የረመዳን ወር የሰላም የመረጋጋት የነፃነትና የክብር መገለጫ ነው

ተሾመ ብርሃኑ ከማል

የዘንድሮ የረመዳን በዓል ከግንቦት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በጾም ይከበራል፡፡ ረመዳን በተለያዩ አገሮች በተለያዩ መንገዶች፣ ልምዶችና እሳቤዎች ይከበራል፡፡

በረመዳን ወር ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በርካታ በረከት የሚያስገኙ መልካም ነገሮች ያከናውናል ተብሎም ይጠበቃል፡፡  በዚህም ምክንያት ሙስሊሞችና የሌላ እምነት ተከታዮች ወሩ መልካም የጾም ጊዜ ሆኖ እንዲያልፍ ምኞታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያና የመሳሰሉት የአገር መሪዎች ደግሞ ኅብረተሰቡ በሰላም፣ በመረጋጋት፣ በነፃነትና በክብር እንዲያሳልፈው መልዕክታቸውን በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን ያስተላልፋሉ፡፡  በረመዳን ወር እንደዚህ ያለውን የላቀ ኢስላማዊ  ሥነ ምግባርን ሲያሳይ በአካባቢው የሚገኙ የሌሎች እምነት አባቶችና ተከታዮች የላቀ ከበሬታን ይሰጡታል፡፡ በልዩ ልዩ አገሮች የሚገኙ የክርስትናና የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ‹‹የእንኳን አደረሳችሁ›› መልዕክት የሚያስተላልፉ ከመሆናቸውም በላይ ለዚህ ወር ትኩረት በመስጠት ስለዓለም ሰላም፣ አብሮ መኖር፣ መቻቻል፣ የእርስ በርስ መተሳሰብና ፍቅር እንዲሰፍን ያስተምራሉ፡፡

በሃይማኖቶች መካከል የአስተምህሮት ልዩነት ቢኖርም፣ ሁሉም ከፈጣሪ ጋር የተያያዘ በመሆኑ እንደሚያመሳስላቸው አበክረው ያወሳሉ፡፡ እንደኩዌት ባሉ አገሮች አብያተ ክርስቲያናት፣ ሙስሊሞች ጾም እንዲይዙባቸው ወይም ጾመው ከዋሉ በኋላ እንዲያፈጥሩባቸው ይጋብዛሉ፡፡ ከሙስሊሞች ጋርም አብረው አንድ ማዕድ ይመገባሉ፡፡ ‹‹በአንድ ማዕድ ስንበላ የበለጠ አንድ እንሆናለን፤›› በማለትም ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎች ለሰላምና ለፍቅር ተቀራርበው መጣር እንዳለባቸው ማስተማሩን በተግባር ያሳያሉ፡፡ እንዲህ በሚያደርጉ አገሮች በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

በዘር፣ በጾታ፣ በቋንቋ መለያየት ምክንያት ኅብረተሰቡ መለያየት እንደሌለበት ሁሉ በሃይማኖትም መለያየት እንደሌለበት መንግሥታቱ ይመክራሉ፡፡ በአንዳንድ ሙስሊም አገሮች የመጀመርያው የረመዳን ቀን ክብረ በዓል ሆኖ ስለሚከበር ሥራ አይኖርም፡፡ ሱቆችም ሆኑ ምግብ ቤቶች እስከ ማታ ድረስ ይዘጋሉ፡፡ የትምህርትና የሥራ ሰዓታት የሚቀነሱበት አጋጣሚም አለ፡፡ ነጋዴዎች ከተምር ምርት ጀምሮ ብዙ የምግብ ሸቀጦችን ወደ ገበያ ያቀርቡበታል፡፡

ረመዳን በዋነኛነት ከማንኛውም ወር ሁሉ በበለጠ መልኩ ራስን ለሥነ ሥርዓት በማስገዛት፣ በሰላምና በመቻቻል ማለፍ ያለበት ወር መሆኑን በሃይማኖቱ ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው አባቶች አበክረው ያሳስባሉ፡፡ ሙስሊሞች ወርሐ ረመዳንን ራሳቸውን ለሥነ ሥርዓት በማስገዛት ያሳልፋሉ ሲባል በሰዎች ውስጥ የሚገኝን የስግብግብነት፣ የራስ ወዳድነት፣ የምቀኝነት፣ የተንኮል፣ የጠብ ጫሪነት፣ የትንኮሳ፣ የሌሎችን መብት የሚፃረር ተግባርና ከመሳሳሉት መጥፎ ባሕርያትን ሁሉ በመቆጣጠር ራሱን ለፈጣሪ ያስገዛል ማለትን ይጨምራል፡፡

ቅዱስ ቁርዓን የሚያስተምረው ኅብረተሰቡ የዘር፣ የጾታ፣ የሃይማኖት፣ የዜግነትና፣ የቀለም ልዩነት ሳያደርግ ከሁሉም ጋር ተቻችሎ እንዲኖር፣ በጥልቅ ሃይማኖታዊ ስሜት፣ በፍቅርና በመደጋገፍ የሰውን ታላቅነት ተቀብሎ አስፈላጊውን ሁሉ ክብር መስጠት በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተቸገሩን በመርዳት እንዲያሳልፈውና ከፈጣሪ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያድስ ነው፡፡ 

