የአንበሳው ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው

አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት በቀድሞ ስሙ በኢትዮጵያ የተሽከርካሪ መኪናዎች አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር በሚል ስያሜ ለትራንስፖርት አገልግሎት መነሻ አድርጎ የጀመረው ጣሊያን ኢትዮጵያን ለቆ ሲወጣ ጥሏቸው በሄደው አምስት የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ነበር፡፡

በዚሁ መሠረት ድርጅቱ በ1935 ዓ.ም. በሕግ ታውቆ ሥራውን ሲጀምር በአዲስ አበባ ከተማና በክፍለ አገር ሕዝቡን ያለምንም ችግርና የሥራ መጓተት አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር በጊዜው የነበሩ ሠራተኞችና መዛግብቶች ምክስርነታቸውን እንደሚሰጡና እንደሚያረጋግጡ የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ ድርጅቱ እንዲህ እያለ ወደፊት ቢራመድም በ1966 ዓ.ም. አብዮት ተብየው ሲፈነዳ በአክሲዮን ማኅበርነት ይንቀሳቀስ የነበረው ድርጅት ከነሐሴ 21 ቀን 1966 ዓ.ም. ጀምሮ በወታደራዊ መንግሥት እንዲወረስ ተደረገ፡፡ እስከ ሰኔ 30 ቀን 1986 ዓ.ም. ድረስም የተከማውንና የክፍለ አገሮቹን አውቶብሶች በባለቤትነት ይዞ ሲያስተዳደር ቆየ፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 1986 ዓ.ም. በኋላም ድርጅቱ ለሦስት ተከፈለ፡፡ ይኸውም አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት፣ ዓባይ ቴክኒክ አገልግሎት ድርጅትና ዋሊያ አገር አቋራጭ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ተብለው በሚጠሩ ሦስት ድርጅቶች ተከፋፈለ፡፡

በአሁኑ  ወቅት ከሦስቱ ድርጅቶች እየተንገዳገደ በሕይወት ያለው አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ብቻ ነው፡፡ ዓባይ ቴክኒክ አገልግሎት ድርጅት ለባለሀብት ተሸጧል፡፡ ዋሊያ አገር አቋራጭ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ከስሟል፡፡ አሁን ደግሞ አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት እንዲከስምና ህልውናው እንዲያበቃ ከመንግሥት ጫናና ተፅዕኖ ባሻገር በየፈርጁ ሌብነት እየተስፋፋበት ይገኛል፡፡ ይኸውም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ሠራተኞች የሥራ ልብስና የወር ደመወዝ በሕይወት ያሉ በማስመሰል እየፈረሙ ለግል ጥቅም የሚያውሉ ሰዎች በውስጡ እንዳሉ የአንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የሰሞኑን ትኩስ ወሬ ሆኖ በከተማው ውስጥ እየናኘ ይገኛል፡፡ ሌቦቹም ከሥራ ታግደው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ ነው ተብሏል፡፡

ነገርዬው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ለድርጅቶች በኮንትራት የሚሰጡ አውቶብሶች በየወሩ ተጽፎ የሚላከው የአገልግሎት ክፍያ ቼክ ለግለሰብ ኪስ መደጎሚያነት ይሰጥ እንደነበር አንዳንድ ሠራተኞች ሲናገረ ይደመጣሉ፡፡ ቼኩን ለግለሰቦቹ የሚያመጣው  ታማኝ የከተማ አውቶብስ ሾፌር እንደነበር ሠራተኞቹ ያወራሉ፡፡ አሁን ግን የኰንትራት አገልግሎት ክፍያ የሚሰበስብ ቋሚ ሠራተኛ መመደቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ድርጊት ሲፈጸም የነበረው ከ2002 እስከ 2005 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ነበር ይባላል፡፡  ድርጅቱ ይህንን የሚያጣራበት መንገድ ካለው አጣርቶ እውነታውን ቢያወጣ መልካም ነው፡፡

በአንበሳ የተከማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ላይ  ተገልጋዩ ኅብረተሰብ የሚያነሳው ቅሬታና እሮሮ ትክክልና ተጨባጭ እውነታ ነው፡፡ የስምሪት ቁጥጥር መላላት፣ የሾፌሮች የመስመር ቁጥር መድረሻ ላይ ሲደርሱ መጥፋትና በተሰጣቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት አገልግሎት የማይሰጡ መሆኑ፣ ንፅህናቸው የማይጠበቅ መሆኑን ሁሉ ከሕዝብ አንደበት በሚዲያ ሲገለጽ ሰምተናል፡፡ ስለጉዳዩ በድርጀቱ የተሰጠውን መልስም ሰምተናል፡፡ መቼም አንድ ችግር ሲገለጽና ተግሳፅ ሲቀርብ አሜን ብሎ የሚቀበል የለም፡፡

