የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ሕጉን በፕሬስ ነፃነት ቀን አምላክ በሉልን!

በበሪሁን ተሻለ

‹‹ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደና በርካታ ሒደቶችም ያለፈ …›› ተብሎ መግለጫ የቀረበለት አዲስ የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ለዝርዝር ዕይታ ለኮሚቴ ተመርቷል፡፡ ጉዳዩ የተመራለት ኮሚቴም በዚህ የሚያዝያ ወር የመጨረሻ ሳምንት ረቡዕ ላይ የ‹‹ሕዝብ ስሚ›› ጠርቷል፡፡ ረቂቅ ሕጉ የተለመደውንና ሆይ ሆይታውና ግርግሩ የበዛበትን አሠራር ተከትሎ ከመረማመድ የሚከላከለው ተዓምር ካልተፈጠረ በቀር በታወቀው ፍጥነት ሲሆን፣ ሚያዝያ ራሱ ውስጥ አለበለዚያ ግንቦት መጀመሪያ ላይ ላለመፅደቁ ጥርጥር የለውም፡፡

ኢትዮጵያ የኮምፒዩተር ወንጀል ሕግ የሚያስፈልጋት ስለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ዘመኑ ደግሞ የአይቲ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ነው፡፡ አገራችንም ‹‹የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የአገሪቱን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ እንዲሁም የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ግንባታን ለማፋጠን በሚያግዝ መልክ በጥቅም ላይ ማዋል›› ዓላማ ያለው የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ባለሥልጣን የሚባል የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ያቋቋማቸው፣ ከዚያ በፊት በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ብሔራዊ የኮምፒዩተርና የኢንፎርሜሽን ማዕከል ይባል በነበረው ሲሠሩ የነበሩ ሥራዎችና ኃላፊነቶች ወደ ባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት እንዲዛወር ያደረገችው በ1995 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ዛሬ በተለይም ከጥቅምት 2003 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አለን፡፡

ከዚህም በላይ አሁን አቅምና አቋሙ በአዋጅ ደረጃ ከፍ ያለው የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የተቋቋመው በ1999 ዓ.ም. ነው፡፡ የኢንፎርሜሽንና የኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ይህን ያህል ስፋት ካገኘና አብሮም ሥጋት ይዞ ከመጣ ደግሞ፣ የወንጀል የመከላከልንና ወንጀል ሲፈጸምም ይህንኑ የመመርመርንና ለሕግ የማቅረብን ነባር የመንግሥት ሥራ መልሶ ማየትን የግድ ይላል፡፡

የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በወንጀል ድርጊት ውስጥ ከሚኖረው ሚና አንፃር የኮምፒዩተር ወንጀል የሚባለው የወንጀል መደብ በሦስት ይከፈላል፡፡ አንደኛው በመረብ በተሳሰሩ የኮምፒዩተር ሥርዓት፣ የኮምፒዩተር ዳታ ሥርዓትና መረብ በራሱ ላይ የሚፈጸም የጥቃት ወንጀል ነው፡፡ ሁለተኛው የወንጀል ዓይነት የኮምፒዩተር ሥርዓቱን ራሱን የመደበኛ ወይም ነባር ወንጀል መፈጸሚያ መሣሪያ አድርጐ የመጠቀም ወንጀል ነው፡፡ ሦስተኛው ሁለትና ከዚያ በላይ እርስ በርስ በተሳሰሩ የካምፒውተር ሥርዓት አማካይነት የሚሠራ ወንጀል በኮምፒዩተር ሥርዓቱ ውስጥ እግረ መንገዱን የሚያስመዘግበውና ኋላም የወንጀሉ ማስረጃ ሆኖ የሚያገለግለውን መረጃ የሚሰጠው ወንጀል ነው፡፡ ስለዚህም በኮምፒዩተር ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ በኮምፒዩተር አማካይነት የሚፈጸም ወንጀልና ኮምፒዩተር እንዳጋጣሚ የመዘገበው ወንጀል የሚባሉ ናቸው፡፡

