የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ በጣም ተደስቻለሁ

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለረዥም ዓመታት ሲያከራክር የነበረውን በቦንጋ ማዘጋጃ ቤትና በእኔ መካከል የተፈጠረው የሕግ ሒደትና በመጨረሻም ለተከበረው ምክር ቤት ለሕገ መንግሥት ትርጉም ያቀረበውን አስመልክቶ ትርጉም እንደሚያስፈልገው በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡

ለአንድ ዜጋ ከዚህ በላይ የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ የግለሰብ ጉዳይ ነው ብሎ ሳያጣጥል ከቦታው ድረስ በመጓዝ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ መወሰኑ በሕገ መንግሥታችን እንድኮራ አድርጎኛል፡፡ ከእንግዲህ የሚቀረው አጠቃላይ ውሳኔውንና የተነሱትን ጉዳዮች ይዞ ለአፈጻጸሙ ወደ ፍርድ ቤቶች መሄድ ስለሆነ ፍትሕ አገኝበታለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡

  • (ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል)
  •  

ልማትና ጥፋት አብረው አይሄዱም

አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛትነት ተከፋፍለው በነበረ ጊዜ ኢትዮጵያንም ለመያዝ ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርገዋል፡፡ በወቅቱ የነበሩት የአገሪቱ መሪዎችና ሕዝባችን አገሪቱን ለመከላከል ሲሉ በርካታ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ አፄ ዮሐንስ በተደጋጋሚ የመጣባቸውን ወራሪ ጦር አሸንፈው በመጨረሻም ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ አፄ ምኒልክ ተደጋጋሚ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ፈጥረዋል፡፡ አድዋ ላይም ታሪካዊ ድል አስመዝግበዋል፡፡ ይኼ የሕዝብና የመንግሥት አመራር ጥምር ውጤት ነው፡፡

አፄ ምኒልክ ጠላት በጦርነት ብቻ ሳይሆን በተለያየ ዘዴ ገብቶ አገራቸውን ችግር ላይ እንዳይጥል ፈረንጆችን የሚከታተሉት በጥርጣሬ ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የዲፕሎማቲክ ተቋማት ግንባታ የአውሮፓ መሪዎች ለኤምባሲዎቻቸው የሚሆን የመኖሪያና የሥራ ቦታ ምኒልክን ሲጠይቋቸው በጣም ግር ብሏቸው ነበር፡፡ ለጠያቂዎቻቸው የሰጡት ምላሽም ‘ለፈረንጅ መሬት ሰጥቼ እኔስ ምን ልገዛ፣ ሕዝቡስ በምን ሊኖር ነው?›› የሚል ጥያቄያዊ ምላሽ ነበር፡፡ ጉዳዩ የዓለም ሕግ መሆኑን ሲረዱት ግን ዘዴኛውን የጦር ሚኒስትራቸውን ሀብተጊዮርጊስን አስጠርተው ለጉዳዩ መላ እንዲያበጅለት ጠየቁት፡፡ ሀብቴም በጉዳዩ ካሰቡበት በኋላ ‹‹ጃንሆይ መቼም ፈረንጅ ጊዜና መግቢያ ቀዳዳ ከሰጠነው አገራችንን ከመውረር አይመለስም፡፡ ጉዳዩ የማይቀር ከሆነ ግን ድንበሩ ሊለዋወጥ የማይችልና በውል የታወቀ፣ የእኛ ሰው የማይሰፍርበትን ገደላ ገደልና ጠፍ መሬት ይሰጠው፡፡ በዓይነ ቁራኛ የሚከታተላቸውንም ሰው እናድርግበት፤›› አሉ፡፡ በዚያ ዘመን ከአገራችን ጋር ግንኙነት የነበራቸው አገሮች ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እንግሊዝና ሩስያ ነበሩ፡፡ በምክክሩ መሠረትም በቀበና ወንዝና በየካ ተራራ የተከለለ ወጣ ገባ መሬት ተሰጣቸው፡፡ ለጥበቃውም መኖሪያቸው በዚያው አካባቢ ሆነው ራስ አባተ በሚስጢር ተመድበው ክትትል እንዲያደርጉባቸው ተወሰነ፡፡ አፄ ምኒልክ የትም ቦታ ቢሰጣቸው የሚጐዳ ሆኖ ሳይሆን በረጅም ጊዜ በፈረንጆች የሚመጣው ተንኮል የሚያስከትለውን ጉዳት ከማሰብና ቦታውን የጦር መሣሪያ ማከማቻ እንዳያደርጉት በመሥጋት ነው፡፡

