የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስንል ምን ማለታችን ነው?

በተስፋዬ ንዋይ (የሕግ ባለሙያ)

በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የኅብረተሰብ ከፍል በተደጋጋሚ ከሚነሱ ቃላት ውስጥ ዴሞክራሲ የሚለው የመጀመርያው ረድፍ ላይ የሚገኝ መሆኑ ጥያቄ አይቀርብበትም፡፡ በ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ የተማሪዎች ንቅናቄ በተረገዘበት ጊዜ፣ ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያስፈልግ መሆኑ የተነሳበት ዓላማ ነበር፡፡ በዚያም ‘ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይቋቋም፣ የሕዝቦች መብት የተከበረባት አገር ትገንባ’ በማለት ብዙ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡ ዴሞክራሲ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በማንሳት ሕይወታቸው የጠፋ፣ አካላቸው የጎደለ፣ የወጣትነት ዘመናቸውን በበረሃ፣ ወዘተ ያሳለፉ በርካታ ኢትዮጵያውን እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ይሁንና በዚህ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያስፈልግ ነበር ሲባል ምን ማለት ነው? የምንፈልገው ዴሞክራሲ ምን ዓይነት ባህሪያትን የያዘ ነው? አሁን ያለንበት ሥርዓት በእርግጥም ዴሞክራሲያዊ ነው አይደለም ለማለት መገለጫዎቹ ምንድን ናቸው? በዚህ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን የሚያስችል በቂ ማኅበረሰባዊ ሁኔታዎች የሉም ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች እጅግ አንገብጋቢና ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመንግሥት በኩል በዴሞክራሲ ግንባታ ሥራችን ላይ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ አልሆንም የሚል ሐሰብ የሚነሳ ሲሆን፣ ይህም ገዢ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በሌላ በኩል ይኼን የመንግሥት ሐሳብ የማይቀበሉ አካላት በሚፈለገው ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲ ወይም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽታ ራሱ የለም ብለው ሁሉንም በዜሮ የሚያባዙ አሉ፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ መንግሥት በሚፈለገው ደረጃ ዴሞክራሲ ላይ አልሠራሁም ሲል ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የሚችሉበት አቋም ላይ አይደሉም ማለቱ ነው? ብዝኃነት ያላቸው አስተሳሰቦች ሊስተናገዱ የሚችሉበት ሁኔታዎች መፍጠር አልቻልኩም ለማለት ፈልጎ ነው? የሚሉት መታየት አለባቸው፡፡ በዚህ ጸሐፊ ዕምነት በአገራችን ባለው ዴሞክራሲያዊ ሁኔታና ዴሞክራሲው ሊገለጽባቸው በሚገቡ አስተሳሰቦች ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ በሁሉም አካላት መያዝ ሳይቻል የተሰጠ መሆኑን ነው፡፡ መቼም ቢሆን በዚህ አግባብ ስለዴሞክራሲያዊ ሁኔታው የሚሰጠው አስተያየት አሁን ያለውን፣ ወይም አለ የተባለውን ችግር በበቂ ደረጃ ሊፈታ የሚችልና አገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርስ አይደለም፡፡ ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ በዓለም የሚታወቁ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሞዴሎችና መገለጫዎቻቸው፣ ከእነዚህ ሞዴሎች ውስጥ ለአገራችን ሊጠቅም የሚችለው ሞዴል የትኛው እንደሆነ፣ አገራችን የጀመረችውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የበለጠ ለማስቀጠል መደረግ ያለባቸው ተግባራት ይዳሰሳሉ፡፡

ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ሥርዓት ለምን?

