የውክልና ሥልጣን ማስረጃ እንዴትና ለምን?

በገዙ አየለ መንግሥቱ

ይህ ርዕሰ ጉዳይ የሕግ ነጥብ ይሁን እንጂ በተለያዩ አጋጣሚዎች አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የሚጠቀምበትና የሚገለገልበት ዋነኛ አገልግሎት መሆኑ  ይታወቃል፡፡ ይህን ርዕሰ ገዳይ ለመጻፍም ያነሳሳኝ በአብዛኛው የማያቸው የውክልና ሰነዶች ይዘታቸው ላይ የሚታዩት መደጋገም እንዲሁም አላስፈላጊ የሆነው የሰነዶች ይዘትን መሠረት ሳይሆን፣ በአንድ አጋጣሚ በዚሁ በአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋነት በሚነሳው የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ቀርቤ ያጋጠመኝ እንግዳ ነገር ነው፡፡ በወቅቱ ከውክልና ሕግ መሠረታዊ ዓላማ ጋር እንዲሁም የውክልና ሕጉ ራሱ ከሚያስቀምጣቸው መሠረታዊ ይዘቶች የማይጣጣም እንግዳ ማስረጃ ተጠይቄያለሁ፡፡

በመሠረታዊነት ውክልና ከሚያስፈልግባቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል ወካይ በአንድ ጊዜ የተለያዩ ድርጊቶችን በተለያዩ ቦታዎች ተገኝቶ መከወን ስለማይችል በቀላሉ ባለበት ቦታ ሆኖ ውክልና ሥራውን ሊከውንለት የሚችል ተወካይ በመወከል በአንድ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ ተግባራትን በተወካዩ አማካይነት ማከናወን መቻል አንዱ መሠረታዊ የውክልና ሥልጣን ማስረጃ ጠቀሜታና አንዱ የውክልና ሕግ ዓላማ ነው፡፡

በጽሕፈት ቤቱ ቀርቤ የውክልና ሥልጣን ማስረጃ ለመስጠት አስፈላጊ የሚላቸውን ሰነዶች ይዤ ቀርቤያለሁ (ጽሕፈት ቤቱ የሚፈልገውን ነው ያልኩት ከልማዳዊው አሠራር አንጻር)፡፡ ከዚያ በኋላም በጽሕፈት ቤቱ ሠራተኛ የውክልና ሰነዱ ይዘት በጥሞና ተነቦ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዳደርግ (ኮሜንት) ተሰጠኝ፡፡ ይህች የውክልና ሥልጣንን የመመርመር ሥልጣን በራሱ በሕጉ ያልተቀመጠች ነገር ግን ሁልጊዜ ወካይ ባይፈልግም በሠራተኞች የምትደረግ ምርመራ በመሠረታዊው የውክልና ይዘት ላይ የሚደረግና በተደጋጋሚ ያጋጠመኝ ጉዳይ ነች፡፡ በዚህም ምርመራ በአንድ ወቅት በስሜ ያለኝን ቤት እንዲሸጥልኝ በማለት ያቀረብኳትን የውክልና ሰነድ የማይንቀሳቀስ ንብረቴን ብለህ ካላስተካከልህ ውክልናዋን አንሠራልህም ተብዬ ከፍተኛ የማስረዳት ሙከራ ባደርግም ሙከራዬ ከንቱ ሆና ማስተካከያዋን አድርጌያለሁ፡፡ በዚህች ነጥብ እንኳን ብንመለከት በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ግለሰቦች ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉበት የማይንቀሳቀስ ንብረት ቤት ብቻ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ስለሆነም ቤት ብሎ የጠቀሰ ግለሰብ የማይንቀሳቀስ ንብረቱን እያለን መሆኑን እየታወቀ የአገላለጽ ልዩነት በመኖሩ ብቻና እኔ በምፈልገው አልመጣችም በማለት ውክልና አገልግሎት አታገኝም ለማለት የሚያስችል የሕግም መሠረት የለም፡፡ ይህችኛዋ ነጥብ በኋላ የምመለስባት ነች፡፡