በኮምፒዩተር ላይ የሚፈጸም ወንጀል ማለት በኮምፒዩተሩ በራሱ፣ ወይም በአካሉ ላይ ጉዳት ማድረስን ወይም እሱን ራሱን መስረቅን ወይም የፋይበር ኦፕቲክስ ወይም የስልክ ኬብል መስረቅንና ስለዚህም በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ መስተጓጐል መፍጠርን የሚመለከት ወንጀል አይደለም፡፡ ይኼ በነባር የንብረት ጥበቃ ሕጐች የታቀፈ ከዚያ ወዲህም በቴሌኮሙዩኒኬሽንና የኤሌክትሪክ ኃይል አውታሮች ደኅንነት ጥበቃ አዋጅ ላይ የተለየ ጥበቃ ያገኘ ነባር የወንጀል ዓይነት ነው፡፡ አዲስ ሕግ ያስፈለገው በኮምፒዩተር ላይ የሚሠራ ወንጀል ኮምፒዩተሩ ሥርዓት ውስጥ ጣልቃ መግባትን፣ መበጥበጥን፣ ማበላሸትንና ማተራመስን የሚመለከተው ነው፡፡ ይህ በእርግጥም አንድን ወይም ሌላን ድርጊት ወንጀል አድርጐ መፈረጅን እንደ አዲስ ጉዳይ አድርጐ ያቋቁማል፡፡

በኮምፒዩተር አማካይነት የሚፈጸሙ ወንጀሎች አዲስ ወንጀሎች አይደሉም፡፡ የማታለል፣ የማጭበርበር፣ የስርቆት፣ የኮፒ ራይት ጥሰትና የገንዘብ እጥበት ወንጀል ናቸው፡፡ ድሮም የነበሩ አዲስ መፈጸሚያ ዘዴ ያገኙ የወንጀል ዓይነቶች ናቸው፡፡ በኮምፒዩተር አማካይነት የሚፈጸሙ እነዚህና ሌሎችም ነባር ወንጀሎች ግድ የሚያደርጉት የአዲስ ሕግ መውጣትን አይደለም፡፡ በገሀዱና በግዙፉ ዓለም ስርቆት ወንጀል ነው፣ ስለዚህም በምናባዊው (ቨርቹዋል) ዓለም ውስጥም ወንጀል መሆኑን ማረጋገጥን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሦስተኛው ጉዳይ ኮምፒዩተርን ከነፍጥርጥሩ በወንጀል ማስረጃነት መጠቀምን የሚጠይቀው ነው፡፡

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ የወንጀል ሕጓን በአዲስ መመርመር ያለባት መሆኑ እውነት ነው፡፡ የኮምፒዩተር ወንጀል ሕግም አስፈላጊነት አንድና ሁለት የለውም የተባለውም ለዚሁ ነው፡፡

ይህን የማድረግ፣ የኮምፒዩተር ወንጀልን የመደንገግ፣ የመንግሥት ሕግ የማውጣት ግዴታና ግዳጁ ግን በርካታ ጥንቃቄዎችና ጠባቂዎች ያስፈልጉታል፡፡ በቅጡና በደንብ ሥራዬ ተብሎ የተጠናና በባለሙያዎች ውይይት የዳበረ፣ ሁሉንም አማራጮች አጋልጦ አገላብጦ የሚያሳይ የፖሊሲ ውሳኔ ያስፈልገዋል፡፡ በአስፈጻሚው አካል ውስጥ ጉዳዩ በሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም መሥሪያ ቤቶች ባለሙያዎች ተፀንሶና እነሱ በመሩት ሰፊ ጥናት ተመሥርቶ የአሁኑን መልክ ያገኘው የሕግ ሐሳብ ብዙ የሚቀረውና ብዙ የሚያነጋግር ጉዳይ ያለበት ረቂቅ ነው፡፡

በእንዲህ ዓይነት የሕግ ማውጣት ጉዳይ በአረም መመለስ አዲሳችን ባይሆንም ባህላችን ግን መሆን የለበትም፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ ብቻ በሚያሳፍር ሁኔታ በአረም ተመልሰናል፡፡ የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ተሽሮ አዲሱ የ1996 ዓ.ም. የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ከተተካበትና በኩራት ከተገለጸበት ምክንያቶች አንዱ ይኼው የኮምፒዩተር ወንጀል ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ላይ የሚታየው ሌላው ክፍተት›› ይላል የወንጀል ሕጉ መግቢያ፣ ‹‹የቴክኖሎጂ ዕድገትና የዘመናዊ ኑሮ ውስብስብነት የወለዳቸውን ወንጀሎች በተገቢው ሁኔታ አለማካተቱ ነው፡፡ እንደ አውሮፕላን ጠለፋ የኮምፒዩተር ወንጀሎችና በወንጀል አማካይነት የተገኘን ገንዘብና ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የመሳሰሉት ወንጀሎች የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ያልዳሰሳቸው ናቸው፡፡››

