የ‹‹ቁምራ›› ዘመን ቁጠባ

በጌታቸው አስፋው

የመዋዕለ ንዋይ ገንዘብ ምንጭ ቁጠባ በመሆኑ ስለቁጠባ በተደረገው ቅስቀሳና ንግድ ባንኮች እስከ ገጠሩ ዘልቀው በመግባታቸው ብዙ ሰው በርካታ ጥሬ ገንዘብ ቆጥቦ፣ በ2002 ዓ.ም. የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዝግጀት ወቅት 9.5 በመቶ ብቻ የነበረው ቁጠባ በዕቅዱ መጨረሻ ዓመት 2007 ዓ.ም. በዕቅድ ከተያዘው 15 በመቶው በጣም በልጦ 21.8 በመቶ ሆኗል፡፡ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን መጨረሻ ዕቅድ ዓመት 2012 ዓ.ም. ቁጠባ የአገር ውስጥ ጥቅል ምርትን ሲሶ ወይም 29.6 በመቶ እንዲሆንም ታቅዷል፡፡

በብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. 2014/15 ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት የቁጠባው መጣኝ በ2002 ዓ.ም. ከነበረበት 9.5 በመቶ ወደ 17.2 በመቶ በእጥፍ የዘለለው፣ በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መለኪያ ዋጋ መከለስ ምክንያት ኢኮኖሚው በወረቀት ላይና በኢኮኖሚ ባለሟሎች ጭንቅላት ውስጥ ሦስት እጥፍ ባደገበት በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡

ነገር ግን ሌላ ምክንያት ቢኖር ነው እንጂ የምርቱ በመጠን ሦስት እጥፍ ማደግ ለቁጠባው መጣኝ በአንድ ዓመት ውስጥ እጥፍ መሆን ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም በምርት ዕድገቱ ምክንየት ቁጠባ ብቻ ሳይሆን ፍጆታም በተመሳሳይ ሁኔታ ስላደገ የፍጆታና የቁጠባ ድርሻ መጣኙ ብዙ ሊለወጥ አይችልም፡፡

የቁምራ ዘመን በኢትዮጵያ ወጣቶች የተፈጠረ ስያሜ ሲሆን፣ ትርጉሙ ከቁርስ ምሳና ራት በቀን ሦስት ጊዜ መብላት የቀድሞ ዘመን ወደ ቁምራ (ቁርስን ምሳን ራትን) አጠቃሎ በቀን አንድ ጊዜ መብላት የተሸጋገርንበትና ላለመራብ ቁምራው የሚበላበትን ሰዓት የማስላት ዘመን ነው፡፡ የቁምራ ተጠቃሚ ቁጥር እየበዛ ስለመጣ እንደ ክብደታችንና እንደ ቁመታችን ሰዓቱን የምናሰላበት የቁምራ ሶፍትዌር መመረት ሳያስፈልግም አይቀርም፡፡

እኛ ኑሯችን በሙሉ ቁጠባ ነው፡፡ በዕድርና በዕቁብ አማካይነት ገንዘብ እንቆጥባለን፡፡ ራስጌ ሥር ለክፉ ጊዜ ብለን ገንዘብ እንቆጥባለን፡፡ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ተመግበን ምግባችንን እንቆጥባለን፡፡ አንድ ካናቴራ፣ ሸሚዝ፣ ሱሪ፣ ኮት ወይም ጫማ ለስድስትና ለሰባት ዓመታት ለብሰንና ተጫምተን፣ የቤት ዕቃዎቻችን ለብዙ አሥርት ዓመታት ተጠቅመን፣ ዛኒጋባ ቤቶቻችን ሁለትና ሦስት ትውልድ አሳልፈው ቁሳቁሶች እንቆጥባለን፡፡

ዘመድ ናፍቆን ለመጠየቅ የሄድን መስለን ሰው ቤት በመቀላወጥ ቁምራውንም መልሰን ለነገ እንቆጥባለን፡፡ የማናውቀው ሰው ሲሞት ሳንጠራ ቀብረን የእዝን በመብላት እንጀራና ወጥ ቢጠፋም ንፍሮውን በእጃችን ሙሉ ዘግነን ቁምራውን መልሰን ለነገ እንቆጥባለን፡፡ የቁጠባ ቁጠባ መሆኑ ነው፡፡

