የጽንፈኛ ፖለቲከኞች መርህ አልባነት!

    በኤርሚያስ ባልከው

ይህን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ ምክንያት የሆነኝ ሪፖርተር ጋዜጣ በእሑድ መጋቢት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ቅፅ 21 ቁጥር 1660 ዕትሙ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ የተለያዩ አቋሞች ይዘዋል›› በሚል ርዕስ የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን አስተያየት ካነበብኩ በኋላ ነው፡፡

ሐሳቤን በሁለት ከፍዬ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ በመጀመሪያው ክፍል ጠቅላይ  ሚንስትሩ ከጋራ ምክር ቤቱ አባላት ጋር ያደረጉት ውይይት ላይ እኔም ተሳታፊ የነበርኩ እንደመሆኔ መጠን ያለኝን ሐሳብ ለማቅረብ ሲሆን፣ በሁለተኛ ክፍል ደግሞ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ አንዳንድ የተቃዎሚ ፓርቲ መሪዎች የሰጡት ሐሳብ ላይ ያለኝን አስተያየት ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡

  • ላይ የተነሱ ወሳኝ አጀንዳዎች

ለመድበለ ፓርቲ መጠናከርና መጎልበት ወሳኝ ድርሻ ሊኖረው የሚችለው በመጀመሪያ ደረጃ ሕግ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ስለመደራጀት መብት በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ይህንን ተከትሎ የወጡ የተለያዩ አዋጆች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የምርጫ ሕጉ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ ሕጉና የፓርቲዎችን ሥነ ምግባር ለመደንገግ የወጣው ሕግ ወሳኞቹ ናቸው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስርሩ ጋር የተደረገው ውይይት እነዚህ ሕጐች ያሉባቸውን ጉድለቶች ለማረምና አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ የሚያስችል ማሻሻያ እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚህ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት አዋጆቹ ይሻሻላሉ ወይም አይሻሻሉም የሚል ሳይሆን፣ ፓርቲዎች የተደራጁ ሰነዶች አዘጋጅተው ቀጣዩ ምርጫ ከመድረሱ በፊት ቢያቀርቡ ለመወያየት ፈቃደኛ ነን የሚል ነው፡፡

በተጨማሪም በምርጫ ሥርዓቱም ላይ ቢሆን መነጋገር እንደሚቻልና አሁን የምንከተለው የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት (First Past the Post Representation) ይቀጥል፣ ወይስ ወደ ተመጣጣኝ ውክልና (Proportional Representation) የምርጫ ሥርዓት ይለወጥ፣ ወይስ ሁለቱንም (Mixed) ምርጫ ያካተተ የምርጫ ሥርዓት እንከተል በሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡

ለፓርቲዎች የሚደረግ የፋይናስ ድጋፍን በሚመለከት እስካሁን ያለው አሠራር ሁለት ዓይነት ነው፡፡ የመጀመሪያው ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት ለምርጫ ዘመቻ ከመንግሥት የሚያገኙት የፋይናንስ ድጋፍ ሲሆን፣ ሁለተኛው ለፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክር ቤቶች ውስጥ ያላቸውን መቀመጫ መሠረት በማድረግ መንግሥት የሚሰጠው የፋይናንስ ድጋፍ ነው፡፡

ነገር ግን ይህ በሁለተኛ ደረጃ የተጠቀሰው ድጋፍ በአሁኑ ጊዜ ሕጋዊ ሥርዓትን ይዞ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ከ2002 ዓ.ም. ምርጫ ወዲህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሙሉ በሙሉ የምክር ቤት መቀመጫዎች እንዳያገኙ በመደረጉ፣ የመቀመጫ ብዛትን መሠረት አድርጎ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚሰጥ ድጋፍ የለም፡፡

