ውጤታማነት የሚጠበቅባቸው የፖሊሲ ጥናት ማዕከላት

የኢትዮጵያ መንግሥትና ባለሥልጣኖቹ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ለማምጣት ለሕዝቡ ቃል ከገቡ በኋላ ቃላቸውን መጠበቅ ተስኗቸው ሲንገዳገዱ ማየት የተለመደ ነገር ነው፡፡ የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ ኢትዮጵያ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ነበር፡፡ በኢኮኖሚው መስክ ኢትዮጵያ ትክክለኛ መስመር ስለመያዟ ቀንደኛ ተቺዎቹ ጭምር ይመሰክራሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ የማሸጋገርና በመንግሥት የውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ላይ የዜጎቹን ትርጉም ያለው ተሳትፎ ከማረጋገጥ አኳያ በረጅም ርቀት ላይ እንደምትገኝ የብዙ ታዛቢዎች ምስክርነት ይሰጣል፡፡

ይህ ሐሳብ በቅርብ ወራት የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለመገምገም በመንግሥት በተሰናዱ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮችም ላይ ተንፀባርቋል፡፡ በዋነኛነት መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ያጎሉት ሐሳብ የመንግሥት ሠራተኞች አቅም ማነስና አላስፈላጊ የቢሮክራሲ መንዛዛት፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሙያዊ አገልግሎትን እየጎዳው እንደሆነ ነው፡፡ ተመሳሳይ ሥጋቶችና ወቀሳዎች ገዥው ፓርቲ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በመቐለ ባካሄደው ጉባዔ ላይም ተንፀባርቀዋል፡፡ በሁለቱም መድረኮች መንግሥት እነዚህ ክፍተቶች መኖራቸውን አምኗል፡፡ እንደተለመደው ችግሮቹን ለመቅረፍ ቃል የገባ ሲሆን፣ ይህን ለመፈጸም አሁን የሕዝብ ተሳትፎ ያስፈልገኛል ብሏል፡፡

የያዝነው ዓመት ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወደ ሥራ የሚገባበት የመጀመሪያ ዓመት ነው፡፡ ይኼው ዕቅድ ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ታልሞ ሲሠራበት የነበረው ዕቅድ ቀጣይ ክፍል እንደመሆኑ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ሌላ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ ከዕቅዱ ረቂቅ ለመረዳት እንደሚቻለው እንደ ሌሎች የመንግሥት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ሁሉ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ የሕዝቡን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ታልሟል፡፡ የዴሞክራሲን መርሆዎች የካተተ የፖሊሲ አፈጻጸም በገዥው ፓርቲ ዕውቅና ማግኘቱ ቢያንስ ከጽንሰ ሐሳብ አንፃር የምዕራባውያንና የአገሬውን ምሁራን ቡራኬ አግኝቷል፡፡

ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥት ለተቺዎቹና ለተቃዋሚዎቹ አስተያየት ስሱና በቀላሉ የሚበረግግ እየሆነ መምጣት አገርኛና ዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶችን ሥጋት ላይ ጥሏል፡፡ በመሠረቱ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ባሉት ዓመታት ገዥው ፓርቲ በአንድ ወገን፣ ምሁራን፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የምርምር ተቋማት፣ ሚዲያና የሙያ ማኅበራት ለሌላ ወገን ሆነው ውጥረት የበዛበት ግንኙነት ነው የነበራቸው፡፡ የዚህ ውጥረት መሠረታዊ መነሻ በሁለቱም ወገኖች ተመራጭ የሆነው የወገንተኝነት ፖለቲካ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ መንግሥትም በልዩነቱ ላይ ተደራድሮ ከማጥበብ ይልቅ የመገፋፋት ፖለቲካን በማጠናከር ለአካሄዱ የተመቹ ምሁራንን በጥቅማ ጥቅም በማማለል ወደ ራሱ የማስጠጋት አሠራር መከተሉ ውጥረቱን እንዳቆየውም የሚተቹ አሉ፡፡

