የሥነ ሥርዓት ሕጋችን በወፍ በረር ሲቃኝ

የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጋችን የወጣበትን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባለፈው ሳምንት ስለ ውልደቱና ዕድገቱ፣ ስለ ይዘቱና አወቃቀሩ የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳታችን ይታወሳል፡፡ በዚህ የጽሑፉ ሁለተኛና የመጨረሻ ክፍል ደግሞ የሥነ ሥርዓት ሕጉን አስተዋጽኦ፣ በድንጋጌዎቹ የሚታዩ ክፍተቶችንና በወጉ ያልተፈጸሙትን አንዳንድ መርሆቹን በወፍ በረር ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡ በየአንዳንዱ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ሊቀርቡ የሚችሉ የተለያዩ ትችቶች ቢኖሩም፣ ጽሑፉ ሕጉን በጠቅላላው መቃኘት በመሆኑ ድንጋጌዎቹ ለማሳያ ካልሆነ በቀር በዝርዝር ትችት አይቀርብባቸውም፡፡ በሕጉ ላይ ዝርዝር ትችት ቢቀርብ ዓመቱን ሙሉውን ብንጽፍ እንኳን አይበቃም፡፡

በዕድሜው አስተዋጽኦው የታወቀለት ሕግ

የሥነ ሥርዓት ሕጉ ለአገራችን የሕግ ሥርዓት ያለውን አስተዋጽኦ ላሰበ ሰው እስካሁን ለ50 ዓመታት በተለያዩ መንግሥታት እየተፈጸመ ያለ መሆኑ በራሱ አስረጂ ነው፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ዋና ዓላማ የፍትሐ ብሔር ክርክሮች በፍጥነት፣ ፍትሐዊ በሆነ መልኩና ወጪ ቆጣቢ ሆነው እልባት እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡ ይህንን ዓላማውን ለማሳካት ሕጉ የተለያዩ መርሆችን ያካተተ ሲሆን፣ ባለፉት 50 ዓመታት ሙግቶች ሥርዓት ይዘው እንዲመሩ፣ ተከራካሪዎች ፍትሐዊ የሆነ ዳኝነት እንዲያገኙና መብት ከመጠየቅ፣ ሙግት ከመካፈል፣ ምስክር ከመሆን ጋር በተያያዘ የሚያወጡዋቸው ወጪዎች እንዲቀንሱ ረድቷል፡፡ ፕሮፌሰር አለን ሴደለር በሕጉ ማብራሪያ ላይ በጻፉት መጽሐፍ የሥነ ሥርዓት ሕጉ አስተዋጽኦ ከመውጣቱ በፊት በፍርድ ቤት የነበረ የጉዳይ መዘግየትን በማስቀረትና ሙግቶች በተቻለ ፍጥነት ተገማች ሆነው እንዲከወኑ መርዳቱን በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡ አቶ ማርቆስ ወልደ ሰንበት ለረዥም ዓመታት በሕግ አማካሪነትና ጠበቃነት የሚሠሩ ባለሙያ ሲሆኑ፣ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ አስተዋጽኦ ሰፊ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ እንደእርሳቸው አስተሳሰብ ሕጉ ከመወጣቱ በፊት የነበሩትን የሥነ ሥርዓት ደንቦችን ለማካተት ጥረት ያደረገ ሲሆን፣ ያልተካተቱትም ክፍተት በመሸፈን የሚጠቅሙበትን ሥርዓት ይዟል ይላሉ፡፡ ክስ ሲመሠረት፣ መልስ ሲቀርብ፣ ዳኞች ሲያከራክሩ፣ ማስረጃ ሲሰሙና ሲፈርዱ ሊከተሉት የሚገባቸው ዝርዝር የሥነ ሥርዓት ደንቦች በሕጉ ባይካተቱ ኖሮ ሙግቶች የሚጀመሩ እንጂ የማይጠናቀቁ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያው በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡ የሕግ አማካሪውና መምህሩ አቶ አንድነት ሽመልስም ሕጉ ያካተታቸው ዘመናዊ የሥነ ሥርዓት መርሆች አስተዋጽኦውን በአግባቡ እንድንረዳ ያስችለናል በማለት