የአዲስ አበባ የጥልቅ ጉድጓድ የውኃ ቁፋሮ ሥራን መንግሥት ትኩረት ያድርግበት

ይኼንን አስተያየት እንድጽፍ ያነሳሳኝ እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 3 ቀን 2016 በእንግሊዝኛ በታተመው ሳምንታዊው ካፒታል ጋዜጣ ገጽ ሰባት ላይ “Digging for water to start as dam levels drop” በሚል አርዕስት የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የሰጠውን መግለጫ ካነበብኩ በኋላ ነው፡፡

የመግለጫው ጥቅል ሐሳብ በኤሌኒኖ ተፅዕኖ ምክንያት የከተማው ግድቦች የውኃ መጠን በመቀነሱና በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተውን የመጠጥ ውኃ ችግር ለመፍታት ሲባል የጥልቅ ውኃ ጉድጓድ ጥናትና ቁፋሮ ሥራ እንደሚካሄድ የሚያትት ነው፡፡

ለአንድ አፍታ ቆም ብለን ቤታችን ድረስ በቧንቧ መጥቶ ለመጠጥና ለሌላ ጥቅም የምናውለውን ውኃ እንዴት ወደ እኛ እንደሚደርስ እናስብ፡፡ ዓለም እንደ ማዕድን የሚቆጠረው አንጡራ ሀብት ቤታችን ድረስ እንዴት እንደሚመጣ በአጭሩ ላስረዳ፡፡

ለመጠጥነት የሚውለው ውኃ የሚገኝበት መንገድ በሁለት ይከፈላል፡፡ አንደኛው የገጸ ምድር ውኃ ሲሆን፣ ይህም ከዝናብና ከወንዞች በምድር ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ሁለተኛው የከርሰ ምድር ውኃ ሲሆን፣ በምድር ውስጥ ከሚገኝ አለት የሚመነጭ ነው፡፡ የእነዚህ የውኃ ምንጮች የጥናትና ግንባታ ሒደት የተለያየ ቢሆንም ሁለቱም በቧንቧ አንዱ ከሌላው ተልከው በጋራ እንጠቀምባቸዋለን፡፡

የገጸ ምድር ውኃ በሚፈለገው መጠን መኖሩ ሲረጋገጥና ውኃውን የሚይዝና የሚቋጥር ምቹ ቦታና ሁኔታ በጥናት ከተረጋገጠ በኋላ የግድብ ዲዛይን ግንባታ ሥራ ይካሄዳል፡፡ በኋላ የማጣሪየና ማከሚያ ተቋም በመትከል ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ይደረጋል፡፡ ይህ ሥራ እጅግ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚፈልግ ሲሆን፣ ከአየር ሁኔታ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው፡፡ የለገዳዲና የገፈርሳ ግድቦች በአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

እንግዲህ ከላይ ካነሳሁት ጋዜጣዊ መግለጫ ጋር እንዲስማማ ሁለተኛ አማራጭ የሆነው የከርሰ ምድር ውኃ ግኝት ምን እንደሚመሰል ላስረዳ፡፡ የከርሰ ምድር ውኃ ከጥናቱ ጀምሮ ተቆፍሮ ጥቅም ላይ እስኪውል ድረስ ያለው ሒደት ውስብስብ፣ ፈታኝና ዕውቀት ከህሎት (ልምድ) የሚጠይቅ ሲሆን፣ በተለይ የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ፣ ገንዘብና ዕውቀት ይጠይቃል፡፡

በአገራችን የከርሰ ምርድ ውኃ ጥናት፣ ፍለጋና ግኝት አስተዳደርን በተመለከተ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ከፍተኛውን የመንግሥት ሚና ይጫወታል፡፡ ሚኒስቴሩ የከርሰ ምድር ውኃን በተመለከተ ፖሊሲ ያወጣል፣ በጀት ይመድባል፣ ይቆጣጠራል፡፡ በጥናት፣ በዲዛይንና በቁጥጥሩም የውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ የተባለ የመንግሥት የልማት ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ መሥሪያ ቤት የከርሰ ምድር ውኃ የሚገኝባቸውን ሥነ ምድራዊና ወሰነ ውኃዊ ጥናቶች በማካሄድ የቁፋሮ ቦታዎችን ለይቶ ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ ጋር የተያያዙ ዝርዝር ነጥቦችን ለምሳሌ የሚቆፈረው ጉድጓድ ጥልቀት፣ የጉድጓድ ስፋት በአጠቃላይ የጉድጓዱን ዲዛይን በግልጽ ያብራራል፡፡

የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች ሲሰናዱ በአብዛኛው በተለይም የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎችን ይቆጣጠራል፡፡ ያማክራል፡፡ ኮንትራቱንም ያስተዳድራል፡፡

በዚህ የሥራ ሒደት ላይ ከሥራው ባለቤት (ከአሁን በኋላ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን) እና ተቆጣጣሪው የውኃ ሥራዎች ዲዛይን ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ  እንዲሁም ለሥራው መሳካት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱትን የቁፋሮ ድርጅቶችን ሳይጠቅሱ ማለፍ ሥዕሉን ያልተሟላ ያደርገዋል፡፡

እንግዲህ የአዲስ አበባ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሟላት በአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥር ከጥቂት ዓመታት በፊት የተቋቋመው የውኃና ሳኒቴሽን ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተጠቃሽ ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትንና ዘመናዊ ፍሳሽ አስተዳደርን እንዲመራ በከፍተኛ የመንግሥት ብድርና ዕርዳታ ገንዘብ እንዲሁም በከፍተኛ የሠለጠነ የሰው ኃይል የተደራጀ ነው፡፡

ይህ መሥሪያ ቤት የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና እንዲሁም ሦስተኛዋ የዓለም ዲፕሎማቲክ ከተማ የሆነችውን የአዲስ አበባን የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና የዘመናዊ ፍሳሽ ማስወገድ ሥራ በተመለከተ በአፍሪካ ካሉት አምስት ቀዳሚ ከተሞች ተርታ ለማሰለፍ እንደሚተጋ በመሥሪያ ቤቱ ራዕይ ላይ በግልጽ ተከትቦ ይታያል፡፡

በአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና በውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ መካከል ባለው ስምምነት መሠረት የውኃ ሥራዎች ዲዛይን ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ በአዲስ አበባና አካባቢው የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ጥናትና ፍለጋ በማካሄድ በቂ የከርሰ ምድር ውኃ ሊኖር እንደሚችል ያረጋግጣል፡፡ እንዲሁም የቁፋሮ ቦታውን በግልጽ ለይቶ በካርታና በሪፖርት ያሳያል፡፡

ከጥናቱና ፍለጋው በኋላ የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ጨረታ ይወጣል፡፡ ከዚህ ሒደት በኋላ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለቱን የመንግሥት አካላት ሌላ ሦስተኛ ባለድርሻ አካል ይቀላቀላቸዋል፡፡ ጨረታውን ያሸነፈው የጥልቅ ውኃ ጉዳጓድ ቁፋሮ ድርጅት የሥራው አካል ይሆናል፡፡

በአዲስ አበባና አካባቢው እየተካሄዱ ያሉት የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች እንዳለመታደል ሆኖ ከአገር ውስጥ ይልቅ በአብዛኛው በቻይና የቁፋሮ ድርጅቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ የአብዛኞቹ ጥልቀትም አምስት መቶ ሜትር ገደማ ነው፡፡

ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ በጣም ፈታኝና አስቸጋሪ በመሆኑ፣ በዚህ ዙሪያ የተሳካ ሥራ ለመሥራት ያሉትን ተግዳሮቶች እንመልከት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን የንጹህ የመጠጥ ውኃ ፍላጎት ለማሟላት በመጀመርያ በቂ የውኃ ምንጭ ማግኘት የግድ ይላል፡፡ በቂ የከርሰ ምድር ውኃ ለማግኘት ደግሞ በሥነ ምድራዊና ወሰነ ውኃዊ መስክ የሠለጠነና ልምድ ያለው ባለሙያ መኖሩ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህም በፌዴራል ደረጃ የተቋቋሙት የውኃ ሥራዎች ዲዛይን ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝና የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካይል ሰርቨይ በአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

