የ16 ቀናት ፀረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ

በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ከኖቬምበር 25 እስከ ዲሴምበር 30 የፀረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ ለ16 ቀናት ይከበራል፡፡ የዘንድሮውም በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በማስወገድ ረገድ ወንዶች የራሳቸው ሚና እንዳላቸው የሚያዘክረው ይሄው ዘመቻ፣ በመላው ዓለም ለ25 ጊዜ በአገራችን ድግሞ ለ10ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡ በዘመቻው እንዳንዱ ቀናት የራሳቸው የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶላቸው የሚከበሩ ሲሆን፣ በእነዚህ ቀናት ወንዶች የፀረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ አጋር እንደሆኑ ለማሳየት ነጭ ሪባን ያስራሉ፣ ሴቶቹ ደግሞ ብርቱካናማ ቀለም ያለው ሪባን ያስራሉ፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ጾታ የማይለይ ሁሉንም የሚመለከት ማኅበራዊ ችግር መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ እነዚህ ሳምንታት ለምን የፀረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ ጊዜያት በመሆን ተመረጡ? ለዘመቻው መነሻ የሆነው ክስተት ምንድን ነው? መቼና በማን ተፈጠረ? የሚሉትን ነጥቦች በመዳሰስ በዚህ ጽሑፍ ታሪኩን መነሻ ያደረገ ምልከታ ለማድረግ ይሞከራል፡፡

መነሻ ታሪክ

በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ይቁም የሚለው ዘመቻ መነሻ የተፈጸመው እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 6 ቀን 1989 በአገረ ካናዳ በሞንትሪያል ኩቤክ ከተማ በኢኮል ፓሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ በተፈጸመ ግድያ ነው፡፡ ማርክ ሊፓይን የተባለ የ25 ዓመት ወጣት በዕለቱ 11 ሰዓት አካባቢ የሞንቲሪያል ዩኒቨርሲቲ አካል ወደሆነው የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ይገባል፡፡ ኮሌጁን በሚገባ የሚያውቀው ሊፓይን ወደ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ያመራል፡፡ 50 ተማሪዎች ካሉበት በሁለተኛው ፎቅ ከሚገኘው አንዱ ክፍል ይገባና ሁሉም እንዲያዳምጡት ይጠይቃቸዋል፡፡ ተማሪዎቹም ንግግሩ የቀልድ መስሏቸው ቸል ሲሉት በቦርሳው የያዛትን ሽጉጥ በማውጣት ወደ ጣራው ይተኩሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም ተደናግጠው ለመሸሽ ሲሞክሩ ከተማሪዎቹ ውስጥ ወንዶቹና ሴቶቹ ተለይተው እንዲቆሙ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ከ50 ተማሪዎች ውስጥ ሴቶች ባንድ ጥግ ቀሪዎቹ ወንዶች ደግሞ በሌላው ጥግ ይቆማሉ፡፡ ሊፓይን ወንዶቹ ከክፍሉ እንዲወጡ ካዘዘ በኋላ ‹‹እዚህ ክፍል ለምን ሽጉጥ ይዤ እንዳመጣሁ የሚነግረኝ አለ?›› በሚል ይጠይቃቸዋል፡፡ ከሴቶቹ ተማሪዎች አንዷ ‹‹አናውቅም›› ስትል መልስ ትሰጣለች፡፡ እሱም ‹‹I am fighting feminism›› ሴቶች የወንዶቹን ያህል መብት ይኑራቸው የሚለውን ሐሳብ ለመታገል ነው፤›› ሲል ያምባርቅባቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተማሪዎቹ አንዷ ‹‹ተመልከተን! እኛ የምሕንድስና ተማሪዎች ነን፡፡ መደበኛ ሕይወት ለመኖር የምናስብ እንጂ ሴቶች ከወንዶች የተለየ መብት ያግኙ ብለን ለመጮህ የተዘጋጀን ፌሚኒስት አይደለንም፤›› በማለት በማስተዛዘን ትመልስለታለች፡፡ ማርክ ሊፓይንም ‹‹እናንተ ሁላችሁም ሴቶች ናችሁ፡፡ ነገ መሐንዲስ ትሆናላችሁ፡፡ በወንዶችም ላይ ጣታችሁን ትቀስራላችሁ፡፡ እኔ ፌሚኒስትን እጠላለሁ፤›› በማለት ከግራ ወደ ቀኝ በመደዳው ተማሪዎች ላይ ይተኩሳል፡፡ ስድስቱን ይገድላል፤ ሦስቱን ያቆስላል፡፡ ከዚያም በኮሪደሩ ላይ፣ ወደ ሌላ ክፍል፣ አንደኛ ፎቅ ወደሚገኘው የኮሌጅ ካፍቴሪያ፣ ወደ ሦስተኛ ፎቅ እየተዘዋወረና እየተኮሰ ሰውን መጉዳት ተያያዘው፡፡ ከ20 ደቂቃ የተኩስ ቆይታ በኋላ ሊፓይን ጭንቅላቱ ላይ ተኩሶ ራሱን አጠፋ፡፡ በዚህች አጭር ደቂቃ 14 ሴቶችን (12 የምሕንድስና ተማሪዎችን፣ አንድ የነርሲንግ ተማሪና አንድ የዩኒቨርሲቲውን ሴት ሠራተኛ) ገደለ፡፡ አራት ወንዶችን ጨምሮ ሌሎች አሥራ አራት ሰዎችን አቆሰለ፡፡ በወቅቱ ለሪፖርተሮች ስለጭፍጨፋው መግለጫ ይሰጥ የነበረው የሞንትሪያል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ሕንፃው ውስጥ እንደገባ የራሱ ልጅ ተገድላ ማየቱ ተዘግቧል፡፡ የኩቤክ እና ሞንትሪያል መንግሥታት የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ያወጁ ሲሆን፣ በአንድ ክፍል ውስጥ የተገደሉት ዘጠኝ ተማሪዎች በኅብረት እንዲቀበሩ ተደርገዋል፡፡