በቅርቡ ያጋጠመኝ ደግሞ ውክልና ለመስጠት በተለይም መሸጥ መለወጥንና በዋስትና ማስያዝን የሚመለከቱ የውክልና ሥልጣን ማስረጃዎች ለመስጠት ውክልና ሰጪው ግለሰብ የትዳር ሁኔታውን የሚገልጽ ማስረጃ ይዞ ካልቀረበ ውክልናውን በተመለከተ አናስተናግድም የሚል ነው፡፡ ይህ ነጥብ ነው እንግዲህ በሕግ መሥሪያ ቤቱ እንደ ቅድመ ሁኔታ ያላስቀመጠው በመሠረታዊ የውክልና ዓላማን ሙሉ በሙሉ የሚያስተጓጉል ሆኖ ያየሁት፡፡ በመሠረታዊነት ውክልና ሰጪው ግለሰብ (አካል) የተቀላጠፈ አገልግሎት አግኝቶ የሚፈልገውን ተግባራት በአጭር ጊዜ እንዲከናወንለት የሚፈልግ ግለሰብ የጋብቻ ማስረጃ ፍለጋ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ማዘጋጃ ቤት እስከሚዘልቅ እንግልት በመሄድ የተባለውን ተግባር ሳያስፈጽምና የፈለገውን ሳይከናወንለት በመሠረታዊ የንግድም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴዎቹ ላይ ውክልና ባለመስጠቱ መስተጓጎልን የሚፈጥርበት፡፡ በተለይ ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች ያላገባ የሚለውን የጋብቻ ማስረጃውን ማን ይሰጣል በሚለው ጉዳይ ላይ አንዳንድ አካባቢዎች በቀበሌ በመጣ ማስረጃ እንጂ ማዘጋጃ ቤቶች ያላገባ ማስረጃ ሳይሆን ያገባ የጋብቻ ሠርተፊኬት ነው የምንሰጠው በማለት ያላገባ ሠርተፊኬት አይሰጡም፡፡ በመሆኑ አሁን የሰነዶች ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤትም እንዲህ ዓይነት ማስረጃ ሲፈልጉ ያለው ወጥነት የሌለው አሠራር አንዱ ችግር ሆኖ፣ ጽሕፈት ቤቱ የሚፈልገው ደግሞ ከማዘጋጃ ቤት የሚወጣውን (የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ሥራ በጀመሩባቸው ቦታዎች በእነዚህ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ ሠርተፊኬት እንጂ ከቀበሌ የመጣ ፎቶ ያልተያያዘበትን አንቀበልም መባሉ ችግሩን ድርብርብ ያደርገዋል፡፡

ከላይ የተገለጸው ተግባርም በመሠረቱ በውክልና ሕጉ ውስጥም ሆነ በሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ አዋጅ ውክልና ለመስጠት እንደ ቅድመ ሁኔታ ያላስቀመጠው የውክልና ዓላማን የሚጥስ አሠራር ነው፡፡ በመሠረታዊነት ውክልናው ከተሰጠም በኋላ ቢሆን የመሸጥ የመለወጥ ተግባራቱን የሚያከናውኑት ማዘጋጃ ቤት፣ ቀበሌ፣ ወይም መንገድ ትራንስፖርት የሽያጭ ውሉን ከማከናወናቸው በፊት ይህንን ማስረጃ የሚጠይቁ በመሆኑና ይህ ባይሆን እንኳ ውክልናውን በተመለከተ በተለይ ግለሰቡ ያገባ/ያገባች ከሆነች በየራሳቸው በተናጠል በተለያየ ቦታ ቀርበው ውክልናውን መስጠት ስለሚችሉ የጽሕፍት ቤቱ ጥያቄ ፋይዳ የሌለውና ቀልጣፋውን የውክልና አሰጣጥ ተግባር የሚያንዛዛ፤ ውክልናን በፈለጉ ጊዜ የመስጠትን ግለሰቦች መብት የሚገድብ እንዲሁም ውክልና በወካይና በተወካይ ነፃ ፈቃድ የሚከናወን ውል መሆኑን የረሳ አሠራር በመሆኑ ሊስተካከል የሚገባው ነገር ነው፡፡