ይገልጻሉ፡፡ እንደ እርሳቸው ሐሳብ በሕጉ የተካተቱት ተከሳሾች በአንድነት ተጣምረው የሚከሰሱበት ሁኔታ (አንቀጽ 36)፣ በተሰጠ ፍርድ ተከራካሪ ያልሆነ ወገን መቃወሚያ ማቅረብ የሚችልበት ሥርዓት (አንቀጽ 358)፣ በተያዘ ወይም በተከበረ ንብረት ላይ የቀዳሚነት መብት ያለው ወገን መብቱን የሚያስከብርበት ሥርዓት (አንቀጽ 418) ለአብነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸው፣ እነዚህን መሰል ዘመናዊ መርሆች በሕጉ ባይካተቱ ኖሮ ቀደም ሲል ተፈጻሚ በነበሩት ደንቦችና ልምዶች ጉዳዮቹን በአግባቡ ማስተናገድ የማይቻል እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

የሕጉን ክፍተቶች ፍለጋ

የሥነ ሥርዓት ሕጉ ለ50 ዓመታት በሚፈፀምበት ወቅት ምንም ዓይነት ክፍተቶች አልነበሩትም ማለት አይቻልም፡፡ አሁን በፍርድ ቤቶች አካባቢ ለሚታየው የጉዳዮች መጓተት፣ ፍትሐዊ ያልሆኑ ፍርዶችና ባለጉዳዮች ለተጨማሪ ወጪ እንዲጋለጡ አስተዋጽኦ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ሕጉ በአግባቡ ያልሸፈናቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሌላው ምክንያት ሕጉን በአግባቡ ካለመተግበር ጋር የተያያዘ በመሆኑ በቀጣዮቹ ክፍሎች ምልከታ ይደረግበታል፡፡ አቶ ማርቆስ ወልደ ሰንበት ሕጉ ከዕድሜው አንፃር ያላካተታቸው የሥነ ሥርዓት ደንቦች በብዛት አይስተዋልም በማለት ስለ ምሉዕነቱ ምስክርነታቸውን ቢሰጡም፣ ሕጉ ከህንድ ሲቀዳ ከነበረው ታሪካዊ ሥራ ጀምረው ክፍተት ማስተዋላቸውን ይገልጻሉ፡፡ አቶ ማርቆስ የሕንድ የሥነ ሥርዓት ሕግ በተለያዩ ክፍሎች የተከፈለ (Schedule, part, rule) ዓላማዎቹን በአግባቡ የማያሳኩ ደንቦችን ያካተተ ቢሆንም፣ ወደ እኛ ሕግ ሲቀዳ ሕጉ ከሁሉም መርጦ ተደባልቆ ተወስዷል፡፡ ይህም የተወሰኑ ጠቃሚ መርሆች እንዲቀሩ በማድረጉ የተሻለ ዝርዝር እንዳይሆን አድርጎታል ይላሉ፡፡ የሕጉን ክፍተት ለመሙላት በደርግ ዘመንና በኢሕአዴግ ዘመን በተዋቀሩት ኮሚቴዎች ውስጥ አባል የነበሩት አቶ ማርቆስ መንግሥታቱ ሕጉ እንዲፈፀም ቢፈቅዱም ክፍተት እንደነበረበት ተረድተው የማሻሻል ሥራም ተጀምሮ ነበር ይላሉ፡፡ የተወሰኑትን ክፍተቶች ሲገልጹ ምንጫቸው ከህንድ ሲተረጎም ያልተካተቱ ነጥቦች ላይ፣ በአማርኛውና በእንግሊዝኛው ቅጽ ላይ ያለ የሐሳብ ልዩነት፣ የፍርድ ቤቶችን መጨናነቅ በተሻለ የሚቀርፉ አሠራሮች አለመኖራቸው እንደ ክፍተት እንደሚታዩ ይገልጻሉ፡፡ አቶ ማርቆስ ለአብነት የሥነ ሥርዓት ሕጉን አንቀጽ 403 ያነሳሉ፡፡ ይህ ድንጋጌ ንብረት በአፈጻጸም ጊዜ ለተለያዩ ባለገንዘቦች የሚከፋፈልበትን ደንብ የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ አከፋፈሉ ‹‹In a prescribed manner…›› በሚል የተገለጹ ሲሆን፣ በህንዱ ‹‹Ratably›› እንዲከፋፈል የሚያዘውን መርህ አስቀርቶታል፡፡ ይህም ለዘመናት በልማድ ይፈፀም የነበረውን ልማድ በተለይም አፈጻጸም ቀድሞ የጀመረው ቅድሚያ ያገኛል በሚል ክፍፍሉ ፍትሐዊና ግልጽ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ በጊዜ ሒደት የድንጋጌው አተረጓጎም የተስተካከለ ቢመስልም ሕጉ ካልተሻሻለ ሕጉ ክፍተት እንዳለው ጠበቃ ማርቆስ ያምናሉ፡፡ አቶ ማርቆስ ለፍትሕ መዘግየት ዓቢይ አስተዋጽኦ ያለው ሁሉም ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤቱ እንዲሄዱ መደረጉ መሆኑን በመግለጽ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ሳይመጡ ሊቋጩ የሚችሉበት ዘዴዎች በሕጉ ሊካተቱ ይገባ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ለአብነት የስፔን የሥነ ሥርዓት ሕግን የጠቀሱ ሲሆን፣ ሕጋቸው በግዴታ መታረቅን (Mandatory compromise) ያካተተ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች ባለጉዳዮች ጉዳያቸውን በእርቅ እንዲጨርሱ የሚመሩ ሲሆን፣ በእርቅ መጨረስ አለመቻላቸው በሰርተፍኬት ሲረጋገጥላቸው (Certificate of non-Compromise) ብቻ ጠቀም ያለ ዳኝነት ከፍለው በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እንዲታይ ይደረጋል፡፡ የዳኝነት ክፍያው ክስ የቀረበበት ገንዘብ እስከ 30 በመቶ ስለሚደርሰ ባለጉዳዮች በተቻለ መጠን ጉዳያቸውን ከፍርድ ቤት ውጪ በእርቅ ለመጨረስ ይበረታታሉ፡፡ ከዚህ አንፃር አቶ ማርቆስ ወልደ ሰንበት የሥነ ሥርዓት ሕጋችን በፍርድ ቤት ክትትል የሚደረግበት (Court annexed arbitration) ሕጉ በስፋት ቢያካትት በተለይ ኢንቨስትመንትን ለማፋጠንና የፍርድ ቤቶችን ጫና ለመቀነስ እንደሚያስችል ይገልጻሉ፡፡ የፍርድ ቤት ጉዳዮች አስተዳደርን (Case management) የተመለከቱም ዝርዝር የሥነ ሥርዓት ደንቦች በሕጋችን አለመካተቱ በዳኞች መካከል፣ እንዲሁም በዳኞችና በድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች መካከል ያለው መስተጋብር በታወቀ መርህ እንዳይገዛ አድርጎታል፡፡ የስፔን ሕግን መነሻ አድርገው አቶ ማርቆስ ነጥቡን ሲያብራሩ ሦስትና ከዚያ በላይ ዳኞች በሚሰየሙባቸው ችሎቶች ሰብሳቢ ዳኛው ጉዳዩን አጥንቶ የፍሬ ነገር ዝርዝሩን ጨምቆ ሪፖርት የሚያደርግ ዳኛ ከመካከላቸው አንዱን ይሰይማል፣ ዳኛው ሪፖርቱን በ28 ቀናት ለመስማት ጉዳዩ በተቀጠረበት ቀን በይፋ እንዲያሰማ ይደረግና ሰብሳቢ ዳኛው ባለጉዳዮቹ የቀረ ፍሬ ነገር ወይም ክርክር መኖሩን ይጠይቋቸዋል፡፡ ፍርድ የሚጽፍ ዳኛም እንዲሁ ይሰየማል፡፡ የእኛ ሕግ ስለእነዚህ ጠቃሚ የጉዳይ አመራሮች መርሆች ያላስቀመጠ በመሆኑ በተግባር የባለጉዳዮች ፍሬ ነገሮች ሲቆረጡ፣ በአንድ ዳኛ ፍላጎት ብቻ ሲወስኑ ይስተዋላል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በየነ የሥነ ሥርዓት ሕጋችን በአንድ በኩል በአሁኑ ወቅት የማይጠቅሙ ወይም ጊዜ ያለፈባቸውን አንዳንድ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑን በሌላ በኩል ደግሞ ጊዜው የሚጠይቀውንና የፍትሕ ብሔር ሙግትን በተሻለ ፍትሐዊ የሚያደርጉ ሥርዓቶችን አልፎ አልፎ አለመያዙን ይገልጻሉ፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ የሥነ ነገር የፍርድ ቤቶች ሥልጣንን በተመለከተ፣ የዙፋን ችሎትን የሚመለከተው ድንጋጌ እንዲሁም በፍርድ ሚኒስቴር እንደሚሻሻል የተገለጸበት ክፍሉ ከጊዜው ጋር የማይሄዱና በተለያዩ ጊዜያት በወጡ አዋጆች የተሻሩ ክፍሎችን አካትቷል፡፡ እነዚህን ድንጋጌዎች በተመለከተ አዳዲስ የወጡ ሕግጋት ስለሿሯቸው