የሜዳ አህያ

በመንጋ የሚኖሩት የሜዳ አህዮች ሦስት ዝርያ አላቸው፡፡ ከሌሎች እንስሳት በተለየ መልኩ በነጭና ጥቁር መስመር ባሸበረቀ ቆዳቸው ይታወቃሉ፡፡ ዓይነ ግቡዎቹ የሜዳ አህዮች ለዓይን ሲታዩ አንድ ዓይነትና በነጭና ጥቁር የተሰመረ ቆዳ ያላቸው ቢመስሉም፣ የአንዱ የሜዳ አህያ የቆዳ ቀለም መስመር ከሌላው ጋር በፍጹም አንድ አይደለም፡፡ ከሦስቱ ዝርያዎች ውስጥ በተመሳሳይ ዝርያ ውስጥ የሚገኙትም ቢሆኑ፣ ሁለት አንድ ዓይነት የቆዳ መስመር ያላቸውን ማግኘት አይቻልም፡፡

የሜዳ አህዮች በመንጋ አብረው የሚኖሩ ሲሆን፣ ሳር የሚግጡትም በጋራ ነው፡፡ በቤተሰባቸው ውስጥ ጥቂት ወንዶች፣ ብዙ ሴቶችና ልጆቻቸው አብረው ይኖራሉ፡፡ በአብዛኛው ራሳቸውን ከአንበሳና ጅብ ለመከላከል ተጠንቅቀውና ነቅተው ይጠብቃሉ፡፡

በአንድ አካባቢ በብዛት መገኘታቸው፣ ጠላታቸውን ከብዙ አቅጣጫ ለማየትና ራስን ለመከላከል ያስችላቸዋል፡፡ አንድ የሜዳ አህያ ሲጠቃም፣ ቤተሰቦቹ ለማስጣል ግብግብ ይገጥማሉ፡፡ የተጐዳውን የሜዳ አህያ በመክበብም፣ ከአዳኝ ለማስጣል ይጥራሉ፡፡

ከሳር በሊታ የሚመደቡት የሜዳ አህዮች፣ እስከ 25 ዓመት ድረስ ይኖራሉ፡፡ መገኛቸውም አፍሪካ ነው፡፡ ከ200 እስከ 450 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ሲሆን፣ በፈጣን ሯጭነታቸውም ይታወቃሉ፡፡ በሰዓት 40 ኪሎ ሜትር እንደሚሮጡም የኪድስ ባዮሎጂ ድረገጽ አስፍሯል፡፡