በመሆኑም አንድ ሰው ከሚኖርበት አካባቢ ርቆ ውክልና ለመስጠት ቢፈልግ እንኳን የተባለውን የጋብቻ ሁኔታ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ ብቻ በሕግ የተጎናጸፈውን መብት የሚያጣበትና በአጠቃላይ በአገር ደረጃ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችንም የሚጎዳ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ያህል እንኳን በውጭ አገር ያለ ግለሰብ ከሚኖርበት አገር ይህንን ማስረጃ ማግኘት ባይችል ውክልና ሳይሰጥ ሊቀርና በአገሩ ማስፈጸም ላይችል ነው ማለት ነው፡፡

ውክልና (እንደራሴነት) ከዚህ የተለየ ብዙ ትርጓሜ ቢኖረውም እንደራሴነት ወይንም የእንደራሴነት ሥልጣን አንድ ተወካይ በወካዩ በተሰጠው የእንደራሴነት ሥልጣን ማስረጃ መሠረት ከሌላ ሦስተኛ ወገን ጋር ስምና ወካዩን በመወከል የተለያዩ ሥራዎችን የእንደራሴነት ሥልጣን ለሰጠው ግለሰብ የሚሠራበት የውል ወይም የሕግ አግባብ ነው፡፡

ሌላው በውክልና ሥልጣን ማስረጃ ላይ በተደጋጋሚ የሚታየውና ያልተገታው ጉዳይ በውክልና ሥልጣን ማስረጃ ላይ በተንዛዛና በአላስፈላጊ ይዘቶች የተሞላው አሠራር ነው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2199 ላይ የተጠቀሰውም ይኸው የእንደራሴነት ትርጓሜ ሲሆን፣ ይህ አንቀጽ ግን በምንም ሁኔታ የውክልና ሥልጣን ማስረጃ ሊይዝ የሚገባውን ይዘት (Content) የሚገልጽ የሕግ አንቀጽ አይደለም፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2203 ላይ የተመለከተው ጠቅላላ የውክልና ሥልጣን በጠቅላላ አነጋገር የተደረገ ውክልና ለተወካዩ በፍትሐ ብሔር ቁጥር 2204 የተቀመጡትን የአስተዳደር ሥራ እንዲፍጽም ከሚያደርገው በቀር ሌላ ሥልጣን አይሰጠውም በሚል ተቀምጧል፡፡ በሕጉ አገላለጽ መሠረትም ከላይ ያስቀመጥኩት የውክልና ሰነድ በጠቅላላው ለተወካይ ጠቅላላ የውክልና ሥልጣን የሚሰጡ ይዘቶች አሉት፡፡ በአንድ የውክልና ሥልጣን ማስረጃ ሰነድ ላይ ወካይ ለተወካይ በማናቸውም የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት ቀርቦ እኔ ላስፈጽም የሚባኝን ጉዳዮች እንዲያስፈጽምልኝ የሚል በጥቅል የተቀመጠ የውክልና ሥልጣን ለተወካዩ ከሰጠ በኋላ ወካዩ በተመሳሳይ የውክልና ሰነድ ላይ በአስተዳደር መሥሪያ ቤት፣ በቀበሌ፣ በክፍለ ከተማ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በከተማ ልማት፣ በውኃ ልማት፣ በመንገድ ትራንስፖርት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ወዘተ. በሚል የሚቀመጡ የውክልና ሥልጣን ማስረጃዎች ከሕጉ ዓላማ አንፃር አስፈላጊ አይመስልም፡፡ ሕጉ ጠቅላላ የውክልና ሥልጣን ማስረጃ ጥቅል በሆነ መንገድ ወካይ ለተወካይ አስተዳደራዊ የሆኑ ጉዳዮችን እንዲያከናውንለት ጥቅል በሆኑ ቃላት የሚሰጠው ሥልጣን ሲሆን፣ በተግባር ግን በውክልና ሰነዶች ላይ እየተዘረዘሩ ያሉት ጉዳዮች የሕጉን ዓላማ የማያሳኩ እንዲሁም ድግግሞሽ የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድ ወካይ ለተወካዩ በማናቸውም መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ መሥሪያ ቤቶች በመቅረብ መፈጸምና ማስፈጸም ያለብኝን ጉዳዮች ሁሉ እንዲያስፈጽምልኝ በሚል የተቀመጠና ለተወካዩ ቢያንስ ጠቅላላ የውክልና ሥልጣን የሚሰጥ ዓረፍተ ነገር ተቀምጦ እያለ ወካይ ወደ ዝርዝራቸው የሚገባባቸው ግን ደግሞ ጨርሶ ሊዘረዝራቸው የማይችላቸውና ያልዘረዘራቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አላስፈላጊ የሆኑና ዝርዝራቸው ያልተካተቱት መሥሪያ ቤቶች ዘንድ ቀርበንም ጉዳያችን ለማስፈጸም አዳጋች የሚሆኑበትን ጊዜ ማሰብ እንችላለን፡፡ በዚህ ሁኔታም ወካይ በተወካዩ አማካይነት እንዲፈጸሙለት የሚፈልጋቸው ጉዳዮች ሊዘገዩ የሚችሉበት ሁኔታም ከመኖሩ በላይ ጭራሹኑ በተባለው የውክልና ሰነድ መሠረት የታለመውን ሥራ ለመሥራት አዳጋች ይሆናል፡፡

