የሩብ ክፍለ ዘመን ‹‹የነፃነት›› ሕመም

በየማነ ናግሽ

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ነፃ አገር መሆኗን ያወጀችበት ግንቦት 16 ቀን 1983 ዓ.ም. 25ኛ ዓመት አክብራለች፡፡ በበዓሉ ላይ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ‹‹ለወርቅ ኢዮቤልዩ ያገናኘን›› በማለት ሌላ ሃያ አምስት ዓመታት የሥልጣን ዘመን ተመኝተዋል፡፡

ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ የኤርትራን ነፃነት የሚያቀነቅኑ ብዙ ኤርትራውያን ወጣቶች ለ30 ዓመታት መስዋዕት መሆናቸውንና በመጨረሻም የዛሬ 25 ዓመት የግዛት ነፃነታቸውን መጎናፀፋቸውን ትልቅ ግምት ቢሰጡትም፣ ነፃ ባሉት ግዛት ኤርትራውያን የተመኙት ነፃነት ግን ዛሬም እንደናፈቃቸው ናቸው፡፡

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ከሽግግር ወቅት በኋላ ሕገ መንግሥት አርቅቃና አፅድቃ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመገንባት ጥረት እያደረገች መሆኗ፣ ዛሬ የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ ቢመጣም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ የመንቀሳቀስና ንብረት የማፍራት መብት፣ የመቃወምና የመደራጀት መብትን ጨምሮ መሠረታዊ ነፃነቶችና መብቶች በሕገ መንግሥቱ ተረጋግጠዋል፡፡ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ያልተደረገ ቢሆንም፣ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን አምስተኛን ዙር ጠቅላላ ምርጫ ጨምሮ፣ ዜጎች ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፋቸውን የመምረጥና የመመረጥ መብት ተግባራዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል፡፡ ምንም እንኳ ምርጫዎቹ በውዝግብ ቢቋጩም፡፡

ካለፉት ሥርዓቶች ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣ ባህል፣ ከሕዝቡ ቁጥርና ስብጥር፣ ከባህልና ከመሳሰሉት የተነሳ አሁንም በኢትዮጵያውያን መካከል ያለው ልዩነት አንዳንድ ጊዜ የማይታረቅ ቢመስልም፣ የመገንጠል ሐሳብ የነበራቸው ድርጅቶች ጭምር በአገር ውስጥ ተፅዕኖ የሚፈጥሩበትን መንገድ ለማፈላለግ ጥረት ላይ መሆናቸው ይነገራል፡፡ በርካታ የአገሪቱ የፖለቲካ ታዛቢዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ለውጥ አያዛልቅም የሚል አስተያየት የሚሰጡ ቢሆንም፣ የዛሬ 25 ዓመት የመበታተን አደጋ ተደቅኖባት የነበረች አገር ዛሬም ድረስ አንድነቷ እንደተጠበቀ መቆየቷ ራሱን የቻለ መነጋገሪያ ነው፡፡

በተለይ እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ በአገሪቱ የተለያዩ የተቃውሞ ሐሳቦችን የሚያንፀባርቁ የግል ጋዜጦችና ተቃዋሚዎች እንደ አሸን ፈልተው ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ የራሷን አገር የመሠረተችው ትንሿ ኤርትራ ግን በርካታ ድርጅቶች ትጥቅ አንግበው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የዴሞክራሲ ጭላንጭል አንፃር የኤርትራ ሙሉ በሙሉ የተዘጋ ይመስላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2001 በርካታ ጋዜጠኞች ለእሥር የተዳረጉ ሲሆን፣ ጥያቄ ያነሱ ‹ቡድን አምስት› በመባል የሚታወቁ የአገሪቱ የገዥው ድርጅት አባላት ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በሕይወት ስለመኖራቸውም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ኤርትራን በዜጎች ሰብዓዊ መብት ጥሰት ብዛት ከዓለም ተቀዳሚ አድርገው የሚያስቀምጡዋት ሲሆን፣ ብዙዎቹ ‹‹አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ›› ይሏታል፡፡