ከአደጋው በኋላ ሊፓይን  ራሱን ለማጥፋት ሲያስብ የጻፈው ደብዳቤና ለሌሎች ጓደኞቹ የጻፋቸው ሁለት ደብዳቤዎች በኪሱ ተገኝተዋል፡፡ ከደብዳቤዎቹ ይዘት ሊፓይን ፊሚኒስቶችን እንደሚጠላና ሊገደሉ ይገባል በሚል የአሥራ ዘጠኝ ታዋቂ ሴቶችን ስም ጽፏል፡፡ ሌፓይን ራሱ ምክንያታዊ እንደሆነ የሚገልጸው ይህ ደብዳቤ፣ ፌሚኒስቶች ሕይወቱን እንዳበላሹበት ይገልጻል፡፡ የሕይወት ታሪኩ እንደሚያሳየው ሊፓይን ከፈረንሳይ ተናጋሪ ካናዳዊ እናትና ከአልጀሪያዊ አባት የተወለደ ሲሆን፣ አባቱ ሴቶችን የሚንቅ፣ ሚስቱን የሚሳደብና የሚማታ፣ የእናትና የልጅን መልካም ግንኙነት የማይወድ ነበር፡፡ በሰባት ዓመቱ እናትና አባቱ የተለያዩ ሲሆን፣ ከእናቱ ጋር ሆኖ በቤተሰቦቿ አድጓል፡፡ ሊፓይን ጥሩ አዕምሮ የነበረው ግን ጭንቀት ያለበት ፌሚኒስቶትን የሚጠላ፣ ሙያ ያላቸውንና በተለይም ፖሊስነትን የመሰሉ ለወንድ መተው አለባቸው ብሎ የሚያስባቸውን ሥራዎች የሚሠሩ ሴቶችን የማይወድ እንደነበር ከሞቱ በኋላ የወጣ ሪፖርት ገልጿል፡፡