የተለያየ እምነት፣ ዘር፣ ብሔር ብሔረሰብ፣ ቀለም ወዘተ ያላቸው ሰዎች በፈጣሪ ዘንድ አንድ መሆናቸውን የሚቀበል ሙስሊም በረመዳን ወር የበለጠ ማሰብ የሚኖርበት ሰዎች በሰውነታቸው አንዳቸው ሌላቸውን ሳይጎዱ በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመግባባትና በስምምነት በወንድማማችነት ስሜት እንዴት እንደሚኖሩ በማሰብ መሆን እንዳለበት ቅንጣት እንኳን የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በራሱ የሚተማመንም በዕውቀት ለመብለጥ እንጅ በኃይል ለማንበርከክ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ያውቃል፡፡ የፈጣሪን ትዕዛዝ እቀበላለሁ የሚል አማኝም ዕውቀት ተቀዳሚው ሥራ እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ ለእምነት ሲባል የሚወጣ ወጪ ቢኖር ከፍተኛው ለትምህርት መዋል እንዳለበት እሳቤ ይሰጣል፡፡ በሌላ አነጋገር እፍኝ በማይሞሉ ጥቂት ሰዎች ከመተማመን ብዙዎችን ለማፍራት ለትምህርት ቅድሚያ መስጠት ማለት ነው፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በጭፍን በደል እያነሳ ከሚቆዝም ወደፊት ላለው ኅብረተሰብ የሃይማኖት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የሕግ፣ የወታደራዊ ጥበብ፣ የኪነ ጥበብ፣ የሥነ ጥበብ፣ የሕክምናና የምሕድስና ወዘተ ምሁራን የመኖራቸው አስፈላጊነት ከምን ጊዜውም የበለጠ ግልጽ ሆኖ ሊታየው ይገባል፡፡ በዚህ ዓመት ረመዳን መታሰብ ያለበትም ይህ እንደሆነ የዚህ ጽሐፍ አዘጋጅ ያምናል፡፡ 

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዚህ የረመዳን ወር

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዚህ የረመዳን ወር ማስታወስ ያለባቸው ሌላው ዋነኛው  ቁም ነገር ኢትዮጵያውያን ሁሉ በራሳቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ልምድ፣ ብሔር፣ ብሔረሰብና ክልል ኩሩ የመሆናቸውን ያህል ከሌሎች አገሮች በሚነሳ ማዕበል የማይናጡ ጠንካራ ሕዝቦች መሆናቸውን ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከል የእምነት ልዩነት ቢኖርም ሰብዓዊ ፍጡር መሆናቸውን፣ ተመሳሳይ ባህል፣ ተመሳሳይ ታሪክ፣ ተመሳሳይ ልምድና ተመሳሳይ ሥነ አዕምሮ የሚጋሩ በመሆናቸው የበለጠ ቢያዳብር እንጂ አያቀጭጭም፡፡ 

በመሠረቱ በአገራችን ሙስሊሞችና ሙስሊም ያልሆኑ ክፍሎች የሚኖሩት አብረው ነው፡፡ በአንድ ግቢ ብቻ ሳይሆን በአንድ ቤት ውስጥ ሙስሊሞችና ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች አብረው የመኖራቸው ጉዳይ እንግዳ አይደለም፡፡ በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ መስክ አንዱ የሌላው ጓደኛ ነው፡፡ ከዚህም በላይ አንዱ ሌላውን ከእምነቱ ተከታይ የበለጠ ያምነዋል፡፡ ያከብረዋል፡፡ ይህ ጾታን፣ ብሔርን፣ ብሔረሰብን፣ ዘርንና ክልልን የሚለይ አይደለም፡፡ ሐዘን ወይም ደስታ ቢኖር ሙስሊሙ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ የሐዘን ተካፋይ ወይም የደስታ ተካፋይ ቢሆን፤ ወይም ከቤተ ክርስቲያን ጎን መስጊድ ቢሠራ፤ የአንዱን ጸሎት ሌላው ቢያዳምጥ የሚሰማው የከፋ ስሜት የለም፡፡ ከሚያለያዩት ነገሮች ይልቅ የሚያገናኙት ነገሮች እንደሚበዙ ስለሚገነዘብም ተቻችሎ ይኖራል፡፡ ስለዚህም፣ ‹‹ኢትዮጵያ፣ ሕዝቦቿ በሰላም፣ በመከባበር፣ በመፋቀር፣ በመተባበር፣ የሚኖሩባት የተቀደሰች ሥፍራ ናት፤›› ተብሎ የሚነገርላትም ለዚህ ነው፡፡ ከ30 እና ከ40 ዓመታት በፊት በፖለቲካ መሪዎች አነሳሽነት አልፎ አልፎ ሁከት ሲፈጠር በቀላሉ ይቀዘቅዝና ይረሳ የነበረውም ለዚህ እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡ 