የአፈጻጸም ክፍተት አይኖራቸውም፡፡ እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ የበለጠ መፍትሔ የሚፈልገው ሕጉ ያልሸፈናቸውን ነጥቦች ለማካተት መሞከር ነው፡፡ የሕግ መምህሩ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ያልሸፈናቸው አንዳንድ ጉዳዮች የተከራካሪዎችን ሕገ መንግሥታዊ የመሰማት መብት የሚጥሱ መሆናቸውን ነጥቦቹን በመጥቀስ ያብራራሉ፡፡ የመጀመርያው የሥነ ሥርዓት ሕጉ የጽሑፉ ክርክር ስለሚፈቀድበት ሁኔታ በግልጽ የሚያስቀምጠው ድንጋጌ አለመኖሩ ነው ይላሉ፡፡ በሌላ አገር የሕግ ሥርዓት ክርክር በጽሑፍና በቃል መቅረብ የሚችል ሲሆን፣ በእኛ አገር ሕግ ግን ሕጉ ከይግባኝ ጋር በተያያዘ ከሚሰጠው ፍንጭ ውጭ የጽሑፍ ክርክር የሚቀርብበትን ሁኔታ አይደነግግም፡፡ በተግባርም የቃል ክርክር የጽሑፍ ክርክርክን ይተካል ተብሎ መታመኑ ተከራካሪዎች ጉዳያቸውን በማስረጃ፣ በሕግ በማስደገፍና በመተንተን እንዳያቀርቡ ከልክሏቸዋል፡፡ የሕግ መምህሩ የጽሑፍ ክርክር (Legal Memorandum or Appellate Brief) ከአቤቱታ (Pleading) የሚለይ ሲሆን፣ የተለያዩ የምሁራን ጽሑፎችን በማጣቀስ ሕጉን፣ ማስረጃዎችን ከሙግቱ መነሻ ፍሬ ነገሮች ጋር እያነፃፀሩ ፍርድ ቤት ለማሳመን የሚቀርብ ጽሑፍ ነው፡፡ አቶ ብርሃኑ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ክፍተት ሌላ ማሳያ የምስክሮችን ቃል ቀድሞ ለማወቅ የሚያስችል ድንጋጌ አለመኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡ የአንድ ተከራካሪ ወገን የመደመጥ መብት ዋና አካል የሆነው የመስቀለኛ ጥያቄ የሚከበረው ተከራካሪው የቀረበለትን የምስክርነት ቃል ሊታመን አይችልም (ለምሳሌ ቃሉ እርስ በራሱ ይጣረሳል፣ ከምናውቀው ሌላ ሀቅ ጋር ይጣረሳል ወዘተ) ወይም ምስክሩ ራሱ አይታመንም (ለምሳሌ ምስክሩ ዝምድና አለው ወዘተ) በማለት ለማስተባበል የሚችልበት ሁኔታ ሲመቻችለት ነው፡፡ በሌላ አገር የሕግ ሥርዓት ይህንን ለማሳካት ‹‹Discovery›› የሚባል ተከራካሪዎች ምስክር በሚሰማበት ቀን ሳይሆን ከዚያ በፊት የሚሰጡትን የምስክርነት ቃል የሚያውቁበት ሥርዓት አላቸው፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጋችን በዚህ ረገድ ክፍተት አለበት በማለት የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ አንድ ተከራካሪ ወገን ወይም ጠበቃው አንድ የምስክርነት ቃል እዛው ሰምቶ የሰጠው ቃል እንዴት ወጥነት እንደሚጎድለው ወይም እንዴት ሊታመን እንደማይችል ለማሳየት አምላክነት ከሌለው በቀር እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ አቶ ብርሃኑ ከእነዚህ ክፍተቶች በተጨማሪ ከፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ጋር ተያይዞ በክልል የተሰጠ ፍርድ በፌዴራል ፍርድ ቤት ወይም በሌላ ክልል ፍርድ ቤት የሚፈፀምበት ሁኔታና በአማርኛና በእንግሊዝኛ ትርጉም መካከል ያሉ ልዩነቶችን እንደ ክፍተት ይተነትናሉ፡፡

የሥነ ሥርዓት ሕጉን ደንቦች የመፈፀም ፈተና

