የፓናማ ሰነድ ያስነሳው ማዕበል

አሜሪካዊው የብሔራዊ ፀጥታ አገልግሎት ተቀጣሪ የነበረው ኤድዋርድ ስኖደንና የዊኪሊክስ መሥራች ጁሊያን አሳንጄ የመንግሥታትን ሚስጥር አደባባይ ሲያወጡ ዓለም ተገርሟል፡፡ እነሱ ባወጧቸው ሚስጥራዊ ሰነዶች በመንግሥታት፣ በአገሮች መሪዎችና በአገሮች ግንኙነቶች ይሆናሉ ተብለው ያልተጠበቁ ነገሮች መደረጋቸውም ተሰማ፡፡ ባለፈው እሑድ መጋቢት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ቡድን የወጣው 2.6 ቴራባይት፣ 11.5 ሚሊዮን የተቀረፁ ድምፆችን የያዘውና ‹‹ፓናማ ፔፐርስ›› የተሰኘው ሰነድ ግን፣ በኤድዋርድ ስኖደንና በጁሊያን አሳንጄ ከተለቀቁት መረጃዎች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ግዙፍ መሆኑ፣ በትልልቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየተዘገበ ይገኛል፡፡

ይህ ግዙፍ መረጃ መወጣት የጀመረው ከዓመት በፊት የዓለም ሀብታሞችና ኃያላን ገንዘባቸውንና ሀብታቸውን በስውር እንዲያስቀምጡ ድጋፍ ከሚሰጠው፣ የፓናማው ሞዛክ ፎንሲካ የሕግ ምክር አገልግሎት ድርጅት ለአንድ የጀርመን ጋዜጣ መረጃ ሲደርስ ነበር፡፡

የዚህ የፓናማ ሰነድ ተፅዕኖን ከመሬት መንቀጥቀጥ ጋር ያነፃፀሩ ዘገባዎችም አሉ፡፡ ምክንያቱም የዚህ ግዙፍ መረጃ ተፅዕኖ ለወራትና ለዓመታትም ሊዘልቅ የሚችል ነውና፡፡ ሰነዱ የዓለም አቀፍ ታዋቂ ፖለቲከኞችን፣ የቢዝነስ መሪዎችንና የታዋቂ ሰዎችን ሀብትና ገንዘብን መሰወር ከሚያስችል የገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ በርካታ መረጃዎችን መያዙ ይነገራል፡፡ ይህ ደግሞ ስለ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር ሙስና በርካታ ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው፡፡ እነዚህ ስማቸው የተጠቀሰ ግለሰቦች ግን ሕግን በመተላለፍ ያደረጉት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለመኖሩን በተለያዩ መንገዶች እየገለጹ ነው፡፡

የዓለም ሀብታምና ኃያላን ሰዎች ገንዘባቸውን በስውር እንዲያስቀምጡ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ የተካነ ነው የተባለው ሞዛክ ፎንሲካ ድርጅት፣ በዓለም አራተኛው የባህር ማዶ የሕግ አማካሪ ድርጅት ነው፡፡ የእዚህን ድርጅት መረጃ ያገኘው የጀርመን ጋዜጣ ደግሞ መረጃውን ለዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ኮንሰርቲየም፣ እንዲሁም በዓለም ላይ ለሚገኙ ከመቶ ለሚበልጡ የመገናኛ ብዙኃን እንዲደርስ አድርጓል፡፡ እነዚህ መገናኛ ብዙኃን በቀጣይ ቀናት የፓናማ ሰነድን በመጠቀም ተከታታይ ዘገባዎችን እንደሚሠሩ ይጠበቃል፡፡

መረጃው እንደሚያመለክተው 215,000 ኩባንያዎችና 14,153 ባለጉዳዮች ከሞዛክ ፎንሲካ ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል፡፡ እነዚህ 143 ፖለቲከኞች፣ ቤተሰቦቻቸውና የቅርብ ሰዎቻቸው ከግብር ነፃ በሆኑ የካረቢያን አገሮች ከፍተኛ ሀብታቸውን ለመደበቅ የአማካሪ ድርጅቱን ዕርዳታ ማግኘት መቻላቸውን የፓናማ ሰነድ የያዘው ሚስጥር ነው፡፡

