ደህናውን መንገድ ቆፋፍሮ በጀት የለም ምንኛው ጉራማይሌ ነው?

ከሜክሲኮ አደባባይ በአረቄ ፋብሪካ በኩል አድርጎ ወደ ሆቴል ዲ አፍሪካና ወደ ጎማ ቁጠባ አቅጣጫ የሚያወጣውን መንገድ ለጥገና በሚል ሰበብ መንግሥት ከቆፋፈረው ሳምንታት አስቆጥሯል፡፡

መንገዱን ደህና አድርገው ከገማመሱና ቆፋፍረው ከአስፓልትነት ወደ ኮረኮንችነት ከቀየሩት በኋላ መለስ ለወስ ብለው የሚያዩት ማሽኖች አልታይ ብለዋል፡፡ ደህነኛው መንገድ እንዲያ በዲንጋይ ቁልል ተለውጦ በመቅረቱ መኪናም እግረኛም ማለፍ ተቸግረዋል፡፡

ከዛሬ ነገ በአፋጣኝ መንግዱ ተጠግኖ አልቆ የወትሮው ሰላማዊ ኑሮ ይቀጥላል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ያልታሰበው ሆነና እንዳገጠጠ እንዲቀር ተፈረደበት፡፡ እርግጥ መንገዱ በአፋጣኝ መሠራት እንደሚችል የሚያሰግድድበት ሁኔታ እንዳለ ከመንገዱ ጸባይ ብንገነዘብም፣ በጀት የለም ተብሎ በአስቸኳይ የተቆፈረው መንገድ በአስቸኳይ እንዲቆም ተደርጓልና ይህ የሆነበት ትክክለኛው ምክንያት ተገምግሞና ተጣርቶ መፍትሔ እንዲሰጠው የሚመለከተውን አካል ለማመላከት እሻለሁ፡፡

በጀት የለም የሚለው ምላሽ የማይመስል ለመሆኑ ማሳያው በጀት ከሌለ ቀድሞውኑ ማን በሌለ በጀት ጀምሩ እንዳላቸው ምላሽ ቢሰጡበት መልካም ነው፡፡ ሁለተኛስ በመንገዱ መዘጋት ምክንትያት ያውም መሐል ከተማ የሚገኝን መንገድ እንዲያ አጎሳቁሎና ቆፋፍሮ መተው አደጋውንስ አያባብስም ወይ?

መንገድ አሠሪው አካል በግብታዊነት የጀመረው ሥራ ከሆነም መንግሥትን ትዝብት ላይ የሚጥለው ነውና ነገሮች መስመር ስተው፣ በጥቂት ወጪ መሠራት፣ መጠገን የሚችለው መንገድ ተባብሶ ብዙ ወጪና ኪሳራ ከማስከተሉ በፊት የዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ መወትወት ተገቢ ሆኖ ስላገኘሁት ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ አስገድዶኛል፡፡

(አስማማው ኃይሌ፣ ከአዲስ አበባ)