በአሁን ወቅት ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ሥርዓት እጅግ ተፈላጊና ተቀባይነት ያለው ብቻ ሳይሆን፣ ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሌለው መንግሥትና ሕዝብ በጨቋኝና በተጨቋኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ይወሰዳል፡፡ ይኼ ሥርዓት አንድም በቀጥታ ሕዝቡ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት፣ ማለትም ሕዝቡን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ሕዝብ በቀጥታ በሚሰጠው ድምፅ የሚወስንበት ቅርዕ ሊኖር የሚችል ነው፡፡ ይኼን በመሰለ ቅርፅ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች ሁሉንም ማኅበረሰብ የሚመለከቱ፣ ውስብስብ ያልሆኑ፣ ብዙ የጥቅም ግጭቶች የሌለባቸው፣ በቁጥር ጥቂት የሆነ ማኅበረሰቦች ሥራ ላይ ሊያውሉት የሚገባ ሆኖ በቀደምት ዘመናት የነበረ ነው፡፡ ሁለተኛው የሕዝቦች ግንኙነት ውስብስብ በሆነበት፣ ፍላጎቶችን በተለያየ መንገድ ማስተናገድ በሚገባበት ወቅት ሊተገበር የሚችል የዴሞክራሲ ሌላኛው ቅርፅ ነው፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጥቅሉ የሕዝብን ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ቢሆንም፣ ዴሞክራሲ የሚያስፈልገው የሚያመጣው አወንታዊ ውጤት ስላለው ነው፡፡ ወይም አሉታዊ የሆኑ ውጤቶች እንዳይኖሩ ለማድረግ ነው የሚለው መታየት አለበት፡፡ ዴሞክራሲ አወንታዊ የሆኑ ውጤቶች ስለሚያስከትል ይመረጣል የሚሉ ምሁራን እንዲሚያነሱት፣ ለማኅበረሰቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ይሰጣል፡፡ ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ ያስችላል፡፡ በሕዝቦች መካከል ቅራኔዎች እንዳይፈጠሩ የማጣጣምና የማቻቻል ውጤት አለው ይላሉ፡፡ ስለሆነም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚፈጥረው ሕገ መንግሥት ሥርዓቱ በበቂ ሁኔታ ቢዘረጋ ተስፋ ያለው አገርና ማኅበረሰብ መፍጠር የሚያስችል ሲሆን፣ ሕዝቡ ራሱን በራሱ ማስተዳደር የሚችልበት ሁኔታ መፍጠር ከተቻለ ዴሞክራሲያዊ ተስፋ ያለውና ውጤቱ ያማረ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህ አመለካከት ማኅበረሰቡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ተሳትፎ በሚያደርግበት ወቅት፣ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ አወንታዊ ውጤቶችን ሊያስመዘግብ ይችላል ከሚል የሚነሳ በመሆኑ፣ መንግሥት የሕዝቡን ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈልግበት አግባብ ይኖራል፡፡ ስለሆነም ማኅበረሰቡ የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች የመንግሥት ሥልጣን ይዞ የሚገኘው አካል የመቀበል ግዴታ ይኖርበታል፡፡

በሌላ በኩል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚፈለገው የራሱ የሆነ አወንታዊ ጥቅም ስለሚኖረው ሳይሆን፣ የመንግሥት ሥልጣን አንድ ቦታ እንዳይሰባሰብ ለማድረግና መንግሥት ጎጂ የሆኑ ውሳኔዎችን እንዳያስተላልፍ ለማድረግ ነው የሚል፣ ዴሞክራሲን አወንታዊ ውጤት ለማምጣት ሳይሆን አሉታዊ ውጤት ለመቀነስ ሥራ ላይ ሊውል የሚገባ ሥርዓት ነው የሚል ሞዴል አለ፡፡ ስለሆነም ሰዎች ሐሳባቸው እንዲገለጽ የሚፈለገው ሌሎች ጠቃሚ ያልሆኑ ሐሳቦች የበላይነት እንዳያገኙ ስለሚፈለግ መሆኑን፣ ምርጫ የሚካሄደው የፖለቲካ ሥልጣን ከአሸናፊው ይልቅ ሌላ ፓርቲ ቢይዝ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ስለሆነና የመሳሰሉትን የመንግሥት ሥልጣን በመያዝ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶች መቀነስ ይሆናል፡፡ ይኼ ሞዴል በተለይ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሰር ዊንስተን ቸርችል የሚያቀነቅኑት ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን ብዙ ተከታዮች ያሉት ነው፡፡