ስማቸው በዚህ ሰነድ ከተጠቀሰው መካከል የአርጀንቲና እንዲሁም የዩክሬን ፕሬዚዳንቶች፣ የአይስላንድና የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የሳዑዲ ዓረቢያው ንጉሥ ሰልማን፣ የቀድሞ የኳታር አሚር ሀማድ ቢን ካሊፋ፣ ፊፋና የእግር ኳሱ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ፣ እንዲሁም ሚሼል ፕላቲኒ እንደሚገኙበት የኮንሰርቲየሙ መረጃ ያመለክታል፡፡ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ጓደኛም ይገኙበታል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ሙስናና ስስት የሚያጋልጠው ይህ የፓናማ ሰነድ፣ ባለፉት አሥር ዓመታት ከታዩት ሁሉ ትልቁ የዜና ሰነድ እንደሆነ እየተገለጸም ነው፡፡ ከግብር ነፃ በሆኑት የካሪቢያን ደሴቶች የሚንቀሳቀሱ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የሕግ አማካሪ ድርጅቶች በሁለት መቶ አገሮች ከሚገኙ ኃያላን ሰዎችና ታዋቂዎች ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል ነው እየተባለ ነው፡፡ የእነዚህን መረጃዎች እውነተኝነት በዓለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ኮንሰርቲየም ሥር ከ100 በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞች ለወራት መርምረዋል፡፡

ቭላድሚር ፑቲንና ታዋቂው የፊልም አክተር ጄኪ ቻንም በፓናማው ሰነድ መጠቀሳቸውን የዘገቡ መገናኛ ብዙኃን አሉ፡፡ በተመሳሳይ የሶሪያ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ፣ የሊቢያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ፣ እንዲሁም የግብፅ የቀድሞ መሪ ሆስኒ ሙባረክ ስምም በፓናማው ሰነድ ተጠቅሷል፡፡ ስማቸው እየተጠቀሰ ያለው ታዋቂ ሰዎች ወይም ባለሀብቶች ብቻ ሳይሆኑ የቅርብ ጓደኞችና ዘመዶቻቸውም ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በሰነዱ ስማቸው የተጠቀሰ በተለያየ መንገድ መረጃውን እያስተባበሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ከቀናት በፊት ነገሩ የሸተታቸው የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ መገናኛ ብዙኃን ፑቲን ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እንዲታቀቡ ቀድመው አስጠንቅቀዋል፡፡ ክሬምሊን የፓናማው ሰነድ ይዘት በመገናኛ ብዙኃን ይፋ ከመውጣቱ በፊት ሰነዱን አጣጥሎታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሙስና የአገሮችን ኢኮኖሚ እያሸመደመደ፣ ድህነትን እያባባሰና የብዙዎች ሕይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ የፖለቲካ መሪዎች የአገራቸውንና የሕዝባቸውን ገንዘብ መዝረፍ ብቻም ሳይሆን፣ እነሱ እንዲመዘብሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ፖሊሲዎችን ጭምር ያፀድቃሉ፡፡ ውጤቱ ደግሞ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሙስና መስፋፋትና የግብር ሥርዓቱን ማበላሸት ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው ጥሩ አዝማሚያ ደግሞ ሰዎች በዚህ የመረጃ ዘመን በተለያየ መንገድ የሚያገኙትን መረጃ ሙስናን ለማጋለጥ፣ መንግሥታት ላይ ተቃውሞ ለማንሳት ጭምር እየተጠቀሙበት መሆኑ ነው፡፡ የፓናማው ሰነድ ደግሞ በዚህ ረገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑ በስፋት እየተዘገበ ነው፡፡