የገቢ ግብር መሰወር

   በተካ መሓሪ ሓጎስ

ይህ ጽሑፍ ከባለፈው ዕትም የቀጠለ ነው፡፡ ባለፈው ዕትም ስለ ተጨማሪ እሴት ታክስ ስወራ ምንነት እንዲሁም የተጨማሪ እሴት ታክስ መሰወርን ስለሚያቋቁሙ ድርጊቶች በተወሰነ መልኩ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ፡፡ በአሁኑ ጽሑፌ ደግሞ ስለ ገቢ ግብር ስወራ ምንነት ላይ ግንዛቤ ሊፈጥር በሚችል መልኩ አቀርበዋለሁ፡፡

የገቢ ግብር ማለት አንድ ሰው በሚያገኘው ገቢ ላይ የሚጣልና የሚሰበሰብ ቀጥተኛ ከሆኑ የግብር ዓይነቶች ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ በአገራችንም የገቢ ግብር ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥቱና የፌዴሬሽኑ አባል የሆኑ ክልሎች በሕገ መንግሥቱ በተሰጣቸው የታክስ ሥልጣን ክልል ሥር የየራሳቸው የገቢ ግብር ሕጐች አውጥተው በሥራ ላይ አውለዋል፡፡ የገቢ ግብርን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94፤ ደንብ ቁጥር 78/1995 እና ሌሎች መመርያዎችን በማውጣት የገቢ ግብር ከግለሰቦችና ከድርጅቶች በመጣልና በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡

ያደጉ አገሮች አብዛኛው ዜጋና ተቋማት በግብር ከፋይነት የሚይዝ መሠረተ ሰፊ የሆኑ የግብር ዓይነቶች በመያዝ ይታወቃሉ፡፡ በተቃራኒው በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ካላቸው ማኅበራዊ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች የተነሳ የራሳቸውን ሀብት በአግባቡ አሟጠው የማይጠቀሙና ኢኮኖሚያቸው ከሚያመነጨው ሀብት የሚሰበስቡት ግብር አነስተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ያለው የታክስ ሥርዓት ከዓለም አቀፍ መሥፈርቶች አንፃር ሲገመገም የዳበረ የታክስ ፖሊሲ አሠራር የሚጐድለው፣ ዝቅተኛ የሆነ የግብር ሕግ ተገዥነት የሚታይበት እንዲሁም ደካማ የሆነ የግብር አስተዳደር ሥርዓት ያለው መሆኑ በዘርፉ ባለሙያዎች ይገለጻል፡፡

አገሮች ወጪያቸውን በራሳቸው የውስጥ ፋይናንስ እንዲሸፈን ለማድረግ እያንዳንዱ አገር በተናጠል እንዲሁም እንደ ዓለም አቀፍ የልማት አጀንዳ ተይዞ በርካታ እንቅስቃሴዎች ሲደርጉ ቆይተዋል፡፡ ምክንያቱም አገሮች የራሳቸውን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ካዳበሩ ዘላቂ የሆኑ የልማት ሥራዎች ለማከናወን፣ ድሃ ተኮር የሆኑ ፖሊሲዎች ለማስፈጸም፣ መልካም አስተዳደር ለማስፈን፣ ተጠያቂነት ያለው የመንግሥት አሠራር ለማጐልበት፣ ዴሞክራሲ ለማስፈን፣ ጠንካራ መንግሥታዊ ተቋማት ለመፍጠር፣ አገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣትና አገራዊና ዓለም አቀፋዊ የልማት ግቦች ለማሳካት ያስችላል፡፡ ስለዚህ አገሮች ጠንካራ የታክስ ሥርዓት በመፍጠር ኢኮኖሚያቸው ከሚያመነጨው ሀብት ግብር በአግባቡ የመሰብሰብ አቅም መፍጠር አለባቸው፡፡ ስለ አገራችን የታክስ ሥርዓት በተመለከተ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የሚታይ ደካማ የሆነ የታክስ ሥርዓት የሚገልጸውና ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት አንፃር የሚፈለግ ግብር በመሰብሰብ በኩል ብዙ የሚቀረው መሆኑ መግለጽ በቂ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደካማ አፈጻጸም እንደ ምክንያት ሊጠቀሱ ከሚችሉት ውስጥ የገቢ ግብር መሰወር ድርጊት አንዱ ነው፡፡

