የሲሚንቶ ገበያ ተቀዛቅዟል ማለት ሟርት አይሆንም?

በአንድ ወቅት ሲሚንቶ ዋጋው አልቀመስ ብሎ ብዙዎችን አንጫጭቷል፡፡ በወቅቱ በአገሪቱ ይካሄዱ ከነበሩት ግንባታዎች ስፋት አንፃር በአገር ውስጥ የሚመረተው ሲሚንቶና በፍላጐቱ መካከል ሰፊ ልዩነት ተፈጥሮ ግራ ሲያጋባ ተመልክተናል፡፡ መቼም ‹‹ግርግር ለሌባ ያመቻልና›› የሲሚንቶ እጥረቱን ተከትሎ ‹‹የኮንትሮባንድ›› ንግዱም ጦፎ ነበር፡፡ ግብይቱንም ቢሆን ትርምስምሱ እንዲወጣ ማድረጉን አንዘነጋም፡፡ ከሲሚንቶ የሚገኘውን ስንጥቅ ትርፍ በመመልከት ትክክለኛው ገንቢም ሆነ ከግርግሩ ‹‹ተጠቃሚ›› ለመሆን የቋመጠ ሁሉ፣ ሲሚንቶ ፈላጊ ሆኖ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወረፋ ውስጥ ገብቶ ግዥ ለመፈጸም ተፍጨርጭሯል፡፡ ወረፋው ደርሶት የጠየቀውን ሲሚንቶ ያገኘው የሲሚንቶውን ቀረጢት እንኳን ሳይመለከት፣ እዚያው ፋብሪካው ደጅ ላይ አየር በአየር ሲቸበችብም ነበር፡፡

ሌላው ቀርቶ በወቅቱ ሲሚንቶ የሚያስገኘውን ትርፍ የተመለከቱ አንዳንድ ኮንትራክተሮች ሳይቀሩ፣ በእጃቸው ላለው የመንገድ ሥራ እንዲያውሉ የተፈቀደላቸውን ሲሚንቶ አየር ላይ እያሻገሩት ነው የሚለው ሀሜትም መስማቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ነገሩን ጠልቀን ከተመለከትነው በወቅቱ የቱንም ያህል እጥረቱ ቢኖር ችግሩ እንዲሰፋ ያደረገው፣ ሲሚንቶ በቀጥታ በግንባታ ላይ ሳይውል ከአንዱ አትራፊ ወደ ሌላኛው እየተሻገረ አየር በአየር መንከባለሉና እንዲህ ያሉት ያልተገቡ ተግባራት ነበሩ፡፡ አንዳንዶችን ደግሞ የሲሚንቶ እጥረቱን ተገን አድርገው በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ግንባታ ላለማጠናቀቃቸው ሰበብ ነበር፡፡

በአንፃሩ ደግሞ የታየው ክፍተት ጥቂት የማይባሉ ኢንቨስተሮችን ወደ ሲሚንቶ ማምረት ሥራ አይናቸውን እንዲጥሉና የተለያየ መጠን የማምረት አቅም ያላቸውን ፋብሪካዎች በተለያዩ አካባቢዎች እንዲገነቡ አስችሏል፡፡

ዛሬ ግን በሲሚንቶ ገበያ ውስጥ እንሰማና እናይ የነበረውን ዓይነት ነገር የለም ሊባል ይችላል፡፡ ግንባታዎች አሁንም የቀጠሉና ወደፊትም የሚቀጥሉ ቢሆንም፣ በጥቂት ዓመታት ልዩነት የተፈጠሩ ፋብሪካዎች ግን ያመረቱት ሲሚንቶ ገበያ ቀዝቅዞብናል የሚል ድምፅ እያሰሙ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየሰማነው ያለነው የሲሚንቶ ገበያ መቀዛቀዝን ሲሆን፣ ይህ ጉዳይ ግን እንደኔ ብዙም አስጊ አይደለም፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ኩባንያዎች ወደዚህ ዘርፍ እንዳይገቡ ጋሬጣ ይሆናል ተብሎም አይታሰብም፡፡ የገበያው መቀዛቀዝ መንስዔ የራሱ የሆነ ፍተሻ ቢያስፈልገውም፣ በሲሚንቶ እጥረት የታለፈው አስቸጋሪ ሁኔታ አሁን እየተነገረ ካለው ሥጋት ጋር እንመዝነው ከተባለ ክስረቱ የዕድገት ምልክት ነው ሊባል ይችላል፡፡

