የመዘዋወር ነፃነት መርህና ፈተናው

በመኮንን መርጊያ

ማንኛውም ተፈጥሮአዊ ሰው ለተለያዩ ዓላማዎች ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ይንቀሳቀሳል፡፡ ይህ እንቅስቃሴው ለራሱ ለተፈጥሮአዊ ሰውም ሆነ ለሌሎች ነፃነት ወይም ለአገር ደኅንነትና ጥቅም ሲባል የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ የዚህ የሰው ልጅ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ተፈጥሮአዊ ባህርይና ውስብስብ ፍላጎቶች፣ እንዲሁም እንቅስቃሴው ከድንበር አልፎ በአገሮች መካከል ከሚፈጥረው ጫና የተነሳ የሚደረገው የሕግ ጥበቃ ከአገሮች አልፎ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዲኖረው አድርጎታል፡፡

ከዚህ የሰው ልጅ ከቦታ ወደ ቦታ የመዘዋወር ዓለም አቀፋዊ ባህርይ የተነሳ “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነት 1948” አንቀጽ 13(1) ሥር፣ ማንኛውም ሰው በሚኖርበት አገር ውስጥ የመዘዋወርና የመኖር ነፃነት እንዳለውና በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር (2) ሥር ማንኛውም ሰው የሚኖርበትን አገር የራሱን አገር ጨምሮ የመልቀቅና ተመልሶ ወደ አገሩ የመግባት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ የዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈራሚ አገሮች በየአገሮቻቸው ሕግጋት ውስጥ ለዜጎች የመዘዋወር ነፃነት ልዩ ሥፍራ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡ ለምሳሌ የጀርመን ፌዴራል ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 11 እና 12 ሥር ስለጀርመን ዜጎች የመዘዋወር ነፃነት ሲደነግግ፣ የካናዳ ሕገ መንግሥት ደግሞ በምዕራፍ 4 በአንቀጽ 6 ሥር የመንቀሳቀስ መብት በሚል ርዕስ ስለካናዳ ዜጎች በአገር ውስጥና ከአገር ወጥቶ የመመለስ ነፃነት አስመልክቶ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ደንግጓል፡፡ ይህ የሚያሳየው የሰው ልጆች የመዘዋወር ነፃነት ጉዳይ በአገሮችም ሆነ በዓለም መንግሥታት ደረጃ ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት እንደሆነ ነው፡፡

የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ ስለመዘዋወር ነፃነት ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ለመዳሰስ አይደለም፡፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው የመዘዋወር ነፃነት ጽንሰ ሐሳብ በአገራችን ሕገ መንግሥት ውስጥ የተሰጠውን ሥፍራና ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት፣ ማብራሪያ ለመስጠትና ይህንን ጽሑፍ የማንበብ ዕድል ያገኙ አካላት ስለመዘዋወር ነፃነት ሕገ መንግሥታዊ መርህ ግንዛቤ እንዲያገኙ ነው፡፡

የመዘዋወር ነፃነት ጽንሰ ሐሳብ ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንፃር

በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው የዜጎች የመዘዋወር ነፃነት ጉዳይ የሁሉም አገሮች ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ እንደሆነ ሁሉ፣ በኢትዮጵያም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 32 ሥር ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት አንቀጽ 32(1) “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት፣ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት ነፃነት አለው” ይላል፡፡ በዚሁ አንቀጽ (2) ሥር “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ የመመለስ መብት እንዳለው” ይደነግጋል፡፡

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አገር እንደመሆኗ መጠን በውስጧ የያዘቻቸው የክልል መንግሥታትም የየራሳቸው ሕገ መንግሥታት አላቸው፡፡ እነዚህ የፌዴራልና የክልል ሕገ መንግሥታት እርስ በርስ ሊቃረኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 50(5) ሥር የክልል መንግሥታት በየራሳቸው ክልል ሥልጣን ሥር በሚወድቁ ጉዳዮች የየራሳቸው ሕገ መንግሥት ሊኖራቸው እንደሚችል፣ ክልሎች ሕገ መንግሥታቸውን ሲያወጡ የፌዴራሉን ሕገ መንግሥት መሠረት ማድረግ እንዳለባቸው ደንግጓል፡፡

ይህ ድንጋጌ በትክክል ተግባራዊ ስለመሆኑ ከዚህ ከያዝነው ጉዳይ ጋር የተያያዘው የመዘዋወር ነፃነት ጉዳይ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና የደቡብ ክልል መንግሥት ሕገ መንግሥቶች ከፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ጋር በተመሳሳይ አንቀጽ ሥር (አንቀጽ 32) “የመዘዋወር ነፃነትና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት መብት” በሚል ድንጋጌ ሥር፣ “በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 32 የተደነገገው እንደተጠበቁ ሆኖ፣ ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ወይም በሕጋዊ መንገድ በክልሉ ውስጥ የሚገኝ ሰው በመረጠው አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት፣ ሠርቶ የመኖር፣ ንብረት የማፍራትና የመያዝ፣ እንዲሁም በፈለገ ጊዜ ከክልሉ የመውጣት መብት አለው፤” በማለት የክልሎቹ ሕገ መንግሥቶች የፌዴራሉን ሕገ መንግሥት መሠረት አድርገውና ሳይቃረኑ መደንገጋቸውን ያሳያል፡፡ ስለዚህ ስለመዘዋወር ነፃነት ሕገ መንግሥታዊ መርህ የፌዴራሉም ሆነ የክልል ሕገ መንግሥታት አንድ ዓይነት ዓላማ እንዳላቸው ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል፡፡