ቁጠባ አላሳለፈልንም እንጂ እንደኛ የሚቆጥብ የለም፡፡ ኑሯችን ሁሉ ቁጠባ ነው፡፡ እንኳንስ እኛ ሰዎቹ የቤት እንሰሶቻችንም ይቆጥባሉ፡፡ የቤት ውሾችና ድመቶቻችን ከተሰጣቸው ምግብ ግማሹን በልተው ግማሹን መሬት ቆፍረው ይቀብራሉ፡፡ ከእኛው ነው የተማሩት፡፡ ወይም የእኛን አቅም ስለሚያውቁ በፈለጉት ጊዜ ልንሰጣቸው እንደማንችል ገብቷቸው ነው፡፡

መንግሥት ብዙ ብር ገበያ ውስጥ አፍስሶ ሸቀጥህን በፈለግኸው ውድ ዋጋ ሸጠህ ብቻ ከምታገኘው ግዙፍ ትርፍ ለእኔም ግብሬን ክፈለኝ፣ ለአንተም ባንክ አስቀምጥ፣ አቶ ጌታው ለሕንፃ መሥሪያ ይፈልገዋል ብሎ ሳያስተምረን በፊትም ቆጣቢዎች ነበርን፡፡

ቁጠባና ፍጆታ ከጽንሰ ሐሳባዊ ትርጉም ባሻገር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን እንደሚመስል መሠረታዊ ጥናት የሚሻ ነው፡፡ ምክንያቱም በብሔራዊ ኢኮኖሚ ትርጉሙ ቁጠባ ማለት ትናንትና ዛሬ ከተመረተው ምርት ውስጥ ለነገና ለተነገ ወዲያ ማቆየት ማለት እንጂ፣ ጥሬ ገንዘብ ወይም ብር ባንክ ውስጥ ማስቀመጥና ማከማቸት ስላልሆነ ነው፡፡

ለብሔራዋ ኢኮኖሚ ባንክ ውስጥ የሚቀመጥ ጥሬ ገንዘብ በባንኩ ደላላነት ከአቶ በዛብህ ወደ አቶ ጌታው ዞረ እንጂ ኢኮኖሚያዊ ድምር ውጤቱ ባዶ ነው፡፡ አቶ ጌታሁን ተበድሮ መዋዕለ ንዋይ ባያደርገው ኖሮ አቶ በዛብህ ለፍጆታ ያውለው ነበር የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የኑሮ ደረጃ ሁኔታ ጋር፣ ከአበዳሪውና ከተበዳሪው ባህሪያት ጋር ሊጠና ይገባዋል፡፡

በዕድገት ውስጥ ያለ ድህነት

በመርህ ደረጃ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (GDP) በሦስት መንገድ ተሰልቶ በሦስቱም መንገድ እኩል ይሆናል፡፡ አንደኛው መንገድ የተጨማሪ እሴት ወይም የምርት ቀጥታ ቆጠራ (Value Added or Product Approach) በየአንዳንዱ ሰውና ድርጅት የተፈጠረ ተጨማሪ እሴት ወይም የምርት ቆጠራ መንገድ ነው፡፡ ሁለተኛው የገቢ ስሌት መንገድ (Income Approach) ምርቱን ላመረቱ የምርት ግብረ ኃይሎች፣ ለሠራተኛው፣ ለመሬት፣ ለካፒታል፣ ለድርጅት ባለቤቶች በደመወዝ፣ በወለድ፣ በኪራይ፣ በትርፍ መልክ ተከፋፍሎ ጠቅላላ ገቢው ጠቅላላ የተመረተውን ምርት (ተጨማሪ እሴት) ያክላል፡፡ ሦስተኛው መንገድ የወጪ ስሌት (Expenditure Approach) የምርት ግብረ ኃይሎች ባለቤቶች ባገኙት ገቢ በሙሉ የፍጆታና የመዋዕለ ንዋይ ሸቀጦችን ይገዛሉ፡፡ ስለዚህም ወጪዎች ገቢን ያክላሉ፡፡ ገቢዎችም ምርትን ያክላሉ፡፡ ሦስቱም እኩል ይሆናሉ፡፡

