የሰሚቱ ሕንፃ መደርመስ ምን አስተማረን?

እሁድ ሚያዝያ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ታትሞ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ሰሚት አካባቢ ባለአምስት ፎቅ ሕንፃ በጥራት ችግር መደርመሱን የሚገልጽ ዜና በፎቶ አስደግፎ ማውጣቱን በማመስገን ልጀምር፡፡ መኖሪያ ቤቴ ሕንፃው ከሚገኝበት ቦታ በቅርብ ርቀት መገኘቱ ብሎም የምህንድስና ባለሙያ በመሆኔ ዜናውን ዝም ብዬ ባልፈው፣ ከህሊና ፀፀት የምድን አልመስል አለኝና ይህን ለመጻፍ ተገደድኩ፡፡

ሪፖርተር ከዜናው ጋር አብሮ ያወጣው ፎቶግራፍ አደጋው እንደተፈጠረ በቅርብ ጊዜ የተነሳ ሲሆን፣ በምሥሉ አምስቱም የአርማታ ወለሎች ተነባብረው ይታያሉ፡፡ አሁን ሄዶ ቦታውን ማየት የሚፈልግ ሰው ግን ይህን ሳይሆን ቀን ከሌት በመቆፈሪያ መሣሪያዎች ተሰባብሮ የተወገደ ባዶ መሬት ብቻ ነው የሚያገኘው፡፡ የእኔ ትዝብት እዚህ ጋር ይጀምራል፡፡

      ሕንፃዎች በመላው ዓለም ይፈርሳሉ፣ ይህ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ሕንፃም ሆነ ማንኛውም ግንባታ በዚህ ዓይነት በድንገት የፈረሰ እንደሆነ የመጀመሪያው ተግባር የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞችን አሰማርቶ የሰው ሕይወት ማዳን መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይህ የተጠናቀቀ ከሆነ ደግሞ ቀጣዩ ሥራ የአደጋውን መንስዔ የሚመረምር ከተለያዩ አካላት የተዋቀረ የባለሙያዎች ቡድን ወደ ሥፍራው ልኮ በጥልቅ መመርመርና ማስረጃዎች እንዳይጠፉ ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ነው፡፡ ነገሩን በቀላል ምሳሌ ለማየት ሁለት መኪኖች ቢጋጩ ፕላን የሚያነሳ ትራፊክ መጥቶ ተገቢው የምርመራ ሒደት ሲካሄድ የምናይበትን ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፕላኑን የሚያነሱት የተጋጩት ሾፌሮች ሳይሆኑ በነገሩ የሠለጠነ ባለሙያ መሆኑ ግድ ነው፡፡ የሰሚቱ ሕንፃ ላይ የሆነው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ ሕንፃው ፈረሰ፣ ፍራሹም ቀን ከሌት በኤክስካቫተርና በጃክሃመር ተሰባብሮ ተወገደ፡፡ ትራፊኩ ፕላን ሳያነሳ ጉዳዩ ተጠናቀቀ፡፡ ተስማምተው ተለያዩ እንበለው ይሆን?

      በእርግጥ ሪፖርተር ለሕንፃው መፍረስ መንስዔው የጥራት ችግር እንደሆነ ገልጾ ጽፏል፡፡ የጥራት ችግር ምኑ ላይ ነው? ኮለኑ ነው? ቢሙ ነው? መሠረቱ ነው? ከግንባታው ዲዛይን ነው? ከፀደቀው ፕላን ውጪ ተሠርቶ ነው? ከታለመለት ወለልና ክብደት በላይ ተጨምሮበት ነው? የሲሚንቶ ችግር ነው? የጠጠር ችግር ነው? የአሸዋ? የብረት? የውኃ? የአሠራር ዘዴ? የባለሙያ ብቃት? የባለሙያ ሥነ ምግባር? የባለድርሻ አካላት ሙስና? የሕንፃው ባለቤት ችግር? የተቋራጭ ችግር? የተቆጣጣሪ መሃንዲስ ችግር? የሕንፃ ዕቃ አቅራቢ ችግር? የክፍለ ከተማው ችግር? ሕንፃው የመሰንጠቅ ምልክት አሳይቶ ቸል ተብሎ ይሆን? ብቻ ምን አለፋችሁ ሕንፃን የሚያህል ነገር ተደርምሶ የጥራት ችግሩ ማንና የት ነበር የሚለው ጉዳይ አዲስ ሕንፃ ከመገንባት ያልተናነሰ ምርምር፣ ባለሙያና በተለይ ደግሞ ጊዜ የሚጠይቅ ራሱን የቻለ ሣይንስ ሆኖ ሳለ፣ ማስረጃውን በማስወገድ ራስን ከተጠያቂነት ለማዳን በሚመስል መልኩ ፍራሹ ከመቅጽበት እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡

      በሠለጠነው ዓለም በተመሳሳይ መልኩ የተደረመሱ ሕንፃዎችን መዝገብ ብናገላብጥ በትንሹ ከሦስት ወራት ባነሰ ጊዜ የምርመራ ሒደታቸው የተጠናቀቀባቸው ፍራሾች ለማግኘት አይታሰብም፡፡ ዓመታትን ፈጅተው ምርመራቸው ያልተጠናቀቀ ሕንፃዎችም የትየለሌ ናቸው፡፡ ወራትንም ሆነ ዓመታትን ፈጅተው የታደሉት አገሮች ትክክለኛውን መንስዔ ይደርሱበታል፡፡ ይማሩበታል፡፡ ሰዎችንና ተቋማትን ተጠያቂ ያደርጉበታል፡፡ አዲስ ሕግ ይቀርጹበታል፡፡ ይፈላሰፉበታል ወዘተ፡፡  

      ሰዎች ከውድቀታቸው የተማሩበትን ሁለት ምሳሌዎች ብናነሳ እ.ኤ.አ. በ1987 በአሜሪካ ወንዝ ውስጥ ተደርምሶ ታሪክ የሆነው ሲልቨር የተባለው ተንጠልጣይ ድልድይ የአሜሪካ ኮንግረስ ብሔራዊ የድልድይ የጥራት ፍተሻ ደረጃውን ከልሶ አዲስ ሕግ እንዲያፀድቅ ያስገደደው ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2006 ደግሞ አውሮፓዊቷ ፖላንድ ውስጥ ካቶዋይስ የንግድ ማዕከል የተባለው ሕንፃ ጣሪያ በመደርመሱ በቀጣዩ ዓመት ማለትም እ.ኤ.አ. በ2007 ለፖላንድ የሕንፃ ሕግ መሻሻል መንስዔ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል፡፡

      ሪፖርተር የጠቀሰው የሕንፃ ሕጋችንም ሆነ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር የሚያያዙ የአገሪቱ ሕጎች በጠራራ ፀሐይ ተጥሰው የአደጋውን ማስረጃ ለመደበቅ የተሮጠው ለምን ይሆን? ዛሬ ሰዎች ባለመሞታቸው ዕድለኛ መሆናችን ነገ እንደ አሸን እየፈሉ ካሉት ሕንፃዎች ፍራሽ ሥር አስከሬናችን ስላለመገኘቱ ዋስትና ይሆነናልን? ሕጎቻችንና ኢንዱስትሪውን መለስ ብሎ ለማየት ተጨማሪ ሕንፃዎች ወድቀው፣ ሕዝብ በተቋማቱ ላይ እምነት አጥቶ፣ ሰዎች እስኪሞቱ መጠበቅ ይኖርብን ይሆን? ለመደርመስ ቋፍ ላይ የሚገኙ ሌሎች ተረኛ የከተማችን ሕንፃዎችስ የትኞቹ ይሆኑ? የመግደል ሙከራ ሰው ካልሞተ በቀር አያስጠይቅ ይሆን? ለመሆኑ ከዚህ ከፈረሰ ሕንፃ ምን ተማርን? ተጠያቂውስ ማነው? መልስ አግኝተው ለሕዝብ ግልጽ መሆን ያለባቸው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

(ኖላዊ አያሌው፣ ከአዲስ አበባ)

* * *

ሽግሽጉ በመንግሥት ሠራተኛው ላይ ብቻ አልተደረገም

ሚያዝያ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በቅጽ 21 ቁጥር 1669 ታትሞ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ፊት ገጽ ላይ ‹‹በከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ አካባቢ ያለ ችግር ካልተፈታ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ፈተና እንደሆነ ተጠቆመ በሚለው ርዕስ ሥር በትግራይ ክልል ከ40,000 በላይ የመንግሥት ሠራተኞች፣ በአማራ ክልል 23,000 የመንግሥት ሠራተኞች ተሸጋሽገዋል ተብሎ የተጠቀሰው ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞችን ብቻ ሳይሆኑ የገጠር ቀበሌና ወረዳ አመራሮችን፣ የከተማ፣ የክፍለ ከተማ ቀበሌና ወረዳ አመራሮችን፣ የፐብሊክ ሰርቫንቶችን፣ የክልልና የዞን አመራሮችን የሚያጠቃልል መሆኑ ታውቆና አጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞች ብቻ እንዳልሆኑ ታይቶ እንዲስተካከል እንጠይቃለን፡፡

(የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር)

* * *

የኤሌክትሪክ ያለህ!!!