ይህ የመዘዋወር ነፃነት ሕገ መንግሥታዊ መርህ በአገራችን ሕገ መንግሥት ውስጥ ሥፍራ ተሰጥቶት የመደንገጉ አስፈላጊነት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች በአገር ውስጥ በየትኛውም አካባቢ የመዘዋወር፣ የመኖሪያ ቦታ የመመሥረትና የመሥራት መብት፣ እንደዚሁም ከአገር የመውጣትና የመመለስ መብት እንዳላቸው ለማረጋገጥና በዚህ ዜጎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚከሰቱ ግንኙነቶች ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ነው፡፡

ከዚህ የምንረዳው የመዘዋወር ነፃነት የአገሪቱ የበላይ ሕግ በሆነው ሕገ መንግሥትና በየክልሎቹ ሕገ መንግሥቶች ሥፍራ መሰጠቱ የፌዴራሉ መንግሥት፣ የክልል መንግሥታት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ማኅበራት፣ እንዲሁም ዜጎች ሁሉ ይህንን የመዘዋወር ነፃነት መርህን የማክበርና የማስከበር ግዴታና ኃላፊነት እንዳለባቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት ሕገ መንግሥቶቻቸውን መሠረት አድርገው በየሥልጣን እርከኖቻቸው በሚያወጧቸው ሕጎች፣ ከመዘዋወር ነፃነት ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና የሕዝቦች የቡድን መብቶችንና የእያንዳንዱን ዜጋ የግል መብቱን የማረጋገጥና የማስከበር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ማለት ነው፡፡ ይህንን ሐሳብ የበለጠ ለመረዳት የመዘዋወር ነፃነት መርህ በአገራችን እንዴት እየተተገበረ እንዳለ እንመለከታለን፡፡

የመዘዋወር ነፃነት መርህ አተገባበር

የመዘዋወር ነፃነት መርህ አገራችን በምትመራበት ፌዴራላዊ አወቃቀር ውስጥ ግልጽነት ባለው ሁኔታ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት የተዋቀረው ብሔረሰባዊ ይዘት ባላቸው ክልሎች ነው፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በየክልሎቻቸው ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ፡፡ ይህ ማለት ግን የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች እንዲሁም ክልሎች ከሌሎች የክልል መንግሥታት ጋር እርስ በርስ አይገናኙም ማለት አይደለም፡፡ የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት መርህ ሲተገበር ክልሎች እርስ በርስና ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ግንኙነት ያደርጋሉ ማለት ነው፡፡ በዚህ ግንኙነታቸው የየራሳቸውን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ዜጎች መብት ከማስከበር አልፈው የሌሎች ክልሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ግለሰቦች መብቶችን ያከብራሉም ያስከብራሉ ማለት ነው፡፡

ይህንን የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት አሁን አገራችን ካለችበት ሁኔታ ጋር አገናኝተን ስንመለከት፣ ከመዘዋወር ነፃነት ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ክልሎች የአፈጻጸም ክፍተት መኖሩን እንመለከታለን፡፡ በአንዳንድ የአገሪቱ ክልሎች  በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው “የዚህ ብሔረሰብ አባላት ከክልላችን ይውጡ” እየተባለ ወደ ግጭት የመግባት  እውነታ የዚህ ክፍተት መገለጫው ነው፡፡

ይህንን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ኃይሎች ምንጫቸው ምንም ይሁን ምን፣ የአገሪቱ የበላይ ሕግ በሆነው ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ የተገለጸውን አጠቃላይ መርህ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባትና ይህንንም ለማሳካት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ግለሰቦች መሠረታዊ መብቶች መከበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ግለሰቦች መብቶች ሲጣሱና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ የመዘዋወር ነፃነት፣ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብቶች ሲረገጡ ይስተዋላል፡፡ በዚህ በማንኛውም መለኪያ ተቀባይነት በሌለው አስተሳሰብ የዜጎች ሕይወት ሲጠፋ፣ ንብረት ሲወድምና በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ ተስተውሏል፡፡

አሁን አገሪቱ ባለችበት ከፍተኛ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ለውጥ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የአገሪቱ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ጭምር በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እየተሳተፉ ባሉበት ወቅት፣ የገዛ ወገኑን “ከአካባቢዬ ለቅቀህ ውጣ” የሚል አስተሳሰብ በማንኛውም መለኪያ ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ከዚህ እንቅስቃሴ በስተጀርባ ሆነው ማንኛውንም ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ አካላት፣ የአገሪቱን የበላይ ሕግ እየጣሱ መሆናቸውንና ይህ ደግሞ በሕግ የሚያስጠይቅ ከፍተኛ ወንጀል መሆኑን ሊረዱ ይገባል፡፡ የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል መንግሥታትም የዚህ እኩይ ተግባራት ምንጮች ምን እንደሆኑ በመለየት ጥፋት ፈጽመው በተገኙ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ የመውሰድ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር፣ የፌዴራልና የክልል ሕግጋትን የመፈተሽና የማስተካከያ ዕርምጃዎችን የመውሰድ፣ በፌዴራልና በክልል መንግሥት እንዲሁም በክልልና በክልል መንግሥታት መካከል ያለውን የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት የማጠናከር ተግባራትን ትርጉም ባለው ሁኔታ በስፋት ሊተገብሯቸው ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው mergia.mekonnen [at] yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