የገቢ መጠን የሚለካው በግብዓተ ምርቶች ገበያ ውስጥ ሲሆን፣ ወጪ ግን የማለካው በምርት ገበያ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህም ገቢ በግብዓተ ምርት ገበያ ወጥቶ ወደ ምርት ገበያ ውስጥ እስከሚገባ ድረስ በሁለት መንገድ ጎድሎ ነው የሚመጣው፡፡ አንዱ ጉድለት ለመንግሥት የሚከፈል ግብር ሲሆን ሌላው ጉድለት ቁጠባ ነው፡፡

በግብዓተ ምርቶች ገበያ ውስጥ የተገኘው የአምራቹ ገቢ ከምርት ገበያ ወጪ ጋር እኩል ለመሆን የጎደለው መሞላት አለበት፡፡ የግብር ጉድለት በመንግሥት ወጪ ሲሞላ የቁጠባ ጉድለት ደግሞ የመዋዕለ ንዋይ ወጪ ይሞላል፡፡

ስለዚህም የግለሰቦች ፍጆታ ወጪ፣ የመንግሥት ፍጆታ ወጪና የግልና የመንግሥት መዋዕለ ንዋይ ወጪ በአጠቃላይ ሸመታዎች (ፍላጎት) ተዳምረው የአምራቾችን ገቢና ምርትን (አቅርቦትን) ያክላሉ፡፡ ሦስቱም የሸመታ ወጪ፣ ገቢና ምርት እኩል ይሆናሉ፡፡ በዚህ ሒሳብ ስሌትም ፍላጎትና አቅርቦት ይጣጣማሉ፡፡ በስንት ብር ዋጋ እኩል እንደሚሆኑ የዋጋ አወሳሰን ኢኮኖሚስቶች ይንገሩን፡፡

የግልና የመንግሥት ፍጆታ ወጪዎች ለዛሬ ለሚጠቅም ምርት ሸመታ የሚወጡ ወጪዎች ሲሆኑ፣ በግብር አማካይነት ከገበያ ወጥቶ በመንግሥት የካፒታል ወጪዎች አማካይነት ወደ ገበያው ውስጥ ተመልሶ የሚገባውና በቁጠባ መልክ ከገበያ ወጥቶ በመዋዕለ ንዋይ መልክ ተመልሶ ወደ ገበያ የሚገባው በረዥም ጊዜ ውስጥ ኢኮኖሚውን ቢያሳድጉም፣ የዛሬውን የሰዎች ችግር ስለማይፈቱ የዛሬን ድህነት ያባብሳሉ፡፡

ቁጠባ በመዋዕለ ንዋይ ከበለጠም እንደዚሁ የሸማቾች ገቢ በሸመታ መልክ ተመልሶ ወደ አምራቾች ስለማይሄድ፣ የተመረተ ምርት ሳይሸጥ ይቀርና አምራቾች ለሚቀጥለው ጊዜ ምርታቸውን እንዲቀንሱ ስለሚያደርጋቸው የምርት መቀነስንና ሥራ አጥነትን ሊፈጥር ይችላል፡፡

ስለዚህም ስለቁጠባ ማደግ ብቻ ሳይሆን የተቆጠበው በገንዘብ ገበያ አማካይነት መዋዕለ ንዋይ ስለሚሆንበት ሁኔታ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በላይ የተገለጸው የዕድገትና የድህነት ሁኔታ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ መሠረተ ልማቶች እየተስፋፉ ስለሆነ መዋዕለ ንዋይ እንዳደገ እናያለን፡፡ የኑሮ ውድነትም ገበያችን ውስጥ ስለሚታይ ድህነት የተንሰራፋ ስለመሆኑና ፍጆታ በቂ ስላለመሆኑ ማስረጃ ነው፡፡

