የኢትዮጵያ ደረጃዎችና ውጤት አልባው ጉዞ

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ለተለያዩ ምርቶችና አገልግሎት ሰጪዎች ብሔራዊ ደረጃዎች በማዘጋጀት፣ በዚያ ደረጃ መሠረት አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡  

በአገር ውስጥ የሚመረቱም ሆኑ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ሊኖራቸው ወይም ሊይዙ ይገባል ያለውን የጥራት ደረጃ በመቅረጽ፣ አምራቾችም ሆኑ አስመጪዎች በዚሁ ደረጃ መሠረት እንዲሠሩ ያሳስባል፡፡ ማሳሰብ ብቻ ሳይሆን እንዲህ የሚባለው የምርት ዓይነት ወደ ገበያ ከመውጣቱ በፊት እንዲህ ያሉ ይዘቶች ሊኖሩት ይገባል በማለት ዝርዝር መስፈርቶችን አዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው ሁሉ ያሳውቃል፡፡

በአገሪቱ የደረጃ መስፈርት መሠረት የሚወጡት ደረጃዎች የአገልግሎት ዘርፉንም የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ኤጀንሲው ይህን ተግባሩን ለዓመታት በመከወን የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡም ከ400 በላይ ለሚሆኑ ምርቶችና አገልግሎቶች ደረጃ ማውጣቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በተለይ በዚህ ወቅት ለሸማቾች በሚቀርቡ የተለያዩ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ከሚታዩ ግድፈቶች አንፃር ኤጀንሲው ደረጃዎች ማውጣቱ አግባብ ነው፡፡ በግድም መሆን ያለበት ዕርምጃ ስለመሆኑ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ ከኤጀንሲው ተከታታይ ይፋዊ የሆኑ መረጃዎች መገንዘብ እንደምንችለው፣ በኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላም በተከታታይ ደረጃ የሚወጣላቸው፣ ምርትና አገልግሎቶች ይፋ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኤጀንሲው ሁሌም እንደሚያደርገው ደረጃ የወጣላቸው ምርቶችና አገልግሎቶችን የሚያቀርቡና የሚሸጡ የንግድ ድርጅቶች በዚሁ በኢትዮጵያ ደረጃ መስፈርት መሠረት መሥራት የሚጠበቅባቸው ስለመሆኑ፣ ይህንን ከተላለፉም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ያልገለጸበት ጊዜ የለም፡፡

ችግሩ ግን እነዚህ ደረጃ ተበጅቶላቸዋል የተባሉ አገልግሎቶችና ምርቶች በትክክል ሲሠራባቸው ባለመታየቱ፣ የኤጀንሲውን ዕርምጃ ፍሬ አልባ እያደረገው ነው የሚለው የሰላ ትችት ዛሬም ይሰነዘራል፡፡ ደረጃ የወጣላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች በትክክል እየተተገበሩ ስላለመሆኑ ገበያው ጭምር የሚያሳብቅ በመሆኑ፣ የደረጃ ቀረጻው ብቻውን ውጤት ያለመሆኑን እያስገነዘብንም ነው፡፡

ኤጀንሲው ባስቀመጠላቸው መስፈርት መሠረት የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው የሚመረቱ እንዲሁም ኤጀንሲው ባስቀመጠው የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ልክ እየተሠራ ያለመሆኑን መሥሪያ ቤቱ ራሱ የሚያውቀውና የሚገነዘበው ነው፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ በርካታ ምርቶችም ሆኑ አገልግሎቶች በብሔራዊ ደረጃው መሠረት ሊተገበሩ ባለመቻላቸው ቁጭት ቢያሳድርም፣ ለምን ውጤታማ ለመሆን እንዳልተቻለ ግን ግልጽ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ኤጀንሲውንም ሆነ ለአገልግሎት ሰጪዎች እንዲሠሩበት የተቀረጸው ደረጃ መተግበሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡

ከደረጃ ውጪ የሆኑ ምርቶችና ለአገልግሎት የወጡት ደረጃዎች በአግባቡ ለምን ተፈጻሚ አይሆኑም ሲባል የሚሰጠው መልስ ብዙም አሳማኝ አይደለም፡፡ በተቀመጠው ደረጃ ልክ በማይሠራ ላይ ቁጥጥር የማይደረግና ዕርምጃ የማይወሰድ ከሆነ፣ ደረጃዎች እያወጡ ብቻ መዝለቁ ምን ይፈይዳል? የሚል ጥያቄ ሲቀርብም፣ የሚሰጠው መልስ የኤጀንሲው ኃላፊነት ደረጃዎችን ማውጣት ብቻ ነው የሚል ነው፡፡ በደረጃዎቹ መሠረት ምርቶች እየተመረቱ መሆኑን፣ ከውጭም እየገቡ ስለመሆናቸው የማረጋገጥ ብሎም የመቆጣጠርና የተቀመጠውን ደረጃ የተላለፉት ላይ ደግሞ ዕርምጃ የሚወስደው ከኤጀንሲው ውጭ ያለ ሌላ አካል ነው በማለት ምላሽ ይሰጣል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ምክንያት አዲስ ባይሆንም ዛሬም ድረስ የሚሰማ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸው ምርቶች በትክክል ስለመተግበራቸው ደግሞ ኃላፊነት አለባቸው ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ንግድ ሚኒስቴር ነው፡፡ ከዚህ መሥሪያ ቤት ውጪ በተለያዩ ዘርፎች ይመለከታቸዋል የተባሉ መሥሪያ ቤቶችን የያዘ አስፈጻሚ ቡድን የማዋቀር ኃላፊነት የተሰጠው የንግድ ሚኒስቴር ይህንን ተግባሩን የዘነጋው ይመስላል፡፡ ስለዚህ ለቁጥጥሩና ለክትትሉ አንዱ ድክመት በቅንጅት እንዲሠሩ ይቋቋማል የተባለው ቡድን አለመፈጠሩና ወደ ሥራ አለመግባቱ ነው ሊባል ይችላል፡፡

በተናጠል ቁጥጥር እያደረጉ ናቸው የተባሉትም፣ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ናቸው ብሎ ለመናገር ደፋር መሆንን ይጠይቃል፡፡ ደረጃቸውን ባልጠበቁ ምርቶችና አገልግሎቶች ሸማቾች እየተፈተኑ ባለበት አገር፣ እነዚህ ተቋማት በየዕለቱ እከሌ የሚባለው ምርት ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፤ በእከሌ በሚባለው ተቋም እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ከደረጃ ውጭ ነው ወይም የአገልግሎት መስጫ መሣሪያዎቹ ከኢትዮጵያ ደረጃ ውጭ ናቸው ብለው ዕርምጃ ሊወስዱ ይችሉ ነበር፡፡ ግን ይህንን ሲያደርጉ አይታይም፡፡ ሥራቸውን በአግባቡ ስላለመወጣታቸው አረጋጋጭ የሚሆንልንም በእንከን የተሞሉ ምርቶች ገበያ ውስጥ እየታዩ ሃይ ባለመባላቸው ነው፡፡ በእነዚህ መሥሪያ ቤቶች ዕርምጃ ተወሰደ የሚለውን ወሬ የምንሰማው ከስንት ጊዜ አንዴ ነው፡፡ ነገር ግን ካለው ችግር አንፃር ድምፃቸውና ዕርምጃቸው በየዕለቱ መሰማት ነበረበት፡፡ ለዚህ ነው ተቆጣጥሮ ዕርምጃ የመውሰድ፣ ለኅብረተሰቡም የማሳወቅ ኃላፊነት የተሰጣቸው መሥሪያ ቤቶች ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ አይደለም ብሎ ደፍሮ መናገር የሚቻለው፡፡ ለዚህም ነው ደረጃዎችን እየፈለፈሉ መሄድ ብቻውን ውጤት አይሆንም የሚባለው፡፡ በሚወጡት ደረጃዎች ልክ አስፈጻሚዎችም ይትጉ፡፡

ነገሩን በደንብ ካጤንነው ኢትዮጵያ ደረጃዎች አሉዎት ከማለት ውጭ ደረጃውን ማስተባበሩ ሥራ ላይ ትኩረት ያለመሰጠቱን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከደረጃቸው ውጭ የሆኑ ምርቶችና አገልግሎቶችን ለመቆጣጠር አንድ አገራዊ ግብረ ኃይልም ሳይፈጠር እስከ ዛሬ መቆየቱ ራሱ ለምን ያስብላል?

በሌላ በኩል ደግሞ በብሔራዊ ደረጃዎች መሠረት ምርት ማምረትና አገልግሎት መስጠት ለሸማቹ ደኅንነት ብቻ የሚያገለግል አይደለም፡፡ አምራቹንም ሆነ ነጋዴውን የሚጠቅም ነው፡፡

በጥራት ማምረት ጥሩ ተወዳዳሪ ያደርጋል፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት ጥራት ላይ የተመሠረተ ምርት አምርቶ ተወዳዳሪ መሆን ግድ ይላልና፣ ኩባንያዎች በብሔራዊ ደረጃዎች በተዘጋጁት መሥፈርት መሠረት በማምረትና በማገልገል ራሳቸውንም ወገናቸውን መጥቀም እንዳለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ በራስ ተነሳሽነት መሥፈርቱን በመጠቀም እየሠሩ አርዓያነታቸውን ያሳዩ፡፡ የወጡ ደረጃዎችን የሚያስፈጽሙ መሥሪያ ቤቶችም ካሸለቡበት እንቅልፍ ነቅተው፣ ለዚህ ወሳኝ ጉዳይ በትብብር ለመሥራት ሸሚዛቸውን ይሰብስቡ፡፡