በዚህ ሰሞን ከተፈጸሙና ለዘመቻው መነሻ ከሆኑት ኩነቶች አንዱ ይህ የሞንትሪያል ጭፍጨፋ ነው፡፡ የ16 ቀናት ፀረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ በመጀመሪያው የሴቶች ዓለም አቀፍ የአመራር ተቋም (Women’s Global Leadership Institute) ቀያሽነት በተቋሙ በ1991 የተጀመረ ዓለም አቀፋዊ ዘመቻ ነው፡፡ የጉባዔው ታዳሚዎች የዘመቻው መነሻ ቀን ኖቬምበር 25 (International Day Violence Against Women) እንዲሁም የዘመቻው ማብቂያ ቀን ዲሴምበር 10 (International Human Rights Day) ለማድረግ የወሰኑት ጾታዊ ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ያላቸውን ግንኙነት ለማጉላት፤ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን አጽንኦት ለመስጠት ነው፡፡ ከ16ቱ ቀናት ውስጥ ኖቬምበር 29 ዓለም አቀፍ የሴቶች መብቶች ተሟጋቾች ቀን፣ ዲሴምበር 1 የዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን እንዲሁም በዚህ ጽሑፍ በስፋት የምንዳስሰው ዲሴምበር 6 የሞንትሪያል ጭፍጨፋ ቀንን የሚያካትቱ ናቸው፡፡ ዘንድሮ የሞንትሪያል ጭፍጨፋ 25ኛ  ዓመት ሲሆን፣ በመነሻ ታሪኩ ከተረዳናቸው ዓቢይ ነጥቦች አንፃር ስለ ሴቶች ጥቃት የተወሰነ ነገር እንመልከት፡፡

የጥቃቱ ምንነት  

በታሪኩ መነሻ ለመገንዘብ እንደቻልነው 14 ሴቶች የተጨፈጨፉት ሴት በመሆናቸው ብቻ ነው፡፡ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትም ከዚህ የተለየ ትርጉም የለውም፡፡ ሴቶች ሴት በመሆናቸው ብቻ የሚደርስባቸው ጥቃት በመሆኑ ነው፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማናቸውም ዓይነት መድሎን ለማስወገድ የተፈረመው ስምምነት (CEDAW) በአንቀጽ 1 በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት (Gender Based Violence) ሴቶች ሴት በመሆናቸው ብቻ የሚፈጸምባቸው ወይም በኅብረተሰቡ ሴቶችን በተለየ የሚመለከት ስለመሆኑ ይገልጻል፡፡ ጥቃቱ አካላዊ፣ አዕምሮአዊና ወሲባዊ ጥቃትን የሚያጠቃልል ሲሆን፣ ሴቶችን የማያስፈራራ፣ የሚያስገድድና ነፃነታቸውን የሚነፍግ ድርጊት ነው፡፡ በአገራችን ይህንን ትርጉም የሚያሟሉ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መኖራቸው ለሁሉም የተገለጸ ነው፡፡ እንደ ሊፓይን በአደባባይ ብዙኃን ሴቶችን የመጨፍጨፍ ድርጊቶች ባናስተውልም የሚደበደቡ፣ በስለት የሚወጉ፣ አሲድ የሚደፋባቸው፣ በብዙ ወንዶች የሚደፈሩ፣ በቤት ውስጥ ጥቃት የሚደርስባቸው፣ የሚሰደቡ፣ የሚለከፉ ብዙ  ናቸው፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ያሰብናቸው የ16 ቀናት ንቅናቄ እነዚህ ድርጊቶች እንዲወገዱ ካልተቻለም እንዲቀንሱ ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ ቀናቱም ካለፉ በኋላ በየዕለት ኑሮአችን ሴቶችን ከጥቃት የመንከባከብ ግዴታ በሁሉም ላይ ተጥሏል፡፡