እየኖሩ ማደግ ሳለ እየሞቱ ማደግ

ብዙ ሰዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የኑሮ ሁኔታ የሚገልጹት ኢኮኖሚው የሚወራለትን ያህል አላደገም በማለት ነው፡፡ ነገር ግን የብሔራዊ ኢኮኖሚ ሒሳብ ባለሙያዎቹና የስታስቲክስ ባለሥልጣን ብዙ ሺሕ መረጃ ሰብሳቢዎችን አሰማርተው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ስሌት ዘዴ ተጠቅመው የለኩትን ነገር ትክክል አይደለም ብሎ ለማለት ትክክለኛው ነው የሚሉትን የራስን ማቅረብ ይጠይቃል፡፡

በናሙና ጥናት ደረስንበት የሚሉት የዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ወይም የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንም ቢሆኑ፣ በመጠኑ ከመንግሥት ቁጥር ዝቅ አድርገው ውጤታቸውን የሚያቀርቡት ፈራ ተባ እያሉ በመንታ ልብ ነው፡፡ መንግሥት ለእነርሱም አስፈሪ ሆኗል፡፡በቁጥሮቹ ላይ ከመከራከር ይልቅ ውሸቱን እንደ ውሸት ተቀብሎ በተሰጠው ቁጥርና ገበያ ውስጥ በሚታየው የኑሮ ሁኔታ መካከል ያለውን ልዩነት መመርመር ይሻላል፡፡

ከዚህ ቀደም የጻፍኩትን ልድገምና ሰዎች በጭንቅላታቸው ላይ ባለው ፀጉር ብዛት ቢከራከሩ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ በፀጉሩ ጥቅም ላይ ቢከራከሩ ግን ትርጉም አለው፡፡ የፀጉሩ መብዛት ጥቅም ከዝናብና ከፀሐይ ለመከላከል ጉዳቱም የተባይ ቤት መሆን ይሆናል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱም እንደዚሁ ነው፡፡

የኢኮኖሚ ዕድገቱ ሕዝብን ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግንም ይፈትነዋል፡፡ ምክንያቱም ኢሕአዴግ ራሱን ያዘጋጀው የግብርና ኢኮኖሚን ለመምራት ብቻ ሳይሆን፣ በኢንዱስትሪ የበለፀገች የግሎባላይዜሽን ዘመን አገር መሪ ለመሆን ከፍተኛ የገንዘብ አስተዳደር ችሎታን ይጠይቃል፡፡ የአቅም ማነስ ምልክቶቹ አሁንም መታየት ጀምረዋል፡፡

ለቁጥር የትርጉም ዋጋ ሳይሰጠው ለብቻው ቢነገር ይበልጣል ያንሳል ለማለት ካልሆነ በቀር ምንም ጥቅም የለውም፡፡ የኢኮኖሚው በይበልጣል ጠንቋይ ማደግ ካለፉት ጊዜያት መብለጥ ለዋጋ ንረትና ለከፋ ድኅነት ዳረገን እንጂ ጥቅም አላገኘንበትም፡፡

በሦስት መቶና በአራት መቶ ዶላር ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢያችን በሸቀጦች ዋጋ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ተስተካከልን፡፡ እንደነርሱ ነፍስ ወከፍ ገቢያችን ሰላሳ ሺሕና አርባ ሺሕ ዶላር ሲደርስ የሸቀጦቻችን ዋጋ የት ሊደርስ ነው?

