የኩባንያ ጠቅላላ ጉባዔ ተግባራዊ እንቆቅልሾች

ኩባንያ በኢትዮጵያ ታሪክ መቼም ጀመረ መች በአሁኑ ዘመን የደረሰበት ስፋት ትርጉም ያለው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኩባንያዎች ቁጥር በዝቷል፣ የሚቋቋሙበትና የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ በጣም ብዙ ነው፣ አክሲዮን ማኅበራቱ የያዟቸው ባለአክሲዮኖች ብዛት ጨምሯል፣ ኩባንያዎቹም የሚንቀሳቀሱበት ዘርፍ እንዲሁ ሰፍቷል፡፡ የተደራጁ ኩባንያዎች የተጀመሩት ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ቢሆንም ዕድገታቸው አርኪ አይደለም፡፡ በኩባንያዎቹ የሚታሰቡ ዕቅዶች፣ የሚነደፉ አቅጣጫዎች ወዘተ. በልማድ እንጂ ሕጉንና ደንቡን በመከተል አይደለም፡፡ ኩባንያዎቹን ያቋቋሙ ባለአክሲዮኖችም የኩባንያዎቹ ባለቤቶች የሚያስመስላቸውን ሥራ ሲሠሩ አይታይም፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ በሚገኙበት የጠቅላላ ጉባዔ በራሳቸው ጉዳይ ታዛቢ ሆነው ይሄዳሉ፡፡ ባለአክሲዮኖቹ መብታቸውን አያውቁም፤ ቢያውቁም አይጠይቁም፣ ቢጠይቁም በተወሰኑ ቡድኖች የተቀነባበረ ስልት ተድበስብሶ እንዲያልፍ፣ አንዳይሰማ ይደረጋል፡፡ በዚህ ሰሞን የሚከናወኑ የኢንሹራንስና የባንክ አክሲዮን ማኅበራት ጉባዔዎችን ለመታዘብ ዕድል የሚያጋጥመው ሰው እነዚህ እውነታዎችን ይረዳል፡፡ የአክሲዮን ማኅበራቱ የትርፋቸው ዕድገት ጤናማ ስለአለመሆኑ፣ የማኔጅመንቱና የዳይሬክተሮች ቦርድ ጥፋት፣ የውጭ ኦዲተር ገለልተኝነትና ብቃት ወዘተ. ሰፋ ያለ ጊዜ ተወስዶ ውይይት የተደረገበት ጉባዔ እምብዛም ነው፡፡

ጸሐፊው ከዚህ በፊት በዚህ ዓምድ በሁለት ርዕሶች የጠቅላላ ጉባዔዎችን አካሄድና የባለአክሲዮኖችን መብት የተመለከተ ጽሑፍ ያቀረበ ቢሆንም፣ ጽሑፎች ሕጉንና አተገባበሩን በአጠቃላይ የሚዳስሱ በመሆናቸው የጽሑፎቹ ዓላማ ሙሉ በሙሉ ተሳክቷል ለማለት ያስቸግራል፡፡ የኩባንያ አስተዳደር የሕግና የመመርያ ችግር ያለበት ቢሆንም የአተገባበሩ ችግሮች ያህል የተወሳሰበ አይደለም፡፡ የኩባንያ አስተዳደር ዲሞክራሲያዊ ካልሆነና በአስተዳደሩ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ግዴታቸውን ካልተወጡ ኩባንያዎች እየቀጨጩ ይሄዳሉ፣ የቢዝነስ ልምዱም ይጠፋል፤ ግለሰቦችም ካጠፉት ጥፋት ሳይማሩ የበለጠ የማያጠፉ ትውልድ ይተካሉ፡፡ ኩባንያዎቹም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የመሆን ተስፋ አይኖራቸውም፡፡ በኢኮኖሚው ባላቸው ሰፊ ተፅዕኖም ኢኮኖሚውን ሊጎዱት ይችላሉ፡፡ በምዕራባውያኑ የደረሰው ዓይነት የኪሳራ ሥጋት ሩቅ አይሆንም፡፡ ከዚህ በመነሳት መሬት ላይ ያሉ የኩባንያ የአስተዳደር ችግሮችን በተለይም በኩባንያ ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት የሚታዩትን ችግሮች መዳሰስ ብልህነት ነው፡፡ በዚሁ መሠረት በተመረጡ ነጥቦች ላይ ዳሰሳ ለማድረግ ሙከራ የተደረገ ሲሆን፣ በኩባንያ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ተጨማሪ ሐሳቦችን እንደማያንፀባርቁ ይታሰባል፡፡