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የመጀመሪያውን ሕግ ያወጣነው በ2004 ዓ.ም. የካቲት ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ይኼው አዋጅ ራሱ እንደገና በሌላ አዋጅ ተተክቷል፡፡ የ1996 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ ከ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ይልቃል የተባለበት ሌላው ምክንያት በ1996 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ የኮምፒዩተር ወንጀሎች ተካተቱ መባሉ ነበር፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኮምፒዩተር ወንጀል ሕግ ረቂቅ ቢፀድቅ ከሚሻሩት ሕጐች መካከል አንዱ የወንጀል ሕጉ በኮምፒዩተር አማካይነት የሚፈጸሙ ወንጀሎች ብሎ ከአንቀጽ 706 እስከ 711 የደነገጋቸው ስድስት አንቀጾች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ዝርዝርና ይዘት ይልቅ ይበልጥ የሚደንቀው በኮምፒዩተር አማካይነት የሚፈጽሙ ወንጀሎች ብሎ የወንጀል ሕጉ በስድስተኛ መጽሐፍ ‹‹በንብረት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች›› ረድፍ ውስጥ እንዲካተቱ ማድረጉ ነው፡፡ ይኼ ሁሉ የአለባብሶ ማረስ ውጤት ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም. የወጣው የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ‹‹ከጠለፋና ተደራሽነት ጋር የተያያዙ ወንጀሎች›› ብሎ በኮምፒዩተር ላይ የማፈጸሙ ወንጀሎችም ሆኑ በኮምፒዩተር አማካይነት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚሸፍን ሕግ አለመኖሩን እግረ መንገዱን መስክሮ አልፎ ነበር፡፡ አዲሱ ሕግ ቢፀድቅ የሚሽረውም በዚህ በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የተጠቀሰውን ድንጋጌ ጭምር ነው፡፡ ስንት ጊዜ አለባብሰን እናርሳለን? ስንት ጊዜ እንሳሳታለን? ስንት ጊዜ እንደገና በአረም እንመለሳለን?  

ኢትዮጵያ የኮምፒዩተር ወንጀሎች ሕግ የሚያስፈልጋት መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይልቁንም የዘገየና በአረም የተመላለስንበት የተወዘፈ ሥራ ነው፡፡ የሞባይል ስልክ ዛሬ ቤትን ከውጭው ዓለም ጋር በሽቦ የሚያገናኝ ተራ ቀፎ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ስማርት ፎን ያለው ባለሞባይል ስልክ ባለቤት ሁሉ አነሰም በዛም በኮምፒዩተር መረብ ሥርዓት ውስጥ የተሳሰረ ነው፡፡ አሁን የምንገኝበት የ2007/08 የበጀት ዓመት የገቢ በጀት ዝርዝር እንደሚያሳየው፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽንን አገልግሎት የሚያገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ተጨማሪ እሴት ታክስ ብቻ 5.8 ቢሊዮን ብር ይከፍላል፡፡ ይህ ለቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ከምንከፍለው ዋናው ወጪያችን የተለየው የ15 በመቶ ታክስ ብቻ ነው፡፡

ይህ የአገልግሎት ሒሳብና ግብር ከፋይ ሕዝብ ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት አለበት፡፡ ጥራት ያለው አገልግሎት ማለት ደግሞ ከወንጀል ድርጊት የፀዳ አገልግሎት ማለት ጭምር ነው፡፡ ወንጀልን የመከላከል የመንግሥት ሥራ ከቴሌፎን ደንበኛው ክፍያ ጋር ግንኙነት ባይኖረውም፣ የ5.8 ቢሊዮን ብር የተጨማሪ እሴት ታክስ በዓመት ከፋይ ሕዝብ ግን እውነትም ተጨማሪ እሴት ከመንግሥት ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት ጭምር የሚያከብረውና መንግሥትንም ጭምር የሚገዛ የኮምፒዩተር ወንጀል ሕግ አገራችን ያስፈልጋታል፡፡