ከዚህ የኢትዮጵያ ሁኔታ ፍፁም ተቃራኒ በሆነ አካሄድ የበለፀጉ አገሮች ለስኬታቸው ቁልፍ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የምርምር ተቋማት በተለይ ፖሊሲ ላይ አተኩረው የሚሠሩት የሚያወጧቸውን ሥራዎች ለመንግሥት ውሳኔ አሰጣጥ እንደ ግብዓት መጠቀም ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመሥርተው የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በተለይ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት በመንግሥትና በሕዝቡ መካከል መደበኛ ያልሆነ ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ እነዚህ ተቋማት ጥልቅ ትንታኔ ያቀርባሉ፡፡ በአብዛኛው እነዚህ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ ሳይንሳዊና ባህላዊ ፖሊሲዎች ላይ አተኩረው በቋሚነት ጥናት ያደርጋሉ፡፡ የጥናት ውጤቶቻቸው ለሕዝቡና ለፖሊሲ አውጭዎች እንዲደርሱም ያደርጋሉ፡፡ በተለይ ፖሊሲ አውጭዎች አስተማማኝ፣ ተደራሽና ጠቃሚ መረጃን ለሕዝቡ አጥብቀው ይሻሉ፡፡ በሥራ ላይ ያሉት ፖሊሲዎች እንዴት እየሠሩ እንደሆነና በአማራጭ ፖሊሲዎች፣ ለውጥ ለማድረግ ስለሚያስፈልገው ወጪ ስለሚያስከተለው ተፅዕኖ በዝርዝር ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ የፖሊሲ ጥናት ተቋማቱ ደግሞ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ጠቃሚ መረጃዎችን በወቅቱ ያቀርባሉ፡፡ ይህ ደግሞ ፖሊሲ አውጪዎች ብቻ ሳይሆኑ ሕዝቡም በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲሰጥ ያስችላል፡፡ በዚህም የፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ. የ2014 የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ጠቋሚ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በዓለም ላይ ከ6,600 በላይ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ይገኛሉ፡፡

መሰል ተቋማት ቢያንስ በስም ደረጃ በኢትዮጵያም ይገኛሉ፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ሪፖርት እንዲያውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ በአቶ ንዋይ ገብረአብ የሚመራውን የኢትዮጵያ የልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ውስጥ 15ኛው ምርጥ ተቋም አድርጎ ያስቀምጠዋል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ያሉት ተቋማት ገለልተኛና ሙያዊ ዕውቀትን የሚያመርቱ፣ በመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ ትክክለኛ ግምገማ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የመንግሥት እንቅስቃሴዎችን በቋሚነት የሚከታተሉና የሚገመግሙ መሆናቸው ወይም አለመሆናቸው አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ጉዳዩ ለክርክር የተጋለጠ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተቋማት በኢትዮጵያ አሉ በማለት የሚከራከሩትም ቢሆን የእነዚህ ተቋማት ቁጥርና ተፅዕኖ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ የሚቀበሉ ናቸው፤›› ያሉት የማኅበራዊ ጥናት መድረክ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ የፖሊሲ ጥናት መድረክ መሥራችና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በልቀት ደረጃ ከሚገኙ ጎምቱ ምሁራን አንዱ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ራህመቶ ናቸው፡፡ ‹‹የማኅበራዊ ጥናት መድረክ የፖሊሲ ጥናት ተቋምን መሥፈርት ያሟላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ተቋሙ በአገሪቱ የመጀመሪያው ገለልተኛ የፖሊሲ ጥናት ተቋም ነኝ ብሎ ነው ራሱን የሚገልጸው፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

በመስከረም ወር 2005 ዓ.ም. አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ብቅ ሲሉ ይህ የጥናት ተቋማት ሁኔታ እንደሚቀየር ብዙዎች ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ አቶ ኃይለ ማርርያም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በማስተማርና በአመራር ደረጃ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሕይወት ጋር በሚገባ የተዋወቁ ስለነበሩ፣ በምርምርና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አስተዳደር የመፍጠር ፍላጎት እንደሚኖራቸው ተገምቶ ነበር፡፡