ይህም የአገራችን ሲሚንቶ ምርት መጠን ደረጃ ከፍ እያለ በመምጣቱ የሲሚንቶ አምራቾች ከአገር ውስጥ ገበያ ባሻገር ዓይናቸውን ከኢትዮጵያ ውጭ በመጣል ገበያ እንዲያፈላልጉ የሚገፋፋቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ በአንድ ወቅት ምርቱን ለማግኘት ፈጣሪ የሚለመንበት የነበረው የሲሚንቶ ምርት፣ ዛሬ የተትረፈረፈ ምርት እየታየበት ነው መባሉ የዘርፉ የቢዝነስ ስትራቴጂ መፈተሽ እንዳለበት ያመለክታል፡፡

ከዚህም በኋላ ቢሆን ወደ ምርት ይገባሉ የተባሉ አዳዲስ ፋብሪካዎች ስለሚኖሩ የአገሪቱ ዓመታዊ የሲሚንቶ ምርት ወደፊትም ከፍ ማለቱ አይቀርም፡፡ ይህም ዜና ጥሩ ነው፡፡

የአገር ውስጥ ገበያውም ቢሆን አሁን እንደሚባለው ተቀዛቅዞ ይቀጥላል ተብሎ አይታመንም፡፡ የምርት መጠኑ እየጨመረ መምጣት ግን አዳዲስ ገበያ ወደማፈላለግ ሊገፋፋን ይገባል፡፡ መገፋፋት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ አቅምን ፈጥሮ ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚቻል በመሆኑ፣ የሰሞነኛው ሥጋትም በዘርፉ ብዙ መሠራት እንዳለበት ይጠቁማል፡፡ ስለዚህ አዳዲስ ሐሳቦችን በማመንጨት ለተሻለ ተጠቃሚነት የሚገፋፋ መልካም ዕድል ተደርጐ መወሰድ አለበት፡፡

በሲሚንቶ ኮንክሪት ምርጥ የሚባል መንገድ መገንባት እንደሚቻል ባለሙያዎች ማረጋገጣቸውን በምሳሌነት መጥቀስ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንም ሲሚንቶን ዋነኛ ግብዓት የሚደረገውን የኮንክሪት መንገድ ግንባታዎችን ጀምሯል፡፡

ስለዚህ አሁን ተቀዛቀዘ የተባለው ገበያ ጊዜያዊ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ፋብሪካዎችን የሚያስከፍት ብዙ ሥራዎች ያሉ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ችግሩ ግን እንደ ብዙዎቹ የአገራችን ኩባንያዎች ገበያን አጥብቦ የመመልከትና በቀላሉ ወዲያው ወዲያው ትርፍ የሚገኝበት ገበያ ላይ ማተኮራቸው ያመጣው ሰበብ ካልሆነ በስተቀር የገበያው መቀዛቀዝ ባልተነገረ ነበር፡፡

በመሆኑም ተቀዛቅዟል የተባለውን ገበያ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎቻችን አሁን ገጠመን የሚሉት ምክንያት ለቢዝነሳቸው አማራጭ ገበያን ለመፈለግ ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራ ካለመሥራት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አይገባ ይሆን?