በ1990ዎች መጀመርያዎቹ አዲስ ሕገ መንግሥት ተርቆ የነበረ ቢሆንም በኢሳያስ አፈወርቂ ውድቅ ተደርጓል፡፡ የአዲሲቷ ኤርትራ ወጣቶችም በኃይል እየታነቁ ለወታደራዊ ግዳጅ ወደ ሳዋ (ወታደራዊ ማሠልጠኛ) ይወሰዳሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሪፖርቶች ሳይቀሩ ኤርትራ ውስጥ የገቡበት የማይታወቅ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን፣ እንዲሁም ኢሰብዓዊ በሆነ አያያዝ ያላንዳች ወንጀል በእስር የሚማቅቁ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ዜጎች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ በስደት ሕይወታቸውን የሚያጡም ቁጥር ሥፍር የላቸውም፡፡

ባድመ እንደ ምክንያት

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከተለያዩ በኋላ ‹‹ኮንፌዴሬሽን›› የሚመስል ግንኙነት እንደነበራቸው፣ ቀረጥ አልባ ንግድ፣ ነፃ የሰው ኃይል ዝውውርና በአንድ ገንዘብ ሲተዳደሩ መቆየታቸው፣ ይኼም ሰላማዊ ግንኙነት አሥር ዓመት ሳይሞላው ነበር እክል የገጠመው፡፡

ሁለቱም ድርጅቶች ማለትም ሕወሓትና ሻዕቢያ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በይደር ያቆዩት እንደሆነ የሚነገረው የድንበር ግጭት ተከሰተ፡፡ ደርግን ከመጣል በዘለለ አንድ የሚያደርጋቸው የፖለቲካ አስተሳሰብና ወታደራዊ ስትራቴጂ ያልነበረ በመሆኑ፣ የድርጅቶቹ ልዩነትና የበላይ የመሆን ተፎካካሪነት በድንበር ምክንያት ተጋልጧል የሚሉም አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያ በጦርነቱ የወታደራዊ የበላይነት በማግኘት አሸናፊነቱ ብትጎናፀፍም፣ ይግባኝ የሌለው የተባለው የዘ ሔግ ፍርድ ቤት ፍርደ ገምድል ውሳኔ ሰጥቷል በማለት ጉዳዩ ዕልባት ሳያገኝ እነሆ እስከ ዛሬ ዘልቋል፡፡

ሁለት አሥርት ሊደፍን ሁለት ዓመት ብቻ የሚቀረው ‹ሰላምም ጦርነትም አልባ› ግንኙነት፣ በቅርብ ጊዜም ዕልባት የሚያገኝ አይመስልም፡፡ የኤርትራ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2006 በሶማሊያ ተነስቶ ከነበረው እሳላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ቡድን ጀርባ መኖሩ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ዛሬም ድረስ አልሸባብን እንደሚደግፍ የተለያዩ ሪፖርቶች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ የውክልና ጦርነት በዘለለም በቀጥታ የኢትዮጵያ አማፂ ቡድኖች በኤርትራ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መንግሥት ደጋግሞ ይገልጻል፡፡ ከመቶ ሺሕ በላይ የኤርትራ ወጣቶችም ሥርዓቱን በመሸሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ሆኑ እሳቸውን የተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ‹‹ዋናው ጠላታችን ድህነት ነው›› የሚል መርህ የሚከተሉ ቢሆንም፣ በዚያ አካባቢ ለሚቃጡ ጥቃቶች የኤርትራ መንግሥትን መወንጀላቸው የተለመደ ነው፡፡

የአስመራው ደርግ

ሩብ ክፍለ ዘመን ያከበረው የኤርትራ መንግሥት አንድ አምስተኛው የኤርትራ ሕዝብ ወደ ጎረቤት አገሮች እንዲሸሽ ምክንያት ሆኗል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ አገር ውስጥ ላለው አፈናና ችግር የኢትዮጵያና የአሜሪካ መንግሥታትን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

በኤርትራ የነፃነት ቀን በሕዝብ ፊት ባደረጉት ንግግር፣ የኤርትራን ሕዝብ በተለይ ከ1952 ዓ.ም. ጀምሮ እየተፈራረቁ ገዝተዋል የሚሏቸውን ከፋፍለው ያቀረቡ ሲሆን፣ የኤርትራ ሕዝብ ለነፃነት የከፈለውን መስዋዕትነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ በዚህ ንግግራቸው፣ ‹‹ወያኔ የአሜሪካ ቅጥረኛ ነው፡፡ በአሜሪካ የዚህን ቀጣና ሀብትና ፀጋዎችን ለመበዝበዝ የተወከለ ሥርዓት ነው፤›› በማለት በአካባቢው ለሚታየው አለመረጋጋት ሁለቱን መንግሥታት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