የባለቤትነትና የማዘዝ ሥልጣን መለያየት

ብዙ የባለአክሲዮን ቁጥር ባለባቸው የአክሲዮን ማኅበራት ባለአክሲዮኖቹ የአክሲዮኖቹ ባለቤቶች ቢሆኑም ኩባንያውን የማዘዙ ሥልጣን የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ላይ ይወድቃል፡፡ በዚህ መልኩ ባለቤትነትና የማዘዝ ሥልጣን በተለያየበት ሁኔታ የባለአክሲዮኖችና የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ሚና የተለየ ስለሚሆን የጥቅም ግጭት አይቀሬ ነው፡፡ ባለአክሲዮኖቹ የኩባንያውን ዕድገት፣ ትርፍና የገበያ ተወዳዳሪነት ሲመኙ የዳይሬክተሮች ፍላጎት ደግሞ ከኩባንያው ዘለቄታዊ ጥቅም ይልቅ የግላቸውን ጥቅም የሚያሟሉበትን ሁኔታ ለማሳካት ትግል ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ይህ ግጭት ኩባንያዎቹ አነስተኛ ትርፍ እንዲያገኙ፣ ተወዳደሪ እንዳይሆኑና ሲከፋም እንዲከስሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ ሚዛናዊ የሆነ የሥልጣን ክፍፍልና አተገባበር አስፈላጊ ነው፡፡ ባለአክሲዮኖቹ የማዘዝ ሥልጣናቸው አነስተኛ ቢሆንም፣ በጠቅላላ ጉባዔያቸው በሚወስኗቸው ጉዳዮች የኩባንያውን አስተዳደር በንቃት መምራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትንና የውጭ ኦዲተሮችን መሾምና መሻር፣ የሥራ ዋጋቸውን የመወሰን፣ በኩባንያው መሠረታዊ ጉዳዮች (ደንብ በማሻሻል፣ የኩባንያውን የካፒታል ዕድገት፣ መቀላቀል፣ መፍረስ ወዘተ በመወሰን፣ የሒሳብ ሚዛኖችን በማጽደቅ ወዘተ.) የመጨረሻ ውሳኔ የሚያስተላልፍ በመሆኑ ከባለቤትነት መብት የሚመነጨውን የማዘዝ ሥልጣን ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡

በአገራችን የኩባንያዎች ተሞክሮ ግን የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ይህንን ሥልጣን በአግባቡ ሲወጣ አናስተውልም፡፡ ባለአክሲዮኑ ወደ ጠቅላላ ጉባዔ በብዛት አይመጣም፡፡ ዋናው ጉባዔ ላይ የማይመጣው የራት ግብዣው ላይ ቁርጥ ለመቁረጥና ውስኪ ለመራጨት የሚመጣው ይበዛል፡፡ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች በውክልና የሚሳተፉ ቢሆንም ይህ ሥርዓትም ቢሆን በኋላ እንደምንመለከተው የራሱ ችግሮች አሉት፡፡ ጸሐፊው ባደረገው ምልከታ በጠቅላላ ጉባዔ የሚገኙ ባለአክሲዮኖች በመድረኩ ላይ የሚታየው ድራማ ተመልካቾች እንጂ በራሳቸው ሀብትና ጥቅም ላይ የሚወስኑ አያስመስላቸውም፡፡ ለአብነት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን ምርጫ ብንመለከት አዲሶቹን የቦርድ አባላት የሚያስመርጥ አስመራጭ ኮሚቴ የሚያቋቁመውና ሙሉውን የምርጫ ሥርዓት በስውር የሚመራው የቀድሞው ቦርድ ነው፡፡ ይህንን ተበደልን የሚሉ ባለአክሲዮኖች በተለያዩ ጊዜያት በመገናኛ ብዙኅን ከሚያወጡት መረጃ መረዳት ይቻላል፡፡ ቦርዱ አስመራጭ ኮሚቴዎችን ቀድሞ መርጦ (ወይም ለይስሙላ በአንዳንድ ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጁ ጠቋሚዎችን አስመርጦ) ለጠቅላላ ጉባዔው ያቀርባል፤ ጉባዔውም አካሄዱን ሳይመረምር ይቀበልና ይቀጥላል፡፡ የአስመራጮቹ ዓይን ቀድሞውንም ፕሮግራም የተደረገ በመሆኑ ማየት ከሚፈልጉት ሰው ብቻ ጥቆማ ይቀበላሉ፡፡ ተሳታፊው ይህንን ሳያውቅ እጁን ለጥቆማ ካነሳ ዕድሉን ለማን መስጠት እንዳለባቸው ስለሚያውቁ ድራማውን በአግባቡ ይከውኑታል፡፡ በስህተት በጉባዔው ዕድል የተሰጠው መስሎት ከተናገረ እንኳን ዕድሉ ለእርሱ እንዳልተሰጠው ተነግሮት ለሌላ ባለአክሲዮን ይሰጣል፡፡

ምርጫውም ሲከናወን ባለአክሲዮኖቹ እጩዎቹን በደንብ እንዲያውቁ ተደርጎ፣ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ምርጫ አይከናወንም፡፡ እጩዎቹ ራሳቸውን አስተዋውቀውና ምን ለመሥራት እንዳሰቡ ገልጸው፣ ተመዝነው ቦታውን ስለማይዙት ኃላፊነቱንም የዚህኑ ያህል ያቀሉታል፡፡ ጉባዔው ካለፈ በኋላ ‹‹እከሌ እከሌን ምረጥ ብሎኝ ነው እንጂ እኔ መምረጥ የምፈልገው እከሊትን ነበር›› የሚል ድምፅ (ጉምጉምታ) የሚሰማው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

በመሠረቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን አስመራጭ ኮሚቴ መምረጥ ያለበት ገለልተኛ ወገን ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የውጭ ኦዲተሮች ወይም ንግድ ሚኒስቴርና ብሔራዊ ባንክን የመሰሉ ተቆጣጣሪ መሥርያ ቤቶች ተወካዮች መድረኩን ተረክበው ካላስመረጡ የቀድሞው ቦርድ በመንፈስ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ አልፎ አልፎ በሙያና በሥነ ምግባር ብቃታቸው ተመርጠው መሥራት ያልቻሉ የቦርድ አባላትን የምናስተውለው ከቀደመው መንፈስ ለመራቅ በመወሰናቸው ነው፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ አዲስ ሐሳብ፣ አዲስ ጉልበትና አዲስ መንፈስ ይዞ የሚመጣ የቦርድ አባል አይኖርም፡፡ እህትማማች (በተመሳሳይ መሥራች አባላት የተቋቋሙ ኩባንያዎች) በሆኑ የአክሲዮን ማኅበራት በተለይ በባንኮችና የኢንሹራንስ ድርጅቶች ማን፣ መቼ የየትኛው ኩባንያ ዳይሬክተር እንደሚሆን ቀድሞ የታወቀ ነው፡፡ ‹‹እከሌ ከኢንሹራንሱ ወደ ባንኩ ይገባል፤ እከሌ ደግሞ ወደ ኢንሹራንሱ ይሄዳል፤›› የሚለው ከጉባዔው በፊት ተፈጭቶ የሚቦካ ነው፡፡ የባለአክሲዮኖቹ ጉባዔ ይህንኑ ሐሳብ ለማስፈጸም (የተቦካውን ለመጋገር) እንጂ ባለቤት እንደመሆኑ አስተዳዳሪዎቹን በእውነት ለመሾምና ለመሻር የታደለ አይመስልም፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫ በአብዛኛው ጠቅላላ ጉባዔ አከራካሪ የማይሆንበት ምክንያትም ይሄው የአመራረጥ ሥርዓት ነው፡፡ ምርጫው አከራካሪ በሆነባቸው የተወሰኑ አጋጣሚዎችም አከራካሪነቱ በቦርዱ መከፋፈል ካልሆነ በቀር ከጉባዔው የሚነሳ አይደለም፡፡