ዛሬ ጐረቤት አገሮች ሲሚንቶ ባህር አቋርጠው እያስገቡ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ለጐረቤት አገሮች ማቅረብ ምን ይገድ ነበር? አሁንም ቢሆን የሲሚንቶ ፍላጐት በአገር ውስጥ ተሟልቷል ብሎ ማመን ቢከብድም፣ በውጭ ምንዛሪ ጥም የደረቀውን የአገሪቱን ከናፍሮች ለማርጠብ ግን እንዲህ ያሉ ዕድሎች ፈጽሞ ሊታለፉ አይገባም፡፡ በተለይ ድንበር ተሻጋሪ ጥሩ ጥሩ መንገዶች መገንባት፣ የሲሚንቶ ጥሬ ዕቃው እዚሁ መገኘቱና የመሳሰሉት ዕድሎች አሉ፡፡

እንደኔ እንደኔ በዚህ ወቅት በጋራም ሆነ በተናጠል የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የአገር ውስጥ ፍላጐትን እያሟላን ነው ካሉ፣ ቢያንስ ቀሪ ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚችሉበትን መንገድ ዛሬ አንድ ብለው መጀመር አለባቸው፡፡

ሌላው ደግሞ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገዶች ግንባታ ተጀምሯልና፣ ይህ እንዲስፋፋ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር የሲሚንቶ ምርትን ማቅረብ ይቻላል፡፡ መቼም ሌላ ሰበብ ካልተፈለገ የኮንክሪት መንገዶች በከፍተኛ ወጪ የሚገነባውን የአስፓልት ምርት በመደገፍ የሚኖረው አስተዋጽኦ፣ ሲሚንቶ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ከመሆን አልፎ የውጭ ምንዛሪ አዳኝም በመሆን ‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ…ቡና….ቡና…›› ተብሎ ለቡና እንደተዜመ ሁሉ ለሲሚንቶም ተስማሚ ስንኝ ሊገጠምለትና ዜማ ሊቀኝለት ያስችላል፡፡ እዚህ ደረጃ ለመድረስም ተዓምር ሆኖ መታየት የለበትም፡፡ ከታሰበበት የሚሳካም ነው፡፡ በተለይ የሲሚንቶ ግብዓት የሚሆነው ዋነኛ ጥሬ ዕቃ እዚሁ መኖሩ፣ እንደሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶች ጥሬ ዕቃውን ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ አጣሁ፣ የወደብ አገልግሎት ተስተጓጐለብኝ የሚል ሰበቦች የለውምና ዘርፉን የውጭ ምንዛሪ መገኛ ለማድረግ መሥራት ጊዜው አሁን ነው፡፡ የመንግሥትም ድጋፍ ከተፈለገ ይነፈጋቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ለመንገድ ግንባታውም ቢሆን በአገሪቱ ከሚሠሩ መንገዶች ቢያንስ አሥርና 15 በመቶ በኮንክሪት እንዲሠሩ የሚያስችል አሠራር እንዲቀረጽ ማድረግም አይከብድም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የፋብሪካዎቹ የእስከዛሬ ጉዞም በቅጡ መፈተሽ አለበት፡፡ የትርፍ መጠናቸውን ማስላት ይኖርባቸዋል፡፡ እንደሚባለው የሲሚንቶ የመሸጫ ዋጋ የተጋነነ ነው፡፡ ስለዚህ በአገር ውስጥ የተለመደውን ዋጋ ይዞ ድንበር ተሻግሮ ለመሸጥ ከተሞከረ ሲሚንቶው ሳይላክ ቀረ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የቢዝነስ ስትራቴጂው ተወዳዳሪ መሆን አለበት፡፡ የዋጋው ነገር ለውጭ ገበያው ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥም ተፈጻሚ ማድረጉም መዘንጋት የለበትም፡፡ ከብዙ ጥቂት በማትረፍ የማያቋርጥ ትርፍን ለማስቀጠል ከተፈለገ፣ የትርፍ ህዳጋቸውን ማጥበብ ግድ ይላቸዋል፡፡ ቀጣዩ ስትራቴጂያቸውም ከዚህ አንፃር መቃኘት ይኖርበታል እንጂ ገበያ ቀዘቀዘ ተብሎ ሲነገር ገበያችሁን ለማስፋት እናንተስ ምን ሠራችሁ? የሚል ጥያቄ መቅረቡ አይቀርምና፣ በዘርፉ ያለውን ዕድል በአግባቡ ይጠቀሙ፡፡