ይሁንና የሕዝብና የመንግሥት ሥልጣን ይዘው በሚገኙ አካላት መካከል የሚኖረው ግንኙት ምን መምሰል አለበት የሚለው በሁለት ሞዴሎች ሊተነተን የሚችል ነው፡፡ አንደኛው ሞዴል የውክልና ሞዴል የሚባል ሲሆን፣ በዚህ ሞዴል መሠረት የሕዝብ ውክልና አግኝቶ የመንግሥት ሥልጣን የያዘ አካል ሕዝብ ምርጫ በሚያካሄድበት ወቅት የሰጠው ውክልና አለ፡፡ ማለትም ይህን ይህን ተግባር እንድታከናውን እፈልጋለሁ፣ ይህን ተግባር ደግሞ አንተም ሆነ ሌሎች እንዳያከናውኑ እንድታደርግልኝ እፈልግለሁ የሚልበት ነው፡፡ ውክልና ተቀባዩ ደግሞ በዚህ አግባብ ኃላፊነቱን ይወጣል ማለት ነው፡፡ በውክልና የዴሞክራሲ ሞዴል መሠረት መንግሥት የሆነው አካል በምርጫ ወቅት ሕዝቡ የሰጠውን አደራ ብቻ ተቀብሎ በራሱ ሕዝብን ሳይሰማ የሚተገብር ሳይሆን፣ በሁለት የምርጫ ጊዜያት ቢሆን ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ሐሳቦች እየሰማ የሚሠራና ለሕዝብ ፍላጎቶች ምላሽ እየሰጠ ለመቀጠል የሚፈልግ ሞዴል ነው፡፡ ስለሆነም ይኼ ሞዴል በምርጫ ብቻ የሕዝብ ፍላጎት የሚንፀባረቅበት መድረክ የሚመለከት ሳይሆን፣ የሕዝብ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚቀያየር ነው፡፡ በአንድ የምርጫ ወቅት ሕዝቡ የነበረው ሐሳብ በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀያየር በመሆኑ፣ መንግሥት ይኼን ፍላጎት ተገንዝቦ መሥራት ይኖርበታል፡፡

ይህን ሐሳብ ፍሬደሪክ ሳቹር የተባለ ጸሐፊ “Constitutions of Hope and Fear” በሚለው መጣጥፉ እንዲህ ብሎ ይገልጸዋል፡፡ “Issues that are salient at election time may be dis-placed by others that could not even have been imagined during the election, and the speed with which new issues rise, and old ones fall, can make the subjects of electoral campaign debates poor proxies for the issues with which the winning candidate must deal during her term of office.”

ስለሆነም በምርጫ ወቅት መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮች በሌሎች በምርጫ ወቅት ባልታሰቡ ጉዳዮች ሊተኩ የሚችሉበት፣ አዳዲስ ጉዳዮች የሚነሱና የሚወድቁበት ፍጥነት ከፍተኛ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊኖር ስለሚችል፣ በምርጫ ወቅት የተደረጉ ክርክሮች ከምርጫ በኋላ አሸናፊው ወገን በሚያስተናግዳቸው ጉዳዮች ለማሳየት ደካማ መገለጫ ሊሆን ይችላል እንደ ማለት ነው፡፡