ይህ አካሄድ የተወሰኑ ባለ ብዙ ባለአክሲዮኖችን ከሚጠቅም በቀር ኩባንያውንም፣ አነስተኛ ባለአክሲዮኖችንም የሚጠቅም አይሆንም፡፡ የንግድ ሕግ ቁጥር 352 የተለያዩ የአክሲዮን ክፍል ያላቸው ባለአክሲዮኖች በዳይሬክተሮች ቦርድ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸው ቢደነግግም ተፈጻሚ ሳይሆን ዘመናት ተሻግሯል፡፡ ብዙ ባለአክሲዮን ባለባቸው ማኅበራት ብዙኅኑ ከአነስተኛ ታላላቅ ባለሀብቶች የተሻለ የመምረጥ መብት/አቅም ቢኖራቸውም በተግባር አይጠቀሙበትም፡፡ ለአብነት የባንኮችን ተሞክሮ ብንወስድ የባንክ ሥራ አዋጅ ተደማጭነት ያለው ባለአክሲዮን (Influential Shareholder) የካፒታል ገደብ የተደረገበት በመሆኑ ታላላቆቹ ባለአክሲዮኖች ያላቸው ድምፅ ብዙኅኑና አናሳ አክሲዮን  ካለው በአንፃራዊነት ብዙ አይሆንም፡፡ እነዚህ የባለአክሲዮኖች ክፍል የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ካጠናከሩና በሚገባ ተመካክረው ወደ ጉባዔ ከገቡ የኩባንያው አሠራር ለብዙኅኑ እንዲጠቅም ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