ከዚህም በላይ ሌላ የምንጠብቀው አደጋ አለ፡፡ ለህዳሴው ግድብ መንግሥት ከሕዝብ የተበደረውን ብዙ ቢሊዮን ብር የቦንድ ግዢ ከነወለዱ ለሕዝብ ሲመልስ የዋጋ ንረት ከፍተኛ እንደሚሆን ለኢኮኖሚስቶች ሚስጥር አይደለም፡፡ ማቀድ አይቸግረንምና መንግሥት ላለመክፈል ካላቀደ በቀር የዋጋ ንረት አደጋ ላይ ነን፡፡ አስፈሪ የዋጋ ንረትና ግሽበትን መንግሥት ለወደፊት እየገፋውና እያስተላለፈው ነው እንጂ እየቀረፈው አይደለም፡፡

የኢኮኖሚ ባለሟሎች የሚበልጡና የሚያንሱ ቁጥሮች መፈብረክ ላይ ችግር የለባቸውም፡፡ ቁጥር የሚፈበርኩ ብዙ የኢኮኖሚ ልኬት ሞዴሎች (Econometric Models) አሉ፡፡ ችግሩ ቁጥሩን መተርጎሙ ላይ ነው፡፡ ቁጥርን መተርጎም ሳይቻል ሲቀር ደግሞ ኢኮኖሚክሱ ተጠቃሎ ማሳረጊያው ይበልጣል ያንሳል ይሆናል፡፡

መሠረታዊ ሁኔታዎች ተሟልተውለት እንደ ሰው ለመኖር የሚፈልገው ሕዝብና እንደ ቻይና ለማደግ የሚፈልጉት የኢኮኖሚ ባለሟሎች የኢኮኖሚ ቁጥሩን በመተርጎም ላይ አልተግባቡም፡፡ ፍጆታ ለዛሬ ነው፣ መዋዕለ ንዋይ ግን ለነገ ነው፡፡ ሕዝቡ ነገ ለመኖር ዛሬ መሞትን አልመረጠም፡፡ መንግሥት ዛሬ ሙትና ነገ ትኖራለህ እያለው ነው፡፡

ኢኮኖሚስቶች ኢኮኖሚን በአጭር ጊዜና በረዥም ጊዜ ውጤት ከፋፍለው መተንተናቸው አዲስ አይደለም፡፡ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ሊቁ ኬንስም እንደ ፌዝ ‹‹በረዥም ጊዜኮ ሁላችንም ሟቾች ነን፡፡ ለምን ስለረዥሙ ጊዜ እንጨነቃለን?›› አለ ይባላል፡፡ ለረዥም ጊዜ ማሰብ ቢያስፈልግም እንኳ ነገ ለመኖር ዛሬን እየሞቱ መሆን የለበትም፡፡ ዛሬን ሳንሞት ነገ መኖር የምንችልበት መንገድ አለ፡፡ የዛሬ ኑሮ ሁኔታ የሚገለጸው በፍጆታ መልክ ነው፡፡ የነገ ዕድገት ሁኔታ የሚገለጸው ግን በመዋዕለ ንዋይ መልክ ነው፡፡ ፍጆታና መዋዕለ ንዋይ ሀብት የሚሻሙ ተፃራሪዎች አይደሉም፡፡

ይልቁንም የሚደጋገፉ ሒደቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን መደጋገፋቸው ችሎታ ባለው ባለሙያ መገራት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግርም ከይበልጣል ያንሳል ትንታኔ ወጥቶ፣ የፍጆታንና የመዋዕለ ንዋይን መደጋገፍ የሚፈጥር ባለሙያ ባለመኖሩ እየኖሩ ማደግ ሲቻል እየሞቱ ማደግ እንደ አማራጭ መወሰዱ ነው፡፡

ለዚህም ነው ቁጠባ ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከምንም በላይ ትኩረት የተሰጠው፡፡ የቤት እንሰሶቻችን በዓመት በዓል ቀን በሰው ተግጦ ከተሰጠ የአጥንት ቀለባቸው ውስጥ ግማሹን በልተው ግማሹን ቆጥበው ምድር ውስጥ ይቀብሩታል፡፡ የኢትዮጵያ ደሃም እንደዚሁ ሀብታም ከጋጠው ቆጥበህ አስቀምጥ ነው የተባለው፡፡

