የኤሌክትሪክ ፍጆታችን ባለን የኃይል መጠን ላይ ይገደብ

ከቅርብ ወራት ወዲህ የመብራት መጥፋትና በተደጋጋሚ መቋረጥ በከተማው ውስጥ ይታያል፡፡ ማምሻው ላይ የጨለመው በማግሥቱም ቀኑን ሙሉ መብራት ይቋረጣል፡፡ ይክ ክስተት አስጠሊታና አሰልቺ ነው፡፡

ሰሞኑን ታዲያ ከሥራ መልስ መኖሪያ ቤቴ ወደሚገኝበት አስኮ አዲሱና አሮጌ ተብሎ ወደሚጠራው ሠፈር ስሄድ እንደወትሮው መብራት የለም፡፡ ጨለማ ነው፡፡ የለየለት ጨለማ፡፡ ‹‹አሁንስ በዛ››፣ ‹‹ከሥልጣኔ ወደ ጋርዮሽ ኅብረተሰብ እየተመለስን ይሆን?›› የሚሉ ንግግሮችን ከታክሲ ተሳፋሪዎች ውስጥ ማድመጤን አስታውሳለሁ፡፡

አገራችን አደገች፣ ተመነደገች፣ ባለ ሁለት አኃዝ ዕድገት አሳየች የሚለው አነጋገር ወሬ ብቻ የሆነ ይመስላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ውስጥ ባለንበት ወቅት ጨለማ ሲውጠን ያሳስባል፡፡ ጊዜውም ያስፈራል፡፡ ‹‹ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል፤›› የሚለው እውነታ ገና አልሠራም፡፡ ጨለማው በጣም ረዘመ፡፡ በጣምም ዘገየ፡፡ መቼም በየጊዜው ቢሮክራሲ እየተባለ የሚሰጠው ምክንያት የሥነ ልቦና ፍርኃት ለመልቀቅ የተደረገ ነው ለማለትም በመረጃ የተደገፈ አባባል አልሆንልህ አለኝ፡፡ እንዴት ሊሆን ይችላል? አስተሳሰብን ለመለወጥም ቢሆን የሚሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ ደካማ አካሄድ ነው፡፡

በሌላ ጊዜ እዚያው ዘመን በጠገበው ሠፈር አካባቢ ከሚኖረው ውስጥ ግማሹ ነዋሪ ‹‹መብራት›› ሲያገኝ ግማሹ መብራት ተቋርጦበት ቆይቷል፡፡ መብራቱ መጣ ተብሎ ‹‹ብዙም ሳይቆይ ድርግም ይላል፡፡ ነገሩ ሁሉ የልጆች ጨዋታ ሆነ፡፡ ‹‹መብራት ኃይልን መቼም አላምነውም፤›› የሚል ጓደኛ አለኝ፡፡ በብዙ ተማሮበታል፡፡ በየቀኑ በሚጠፋው መብራት ምክንያት ቢሯችን ውስጥ ሥራችንን በተገቢው መንገድ ለማከናወን አልቻልንም፡፡

በአሁኑ ጊዜ በከተማው ውስጥ የምንሰማቸው የተለያዩ ወሬዎች አሉ፡፡ ከእነዚሁ ውስጥ በጥቂቱ ከዋናው ማሰራጫ የሚለቀቀውን ኃይል የመሸከም የአቅም ችግር አለ ይባላል፡፡ የትራንስፎርመሮቹ ደረጃ ዝቅተኛ መሆን፣ የመብራት ኃይል ማኔጅመንት ችግሩን ለማስወገድ አለመቻል፣ አሁን ያለበት የኤሌክትሪክ መሐንዲሶች በቂ የሙያ ዕውቅና ክህሎት ማጣት፣ በቂ ዘመናዊ (ዓለም አቀፋዊ) የሥራ ልምድ የሌላቸው መሆን፣ የመብራት ኃይል ችግሮችን ለማስወገድ ‹‹በጨረታ ተወዳድረው›› ከባህር ማዶ የመጡት ባለሙያዎችም በታሰበውና በታቀደው መሠረት ሥራውን ሊሠሩ አለመቻላቸው ከችግሮቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንስፎርመሮችና ገመዶች ደረጃቸውን የጠበቁ ባለመሆኑ፣ የሚተላለፈውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋቁመው ሊያስተላልፉ አለመቻላቸው ይባሱኑ ያለንን ኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ጨርሰናል የሚሉትና ሌሎችንም ጨምሮ የምንሰማቸው ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡

በከተማችንም ሆነ በሌላ የአገሪቱ አካባቢዎች ለተፈጠረው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት የመንግሥት የበላይ ኃላፊዎችም ሳይውሉ ሳያድሩ ውሳኔ ሊሰጡበት ይገባል፡፡ አሉ የተባሉ መሐንዲሶችም በምን መልኩ ችግሮችን ሊለዩና ሊፈቱ እንደሚችሉ የፕሮጀክት ጥናት አዘጋጅተው ሊያቀርቡ ይገባል፡፡ ለእስካሁኑ ግን ዘግይተዋል፡፡ ሥራው ለቦጫቂና ለሙሰኛ ጨካኝ ሠራተኞች መተዳደሪያነት መተው የለበትም፡፡

በ1999 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው ‹‹ግልገል ጊቤ ሦስት›› የኃይል ማመንጫ ቀድሞውኑ እንደታቀደው 10 ዩኒት፣ እያንዳንዱ 187 ሜጋ ዋት በማምረት በጠቅላላው 1,870 ሜጋ ዋት ኃይል እንዲያመነጭ ነው፡፡ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ሲነገረን የነበረ ሲሆን፣ ዘግይቶ ወደ ሥርጭት እንደገባ ተሰምቷል፡፡ በባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ታግዞ ከወላይታ ሶዶ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ ማሰራጫ መስመርም ተዘርግቷል፡፡ ይህ ለአገራችን ትልቅ ድል ነው፡፡ ይህን መልካም ሥራ ይበል ልንል ይገባል፡፡

እንግዲህ ዋናው ነገር አጠቃቀማችንና ፍጆታችንን ካለን የኃይል መጠን ጋር ካላስተካከልነው በአመራራችን ላይ ችግር መኖሩን የሚጠቁም ነው፡፡ ‹‹ሳይተርፈው ያበደረ ሳይቀበል ተቀበረ፤›› እንደሚባለው እንዳይሆን፡፡ የምናደርገው እንቅስቃሴና ተግባር ካለን በላይ አይሁን፡፡

በከተማችን ብቻ ሳይሆን በመላው የአገራችን ክልሎች ልማት አለ፡፡ ይህ የማይካድ እውነት ነው፡፡ ባቡርን ጨምሮ የትራንስፖርት ልማት አለ፡፡ የኢንዱስትሪው ልማት፣ ብዛት ያላቸው የሕንፃ ግንባታዎች፣ ሪል ስቴቶችና የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የተለያዩ ፋብሪካዎች፣ በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋሉ ተብለው የታሰቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሌሎችም ግንባታዎችና መሰል ሥራዎች በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተለይ በገጠሩ አካባቢ የሚኖሩት ወገኖቻችን ከኃይል አቅርቦቱ መቋደሳቸውን ሳንዘነጋ ነው፡፡ ዕድገቱ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ሥራችን ሁሉ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አካሄዳችን ‹‹በአቦስጡኝ›› ላይ የተመሠረተ አይሁን፡፡

አሁን የተፈጠረውን እጥረት በምን መልኩ እንፍታው? ልንል ይገባናል፡፡ የዛሬን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም ራዕይ ባለው አካሄድ ችግሩን ልንቀንሰው ወይም ልናስወግደው ግድ ይላል፡፡ ወዴት እንደምንሄድ በቅድሚያ እንወቅ፡፡ ዘመናዊና ዓለም አቀፋዊ አሠራርን መተግበር አለብን፡፡ አለበለዚያ የምንይዘውና የምንጨብጠውን ያሳጣናል፡፡ ወደ ልማቱ ገባሁ የሚለው ሁሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ፈላጊ ነው፡፡ የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት በአፍሪካ 625 ሚሊዮን ሕዝቦች የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ እንዲያውም አገራችን ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች በተሻለ ማደጓን ሪፖርቱ ላይ ገልጿል፡፡ ከ13 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን ወደ 27 በመቶ ማሳደጓን ለዓለም ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ትልቅ ዜና ነው፡፡