ኢማም ሐሰን ቃሲም ኦኪኪኦላ የተባሉ ናይጄሪያዊ ሙስሊም ምሁር ባለፈው የካቲት ወር በጻፉት መጣጥፍ ‹‹ምንም እንኳን የሙስሊሞች፣ የክርስቲያኖችና የአይሁዳውያን እምነት ምንጩ አንድ እንደሆነ የታወቀ ቢሆንም፣ በአውሮፓውያንና በአሜሪካውያን፣ እንዲሁም በአንዳንድ አፍሪካውያን ኢስላም እንግዳ እንደሆነ ተደርጎ ይታመናል፡፡ ስለሆነም እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት ለመለወጥ ማስተማር ተቀዳሚውን ሥፍራ መያዝ አለበት፤›› በማለት የሃይማኖትን ምንነት ጠልቆ ባለመገንዘብ ምክንያት በዓለማችን የሰፈነውን ሥጋት፣ ጥላቻ፣ አመጽና ጥርጣሬ በማስወገድ የተሻለ መከባበርና መተሳሰብ ዕውን ይሆን ዘንድ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ፣ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሙስሊሞች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ለሕዝቦች በሰላም አብሮም መኖርና መከባበር ጠንክረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ፣ ቱርክ፣ ሊባኖስ፣ ግብፅ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ፓኪስታን፣ ናይጄሪያና ማሌዢያ ያሉ የተለያየ ሃይማኖት የሚገኝባቸው አገሮች በመጫወት ላይ ያሉት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ ከሃይማኖታዊ ምክንያት ይልቅ ፖለቲካዊ አመለካከት እያየለ አልፎ አልፎ ችግር መስተዋሉ አልቀረም፡፡ ይህም በአገራችን ሙስሊም፣ ክርስቲያንና ኦሪታውያንን እርስ በእርስ በማለያየትና አንዳቸውን ከሌላቸው በማበላለጥ ይጠቀሙበት እንደነበረው ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ ኢስላምን በሚመለከት በአልመኢዳህ (5፡48) ‹‹ወደ እናንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና በእርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲኾን በእውነት አወረድን፡፡ በመካከላቸውም አላህ ባወረደው ሕግ ፍረድ፡፡ እውነቱም ከመጣልህ በኋላ ዝንባሌዎችን አትከተል፡፡ ከአንተ ለሁሉም ሕግና መንገድን አደረግን፡፡ አላህ በሻ ኖሮ አንድ ሕዝብ ባደረግሁት ነበር፡፡ ግን በሰጣችሁ ሕግጋት ሊሞክራችሁ (ለያያችሁ)፡፡ በጎ ሥራዎችንም ለመሥራት ተሽቀዳደሙ፤ መመለሻችሁ በጠቅላላ ወደ አላህ ነው፡፡ በእርሱም ትለያዩበት የነበራችሁትን ነገር ይነግራችኋል፤›› ተብሎ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ነቢዩ መሐመድም (ሱዓወ) ከክርስትናና ኦሪት ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ተከባብረው አብረው ኖረዋል፡፡ አቡዳውድ የተባሉት የነቢዩ ሙሐመድ ሐዋርያ እንደጠቀሱት ‹‹ማንኛውም ሙስሊም ያልሆነ ዜጋን የጎዳ እኔን እንደጎዳ ይቆጠራል፤›› በማለት በመጀመርያው የሙስሊም ዓለም የሃይማኖት ነፃነትና ብዝኃነትን ያረጋገጡትም እሳቸው ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር እንኳንስ በተመሳሳይ እምነት ጥላቻን ማናፈስ በተለያየ ሃይማኖት ላይ ተመሳሳይ ችግር መፍጠር ትክክል አለመሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ዳሩ ግን ሙስሊሙ በእንዲህ ባለው ጥብቅ መሠረት እምነት የሚመራ እንጂ አክራሪም፣ አሸባሪም አለመሆኑን በተግባር ማሳየት ያለበት ራሱ መሆኑን ነው፡፡  

ዶክተር አስላም ዓብዱላህ የተባሉ የሃይማኖት አባት በረመዳን ጾም መደረግ  ካለባቸው ውስጥ ‹‹ሙስሊም ያልሆኑ ወዳጆቻቸውን ወደ ቤታቸው በመውስድ አብረዋቸው እራት እንዲበሉ መጋበዝ፣ ቤት የሌላቸውን በመመገብ፣ ሕዝባዊ ጠቀሜታ ላለው መልካም ተግባር ገንዘብ አዋጥቶ በመስጠት፣ በሌሎችም ሆነ በራሳችን ምክንያት የተፈጠረ ችግር ቢኖር ይቅርታ በመጠየቅና ይቅርታ በማድረግ፣ ምንም ያህል የሚያስቆጣ ሁኔታ ቢገጥመን ታጋሾች በመሆን ልናሳልፈው ይገባል፤›› ሲሉ መክረዋል፡፡ 

በመቻቻል፣ በመከባበርና በሰላም አብሮ መኖር መርሕ አራማጅነታቸው በዓለም የታወቁት ቱርካዊው ኢስላማዊ ምሁር ፈትሁላህ ጉለን ደግሞ ሙስሊሞች በብሩህ ምሽት ኮለል ብላ እንደምትታይ ጨረቃ አንፀባራቂው የሆነውን የረመዳን ወር እንዴት በሰላም፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በመረዳዳት ማሳለፍ እንደሚገባቸውና ረመዳን በየልቦናቸው የሚያስተላልፍላቸውን ቅዱስ ብርሃን ተጠቅመው ለነፍሳቸውና ለሥጋቸው ፋይዳ ያለው ኢስላማዊ ተግባር ማከናወን እንዳለባቸው አበክረው ይመክራሉ፡፡ 

ፈትሑላህ ጉለን በጥልቅ ዕውቀታቸውና በተባ ብዕራቸው ስለረመዳን ካሉት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡

በአንድ ኢፍጣር ቀን (ማታ የሚበላበት ሰዓት) ስለተደረገው ግብዣ ፈትሑላህ ጉለን ሲገልጡ ‹‹የደራስያንና የጋዜጠኞች ፋውዴሽን በኮንራድ ሆቴል ባዘጋጀው የእራት ግብዣ ሥነ ሥርዓት፣ የተለያዩ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች ተከታዮች ተገናኝተው ነበር፡፡ ከነዚህም መካከል የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ፣ የቱርክ አይሁዶች መሪ (ራባይ)፣ የአሜሪካ ፓትሪያርኬት ጳጳስ ተገኝተው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ተመሳሳይ ቋንቋና ቀለም›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ፊልምና የዕውቅ ገጣሚያን ቅኔዎች ቀርበዋል፡፡ በነዚህም ፊልሞችና ግጥሞች የሰላምና የመቻቻል አስፈላጊነት ተንፀባርቀዋል፡፡ የደራስያኑና የጋዜጠኞች ፋውዴሽኑ ፕሬዚዳንት ‹‹የእያንዳንዱ ሰው የጋራ አካፋይ ሰው መሆኑ በቂ ሆኖ እያለ ሰዎች ይህንን በኃይል ለመለያየት ሲደክሙ ይታያሉ፤›› ያሉ ሲሆን፣ ሌላው ተጋባዥም ‹‹ለመሆኑ ሰዎች ምንም ዓይነት የሃይማኖትም ሆነ የአመለካከት ልዩነት ይኑራቸው አብሮ ከመኖር የተሻለ ነገር አለን?›› በማለት በጽሑፋቸው ገልጸዋል፡፡ ለፈትሑላህ ጉለን ሃይማኖት የግል ጉዳይ ሲሆን፣ የተለያዩ እምነት ያላቸው ሰዎች አብረው ለመኖር የሚያስችሏቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ በተለያዩ ሥራዎቻቸው ይገልጻሉ፡፡ 