ረቂቅ ሕጉ የአዋጁን አስፈላጊነት በሚገልጽበት መግቢያው የኢንፎርሜሽንና የኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጾ፣ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተገቢ ጥንቃቄና ጥበቃ ካልተደረገለት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ሊያደናቅፍ፣ እንዲሁም የዜጐችን የግል ነፃነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ለሚችሉ ለተለያዩ የኮምፒዩተር ወንጀሎችና ሌሎች የደኅንነት ሥጋቶች የተጋለጡ በመሆኑ ነው ይላል፡፡

በሥራ ላይ ያሉ የአገሪቱ ሕጐች ከአዳዲስ ለውጦች ጋር በበቂ ሁኔታ ተጣጥመው የማይሄዱ የኮምፒዩተር ወንጀልን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር፣ ለመመርመርና ተጠርጣሪዎችን ወደ ፍትሕ ለማቅረብ የሚያስችሉ ባለመሆናቸውም ነው ይላል፡፡

የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተገቢ ጥንቃቄና ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ለዚህም ከሌሎች መካከል የኮምፒዩተር ወንጀል የሕግ ሥርዓት መዘርጋቱ ተገቢ ነው፡፡ የኮምፒዩተር ወንጀልን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለመመርመር ኤሌክትሮኒክ ማስረጃዎችን ጭምር ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ሥልቶችንና ሥርዓቶችን በሕግ የመደንገግ ጉዳይም፣ በተለይም በዚህ ልዩ ጉዳይና   በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ይበልጥ ዓይን ሊያርፍበት፣ ተገቢ ጥንቃቄና የሁሉም ሰው ጥበቃ ሊደረግለትና ሁሉም ዘብ ሊቆምለት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ይህ ጥንቃቄና ጥበቃ ረቂቁን ሕግ ቆቅ ሆኖ ከመመርመር ብቻ ሳይሆን፣ ተጠራጥሮ ከመነሳት ይጀምራል፡፡ በዚህ ረገድ ተጠራጥሮ የማይጠግብ፣ ጠይቆ የማያባራ አበጣሪና አጣሪ ሊጋፈጠው ይገባል፡፡ የዚህ ምክንያት የረቂቅ ሕጉ አመንጪ መንግሥት በመሆኑ አይደለም፡፡ ወይም የረቂቅ ሕጉን ሐሳብ ያሰናዳው አግባብ ያለው ክፍልን የሳይንስና ቴክኖሎጂና የሕግ ዕውቀት በመጠራጠርም አይደለም፡፡ እሳት የላሱ፣ ወደር የሌላቸው ምርጥ የሳይንስና የሳይበር ቴክኖሎጂ የደኅንነትና የሕግ ሊቃውንት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ችግሩ ግን እነዚህ ባለሙያዎች የወንጀል ሕጉን የሚመለከቱት ከራሳቸው የተጋረደ ‹‹የሥራ ድርሻ›› እና ‹‹ሥልጣንና ተግባር›› አንፃር ብቻ ነው፡፡ ለዲፓርትመንታቸው ያደላሉ፡፡ ለእናት ቤታቸው ‹‹ይቀናሉ››፡፡ የጠራና የተቋቋመ ሕግ አፈጻጸም ላይ እንኳን በአንድ ጉዳይ ፖሊስ ከዓቃቤ ሕግ፣ ዓቃቤ ሕግ ከፖሊስ የተለያየ ዕይታ የሚኖራቸው በዚህ ወገንተኝነታቸው ምክንያት ነው፡፡ ሕጉ ምን እንደሚል የመወሰን የመጨረሻው ሥልጣን ለፍርድ ቤትም የተሰጠው ለዚህም ነው፡፡