ለአብነት ያህልም በአብዛኛው የውክልና ሥልጣን ማስረጃ ሰነድ እንደሚያሳየው ወካዩ ለተወካይ በጠቅላላው በመንግሥታዊ ድርጅትም ሆነ በሕዝባዊ ድርጅት ጉዳዩን እንዲያስፈጽምለት ውክልና የሰጠ መሆኑን ከገለጸ በኋላ ሙሉ (Exhaustive) ያልሆነ የመሥሪያ ቤት ዝርዝሮችን፣ በአስተዳደር መሥሪያ ቤት፣ በቀበሌ፣ በክፍለ ከተማ፣ በቴሌ ኮሙዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት፣ በሞባይል መሥሪያ፣ በውኃ ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ በመብራት ኃይል ባለሥልጣን፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢሚግሬሽን፣ በቤቶች ኤጀንሲ፣ በኪራይ ቤቶች አስተዳደር፣ በመሬት መምሪያ አስተዳደርና በፖሊስ ኮሚሽን መምሪያ በመቅረብ እኔ የማደርገውንና የምፈጽመውን ሁሉ እንዲያስፈጽሙልኝ በማለት የተሰጡት ዝርዝሮች የወካዩንም ሆነ የተወካዩን ሥራ የሚያወሳስቡ፣ የውክልና ሥልጣኑን ግልፅነት የሚያሳጡ ይዘቶች ናቸው፡፡

ከላይ በተገለጸው የውክልና ሰነድ መሠረት የውክልና ሰነዱ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ መሥሪያ ቤቶች ካለ በኋላ የሚሰጣቸው የመሥሪያ ቤት ዝርዝሮች ሙሉ (Exhaustive) ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ ወካዩም ሆነ ተወካይ በውክልና ሰነዱ ላይ ያልተዘረዘሩና በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተቱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሊፈጸም የሚገባው የወካዩ ጉዳይ ቢያጋጥም፣ ተወካይ በዚህ መሥሪያ ቤት ቀርቦ ጉዳዩን ማስፈጸም ይችላል ወይ? መሥሪያ ቤቱም ቢሆን በውክልና ሰነዱ ላይ ወካይ የሰጠው የውክልና ሰነድ ላይ ተወካይ በማናቸውም የመንግሥት ተቋም በመገኘት የሚለው ጠቅለል ያለ የውክልና ቃል እስካለ ድረስ የመሥሪያ ቤቱ ስም ቀጥሎ በተመለከተው የመሥሪያ ቤቱ ዝርዝር ውስጥ ባይካተትም በውክልና ሰነዱ መሠረት ተወካይ የወካይን ጉዳይ እንዲያስፈጽም ሊፈቅድለት ይገባል ወይ? የሚለው ነጥብም መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