የሥነ ሥርዓት ሕጉ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በሕጉ ላይ ከሚስተዋሉ ክፍተቶች በላይ ሕጉን ባለመተግበር የሚስተዋሉ ችግሮች ዓላማውን እንዳያሳካ እንዳደረገው ይታመናል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ በግልጽ ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎች በልማዳዊ አሠራር በመተካታቸው ሕጉ ጉዳዮች በፍጥነት፣ ፍትሐዊና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቁ ያለውን ዓላማ ማሳካት አልቻለም፡፡ የሰበር ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ በሰጠባቸው ጉዳዮች ሕጉ ለዘመናት በልማድ የተሸፈነ መሆኑን በቀላሉ ለመገንዘብ አስችሏል፡፡ ለአብነት ጉዳዩ ለመልስ በተቀጠረበት ቀነ ቀጠሮ ባለጉዳዮች ወይም አንዱ ባለጉዳይ ባለመቅረቡ ሊፈፀሙ ይገባቸው የነበሩ ሥርዓቶች ለ40 ዓመት አካባቢ በልማድ የተተኩ እንደነበር የሕግ ባለሙያዎች የማያውቁት ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ ለመልስ በተቀጠረበት ቀን ተከሳሽ ካልቀረበ ፍርድ ቤቶች ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ ሊቀጥል የሚገባው ክስ ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ያልቀረበ እንደሆነ ብቻ መሆኑን በአንቀጽ 70 በግልጽ ይደነግጋል፡፡ የሰበር ችሎቱ ፍርዶች ሌሎችም ተመሳሳይ ተጨማሪ በልማድ ይሠሩ የነበሩ ጉዳዮችን በማጋለጥ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ደንቦች አሁንም በተግባር ላይ የመዋል ፈተና እንደተጋረጠባቸው አሳይቶናል፡፡ ጸሐፊው ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎችም ይህንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ አቶ ማርቆስ በረዥም ዘመን የዳኝነትና የጥብቅና አገልግሎታቸው የሕግና የአተገባበሩን መለያየት ማስተዋላቸውን ይገልጻሉ፡፡ ለአብነት የተወሰኑትን ይዘረዝራሉ፡፡ የሕጉ አንቀጽ  343 በሰበር ችሎቱ ሳይቀር በአግባቡ አይተረጎምም፡፡ ድንጋጌው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የቀረበለትን ይግባኝ ሲመረምር የሥር ፍርድ ቤቱ መያዝ ያለበትን ጭብጥ ካልያዘ ወይም ጠቃሚ ፍሬ ነገር ሳይመረምር ከቀረ ይህንኑ እንዲመረምርና አጣርቶ እንዲያቀርብ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ሊያዘው እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በተግባር ግን ፍርዱን ሽሮ ጉዳዩን እንደገና እንዲመለከት የሚታዘዝበት የተሳሳተ አሠራር ይስተዋላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተከራካሪዎች ዳኝነት ላለመክፈል በሚሊዮን የሚገመት ሀብት ወረዳ ፍርድ ቤት ያቀረቡና ፍርድ ቤቱ የክሱ ግምት እንዲታወቅ ተቃውሞ እየቀረበለት እንኳን ጉዳዩን ወዲያው ለግምት ከመላክ ይልቅ ለወደፊት ይታያል በሚል የሚተውበት አሠራር ሰፊ ነው፡፡ ይህም ባለጉዳዮች የሚያዋጣውንም የማያዋጣውንም ጉዳይ ሳይገምቱ ወደ ፍርድ ቤት እያቀረቡ ፍርድ ቤት በመዝገብ እንዲጨናነቅ አድርጎታል፡፡ ፍርድ ቤቶች ጉዳዮችን በእርቅ እንዲጠናቀቁ የማድረግ ሥልጣን ቢሰጣቸውም (አንቀጽ 279) ተከራካሪዎችን ከማስታረቅ ይልቅ አከራክሮ ለመወሰን ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ከሁለተኛ የንብረት ሽያጭ ጨረታ ጋር በተያያዘ የሕጉ አንቀጽ 428 ሥራ ላይ ላልዋሉ ድንጋጌዎች ማሳያ እንደሚሆንም ጠበቃ ማርቆስ ይገልጻሉ፡፡ የድንጋጌው የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቅጅ እንደሚለያይ ገልጸው፣ ፍርድ ቤቶች ሁለተኛ ጨረታ የሚነሳበትን ግምት በተመለከተ የተለያዩ አሠራሮች እንደሚተገብሩ ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶች ባወጣ ዋጋ በማለት ከዜሮ ጨረታውን ይጀምራሉ፤ ሌሎች ደግሞ በመጀመሪያው ጨረታ በቀረበው ከፍተኛ ዋጋ ግምት መገኘት ጨረታው መፈፀም እንዳለበት በአሳማኝነት ይከራከራሉ፡፡ አቶ ማርቆስ ጨረታ ተከናወነ እንዲባል ቢያንስ ሁለት ሰዎች በንብረቱ ሽያጭ ላይ ውድድር ሊያደርጉ እንደሚገባ በመግለጽ ምንም ተጫራች ባልቀረበበት ሁኔታ ጨረታ ተከናወነ ስለማይባል ሁለት ሦስት ጊዜ የመጀመሪያ ጨረታን ማድረግ ሕጋዊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በተግባር ግን ተጫራች ካልቀረበ የመጀመሪያ ጨረታ የተከናወነ አድርጎ በመቁጠር ወደ ሁለተኛ ጨረታ የመቀጠል የተሳሳተ አሠራር አለ፡፡

አቶ አንድነት ሽመልስም የሥነ ሥርዓት ሕጉ ዋና ችግር ተግባራዊነቱ ላይ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ የተለያዩ ጉዳዮች ሊስተናገዱባቸው የሚገቡ ሦስት ሥርዓቶችን (መደበኛ፣ አጭርና የተፋጠነ ሥነ ሥርዓት) መደንገጉን የሚገልጹት የሕግ አማካሪው የተፋጠነ ሥርዓት በሚመለከት ያሉት ድንጋጌዎች (አንቀጽ 300 - 306) እንደጠቀሜታቸው ያህል ያላቸው ተፈጻሚነት አነስተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በተለይ አስተዳደር አካላት የሚሰጥዋቸውን አገልግሎቶች በተመለከተ ለምሳሌ መንጃ ፈቃድ፣ የንግድ ፈቃድ ወዘተ. የተከለከለ ሰው ይህንን ሥነ ሥርዓት በመጠቀም ክሱን ሊያቀርብ የሚችል ቢሆንም፣ በተግባር ግን መደበኛውን ሥርዓት በመጠቀም ጉዳዮች በፍርድ ቤት እየቀረቡ የሚዘገዩበት አጋጣሚ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚቀርብ የሰነድ ማስረጃ ፍርድ ቤቶች አንቀጽ 145 ለሁሉም ጉዳዮች መጠቀማቸው ትክክል እንዳልሆነ የሚገልጹት አቶ አንድነት ይህ ድንጋጌ ከፍርድ ቤት ፍርድ ቤት፣ ወይም ከችሎት ችሎት ለሚመጡ ሰነዶች፤ አንቀጽ 249 (ጭብጥ ከመመሥረቱ በፊት) እና አንቀጽ 264(1) (ከጭብጥ በኋላ) ደግሞ ከሦስተኛ ወገን ለሚመጡ ሰነዶች ተፈጻሚ ሊሆኑ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ አቶ አንድነት የአፈጻጸም ፋይል ለብቻው መክፈት በሥነ ሥርዓት ሕጉ (አንቀጽ 378) ያልተመለከተ በመሆኑ አሁን በፍርድ ቤቶች ያለው አሠራር (የተለየ ፋይል መክፈት) ሕጉን ያልተከተለ መሆኑን በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ረገድ የሕግ አማካሪው የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ፍርድ በተሰጠበት መዝገብ አፈጻጸም እንዲቀጥል ማድረጋቸው ሕጋዊና ተገቢ ነው ሲሉ የክልሉ ፍርድ ቤቶቹን ተሞክሮ ያሞግሳሉ፡፡