አንድ ካናቴራ፣ የውስጥ ሱሪ፣ ኮት፣ ጫማ፣ ወዘተ ለዚያውም የተቀዳደደውን ሰፍቶና ቆጥቦ ስድስትና ሰባት ዓመታት ከመልበስ አልፎ በቁምራ ስሌት በቀን አንዴ በልቶ ከመኖር አልፎ፣ በደሳሳ ጎጆ ከመኖር አልፎ ብር ቆጥብና ባንክ አስቀምጥ፣ ባንኮች ለሕንፃ ገንቢው አበድረው ከተማችን በሕንፃ ትጥለቀለቃለች ይባላል፡፡

የመዋዕለንዋይ ገንዘብ አቅርቦት ችግር

ነጋዴው በገንዘብ ዕጦት ሥራ ሊቆም ነው ይላል፡፡ ንግድ ባንኮች መንግሥት በምናበድረው ገንዘብ ሃያ ሰባት በመቶ ቦንድ እንድንገዛ ያስገድደናል ይላሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ በሚያዘጋጀው ዓመታዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሪፖርት ንግድ ባንኮች በሕግ ተደንግጎ በብሔራዊ ባንክ ማስቀመጥ ከሚገባቸው መጠባበቂያ ተቀማጭ በላይ እስከ ቢሊዮን ትርፍ ብር በየዓመቱ ያስቀምጣሉ፡፡ የባንክ ለባንክ መበዳደርም እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ እሑድ ታኅሳስ 19 ቀን 2007 ‹‹የፋይናንስ አቅርቦት አሁንም እያከራከረ ነው›› በሚል ርዕስ ለንግዱ ማኅበረሰብ የብሔራዊ ባንክ ባለሥልጣን የአክሲዮን ባንክ ሳይስፋፋ የመዋዕለ ንዋይ ባንክ ማቋቋም ዋጋ የለውም በማለት የሰጡትን መልስ፡፡ የልማት ባንክ ባለሥልጣንም ልማት ባንክ ብሔራዊ ባንክ የፈቀደለትን ገንዘብ እንኳ አበድሮ አልጨረሰም በማለት የሰጡትን መከራከሪያ መልስ አውጥቶ ነበር፡፡

ስብሰባውን ያልተካፈለው የገንዘቡ ምንጭ የሆነው ቆጣቢው ድምፁን የማሰማት ዕድል አጥቶ እንጂ፣ የእርሱን ያህል የተጎዳ የለም፡፡ በአሥራ ሁለት በመቶ የዋጋ ንረት የገንዘብ ሸቀጦችን የመግዛት አቅም በአሥራ ሁለት በመቶ ስለሚወድቅ፣ አምስት በመቶ የቁጠባ ወለድ እያገኘ ገንዘቡን ባንክ የሚያስቀምጥ ሰው ለተበዳሪው ሰባት በመቶ ከፍሎ እንዳበደረ ወይም ገንዘቡን በኪሳራ እንደሸጠ ይቆጠራል፡፡ ይህን ለማትረፍ ሳይሆን ለችግር ጊዜ ብሎ እየከሰረ የሚያበድር ቆጣቢ መንግሥትም በዛብህ ብሎ ከአምስት በመቶዋ ወለድ ላይ የካፒታል ዕድገት ታክስ ያስከፍላል፡፡

ሰዎች ገንዘብ የሚቆጥቡት ለሁለት ጉዳይ ነው፡፡ አንድም ለችግር ጊዜ ይሆነኛል በማለት አለበለዚያም ወለድ አግኝቶ ለማትረፍ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ቆጣቢው ኪሳራ እንጂ ትርፍ ስለማያገኝ፣ መቆጠቢያ ምክንያቱ በድሆች ለችግር ጊዜ ተብሎ ነው፡፡ ሀብታም እንደሆነ ድንጋይ እንጂ ገንዘብ አይቆጥብም፡፡

ለችግር ጊዜ ብቻ ተብሎ በደሃው የገቢ ሲሶ ከተቆጠበ፣ ለማትረፍ ተብሎም ቢቆጠብ ከጥንካሬያችን የተነሳ ቁምራቸውን በሦስት ቀን አንድ ቀን ተመግበን ብዙ እንቆጥብ ነበር፡፡ ለኑሮ ብለን ዓረብ አገር ለመሰደድ አሸዋና ባህር የበላን ሰዎች ለዚህ አናንስም ነበር፡፡

