የፓርላማ አባላት ለሕዝብና ለኅሊናቸው ተገዥ የመሆን መብትና የፓርቲ ዲስፕሊን ግዴታ ተቃርኖ

ከፀደቀ 20 ዓመታትን ያስቆጠረው በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአገር ውስጥ የፖለቲካ ተዋናዮች ሙሉ ቅቡልነት አላገኘም፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ተንተኞች እጅግ ዴሞክራሲያዊና የሊበራል አስተሳሰብን የሚያንፀባርቅ ሕገ መንግሥት ነው ይሉታል፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት የፖለቲካ ሥልጣን በምርጫ እንደሚያዝ መደንገጉ ብቻ ሳይሆን፣ ለፖለቲካ ተዋናዮችና ፖለቲካዊ ፍላጐቶች እስከ መጨረሻው  ጥግ ነፃነትን የሚያጐናጽፍ ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ 4 ስለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ነፃነትና ተገዥነት ከሠፈሩት ድንጋጌዎች መካከል አባላቱ በሚወክሉት ፓርቲ አቅራቢነትም ሆነ በግል የፖለቲካ እምነታቸው ለምክር ቤት አባልነት ቢመረጡም፣ ተልዕኳቸው የፖለቲካ ፕሮግራምና ፖሊሲዎቻቸው ላይ ግንዛቤና እምነት ኖሮት ለመረጣቸው የኅብረተሰብ አካል ብቻ እንደማይሆን፣ ‹‹የምክር ቤቱ አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው›› በሚለው አንቀጽ ያልመረጣቸው የኅብረተሰብ ክፍልንም እንደሚወክሉ ያስቀምጣል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ተጠሪነት ወይም ተገዥነታቸውም ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለኅሊናቸው ብቻ ይሆናል በማለትም ንዑስ አንቀጹ ወሳኝ ድንጋጌ ያስቀምጣል፡፡

ከዚህ ባለፈ ወይም ከላይ የተገለጸውን የተጠያቂነት ወሰን ለማስከበርም በቀጣዩ ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ ‹‹ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰስም፡፡ አስተዳደራዊ ዕርምጃም አይወሰድበትም፤›› በማለት የእያንዳንዱን የሕዝብ ተመራጭ የፖለቲካ ነፃነት በግልጽ ያስከብራል፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት ከላይ በተገለጸው ድንጋጌ ለፓርላማ አባላት የሚሰጠው ፖለቲካዊ ነፃነት የምክር ቤቱ አባላት ያለ ፍርኃትና ያለፓርቲ ተፅዕኖ የኅሊና ፍርዳቸውን እንዲሰጡ፣ የሕዝብ ቅሬታ እንዲያነሱ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም ፓርላማው የፖለቲካ ሐሳቦችና አማራጮች እንዲሁም መፈጸሚያ ሥልቶች መወያያ መድረክ እንዲሆንና ሥራ አስፈጻሚውን የመንግሥት አካል የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነታቸውን የምክር ቤቱ አባላት እንዲወጡ ያለመ ድንጋጌ ነው፡፡ በምክር ቤቱ የሕግ ማውጣት ዋነኛ ኃላፊነት ረገድም የሚወጡ ሕጐች ሕጋዊ አስተዳደርን የሚፈጥሩ መሆናቸውን፣ በሌላ አነጋገር የሕገ መንግሥቱ የበላይነትን የማይሸረሽሩ መሆናቸውን፣ አባላቱ ፖለቲካዊ ነፃነት ኖሯቸው እንዲያረጋግጡ የተቀመጠ መሆኑንም ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት ፀድቆ ሥልጣን በምርጫ መያዝ ከጀመረ 20 ዓመታት አልፈው የአምስተኛው ዙር አጠቃላይ ምርጫ ዘንድሮ 21ኛውን ዓመት አስጀምሯል፡፡ ባለፉት የምርጫ ዘመናት የሕዝብን ውክልና አግኝተው ወደ ፓርላማው ከገቡ የግል ወይም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ይልቅ፣ የገዥው ፓርቲ ተወካዮች ከላይ የተገለጸውን ሕገ መንግሥታዊ መብት ተጠቅመው የፓርቲ ዲሲፕሊን ጫናን ሰብረው የኅሊና ፍርዳቸውን ሰጥተዋል ወይ የሚለውን መገምገም የተሻለ ሚዛን ያነሳል፡፡