በአሁን ጊዜ ላይ ሆነን ስናስበው የአፄው ሥጋት ወሰኑን ያለፈ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ መማር የሚገባን ትልቅ ትምህርት አለ፡፡ አሁን ዓለም አንድ መንደር ሆናለች፡፡ ሕዝቡም ከአንዱ የአኅጉር ጫፍ ወደ ሌላው የአኅጉር ጫፍ እየተዘዋወረ የሚሠራበትና የሚኖርበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ በተለይም ሀብታም አገሮችና ሕዝቦች ገንዘባቸውን በተለያዩ አገሮች ውስጥ ኢንቨስት እያደረጉ የሚሄዱበትን አገር ጠቅመው እነሱም የማያልቅ ሰፊ ሀብት እየዛቁ ነው፡፡ በዚህ የኢንቨስትመንት ሥራ በርካታ አገሮች መዋዕለ ንዋይ ወደ አገር እንዲፈስ በማድረግ ለአገራቸው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

 ኢንቨስትመንት ሁልጊዜ በሰጥቶ መቀበል መርኅ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኢንቨስተሩም ኢንቨስት የሚያደርግበት አገርም የየራሳቸውን ጊዜያዊና ዘላቂ ጥቅም የሚያገኙበትን ስልት አስቀምጠው ነው በውል የሚታሰሩት፡፡ ሁለቱም ይኼ ጥቅም አንድም ሳይጓደል ሊያስጠብቅላቸው የሚችል የየራሳቸው መዋቅርና ለአገሩ ተቆርቋሪ የሆኑ ብቃት ያላቸው ሰዎች ያስፈልጓቸዋል፡፡

በአሁን ጊዜ ኢንቨስትመንትን በመሳብና አገሪቱ ለማደግ ከፍተኛ ፍላጐት ካላቸው ታዳጊ አገሮች መካከል አገራችን አንዷ ናት፡፡ መንግሥት ለውጭ ኢንቨስተሮች በሩን ወለል አድርጎ ከፍቶ መሄድ ከሚገባው በላይ እየሄደ ሕጐችን እያሻሻለ፣ በቂ ድጋፍና ማበረታቻ እያደረገ ይገኛል፡፡ የውጭ ዲፕሎማሲውም የተቃኘው በዚሁ ዙሪያ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ያላቸውም ለዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ለኢኮኖሚው አጋዥ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የመሳሰሉት ፍሬ ነገሮች ናቸው፡፡ ይኼ በሁሉም ዓለም የሚደረግ ለአገር ዕድገትም ቁልፍ መሣሪያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኢንቨስትመንቱ የአገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሊሆን የሚችለው የተጠና፣ በሕግ የሚመራና በቂ ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግበት በባለሙያዎች የተገነባ ማኔጅመንት ሲኖረው ነው፡፡ ወደ አገራችን ብዙ ኢንቨስተሮች መግባታቸው ሳይሆን ሁሉም በታሰበው ደረጃና መጠን ሥራ ፈጥረዋል? የቴክኖሎጂ ሽግግሩም ሆነ የውጭ ምንዛሪ ማስገባቱ ምን ይመስላል? ብሎ መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህ ጉድለት ለመኖራቸው ማዕድን ሚኒስትር ለፓርላማ ያቀረበው ሪፖርትና ዋናው ኦዲተር የሰጠውን መግለጫ መስማቱ በቂ ነው፡፡ ለመሆኑ መንግሥት ራሱ ባቋቋመው አካል ተመርምረው ጉልህ ጥፋት የተገኘባቸው መሥሪያ ቤቶች የማስተካከያ ዕርምጃ በመውሰድ ሕዝቡ እንዲያውቀው ካላደረገ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ጥረት እያደረግኩ ነው ማለት እንዴት ይቻለዋል?