ከዚህ አበድሮ በገዛ ገንዘብ መክሰርም ይባስ ብሎ መንግሥት በእኔ መስመር ካልሆነ በቀር ገንዘብ ልትበዳደሩ አትችሉም በማለት ሕግ አውጥቶ ከሳሽ ተቋም መሥርቶ ዘብጥያ ይወረውራል፡፡

በአውሮፓና በአሜሪካ እንዲሁም በቻይና ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት ሕጋዊ የቁጠባ ተቀማጭ ሒሳብ መያዝና ብድር የመስጠት የንግድ ባንክ ሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ በሥውር የባንክ ሥራ (Shadow Banking) ገንዘብ የሚያገበያዩ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ሲሆኑ፣ ሕጋዊ የንግድ ባንኮችም በተባባሪዎቻቸው አማካይነት በዚህ ተግባር በስፋት ይሳተፋሉ፡፡

እነኚህ እንደ ንግድ ባንክ የተቀማጭ ሒሳብ ጥሬ ገንዘብ ለመቀበል ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው የገንዘብ ተቋማት በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በቻይና ከንግድ ባንኮቹ ያልተናነሰ ሀብት ያንቀሳቅሳሉ፡፡ በቻይና ሃያ ትሪሊየን ዶላር የሚጠጋ ሀብት አላቸው፡፡ በአሜሪካም እስከ ሃያ አምስት ትሪሊየን ዶላር ይንቀሳቀሳል፡፡

ኢትዮጵያ የመዋዕለ ንዋይ ገንዘብ አጠረኝ እያለች እየጮኸች ለምን ይሆን ሕዝቡ በነፃነት ገንዘቡን እንዳይገበያይ በሕግ የከለከለችው? ይህ ነፃ ገበያ የሚባለው ነገር ደርግ በ1967 ዓ.ም. ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ከላከው ጀምሮ የተመለሰ አይመስልም፡፡

በቁምራ ስሌት እየኖረ ለባለፀጎች ራሱ ከፍሎ የሚያበድረው ቆጣቢ ከአገር ውስጥ ምርት ቁጠባው 21.8 በመቶ መድረሱ ኢኮኖሚው የተዋቀረበት ሥርዓት ለሀብታም ያደላ እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡ በተለይም ከሦስት ዓመት በፊት ለቤት ሥራ ተብሎ በውዴታ ግዴታ እንዲቆጥቡ የተደረጉት ጫማ አሳማሪዎች፣ ሳልቫጅ ነጋዴዎች፣ የቤት ውስጥ አገልጋዮች፣ የቀን ሙያተኞች በዚህ ስሌት ምን ያህል ለተበዳሪ ሀብታም እየከሰሩ እንደገበሩ ሲታሰብ፣ ከጪሰኛና ከባላባታዊ ሥርዓት የከፋ ለጨቋኝ መደብ የቆመ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ብዝበዛ ሥርዓት ነው፡፡

ከእንግሊዙ ታላቁ ትራንስፎርሜሽን ምን እንማር?

መንግሥት ትራንስፎርሜሽኑ የሚመጣው ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ ከጨመሩ ነው ብሎ ይገምታል፡፡ ለማኑፋክቸሪንግ የሚሆን መዋዕለ ንዋይ ከገበሬውና ከከተሜው ጥሮ ግሮ ለፍቶ አደር ከተገኘ ትራንስፎርሜሽኑ በራሱ ጊዜ እንደሚመጣ ያምናል፡፡ ይህ ግን ሊሆን እንደማይችል በዘንድሮው ድርቅ አይተናል፡፡

ከቁጠባውና ከመዋዕለ ንዋዩ ማደግ ትራንስፎርሜሽኑ መቅደም እንዳለበት ከታላቁ የእንግሊዝ ትራንስፎርሜሽን ምን እንማራለን? የሌለውን ሰው ተርበህ ቆጥብ ማለት ይሻላል ወይስ በቅደሚያ እንዲኖረው ማድረግ? ምክንያትና ውጤትን መለየት አለብን፡፡

