የአፈር ምርመራ ማዕከል ዕድሳትን የሚያማክረው ተቋም አለአግባብ ስሙ መነሳቱን በመግለጽ ተቃወመ

- በበጀት እጥረት የላቦራቶር ዕድሳቱ መዘግቱን ገልጿል

ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በተገኘ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ፈንድ ዕድሳት የሚካሄድለት ብሔራዊ የአፈር ምርመራ ማዕከልን በአግባቡ አልተወጣም፣ ፈንድ አባክኗል፣ ያለጨረታ ሥራውን ተረክቧል የሚሉ ቅሬታዎች የተነሱበት አማካሪ ተቋም ስሙ አለአግባብ መነሳቱን በመግለጽ ተቃወመ፡፡

ዲጋታ ኢንዱስትሪስ የተባለውና ተቋማጭነቱ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ የሆነው ይህ ተቋም፣ በግብርና ሚኒስቴር ባለቤትነት ለሚካሄደው የአፈር ምርመራ ተቋም ዕድሳት አማካሪ ሆኖ የተቀጠረ ሲሆን፣ ለማዕከሉ የላቦራቶር ሕንፃ ዕድሳት ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ከተገኘ አንድ ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 650 ሺሕ ዶላር ዋናውን የዕድሳት ሥራ ሳያጠናቅቅ ገንዘብ ተቀብሎ ሄዷል የሚል ስሞታ እንደቀረበበት መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ይሁንና የኩባንያው ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ሥላሴ ከአሜሪካ በመጡበት ወቅት ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ተቋሙ ሥራውን በአግባቡ እያከናወነ እንደሚገኝና ከተከፈለው በላይ የራሱን ገንዘብ ለፕሮጀክቱ አውሏል፡፡ አቶ ግርማ እንዳስረዱት፣ ዲጋታ ከተቀበለው 650 ሺሕ ዶላር ውስጥ ከ560 ሺሕ ዶላር በላይ ለላቦራቶር ቁሳቁሶች ግዥ ማዋሉን፣ ለግንባታ በወጣው ቀሪ ወጪን ጨምሮ ከተለቀቀለት 650 ሺሕ ዶላር በተጨማሪ ከራሱ ካዝና ከ150 ሺሕ ዶላር በላይ ማውጣቱን አቶ ግርማ አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ግዥ የተፈጸመባቸው የላቦራቶር ዕቃዎች በጂቡቲ ወደብ እንደሚገኙና በቅርቡ ወደ አፈር ምርመራ ማዕከሉ እንደሚደርሱ ተነግሯል፡፡ በምዕራፍ አንድ ለሚከናወነው የዕድሳት ሥራ አንድ ሚሊዮን ዶላር መመደቡን፣ በምዕራፍ ሁለት የሚከናወነውን ጨምሮ በጠቅላላው 2.5 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት የአፈር ምርመራ ማዕከሉ ዕድሳት በበጀት መስተጓጎል ምክንያት መጓተቱንም አቶ ግርማ ተናግረዋል፡፡ ይህም ሆኖ በጀቱ ከተለቀቀና ዕቃዎች ወደ ማዕከሉ በታቀደው ጊዜ መሠረት ተጓጉዘው ከደረሱ በስምንት ወራት ውስጥ የዋናው አፈር ምርመራ ማዕከል የዕድሳት ሥራ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር ከዚህ ቀደም ባጠናቀረው ዘገባ፣ ዲጋታ ኢንዱስትሪስ የተመረጠበት አግባብ ከጨረታ ሒደት ውጪ መሆኑ ሳይበቃ፣ በሰው ኃይል ያልተደራጀና ላላከናወነው ሥራም ከ650 ሺሕ ዶላር በላይ ተከፍሎት መሄዱ በሚኒስቴሩ የተፈጸመ ትልቅ ጥፋት ነው ያሉት ምንጮች፣ ይህ ድርጅት ያለማንም ተቆጣጣሪ መሥራቱና ያከናወነውም ይጠበቅበት የነበረበትን ባለመሆኑ ይህ አድራጎት ተጣርቶ ምላሽ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡

ይህንን ቅሬታ በመያዝ ሪፖርተር በወቅቱ ያነጋገራቸው በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍን የሚመሩት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ማብራሪያ፣ እ.ኤ.አ. በ2014 የአፈር ምርመራ ማዕከሉን እንዲያድስና የላቦራቶር ቁሳቁሶችን እንዲያሟላ ዲጋታ ኢንዱስትሪስ ከተባለው ኩባንያ ጋር ስምምነት ተደርጓል፡፡

ከጨረታ ውጪ ባለው ሕጋዊ አሠራር መሠረት ሥራውን እንዲሠራ ለዲጋታ የተሰጠው ከዚህ ቀደም ባሳየው አፈጻጸም ተመርጦ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ እስካሁን የተከፈለው ገንዘብም ቢሆን በሚኒስቴሩና በኩባንያው መካከል በተደረገ ሕጋዊ ውል መሠረት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ቅሬታ የቀረበበትና ዋናው ሥራ ሳይሠራ ከ650 ሺሕ ዶላር በላይ ተከፍሏል ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በውሉ መሠረት የቅድሚያ ክፍያ የተከፈለ ቢሆንም፣ ክፍያው እስካሁን ለተሠራው ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት ለሚሠራው ሥራም ጭምር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከውጭ የሚመጡ የላቦራቶሪ ቁሳቁሶችም በክፍያው ታሳቢ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው ያለጨረታ ስለመመረጡም በሰጡት ምላሽ፣ ከዚህ በፊት አገር ውስጥ ከላቦራቶሪ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ሲያከናውን ባሳየው ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዋናው ሕንፃ ባይታደስም ሌሎች ለጊዜው የአፈር ምርመራ ሥራው ሳይቋረጥ እንዲከናወን የሚያስችሉ ሕንፃዎች መገንታባቸውን፣ የዋናው ሕንፃ የበርና የመስኮት ዕድሳቶችም በጊዜያዊነት መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

ዋናው የላቦራቶሪ ሕንፃ ዕድሳት ያልተካሄደው አጣዳፊ አገር አቀፍ የአፈር ምርታማነትንና ደረጃን የሚያሳይ የካርታ ዝግጅት ሥራ በመሀል በመምጣቱ ለዚያ ቅድሚያ በመሰጠቱ እንጂ፣ የዕድሳት ሥራው አለመዘንጋቱን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በቅርቡ የዋናው ላቦራቶሪ ሕንፃ እንደሚጀመርና ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ብቃቱ የተረጋገጠ ተቋም እንደሚሆን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል፡፡ ከዋና የአፈር ምርመራ ላቦራቶሪ ባሻገር 17 ቅርንጫፍ ማዕከሎች በየክልሎች መክፈታቸውን ወ/ሮ ፍሬነሽ ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ላቦራቶሪውን ከሚያድሰው ዲጋታ ኢንዱስትሪስና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር በጋራ የሦስትዮሽ ስምምነት በማድረግ ወደ ሥራው ለመግባት ለተቋራጩ መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