ይህንን ክፍተት ለመሙላት ሲባል ላለፉት አሠርት ዓመታት ተግባራዊ እየተደረገ ባለው አሠራር፣ ኢሕአዴግ ሙሉ በሙሉ በያዛቸው የምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት ልክ ከመንግሥት የሚያገኘውን ገንዘብ በከፊል ለምርጫ ቦርድ እያስረከበ፣ ምርጫ ቦርድ ደግሞ ለተቃዋሚዎች የሚያከፋፍልበት አሠራር ነበር፡፡

ነገር ግን ይህ አሠራር ሕጋዊ መሠረት የሌለው ተቃውሞ ያስነሳ በመሆኑ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕጋዊነትን በተከተለ አዲስ አሠራር የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ከጠቅላይ ሚንስተሩ ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አጠቃቀምን በተመለከተ በተደረገው ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መሻሻል የሚገባቸው ብዙ ድክመቶች ያሉ መሆናቸውን አምነው፣ ችግሮቹን ለማሻሻል መንግሥት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ስለማቋቋም በተደረገው ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የጋራ ምክር ቤቱ ሥራ በጠንካራ ጽሕፈት ቤት ባለመመራቱ ምክንያት የሚጠበቅበትን ሥራ እስካሁን ሳይሠራ እንደቀረ ጠቅሰው፣ ከአሁን በኋላ የተጠናከረ ጽሕፈት ቤት እንዲኖር ከተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ጋር እየተመካከሩ እንደሆነና ጽሕፈት ቤቱ በአጭር ጊዜ እንደሚቋቋም ገልጸዋል፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው የተለያዩ ሕጎችና በተለያዩ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙርያ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ሊደረግ የሚገባውን ውይይትና ክርክር አስመልክቶ በተደረገው ውይይትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት አስተያየት አበረታች ነበር፡፡ በተደረገው ውይይት ፓርላማው እንዲያፀድቃቸው በሚደረጉ ሕጎች ላይ በፓርቲዎች መካከል አስቀድሞ ውይይት እንዲካሄድ፣ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮችም ላይም ቀጣይነት ያለው ውይይትና ክርክር የሚካሄድባቸው መድረኮች በሚቋቋመው የጋራ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በኩል መመቻቸት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርን አስፈላጊነት በተመለከተ ኢዴፓ በተለየ ሁኔታ ባቀረበው ጥያቄ ዙሪያ በተደረገው ውይይት፣ አገሪቱ የቋንቋና የባህል ብቻም ሳይሆን የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ያለበት አገር እንደመሆኗ መጠን፣ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይም ሆነ በተለያዩ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ አጀንዳዎች ዙርያ ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት ማምጣት የሚያስችሉ መድረኮች ቢፈጠሩ የሚደግፋ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በእኔ አመለካከት ከዚህ በላይ በጠቀስኳቸው ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡዋቸው አስተያየቶችም ሆኑ የገቧቸው ቃሎች በጣም አወንታዊና የሚመሰገኑ ናቸው፡፡ የተገቡት ቃሎች ምን ያህል በተግባር ሊፈጸሙ ይችላሉ? ለሚለው ጥያቄ መልሱን ሁላችንም ወደፊት የምናየው ቢሆንም ኢሕአዴግ ከሚታወቅበት ግትር አቋሞ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጧቸው አስተያየቶች በራሳቸው እንደ በጐ ጅምር ተቆጥረው ሊያስመሰግኑ ይገባል፡፡ ለተገቡት በጐ ቃሎች ተግባራዊነትም የገዥው ፓርቲ ቅን ልቦናና ቁርጠኝነት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ጠንካራ ትግል አስፈላጊ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ሌሎች ተቃዋሚዎች የሰጡትን በተመለከተ

የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በቅርቡ ያደረግነውን ውይይት በማጣጣል አስተያየት የሰጡ የፓርቲ መሪዎችን ከላይ በመግቢያዬ ላይ በጠቀስኩት በዚሁ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ተመልክቻለሁ፡፡ በተሰጠው አስተያየት ላይ ያለኝን የግል አመለካከት እንደሚከተለው ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡ ስለጉዳዩ በጋዜጣው ላይ አስተያየት የሰጡት ሦስት የፖለቲካ መሪዎች ቢሆኑም፣ እኔ ግን በዚች መጣጥፌ አስተያየት ልሰጥ የመረጥኩት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ባቀረቡት ትችት ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የመረጥኩት በዋናነት በሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ ይኸውም፣

1ኛ. ለረጅም ዓመታት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሆነው የምናውቃቸውም ሆኑ ሌሎች መሪዎች የእነሱን አመለካከት ከማዳመጥ የረዥም ጊዜ ልምድ አንፃር እነዚህ ሰዎች ምን እንደሚያስቡ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚያስቡ ጠንቅቀን ስለምናውቅ፣ ለእነሱ የተለመደና አስቀድሞ ለሚታወቅ አስተያየት መልስ መስጠት አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም፡፡

2ኛ. ሰማያዊ ፓርቲ በቅርብ ጊዜ የተቋቋመና የሌሎችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስህተት ላለመድገም የተቋቋምኩ ነኝ በማለት የሚመፃደቅ ፓርቲ በመሆኑ፣ በውስጡም ከሌሎች ፓርቲዎች በተሻለ የወጣቶች ስብስብን የያዘ ፓርቲ ስለሆነ፣ ከሌሎች ፓርቲዎች የተለየና የተሻለ አዲስ ሥልትና አቀራረብ ሊኖረው ይችላል የሚል ትንሽ ተስፋ ነበረኝ፡፡

ነገር ግን ኢንጂነር ይልቃል በሰጧቸው አስተያየቶች በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የነበረኝ መጠነኛ ተስፋ ፍፁም ስህተት መሆኑን ስላረጋገጥኩኝ፣ በዚህ ምክንያት የተሰማኝን አዘኔታ (Disappointment) መግለጽ አለብኝ ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡ በኢንጂነር ይልቃል ላይ ብቻ ማተኮር የመረጥኩት፡፡

ውይይቱ ለኢሕአዴግ የሕዝብ ግንኙነት ከመሥራት ያለፈ ፋይዳ የለውም ከሚለው የኢንጂነር ይልቃል ትችት ብነሳ፣ ሁልጊዜ እንደዚህ ብሎ መደምደም ባይቻልም ካለፈው ልምዳቸን በተደጋጋሚ እንዳየነው ኢሕአዴግ እንደዚህ ዓይነቱን ውይይት ለሕዝብ ግንኙነት ሥራ ሊጠቀምበት አይችልም ብሎ መከራከር አይቻልም፡፡ አሳምሮ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ ውይይቱን ለሕዝብ ግንኙነት ሥራ ይጠቀምበታ ብሎ በማሰብ ብቻ ከኢሕአዴግ ጋር የሚደረግን ውይይት ሁሉ ማጣጣልና አንቋሾ ማቅረብ፣ እነ ኢንጂነር ይልቃል ከሌሎች ጽንፈኛ የፖለቲካ አመለካከት ካላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስህተት ያልተማሩ መሆኑን የሚያሳይ እጅግ የተሳሳተ ሥልት ነው፡፡

ምክንያቱም ኢንጂነር ይልቃል፣ ‹‹ኢሕአዴግ ከእሱ ጋር የሚደረጉ ውይይቶችን ለሕዝብ ግንኝነት ሥራ ይጠቀምባቸዋል፤›› ከሚል ተገቢ ግምታቸው ተነስተው፣ ‹‹ስለዚህ ከኢሕአዴግ ጋር ምንም ዓይነት ውይይት ማካሄድ የለብንም፤›› ወደሚል መደምደሚያ ደርሰው ከሆነ ከፊታቸው ያለው አማራጭ የሰላማዊ ትግልን አቁመው አርፈው መቀመጥ፣ ወይም ወደ ውጭ አገር ተሰደው ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ድርጅቶች ጋር መቀላቀል ነው፡፡

