የሚያስፈልገን ግን የሌለን ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ

(ክፍል ሁለት)

በጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

ከዚህ በቀደመው ጽሑፌ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ምን ማለት እንደሆነ በአጭሩ ለመግለጽ ሞክሬያለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ያስፈልጋል ብዬ ከማምንባቸው ምክንያቶች አንዱ ላይ አተኩሬ ሙግቴን አቀርባለሁ፡፡ ይህ ምክንያት ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ እንደ ሥርዓተ መንግሥት ከሌሎች የመንግሥታዊ ሥርዓቶች በተሻለ ሁኔታ፣ የሕዝብ ይሁንታና ተቀባይነት ያላቸውን መንግሥታት ሊፈጥር መቻሉ ነው፡፡ የሕዝብ ይሁንታ ወይም ተቀባይነት ያለው መንግሥት ማጣት ያ መንግሥት ባለበት ሀገረ መንግሥት ነዋሪ የሆነው ሕዝብ የማስተዳደር ሥልጣኑን፣ ወይም መብቱን ያመነለት መንግሥት የሕዝብ ይሁንታ ወይም ተቀባይነት ያለው መንግሥት ለዜጉቹ ሳይሆን በገዛ ፈቃዳቸው ባወጣው ሕግ የሚገዙለት መንግሥት ነው፡፡ ጠመንጃ ሳይደግን ሕጉ የሚከበርለት፣ ፈቃዱ የሚፈጸምለት መንግሥት ነው፡፡

መንግሥትነቱ ወይም አስተዳዳሪነቱ፣ ሥልጣኑ በአጠቃላይ ተገቢ ነው፣ ልክ ነው ብሎ ሕዝቡ የሚመለከተው መንግሥት ነው የሕዝብ ይሁንታ ወይም ተቀባይነት ያለው፡፡ ለአንድ መንግሥት በሕዝቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነትና ይሁንታ አነስተኛ በሆነ ቁጥር ፈቃዱን ለማስፈጸም ኃይል መጠቀም ይኖርበታል፡፡ ተቀባይነቱ ዝቅተኛ የሆነ መንግሥት የሚያወጣው ሕግ የማይከበር፣ አመፅ ዘወትር የሚያሠጋውና ደጋግሞ የሚያጋጥመው መንግሥት ነው፡፡ ብዙ ሀብትና አቅሙን ሕዝብ ለማስገደድ፣ ጉልበቱን ለማጠናከር ያወጣል፡፡ በአመፅ ፍራቻ ሁሌ ይረበሻል፡፡ ሥልጣኔን አጣለሁ ብሎ ይሠጋል፡፡ ይህ ፍራቻና ሰቀቀን እያስደነበረው ጉልበት፣ ጭካኔ፣ ግፍ ያበዛል፡፡ ያስራል፣ ያሳድዳል፣ ያሰቃያል፣ ከዚያም አልፎ ይገድላል፡፡ እንዲህ ያለ መንግሥት በሚያስተዳድረው ሀገረ መንግሥት መኖር አይመችም፡፡

የሕዝብ ይሁንታ የሌለው መንግሥት ፈቃዱን ለማስፈጸም ምንም እንኳን የፖሊስ፣ የደኅንነት ብሎም የወታደራዊ ኃይል ባያደራጅም የሚኖረው ኃይልና አቅም ወሰን የለሽ ስላልሆነ ያለውን ውሱን ኃይል ቅድሚያ በሚሰጠው ሥልጣኑን የማስጠበቅ፣ ፖለቲካዊ ተቃውሞና አመፅን የመቆጣጠር ርብርብ ላይ ያውለዋል፡፡ ስለዚህ የሕዝቡን፣ የዜጐችን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ የሚኖረው ኃይልና አቅም ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት አነስተኛ ስለሆነ በኃይልና በማስፈራራት ካልሆነ ግብርም ሆነ ቀረጥ የመሰብሰብ አቅሙ ደካማ ነው፡፡

የዜጐቹን ሀብት፣ ዕውቀትና ጉልበት አስተባብሮ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ይከብደዋል፡፡ ዱላና ጠመንጃውን በመፍራት ከአንገት በላይ በሆነ እሽታ የሚታዘዘው ሕዝብ በሙሉ አቅሙና ጉልበቱ ስለማይተባበረው ዕቅድና መርሐ ግብሮቹን ለማስፈጸም ያዳግተዋል፡፡

ዝቅተኛ የሆነ የሕዝብ ይሁንታ ያለው ወይም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ አናሳ የሆነ መንግሥት የሀገረ መንግሥቱን ሉዓላዊነትና ደኅንነት ለማስጠበቅም ይቸገራል፡፡ የአገሪቱ የውጭ ጠላቶች በቀላሉ ብዙ ተባባሪ አግኝተው በአገሪቱ ውስጥ አለመረጋጋት መፍጠር ይችላሉ፡፡ የአገሪቷ ዜጋ የሆኑ፣ የአገሪቱን መንግሥት እንደ መንግሥት ለመቀበል አሻፈረኝ ያሉ ዜጐችን በመመልመል ሌሎች አገሮች ሀገረ መንግሥቱን ለማዳከም ይመቻቸዋል፡፡

በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ ዝቅተኛ የሆነ መንግሥት የውጭ ጠላትን ሲጋፈጥ ከጀርባው ጉድ እንዳይሠራ ይፈራል፡፡ ከውጭ ያለው ጠላት ከውስጥ አጋር አድብቶ እንዳይመታው ይሠጋል፡፡ እናም በአጠቃላይ የሕዝብ ይሁንታና ተቀባይነት ለአንድ መንግሥት ጥንካሬ፣ ውጤታማነትና መረጋጋት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ በሕዝብ ዘንድ ያለ ተቀባይነትና ይሁንታ ከፍ ባለ መጠን የዚያኑ ያህል የመንግሥት ጥንካሬና ውጤታማነት፣ የሀገረ መንግሥት ሰላምና መረጋጋት ይጨምራል፡፡ ስለዚህ የአንድ መንግሥት በሕዝብ ተቀባይነትና ይሁንታ ማግኘት ተፈላጊ ነገር ነው፡፡

ታዲያ አንድ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝባቸው የሚችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡ በተለያየ ጊዜ በታሪክ እንደታየው አንዳንድ መንግሥታት በመራሔ መንግሥቱ ግርማ ሞገስ፣ ሰብዕና ወይም ተወዳጅነት በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛሉ፡፡ የነፃነት ትግል በስኬት የመሩ፣ አንደበተ ርቱዕ ወይም የሕዝብን እምነትና ይሁንታ የሚገዛ የተለየ ሰብዕና ያላቸው መሪዎች ሲኖሩ፣ አልፎ አልፎ የእነዚህ መሪዎች ልዩ ሰብዕና ወይም ታሪክ ለሚመሩት መንግሥት ሕዝባዊ ተቀባይነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

ታዲያ እንዲህ ያለው የሕዝብ ይሁንታና ተቀባይነት ዘላቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ምንጩ የመንግሥታዊ ሥርዓቱ ባህሪና ተቋማቱ ሳይሆኑ የአንድ ግለሰብ ሰብዕናና ዝና ነው፡፡ ያ ሰው ሲሞት ወይም ከሥፍራው ሲለቅ የሕዝባዊ ይሁንታው መነሻና መንስዔም አብሮ ይጠፋል፡፡ በግለሰብ ላይ የተመሠረተው የሕዝብ ተቀባይነት ሰውዬው ሲሞት ይከስማል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ የሕዝብ ተቀባይነት የማያዛልቅና የማያዋጣ ነው፡፡ እንዲያውም ዞሮ ዞሮ ወደ ከፋ ቀውስና ችግር ሊያመራ ይችላል፡፡

ሌላው በአንድ አገር ሕዝብ ዘንድ አንድ መንግሥት ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርግ አማራጭ ያ መንግሥት ሥልጣኑን የያዘበትና ሥልጣኑን የሚጠቀምበት መንገድ ከሕዝቡ ባህል፣ ወግ ወይም ሃይማኖታዊ እምነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሲሆን ነው፡፡ ስለዚህ ሃይማኖትና ባህልም ለአንድ መንግሥት ሕዝባዊ ይሁንታና ተቀባይነት ሊያስገኙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ባህልና ሃይማኖት የሕዝባዊ ይሁንታ ምንጭ እንዲሆኑ ከተፈለገ፣ በሀገረ መንግሥቱ ያለው ሕዝብ መቶ በመቶ ባይሆንም በእጅጉ የሚበዛው የአገሪቱ ሕዝብ በባህል ወይም በሃይማኖት አንድ መሆን አለበት፡፡ ሕዝቡ በባህልና በሃይማኖት የተከፋፈለ ከሆነ ባህልና ሃይማኖት ለአገሪቱ መንግሥት የሕዝባዊ ይሁንታ ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

ምክንያቱም የአንድ ሃይማኖት ወይም ባህል ተከታዮች የአገሪቱ መንግሥት በባህላችን ወይም በሃይማኖታችን በተደነገገው መንገድ ሥልጣን የያዘና የሚሠራ ነው ብለው ሲደግፉት፣ ከዚያ እምነትና ባህል ውጪ የሆኑት የአገሪቱ ዜጐች ደግሞ ቅር ይሰኛሉ፡፡ እነዚህ ቅር የተሰኙ ዜጐች ደግሞ ለመንግሥት ይሁንታቸውን ይነፍጋሉ፡፡ ቅር የተሰኙ፣ የእነሱን ባህልና ሃይማኖት የማይከተሉ ዜጐች ቁጥር በበዙ ቁጥር የሕዝባዊ ይሁንታና ተቀባይነት እጥረቱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ የባህልና የሃይማኖት ብዝኃነት ባለበት አገር ከባህልና ከሃይማኖት የመነጨ የሕዝብ ይሁንታና ተቀባይነት ማግኘት በእጅጉ ከባድ ነው፡፡