አቶ ብርሃኑ የሥነ ሥርዓት ሕጉን በመፈጸም ረገድ ያለው ክፍተት የሥነ ሥርዓት ሕጉን ድንጋጌዎች ዋጋ ያሳጣና በስፋት የሚስተዋል እንደሆነ ያምናሉ፡፡ የሕግ መምህሩ ፍርድ ቤቶች ጭብጥ በተገቢው ጊዜ አለመያዝና በክርክር ጊዜ የማጠቃለያ ሐሳብ (Closing argument) አለማቅረብ በተከራካሪዎች የመሰማት ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮች እንደሆኑ በስፋት ይተነትናሉ፡፡ ሕጉ የአቤቱታ ማቅረብ ሥነ ሥርዓት እንዳለቀ የመጀመርያ መሰማት ደረጃ እንደሆነ በመደንገግ ዳኞች የተከራካሪዎችን አቤቱታዎች፣ ማስረጃዎችና የቃል ገለጻ መሠረት አድርገው ጭብጥ እንደሚመሠርቱ ቢታወቅም በተግባር እንደማይፈጸም መምህሩ ይናገራሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች ለተከራካሪዎች ጭብጡን ሳያሳውቁ በደፈናው ክርክር አቅርቡ ማለታቸው በሚገባው ነጥብ ላይ ተገቢውን ክርክር ለማሰማት አያስችላቸውም፡፡ አልፎ አልፎም አንዳንድ ዳኞች ቀድመው ያልያዙትን ጭብጥ ፍርድ ሲጽፉ በመመሥረት ክርክር ያልተደረገበትን ፍሬ ነገር ወይም ግራ ቀኙ ያላወቁትን ጭብጥ የሚተነትኑበት ድንገቴ አሠራር መኖሩን አቶ ብርሃኑ ይተቻሉ፡፡ በሌላ በኩል ሕጉ በአንቀጽ 259 ተከራካሪ ወገኖች የማጠቃለያ ሐሳብ እንደሚያቀርቡ በግልጽ ቢደነግግም፣ በተግባር በፍርድ ቤቶች እንደማይከበር በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡

እንደማጠቃለያ

የሥነ ሥርዓት ሕጉ ለ50 ዓመታት ለኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ያደረገው አስተዋጽኦ ሰፊ ነው፡፡ ሙግቶች መስመር እንዲይዙና የፍርድ ቤቶች አካሄድ ተገማች እንዲሆን ማድረጉ አውጪዎቹን ሊያስመሰግን ይገባል፡፡ በ50 ዓመት ዕድገቱ የሦስት መንግሥታትን የሕግ ሥርዓት ቀርጾ መንግሥታቸውን ተከትሎ ከመጣ ለውጥ ውጪ ሁለገብ ሆኖ ማገልገሉ የሕጉን ዘመናዊ መርሆዎች ገላጭ ነው፡፡ ሕጉ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከገጠሙት ተግዳሮቶች ውስጥ የተወሰኑትን በዚህ ጽሑፍ ተመልክተናል፡፡

ሕጉ ያላካተታቸው መርሆዎችና ድንጋጌዎች መኖራቸውን፣ ፍርድ ቤቶች ድንጋጌዎችን ሲያስፈጽሙ ከሕጉ ይልቅ ልማድን መምረጣቸው፤ አልፎ አልፎም ሕጉን ወደ ጎን ማድረጋቸው ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ችግሮቹን መቅረፍ የሚቻለው የመጀመርያውን ሕጉን ዘመናዊና ወጥ በማድረግ በማሻሻል ሲሆን፣ የሁለተኛው ችግርን ለመቅረፍ ደግሞ ዳኞች ሕጉን እንዲከተሉ ማሠልጠንና መቆጣጠር ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ በአስረጅነት የጠቀስኳቸው የሕግ ባለሙያዎች ሕጉ ወጥ ሆኖ የተሰደረ (Codified) ቢሆን ነገር ግን የየክልሎቹን ዓውድ ቢያገናዝብ መልካም እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ያም ሆኖ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ከሚመለከተው ውጭ ያለውን የሥነ ሥርዓት ሕግ የማውጣት ሥልጣን የክልሎቹ በመሆኑ አጥንተው መወሰን የሚኖርባቸው እነሱው ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው getukow [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