እርግጥ አቶ ኃይለ ማርያም መስከረም 11 ቀን 2005 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንዲሠሩ ይሁንታ ለሰጧቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር ትኩረት ካደረጉባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ይኼው የጥናት ተቋማት ሚና አንዱ ነበር፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎቻችን፣ የምርምር ማዕከሎቻችንና የሙያ ማኅበሮቻችን የዴሞክራሲ ባህል ለመገንባት የምናደርገውን ጥረት የሚያግዙ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር በማድረግ ቁልፍ ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶችና ምርምሮች፣ በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሠረቱ ጥናቶችን እንዲሠሩ ለማበረታታት ትኩረት ሊደረግ ይገባል፤›› ብለው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ንግግር ካደረጉ በኋላ ባሉት ሦስት ዓመታት በጉዳዩ ላይ መሠረታዊ ለውጥ አልታየም ብለው የሚተቿቸው አሉ፡፡ ለዚህ ለውጥ አለመኖር ብዙዎቹ ገዥው ፓርቲ የሚከተለው ጠቅላይና እኔ አውቅልሃለሁ የሚለው ርዕዮተ ዓለም እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ አስተያየት ሰጪዎች በተጨማሪም አቶ ኃይለ ማርያም ወደ ሥልጣን የመጡት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የሥራ ዘመን መካከል መሆን፣ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚመች እንዳልሆነ ተከራክረዋል፡፡ አሁን ዋናው ጥያቄ በመጭዎቹ አምስት ዓመታት ነገሮች ይቀየራሉ ወይ ነው፡፡

በእነዚህ ተግዳሮቶች መካከልም ቢሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት የተወሰዱ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች በኢትዮጵያ ውጤታማ የፖሊሲ ጥናት ተቋማትን ለመፍጠር መሠረት የሚጥል እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡ በመሠረቱ የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዴሚን የመንግሥት የፖሊሲ ጥናት ተቋም አድርጎ የማቋቋም ውሳኔ የተሰጠው አቶ ኃይለ ማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተመረጡበት ዓመት ነበር፡፡ አካዴሚው መጀመሪያ ላይ በ1999 ዓ.ም. የተመሠረተው ሳይንቲስቶች በኢትዮጵያ የሳይንስ ባህልን በማስፋፋት ላይ ካደረጉት መደበኛ ያልሆነ ውይይት ነበር፡፡ በወቅቱ ሳይንቲስቶቹ አካዴሚ በመመሥረት ዓላማውን ለማስረፅ እንደሚቻል አምነው ነበር፡፡

በሒደትም አካዴሚው በመጋቢት 2002 ዓ.ም. ዕውቅና ዝነኛ የሆኑ ሳይንቲስቶችን በማቀፍ ገለልተኛ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመና መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሆኖ ተቋቋመ፡፡ ሳይንሳዊ የሆነ ዕውቀት ለልማት፣ ለብልፅግናና ለተሻለ የጤና አገልግሎትና የዜጎች ኑሮ ለማሻሻል አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ለመሥራት አልሞ የተቋቋመው አካዴሚ በሁሉም የሳይንስ ዘርፎች ላይ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ሒሳብ፣ ጤና ሳይንስ፣ ግብርና ሳይንስ፣ ኢንጂነሪንግ፣ ማኅበራዊ ሳይንስና ሂዩማኒቲስና ሥነ ጥበብን ጨምሮ ምርምርና ጥናት ማድረግን ዓላማው አድርጎ ነበር፡፡ በተጨማሪም ዓላማውን ለማሳካት አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ኮንፈረንሶችና ወርክሾፖችን የማድረግ፣ ልቀት ላሳዩ ሳይንቲስቶች ሽልማት እንደሚሰጥና በራሱ ጆርናልና በሌሎች መጻሕፍትና የሕትመት ውጤቶች ጥናቶችን እያተመ ለማሠራጨትም አልሞ ነበር፡፡