በሕጉ ማርቀቅና ዝግጅት ወቅትም ሁሉም ዓይነት የኮምፒዩተር የወንጀል ሕግ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች የሚብላሉበት፣ ረቂቅ ሕጉን ያቀረቡት የመንግሥት የሥልጣን አካላት የራሳቸውን ምርጫና ውሳኔ ከውይይትና ከጥያቄ በላይ የማድረጋቸው ባህል የሚሰበርበት ውይይትና ምርመራ ያስፈልጋል፡፡ የሕግ አወጣጥ ሥርዓታችን ከዚህ አሮጌ ቀፎው መውጣት አለበት፡፡ በኮምፒዩተር ላይ፣ በኮምፒዩተር አማካይነት የሚፈጸም ወንጀልንና ሕገወጥነትን በሕግ ስንደነግግም ሆነ ዕርምጃ ስንወስድ፣ የሚወጣውም ሕግና የሚወሰደው ዕርምጃ የመንግሥትንም የሕግ አክባሪነት የውኃ ልክ የሚያስገምት ከሆነ ጨዋታው እዚህ ላይ ይፈርሳል፡፡

በዚህ ምክንያት በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ሰ እንዲሁም የሕግና የሳይበር ደኅንነት ባለሙያዎች በቂ ጊዜ አግኝተው በጥናት ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ አዘጋጅተው ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡበት መደረጉ፣ የሕጉ አወጣጥ አንድ አካል ቢሆንም ለሌላውም ተመሳሳይ ሥራ መልካም ጅምር ነው፡፡ ከዚህ አጠቃላይ ግምገማና አስተያየት በተረፈ ግን በኮምፒዩተር ላይ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ወንጀል አድርጎ ከመደንገግ አዲሱ ሥራ ይልቅ፣ ከእሱም በባሰ ሁኔታ በኮምፒዩተር አማካይነት የሚፈጸሙ ነባር ወንጀሎችን የሚመለከተው የረቂቁ ሕግ ክፍል ብዙ ችግርና የተለመዱ አስተዛዛቢ ጉዳዩን የሚያጋልጥ እንከን ያለበት ነው፡፡

በተለይ በረቂቅ ሕጉ አንቀጽ 13 የተደነገገው በጽሑፍ በንግግር አማካይነት የሚፈጸም የማስፈራራት የዛቻ ወንጀል (ንዑስ ቁጥር 1)፣ መረጃ በመላክ፣ መልዕክት በመጫን፣ ፍርኃትን፣ ሥጋትን፣ የሥነ ልቦና ጫናን የመፍጠር ወንጀል (ንዑስ አንቀጽ 2) የሚገርሙና የሚያሳዝኑ፣ በትርጉማቸው ቦርቃቃ በአፈጻጸማቸው ልቅ የሚሆኑ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ አንድ ሰው ላስፈራራ ብሎ አስቦ አልሞ የሚያስፈራራ ተጨባጭ ድርጊት (ሐሳብን በመግለጽም ጭምር) ቢፈጽምና ቢጠየቅ ያባት ነው፡፡ የማስፈራራቱ መለኪያ ግን የአድራጊው ሐሳብና ድርጊት መሆኑ ቀርቶ ፈራሁ፣ የፍርኃት ስሜት አደረብኝ የሚለው ከሆነ ሕጉ ሕግ መሆኑን ያቆማል፡፡ የዚህ ሕግ ሌላው ውጤት አስፈራሩኝ ያለውን ተበዳይ መታደግ ይቅርና እንዲያውም በኮምፒዩተር አማካይነትም ሆነ ከዚያ ውጪ ሐሳቡን የሚገልጸውን ሰው ሁሉ ያስፈራራል፣ ያስቦካል፣ ሐሞት ያፈሳል፣ ቅስም ይሰብራል፡፡

ይህ የአወዛጋቢውና ሕገ መንግሥቱን ከሚፃረረው፣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን መሠረታዊ መርህ በአፍጢሙ ከሚደፋው፣ ከፀረ ሽብር ሕጉ አንቀጽ 6 ያልተለየና ከእሱም የልተማረ አደገኛ ድንጋጌ ነው፡፡ የፀረ ሽብር ሕጉ አንቀጽ 6 ማንም ሰው መልዕክቱ እንዲታተምላቸው የተደረገው የኅብረተሰብ አባላት፣ በከፊል ወይም በሙሉ የሽብርተኝነት ድርጊት እንዲፈጽሙ ወይም ለመፈጸም እንዲዘጋጁ ወይም እንዲነሳሱ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያበረታታቸው፣ ወይም በማናቸውም ሌላ ሁኔታ የሚገፋፋቸው እንደሆነ አድርገው ይረዱታል ተብሎ ሊገመት የሚችል መልዕክት ሆነ ብሎ ወይም በግዴለሽነት ያተመ ወይም ያላተመ እንደሆነ፣ ከአሥር ዓመት እስከ 20 በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል ይላል፡፡