መንግሥት ለአበባ እርሻ ባለፉት 15 ዓመታት በቂ ትኩረት ሰጥቶ በርካታ የውጭ ዜጐች ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች በአብዛኛው አሁን እያጨቃጨቀ ካለው የፊንፊኔ ዙሪያ ሰፋፊ ቦታዎችን ተረክበዋል፡፡ የባንክ ብድር ተመቻችቶላቸዋል፡፡ በተቻለ ሁሉ የመሠረተ ልማት አውታሮች ተሟልቶላቸዋል፡፡ ያለቀረጥ  በርካታ የመገልገያ መሣሪያዎች እንዲያስገቡ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ነገር ግን  ኩባንያዎቹ በየዓመቱ ምን ያህል ቶን አበባ ወደ ውጭ እንደላኩ፣ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማስገባት እንደሚገባቸውና ምን ያህል እንዳስገቡ፣ ከመንግሥት የሚፈለግባቸውን ልዩ ልዩ ገቢዎች ሙሉ በሙሉ ከፍለው፣ ግዴታቸውን በአግባቡ አሟልተዋል ብሎ አፍ ሞልቶ የሚናገር ያለ አይመስልም፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በተመለከተም በርካታ የአገሪቱ ወጣት በእርሻ ሙያ ተመርቆ ያለሥራ በሚቀመጥበት አገር፣ የአበባ እርሻ ቴክኖሎጂ ከአንድና ሁለት ኩባንያዎች ብቻ ትምህርትና ሥልጠና ወስደው ቴክኖሎጂውን የራስ ማድረግ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድንነው? የእርሻ ሥራው ግዙፍ ማሽነሪዎችና ውስብስብ ቴክኖሎጂ የለበትም፡፡ ይልቅስ የሚቀጠሩት ሠራተኞች ትምህርት ኖሯቸው ነገ ይኼንን ሥራ የራሳቸው እንዲያደርጉ ኩባንያዎቹ የሚፈልጉ አይመስልም፡፡ ባለሀብቶቹ የሚቀጥሯቸው ሠራተኞች በአብዛኛው ቴክኖሎጂውን ሊያሸጋግሩ የሚችሉትን ሳይሆን ተራ የቀን ሠራተኞችን ነው፡፡ እስካሁን ያለው ስታትስቲክስ የሚያሳየውም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በዚህ ዓይነት ሁሉንም ኢንቨስትመንት ብናይ በርካታ ህፀፆች ይገኙባቸዋል፡፡

አሁን ከተሠሩት ዘመናዊ የቢራ ፋብሪካዎች ብንወስድ፣ ቀድሞ ከነበሩት ፋብሪካዎች በጣም የተለየ ነው፡፡ የቀድሞው ብዙ የሰው ጉልበት የሚፈልግ ሲሆን፣ ለዜጐች የሥራ ዕድልን በስፋት ይፈጥራል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያሉት ፋብሪካዎች ግን በአብዛኛው በኤሌክትሮኒክ ኃይል የሚጠቀሙ በመሆኑ በጣት የሚቆጠሩ ባለሙያዎች ያለሰው ጉልበት የሚያንቀሳቅሷቸው ናቸው፡፡ ስለዚህም የሥራ ዕድል የመፍጠሩ ሁኔታ ከቀድሞው በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡

ፋብሪካዎቹን ለማስፋፋት ግን ከመንግሥት ሰፊ መሬት ይረከባሉ፡፡ ሚሊዮን ብሮችን ተበድረው በውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉትን ያስገባሉ፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማለት ዘመናዊ ፋብሪካዎችን ከእስያ ወይም ከአውሮፓ ነቅሎ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አይደለም፡፡ ይልቅስ የእኛን ልጆች ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ማዋሃድ ማለት ነው፡፡ አስተሳሰባቸውን ጭምር ከቢሮክራሲ ሥራ አላቆ ወደ ምርታማነት መቀየር ማለት ነው፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን ፋብሪካዎች ሥሪታቸውንና ምንነታቸውን ከሥር መሠረቱ አውቆ ወደ ራስ ሀብት መቀየር መቻል ማለት ነው፡፡ በአንድ ቢራ ፋብሪካ ውስጥ የሚመረተው ምርት በመጨመሩ በዘመኑ ቴክኖሎጂ የሚሠራው ፋብሪካ ውስጥ የሚሠሩ ዜጐች ዋና ሥራቸው የመጫንና የማውረድ እንዲሁም ከመጋዘን መጋዘን ምርቶችን ማጓጓዝ ከሆነ ይኼ ሒደት ምንም ዓይነት የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳይ የለበትም፡፡

ኢንቨስትመንትን መሳብ ተገቢ ቢሆንም በብዙ ሥራና ድካም ተስቦ የመጣው ኢንቨስተር የመንግሥትን ዕቅድና ፍላጐት ለማሳካት የሚችል የክልልም ሆነ የፌዴራል መዋቅር በበቂ እውቀትና ከሙስና በፀዳ መልኩ ካልተደራጀ ከጥቅሙ ጉዳቱ እጅግ ያመዝናል፡፡