ሌላው ወይም ሦስተኛው የአንድ አገር መንግሥት ሕዝባዊ ተቀባይነትና ይሁንታን አገኝበታለሁ ብሎ ተስፋ ሊያደርግ የሚችልበት መንገድ፣ ተጨባጭ በሆነ ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት የዘጐቹን ኑሮ በማሻሻል ነው፡፡ ደሃውን ከድህነት በማውጣት፣ የሥራና የትምህርት ዕድል፣ የጤናና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስፋፋት መንግሥታት የሕዝባቸውን ይሁንታና ተቀባይነት ለማግኘት ሊጥሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በተለይ ድህነት በተንሰራፋባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ከፍተኛ መስህብ አለው፡፡ ዜጐች መንግሥት አገርን በማልማትና ኑሮዋቸውን በማሻሻል ስኬታማ ለሆነ መንግሥት ይሁንታቸውን የመስጠት ዕድላቸው እጅግ ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን ልብ ማለት ያለብን ነገር ይህ የልማት ሒደት ጊዜ የሚፈጅ መሆኑን ነው፡፡ ሒደቱ በጣም ቢፈጥን እንኳን ከአንድ በላይ አሠርት ዓመታት ይፈጃል፡፡

በተከታታይ የአገሪቷን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረዳ ማሳደግና አዲስ የሚፈጠረውን ሀብት በፍትሐዊ ሁኔታ መከፋፈል ይኖርበታል፡፡ በጣም ፈጣን የሆነና ፍትሐዊ ዕድገት ካለ ሕዝባዊ ይሁንታና ተቀባይነት ለማግኘት ይቀላል፡፡ ነገር ግን የሁሉም አገሮች ኢኮኖሚ ከዓመት እስከ ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሄድ አይችልም፡፡ የየትኛውም አገር ምጣኔ ሀብት በየጊዜው እክል ያጋጥመዋል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያለ በግብርና ላይ የተመሠረተ ምጣኔ ሀብት የአየር መዛባት ሲያጋጥም፣ ዓለም አቀፍ የጥሬ ዕቃና የእርሻ ምርቶች ዋጋ ሲቀንስ በከባዱ ይጎዳል፡፡

የመንግሥት ሕዝባዊ ተቀባይነትና ይሁንታ ምንጭም ከኢኮኖሚው መዋዥቅ ጋር አብሮ ይዋዥቃል፡፡ በተለይ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ሲከሰት የከፋ የፖለቲካ ቀውስ ይከተላል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪ ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ ደግሞ የሀብት ክፍፍል ነገር ነው፡፡ ከፍተኛ ዕድገት ቢኖርም የዕድገቱ ፍሬ በፍትሐዊ (ርትዓዊ) መንገድ ለአገሪቱ ዜጐች መከፋፈሉን ሕዝቡ ካላመነበት መንግሥት የሕዝቡን ይሁንታ ያጣል፡፡ የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊነት እንዲረጋገጥ ማድረግ ይበልጡን አስፈላጊ የሚሆነው ደግሞ የብሔር ብዝኃነት ባለባቸው አገሮች ነው፡፡ እንደዚህ ባሉ አገሮች የሀብት ክፍፍል ፍትሐዊነት ካልተረጋገጠ መዘዙ ከባድ ነው፡፡ ለሕዝብ ይሁንታና ተቀባይነትም ጠንቅ ነው፡፡ ስለዚህ የኢኮኖሚ ዕድገት ብቻውን ለመንግሥት የሕዝብ ይሁንታና ተቀባይነትን በአጥጋቢ ሁኔታ አያስገኝም፡፡

ስለዚህ ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው የመራሔ መንግሥት ሰብዕና፣ ባህል፣ ሃይማኖት ወይም ዕድገት የመንግሥትን ሕዝባዊ ተቀባይነትና ይሁንታ በአስተማማኝ ሁኔታ አያረጋግጡም፡፡ እነዚህ የሕዝባዊ ይሁንታ ምንጮች የሚያስገኙት ሕዝባዊ ተቀባይነት ዘላቂ ያልሆኑ፣ ደካማና የማያስተማምኑ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ዘላቂ የሆነ፣ ጠንካራና አስተማማኝ ሕዝባዊ ይሁንታንና ተቀባይነትን የሚያስገኝ የመንግሥት ሥርዓት ነው፡፡ የሚያስገኘው ይሁንታና ተቀባይነት በአንድ ወቅት በሥልጣን ላይ ባለ መንግሥት ሳይሆን በመንግሥታዊ ሥርዓቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ እንዴትና ለምን ዘላቂ፣ ጠንካራና አስተማማኝ የሕዝብ ይሁንታን እንደሚያስገኝ ደግሞ በሚቀጥለው ጽሑፌ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡         

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕገ መንግሥት ኤክስፐርትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው gediontim [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