጠግተው የተፈጠሩትን የአማራ ክልል ወረዳዎች እነ ጃን አሞራንና መንዝን በመንገድ ያስተሳሰረው ማነው? የቀረ ነገር የለም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በብአዴን እምነት ማንነቱን አውቆ አካባቢውን እንዲያለማ ማድረግ መጥቀም ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

‘ኢትዮጵያዊነት በጎጠኝነት ተተክቷል!’

ሌላኛው አንኳር ጥያቄ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ጎጠኝነት ኢትዮጵያዊነትን ተክቶታል በሚል የቀረበው ነው፡፡

አቶ በረከት ኢትዮጵያዊነትና ብሔርተኝነት እርስ በርስ የሚቃረኑ ሳይሆኑ የሚደጋገፉ ናቸው ብለዋል፡፡ ‹‹ጎጠኝነትና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ግን የማይገናኙ ፍጥረቶች ናቸው፤›› በማለት ጎጠኝነት በሰዎች መካከል ልዩነት ሲፈጥር፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ጎጠኝነት እንዳይፈጠር የሚከላከል እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ከማንነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነት ላይ ማተኮር አይሻልም ወይ በማለት የሚቀርበው ጥያቄም፣ ሁለቱ የማይተካኩና የማይነጣጠሉ ጉዳዮች መሆናቸውን ካለመገንዘብ የሚመጣ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነት እንዲለመልም የብሔሮች ማንነት መስዋዕት መሆን የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ መሠረት ብሔር ብሔረሰቦቹ ናቸው፡፡ እነሱ ሲነኩ ኢትዮጵያም መነካቷ አይቀርም፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያዊነት እየደከመ ሄዷል የሚባለው ነገር ከሀቅ የተጣላ ድምዳሜ ነው፡፡ እንኳን አሁን ከዳር እስከ ዳር ለምታ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ገና ልማት ሳይመጣ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከፍተኛ ነበር፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎለብት እንጂ የሚያዳክም አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ሕዝቡን እያዋሀደ ያለው በልማትና በዴሞክራሲ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኅዳር 11 ቀን 1973 ዓ.ም. በ37 መሥራች ታጋዮች የመጀመሪያ ጉባዔውን አድርጎ በይፋ የተመሠረተው ኢሕዴን በሰቆጣ ልዩ ስሙ ሚሲግ ሚካኤል በተባለ ቦታ ላይ የትጥቅ ትግልን በይፋ የጀመረ ሲሆን፣ በ1981 ዓ.ም. ኢሕአዴግን ከሕወሓት ጋር ሲፈጥሩ 30,000 ወታደሮች ነበሩት፡፡ ኦሕዴድና ዴኢሕዴን ቆየት ብለው ግንባሩን የተቀላቀሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ድርጅት መሥራቾች መካከል የቀድሞ የኢሕዴን ታጋዮች ይገኙበታል፡፡  

በክብረ በዓሉ መጨረሻ ላይ ለተሰው ታጋዮችና ከፍተኛ ግልጋሎት ለሰጡ እንደ አቶ በረከት ስምኦን ላሉ ታጋዮች ሽልማት ተበርክቷል፡፡