ይኼ ሞዴል ለሕዝብ ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑና ተጠያቂነት የማረጋገጥ አሠራሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ የሚመጣ መሆኑ እንደ አወንታዊ ጎን የሚታይ ቢሆንም፣ ይሁንና ትክክለኛው የሕዝብ ፍላጎት የትኛው እንደሆነ መለየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሕዝቡ ፍላጎቶቹንና ምኞቶቹን ሊያቀርብ ስለሚፈልግባቸው ነገሮች በቂ የሆነ ግንዛቤ ኖሮት ማቅረብ ላይ እጥረቶች የሚኖሩ መሆናቸው፣ የሞዴሉን ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡

ሁለተኛው የዴሞክራሲ ሞዴል ትረስቲ ሞዴል የሚባለው ሲሆን፣ በዚህ ሞዴል መሠረት የመንግሥት ሥልጣን ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ያገኘ አካል ማከናወን የሚጠበቅበት፣ በሁለቱ የምርጫ ጊዜያት ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የተለያዩ ሐሳቦችና ፍላጎቶች ከሥር ከሥር እየተከታተለ ለእነዚያ ምላሽ መስጠት አይደለም፡፡ ይልቁንም ከሕዝቡ ጋር ምርጫው በሚካሄድበት ወቅት የገባውን ውል ወይም ስምምነት መፈጸም ብቻ እንደሆነ የሚያስቀምጥ ሞዴል ነው፡፡ ይኼ ሞዴል ሕዝቡ ከአጭር ጊዜ ጥቅም አንፃር የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያነሳና የሚያንፀባርቅ በመሆኑ፣ መንግሥት ማድረግ ያለበት ለእነዚህ ፍላጎቶች በየጊዜው ምላሽ መስጠት አይደለም፡፡ መሠረታዊ የሕዝብ እሺታ ያገኘ በመሆኑ ለሕዝብ ሊጠቅም የሚችል ውሳኔዎች እያሳለፈ የሥልጣን ዘመኑን መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ይኼን ሞዴል ቅርፅ አስይዘዋል ከሚባሉ ልሂቃን አንዱ የሆነው ጆን ስቲዋርት ሚል እ.ኤ.እ. በ1865 የእንግሊዝ ፓርላማ አባል ለመሆን የምረጡኝ ዘመቻ በሚያደርግበት ወቅት፣ ምርጫውን አሸንፎ ፓርላማ የሚገባ ከሆነ በፓርላማው ውስጥ የሚያራምደው ሐሳብ መራጮች በየጊዜው የሚያቀርቡዋቸውን ሐሳቦች አይደለም፡፡ ይልቁንም ራሱ ለሕዝቡ ወይም ለመራጮቹ ይጠቅማል ብሎ የሚያስበውን ሐሳብ ብቻ ያራምዳል፡፡ የመራጮቹ ጥቅም ከአጠቃላይ አገራዊ ጥቅም አንፃር የሚጋጭ ከሆነ፣ አገራዊውን ጥቅም የሚያስቀድም እንደሆነ አውስቶ ነበር፡፡ በዚህም በሕዝቡ ተመርጦ ለአንድ የምርጫ ጊዜ ፓርላማ ቆይቷል፡፡

ይኼ ሞዴል የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ኃይል በየጊዜው ከሕዝብ የሚመጡ ፍላጎቶችን በመመልከት ለእነዚያ ቀጥተኛ ምላሽ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቡ የፍላጎት አቅጣጫዎች የመቀየስና ፍላጎቶችን የመፍጠር አቅም የሚኖረው ነው፡፡ ዘላቂ የሕዝብ ጥቅም የሚያረጋግጥ ሥራ ለማከናወን የሚሞክር መሆኑ እንደ ጠንካራ ጎን የሚታይ ቢሆንም፣ ሕዝብን ለማሳመን በቂ የሆነ አቅምና ተዓማኒነት የሌለው ከሆነ ግን ግጭቶችና አለመግባባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡

ከሁለቱ ሞዴሎች አንፃር ምን እንመስላለን?