የገቢ ግብር መሰወር ጽንሰ ሐሳብ

በአገራችን ያሉት የግብር ሕጐች ላይ ግብር አለመክፈል በወንጀል የሚያስጠይቅበት ሁኔታ በተመለከተ በግልጽ የሚያስቀምጡ አይደሉም፡፡ ከዚህ የተነሳ ግብር ያልከፈለ ሁሉ በወንጀል መጠየቅ አለበት የሚል አስተሳሰብ በብዙዎች ዘንድ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽነት እንዲፈጠር አለማድረግ ግብር ከፋዮች ላልተፈለገ እንግልት እንዲዳረጉ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል ሕጉ በአግባቡ ተተርጉሞ ሥራ ላይ ካልዋለ በአገሪቱ ዝቅተኛ የግብር ሕግ ተገዥነት  እንዲፈጠር ዕድል ይሰጣል፡፡ በሌሎች ሕጐችም እንደሚቀመጠው በሕግ አድርግ ወይም አታድርጉ የሚለው ትዕዛዝ በማለፍ ሕጉን በተላለፋ ሰዎች ላይ የሚያመጣው ኃላፊነት መኖሩ የግድ ነው፡፡ እንዲህ ካልሆነ ሕጉ አስገዳጅነት የሌለው ጥርስ አልባ አንበሳ ያደርገዋል፡፡ ሕግ መተላለፍ የሚያስከትለው ኃላፊነት ፍትሐ ብሔራዊ ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት ሁለቱም በአንድ ላይ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከዚሁ አንፃር የገቢ ግብር አለመክፈል የወንጀል እንዲሁም የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት ስለሚያስከትሉ ጥፋቶች በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 ላይ ተቀምጠዋል፡፡ የገቢ ግብር አለመክፈል በወንጀል የሚያስጠይቀው በምን ዓይነት ድርጊት እንደሆነ ግን በድንጋጌው የአማርኛው ፍቺ ላይ የተወሰነ የግልጽነት ችግር አለው፡፡ በዚሁ ምክንያት ድንጋጌው በተለያየ መንገድ ተተርጉሞ የተዘበራረቀ አሠራር እንዲኖር አድርጓል፡፡

በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 ላይ የተቀመጠው ግብር ባለመክፈል ስለሚኖር የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስቀምጠው የድንጋገው የአማርኛው ፍቺ ላይ የአንቀፁ ርዕስ ሕግን በመጣስ ግብርን ስላለመክፈል የሚል ሲሆን ዝርዝሩ ደግሞ፣ ‹‹ማንኛውም ግብር ከፋይ ሕግን በመጣስ ገቢውን ያላሳወቀ ወይም የሚፈለግበትን ግብር ያልከፈለ እንደሆነ ወንጀል እንደፈጸመ ይቆጠራል፡፡ ስለሆነም በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 86 መሠረት ገቢውን አሳንሶ በማሳወቁ ምክንያት ከሚጣልበት መቀጮ በተጨማሪ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአምስት ዓመት በማያንስ እስራት ይቀጣል፤›› ይላል፡፡ የአንቀጹ ርዕስ ላይና በዝርዝሩ ውስጥ ሕግን በመጣስ ግብር ስላለመክፈል የሚለው አገላለጽ ምን ለማለት ተፈልጐ እንደገባ ግልጽ አይደለም፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 4 ላይ ማንኛውም በአዋጁ በሚሸፈን ገቢ ያገኘ ሰው በአዋጁ በተደነገገው መሠረት ግብር የመክፈል ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በአዋጁ የተሸፈኑ ገቢዎችን ያገኘ ሰው በሕጉ መሠረት ግብር ካልከፈለ ሕጉን ተላልፈሀል መባሉ አይቀርም፡፡ ነገር ግን የሚፈለግበትን ግብር ካልከፈለ ሊኖር ስለሚችለው የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት በግልጽ ማስቀመጡ የግድ ነው፡፡ ግብር ያልከፈሉ ሁሉ በወንጀልና የፍትሐ ብሔር እንዲጠየቅ ማድረጉ የሕጉ ፍላጐት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለማወቅ ግልጽ ያልሆነው፣ የሕጉ ክፍል ከሕግ አተረጓጐም መርሆች አንፃር ታይቶ ተገቢውን ትርጉም ሊሰጥበት ይገባል፡፡