በሐሳብ ደረጃ ከላይ የተጠቀሱትን እንደ አበባ እርሻ ዓይነት ኢንቨስትመንቶች ጥቂት የውጭ ኢንቨስተሮችን ካስገቡ በኋላ ለውጭ ዜጐች ዝግ መሆን አለባቸው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ለእነሱ የሚያደርገውን ድጋፍ ካደረገላቸው ወጣት ምሁራን ተደራጅተው ለመሥራት የሚችሉት ቀላል የእርሻ ሥራ ነው፡፡ የሚገርመው ለዚህ ሥራ የተሰጡ አንዳንድ እርሻዎች በኪሳራ ይሁን በሌላ ምክንያት ተዘግተው እርሻ ማቆማቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ለአንድ የእርሻ ማሳ የተሰጠው አርባ ሔክታር መሬት ቢሆን ሃያ የእርሻ ዲግሪ ያላቸው ምሁራን ተደራጅተው በዚሁ ቦታ ላይ 180 የወተት ላሞችን በቀላሉ ሊያረቡ ይችላሉ፡፡ ይኼ ማለት በቀን ከአራት ሺሕ ሊትር ወተት በላይ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በርካታ የአካባቢ ወጣቶች በተለይም ለሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡

የዚህ ዓይነት በርካታ እርሻዎች ሲኖሩ በምግብ ራስን ከመቻል ጋር የሚኖረውን ትስስር ማየት ተገቢ ነው፡፡ ይኼ አሠራር በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ሺሕ ዶሮዎችንና ዕንቁላል፣ በጐችና ፍየሎች እንዲሁም የንብ እርባታን ወጣቱ ሥራዬ ብሎ እንዲይዘውና አስተማማኝ ገቢ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ለናሙና ያህልም የተዘጉትን የአበባ እርሻዎች ወደ ወጣቱ በማዞርና መንግሥት በቂ ድጋፍ እያደረገላቸው ውጤቱን ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም እንደነዚህ ያሉ ሥራዎችን እየፈጠረ ወጣቶቹን ማበርታት አለበት፡፡ ሌሎች ወጣቶች የሚበረታቱት የተማረው ወጣት ተጨባጭ ሥራ ሠርቶ ወደ አምራችነት ሲለወጥና ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ሲፈጥር ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት የተጠናወተው የኦሮሚያ ክልል ቋሚና ዘላቂ ጉዳዮችን ትኩረት ሰጥቶ ከመሥራት ይልቅ መሬቱን ባለሥልጣኖች ሲቀራመቱት፣ በሙስናና በአማላጅ የክልሉን የተፈጥሮ ሀብት ያለአግባብ ሲያባክኑ ይታያሉ፡፡

በማዕከል ደረጃም የኢንቨስትመንት አፈጻጸም አጠያያቂ የሆኑ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ምንም እንኳን ከአገራችን ሁኔታ አንፃር የእርሻ ኢንቨስትመንት ጠቃሚነቱ ጉልህ ቢሆንም አፈጻጸሙ ሊጤን ይገባዋል፡፡ አንድ ኢንቨስተር 20,000 ሔክታር መሬት እንዲያለማ ቢሰጠው ይኼ ማለት ደርግ ባካለለው የገበሬ ማኅበር አደረጃጀት መሠረት ሃያ አምስት የገጠር ገበሬ ማኅበር ነው፡፡ አንድ አነስተኛ ወረዳ ማለት ነው፡፡ ኢንቨስተሩ ይኼን ቦታ ሙሉ በሙሉ በተሰጠው ጊዜ አልምቶት ከሆነና ለሥራ የሚመጥኑ በርካታ ወጣት ምሁራንን ቀጥሮ በዚያው ልክ የውጭ ምንዛሪ እያስገባ ከሆነ እሰየው፣ ሌላም ይጨመርለት፡፡ ነገር ግን ከተሰጠው መሬት ሩቡን ያህል እንኳ ሳያለማ ጠቅላላው መሬቱ በባለቤትነት ይዞ፣ የሚያመርተውንም ምርት በጠቅላላው ወደ ራሱ አገር ልኮ ባለሙያዎችን ከአገሩ በማስመጣት ባኞ መሬት የራሱን ሕዝብ መቀለብ ማለት ምን ማለት ነው?