በአገራችን ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ፌደራላዊ ሥርዓት በ1987 ዓ.ም ከተመሠረተ በኋላ አገራችን ቢያንስ በሕገ መንግሥት ደረጃ
ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ሥርዓት ብቻ ልትቀበል እንደምትችል ለዓለም አስመስክራለች፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት መሆናቸው፣ ይኼም የሚገለጸው በቀጥታ በሚካሄድ ተሳትፎና በሚመርጡዋቸው ወኪሎች መሠረት ሊሆን እንደሚችል፣ ዜጎች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ በተለይም አባል የሆኑበትን ማኅበረሰብ የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ፕሮጀክቶች ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት ያላቸው መሆኑ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊበተን የሚችል መሆኑ፣ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ሕዝቡ በመረጠው ተወካይ ላይ ዕምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ለማንሳት የሚችል መሆኑ፣ ማንኛውም የምክር ቤት አባል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት የማይከሰስ ወይም አስተዳደራዊ ዕርምጃ የማይወሰድበት መሆኑ በሚታይበት ወቅት ሕገ መንግሥቱ የውክልና ሞዴልን ይበልጥ የሚደግፍ መሆኑን፣ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ የትረስቲ ሞዴል የሚከተል ሕገ መንግሥት ያለን መሆኑ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ዴሞክራሲን እንደ ፍርኃት ማስወገጃ መሣሪያ ሳይሆን እንደ ተስፋ መፍጠሪያ መሣሪያ ይመለከታል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ለመገደብ የሚያስችሉ ብዙ ድንጋጌዎች ያሉት ቢሆንም፣ የመንግሥት ሥልጣን ሕዝብን ሊጠቀም የሚችል ሥራ ሊሠራበት የሚችል እንደሆነና ይኼን ሥራ በተግባር ለመተርጎም ደግሞ የሕዝብ ተሳትፎ መሠረታዊ መሆኑን የሚያትት ነው፡፡ መፍታት የሚፈልገው ችግር በነጠላ ሲታይ የመንግሥት ሥልጣን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ተግባር ላይ መዋሉን ማስቀረት ቢሆንም፣ መሠረታዊ ሐሳቡ ግን በሕገ መንግሥቱ የሚፈጠረው መንግሥት የመንግሥትን ሥልጣን በመጠቀም ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ማረጋገጥ ነው፡፡ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ሲባል ደግሞ፣ መንግሥትን በመፍራት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን መንግሥት ጥሩ ነገር ሊሠራ ይችላል ከሚል ሐሳብ ላይ የሚነሳ ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሕዝብ ተሳትፎ ይበልጥ የሚፈለገው ማኅበረሰብን የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ፕሮጀክቶች ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት ያላቸው መሆኑን የሚያሳየው ድንጋጌ ሲሆን፣ ማኅበረሰቡ አስተያየት እንዲሰጥ መደረጉ አንድም ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸው የተለያዩ ሐሳቦች የራሳቸው ጠቀሜታ ያላቸው በመሆኑ “Wisdom of Crowds” በፖሊሲና በፕሮጀክት አፈጻጸም ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስህተቶችን ለመቀነስ የሚያግድ የሚችል ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማኅበረሰቡ በፖሊሲዎችና በፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፍ መደረጉ ራስን በራስ የማስተዳደር መርህ በበቂ ደረጃ ለማሳየት የሚያግዝ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ አግባብ የተተገበሩ ፖሊሲዎች የሚያመጡት አሉታዊ ውጤት ቢኖር ውጤቱን በጋራ የመቀበል የእኔነት ስሜት (Sociological Legitimacy) እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ መንግሥት የሚያዘጋጃቸው ፖሊሲዎችና ፕሮጀክቶች ላይ ሕዝብ አስተያየት እንዲሰጥ ከተደረገ በኋላ፣ አስተያየቶቹን ሁሉ ተቀብሎ የፖሊሲው ወይም የፕሮጀክቱ አካል ማድረግ አለበት ወይ? አንዳንድ አስተያየቶች የፖሊሲው ወይም የፕሮጀክቱ አስፈላጊነት የማይደግፉ ከሆነ አስተያየት መቀበሉ ብቻ ምን ጥቅም አለው? ማኅበረሰቡ በቀረበው ፖሊሲ ወይም ፕሮጀክት ላይ ተቃውሞ እንዲያቀርብ ሁኔታዎች በመመቻቸታቸው  ብቻ ፕሮጀክቱ ወይም ፖሊሲው በታማኝነት እንዲፈጸም ያደርጋል ወይ? የሚሉት መታየት አለባቸው፡፡ በአንድ በኩል አስተያየት መስጠቱ ብቻ በቂ በመሆኑ የቀረበው አስተያየት ፕሮጀክቱን ሊያስለውጥ የማይችል በቂ ያልሆነ ምክንያት እስከሌለ ድረስ ፕሮጀክቱ መለወጥ የለበትም የሚል የሚቀርብ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የቀረበው ምክንያት በቂ ሆነም አልሆነ የበላይነት ያለው አስተያየት ፕሮጀክቱ እንዲቀር የሚይፈልግ ከሆነ ይህ መተግበር አለበት ሊባል ይችላል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ረቂቅ ተዘጋጅቶ ሕዝብ አስተያየት እንዲሰጥ ከተደረገ በኋላ፣ ሕዝቡ አልፈልግም ቢል በሕገ መንግሥቱ መሠረት መንግሥት ማድረግ ያለበት ምንድነው? አስተያየቱን ተቀብሎ በትረስቲ ሞዴል መሠረት ሕዝቡን ሊጠቅም የሚችል ፕሮጀክት በመሆኑ ይተገብረዋል፡፡ ወይም በውክልና ሞዴል መሠረት ፕሮጀክቱን ይሰርዘዋል፡፡ ክልሉን እየመራው የሚገኘው ድርጅት ኦሕዴድ በገለጻቸው የተለያዩ አቋሞች ላይ ፕሮጀክቱ ሕዝቡን ይጠቅማል ተብሎ የተጀመረ ቢሆንም፣ ሕዝቡ በመቃወሙ ምክንያት ፕሮጀክቱ መሰረዙን የገለጸበት አግባብ ሲታይ የውክልና ሞዴል መተግበሩን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይኼን የውክልና ሞዴል ድርጅቱ ባይተገብረው ማለትም የትረስቲ ሞዴል ቢከተል በኋላ ላይ ሊደርስበት የሚችለውን ችግር በመፍራት ይኼን ውሳኔ ሊወስን እንደቻለ ሊታይ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕዝቡ በፕላኑ ላይ ጥያቄ ያላነሳ በመሆኑ የትረስቲ ሞዴልን በመከተል እየተገበረው እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