በሕጉ መሠረትም በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2204 አንፃር ስናየው ወካዩ ለተወካዩ ጠቅለል ባሉ ቃላቶች እኔን በተመለከተ በማናቸውም መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በመቅረብ ማስፈጸም ያለብኝን ጉዳዮች እንዲያስፈጸምልኝ በማለት የውክልና ሥልጣን ከሰጠውና ጉዳዩ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2205 መሠረት ልዩ የውክልና ሥልጣን ማስረጃ ማቅረብ የሚያስፈልገው ከሆነ፣ የመሥሪያ ቤቱ ስም በዝርዝሩ ውስጥ ባይጠቀስም መሥሪያ ቤቱ በውክልና ሰነዱ መሠረት ለተወካዩ የተባለውን የውክልና ተግባር እንዲያከናውን መፍቀድ እንደሚኖርበት የሕጉ ዋነኛ ዓላማ ይመስላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩም ያልተጠቀሰው መሥሪያ ቤት ሌሎች መሥሪያ ቤቶች በስም መዘርዘራቸው ወካዩ ለተወካይ በስም ያልጠቀሳቸውን መሥሪያ ቤቶች በተመለከተ ግን የውክልና ሥልጣን መስጠት ስላልፈለገ ሊሆን ይችላል በማለት የውክልና ሰነዱን ከመተርጎም የሚያግድ ጉዳይ እንደሌለ መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ የውክልና ሰነድ አረጋጋጩ ተቋም የውክልና ሰነዱን ይዘት በተመለከተ ያለውን ሥልጣንና ተግባር ማየቱ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

ስለ ሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ የወጣው አዋጅ ቁጥር 334/1995 የሰነድ ማረጋገጥ ሥራን በተመለከተ በሚያወራው አንቀጽ 1(1) በግልፅ እንደተጠቀሰው ሰነድ ማረጋገጥ ማለት አዲስ ሰነድ በአዘጋጁ ወይም ጉዳዩ በሚመለከተው ሰው ሲፈረም ማየትና ይኼውም መፈጸሙን በማረጋገጥ በሰነዱ ላይ መፈረምና ማኅተም ማድረግ ነው ይላል፡፡ የውክልና ሥልጣን ማስረጃ ሰነድን በተመለከተም በአዋጁ መሠረት በየደረጃው ሰነዱን ለማረጋገጥ ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት የውክልና ሰነዱን ይዘትና መካተት ያለባቸው ነገረች ማየት ሳይጠበቅባቸው ሰነዱ ሲፈረም ማየትና ይህንን በማረጋገጥ በሰነዱ ላይ መፈረምና ማኅተም ማድረግን እንደ ግዴታ ያስቀመጠ ይመስላል፡፡ ይህ ጉዳይ ከፍትሐ ብሔር ሕጉ ቁጥር 2189 ላይ በተቀመጠው መሠረትም በውል የተገኘን የእንደራሴነት ሥልጣን የሚወስኑት ተዋዋይ ወገኖች እንጂ ሰነዶቹን ለማረጋገጥ ሥልጣን የተሰጠው አካል በውሎቹ ይዘት ላይ ያለው ሥልጣን የተገደበ መሆኑን በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ በሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 334/1995 አንቀጽ 1(1) መሠረትም ሰነድ ማረጋገጥ ማለት አዲስ ሰነድ በአዘጋጁ የሚለው ሐረግ ሰነዱን ሊያዘጋጅ የሚችለው ራሱ የውክልና (እንደራሴነት) ሥልጣን የሚሰጠው ግለሰብ እንጂ ሰነድ አረጋጋጩ አካል እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም በአዋጁ አንቀጽ 4 ላይ እንደተመለከተው የዋስትና ማረጋገጥ ተግባራትንና የአረጋጋጩን ግዴታዎች ሲዘረዝር ሰነድ አረጋጋጩ አካል ለመረጋገጥ የሚቀርቡ ሰነዶችን ሕጋዊነት ማረጋገጥ ያለበት መሆኑን በግልፅ የሚያመለክተ ሲሆን፣ ይህን ግዴታ አንድ ሰው የውክልና ሰነዱን የመመርመር ሥልጣን እንደሚሰጣቸው አድርጎ መተርጎም ይችላል፡፡ በተመሳሳይ አዋጁ በአንቀጽ 13(2) ላይ የሰነድ አረጋጋጩ አካል የሰነዱን ሕጋዊነት ከመመርመር አልፎ የሰነዱን ይዘት ለመለወጥና ለመቀየር እንደማይችል ተቀምጧል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በአብዛኛውና ደንበኞች በተዘጋጀው መሠረት ሞልተው እንዲያቀርቡ ማስደረግ የተለመደው ተግባራዊ አሠራር ሆኗል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የመሥሪያ ቤቶቹ ሥራ የሕግ ዕውቀት የሌላቸውን ደንበኞቻቸውን ከማገልገል አንፃር ጠቀሜታው የጎላ ቢሆንም፣ አሠራሩ በአብዛኛው ከልማዳዊው አሠራር ወጥቶ ሕጉ በሚለው መሠረት ግልፅ፣ ቀላልና ያልተንዛዛ የውክልና ሰነድ ማዘጋጀት ችለዋል የሚለው ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀሬ ነው፡፡