905 ይደውላሉ፡፡ የስልኩ ኦፕሬተር ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት የትኛውን ቁጥር መንካት እንዳለብዎት ይነግሩዎታል፡፡ እንደ ወረፋው ወይም ተረኛው ብዛትም እስከ አንድ ደቂቃ ወይም ለጥቂት ሰከንድ ይጠብቁ፣ ይቆዩ ይላል፡፡ በተባለው ጊዜ መስመሩን የሚያገኝ ግን ዕድለኛ ብቻ ነው፡፡ ምናልባት አንዳንዱ ደዋይ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል ግምቱን ሊያዛባው ይችላል፡፡ ዋናው ነገር የሚሰጠው የጥበቃ ጊዜ ግምት ትክክል አለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህን ያህል ጊዜ ይጠብቁ ብሎ መግለጽ ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡ በመጨረሻም አቤቱታው አስመዘገብኩ ብለው ስልኩን ከዘጉ በኋላ ባለሙያዎች መጥተው የተበላሸውን የኤሌክትሪክ መስመር የሚጠግኑበትን ጊዜ በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ እንጀራ የሚጋገረው፣ ወጥ የሚሠራው፣ ውኃ የሚሞቀው፣ ኮምፒዩተር የሚሠራው በኤሌክትሪክ ኃይል ስለሆነ ሁሉም ነገር የኤሌክትሪኩን መስመር መቀጠል ይጠብቃል፡፡ ባለሙያዎች ግን ቀጣዮቹ አይመጡም፡፡ እንደገና ይደውላሉ፡፡ ወረፋ ተይዟል ይባላሉ፡፡ ወረፋው አይታወቅም፡፡ አንድ ቀን ይጠብቃሉ አይመጡም፡፡ በከሰልና በናፍጣ ያበስላሉ፡፡ በሻማ መብራት ይጠቀማሉ፡፡ ሁለት ቀን ይጠብቃሉ፡፡ አይመጡም፡፡ ይደውላሉ ተመሳሳይ መልስ ያገኛሉ፡፡  ወደ ጎረቤት ሄዶ እንጀራ መጋገር፣ እንጨት እያነደዱ መሥራት ይጀመራል፡፡ ሦስተኛውን ቀን ይጠብቃሉ አይመጡም፡፡ ይደውላሉ ‹‹እኛ ለጥገና ክፍል አስተላልፈናል፤ ይጠብቁ፤›› ይባላሉ፡፡ አይመጡም ወደ ቅሬታ ክፍል ያመለክታሉ፡፡ ይነገራቸዋል ይባላሉ፡፡ አይመጡም፡፡ በአራተኛው ቀን ይደውላሉ፡፡ ተመሳሳይ መልስ ያገኛሉ፡፡ ለመሆኑ የኤሌክትሪክ መስመር ለመቀጠል ወረፋው ምን ያህል ቀን ይወስዳል? ይህን የምለው ከምንም ተነስቼ አይደለም፡፡ በሚያዝያ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ወይም በእነሱ አቆጣጠር በ2.05.16፣ በቁጥር 208540 ካስመዘገብኩት አቤቱታ በመነሳት ነው፡፡ ኧረ የኤሌክትሪክ መስመር ቀጣይ ያለህ!!

(ተ. ብርሀኑ፣ ከአዲስ አበባ)

* * *

መብታችንን ያለአድሏዊነት በፍትሕ ያለእንግልት የምናገኘው መቼ ይሆን?