ከአምስተኛው አገራዊ ምርጫ በኋላ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያሉ ግንኙነቶች በሚታዩበት ወቅት፣ የውክልና ሞዴል ጎልቶ መታየቱን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ማለትም የውክልና ሞዴል በመተው የትረስቲ ሞዴልን ብቻ መከተል፣ ገዢው ፓርቲ ወደ ፊት ሊኖር ከሚችለው ችግር አንፃር በመመልከት የወሰደው ዕርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡

በአገራችን አምስተኛው አገራዊ ምርጫ ከተካሄድ በኋላ ዓመት ሳያስቆጥር በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በመንግሥት አሠራር ላይ ሕዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ አንስቷል፡፡ ይኼንንም መንግሥት አምኗል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙት እየሻከረ መጥቷል፡፡ ይኼን ሁኔታ በቅርበት የሚመለከቱ አካላት እንደሚያነሱት ከሆነ፣ የተካሄደው ምርጫ በገዢው ፓርቲ በኩል ማጭበርበር የነበረበት በመሆኑ ምክንያት፣ ሕዝቡ በአጭር ጊዜ ተቃውሞውን ሊያነሳ ችሏል፡፡ ስለሆነም ዴሞክራሲያችን ችግር አለበት የሚባለው ሕዝቡ በምርጫ ወቅት ያነሳቸው ጉዳዮችና ፍላጎቶች ምን ነበሩ? አሁን ያለው ደግሞ ምንድነው የሚለው መታየት አለበት፡፡

ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እያነሳቸው ያሉት ጥያቄዎች፣ ተቃውሞዎችና አስተያየቶች በሁለት መንገድ መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ የመጀመርያው ሕዝብ በእርግጥም የውክልና ሞዴል የሆነውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተግበር የሚፈልግ በመሆኑ መንግሥት ልትሰማኝ ይገባል፣ ባለፈው ምርጫ የሰጠሁህ ድምፅ በትረስቲ ሞዴል ብቻ በመንቀሳቀስ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ የፈለግከውን እንድታደርግ የምፈቅድልህ አይደለም፣ እንደነገርከኝ ተግብረው የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥት በዚህ አግባብ ማድረግ የሚጠበቅበት በእርግጥ የተነሱ ጥያቄዎች ሕዝብ በምርጫ ወቅት በመንግሥት ላይ ያለውን ዓመኔታ በገለጸበት አግባብ ታይተው በቅንነት ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ሕዝቡ የትረስቲ ሞዴል ብቻ ሳይሆን የውክልና ሞዴል ላይ ትኩረት አድርጎ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በማንሳቱ፣ የትረስቲ ሞዴል በሚባለው አግባብ የሕዝቡን ቀዳሚ ሐሳብ የማይቀበሉ አስተያየቶች እንዳይቀላቀሉ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ከመነሻው በኮንትራት ለአምስት ዓመታት መርጬሃለሁ የሚለው የሕዝብ ሐሳብ ትክክል አለመሆኑን የሚመለከቱ አስተያየቶች፣ በፊት የተሰጠውን የትረስቲ ሥልጣን በውክልና ሥልጣን ሰበብ እንዳያጠፉት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

የውክልና ወይም የትረስቲ ሞዴል መቼ መተግበር አለበት?

የውክልና ሞዴል ወይም የትረስቲ ሞዴል መተግበር ያለበትን ዓውድ፣ ማኅበራዊ ሁኔታ፣ ጊዜና የመሳሰሉት ታይተው ሥራ ላይ ካልዋሉ የሚፈጥሩት አደጋ ከፍተኛ ነው፡፡ የውክልና ሞዴል የሚባለውን ለመተግበር ሕዝቡ ስለፖሊሲዎች ወይም ፕሮጀክቶች ሐሳቡን በተደራጀ መንገድ የሚያቀርብበት አሠራር መፈጠር አለበት፡፡ ስለፖሊሲዎች ወይም ፕሮጀክቶቹ ጥቅምና ጉዳት፣ ፕሮጀክቶቹ ተዘጋጅተው ከማለቃቸው በፊት ከሕዝቡ ጋር ውይይት መካሄድ አለበት፡፡ ሐሳቦች በተለያዩ አካላት ተደራጅተው የሚመጡበት አግባብ መኖር አለበት፡፡ ከተሰጡ ሐሳቦችና አስተያየቶች ውስጥ መንግሥት የሚቀበላቸው የትኞቹ እንደሆኑ፣ የማይቀበላቸው የትኞቹ እንደሆኑ ገዢው ፓርቲ በምርጫ ወቅት ለሕዝብ ካቀረባቸው ፕሮግራሞች አንፃር ምን እንደሆነ ማሳየት አለበት፡፡ ይኼን ሁሉ ካደረገ በኋላ የቀረበው ፖሊሲ ወይም ፕሮጀክት ላይ ተቃውሞ ከበረታ፣ አንድም ፕሮጀክቱን የመሰረዝ ዕርምጃ በመውሰድ የውክልና ሞዴል ሊተገብር ይችላል፡፡ አለበለዚያም ሐሳቦች እንዲሰጡ በቂ ጊዜና ዓውድ የሰጠ በመሆኑ ፕሮጀክቱን ይተገብራል፡፡