የእንደራሴ ጣጣ

ከተግባር ከተነሳን የባለአክሲዮኖች ጉባዔ በአብዛኛው የሚከናወነው በውክልና (Proxy) ነው፡፡ የንግድ ሕጉ ቁጥር 398 አንድ ባለአክሲዮን ሊሾም የሚችለውን እንደራሴ ቁጥር እንጂ አንድ ግለሰብ ስለሚቀበለው የውክልና ሥልጣን መጠን አይደነግግም፡፡ አንድ ባለአክሲዮን ከአንድ እንደራሴ በቀር ለመሾም አይችልም፡፡ እንደራሴነት በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት በተሰጠ ውክልና ወይም በኩባንያው በተዘጋጀ ፎርም በተሰጠ ውክልና ይፈጸማል፡፡ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔን የሚያዳክመው አንዱ ውክልና ገደብ ያልተደረገበት መሆኑ ነው፡፡ አንድ ባለአክሲዮን ወይም ተወካይ ከምን ያህል ሌሎች ባለአክሲዮኖች ውክልና መቀበል እንደሚችል የተቀመጠ ገደብ የለም፡፡ብሔራዊ ባንክ ገደብ ያስቀመጠ ቢሆንም ችግሩን በአግባቡ መቅረፉንና ተግባራዊነቱን ብዙዎች ይጠራጠራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተወሰኑ ባለአክሲዮኖች (በተለይ ለኩባንያው አስተዳደር የቀረቡ ዳይሬክተሮች ወይም ሥራ አስፈጻሚዎች) ከብዙ ባለአክሲዮኖች ውክልና በመውሰድ የፈለጉት ምርጫ እንዲከናወን አስችሏቸዋል፡፡ ግለሰቦች የደም ወይም የጋብቻ ዝምድና ያላቸውን፣ የንግድ ሸሪኮቻቸውን ወይም ለግል ጥቅማቸው የሚመቻቸውን ሰው የቦርድ አባል ለማድረግ ደፋ ቀና ሲሉ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ ይህ ውክልና የማሳደድ ትጋታቸው ኩባንያውን ለማሳደግ እንደማይሆን ሰይጣንም ያውቀዋል፡፡ ባንኮችን በተመለከተ የባንክ ሥራ አዋጅ በአንቀጽ 13 ብሔራዊ ባንክ ማንኛውም ሰው ለሌላ ባለአክሲዮን እንደራሴ ሆኖ የሚሰጠውን የድምፅ መጠን ሊገድብ እንደሚችል ቢደነግግም ተግባራዊ ባለመደረጉ ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም፡፡ በሌሎች አገሮች ውክልናን የተመለከቱ ሰፋ ያሉ ድንጋጌዎች ያሉ ሲሆን ተወካይ መሆን የሚችለውን፣ በምን ጉዳዮች መወከል እንደሚቻል እንዲሁም አማራጭ የውክልና አሰጣጥን ያካትታሉ፡፡ ባለአክሲዮኖችም ያለ ውክልና በአሌክትሮኒክ ዘዴ ወይም በድረ ገጽ የሚሰጡበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ፡፡ በእኛ አገር የቴክኖሎጂውም ዕድገት፣ የኩባንያዎቹም አቅምና ዘመናዊነት ይህንን የሚያስችል ባለመሆኑ እስካሁን ሊተገበር አልቻለም፡፡

የመረጃ ክፍተት

የኩባንያ ሕግ ባለአክሲዮኖችም ሆኑ ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች ኩባንያውን በተመለከተ ግልጽ ሊያደርጉት የሚገቡ መረጃዎች እንዳሉ ይደነግጋል፡፡ ባለአክሲዮኖች ገንዘባቸው ምን እየተሠራበት እንደሆነ፣ ኩባንያውን የሚያስተዳድሩ አካላት ያለባቸውን ጥፋትና ክፍተት ለመለየት፣ የኩባንያውን አፈጻጸም ለመገምገም ወዘተ መረጃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ መረጃዎች በዋናነት ለባለአክሲዮኖች ጠቃሚ ቢሆኑም ለሦስተኛ ወገኖች (ለተቆጣጣሪዎች፣ ለባለገንዘቦች፣ ከድርጅቱ አክሲዮን ለመግዛት ለሚፈልጉ) ጠቃሚ መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስ የንግድ ሕጋችንን ጨምሮ የሌሎች አገሮች የኩባንያ ሕጎች ግልጽነት የሚሰፍንባቸውን አራት መንገዶች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ በኩባንያው ጽሕፈት ቤት ሰነዶችን ለተፈቀደላቸው ሰዎች ክፍት በማድረግ፣ የኩባንያውን ሰነዶች ለመዝጋቢ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በማስመዝገብ፣ የተወሰኑ ሰነዶችን እንዲታተሙ በማድረግና ለባለአክሲዮኖች በጉባዔዎች ወቅት መግለጫ በመስጠት እንደሆኑም ይዘረዝራሉ፡፡