በመጀመርያ ድንጋጌው የወንጀል ድርጊት የሚገልጽ በመሆኑ ከወንጀል ሕግ የአተርጓጐም መርሆዎች አንፃር መታየት ይኖርበታል፡፡ በአገራችን በ1949 ዓ.ም. በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እንዲሁም በ1997 ዓ.ም. ሥራ ላይ በዋለው የወንጀል ሕግ ላይ በመርህ ደረጃ የሚቀመጠው የወንጀል ሕግ ተጠያቂነት ጥፋትን መሠረት ያደረገ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ ጥፋትን መሠረት ያደረግ የወንጀል ሕግ ተጠያቂነት በሚደነግገው መርህ መሠረት አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ወንጀሉን የሚያቋቁሙ ሕጋዊ ግዙፋዊና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ነው፡፡ በልዩ ሁኔታ ግን ሕግ አውጭው አካል በግልጽ ሲደነግግ ጥፋትን መሠረት ያላደረገ በመከላከያ ማስረጃ ከተጠያቂነት ማምለጥ የሚፈቅድ (Strict liability) እና በመከላከያ ማስረጃ ከተጠያቂነት ማምለጥ የማይፈቅድ ፍፁም የሆነ ኃላፊነት (Absolute liability) የሚደነገጉ የወንጀል ድንጋጌዎች በአንዳንድ ሕጐች የሚቀመጡበት ሁኔታ አለ፡፡ በአገራችን የታክስ ሕጐች ላይ ያለው የድርጅት ሥራ አስኪያጅ የወንጀል ተጠያቂነት ጥፋትን መሠረት ያላደረገ በመከላከያ ማስረጃ ከተጠያቂነት ማምለጥ የሚፈቅድ ጽንሰ ሐሳብ የያዘ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም በአንድ ድርጅት በተፈጸመ የታክስ ወንጀል ሥራ አስኪያጅ በቀጥታ ተጠያቂ የሚያደርግ ሲሆን፣ ሥራ አስኪያጁ በድርጅቱ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት እንዳይፈጸም አስቀድሞ ተገቢውን መከላከል ማድረጉ (Due diligence) ካሳየ የወንጀል ተጠያቂነቱ የሚያስቀር በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በአገራችን የወንጀል ሕግ ተጠያቂነት በመርህ ደረጃ ጥፋት ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚገባ በልዩ ሁኔታ በሕጉ ላይ ከተገለጸ ግን፣ ጥፋትን መሠረት ያላደረገ ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚችል መግለጽ ይቻላል፡፡

ከዚህ አንፃር በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 ላይ የተቀመጠው የግብር አለመክፈል ድርጊት በወንጀል የሚያስጠይቅበት ሁኔታ ግልጽ ባይሆንም፣ ሕግ አውጭው አካል ድርጊቱ የሚያስቀጣው ጥፋትን መሠረት ባላደረገ ሁኔታ ነው ብሎ በግልጽ ካልደነገገው፣ የወንጀል ተጠያቂነቱ ሊኖር የሚችለው ጥፋትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ብቻ ነው፡፡ በወንጀል ሕግ ላይ ጥፋት ለማረጋገጥ ደግሞ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ሕጋዊ ግዙፋዊና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው መገኘት አለባቸው፡፡