በድንበር ሳቢያ ከሱዳን፣ ከኢትዮጵያና ከጂቡቲ ጋር የተደረጉ ጦርነቶች በሙሉ በዚህ ሩብ ክፍለ ዘመን የገጠሟቸው ፈተናዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2009 በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የተጣለባቸው ማዕቀብም እንዲሁ የኤርትራን ራስን በራስ የመከላከል የአቅም ለማዳከም፣ እንዲሁም ከአካባቢውና ከዓለም ለመነጠል የተደረገ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሴራ እንደሆን ገልጸዋል፡፡

‹‹ዋናው የሚያሳስቡን ግን እነዚህ እንቅፋቶች አይደሉም፡፡ እነዚህን ችግሮች የተወጣንባቸው መንገዶች የበለጠ ትርጉም ይሰጡናል፤›› ብለዋል፡፡ በእርግጥ ከዚህ የነፃነት በዓል መከበር ጎን ለጎን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከኤርትራ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ወጣቶች እየሸሹ መሆናቸው እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡

ፍራንስ 24 የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በሠራው ዘጋቢ ፊልም የኤርትራ የነፃነት ቀን በዓልና ተቃርኖዎችን አመላክቷል፡፡ ጣቢያው ያነጋገራቸው የቀድሞ የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ ዲፕሎማት አቶ ፈትሒ ኦስማን፣ ‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ጥፋት እንጂ የተሳካ አንዳች ነገር የለም፡፡ እስከ ዛሬ አንድ ኤርፖርት የለንም፡፡ አንድ አውሮፕላንም የለንም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

‹‹ዛሬ ነፃነታችን ያገኘንበት ቀን ቢሆንም፣ በሌላ ጨቋኝ መንግሥት ሕዝባችን እየተበተነ ነው፡፡ በእርግጥም ኤርትራ እንደ አገር አንድ ትልቅ እስር ቤት ሆናለች፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ ግን በንግግራቸው መቋጫ ትግሉን ለማቀብ በዲፕሎማሲ፣ በባህልና በተለያዩ መንገዶች በተደራጀ መንገድ ለመሥራት ቃል ገብተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለንግግራቸው ማሳረጊያ ያደረጉት ‹‹ህንፀት አገር›› (የአገር ግንባታ) ሲሆን፣ ለሚቀርቡባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ውንጀላዎች ማስተማሚያ የሚያቀርቡት ቋሚ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡

‹‹ከውስጥም ከውጭም የተጋረጡብንን ፈተናዎች በሚገባ ተወጥተናቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመከላከል አቅማችንም ባህላችንም የላቀ ደረጃ ላይ ደርሶ በመጓዝ ላይ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ለውጭ አገር ዕርዳታ እምብዛም እጁን የማይዘረጋ መሆኑንና ‹‹ራስን በራስ የመቻል›› መርህ እንደሚከተል ይናገራል፡፡ አገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ነፃነት ዕጦት ብቻም ሳይሆን ድህነትም ከፍተኛ መሆኑ የሚነገር ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚወጡ ሪፖርቶችም ወደ አውሮፓ በየቀኑ በሚጓዙ ስደተኞች ቁጥር ከሶሪያውያን ቀጥሎ ኤርትራዊያን መሆናቸውን ያሳያሉ፡፡

በእርግጥ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ወርቅ በኤርትራ ምድር መገኘቱ  ለኤርትራ መንግሥት ትልቅ ዜና ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በየመን እየፈረጠመ ያለው (በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራ) የዓረብ አገሮች ቅንጅት አባል መሆኑ ለኤርትራ መንግሥት ዕፎይታ የሰጠ ይመስላል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያዊያን እንደሚሉት፣ በቸልተኝነት ከኢትዮጵያ እጅ ያመለጠው የአሰብ ወደብ ኪራይም ለኤርትራ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል፡፡

አቶ ኢሳያስ፣ ‹‹የመከላከል አቅማችን የላቀ ከፍታ ላይ ደርሷል፤›› ያሉትም ይህንን ያመላክታል የሚሉ አሉ፡፡ አቶ ኢሳያስ በንግግራቸው በዝርዝር ያልገለጿቸው አዳዲስ የፖለቲካ ዕቅዶችን ማለማቸውን ተናግረዋል፡፡ ምን እንደሆኑ ባይታወቁም፡፡