ነገር ግን በ2005 ዓ.ም. መንግሥት ለፓርላማ ያቀረበው ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዴሚ የመንግሥት የፖሊሲ ጥናት ተቋም እንዲሆን የሚጠይቅ ነበር፡፡ ረቂቁ አዋጅ ሲፀድቅ አካዴሚው ከገለልተኛ ተቋምነት ወደ መንግሥት የጥናት ተቋም ተቀይሯል፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 783/2005 አካዳሚውን ለማቋቋም መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን ያስቀምጣል፡፡ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለማከናወን፣ በቂ የሆነ ሳይንሳዊ መረጃ የያዙ ዕውቅ ባለሙያዎችን በመንግሥት ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ለማሳተፍ፣ የፖሊሲ ዝግጅትና አፈጻጸምን ለማገዝ፣ በሳይንስ ዙሪያ መንግሥትን ለማማከር፣ ዋና ዋና የሳይንስ ግኝቶችን በሰፊው እንዲታወቁ ለማድረግ የሚያስችሉ ሕዝባዊ መድረኮችንና አግባብ ያላቸውን ሌሎች መርሐ ግብሮችን ማደራጀትና በብሔራዊ የኢኖቬሽን ሥርዓት ውስጥ በባለድርሻ አካላት መካከል በሚደረገው ግንኙነት በሚካሄደው ጥናትና ምርምርና በሚሰጠው በመረጃ ላይ የተመሠረተ ሙያዊ እገዛ ለቴክኖሎጂ ሽግግር የራሱን ሚና መጫወት፣ በማቋቋሚያ አዋጁ ከተጠቀሱ ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በማቋቋሚያ አዋጁ አካዴሚው ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው ተቋም ሆኖ ተቋቁሟል፡፡ ነገር ግን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካይነት ከመንግሥት ጋር ግንኙነት እንዲኖረው ተደርጎ ነው የተቋቋመው፡፡ ከሚኒስቴሩና ከሌሎች አግባብነት ካላቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚቀርብለት ጥያቄ መሠረት በመረጃ ላይ የተመሠረተ ሳይንሳዊ ምክር እንደሚሰጥም ተደንግጓል፡፡ መንግሥትም በፋይናንስና አግባብነት ባላቸው ሌሎች መንገዶች አካዴሚውን እንደሚደግፍም ያስቀምጣል፡፡ የአካዴሚው በጀት ከመንግሥት ከሚሰጠው የበጀት ድጋፍ በተጨማሪ ከአገልግሎት ክፍያ፣ ከአባላት መዋጮና ከሌሎች ምንጮች እንደሚመነጭም ተገልጿል፡፡ አካዴሚው ዘላቂ የሆነ የፋይናንስ ምንጭ ለመፍጠር እንዲያስችለው የገቢ ማስገኛ ፋውንዴሽን ማቋቋም እንደሚችልም አዋጁ ይፈቅዳል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚን በአዋጅ የማቋቋም አስፈላጊነት በሚመለከት የቀረበው ማብራሪያ ሰነድ እንደሚጠቁመው፣ አካዴሚው ከመንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት በጋራ ጠቀሜታ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በዳበሩት አገሮች የሚገኙ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ሮያል ሶሳይቲና የአሜሪካ ብሔራዊ የሳይንስ አካዴሚ አልያም በቅርብ ጊዜያት የተቋቋመው የደቡብ አፍሪካ ሳይንስ አካዴሚ ልምድ ተመሳሳይ ግንኙነትን እንደያዘም ያሳያል፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ አካዴሚው ለማንኛውም መንግሥታዊ አካል ተጠሪ ሳይሆን መቋቋሙን ይጠቁማል፡፡ መንግሥት የሠራው ውጤት ዋና ተጠቃሚ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ ‹‹በአገር ጉዳይ ላይ ያተካረ ሥራ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ከውጭ በሚገኝ ድጋፍ ላይ ጥገኛ መሆኑ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው ስለሚችል አግባብነት አይኖረውም፤›› ሲል የሚገልጸው ይህ ሰነድ ሕጋዊ ማዕቀፉ የአካዴሚውን ተቋማዊ ጥንካሬ ከማሳደግም በላይ ከውጭ ተፅዕኖ የመጠበቅ ዓላማ እንዳለው ያመለክታል፡፡

አካዴሚው ከተመሠረተ በኋላ የተለያዩ ጥናቶችንና ምርምሮችን በመሥራት፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በማካሄድና ወርክሾፖችን በማዘጋጀት ተጠምዷል፡፡ ከአካዴሚው የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ከ40 በላይ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በጤና አገልግሎት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥርዓትና በትምህርት ጥራት ላይ የተካሄዱት ውይይቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይሁንና የአካዴሚው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር እስካሁን ለሕዝብ ተደራሽ አልሆነም፡፡