እነዚህ ፍሬ ነገሮች ከአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 አንፃር ስናያቸው የሚፈለግበትን የገቢ ግብር አለመክፈል የወንጀል ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ጥፋት ባለው የሐሳብ ክፍል የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት መኖሩ ማስረዳት ግድ ይላል፡፡ በዚሁ ድንጋጌ ላይ ጥፋት ባለው የሐሳብ ክፍል ወንጀል ተፈጸመ የሚባለው ሆነ ተብሎ ድርጊቱ ሲፈጸም ነው፡፡ ምክንያቱም በወንጀል ሕጋችን በቸልተኝነት የተፈጸመ ድርጊት በወንጀል የሚያስጠይቅው በሕጉ ላይ በግልጽ ተደንግጐ ሲገኝ ብቻ ነው /የወንጀል ሕግ አንቀጽ 59(2) ይመልከቱ/፡፡ በአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 ላይ ግብር ያልተከፈለው በቸልተኝነት ከሆነ በወንጀል ሊያስጠይቅ እንደሚገባ በሕጉ ላይ በግልጽ ስላልተደነገገ ግብር አለመክፈል በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርገው ሆነ ብሎ የሚፈለግበትን ግብር ካልከፈለ እንደሆነ አድርጐ መተርጐሙ ከወንጀል ሕግ መሠረታዊ መርሆዎች አንፃር ተቀባይነት ያለው አተረጓጐም ነው፡፡ በሌላ በኩል የድንጋጌው የእንግሊዝኛ ፍቺ ላይ የድንጋጌው ርዕስ “Tax evasion” የሚል ሲሆን፣ ዝርዝር ይዘቱ ላይ ደግሞ “A tax payer who evades the declaration or payment tax commits an offense and in addition to the penalty for the understatement of income referred to in article 86, may be prosecuted and on conviction be  subject to imprisonment for a term of not less than five (5) years” በማለት ተገልጿል፡፡ የድንጋጌው የእንግልዝኛ ፍቺ ላይ ግብር አለመክፈል በወንጀል የሚያስጠይቀው የግብር መሰወር ድርጊት መኖር እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ የድንጋጌው የአማርኛ ፍቺ ላይ ያለው ግልጽነት የመጐደል ሁኔታ መንስዔው በውጭ ባለሙያዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚረቀቁ ሕጐች ወደ አማርኛ ሲተረጐሙ የሚፈጠር የቃላት፣ ሐረጐችና ዓረፍተ ነገሮች በተገቢው የሕግ ቃል ካለመተርጐም የሚፈጠር ችግር ይመስለኛል፡፡ በአጠቃላይ ሊከፈል የሚገባ የገቢ ግብር አለመክፈል  በወንጀል የሚያስጠይቀው ሆነ ተብሎ ለሚፈጸም የግብር መሰወር ድርጊት የሚመለከት መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የገቢ ግብር መሰወር ድርጊት በወንጀል የሚያስጠይቅ ስለሆነ ይህንኑ ለማስረዳት የሚቀርቡ ማስረጃዎችም ስለ ድርጊቱ መፈጸም በቂና አሳማኝ በሆነ ሁኔታ ሊያስረዱ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ ለገቢ ግብር መሰወር ወንጀል ለማስረዳት ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ በታክስ ኦዲተሮች ተሠርተው የሚቀርቡ የታክስ ኦዲት ግኝቶች በዋናነት የሚጠቀስ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት አንድ እውነታ አለ፡፡ ይኸውም አካውንቲንግ ትምህርት የተማረ ሁሉ ወይም ደግሞ ኦዲተር የነበረ ሁሉ ታክስ ኦዲት መሥራት ይችላል ማለት አይደለም፡፡ ታክስ ሕጎች በውስጣቸው የሕግ፣ የአካውንቲንግና የኢኮኖሚክስ ጽንስ ሐሳብ የያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ የታክስ ኦዲት የሚሠሩ ባለሙያዎች ከአካውንቲንግ ትምህርት በተጨማሪ በሥራ ላይ ያሉ የታክስ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች እንዲሁም መሠረታዊ የኢኮኖሚክስ መርሆዎች ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ የሚሠሩ የታክስ ኦዲቶች ጥራት አጠያያቂ ይሆናል፡፡ የገቢ ግብር መሰወር ወንጀል ሊያቋቁሙ ስለሚችሉ ደርጊቶች በማሳያነት ማስቀመጡ በሕጉ ላይ የሚኖር ግንዛቤ ሊያሻሽል ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው tekameharihagos [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