ከአሥር እስከ 20 ዓመት ከሚያስቀጣው ወንጀል ለመከላከል በዚህ ድንጋጌ መሠረት ማንም ነባራዊ መለኪያ የለውም፡፡ አዕምሮ የማመዛዘንን ሕግ ተከትሎ ነባራዊና ተጨባጭ መለኪያ ይዞ፣ ይህ ንግግር ወይም ኅትመት አያነሳሳም ብሎ መወሰን አያዋጣም፡፡ ከመፈጸም ተከልከል የተባለው ሰው በራሱ የሚያዝበት መለኪያ ነው፡፡ መለኪያውም በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያበረታታና የሚገፋፋቸው እንደሆነ አድርገው ይረዱታል ተብሎ ሊገመት የሚችል መልዕክት ከመጻፍ መከልከል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ቀድሞው ወደ ‹‹ከአገር ሆድ ይሰፋል›› ቦታና ጊዜ ተመለሱ ማለት ነው፡፡

በኮምፒዩተር ወንጀል ሕጉ የተከለከለውም ይህን አታድርጉ የሚል ተጨባጭና ነባራዊ መለኪያ የለውም፡፡ እንዲህ አለኝና ፈራሁ፣ ይህንን አሳየኝና ሠጋሁ ያለ ሁሉ መክሰስና መፋረድ ይችላል፡፡

በዚሁ በተጠቀሰው የአንቀጽ 13 ድንጋጌ የሌለውን ሰው ክብር ወይም መልካም ስም የሚያጎድፍ ጽሑፍ፣ ንግግር፣ ሥዕል ወይም ተንቀሳቃሽ ምሥል በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካይነት ያሰራጨ እንደሆነ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት፣ ወይም በመቀጮ ወይም በሁለቱም ይቀጣል ይላል፡፡

በሌሎች ዴሞክራሲያዊ አገሮች ቀርቶ በአፍሪካም ጭምር በርካታ አገሮች ስም ማጥፋትን ከወንጀል ሕጋቸው አስወጥተው ፍትሐ ብሔራዊ ጉዳይ ብቻ ባደረጉበት ዓለምና አኅጉር፣ በተለይም የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫዋ ኢትዮጵያ በ2008 ዓ.ም. ውስጥ ስም ማጥፋትን በአዲስ ሕግ ወንጀል አድርጋ ደነገገች ሲባል፣ በወንጀል ሕግ የማይታደጉት ትልቅ ስም ማጥፋት ያስከተላል፡፡ ገጽታም ያጠፋል፡፡ በዚያ ላይ መልካም ስም የሚያጎድፈው ጽሑፍ፣ ንግግር፣ ሥዕል ያዘለው ፍሬ ነገር (ፋክት) ይሁን አስተያየት (ኦፒኒየን) ልዩነት የለውም፡፡ እውነት ይሁን ውሸት ልዩነት አያመጣም፡፡ የሕዝብ ጥቅም ከቁጥር አይገባም፡፡ በቅጣቱ መጠን ረገድም በኮምፒዩተር የስም ማጥፋት ወንጀልና በሌላ የስም ማጥፋት ወንጀል መካከል ከፍ ያለ ልዩነት አለ፡፡

በሕዝብ ደኅንነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የተባሉትም ለተርጓሚና ለደርጋሚ የተጋለጡ ቦርቃቃ ናቸው፡፡ ውጤታቸውም ተፈለገም አልተፈለገም በንግግርና ሐሳብን በመግለጽ መረጃ በመቀበል ነፃነት ላይ ፍራቻንና ሽብርን መልቀቅ ነው፡፡