የከተማ የንፁህ መጠጥ ውኃ ለማሟላት ከውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በተጨማሪ  በከተማ ደረጃ ከከንቲባው ጀምሮ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንና ሌሎቹም ከፖለቲካ ፍጆታነት ያለፈ ሳይንሱና ዘርፉ የሚጠይቀውን አመራር መስጠት አለባቸው፡፡ በይድረስ ይድረስ ሳይሆን የከተማውን የመጠጥ ውኃ ችግር በዘላቂነት የሚፈታ የመጠጥ ውኃ ስትራቴጂ ወይም ፍኖተ ካርታ በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ውስጥ ባሉ ባለሙያዎች በጥንቃቄ እንዲዘጋጅና ተግባር ላይ እንዲውል መደረግ አለበት፡፡

ይህንን ተግባር እንዲመራ በአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥር የተቋቋመው የውኃና ሳኒቴሽን ልማትና ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትም ዕውቀትና ልምድ ያለው፣ ራዕይን የሰነቀ፣ መልካም ሥነ ምግባር የተላበሰና ከስሜታዊነት ያልሆነ በሳል አመራር ያስፈልገዋል፡፡ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱም የከተማውን የንፁህ መጠጥ ውኃና ዘመናዊ የፍሳሽ አስተዳደር በተመለከተ ትልቁን ኃላፊነት ይሸከማል፡፡

ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ አሁን ያለውን መዋቅር ስናጤን ችግር ያለበት ይመስላል፡፡ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊና የቴክኒክ ምክትል ሥራ አስኪያጁ በምሕንድስና ሙያ የተመረቁ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ትልቁንና ወሳኙን የከርሰ ምድር ውኃ ምንጭን በበቂና በአስተማማኝ ሁኔታ የማግኘት ሥራን ትኩረት ያልሰጠና ፈታኙን የከርሰ ምድር ውኃ ፍለጋ፣ ጥናትና ቁፋሮ ሥራን ስንኩል ያደርገዋል፡፡ በቴክኒክ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅነት ደረጃ በከርሰ ምድር ውኃ የሠለጠነ፣ ልምድና ብቃት ያለው አመራር ቢመደብ ሥራውን የተቀላጠፈ በማድረግ የከተማውን የመጠጥ ውኃ ፍላጎት ለማርካት ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡

ለዚህ ታላቅ ሥራና ኃላፊነት የሚመጥኑ ኃላፊዎችም በቴክኒክ ዘርፉ ላይ አልተመደቡም፡፡  ከአንድ ሲቪል ሠራተኛና አመራር የሚጠበቀው መልካም ሥነ ምግባር የጎደላቸው፣ ተሳዳቢ፣ ቁጡና በገዢው ፓርቲ አባልነታቸው የሚያስፈራሩ መሆናቸው ሲታይ ምን ያህል ሥራውን እንደሚጎዳው ማንም የሚገነዘበው ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የገዥው ፓርቲ አባል ማለት ራስን ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም መስዋዕት የማድረግ ግዴታና እንደ ሻማ ቀልጦ ለሌላው ብርሃን የመስጠት መንፈሳዊ ዝግጁነትን ይጠይቃል፡፡  በእነዚህ አመራሮችና በሌሎች አንብላ ባይ፣ አስመሳይ የገዢው ፓርቲ አባላት በኩል የምንመለከተው ግን ምትክ የለሽ ሕይወታቸውን መስዋዕት ባደረጉትና ለመልካ የሕዝብ ልዕልና ሲታገሉ ጉዳት በደረሰባቸው የማፌዝ ተግባር ነው፡፡