እንግዲህ የኤሌክትሪክ ኃይል የሥራችን፣ የምግባችንና የቀጣይ ልማታችን መሠረት ነው፡፡ የህዳሴ ግድባችንንም ልናሰምርበት ይገባል፡፡

ዋናውን የህዳሴ ግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ብዙ አድካሚ ጉዞና ጥልፍልፍ መሰናክሎች ከፊታችን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሊሆን አይችልም፡፡ በተለይ በዓባይ ጉዳይ ተጠንቅቀን ዘብ ልንቆም ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ ከተለያዩ አገሮች ወደ አገራችን በተለያዩ የንግድ ዲፕሎማሲ ሰበብ የሚገቡትን ሁሉ ልንከታተል ይገባናል፡፡ በእጅ አዙር አገራችን ውስጥ ሊከሰት የሚችል አደጋን ነቅቶ መጠበቅ ይገባል፡፡ ‹‹ያወቀ ተጠነቀቀ፣ የዘነጋ ተነጠቀ፤›› እንደሚለው እንዳይሆን፣ ከአሁኑ በአዲስ ፕሮጀክቶች ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ ለማስወገድ እንሞክር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለጊዜውም ቢሆን ሌሎች መፍትሔዎች አሉ፡፡ ታዳሽ ኃይሎች ማለትም ከፀሐይ፣ ከነፋስ፣ ከከርሰ ምድር እንዲሁም ከባዮጋዝ የሚመነጨውን ኃይል በመጠቀም አቅርቦቱን ማሻሻል ይቻላል፡፡ ካስፈለገም ከወዳጅ አገሮች በውሰት፣ በስጦታ ወይም በግዥ ትላልቅ ሕንፃ የሚያካክሉ ጀነሬተሮችን አምጥቶ መጠቀምም አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በምናብና በምኞት ላይ ሳይሆን ያለብን ችግር በእነዚህ የኃይል አማራጮች እንድንጠቀም ያስገድደናል፡፡

በመጨረሻም ያለንን የኃይል መጠን አውቀን በጋራ ተባብረን አዳዲስ ግንባታዎችን ልናቅድ የምንችለው እንደ ፕሮጀክቱ ጠቃሚነት አንፃር መጀመርያ ለጠየቀ ቅድሚያ ሰጥቶ በማስተናገድ ነው፡፡ በዚህ አሠራርና አካሄድ መሠረት ሀቀኝነትን ደርበንበት መጓዝ አለብን፡፡ በቅድሚያ ግን እንዘጋጅ፡፡ ‹‹በሰኔ ካልዘሩ፣ በታኅሳስ ካለቀሙ፣ እህል አይገኝም ከድንበር ቢቆሙ፤›› ይላሉ አበው ሲተርቱ፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ ለጎረቤቶቻችን የኤሌክትሪክ ኃይል ልንሰጣቸው ቃልና ግዴታ የገባነውንም ሳንዘነጋ፡፡ በመሆኑም ‹‹የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች›› የሚለው ተረት እኛ ላይ እንዳይተረት እንጠንቀቅ፡፡ በአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ፍጆታችን ባለን ኃይል መጠን ላይ ይገደብ ለማለት እወዳለሁ፡፡ በመጨረሻም ሕዝቦች ከጭቆና ነፃነትን እደሚመርጡ ሁሉ ከጨለማ ብርሃንን ይመርጣሉና መንግሥት በጥሞና ችግሩን ይፍታው፡፡

(ባጫ፣ ከአዲስ አበባ)