ስለእንግሊዙ ትራንስፌርሜሽን ሚካኤል ፐርልማን የተባሉ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የካፒታሊዝም አፈጣጠር (The Invention of Capitalism Duke University Press 2000) በተሰኘ መጽሐፋቸው፣ ገበሬዎች በገዛ ንብረታቸው ራሳቸውን በራሳቸው ቀጥረው ከሚኖሩበት የግብርና ሥራ ኑሮ ለመላቀቅና በፋብሪካ ተቀጥረው ለመሥራት ፈቃደኛ እንደማይሆኑ የነፃ ገበያ የመጀመሪያዎቹ ጠንሳሾች እንደተረዱ ጽፈዋል፡፡

ስለሆነም በጊዜው የፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ዝነኛ የሆኑት አዳም ስሚዝ፣ ዴቪድ ሪካርዶ፣ ጀምስ ስቱዋርት ሚልና ሌሎችም ከርዕዮተ ዓለም ቀኖናዊ እምነታቸውና ከነፃ ገበያ ፍፁም ነፃነት አስተምሮታቸው ውጪ ከአርሶ አደርነት ወደ የእርሻና የገጠር ፋብሪካ ወዛደርነት ለሚደረገው ትራንስፎርሜሽን፣ የመንግሥት ጣልቃ በመግባት ተፅዕኖ መፍጠርን አስፈላጊነት አሳስበዋል፡፡

ፋብሪካ በከተማ ብቻ ሳይሆን በገጠርም ሊቋቋም የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡ የአውሮፓ ፋብሪካዎች ወደ አፍሪካ የሚመጡት በከተሞቹ ማማር ሳይሆን ጥሬ ዕቃ፣ ርካሽ ጉልበት፣ መሬትና ገበያ ፍለጋ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ያለውም ከተማ ሳይሆን ገጠር ነው፡፡

በመንግሥት የገጠር መሬት ፖሊሲ ኢሕአዴግና ቅንጅት በ1997 ዓ.ም. ባደረጉት ክርክር የኢሕአዴግ ፅኑ እምነት የነበረው መሬት የገበሬው የግል ንብረት ከሆነ ሸጦ ወደ ከተማ ይሰደዳል የሚል ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ያንኑ ፖሊሲ እስካሁን ድረስ እንዳልለወጠ በተለያዩ ስትራቴጂዎቹና የፖሊሲ ዶኩሜንቶቹ ደጋግሞ ይገልጻል፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት አርሶ አደር ወዝ አደር እንዲሆን ተፅዕኖ አሳደረ፡፡ የእኛ መንግሥት በፖሊሲ ተከላከለ ወይም ከለከለ፡፡

ይህ የኢሕአዴግ እምነት ከእንግሊዙ ታላቅ ትራንስፎርሜሽን በተቃራኒ መንገድ ነው፡፡ ወይ እነርሱ ወይ እኛ ተሳስተናል፡፡ የተሳሳትነው እኛ መሆናችንን በማስረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

እነርሱ በሁለት በመቶ የገበሬ ቁጥር መላውን ሕዝብ ሲመግቡ፣ እኛ በሰማንያ አምስት በመቶ ቁጥር እንኳ ራሳችንን መመገብ አልቻልንም፡፡ እነርሱ ከተፈጥሮ ጥገኝነት ተላቀው የአየር ንብረት ለውጥ አያስጨንቃቸውም፡፡ እኛ ድርቅ በመጣ ቁጥር ለዕርዳታ ጥሪ እንጮሃለን፡፡ እጆቻችን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፡፡ የኤምባሲዎችን በር እናንኳኳለን፡፡ የእኛን ግማሽ ያህል ዕድገት ያላስመዘገቡት አፍሪካውያን በረሃብ ስማቸው ሳይጠራ እኛ በማደግም አንደኛ፣ በመራብም አንደኛ እንሆናለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው   Getachewasfaw240 [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