የከርሰ ምድር ውኃ ጥናትና ፍለጋ፣ እንዲሁም የጨረታ ሒደት ሥራዎች ወሳኝ የመሆናቸውን ያህል የቁጥጥር ሥራውም ታላቅ ሚና ይጫወታል፡፡ እዚህ ላይ የአገሩንና የሕዝቡን ጥቅም የሚያስቀድም በእውቀትና በልምድ የታነፀ ባለሙያና የቁጥጥር መሥሪያ ቤት ያስፈልጋል፡፡

በብዛት እንደምታዘበው የፀረ ሙስና ዘመቻው በመንገዶችና ሕንፃዎች ግንባታ ላይ ብቻ ያተኮረ ይመስላል፡፡ ለውኃ ሥራዎች ግንባታም የሥራዎቹን ባህርይ ያገናዘበ የፀረ ሙስና ትግል እንዲደረግ ትኩረት ቢሰጠው ጥሩ ነው፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በከርሰ ምድር ውኃ ሴክተር ላይ የከርሰ ምድር ቁፋሮ ድርጅቶች ሚና የማይተካ ነው፡፡ በከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮ ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች መንግሥታዊ ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በተለይም የጥልቅ ውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ የሚያካሄዱ ድርጅቶች በአብዛኛው የውጭ ሲሆኑ ከእነዚህም የቻይና ድርጅቶች ይበዛሉ፡፡

አብዛኞቹ የውጭ ድርጅቶች የሚታየውን የመጠጥ ውኃ ፍላጎትና አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት በመንግሥት ግብዣ የመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ግን ብዙ ፈተና ያጋጥማቸዋል፡፡ ሥራው ውድ የቁፋሮ መሣሪያዎችን፣ ከፍተኛ ገንዘብና የሠለጠነ ከፍተኛ ባለሙያ ይጠይቃል፡፡

በአብዛኛው ሥራውን በራሳቸው ገንዘብ ነው የሚያካሂዱት፡፡ በዚህ ላይ የሥራውን ባህሪይ በወጉ የሚረዳ አመራርና ባለሙያ ካላገኙና የሥነ ምድር ሁኔታው አስቸጋሪ ከሆነ (ጠንካራ አካላትና ሌሎችም አስቸጋሪ ሁኔታዎች) ፈተናዎች ይበዛል፡፡

በዚህ ላይ አንዳንዶቹ የቁፋሮ ድርጅቶች የራሳቸው ችግር እንዳለባቸው የሚታወቅ ሆኖ ከጨረታ ውድድሩ ጀምሮ ቁፋሮው ተጠናቆ ክፍያው እስኪፈጸም ድረስ ብዙ የሙስና ፈተናዎች ያገጥሟቸዋል፡፡ በጥልቅ የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ ወቅት 500 ሜትር ጥልቀት ሥራ ለማከናወን የሚችሉ ድርጅቶች ቁጥር ማነስ የጥልቅ ውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ ዋጋው እንዲንርና ጥቂቶች የውጭ ኩባንያዎች እንዲቆጣጠሩት አድርጎታል፡፡

በተለይም ለዋጋው መናር የመንግሥት የቁፋሮ ድርጅቶች እንዲሸጡ መደረግና በየክልሉ ያሉት መንግሥታዊ የቁፋሮ ድርጅቶች አቅም ማነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡

የጥልቅ ውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራን አስቸጋሪ ከሚያደርጉት አንዱ ተፈጥራዊ የከርሰ ምድርና የሃይድሮጂኦሎጂ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ በአብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ የሚቆፈሩት ጉድጓዶች ስፋት ከ12 ኢንች እስከ 26 ኢንች ሲሆን እጅግ ጠጣር አለቶች፣ ፈራሽና ለስላሳ አለቶች፣ የከርሰ ምድር ውኃ ግፊት የማሽኑ አቅምና የቆፋሪዎች ብቃት ማነስና ሌሎችም ሁኔታዎች የቁፋሮ ሥራውን ፈታኝ ያደርጉታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን የንፁህ ውኃ አቅርቦት በተመለከተ ስላሉት ሁኔታዎች ከሞላ ጎደል የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ዙሪያ የሚካሄደውንና ለወደፊቱ የሚካሄደውን የጥልቅ ጉድጓድ ውኃ ቁፋሮ ሥራን ለማሳካት ራዕይንና ብቃትን የሰነቀ አመራር ወይም ተቋም፣ የሠለጠነና ልምድ ያለው፣ በሥነ ምግባሩ የታነፀ ባለሙያ፣ ልምድና አቅም ያላቸው አገር በቀል ድርጅቶት እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ መንግሥታዊ የጥልቅ ጉድጓድ ውኃ ቁፋሮ ድርጅቶችንም በፌዴራል ደረጃ በማቋቋምና በየክልሉ ያሉትን የቁፋሮ ድርጅቶች በማጠናከር በውጭ ድርጅቶች ቁጥጥር ሥር ያለውን የጥልቅ የከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮ ሥራን መንግሥት መታደግ ይጠበቅበታል፡፡