ከባለአክሲዮኖቹ አንፃር መረጃ የማግኘትን መብት ከመረመርን አተገባበሩ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ ባለአክሲዮኖች እንኳን የኩባንያውን የራሳቸውን የአክሲዮን ሁኔታና የትርፍ ድልድል መጠን መረጃ ለማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ አነስተኛ ነው፡፡ የመረጃ ክፍተቱ ደግሞ የሚከፋው በጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ነው፡፡ የንግድ ሕጉ አንቀጽ 406 ማንኛውም ባለአክሲዮን ከማኅበሩ ዋና መሥርያ ቤት ለጉባዔው ጠቃሚ የሆኑ ሰነዶችን ለማወቅ ወይም ቅጅዎቻቸውን ለመውሰድ በማናቸውም ጊዜ ሁሉ መብት እንዳለው ቢገልጽም በተግባር እስካሁን አልተተረጎመም፡፡ የአክሲዮን ማኅበራት የሒሳብ ሚዛኖችን፣ የታሪፍና የአኃዝ ሒሳቦች፣ የአስተዳዳሪዎቹንና የኦዲተሮችን ሪፖርት ቃለ ጉባዔ ወዘተ. ለባለአክሲዮኖች ዋና መሥርያ ቤታቸው እንዲያውቁ ሁኔታዎችን አያመቻቹም፡፡ በጠቅላላ ጉባዔ ላይ ሰፋፊ የሪፖርት ሰነዶች የመስጠት ልማድ በስፋት በመዳበሩ ባለአክሲዮኖች የውጭ ገጹን ቀለምና ርዕሶቹን ከማየት ውጭ በሪፖርቱ ላይ ለመወያየትና ለማፅደቅ የሚያስችል ዕውቀት አያገኙም፡፡ በጉባዔው ባለአክሲዮኖች አልፎ አልፎ የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች እንዲሁ በስማ በለውና በአሉባልታ ስለሚሆን ጉባዔው ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የኩባንያው ትርፍ ለምን እንደቀነስ፣ ወጪው ለምን እንደበዛ፣ ዕዳዎች ለምን እንዳልተሰበሰቡ፣ ብዙ ደንበኞች ለምን ኩባንያውን እንደለቀቁ ወዘተ. ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ውይይት አይደረግም፡፡ ባንኮችን በተመለከተ ችግሩ የበለጠ የተወሳሰበ ነው፡፡ ትላልቅ ባለአክሲዮኖች ተበዳሪም ስለሚሆኑ በሪፖርቱ ሰፊ ውይይት ተጎጅም ሊሆኑ ስለሚችሉ የቦርድና የኦዲተር ውይይት ሰፋ ያለ ውይይት ሳይደረግበት እንዲያልፍ ጥረት ያደርጋሉ፡፡

የሥነ ሥርዓት ጉዳዮች አለመሟላት

የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ የሚደረግበትን ጊዜና የአከናወኑን ሁኔታም የተመለከቱ የአተገባበር ችግሮች እንደሚስተዋሉ ከሚወጡ የጥሪ ማስታወቂያዎችና የኩባንያ ልምዶች መረዳት ይቻላል፡፡ የተወሰኑትን ለመመልከት እንሞክር፡፡ በመጀመሪያ የአጀንዳ አቀራረጽ ላይ የደንበኛና የድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ አጀንዳዎችን በመለየት ረገድ ብዥታ ይታያል፡፡ በዚህ ረገድ ለምሳሌ በባንኮችና በኢንሹራንሶች አካባቢ የአክሲዮን ዝውውሮችን ማፅደቅ እንደ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ አጀንዳነት የሚያዝበት አጋጣሚ አለ፡፡