ወ/ሮ ብርቱካን ይባላሉ፡፡ በሦስተኛው ዙር የምርጫ ዘመን የኢሕአዴግ መሥራች ፓርቲ ከሆኑት አንዱ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ብአዴን) ወክለው በሕዝብ የተመረጡና ፓርላማውን የተቀላቀሉ አባል ናቸው፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው አገር አቀፍ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት፣ በብሔራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን አመራሮች በ1999 ዓ.ም. ኅዳር ወር ለፓርላማው ቀርቧል፡፡

በቆጠራው ውጤት መሠረት የአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ 77 ሚሊዮን እንደሆነ፣ ይህም ቀደም ከተገለጸው ግምት ጋር የሚጣጣም እንደሆነ ነገር ግን በቆጠራው ውጤት መሠረት የአማራ ክልል ሕዝብ 17.2 ሚሊዮን ሆኖ እንደተገኘ፣ ይህም በስታትስቲክስ ባለሥልጣን ከተገመተው 19.6 ሚሊዮን ያነሰ መሆኑ በኮሚሽኑ ጸሐፊና የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በነበሩት ወ/ሮ ሳሚያ ዘካሪያ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

በወቅቱ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር የብአዴን ሊቀመንበር የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሰ ቢሆኑም፣ የብአዴን አባሏ ወ/ሮ ብርቱካን ሪፖርቱን ክፉኛ ለመተቸትና ለመቃወም የተቸገሩ አይመስሉም፡፡

በተለይ የአማራ ሕዝብ ቁጥር በሁለት ሚሊዮን ሊቀንስ የቻለበት ምክንያት የተገናኘው ከኤችአይቪ ጋርና ከስደት ጋር በተያያዘ ነው የሚል ምክንያት መቅረቡ የፓርላማ አባሏን አበሳጭቷቸዋል፡፡

በዚህ ሪፖርት ላይ ተቃውሞ ካቀረቡ የፓርላማ አባላት መካከል አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙት የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ቢሆኑም፣ የወ/ሮ ብርቱካን ከተለመደው የፓርቲ ዲሲፕሊን ወጥቶ መናገር ግን የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡

በመሆኑም ወ/ሮ ብርቱካን በሁለት ነገር ይታወሳሉ፡፡ አንድም የፓርቲ ዲሲፕሊን ጫናን ሰብረው የተሰማቸውን በመናገራቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ግን ወ/ሮ ብርቱካን የሰላ ትችታቸውን ከሰነዘሩ በኋላ ተመልሰው ወደ ፓርቲ ዲሲፕሊን አፎት መሸሸጋቸው ነው፡፡ በሪፖርቱ ላይ ሐሳቦችና ተቃውሞዎች ከተንሸራሸሩ በኋላ ሪፖርቱን ወደ ማፅደቅ ሲገባ ወ/ሮ ብርቱካን ሪፖርቱ እንዲፀድቅ በመደገፍ ከፓርቲ ጓዶቻቸው ጋር ተመሳስለዋል፡፡

ይህ የፓርቲ ዲሲፕሊን ተፅዕኖ በተለይ አሁን ማለትም ፓርላማው ሙሉ በሙሉ በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር በሆነበት ወቅት፣ አሳሳቢ እንደሚያደርገው የበርካቶች እምነት ነው፡፡

ፓርላማው በአንድ ርዕዮተ ዓለም ተከታዮች በተሞላበት ወቅት በፓርቲ ዲሲፕሊን መታጠር፣ ፓርላማው በሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ላይ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እንዳያደርግ፣ እንዲሁም የተለያዩ ሐሳቦችና አማራጮች መንሸራሸሪያ መድረክ እንዳይሆን ያደርገዋል የሚሉ ሥጋቶችን ይንፀባረቃሉ፡፡