(ረምኃ ቀስቀስ፣ ከአዲስ አበባ)

****

የዘውዲቱ ሆስፒታል የሕክምና ስህተት የሆስፒታሉ ችግር ብቻ አይደለም

ሚያዝያ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው ሪፖርተር ጋዜጣ፣ በዘውዲቱ ሆስፒታል ታካሚ በነበሩት በወይዘሮ ሰላም ደሞዜ ላይ የተፈጸመው ስህተት በመላ ኢትዮጵያ ባሉ የሕክምና ተቋማት አይፈጸምም ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም ስህተቱ የተሠራው ታማሚዋን ባከመው ዶክተር ብቻ ሳይሆን ተጠያቂ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ማለት ከጤና ጥበቃ ጀምሮ ባሉት ጭምር በመሆኑ ነው፡፡

በመሠረቱ አንድ ታካሚ ወደ ኦፕሬሽን ክፍል ከመግባቱ በፊትና ሙሉ ማደንዘዣ ከመውሰዱ በፊት በሕክምና ካርዱ ላይ ወይም በኮምፒዩተር ውስጥ ያለው የታካሚው መረጃ በአጭር ካርድ ተጽፎ በእጁ ላይ መንጠልጠል አለበት፡፡ ይኼ ሲደረግም የተካሚው ማንነት ተጠይቆ በድጋሚ መረጋገጥ አለበት፡፡ ይህ አሠራር በመላው ዓለም የሚሠራበት ሲሆን፣ በተለይ በመኪና አደጋ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም ከኪሳቸው መታወቂያ በማውጣት ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ስማቸው እጃቸው ላይ ካለው ጋር እንዲናበብ መደረግ አለበት፡፡

ይኼ አሠራር ሰዎችን በቀላሉ ለመለየት የሚረዳ ሲሆን፣ በአደጋ ጊዜ ሰው ስሙን መናገር የማይችለበት ሁኔታ በመኖሩ የሚጠቅም አሠራር ነው፡፡ በመሆኑም በዘውዲቱ ሆስፒታል በተፈጠረው ስህተት ዶክተሩ ብቻ ተጠያቂ ባለመሆናቸው ከጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ጀምሮ ለተሠራው ስህተት ባለድርሻ በመሆናቸው፣ ዶክተሩን ወደ ሥራ መልሳችሁ ስህተቱን እንዳይደገም ከላይ በተጠቀሰው መሠረት እንዲታረም ብታደርጉ መልካም ነው፡፡

በአገራችን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ባለሥልጣናት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በስህተት እንደሚወድምና አልፎ አልፎ የሰው ሕይወት እንደሚጠፋ ለማንም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ተባረሩ፣ ከሥልጣን ሲባል ሰምተንም አናውቅም፡፡ የሙያተኞች የሥራ ስህተት ዕርምጃ የሚያስወስድ በኃላፊነት የሚያስጠይቅ ቢሆንም፣ ከተፈጠረው ስህተት ተነስቶ አስተማሪ የሆኑ ዕርምጃዎችን መውሰድ ከሁሉም በላይ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ መልክ እየተራረምን ወደ ተሻለ አሠራር ቀጣይነት ባለው መልኩ መሄድ በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

(መታሰቢያ መላከሕይወት፣ ከአዲስ አበባ)