በዚህ ሰሞን የወጡ የጥሪ ማስታወቂያዎችን ማስተዋል በቂ አስረጅ ነው፡፡ የንግድ ሕጉ የድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ አጀንዳዎችን ለይቶ በመግለጹ ለጉዳዩ መፍትሔ ይሰጣል፡፡ የሕጉ ቁጥር 425 የማኅበሩን ዜግነት መለወጥ፣ የኩባንያውን ካፒታል መጨመር፣ የመተዳደሪያና የመመሥረቻ ጽሑፎችን ማሻሻል በድንገተኛ ጉባዔ የሚወሰኑ ጉዳዮች ስለመሆናቸው ይደነግጋል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በባህርያቸው ከዕለት ተዕለት ሥራ ባለፉ የማኅበሩን መሠረታዊ ሁኔታ የሚለውጡ በመሆኑ በድንገተኛ ጉባዔ መታየታቸው አግባብ ነው፡፡ የአክሲዮን ዝውውር ግን ድንገተኛ ጉባዔ የማይጠይቅ ተራ የአስተዳደር ሥራ በመሆኑ በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ መታየት የሚችል ነው፡፡

ሁለተኛው ከድምፅ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በተለይ ድምፅ ቆጠራ የሚፈልጉ ምልዓተ ጉባዔ መሟላቱን ለማረጋገጥ፣ የዳይሬክተሮችን ምርጫ የማፅደቅ ሥራዎች መሠረት የሚያደርጉት የተከፈለ አክሲዮን /Paid up share/ መጠን ነው? ወይስ ቃል የተገባ /Subscribed share/? የሚለው ነጥብ አከራካሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ የሕጉ የአማርኛ ቅጅ ‹‹ከዋናው ገንዘብ ውስጥ ባላቸው ድርሻ መጠን ነው›› በማለት የሚገልጽ ሲሆን የእንግሊዘኛው ቅጂ “In proportion to the amount of capital represented” በማለት የተሻለ ገልጾታል፡፡ በባንኮች አካባቢ ጉዳዩ አከራካሪ ስለነበረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 14 ቀን 2010 በሰጠው ማብራሪያ ለድምፅ መስጠት ዓላማ ሊታይ የሚገባው የተከፈለ አክሲዮን መጠን ሳይሆን ቃል የተገባ የአክሲዮን መጠን መሆኑን ከሕጉ መንፈስ በተጣጣመ መልኩ በመተርጎሙ በዚህ መልክ ሊታይ ይገባል፡፡

የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ሊደረግበት የሚገባው ጊዜ በሕጉ በግልጽ ተመልክቷል፤ የበጀት ዓመቱ ባለቀ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ መደረግ ይገባዋል፡፡ ሆኖም በተግባር በመተዳደሪያ ደንብ ጊዜውን ያላስረዘሙ አክሲዮን ማኅበራት ከአራት ወራት ባለፈ ጊዜ ውስጥ ጉባዔያቸውን ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ሕጉ በአራት ወራት ያለማድረግ ውጤትን ባይገልጽም ድንጋጌው የራሱ ዓላማ ይኖረዋል፡፡ የበጀት ዓመቱ እንዳለቀ በተወሰነ ቅርብ ወራት ማድረግ የድርጅቱን ትርፍና ኪሳራ በአግባቡ ለመለየት፣ ለባለአክሲዮኖችም ሆነ ለሦስተኛ ወገኖች ጥቅም ስለሚኖረው ሕጉ ባስቀመጠው መፈጸሙ ይመከራል፡፡ የጊዜውን ገደብ አለመጠበቅ ከአስተዳደር ውጤታማነት /Efficiency/ ጋርም ይያያዛል፡፡

ሌላው የጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔዎችን የማስመዝገብ ግዴታ ነው፡፡ በርካታ ኩባንያዎች ባንኮችን ጨምሮ የጠቅላላ ጉባዔ ቃለ ጉባዔዎችን አያስመዘግቡም፡፡ ይህም ሦስተኛ ወገኖች ኩባንያውን በተመለከተ ሊያውቁ የሚገባቸውን መረጃ እንዳያገኙ የሚያደርግ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹም ሥራቸውን በአግባቡ ለመወጣት ያስቸገራቸዋል፡፡ በተለይ የአመራር ለውጥ የተደረገባቸው ቃለ ጉባዔዎች ካልተመዘገቡ የኩባንያዎቹ አመራሮች ድርጅቱን በመወከል የሚሠሩትን ሥራ ያደናቅፋባቸዋል፡፡

መፍትሔው ምንድን ነው?