ይኼ በአጭሩ ምኒልክ በዚያን ወቅት የጠረጠሩት ነገር ዛሬ ደረሰ ማለት ነው፡፡ ሕዝቡስ በምን ሊኖር? እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እየበዙ በሄዱ ቁጥር ከነጭራሹ ከቁጥጥር ውጭ ይሆኑና ሕዝቡን ለብሶት ይዳርጉታል፡፡ መንግሥት የእነዚህን ሁሉ ችግሮች ምንጭ አውቆታል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፡፡ ከወሬ ውጪ በቁርጠኝነት ሊታገለውና ሊታስተካክለው ግን አልደፈረም፡፡ ‹‹ሳስበው ሳስበው ደከመኝ›› ያለው እረኛ ችግር መንግሥትንም ገጥሞታል፡፡ መንግሥት ወትሮውንም ቢሆን ጥሩ ሕግ ያወጣል እንጂ የመተግበር ችሎታውም ሆነ ቁርጠኝነቱ እስከዚህም ነው፡፡ አንድ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ለማስፈጸም ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለው ጉዳይ መጠናት አለበት፡፡ ለማስፈጸም የማይቻል ሕግ ሰው እስኪገኝለት ቢዘገይ ያለዚያም ቢቀር ይሻላል፡፡

በየስብሰባው ላይ የታይታ ንግግር እየተናገሩ የኢሕአዴግን ልብ የሚያማልሉ ጮሌዎች፣ ዛሬ የአገሪቱ ቁልፍ ሰዎች ሆነዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደ መልአክ ይናገራሉ፣ እንደ ሰይጣን ያስታሉ የሚኖሩት ግን እንደ ሰው ነው፡፡ ለአገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉና የዳበረ አቅም ያላቸው የኢሕአዴግ ሰዎችም ቢሆኑ በእነዚህ አድር ባዮች እየተገፉ ዛሬ ከጨዋታው ሜዳ ውጪ ቆመው ፍጻሜውን ለማየት የሚጓጉ ብዙዎች ናቸው የሚል እሳቤ አለ፡፡

ሁልጊዜ በጐ ነገር ታስቦ ሲሠራ ውጤቱ በጐ ነገር ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ሥራውን እንደሚተገብረው ሰው አስተሳሰብ፣ አቅምና ቅን ልቡና ነው፡፡ የበጐ ሐሳብ ውጤት በጐ ነገር የሚሆነው፡፡ ሕዝብን የሚያስከፋ፣ መብቱን የሚነፍግ፣ የተገኘ ሁሉ ሀብት ለእኔ ይሁን የሚሉ ሹመኞች እስካሉ ድረስ በጐ ነገር መጠበቅ አይቻልም፡፡ መንግሥት አለማለሁ ሲል ባለሥልጣናቱ እበላለሁ ካሉ ልማትና ጥፋት አብረው የሚጓዙ አይደለም፡፡      

(ሳሙኤል ረጋሳ፣ ከአዲስ አበባ)

*********

ማስተካከያ

በሪፖርተር የእሑድ ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ዕትም ‹‹ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው ፋብሪካ 250 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስታፋ ብረት ለማምረት መዘጋጀቱን አስታወቀ፤›› በሚል ርዕስ የወጣው ዘገባ ይታወሳል፡፡ በዘገባው ሲ እና ኢ ብረት ፋብሪካ፣ በዓመት በጠቅላላው 1.4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የብረት ምርቶች የማምረት አቅም እንዳለው ተጠቅሷል፡፡

ሆኖም ፋብሪካው ከ5.5. እስከ 32 ሚሊሜትር ውፍረት ያላቸውን ብረቶች በአንድ ጊዜ በዓመት የማምረት አቅሙ 400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እንደሆነና አንድ ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም ሊኖረው የሚችለው ግን አንዱ የምርት ዓይነት ብቻ በተናጠል ቢያመርት እንደሆነ በመግለጽ ጋዜጣው የተጠቀመበትን አገላለጽ እንዲያስተካክል ጠይቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፋብሪካው ባለቤቶች ከደቡብ አፍሪካ የተመለሱ ባለሀብቶች ብቻ ሳይሆኑ ቻይናውያንም ያሉበት መሆኑ እንዲታወቅ ፋብሪካው በጠየቀው መሠረት ተስተካክሎ እንዲነበብ የሪፖርተር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በአክብሮት ይጠይቃል፡፡