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በአንድ የዞን ሰነዶች ምዝገባ ጽሕፍት ቤት የደሰበትና ምናልባትም ኅብረተሰብ ላይ በውክልና ሰነድ ይዘቶችና ፎርም ምክንያት የሚደርሱ እንግልቶችን ማንሳቱ ጠቀሜታ አለው፡፡ በእነዚህ መሥሪያ ቤቶች አንድ ሰው የውክልና ሥልጣን ማስረጃውን ይዞ ሲቀርብ በአረጋጋጩ አካል ውክልናህን በአንቀጽ 2199፣ 2204፣ 2205፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 58 ወዘተ መሠረት ሰጥቻለሁ የሚሉ አንቀጾች ካልተካተቱ በስተቀር ወይ ፍንክች ውክልናው መስተካከል አለበት በማለት ሰነድ አረጋጋጩ አካል ራሱ ያዘጋጀውን ፎርማት እንዲጠቀሙ ወይም በሚሰጣቸው (Guidance) መሠረት ውክልናውን እንዲያስተካክሉ ያደርጋል፡፡ ይህ አካሄድ ሰነድ አረጋጋጩ አካል ከተሰጠው ሥልጣን በላይ አግባብ ያልሆነ ሥልጣን እንዲኖረው (Exercise) የሚያደርግበት ልማዳዊ አካሄድ እንደሆነ ግልፅ ከሆኑት የሕግ ድንጋጌዎች መረዳት እንችላለን፡፡