በመሠረቱ የትራንስፖርት አሠራር ዘዴው ካልተለወጠ በስተቀር በእስራኤላዊው ሥራ አስኪያጅ ተጠንቶ በየክፍሉ ሥራ ላይ ይውል የነበረው የአስተዳደር ስልት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲሠራበት የነበረ ነው፡፡

የአውቶብሶቹን ንፅህና የሚጠብቁ የተሽከርካሪ ፅዳት ሠራተኞች እንደነበሩና አውቶብሶቹን ለእጥበት የሚያቀርቡና ነዳጅ የሚሞሉ የሌሊት አገልግሎት ሾፌሮች እንደነበሩም የሚካድ አይደለም፡፡ እዛው ላይ አንድ እውነታ ሳልጠቁም አላልፍም፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ አንድ አውቶብስ ሳይፀዳ ስምሪት ላይ ቢገኝ ወዲያውኑ የጎን ቁጥሩ፣ የመስመሩ ቁጥሩ ተገልጾ አውቶብሱ ለምን ሳይፀዳ ስምሪት ላይ እንደዋለ ስልክ ተደውሎ ሥራ አስኪያጅ ይጠየቅ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አውቶብሶቹ የሚታጠቡት በውኃ ብቻ አይደለም፡፡ በሚገባ በተለምዶ በውሻ ቆዳ ተብሎ በሚጠራው በኦሞ ተፈትጎ መስታወት መስሎ ነው፡፡

ፅዳት ሲሆን ቦታ አጣ፡፡  የሥራ ባህል ተቆርቋሪነትም በመደምሰሱ አገልግሎት ሲሰጥ የዋለው አውቶብስ ሳይፀዳ ቆሻሻውና ትውከቱ በወለሉ ላይ እንደተዝረከረከ መልሶ ስምሪት ላይ ይውላል፡፡ ይህ ተጠቃሚው የሚገልጸው ቅሬታ ነው፡፡ ታዲያ ስለፅዳቱ ለወደፊቱ ከወጣት ማኅበር ጋር እየተነጋገርን ነው ብሎ በሚዲያ ማደናገሪያና ማስተባበያ መስጠት ራስን ማታለል አይሆንም? ወይስ የሌሊቱ አገልግሎት ሥራ ሌሊት ሙሉ በሙሉ ተሰርዞ አውቶብሶቹ ሳይፀዱ እንዲወጡ እየተደረገ ነው?

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በሦስት ዲፓዎች ተከፋፍለው ራሳቸውን ችለው የሚተዳደሩ ቅርንጫፎች ያሉት ስለሆነ የእያንዳንዱ ዴዲፓ ሥራ አስኪያጅ የአውቶብሶቹን ፅዳት የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ተገልጋዩም ሕዝብ የቆሻሻውን አውቶብስ የጎን ቁጥርና መስመሩን በመመዝገብ ለሚመለከተው አካል ቢያሳውቅ ይህ አውቶብስ ከየትኛው ዴፖ እንደተሠራ ስለሚታወቅ ለዕርምጃ አወሳሰድ ያመቻል ብለን እንገምታለን፡፡

ሌላው ይቅርና በከተማው ውስጥ አውቶብሶች ተሳፋሪን የሚጭኑበትና የሚያወርድበት ፌርማታ (የአውቶብስ ማቆሚያ) ምልክት የሌለበት ከተማ ሆኗል፡፡ ምናልባት መንገዶች በግንባታ ላይ በመሆናቸው የአውቶብስ ፌርማታ ምልክት አልተደረገም የሚል መልስ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ግንባታቸው አልቆ ለተሽከርካሪ ክፍት በሆኑት መንገዶችስ ፌርማታ አለ ወይ? ከድርጅቱ መልስ እንፈልጋለን፡፡ አልፎ አልፎ በሚታዩት ፌርማታዎች ላይ የቤት መኪናዎችና ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎች ሲቆሙበት የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ፖሊሲዎች የቤት መኪናዎች ከፌርማታ 12 ሜትር ዕርቀት እንዲቆሙ የሚጠይቀውን የትራፊክ ደንብ በራሳቸው ሥልጣን ሰርዘውታል ማለት ይቻላል፡፡ በፌርማታው ላይ አውቶብሱ ቆሞ ተሳፋሪ ቢያወርድ የሚጠቀመው የአውቶብስ ሾፌሩ እንጂ በፌርማታ ላይ የቆመው መኪና አይደለም፡፡ ምናልባት ይህ አካሄድ ወቅቱ የወለደው ዴሞክራሲ እንዳይሆን እንሠጋለን፡፡