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ተግባራዊ ኩነቶችን መዳሰስ እንጂ የሕግ ድንጋጌዎችን መተንተንና  ክፍተታቸውን መለየት አለመሆኑ በመግቢያው ተገልጿል፡፡ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ አተገባበር በአገራችን በርካታ ችግሮች እንደሚስተዋሉበት ጥናትም የሚፈልግ አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ ከጥቅም ግጭት፣ ከውክልና፣ ከመረጃና ከሥነ ሥርዓት አንፃር የተነሱት ማሳያዎች ችግሩን ያመላክታሉ፡፡ የእነዚህ ችግሮች ውጤት የአገር ኢኮኖሚን እስከመጉዳት ሊደርስ እንደሚችል የምዕራባውያኑ ተሞክሮ ጥሩ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የምዕራባውያኑ የገንዘብ ድርጅቶች ከቁጥጥር መላላት የተነሳና የድርጅቶቹ የመልካም አስተዳደር እጦት አሁን እየሆነ ያለውን ቀውስ እንድንመለከት ምክንያት መሆኑን በርካታ ጽሑፎች አስነብበውናል፡፡ የእኛም አገር የኩባንያ አስተዳደር በጊዜ ልዩነት ካልሆነ በቀር አካሄዱ ወደዚሁ ቀውስ እንዳይሆን ሥጋት አለ፡፡ በኩባንያዎች ተጠቃሚ የሆኑት ትንሽ ግለሰቦች ወይስ ባለአክሲዮችና አጠቃላይ ኅብረተሰቡ የሚለው በጥንቃቄ ሊመረመር ይገባል፡፡

ከላይ ከዘረዘርናቸው ችግሮች ስንነሳ የችግሮቹ ምንጮች ባለአክሲዮኖቹ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የውጭ ኦዲተሮችና ተቆጣጣሪ የመንግሥት ድርጅቶች መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ ባለአክሲዮኖች መብታቸውን አውቀው አይጠቀሙም፣ ዳይሬክተሮች ኃላፊነታቸውን ቸል በማለት ለግል ጥቅማቸው ይተጋሉ፣ ኦዲተሮችም ከሙያ ሥነ ምግባራቸውና ከሕግ ግዴታቸው ያፈነገጡ ሪፖርቶችን ያወጣሉ፣ ተቆጣጣሪውም ቁጥጥሩን ያላላው ይመስላል፡፡ መፍትሔውንም ከእነዚሁ ባለድርሻ አካላት ላይ መፈለግ ብልህነት ነው፡፡ ባለአክሲዮኖች መብታቸውን አውቀው ቢጠየቁ፣ አነስተኛ ባለአክሲዮኖች የራሳቸውን ቡድን በማቋቋም የኩባንያውን የዕለት ተዕለት ሥራ ቢከታተሉ፣ ያጠፉ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን ቢሽሩ በወንጀልና በፍትሐ ብሔር  ቢጠይቁ በሀብታቸው ላይ ያላቸውን መብት ያሰፋሉ፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትና ኦዲተሮች ጥያቄ በተነሳ ጊዜ የሚኖረውን ተጠያቂነት በማሰብ በቅንነትና በታማኝነት ቢንቀሳቀሱ መልካም ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ግን ብሔራዊ ባንክን የመሰሉ ተቆጣጣሪ የመንግሥት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በመሳተፍ፣ ውክልና (Proxy) የሚገደብበትን መመርያ በማውጣት፣ ልዩ ምርመራ በማድግርና ዕርምጃ በመውሰድ፣ የውጭ ኦዲተሮች በብቃትና በገለልተኛነት እየሠሩ መሆናቸውን በማረጋገጥ ወዘተ. ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getukow [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