በመጪው የረመዳን ወር ልዩ ትኩረት ቢሰጠው ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም ሕዝብ የሚጠቅም፤ በተለይም ከኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነታ ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ ፈትሑላህ ጉለን ‹‹የነፍሳችን ሐውልት›› በሚል ካዘጋጁት መጽሐፍ ላይ እናገኛለን፡፡

ጉለን ‹‹መጾም ለመክሳት ሲባል ወይም ከምግብና ከመጠጥ ራስን ለተወሰነ ጊዜ ለመከልከል ሲባል በፍጹም የሚደረግ አይደለም፡፡ በየዕለቱ የሚደረጉ ጸሎቶች ለመቀመጥና ለማጎንበስ ታስበው የተዘጋጁ የአካል ማሠልጠኛ ስፖርቶች አይደሉም፡፡ ምጽዋት መስጠት ካለው ገቢ ትንሽ ግብር መክፈል ወይም በማያውቁት አገር የሚገኙ ለማያውቋቸው ችግረኛ ሰዎች ከችግራቸው ፋታ እንዲያገኙ ሲባልና፣ ለማይታወቅ ዓላማ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ሐጅ መሄድ ሲባል ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በመጓዝ ያጠራቀሙትን የአገር ውስጥ ገንዘብ ወደ ውጭ ምንዛሪ ለውጦ ማጥፋት አይደለም፡፡ ወይም ወደ ሐጅ ለጸሎት የሚሄዱበትን መሠረታዊ ምክንያት አውቀው ካልሄዱ በስተቀር ‹‹ሐጅ›› የሚለውን ስምና ከዚያ ጋር የሚገኘውን ዝና ለማግኘት ከመሆን አይዘልም፡፡ እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች በምሕዋራቸው ዙሪያና በተዘረጋላቸው መስመርና መንፈስ በተግባር ካልዋሉ በስተቀር ከሌላው የዕለት ተዕለት ተመሳሳይ ሥራ እንደምን ተለይተው ሊታዩ ይችላሉ? በአምልኮ ተግባር ውስጥ ቁጥርን ለማብዛት መንቀሳቀስ ከልጅነት ጨዋታ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ መንፈሳዊ ጥያቄ ለማቅረብ ካልሆነ በስተቀር በከንቱ መጮህና ማንቧረቅ የድምፅ ሳጥንን ከማለማመድ/ከማሰልጠን የተለየ ሊሆን አይችልም፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

የረመዳን ወር የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ልቦና የሚመለስበት

የረመዳን ወር የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ልቦና የሚመለስበት፣ ተክሎች አበባ በሚያወጡበት ወራት እንደሚያምሩት ሁሉ የሙስሊሙም ልቦና የሚያብብበትና የሚያምርበት፣ ራሱን በፈሪሃ እግዚአብሔር (ረቢል ዓለሚን) የሚያስገዛበት፣ ልቡን የሚያጠራበት፣ የደረቀ ቀልቡን የሚያርስበትና የሚያረሰርስበት፣ የፈጣሪ ጥልቅ ፍቅር በልቦናው የሚያድርበት፣ በደግነትና በቸርነት የሚሞላበት፣ ሁለመናው ጥሩ እንዲሠራ ጥረት የሚያደርግበት ነው፡፡ እያንዳንዱ ስለኢስላም የሚያውቅ የሚያደርገው ነገር ሁሉ በረመዳን ወር ከሰባት እስከ መቶ እጥፍ ድርብ ምንዳ (በረከት) እንደሚያገኝበት አጥብቆ ይገነዘባል፡፡ ሙስሊሙ በረማዳን ወር ከመስረቅ፣ ከመቅጠፍ፣ ከማጭበርበር፣ በሐሰት ከመመስከርና ከመመቅኘት ወዘተ ርቆ በፀፀት ያሳልፋል፡፡ ፀፀቱም ዳግም ላለመሥራት መሆኑንም ለራሱና ለፈጣሪው ቃል ይገባል፡፡ ትክክለኛ ነገር ማድረግን ይመርጣል፡፡ የተቀደሱ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ 

ከረመዳን ወር በፊት በነበሩት ወራት ያደርገውን የነበረ በጎ ተግባር ያልቃል፡፡ በሽተኛን ይጠይቃል፡፡ የተራበን ያበላል፡፡ የታረዘን ያለብሳል፡፡ የሞተን ይቀብራል፡፡ የታሰረን ይጠይቃል፡፡ እንዲሁም ይፀልያል፡፡ ምህረትንም ይጠይቃል፡፡ የሙስሊሙንና የሌላውን ኅብረተሰብ ሰላም ከሚያደፈርሱ ነገሮች ሁሉ ይርቃል፡፡ በረመዳን ወር ድባቡ ሁሉ ደስ በሚሉና ደስ በሚያሰኙ ተግባራት ይሞላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች መጾም እንደሚያደክም ይናገራሉ፡፡ በእርግጥም የሚጾመው ከ13 ሰዓት በላይ ነውና ሊያደክም ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ወር ከፍተኛ ምንዳ ለማግኘት ለሚሻ ወሩ እንዲረዝምለት ባይሻም በእያንዳንዱ ቀን፣ ሰዓትና ደቂቃ በጎ ነገር ለማከናወን ይጥራል፡፡ በበጎ ነገር ይደሰታል፡፡ በበጎ ሥራው ይፈነጥዛል፡፡ የቀንም የሌሊትም ሐሳቡ ፈጣሪውንና ሰውን ማስደሰት ነው፡፡ አንድ ቀን አልፎ ሌላው ሲተካ የምኞቱን ያህል ሳይሠራ የሚቀር ስለማይመስለው የበለጠ በጎ ነገር ለመሥራት ይጣደፋል፡፡ ወሩ እየተገባደደ ሲሄድም ‹‹አይ እኔ፣ ለመሆኑ ፈጣሪን የሚያስደስት ተግባር ምን ያህል አከናወንኩ?›› ብሎ ራሱን ይጠይቃል፡፡ ‹‹በሚቀጥለው ዓመት ላይ ደርሼ ተመሳሳይ በጎ ተግባር ለማከናወን እችል ይሆን?›› ብሎም በፍርኃት ፈጣሪውን ያስባል፡፡ የሌላው እምነት ተከታይ በረመዳን ወር ሙስሊም ወንድሙ ሲጾም ማሰብ የሚኖርበትም ይህንን በጎ አመለካከት ነው፡፡ ይህን ሲያደርግም አጸፋውን ከሰውም ከፈጣሪም ያገኛል፡፡

የሙስሊሙና የሌላው እምነት ተከታዮች ትብብር ከምን ይመነጫል?

ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች የተለያዩ እምነት ተከታዮች ቢሆኑም በአንድ ፈጣሪ ብቻ ማመናቸው፣ በነቢያት፣ በመላዕክት፣ በጾም፣ በመስገድ፣ በምፅዋትና በመጨረሻው ቀን እምነታቸው በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ቢሆንም፣ ከሌሎች ሃይማኖቶች በተለየ ሁኔታ የበለጠ ተቀራራቢ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም የፈጣሪ ባሮችና አገልጋዮች መሆናቸውን፣ ሁለቱም በዚች ዓለም ላይ የሚደርስባቸውን የፈጣሪ ፈተና አልፈው ገነት እንደሚገቡ ወይም ካላለፉ ሲኦል እንደሚወርዱ ያምናሉ፡፡ ይልቁንም ሙስሊሞች ኢየሱስ የፈጣሪ ቃል እንደነበረና ያም ቃል በቅድስት ማሪያም ማህፀን አድሮ ሰው ሆኖ መወለዱና በኋላም የፈጣሪን ቃል አስተምሮ ማረጉን ያምናሉ፡፡ ኢየሱስን የማያፈቅርም የተሟላ ሙስሊም ሊሆን አይችልም፡፡ ቅድስት ማርያምን ያከብራል፡፡ ያፈቅራል፡፡ ለክርስቲያኑ ፈጣሪ ‹‹ሕያው ዘይመውት ነው፤›› ለሙስሊሙም እንደዚሁ፡፡ ክርስቲያኑ ‹‹እንአምን በሐዱ አምላክ›› ይላል፡፡ ሙስሊሙም እንዲሁ፡፡ ሁለቱም በጾም፣ በጸሎት፣ ለፈጣሪ በመስገድ፣ በመጨረሻይቱ ዕለትና በፍርድ ቀን ያምናሉ፡፡ ክርስቲያኑ ‹‹ካለኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ›› የሚለውን ቃል አጥብቆ ይከተላል፡፡ ሙስሊሙም ከፈጣሪ ጋር ሌላ አያጋራም፡፡ ከእርሱ ጋር ሌላም አያወዳድርም፡፡ በቀጥታ ፈጣሪን ብቻ ይለምናል፣ የሚፈልገውንም እሱን ብቻ ይጠይቃል፡፡

የዚህ ዓይነቱ በጎ አመለካከትና የጠለቀ ዕውቀት ሲኖር የሃይማኖት አባቶች፣ ወላጆች፣ መምህራን ለሥጋና ለመንፈሳዊ ልጆቻቸው አንደኛው ሌላውን ከማንቋሸሽ፣ ስም ከመስጠት፣ ከማጠልሸት፣ ከማዋረድ ይልቅ መከባበር፣ መተሳሰብ፣ መፋቀርና መቻቻል እንዲኖር ማስተማር የላቀ መሆኑን ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ በእርግጥም የነገው ብሩህ ተስፋ፣ የመቻቻልና የመፋቀር ዓለም በዛሬ ልጆች ላይ የተመሠረተ ነውና በቤት ውስጥም ሆነ ውጭ ስለሌላው ሃይማኖት ሲናገሩ በአክብሮት እንጂ በማንቋሸሽና በማጥላላት እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከተቻለም ልዩነቶችንና ተመሳሳይነቶችን አውቆ ማስረዳት ይገባል፡፡ በተለይም በረመዳን ወር ሙስሊሙ ለክርስቲያኑ ደግነትን፣ መከባበርን፣ መቻቻልን፣ በአጠቃላይ በጎ አርዓያነት ማሳየት፣ አስተምህሮቱን፣ መለያ ምልክቱን፣ ቤተ አምልኮቱንና እሴቱን ማክበር ሲኖርበት ክርስቲያኑም ለሙስሊም ወንድሙ ተመሳሳይ ሁኔታ ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ይኽም ማለት ‹‹ትክክል ነው? አይደለም፤ ፀዳቂ ነው? አይደለም፤›› የሚሉትን ሁሉ ለራሱ ለፈጣሪና ለእምነቱ ተከታይ በመተው በሰውነቱ ሊቀበለው፣ ሊያውቀውና ሊያከብረው ይገባል፡፡ 