በሚገርም ሁኔታ በውክልና አረጋጋጩ አካል በውክልና ሰነዱ ላይ እንዲጠቀሱ የሚፈለጉት የሕግ አንቀጾች ራሳቸው ከሚሰጠው የውክልና ሥልጣን አንፃር ምንም አግባብነት የሌላቸውና በፍጹም ሊጠቀሱ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ይኸውም በአብዛኛው በሚባል ሁኔታ የውክልና ሥልጣን ማስረጃዎች የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2199ን ካላካተቱ ውክልና ሰነዱ ያልተሟላ ሰነድ እንደሆነ ተቆጥሮ የውክልና ሥልጣን መስጫውን ሰነድ እንዲቀየር እስከማዘዝ የሚደርሱ የሰነድ አረጋጋጭ ጽሕፈት ቤቶች በተግባር የሚያጋጥሙበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ ውክልና ሰጪው አካልም ይህን የሕግ አንቀጽ በመጥቀስ ውክልና የሚሰጥበት ሁኔታ እጅግ የበዛ ነው፡፡ በመሠረቱ ይህ አንቀጽ የሚያወራው ስለ እንደራሴነት (ውክልና) ትርጓሜ እንጂ ስለውክልና ዓይነቶች ወይም ውክልና ስለሚሰጥበት አግባብ አይደለም፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው ለእንደራሴው የአስተዳደር ሥራዎችን እንዲያከናውን በሰጠው የውክልና ሰነድ ላይ ውክልና ማለት ብሎ ስለእንደራሴነት ትርጓሜ የሚያወራውን የሕግ አንቀጽ በመጥቀስ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2199 መሠረት ውክልና ሰጥቸዋለሁ ብሎ ማስቀመጥ ምንም ትርጉም የማይሰጥ ሆኖ ሳለ፣ ጭራሽ ይህንን የሕግ ድንጋጌ አልጠቀስክም ብሎ የውክልና ሰነዱ እንዲቀየር ማድረግ ከምን የሕግና የሎጂክ መሠረት ተነስቶ እንደሆነ ለማወቅ እጅግ በጣም አዳጋች ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም አንድ ግለሰብ ልዩ የውክልና ሥልጣን የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በተመለከተ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2205 መሠረት የውክልና ሥልጣን ሰጥቻለሁ የሚል ሐረግ ሳያስገባ በአንቀጹ ላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በመጥቀስ ብቻ የሕጉን አንቀጽ ባይጠቅሱ እንኳን የሕጉን አንቀጽ ካልጠቀሳችሁ ብለን ልናስገድድ የምንችልበት ምን የሕግ መሠረት አለን? በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ግለሰብ በተደበላለቀ ሁኔታ ጠቅላላ ውክልናና ልዩ ውክልና የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በአንድ የውክልና ማስረጃ ሰነድ ላይ በመዘርዘር በውክልና ሰነዱ ላይ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2203፣ 2204 እና 2205 መሠረት ሙሉ የውክልና ሥልጣን ሰጥቻለሁ የሚሉ የውክልና ሰነዶች በአረጋጋጩ አካል ሳይስተካከሉ እንዳለ ፀድቀው ተግባር ላይ የሚውሉበት እጅግ የበዛ ጊዜ አለ፡፡ ይህ ተግባር (Practice) የውክልና ሥልጣን አረጋጋጭ አካሉ የሕግ አንቀጽ አልተጠቀሱም ብሎ የውክልና ሥልጣን ማስረጃውን እየቀየረ ባለበት ሁኔታ ልዩና ጠቅላላ የውክልና ሥልጣን በተሰጠበትና ይህንኑ የሚገልጹ የሕግ አንቀጾች በግልፅ ተቀምጠውና በሰነዱ ላይ ሙሉ የውክልና ሥልጣን ሰጥቻለሁ የሚል ሐሳብ እያለ፣ ሰነዱን ማፅደቅ ምንም ዓይነት የሕግ ድጋፍ የሌለው ይልቁንስ የዘልማድ አሠራር ውጤት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሕጉ አነጋገርም የውክልና ሥልጣንን በሚያወራው ድንጋጌ ውስጥ ሙሉ ውክልና የሚል አንድም የሕግ አንቀጽ የለም፡፡ ስለሆነም ይህ አሠራር ሥልጣን የተሰጠው አካል ዘልማዳዊ አሠራር ውጤት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በአጠቃላይ የውክልና ሥልጣን ማስረጃ ሰነዶች በእያንዳንዱ ግለሰብ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያጋጥሙ ጉዳዮች ከመሆናቸው አንፃር ከፍተኛ ጥንቃቄን ይፈልጋሉ፡፡ አብዛኛው የግለሰቦችም ሆኑ የድርጅቶች እንቅስቃሴዎች በውክልና የሚደረጉ በመሆናቸውና ግለሰቦች እጅግ የበዙ ሥራዎቻቸውን በተወካዮቻቸው አማካይነት የሚያከናውኑበት ሁኔታ በጣም የተለመደና በተግባርም በሥራ አጋጣሚ የሚያጋጥሙ ስለሆነ ልማዳዊው አሠራር በሕጉ የተቀመጡትን አግባቦች እንዳያውኩና ደንበኞች ላይ አግባብ ያልሆነ መጉላላት እንዳይርስባቸው ሕጉ የሚለውን አሠራር ውክልና አሰጣጡም ሕጉ በሚለው መሠረት መስጠት የሚያስፈልግና አስፈላጊው አሠራርም አዋጁን በማሻሻል መደረግ ሲገባው፣ መመርያ መጥቷል በማለት ብቻ መሠረታዊውን የውክልና ሥልጣን ዓላማ ከማዛባት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው gezu2015 [at] yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