ሌላው ድርጀቱ አልፎ አልፎ ለአውቶብስ ማቆሚያ ታፔላ ከመትከል ውጭ ቀለማቸው የለቀቀውን የመንገድ ጠርዞች በያመቱ ማደሱን ትቶታል፡፡ ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ፌርማታዎቹ ከጥቅምት ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ዕድሳት ይደረግባቸው ነበር፡፡ በደርግ ጊዜም እንደዚሁ የጠርዞቹ ቀለም ከአገልግሎቱ ውጪ ለመንገዶቹ ውበት ይሰጥ ነበር፡፡ የአንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ቀለም ‹‹ቴትራሳይክሊን›› ራሳቸው የአዲስ አበባ ከተማ ውበት ሆነው የቆዩ ናቸው፡፡ አሁን አሁን ግን  እንኳን ለቀለማቸው አውቶብሶቹ ራሳቸው ወደማይኖሩበት መንገድ እያመሩ ነው፡፡ አውቶብሶች ከግንቦት ወር ጀምሮ በአረንጓዴ ቀለም ሊወረሩ መሆኑን እንድታውቁት፡፡ 73 ዓመታት ለደሃው ኅብረተሰብ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን ድርጅት በሌብነተ በብልሽት አስተዳደር የተጠመዳችሁ የከተማ አውቶቡስ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ህልውና ልታሳጡት በመሆኑ የታሪክ ተወቃሽ መሆናችሁን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

(ጎመረው፣ ከአዲስ አበባ)

*****

የከተማ ፅዳት ያለህ

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንዲሁም ከኒዮርክና ብራስልስ ቀጥላ የኮንፈረንስ ከተማ ስለመሆኗ በአገራችን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ እንዲሁም እየተነገረ ይገኛል፡፡ ‹‹ጽድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነነኝ›› እንዲሉ ከኒዮርክና ከብራስልስ ጋር መወዳደሩ ቀርቶ ከአፍሪካ ከተሞች ጋር ለማወዳደርም ይከብዳል፡፡

በአንድ ወቅት Exploredia የተባለ ድረ ገጽ የለቀቀውን መረጃ ስመለከት፣ አዲስ አበባ በዓለም ቆሻሻ ተብለው ከተቀጠሱት አሥር ከተሞች ውስጥ ድረ ገጹ በዘጠነኛ ደረጃ አስቀምጧታል፡፡ መረጃውን ስመለከት በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ የአፍሪካ ከተማና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እየተባለች የሚነገርላት ይህች ከተማ በዓለም ቆሻሻ ከሚባሉ ከተሞች በዘጠነኛ ደረጃ መቀመጧ አሳዛኝና አሳፋሪ ነው፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋ ውበት እንዲጠበቅ ለማድረግ የውበት፣ መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ኤጀንሲ የሚል ተቋም እንዳቋቋመ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ተቋሙ ምን እየሠራ እንደሆነ አላውቅም? ተቋሙ የከተማዋን ውበት መጠበቅ ከሆነ ሥራው ለምን ከተማዋ በቆሻሻ እስክትሞላና በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ እስከምትሆን ድረስ ተቋሙ ምን እየሠራ እንደሆነ አልገባኝም?

ክቡር ከንቲባ እባክዎ ኤጀንሲው ሥራውን እንዲሠራና የከተማዋ ውበት እንዲጠበቅ መፍትሔ ይፈልጉለት? ከተማችን የአፍሪካና የዓለም አቀፍ መሳለቂያ መሆኗ ይብቃ፡፡ ፅዳትና ውበት የአንድ ከተማ የሥልጣኔ መለኪያ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በዚህ ዙሪያ የድርሻቸውን እንዲወጡ ትኩረት ቢሰጠው፡፡

(ጎይቶም፣ ከአዲስ አበባ)