የጥቃቱን አመክንዮ ፍለጋ

ሊፓይን በሴቶች ላይ ከፈጸመው ጭፍጨፋ በኋላ ግለሰቡ ለምን እንዲህ ዓይነት ፀያፍ ድርጊት እንደፈጸመ የወንጀል ምርመራ ባለሙያዎች፣ የማኅበራዊና የሥነ ልቡና ጠበብት የተለያየ ትንተና ሰጥተዋል፡፡ ሊፓይን በዋናነት ያጠቃቸው ሰዎች ጾታቸው ሴት መሆኑ፣ በጭፍጨፋው ወቅት ሲናገራቸው ከነበሩት ቃላትና ራሱን ከማጥፋቱ በፊት ከጻፈው ደብዳቤ በመነሳት ብዙ ሰው የሊፓይን ድርጊት የፀረ ፌሚኒስት አቋም በኅብረተሰቡ ውስጥ በስፋት የሚታየው በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን ጨምሮ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሰፈነው ሴትን የመጥላት አባዜ (Misogyny) እንደሆነ ተናገሩ፡፡ የወንጀል ምርመራ ባለሙያዎች በበኩላቸው ጭፍጨፋው ተጠቂዎቹ በሴትነታቸው ብቻ የተመረጡበት ሴቶችን በመጥላት የሚፈጸም ወንጀል ዓይነት መሆኑን ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች የሊፓይን ድርጊት የፀረ ፌሚኒዝም አቋም ነው በማለት አንድ የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ብቻ የተቃጣ አድርጎ መውሰድ ሰቆቃውን ያሳንሰዋል በማለት ሰብዕናን ማጥፋት ላይ ያለመ ስለመሆኑ ይተቻሉ፡፡ አንዳንዶቹም ጉዳዩን ቀለል በማድረግ አንድ ያበደ ሰው የሚያደርገው ሥራ ነው በሚል ጠበብ ያለ አስተያየትም የሰጡ አልጠፉም፡፡

የሥነ ልቦና ባለሙያዎች የሚችን ደብዳቤዎቹን አንብበውና ጓደኞቹን አነጋግረው የጠቆሙት አመክንዮ ደግሞ የተለየ ነው፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ድምዳሜ የሊፓይን ድርጊት የሰብዕና መዛባት (Personality disorder) ምልክት ሲሆን፣ ከልጅነቱ ጀምሮ በአባቱ ተፅዕኖ ስለ ሴቶች ዝቅ ያለ አመለካከት በማዳበሩ ነው ይላሉ፡፡ አንዳንዶች የሊፓይን ድርጊት በኅብረተሰብ ውስጥ ከሚታይ ለውጥ የመጣ ድኅነት፣ አቅም ማጣት የመገለል እንዲሁም በወንድና በሴት መካከል ባለ ጽንፍ የያዘ ልዩነት መነሻ የሚዳብር ስለመሆኑ ይተነትናሉ፡፡ ጭከና ያላቸው ፊልሞች፣ በመገናኛ ብዙኃን የሚዘገቡ የኃይል ተግባራትም ተፅዕኖ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡

የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ከተመለከትን በሴቶች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎች አመክንዮ ከላይ ከተገለጹት ለጥቃት መነሻ ከሚሆኑ መላ ምቶች የዘለሉ ላይሆን ይችላሉ፡፡ ሁሉም ወንድ በሴቶች ላይ ጥቃት ይፈጽማል ወይም የሚፈጸሙትን ጥቃት ይደግፋል ባይባልም፣ የሚፈጽሙት ወንዶች መንስዔ ምክንያታቸው የተለያየ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሰረጸው የወንድ የበላይነት አስተሳሰብ፣ ጥቃት በሚፈጸምበት አካባቢና ቤተሰብ ውስጥ ማደግ፣ የሱስ ተገዥ መሆን ወዘተ. በሴቶች ላይ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች መነሻ እንደሚሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የ16 ቀናት ንቅናቄን እያከበርንም ሆነ ከዚያ በኋላ ማንኛውም አመክንዮ ለጥቃት አሳማኝ ምክንያት እንደማይሆን በመገንዘብ የሥርዓተ ጾታ ትምህርትን ማስረጽና የጾታ እኩልነትን በተጨባጭ እንዲተገበር ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