የትረስቲ ሞዴል መተግበር የሚያስፈልገው የመንግሥት ሥልጣን የያዘው አካል ፕሮግራሙን አቅርቦ ሕዝብ የመረጠው በመሆኑ፣ ሕዝቡ የሚያነሳቸው ፍላጎቶች ከተመረጠበት ፕሮግራም አንፃር የሚጋጩ ከሆኑ አስተያየቶቹን ለመቀበል መገደድ ይቸግራዋል፡፡ ኢሕአዴግ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ሥርዓት የሚከተል በመሆኑና ይኼን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሐሳብ አቅርቦ ሕዝቡ ከመረጠው በኋላ፣ የኒዮ ሊብራል የፖለቲካ ኢኮኖሚ መከተል አለብህ በማለት የሚመጣውን አስተያየት ማስተናገድ አይኖርበትም፡፡ ከዚህ በመለስ ባሉ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መጠን፣ ገበያውን በመምራት ሒደት፣ መንግሥት እየወሰደ ባለው ዕርምጃ ከሕዝቡ አስተያየት መቀበል ግን ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል፡፡

መደምደሚያ

በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ድርሻ ያላቸው አካላት በተግባሮቻቸውና በአሠራሮቸው ገደብ እንዳለ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ የሕዝቡ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚቀያየር፣ ሁሉንም የሕዝብ ፍላጎቶች ሊያረካ የሚችልባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደማይችሉ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ፍላጎቶቹ በምርጫ ወቅት ከመረጣቸው የመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አንፃር ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ መንግሥት መተንተንና መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን አገሪቱ ውስጥ ካለው ሕገ መንግሥትና የተለያዩ ሕጎች አንፃር ፍላጎቶቹ እንዴት ተደርገው ሊስተናገዱ እንደሚችሉ ቀድሞ መመልከት አለበት፡፡ ያቀረባቸው አስተያየቶች ሁሉ ውይይት ሳይካሄድባቸው ተቀባይነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መንግሥት ወይም ገዢው ፓርቲ ሰሚ እንጂ የራሱ የሆነ ፕሮግራም የለውም መባል የለበትም፡፡ መንግሥትም ስለተመረጥኩኝ ብቻ የፈለግኩትን በሕዝቡ ላይ መጫን እችላለሁኝ፣ የአምስት ዓመታት ኮንትራት አለኝ በማለት ብቻ ሳይሆን፣ በየጊዜው የሕዝቡ ፍላጎት ምንድነው እያለ እየጠየቀ ለዚህ በሚያገኘው መልስ መሠረት አሠራሩን እያስተካከል መሄድ አለብኝ የሚል ባህል ካልተፈጠረ በስተቀር፣ የውክልና ዴሞክራሲ ሞዴል በቂ ሆኖ ሊሠራ አይችልም፡፡

ሌላውም የሕዝብ ፍላጎት በየጊዜው የሚለዋወጥ መሆኑን በመገንዘብ፣ ለእነዚህ ፍላጎቶች መልስ ሊሰጥ የሚችለው ፍላጎቶቹ በግልጽ ቀርበው አስተያየት ተሰጥቶባቸው መሆኑ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል፡፡ የሕዝብን ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለመረዳት ምርጫ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም፣ ሕዝቡ በተለያዩ መድረኮች ላይ የሚያነሳቸውን ሐሳቦች ከምርጫ ባልተናነስ ትኩረት ሊሰጣቸውና ሊሠራበቸው ይገባሉ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል tiffanymulsa [at] yahoo.com አድራሻቸው   ማግኘት ይቻላል፡፡