ምክንያቱም አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አደርጋለሁ የሚል ድርጅት ከኢሕአዴግ ጋር በየትኛውም ጉዳይ ላይ አልወያይም ብሎ ውሳኔ ላይ ከደረሰ የትም ሊደርስ አይችልም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ ላይ የደረሰ ፓርቲ በምርጫ ተወዳድሮ ከኢሕአዴግ ጋር በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ሊከራከርም፣ በምርጫ ተወዳድሮ የፓርላማ መቀመጫ ካሸነፈም ፓርላማ ገብቶ ከኢሕአዴግ ጋር ሊወያይና ሊከራከር አይችልም፡፡

እንዲህ ዓይነቱ አውዳሚ ሥልት የ1997 ዓ.ም. የቅንጅት ስህተትን ከመድገም ውጪ ሊያመጣ የሚችለው ውጤትም የለም፡፡ በእርግጥም የሰሞኑን የሰማያዊ ፓርቲ ውስጣዊ ሽኩቻ ስንታዘብ የወደፊት የፓርቲው ዕጣ ፈንታ ከመበተንና ከመጥፋት የተለየ እንደማይሆን እያየን ነው፡፡ ኢንጂነር ይልቃል በተቃዋሚዎችና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል የተካሄደውን ውይይት መገምገም የነበረባቸው በውይይቱ ላይ የተነሱት አጀንዳዎች ምን ያህል ለአገራችን ዴሞክራሲ ሒደት መጐልበት አስፈላጊ ናቸው? ከሚለው ጥያቄ ተነስተው መሆን ነበረበት እንጂ፣ ውይይቱ ለኢሕአዴግ ሕዝብ ግንኙነት ካለው ፋይዳ ጋር በተያያዘ መሆን አልነበረበትም፡፡ በአገራችንም ሆነ በዓለማችን ማንኛውም ውይይትና ድርድር የሚካሄደው ከሕዝብ ግንኙነት ካለው ጠቀሜታ አንፃር አይደለም፡፡ ከዚህም አልፎ በተቀናቃኝ ፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ውይይቶችና ድርድሮች የሚካሄዱት ውጤት እንደሚያስገኙ አስቀድሞ የተረጋገጠ በመሆኑም አይደለም፡፡ ይልቁንም በማንኛውም ሁኔታ ከማንኛውም ተቀናቃኝ ኃይል ጋር ችግሮችን በውይይትና በድርድር ለመፍታት መጣርና መታገል የሰላማዊ ትግል ‹‹ሀሁ›› በመሆኑ ነው፡፡

ሁለተኛ የኢንጂነር ይልቃል ትችት፣ ‹‹በጋራ ምክር ቤቱ አባላት ኢሕአዴግን ከማጀብ የተለዬ ፋይዳ የላቸውም፤›› የሚል ነው፡፡ ይህ ትችት በጋራ ምክር ቤቱ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለየ ደካማ አስመስሎ የተሰጠ ትችት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ‹‹የኢሕአዴግ አጃቢ›› የሚለው ተራ ፍረጃ ከአገራችን የግራ ፖለቲካ ባህል ጋር ተቆራኝቶ የኖረ አላስፈላጊ ትችት ቢሆንም፣ በጋራ ምክር ቤቱ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች በሙሉ ጠንካራዎች ናቸው ብሎ መከራከር ግን አይቻልም፡፡

በአንፃራዊነት ከአማራጭ ሐሳብም ጋር ሆነ ከድርጅታዊ ጥንካሬ አንፃር ‹‹ደካማ›› ሊባሉ የሚችሉ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ነገር ግን የኢንጂነር ይልቃል ትችት ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ የመጀመርያው ሁሉንም በምክር ቤቱ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች በጥቅሉ ‹‹ደካሞች›› እንደሆኑ አድርጐ መተቸት ተገቢ አይደለም፡፡ ሁለተኛ የፓርቲዎቹ ደካማነት እውነት ሆኖ ቢገኝ እንኳ፣ ውይይቱን በጭፍን ለማጥላላት ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡

ምክንያቱም በአንድ የፖለቲካ ውይይት ወይም ድርድር ላይ መገኘት ያለባቸው ጠንካራ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው የሚል ሕግ የለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሌሎችን አሳንሶ ራስን ከፍ ከፍ አድርጐ ለማቅረብ የሚደረግ ሙከራ፣ ከብልህ ሳይሆን ከግልብ ፖለቲከኞች የሚመነጭ አስተሳሰብ ነው፡፡

ሦስተኛ ኢንጂነር ይልቃል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚገኙ ፓርቲዎች ላይ ደፋር ትችት ሲያቀርቡ ቢታይም፣ የፓርቲዎችን ድክመትና ጥንካሬ የሚመዝኑበትን መመዘኛ ምን እንደሆነ ሊገልጹ አልሞከሩም፡፡ በእኔ እምነት አንድ ፓርቲ ጥንካሬውም ሆነ ድክመቱ ሊለካ የሚችለው በሚያራምደው አማራጭ ሐሳብና በውስጣዊ ድርጅታዊ ጥንካሬው ነው፡፡ በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት የኢንጂነር ይልቃል ፓርቲ ራሱን እንደ ጠንካራ ቆጥሮ ሌሎቹን እንደ ደካማ ለመኮነን የደፈረበትን ሞራል ከየት ነው ያገኘው? ለምሳሌ ከላይ በጠቀስኳቸው ሁለት መመዘኛዎች መሠረት ሰማያዊ ፓርቲ በምክር ቤቱ ውስጥ ከሚገኘው ከኢዴፓ የበለጠ ጠንካራ ነው ሊባል ይችላል? እንደሚታወቀው ኢዴፓ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ዝርዝር አማራጭ ሐሳቦችን በማቅረብ የሚታወቅ፣ እንዲያውም ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተሻለ አማራጭ ሐሳብ አመንጪና አመላካች ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ ፓርቲ ነው፡፡

የሚያራምዳቸው አማራጭ ሐሳቦች ከራሱ አመራርና አባላት አመንጭቶ ለሕዝብ የሚያቀርብ እንጂ፣ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ በውጭ አገር የሚኖሩ ደጋፊዎች ከገንዘብ ጋር አያይዘው የሚልኩለትን ሐሳብ የሚያስተጋባ ፓርቲ አይደለም፡፡ ከድርጅታዊ ጥንካሬ አንፃር ኢዴፓ እንደማንኛውም በአገሪቱ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደካማ ቢሆንም፣ በአንፃራዊነት ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ሲነፃፀር ግን የተሻለ ድርጅታዊ ጥንካሬ ያለው ፓርቲ ነው፡፡

ኢዴፓ ድርጅታዊ ጥንካሬውን በየጊዜው የገጠሙትን ችግሮች ተጋፍጦ በማለፍም ሆነ፣ በአገሪቱ እስካሁን በተካሄዱ አገራዊ ምርጫዎች ከማንኛውም ፓርቲ የተሻለ ተሳትፎ በማድረግ ያስመሰከረ ድርጅት ነው፡፡ በአንፃሩ ሰማያዊ ፓርቲ ግን ገና በተመሠረተ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ድርጅታዊ ህልውናውን ጠብቆ መቀጠል ተስኖት እየተፈረካከሰ መሆኑን እያየን ነው፡፡

አመራሩም አባላቱም በተለያዩ የሥነ ምግባርና የውስጥ ቅሌት እርስ በእርስ ተካሰው የጠዋት ጤዛ መሆናቸውን እያየን ነው፡፡ ኢንጂነር ይልቃልም ሆኑ ሰማያዊ ፓርቲ ገና ምኑንም ሳይጨብጡ በትዕቢት ተወጥረው ሌሎችን ለማንኳሰስ ሲሞክሩ ማየታችን እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡

ሦስተኛው የኢንጅነር ይልቃል ትችት፣ ‹‹በምክር ቤት ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ ገንዘብ የሚቆርጥላቸው ድርጅቶች ናቸው፤›› የሚል ነው፡፡ ኢንጅነር ይልቃል እውነታውን ሳያውቁት ይቀራሉ ብዬ ባላምንም፣ ኢሕአዴግ እስካሁን ከኪሱ አውጥቶ በምክር ቤቱ ውስጥ ላሉ ተቃዋሚዎች ምንም ዓይነት ገንዘብ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ኢሕአዴግ በፓርላማው ውስጥ ባለኝ መቀመጫ መሠረት ከመንግሥት ሊሰጠኝ ይገባ የነበረ ገንዘብ በከፊል ተቀንሶ በጋራ ምክር ቤቱ ውስጥ ላሉ ፓርቲዎች ይሰጣቸው አለ እንጂ፣ ከራሱ ካዝና አውጥቶ ገንዘብ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ በምክር ቤቱ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች የሚሰጣቸው ገንዘብ ከኢትዮጵያ መንግሥት ካዝና ወጪ የተደረገ ነው፡፡

ከመንግሥት ካዝና የሚወጣ ገንዘብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገኝ ገንዘብ ነው፡፡ ከዚህ ገንዘብ ተካፋይ ለመሆን የተቀመጠው መሥፈርት ደግሞ የጋራ ምክር ቤቱ አባል ሆኖ መገኘት ብቻ ነው፡፡ ነገ ሰማያዊ ፓርቲ በውይይትና በድርድር እምነት ኖሮት የጋራ ምክር ቤቱ አባል ለመሆን ቢወስን የገንዘቡ ተካፋይ ሊሆን ይችላል፡፡ በእኔ እምነትም ሕዝባችን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ገንዘብ የማዋጣት ባህል ችግርም ሆነ ገዥውን ፓርቲ በመፍራት ማውጣት በማይችልበት አገር፣ ከውጭ አገር በሚመጣ ገንዘብ የጽንፈኛ ፖለቲከኞች አጀንዳ ተሸካሚ ከመሆን ይልቅ ከኢትዮጵያ መንግሥት ካዝና ገንዘብ መቀበል የተሻለ ነው፡፡

ሰሞኑን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገው አንድ ውይይት፣ ‹‹ፓርቲዎች ከመንግሥት ሊያገኙ የሚገባው የገንዘብ ድጋፍ ምን ዓይነት ሕጋዊ አሠራር እንዲኖር ይደረግ?›› የሚል ነው፡፡ ማንኛውም በጎ አስተሳሰብ ያለውና የሚሠራውን የሚያውቅ ፓርቲ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር እንዲጠናከር መደገፍ እንጂ መቃወም አይገባውም፡፡

በአጠቃላይ ለኢንጂነር ይልቃል ያለኝ ምክር የእኔ ሐሳብና መስመር ብቻ ነው ትክክል  ብሎ ሌሎች የመረጡትን ሐሳብና መስመር ማንቋሸሽ እስካሁን በትግሉ ውስጥ ለቆዩ ፓርቲዎች አልጠቀማቸውም፡፡ የማይጠቅም ቅድመ ሁኔታ እያቀረቡ ራስን ከውይይትና ከድርድር መድረክ ማራቅ፣ ከዚያም ከምርጫ ተሳትፎ ራስን ማግለል፣ ሰላማዊ ትግሉን አጥላልቶ አገር ጥሎ መሰደድ ምናልባት ለራስና ለቤተሰብ ጠቅሞ እንደሆነ እንጂ፣ ለትግሉና ለአገር ያስገኘው ጥቅም የለም፡፡ ያን ስህተት መድገም አይጠቅምዎትምና ራስዎን ቆም ብለው ይጠይቁ፡፡   

  • ፡- ጸሐፊው የኢዴፓ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው ermiasbalkew [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