የሕግ አስፈጻሚ አካላት ሚና

በሊፓይን ጉዳይ እጅጉን ትችት ከደረሰባቸው ኩነቶች ውስጥ አንዱ የፖሊስ ምላሽ የመዘግየቱና ለ20 ደቂቃ በቆየው ጭፍጨፋ ከዩኒቨርሲቲው ሕንፃ ጀርባ የነበሩት የፖሊስ ኃይሎች ትጋት ማነስ ነው፡፡ የፖሊስ ኃይል በጥንካሬ በተደራጀበት ካናዳ እንኳን ቸልተኝነት መኖሩን ለሚሰማ ሰው አገራችንን በመሰሉ ያላደጉ አገሮችማ የሴቶችን ጥቃት በመከላከል የፖሊስ አስተዋጽኦ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ቀላል ነው፡፡ ፖሊስ ሕዝባዊ ሆኖ ወንጀሎች ከመፈጸማቸው በፊት ለሴቶች ካልደረሰላቸው ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ የማይመለሱ ነገሮች በሚበዙበት ሁኔታ ትጋቱ ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡ ከዓመት በፊት ሀና ከተባለች ሴት ተማሪ ልጅ ጋር የሰማነው የወንጀል ጉዳይ በዚህ ረገድ ዓቢይ አስረጂ ነው፡፡ በጠራራ ፀሐይ ሕፃኗ በብዙ ጎረምሶች ተጠልፋ ስትደፈር፣ ለሦስት ቀናት ያህል ሕይወቷ እስኪሞት ስትሰቃይ ፖሊስም መረጃ አልነበረውም፣ ኅብረተሰቡም ለፖሊስ ያሳወቀው ነገር አልነበረም፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስወገድ የአስፈጻሚ አካላት በተለይ የፖሊስ ሚና ሰፊ በመሆኑ በ16 ቀናት የንቅናቄ ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ የፖሊስ ኃይልን አቅም በመገንባት፣ የምርመራ ቴክኒክ በማሠልጠን፣ የኅብረተሰቡንና የፖሊስን ግንኙነት በማጠናከር መሥራት ለነገ የሚባል አይደለም፡፡

ከሞንትሪያል አደጋ ጋር ተያይዞ ሌላው በጊዜው አከራካሪ የነበረው ጉዳይ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ጉዳይ ነው፡፡ በጊዜው ካናዳ አዳዲስ ሕግጋቶችን ያወጣች ሲሆን፣ የጦር መሣሪያ ባለቤቶች በቂ ሥልጠና እንዲያገኙ፣ የጦር መሣሪያ ባለቤት የሚሆኑ ሰዎችን የማጣራት ዕርምጃ፣ የጦር መሣሪያ ማስቀመጫ ሁኔታዎችን እንዲሁም የጦር መሣሪያ ስለሚመዘገቡበት ሁኔታ ጠንካራ ድንጋጌዎች ተቀርጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በምዕራባውያኑም ሆነ በአገራችን የሚፈጸሙ ወንጀሎች የመተግበሪያ ዘዴ የጦር መሣሪያን የሚያካትት እንደመሆኑ መጠን የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ቸል የማይሉት ጉዳይ ነው፡፡ በአገራችን የጦር መሣሪያ አያያዝንና አጠቃቀምን በዝርዝር የሚገዛ ሕግ አለመኖሩ ነገ ከነገወዲያ ችግሩ ሲሰፋ፣ ጉዳቱ ሲበረክት መውጫ ቀዳዳ እንዳይጠፋ ሥጋት አለና በዚህ ረገድ የሚመለከተው አካል ሊያስብበት ይገባል፡፡

እንደማጠቃለያ

የ16 ቀናት ፀረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ በየዓመቱ መታሰቡ ለሴቶች መብት መከበር ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ዲሴምበር 6 ቀን 1989 በካናዳ የተፈጸመው የ14 ሴቶች ጭፍጨፋ 25 ዓመት የሞላው ሲሆን፣ በእነዚህ ወቅቶች ከሚታሰቡት ዓቢይ ታሪካዊ ክስተቶች አንዱ ነው፡፡ የችግሩ መኖር ከታወቀበት ጀምሮ ምዕራባውያን የሴቶችን ጥቃት ለማስወገድ ጠንክረው ሠርተዋል፤ ተሳክቶላቸዋልም፡፡ ጠንካራ ሕግጋት፣ ጠቃሚ ፖሊሲዎች፣ ትጋት ያለው አስፈጻሚ፣ ንቁ ኅብረተሰብ በመፍጠር ሴቶች መብታቸው እንዲከበር ሠርተዋል፡፡ የእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ከድሮው የተሻለ ቢሆንም፣ አሁንም ብዙ ክፍተቶች እንዳሉበት ለሁሉም የተገለጠ ነው፡፡ የ16 ቀናቱን ዘመቻ በየዓመቱ ስናከብር የጨመርነውን እያደነቅን፤ የጎደለውን ለመሙላት የምንተጋበት ሊሆን ይገባል፡፡

    አዘጋጁ ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getukow [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