መንግሥት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ በቡራዩ ከተማ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ውስጥ በሚሠሩ በርካታ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ሠራተኞች ምክንያት ኮርፖሬሽኑ በብልሹ አሠራር የመጀመርያውን ደረጃ ለመያዝ የሚወዳደር እንጂ ኅብረተሰቡን ለማገልገል የተቋቋመ መሥሪያ ቤት አይመስልም፡፡

እነዚህ ሠራተኞች አገልጋይነታቸውን ዘንግተው አገልግሎት ፈላጊው መብቱን በገንዘብ እንዲገዛ እያስገደዱ ነው፡፡ መብቴን በገንዘብ አልገዛም የሚለውን ያለመብራት እንዲሰቃይ እያደረጉ ይገኛሉና የሚመለከተው አካል ይህንን መሥሪያ ቤት ቢፈትሽና ለኅብረተሰቡ ተገቢውን ምላሽ ቢሰጥ በማለት እጠይቃለሁ፡፡ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን በጥልቀት ተመልክቶ አስፈላጊውን የእርምት ዕርምጃ ለመውሰድ እንዲችልና ሚዲያም ስለጉዳዩ በሚገባ በማጣራት ብልሹ አሠራሩን ለሚመለከተው አካል በማጋለጥ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዲችል ጥቆማዬን በማስረጃ አስደግፌ ላቅርብ፡፡

ይኸው መሥሪያ ቤት ከሚገኝበትና በተለምዶ አሸዋ ሜዳ እየተባለ ከሚጠራው ሠፈር ከፍ ብሎ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ጀርባ ከሚገኙት ቤቶች መካከል ነዋሪ ስሆን፣ ቆጣሪ እንዲገባልኝ የቆጣሪ ክፍያ ከፈጸምኩ ዘጠኝ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህችን ጽሑፍ እስከጻፍኩበት ሚያዝያ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ቆጣሪው አልገባልኝም፡፡ ጉዳዩን መንግሥት እንዲያይልኝ የፈለኩበት ዋናው ምክንያቴም መዘግየቱ ብቻ ሳይሆን፣ የድርጅቱ ሠራተኞች ያደረሱብኝ ኢፍትሐዊ፣ አድሏዊ አሠራርና ኢሰብዓዊ መስተንግዶ ጭምር ነው፡፡

የቆጣሪ ክፍያ አስቀድሜ ፈጽሜ አገልግሎቱን ለማግኘት እየተጠባበቅሁና ጉዳዬንም የኮርፖሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ድረስ በመመላለስ ለወራት እየተከታተልኩ ቢሆንም፣ እስከጠቀስኩት ቀን ድረስ አገልግሎት ሳላገኝ ቆይቻለሁ፡፡ ከእኔ በኋላ የከፈሉና ከእኔ የውል ቁጥር በኋላ በሺሕ ቁጥሮች ርቀው ውል የተዋዋሉ ሰዎች ግን የአገልግሎቱ ተቀዳሚ ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡ ጉዳዩን ለማስፈጸም ከወር በላይ ስመላለስ ፋይሌን እንኳ ለማሳየት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሠራተኞች፣ አንድ ጊዜ ቆጣሪው ከሲስተም ጋር አልተዋወቀም ይሉኛል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ማህደሩ አልተገኘም ወዘተ በሚል ሰንካላ ምክንያት ላልተፈለገ ውጣ ውረድ ሲዳርጉኝ ቆይተው፣ በመጨረሻው ሊያስተናግዱኝ ስላልቻሉ ማህደሬ ወጥቶ ካልታየና ቀነ ቀጠሮ ካልተሰጠኝ ከቢሯቸው አልወጣም በማለቴ ከብዙ ፍለጋ በኋላ ማህደሬ መሬት ላይ ተጥሎ ተገኘ፡፡

ቀደም ሲል ክፍያ የፈጸምኩበትን ሰነድ ባስገባሁበት ቀን የውል ቁጥሬን ተመልክተው ስርጭቱ ከደረሰበት አንፃር በየቤቱ እየገቡ ከሚገኙት ቆጣሪዎች መካከል ቁጥሬ ስለነበር ቆጣሪው ከሲስተም ጋር ተዋውቋል ያሉኝ ሠራተኞች ማህደሩን ሲመረምሩ ግን ቆጣሪው ከሲስተም ጋር አለመተዋወቁን ያረጋግጡልኛል፡፡ ቀጣይ ሊደረግልኝ የሚችለውን ነገር ስጠይቅ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተስተካክሎ እንደሚደወልልኝና ቆጣሪው እንደሚገባልኝ ተነገረኝ፡፡ በተባለው ጊዜ ስልክ ስላልተደወለልኝ ለማጣራት ወደ መሥሪያ ቤቱ ሄድኩ፡፡ አስገራሚው ነገር የተከሰተው ግን ይኼኔ ነበር፡፡