ሙስሊሙ ፀሎት የሚያደርገው ለራሱና ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ ብቻ ሳይሆን በአንድ ፈጣሪ ለሚያምኑ ሁሉ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የሌላው እምነት ተከታይ በአንድ ፈጣሪ ለሚያምነውና በራሱ መንገድ የፈጣሪን ትዕዛዝ ለሚፈጽመው ሙስሊም ኅብረተሰብ ቢቻል በፀሎት፣ ይህ ካልሆነ በጎ ነገር በማድረግና ደግ በመሆን በሚቻለው መንገድ ሁሉ መርዳት ይጠበቅበታል፡፡ ለመሆኑ አንደኛው ሌላውን ሲረዳና ሲያከብር ማየት ይሻላል? ወይስ አንደኛው ሌላውን ሲያጠቃና ሲያንኳስስ? አንደኛ ሌላው ተደስቶ ሲያይ ቢደሰት ይሻላል? ወይስ በአንዱ ደስታ ሌላው ቢከፋ? ሁለቱ ሃይማኖቶች ምቀኝነትን፣ ክፋትንና መጥፎ ምኞትን ይሰብካሉን? ሁለቱም ሃይማኖቶች መከባበርን አይሰብኩምን? ለመሆኑ እንኳንስ ስለሌሎች ስለራሳችን እምነት ምን ያህል ጠልቀን እናውቃለን? አንደኛው ወደሌላው የሚሳበው በፍቅር ወይስ በጥላቻና በእብሪት? መመራት የሚገባውስ በመጻሕፍቱ ወይስ በስሜት? ስሜታችንን ስንከተል ልንሳሳት እንችላለን፡፡ በመጻሕፍቱ ስንመራ ግን የመረዳዳትንና የመከባበርን ትሩፋት ልንጎናጸፍ እንችላለን፡፡ በኃይል፣ በጥላቻ፣ በመናናቅና በጦርነት ለመሳብ ወይም ለማንበርከክ የሚሻ ቢኖር ዘመኑ ያለፈበት አስተሳሰብ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል፡፡ ዘመኑ በሞተበት፣ ዘመኑ በተቀበረበት፣ ዘመኑ ከአካልነት ወደ ምንም በተቀየረበት ሌላ አዲስ ዘመን ሆኖ በዘልማድ ለመቀጠል መሞከር ፋይዳ የለውም፡፡ እርባናም የለውም፡፡ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት አባት መስለው ሲታዩም ሆነ ጥብቅ የሃይማኖት ተከታይ መስለው ሲታዩ ከዘልማድ አስተሳሰብ ማለትም ከመጻሕፍቱ ውጪ በሆነ መንገድ አንዱ ሌላውን ማጥላላት፣ መናቅና ያለ ስሙ ስም መስጠት ከቶ የሚገባ አይደለም፡፡ ይህን ካደረግን ወደ ልማት፣ ወደ ዕድገት፣ ወደነበርንበት ትልቅነት ልንመለስ አንችልም፡፡

የሌላ እምነት ተከታዮች ለሙስሊሞች ምን ሊያደርጉላቸው ይችላሉ?

ሌላው እምነት ተከታይ የራሱን ጾም ሲጾም የሚሰማው ሁሉ ሙስሊሙ ኅብረተሰብም በተመሳሳይ ሁኔታ ሊሰማው ስለሚችል በሚከተሉት መንገዶች ርህራሔንና ደግነትን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከሁሉ አስቀድሞ ራስን ከጥላቻና ከንቀት ማራቅን ይጠይቃል፡፡ በእርግጥም ዓለም ከተፈጠረና ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ያለውን ሁኔታ ስናስበው ከጥላቻና ንቀት መርዝ የሚመነጨው አጸፋው ነውና ራስን ከጥላቻና ከንቀት ራስን ማላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ሙስሊሙ ጾመኛ መሆኑን ወይም መሆኗን በመቀበል እንደራስ ማሰብ፣ በፍቅርና በአክብሮት ማየት ይገባል፡፡ ይህንንም በሚመለከት የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮች አበክረው ያሳሰቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ‹‹በራስህ ላይ ሊደረግብህ የማትሻውን በሌሎች ላይ አታድርግ፤›› የሚለውን ወርቃማ ቃል ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

ሰዎች በእምነታቸው የተለያዩ ቢሆኑም በማኅበራዊ ሕይወታቸው ችግረኞች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የሙስሊሙ ጎረቤት የሆነ ክርስቲያን ደሃ ወይም የሙስሊም ጎረቤት የሆነው ክርስቲያን ሀብታም ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ አንዳቸው የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ቢሆኑ ሌላቸውን መርዳት እንዳለባቸው የታወቀ ነው፡፡ ስለሆነም የሌሎች እምነት ተከታዮች ሙስሊሙ ጎረቤታቸው የሚበላ ነገር የለውም ወይም የላትም ብለው ካሰቡ፣ በሚቻል መንገድ ሁሉ የሚበላና የሚጠጣ ነገር መርዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ባህል በኢትዮጵያ ሥር ሰዶ የቆየ ቢሆንም፣ በአንዳንድ አላዋቂዎች በመመራት እንዳይበረዝም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ከ30 እና ከ40 ዓመታት በፊት በነበረው ባህላችን እንኳንስ በጾም የደከመና በዕድሜ የሚበልጥ ከባድ ሸክም ተሸክሞ ሲሄድ ካዩ፣ ወይም መቀመጫ አጥቶ ሲቆም ካዩ በሸክም ማገዝና አክብሮ ማስቀመጥ የተለመደ ነበር፡፡ ዛሬ ይህ ኢትዮጵያዊ ባህል የተረሳ ይመስላል፡፡ በዚህ ረገድ ተጠያቂዎች የሚሆኑት ስለ ሥነ ምግባር የማያውቁ ልጆች ሳይሆኑ ሥነ ምግባር ያላስተማሩ ወላጆች ናቸው፡፡ የሃይማኖት አባቶችና ትምህርት ቤቶችም ቢሆኑ በዚህ ረገድ ተጠያቂ ከመሆን ከቶ ሊድኑ አይችሉም፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ባህልን ከአባቶች ለመማር ካልተቻለ ከማን መማር ይቻላል? ወይስ በፈረንጆች ልቅ ሕይወት መሰደድ እንደ መልካም ባህል ቆጥረነዋል? ምነው እንዲህ ለመጥፎ ነገር ፈጣን ከምንሆን ለሳይንስና ቴክኖሎጂያቸው ፈጣን በሆንን? ያም ሆነ ይህ በጾም ላይ የሚገኙ ሙስሊሞች ከባድ ሥራ የሚሠሩ ቢሆን ወይም ከባድ ዕቃ ይዘው ብናይ ማገዝ በእጅጉ አስፈላጊ ሲሆን፣ በፈጣሪ ዘንድም በረከት የሚያስገኝ ተግባር ነው፡፡ 