ሌላው የኮምፒዩተር የወንጀል ሕጉ አደገኛ ድንጋጌ በአንቀጽ 16 የተወሰነው ስለ አገልግሎት ሰጪዎች የወንጀል ተጠያቂነት ነው፡፡ አገልግሎት ሰጪ ማለት በራሱ በረቂቁ ትርጉም በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካይነት ቴክኒካዊ የዳታ ፕሮሰሲንግ ወይም የግንኙነት ሥርዓት አገልግሎት ወይም ምትክ መሠረተ ልማት ለተጠቃሚዎች የሚያቀርብ ነው ይላል፡፡ ይህ ትርጉም የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ብቸኛው ድርጀታችንን ጨምሮ የሰርች ኤንጂን (እነ ጉግልን) እና የማኅበራዊ ኔትወርኪንግ መድረኮችን (እነ ፌስቡክን) እንደሚያካትት አናውቅም፡፡ ሲገባን ግን እንደዚያ ማለት ነው፡፡ እነዚህን አካላት የወንጀል ተጠያቂ የሚያደርገው ደግሞ ሕገወጥ የይዘት ዳታውን በማሠራጨት ወይም አርትኦት በማድረግ በቀጥታ የተሳተፈ ከሆነ፣ ሕገወጥ የይዘት ዳታ መሆኑን እንዳወቀ ዳታውን ለማስወገድ ወይም ተደራሽ እንዳይሆን ለማድረግ ወዲያውኑ ዕርምጃ ያልወሰደ ከሆነ፣ ሕገወጥ የይዘት ዳታውን እንዲያስወግድ ወይም ተደራሽ እንዳይሆን እንዲያደርግ በሚመለከተው አካል ተነግሮት ተገቢ ዕርምጃ ሳይወስድ የቀረ እንደሆነ ነው፡፡ በአገልግሎት ሰጪዎች ላይ የቁጥጥር ግዴታ ከማቋቋም በላይ፣ ‹‹በሚመለከተው አካል›› ዳታ እንዲያስወግድ ወይም ተደራሽ እንዳይሆን እንዲያደርግ እንደሚታዘዝ ይደነግጋል፡፡

በተለይ ይህ ጉዳይ የፕሬስ/የሚዲያ ውጤቶችን ይዘት ሕጋዊነትን የመጠበቅ ግዴታን የማንምና የሁሉም የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በአፈጻጸም ተጎሳቅሎ፣ በሳንሱር መዋቅር እጅ ተወርች ታስሮ የነበረውና በደርግ ዘመን ከነጭራሹ ተወርውሮ የነበረው፣ ከዚያ በኋላም ለጸሐፊው ብቻ ሳይሆን ለአንባቢውና ለሰሚው ሁሉ ተርፎ ሞትና ዕልቂት ያስከተለው የኃላፊነትን ጉዳይ በኦንላይን ጉዳይ መልሶ ማተራመስ፣ ሥርዓት አልባ ማድረግና አንድ የፕሬስ ውጤት በሕግ የሚያስጠይቅ ይዘት የሌለው መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ የማነው የሚለው ጥያቄ መልስና ሥርዓት አግኝቶ ነፃ ወጥቶ፣ ተፈጻሚነቱን ለማረጋገጥ ደፋ ቀና ማለት የጀመረው በ1985 ዓ.ም. የፕሬስ ነፃነት ሕግ መሠረት ነበር፡፡ ማተሚያ ቤቶች በዚህ ሕግ ነፃ ወጡ፡፡ በ1996 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ አስደናቂ ማሻሻያ ምክንያት የገነባነውን አፍርሰን ዛሬ የታወቁ ማተሚያ ቤቶችን ጭምር ሳይቀር አይዟችሁ ያለውና የሳንሱር ያህል የሚያገለግለው ማስፈራሪያ ምንጭ የዚህ ጉዳይ አለመጥራትና በግልጽ አለመወሰን ነው፡፡ የኮምፒዩተር ወንጀል ሕጉ ድንጋጌ ደግሞ የምናባዊውን ምኅዳር የይዘት ኃላፊነት የሁሉም ‹‹አገር ወዳድ›› ሁሉ ማድረጉ ከፍ ያለ አደጋና መርዶ ነው፡፡ 

በተለይ የፕሬስ ነፃነት አንዱ አከርካሪ የሆነው የምንጭ ሚስጥራዊነት በዚህ ሕግ ከሚደናገጡት መብቶችና ነፃነቶች መካከል የመጀመሪያው ነው፡፡    

   ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