የፓርቲ ዲሲፕሊን በዘንድሮው ፓርላማ

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ጽንሰ ሐሳብን እስከ ታችኛው እርከን በማድረስ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ከአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት  በማውጣት፣ የአውራ ፓርቲ ሥርዓትን በኢትዮጵያ ቢያንስ ላልተወሰነ ጊዜ መፍጠር ተልዕኮው አድርጐ መንቀሳቀስ መጀመሩን የፓርቲው ልሳን ያመለክታል፡፡ በዚህም ከ1997 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የምርጫ 2002 ዓ.ም. ውጤት በፍፁም የበላይነት መደምደሙን ይገልጻል፡፡ ይባስ ብሎ በዚሁ ስትራቴጂ የተመራው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በ2007 ዓ.ም. የተደረገውን አጠቃላይ ምርጫ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን መቶ በመቶ አሸንፏል፡፡ ይህ አዲሱ ፓርላማ ባለፈው መስከረም 2008 ዓ.ም. ሥራውን በይፋ በመጀመር የአገሪቱን መንግሥት መመሥረቱ ይታወሳል፡፡

ፓርላማው የመንግሥት መመሥረት ሒደቱን ባካሄደ በቀጣዩ ውሎው የተመለከተው የራሱን የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 3/1998 ነበር፡፡ በዚህ ደንብ ላይ በርካታ ማሻሻያዎችን በማድረግ ፓርላማው መቶ በመቶ በኢሕአዴግና በአጋር ድርጅቶች አባላት መሞላቱ የሚያመጣውን ውስንነት ለመሙላት ጥረት አድርጓል፡፡ ዋነኛ ከሚባሉት ማሻሻያዎች መካከል ሕዝቡና የተለያዩ ሕዝባዊ አደረጃጀቶች፣ እንዲሁም የብዙኃንና የሙያ ማኅበራትን ከመንግሥትና ከምክር ቤቱ ጋር የሚወያዩበትንና የሚሳተፉበትን ሁኔታ በአሠራርና በአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ውስጥ እንዲካተት አድርጓል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ይህንን ደንብና ይዘቶቹን ለሕዝብ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡ ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በዚሁ ጉዳይ ላይ ከአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሕግ ፋኩልቲ ተወካዮችና ከብዙኃን ማኅበራት ጋር ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ ላይ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ናቸው፡፡ በርካቶች ከፓርላማ በሚተላለፍ ቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀርባ በጥቁር መነጽራቸው ያስታውሷቸዋል፡፡

አቶ አስመላሽ ሕውሓት ደርግን ለመገርሰስ ባደረገው ትግል ውስጥ ትልቅ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ በጦርነት ላይም የዓይን ብርሃናቸውን ጨምሮ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

የአቶ አስመላሽ ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ አቶ መለስ አማካይነት በሱዳን የትምህርት ዕድል ከተመቻቸላቸው ታጋዮች አንዱ ነበሩ፡፡

አቶ አስመላሽ በሕግ ዕውቀታቸው የሚደነቁ ብቁ የፖለቲካ አቋም ያላቸው እንደሆኑ የማያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ ለረዥም ዓመታት በፓርላማው የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አስመላሽ፣ በዚህ ዓመት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ አባልና በሚኒስትር ማዕረግ በፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ናቸው፡፡

በዕለቱ የፓርላማውን ደንብ ባወያዩበት ወቅት ለነበረ ታዛቢ በደንቡ ውስጥ የእርሳቸው አሻራ እንዳለ መገንዘብ አያቅተውም፡፡ ፀድቆ ሥራ ላይ መዋል ከጀመረ ሁለት ወሮች ያልሞሉትን ከመቶ ገጾች በላይ የያዘ ደንብ ዝርዝር ድንጋጌዎች ሳይደናቀፉ በቃላቸው ያብራራሉ፡፡

ከዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ከቀረቡ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎችና የአቶ አስመላሽንም ቀልብ ከገዙ ጥያቄዎች መካከል፣ ‹‹መቶ በመቶ በኢሕአዴግና በአጋሮቹ በተሞላው ፓርላማ ውስጥ የፓርቲ ዲሲፕሊን ታክሎበት ፓርላማው ተልዕኮውን እንዴት መወጣት ይችላል? የክትትልና ቁጥጥር መርህ ገደል አይገባም ወይ?›› የሚሉ ይገኙበታል፡፡

አቶ አስመላሽ ለቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች በሰጡት የ55 ደቂቃ ምላሽና ማብራሪያ 20 ደቂቃ የሚሆነውን ጊዜ የፈጁት ለዚሁ ወሳኝ ጥያቄ መልስ በመስጠት ነው፡፡

‹‹አስፈጻሚውንና ሕግ አውጪውን አንድ ፓርቲ የሚቆጣጠርበት አጋጣሚ ስለተፈጠረ ብቻ የሥልጣን ክፍፍል፣ አስፈጻሚውን የመከታተልና የመቆጣጠር መርህ ሥራ ላይ አይውልም ብሎ ማስቀመጥ በተግባርም በንድፈ ሐሳብም የሚቻል አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡

ዋናው ነገር የገዥው ፓርቲ አባላት በፖሊሲና በፕሮግራም ደረጃ ልዩነት ይዘው አይከራከሩም ለማለት እንደሆነ፣ ከዚህ ውጪ ባሉ የአፈጻጸም ጉዳዮች ዙሪያ ሐሳብ አንስተው እንዳይከራከሩ የሚገድባቸው እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

አሁን ባለው ፓርላማ የተመረጡ የገዥው ፓርቲ አባላት በአንድ ፓርቲ ፖሊሲ ቢከራከሩ ድራማ ነው የሚሆነው ያሉት አቶ አስመላሽ፣ ከዚያ አልፎ የሚለውጠው ነገር አለመኖሩን ያስረዳሉ፡፡ ለዚህ የሰጡት ምክንያት ደግሞ ሁሉም የፓርቲውን ፕሮግራምና ፖሊሲ ለማስፈጸም አምነው ተቀብለውትና ተወዳድረው የተመረጡ በመሆናቸው፣ ልዩነት በሌላው ነገር ላይ መከራከር አያስፈልግም የሚል ነው፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖ

በጽሑፉ መግቢያ ላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የፓርለማ አባላት ተገዥነት ለሕዝቡ፣ ለሕገ መንግሥቱና ለኅሊናቸው ነው፡፡

የፓርላማ አባላት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተገዥነታቸው ለሕዝቡ እስከሆነና ያለምንም ተፅዕኖ የኅሊና ፍርድ እንዲሰጡ ሕገ መንግሥታዊ መብት ተሰጥቷቸው በፓርቲ ዲሲፕሊን መገደብ እንደማይገባቸውና ውሳኔዎች በድምፅ ብልጫ የሚያልፉ እስከሆነ ድረስ፣ የአባላቱን ሕገ መንግሥታዊ መብት መገደብ ተገቢ እንዳልሆነ በውይይቱ ወቅት ተነስቶ ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄ አዘል አስተያየት ምላሽ የሰጡት አቶ አስመላሽ ግን፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አይቃረንም በማለት ተከራክረዋል፡፡

ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን፣ ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ጉዳይ በፓርቲ ተለይቶ የተሰጠ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ መሆኑን አቶ አስመላሽ ይጠቅሳሉ፡፡ የፓርላማ አባላት በሌላ በኩል ተገዥ የሚሆኑት ለሕዝብ ነው የሚለው ድንጋጌም ከፓርቲ ዲሲፕሊን ጋር አይጋጭም ይላሉ፡፡

‹‹ሕዝቡ የገዥው ፓርቲ ፖሊሲና ፕሮግራሞች ይጠቅሙኛል ብሎ ነው የሚመርጠው፡፡ ስለዚህ የገዥው ፓርቲ አባላት እዚህ የሚመጡት አብዛኛው ሕዝብ የተቀበለውን ፖሊሲና ፕሮግራም ለማስፈጸም ነው፡፡ ስለዚህ ተቃርኖ የለውም፤›› በማለት ሞግተዋል፡፡

ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ ነው ሲባልም ተመሳሳይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አስመላሽ፣ የገዥው ፓርቲ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የሚቀዱት ከሕገ መንግሥቱ በመሆኑ ተቃርኖ የለውም ብለዋል፡፡

የፓርላማ አባላት ለኅሊናቸው ተገዥ ናቸው የሚለውን በተመለከተም ከፓርቲ ዲሲፕሊን ጋር አይቃረንም በማለት ይከራከራሉ፡፡ አንድ ግለሰብ የአንድ ፓርቲ ፖሊሲና ፕሮግራምን ለማስፈጸም ፓርቲውን ሲቀላቀል፣ ብሎም በፓርላማ አባልነት ሲመረጥ ለኅሊናው ፍርድ የተስማማ ስለሆነ ነው በማለት የሚከራከሩት አቶ አስመላሽ፣ ‹‹ለኅሊናው የማይስማማ ከሆነ ማድረግ ያለበት ከፓርቲ መውጣት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የፓርቲ ዲሲፕሊን አንድምታ

አቶ አስመላሽ እንደሚሉት የፖሊሲና የስትራቴጂ ጉዳይ ሲመነጭ በፓርቲ መድረክ አቋም ይያዝበታል፡፡ ‹‹ፓርቲው በራሱ መድረክ ተወያይቶ አቋም የያዘበት ፖሊሲና ፕሮግራም ወደ ፓርላማ ሲመጣ የተለየ አቋም መያዝ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አንድ የፓርላማ አባል ሐሳብ የመግለጽ ነፃነት አለኝ ብሎ ቢከራከርና ቢወያይ እንኳን፣ በድምፅ መስጠት ወቅት የተለየ ድምፅ መስጠት አይቻልም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

‹‹የፓርቲ ዲሲፕሊን ሁሌም ይኖራል፡፡ ይህ መኖሩ ከሥልጣን ክፍፍል ጋር አይጋጭም፡፡ የክትልልና ቁጥጥር መርህን አይጥስም፤›› ያሉት አቶ አስመላሽ፣ ‹‹ለኅሊናዬ ፍርድ አልተስማማኝም የሚል አባል ፓርቲውን ለቆ የራሱን መንገድ መፈለግ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች የፓርቲ ዲሲፕሊን ፓርላሜንታዊ ሥርዓት በሚከተል የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ መኖሩን ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በይዘቱ ፈጽሞ ሊበራል በመሆኑ ከፓርቲ ዲሲፕሊን መርህ ጋር ይቃረናል ይላሉ፡፡

‹‹ዲሲፕሊን ቃሉ እንደሚያስረዳው ቅጣትን ያስከትላል፡፡ ዲስፕሊን ካለ ቅጣት አለ፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ግን የፓርላማ አባላት በሚሰጡት ድምፅ ወይም በሰጡት አስተያየት ምክንያት አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንኳን አይወስድባቸውም ይላል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የለውም፤›› በማለት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ተንታኝ ተቃውሟቸውን ይገልጻሉ፡፡

የተለያዩ አገሮች ወደ አውራ ፓርቲ ሥርዓት የተሸጋገሩት በተመሳሳይ መንገድ ነው የሚሉት ተንታኞቹ፣ ኢሕአዴግም እየፈጠርኩ ነው የሚለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የተቀመጡ መሠረታዊ መርሆዎችን እንዳይጥስ ሥጋት እንዳይገባቸው ያመለክታሉ፡፡ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ የሆነ ፓርቲ አገር እንዲያስተዳደር ያለመው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ ከሕገ መንግሥቱ ይልቅ ለገዥው ፓርቲ ታማኝ የሆኑ የፓርላማ አባላትን ይዞ ህልሙን ሊያሳካ አይችልም ሲሉም ኢሕአዴግ አሠራሩን እንዲፈትሽ ይጠይቃሉ፡፡