የፍትሕ አካላት ልዩ ልዩ ፍትሐዊ ጉዳዮችን ሲያስፈጽሙ ከረመዳን ጋር በተያያዘ ሁኔታ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በማረሚያ ቤት ያሉ ሙስሊሞች በተቻለ መንገድ በተመቸ ሁኔታ እንዲጾሙ ማድረግ፣ የፍርድ ቤት ጉዳይ ቢኖራቸው በጧት ማድረግ፣ ወህኒ ቤቶች ሥራ ቢኖራቸው ቀላል ሥራ ማሠራትና መርማሪዎች ጠበቅ ያለ ምርመራ ማድረግ ቢኖርባቸው ረመዳንን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት፣ በአጠቃላይ ሙስሊም የሕግ ታራሚዎች በረመዳን ወርም ፍትሕ መኖሩን እንዲያምኑ በሚያደርግ ሁኔታ መያዝ ግንባር ቀደም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በመሠረቱ ለሌላው ሰው ደግ እንዲሆን የሚመኙትን ያህል ለሙስሊሞችም ደግ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ገነት የምትገኘው ደግ ነገር መሆኑን የሚያምን፣ የሌላውን እምነት ተከታይ መብት በመጋፋት ወይም ክፉ በመሆን ገነትን ለመውረስ አይመኝም፡፡ ስለሆነም ደግ ሆኖ ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ ደግነትን ማሳየት ይገባል፡፡ 

በብዙ የመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤቶች ለሃይማኖት ተከታዮች የማይመቹ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች በዓቢይ ጾም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ሲጾሙ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት በቤተ ክርስቲያን ቢቆዩ የሚመርጡ ቢሆንም፣ የመንግሥትም ሆነ የግል መሥሪያ ቤቶች አደረጃጀት ይህንን በሚያስተናግድ ሁኔታ ስላልተዋቀረ ብዙ ክርስቲያኖች ሲቸገሩ ይታያል፡፡ አንዳንድ ኃላፊዎች ችግሩን ከግምት ውስጥ ቢያስገቡ ሌሎቹ ባለማስገባታቸው ፈተናው እንዲህ የዋዛ አይደለም፡፡ ስለሆነም በረመዳን ወር የቤት ወይም የመሥሪያ ቤት ሠራተኞች ቢሆኑ በወቅቱ እንዲሰግዱና ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ መፍቀድ፣ ያባከኑት ጊዜ ቢኖር በሌላ ጊዜ እንዲያካክሱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡

ሙስሊሞች በቤትም ሆነ በመሥሪያ ቤት በተለይም ከሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ በጣም ሊደክሙ ስለሚችሉ፣ ድካሙም አንዱ ቀን አልፎ ሌላው በተተካ ቁጥር እየጨመረ ስለሚሄድ ከባድ ሥራ እንዳይሠሩ ማድረግ፣ በፈጻሚውም ሆነ በአስፈጻሚው ዘንድ ጥቅም እንጂ ጉዳት አይኖረውም፡፡ እንዲያውም ጥሩ ግንኙነትንና መተሳሰብን በመፍጠር የበለጠ አምራች እንዲሆኑ ያስችላል፡፡ ከዚህም ሌላ በሙስሊም ድርጅት የሚሠሩ የሌሎች እምነት ተከታዮች ቢኖሩ በሚቻለው መንገድ ሁሉ የሙስሊሙን ባህል ቢጠብቁ የበለጠ ተመራጭነት ይኖረዋል፡፡ ‹‹መከበር በከንፈር‹‹ እንዲሉ በምላስ መልካም ነገርን እየተናገሩ፣ በተግባር አርኪ ውጤትን እያሳዩ፣ ከሙስሊም አሠሪዎች ጋር በረመዳን ወር ማሳለፍ ለራስም ጠቃሚ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ብዙ ጊዜ እንደሚታየው በረመዳን ወር አንዳንድ ነጋዴዎች ከመደበኛው ዋጋ የበለጠ ሲጨምሩ ይታያሉ፡፡ ይህ በእውነቱ አግባብ አይደለም፡፡ የምርት እጥረትን መፍጠርም ሆነ ዋጋን መጨመር ፈጣሪ ከቶ የሚወደው አይደለም፡፡ ስለሆነም የሌሎች እምነት ተከታዮች ነጋዴዎችና ገበሬዎች በረመዳን ወር ዋጋ አለመጨመር ባህላቸው እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የሁሉም ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሠራተኞችና መምህራን የሙከራም ሆነ የዋና ፈተና ቀናትን ቢቻል በረመዳን ወር እንዳይሆን፣ ካልተቻለም ከሰዓት በፊት እንዲሆኑ ማድረግ ሲኖርባቸው ለጿሚዎች ግምት ባለመስጠት ሙሉ ቀን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ የዘንድሮ ረመዳን በአብዛኛው ትምህርት በሌለበት ወር የዋለ ቢሆንም ወደፊት ይህ ጉዳይ ከግምት ውስጥ ሊካተት ይገባል፡፡

ሙስሊሙ በረመዳን ወር በልዩ ልዩ ጉዳዮች ባልተለመደ ሁኔታ ቸልተኛ ቢመስልና ጉዳዩ ባልሆነ ነገር ጣልቃ ባይገባ ከጾምና ከፀሎት ጋር የተያያዘ መሆኑን በመገንዘብ ሁኔታዎችን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ሙስሊሙ’ኮ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም የሚያስብ ነው፡፡ ሲመርቅም ‹‹አገራችንን ሰላም አድርግልን፣ ረሃብና እርዛትን አስወግድልን፣ ክፉን ነገር ሁሉ አርቅልን፤›› በማለት ለሁሉም የሚፀልይና የሚመኝ ነው፡፡ ስለዚህም የሚደረግለት ትብብር ለጋራ ዓላማም ጭምር ነው፡፡

መንግሥት በረመዳን ወር ምን ሊያደርግ ይችላል?

እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከማንኛውም ሃይማኖት ገለልተኛ ነው፡፡ ስለሆነም በማንኛውም ሃይማኖት ጣልቃ አይገባም፡፡ የዜጎቹን መብትም እኩል ያከብራል፡፡ ይኽም ሆኖ የረመዳን ወርን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዴሞክራሲያዊ ገጽታውን የበለጠ ገልጾ በተግባር ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ዜጎች ከማንኛውም ሥጋት ድነው የረመዳን ጾማቸውን በሰላም እንዲጾሙ በገጠርም ሆነ በከተማ ማስቻልም አንዱ ሥራው ነው፡፡ በተለይም በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በሌሎችም ቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሙስሊሞች እርስ በርስ ተከባብረውና ተፋቅረው እንዲኖሩ ማድረግ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር ቢሆን ከመስጊድ አምሽተው የሚመጡት ሙስሊም ሴቶች ልዩ ልዩ አደጋዎች እንዳይገጥሟቸው ፀጥታውን በማስጠበቅ፣ በሕዝቡ መካከል መተሳሰብና መተጋገዝ የሚያስችል ሁኔታ በማመቻቸት፣ አስፈላጊውን ትኩረት መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥት በማንኛውም ኢስላማዊ ዘርፍ ወገን እንደማይዝ ያሳወቀ ቢሆንም፣ የመንግሥትን ጥረት የሚያጎድፉ በዚህም በዚያም ያሉ ክፍሎች እንከን እንዳይሆኑ የፀጥታ ክፍሎች ነቅተው መጠበቅ አለባቸው፡፡

ችግር ሲፈጠር የፀጥታ ኃይሎችን ማሰማራትና ማረጋጋት ብቻ ሳይሆን፣ ምንና እንዴት ማድረግ እንዳለባቸው ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ጉዳይ በክርስትናው እንመልከተው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲገባ የሚፈቀድለት ፀጥታ አስከባሪ አለ፡፡ ሚስጥር ወዳለበት ክፍል መግባት አጥብቆ የተከለከለ ነው፡፡ በሙስሊምም ጫማ አድርጎ ወደ መስጊድ መግባት ወይም ወደ ሴት ክፍል መግባት ወይም የሴትን እጅ መያዝ አይፈቀድም፡፡ ስለዚህ ችግር ሲፈጠር ‹‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› እንዲሉ በአጣዳፊ ወይም በደመ ነፍስ የፀጥታ ኃይል ማሰማራትና ዕርምጃ መውሰድ ብቻ ሳይሆን አመች ሁኔታን መፍጠር ይገባል፡፡ በድሮ መንግሥታት ማለትም በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ጊዜ ፀጥታን ለማስከበር የሚላኩ ፖሊሶች በሥልጠና ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህም ምልምል ወታደሮች ሁከቱን የሚጋፈጡት እንደ ፊጋ በሬ በመሯሯጥ እንጂ ተረጋግተው፣ አልመውና አስበው አልነበረም፡፡ ስለሆነም ዛሬ በሠለጠነው ዘመን ደግሞ ለምሳሌ ሙስሊም ፀጥታ አስከባሪን ወደ ቤተክርስቲያን፣ ክርስቲያን የፀጥታ አስከባሪን ደግሞ ወደ መስጊድ ከማሰማራት እንደየእምነቱ ማሰማራት ይገባል፡፡ ተረጋግቶ መረጋጋት ተቀዳሚ ሁኔታ መሆን ይኖርበታል፡፡ 

ማጠቃለያ

አገራችን በሰላም ለመገንባት፣ የበለጡ የድል ውጤቶችን ለማስመዝገብ፣ ከድህነት ማጥ ለመውጣት፣ አንገታችንን ቀና አድርገን ለመጓዝ እንችል ዘንድ መተባበር፣ መፋቀር፣ መቻቻልና መተጋገዝ ይኖርብናል፡፡ መንፈሳዊ ፍላጎቱ ያልሞላለት በቁሳዊ ተግባር ሊፈተን አይችልምና ረመዳንም አንዳች ጥሩ ነገር ለማከናወን የምንችልበት ለልማታችን የሚበጅ መልካም አጋጣሚ አድርገን ልናየው እንችላለን፡፡ ውዲቱ አገራችንን፣ በታሪክ የበለፀገችና የብዙ አገሮች ባለውለታ የሆነችው አገራችንን፣ ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ተፋቅሮና ተቻችሎ የኖረባት አገራችንን  ለማያውቁና በውስጣቸው ባዕድነት ለሚሰማቸውም ሀቁን እንዲገነዘቡ ልናደርግ የምንችለው ባላገሮች መሆናቸውን በተግባር በማስተማር ነው፡፡ ለዚህም የእርስ በርስ ፍቅራችንን ስናደረጅ ነው፡፡ ለኔ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወንድሜ፣ እህቴ፣ ልጄና ዘመዴ ነው፡፡ ፈጣሪ ፍቅር፣ መተባበር፣ መረዳዳት፣ መቻቻል፣ መተሳሰብና መከባበር ይስጠን፡፡ አገራችንን በሁሉም ረገድ የበለፀገች ያድርግልን፡፡ ረመዳን ሙባረክ፡፡ ረመዳን ከሪም፡፡ አሚን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