ወደ ኮርፖሬሽኑ እንድሄድ ያስገደደኝን ምክንያት ገልጬ ጉዳዬ ከምን እንደደረሰ ስጠይቅ፣ ‹‹ይደወልልሃላ ምን ልትሠራ መጣህ? የሚል የቁጣ ኃይለ ቃልና ግልምጫ ቀመስኩ፡፡ ይደወልልሃል ተብዬ ስላልተደወለልኝ በመቅረቱ በአካል መገኘቴንና ጉዳዬን ተከታትዬ ማስፈጸም የምፈልግ መሆኔን ካስረዳሁ በኋላ ማህደሬ ወጥቶ እንዲታይልኝ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ አሁንም ማህደሬን ለማየት ፈቃደኝነት ጠፋ፡፡ ቢሮው ውስጥ በፀጥታ ተቀምጬ መጨረሻውን ለማየት በመወሰን ትዝብቴን ቀጠልኩ፡፡ ከቢሮው የመውጣት ፍላጎት እንደሌለኝ ሲመለከቱ ማህደሬን መፈለግ ያዙ፡፡ ማህደሬ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ መሬት ላይ ተጥሎ ምንም ሳይታይ ቆጣሪውም በእኔ ስም ከሲስተም ጋር ሳይተዋወቅ በነበረበት ሁኔታ ተቀምጦ አገኙት፡፡ በዚህ ቀን ከብዙ ጭቅጭቅና ንትርክ በኋላ በኃላፊው ጣልቃ ገብነት ቆጣሪው ከሲስተም ጋር እንዲተዋወቅ ተደረገ፡፡

ቆጣሪው ሊገባልኝ ነው ብዬ ፈጣሪዬን በማመስገን የቆጣሪውን መተከል ስጠባበቅ ቀናት ቀናትን እየወለዱ እነሆ ዛሬ ላይ ደረስኩ፡፡ ይህን ደብዳቤ በጻፍኩበት ዕለት ጉዳዬ እልባት አለማግኘቱን ለመሥሪያ ቤቱ ሳሳውቅ ቦርድ አልቋል የሚል ምላሽ ተሰጠኝ፡፡ አንዱ ቅን የሆነና ለብዙ ጊዜ ስመላለስ የተመለከተኝ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኛ፣ ጠርቶ ከአንድ ቀን በኋላ እንድመለስ ነግሮኝ ወደቤት እንድመለስ አሳሰበኝ፡፡ ምክሩን በቅንነት ተቀብዬ በተሰጠኝ ቀጠሮ ወደ ኮርፖሬሽኑ ተስፋ አንግቤ ሄድኩ፡፡ በዚህ ቀን ደግሞ ሠራተኞቹ በሙሉ ስብሰባ ላይ ናቸው አይገቡም የሚል ምላሽ ተሰጠኝ፡፡ ልብ በሉልኝ ከእኔ በኋላ የከፈሉ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲስተናገዱ እኔ በሆነ ባልሆነ ምክንያት አገልግሎት እንዳላገኝ ተደርጌያለሁ፡፡ እዚህ መሥሪያ ቤት ሲመላለሱ አግኝቼ ካነጋገርኳቸው ሰዎችና እንደ እኔ ወይም ከእኔ በበለጠ ሁኔታ በመንገላታታቸው ስሜት ውስጥ ገብተው ከድርጅቱ ሠራተኞች ጋር ኃይለ ቃል የተለዋወጡና በጥበቃ ወደ ውጭ እንዲወጡ ከተገደዱ ሰዎች መረዳት የቻልኩት፣ ይህን መሰል ፍጹም ክብርንና ህሊናን የሚፈታተን አስጸያፊ ተግባር በእኔ ላይ ብቻ የተፈጸመ አለመሆኑን ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ ህሊና ያላቸውና ሰዎች ሲደሰቱ እንጂ ሲያዝኑ ማየት የማይሹ ኃላፊዎች ለችግሬ አፋጣኝ መፍትሔ፣ ለመሥሪያ ቤቱም ዘለቄታዊ ፍትሐዊ የአሠራር ስልትን ይቀይሳሉ በሚል እምነት ይህን ደብዳቤ ጻፍኩ፡፡ መልካም ዘመንንና ቅን አገልጋዮችን ያድለን፡፡

(ቱ.ባ፣ ከአሸዋ ሜዳ አካባቢ)