ከመንግሥት ጋር አጋር ሆኖ የመንግሥት ተቋማትን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችንና ሌሎች ድርጅቶችን በማስተባበር በፖሊሲ ጥናት መስክ ትልቅ ልዩነት እንደሚፈጥር ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የአካዴሚው አንኳር እሴቶች ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ፣ ገለልተኝነት፣ መረጃ ላይ የተመሠረተ የውሳኔ አሰጣጥ፣ ወጥ የሆነ የአዕምሮ ውጤት፣ ተቋማዊ ነፃነት የሚያመለክቱት ተቋሙ ውጫዊ ተፅዕኖን ለማስወገድ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ነው፡፡ በአካዴሚው ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉት እንደ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ፣ ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነና ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ተፈራ ያሉ ጎምቱ ምሁራን አካዴሚው ሳይንሳዊ የሆነ ዕውቀት ማዕከል ይሆናል የሚለውን ተስፋ የጨመረ ሆኗል፡፡ ይህ አካዴሚ በኢትዮጵያ የፖሊሲ ተቋማት እያበበ ያለ ባህል እንደሆነ ጠቋሚ ነው?

እያደገ ያለ ባህል?

በአካዴሚያዊ ምርምርና በውትወታ ሥራ መካከል ያለው ልዩነት አልፎ አልፎ ለመለየት እንደሚያስቸግር የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይባስ ብሎ አንዳንድ ሪፖርቶች የፖሊሲ ጥናት ተቋማት አንድ የተለየ አጀንዳን ለመደገፍ ገንዘብ እንደሚቀበሉ ያሳያሉ፡፡ ለእነዚህ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ‹‹ተዓማኒነት›› የሚለካው ለለጋሾች ዓላማ በመቆም ነው፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተቋቋሙ እንደ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሙያዊ ማኅበሮች ያሉ ሲቪክ ድርጅቶች የፖሊሲ ቅኝት ያላቸው ምርምሮችን ሲሠሩ ነበር፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ባህል በእንጭጭ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሰፊና ብዝኃነት መለያው ለሆነ አገር በሥራ ላይ ያሉት የጥናት ተቋማት ጥቂት ናቸው፡፡ አቶ ደሳለኝ፣ ‹‹ጥቂት ሲቪክ ድርጅቶች ያላቸው ባህሪ ከፖሊሲ ጥናት ተቋማት ጋር ያመሳስላቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ፖሊሲ ላይ አተኩረው ምርምር ያካሂዳሉ፡፡ ሌሎቹ ግን ሕዝባዊ ጠቀሜታ ያለው ፕሮግራምም የላቸውም ነበር፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ደሳለኝ በኢትዮጵያ ያሉ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ከአገሪቱ የፖለቲካ ባህልና ታሪካዊ ዳራ በመነሳት የትኩረት አቅጣጫቸውና አሠራራቸው ላይ ልዩነት ሊፈጥሩ ቢችሉም፣ ዋና ዓላማቸው በሌላው ዓለም ካሉ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ሊለይ እንደማይገባ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖሊሲ ተመራማሪዎች በጣም ጠቃሚ የሆኑ ግን ደግሞ ፈታኝ የሆኑ ሥራዎች ይጠብቃቸዋል፡፡ አንደኛ መንግሥት በማሳመን ገለልተኛ አስተያየት እንዲቀበል ለማሳመን የተቻላቸውን ሁሉ ሊጥሩ ይገባል፡፡ ሁለተኛ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት በተመራማሪዎች፣ በሕዝቡና በውሳኔ ሰጪዎች መካከል የሀሳብ ልውውጥ ባህል እንዲዳብር መርዳት አለባቸው፡፡ ሦስተኛ የፖሊሲ ተመራማሪዎች በሥራቸው አዳዲስ ፈጠራና አቀራረብ ማሳየት አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

ባደጉት አገሮች የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ገለልተኝነት እንደ ትልቅ ችግር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየጎላ ቢመጣም፣ ተመሳሳይ ችግር በቅርቡ የተቋቋሙ የኢትዮጵያ ተቋማትንም እየነካ ነው፡፡ የተለያዩ ምርምሮች የኢትዮጵያ ተቋማት በሁለመናቸው ኢትዮጵያን መምሰል እንዳለባቸውና ሥራዎቻቸው የዜጎች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆን እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ ‹‹በአንድ በኩል መንግሥታዊ ያልሆኑ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት በገንዘብም ሆነ በሐሳብ የውጭ ኃይሎች ላይ ጥገኛ ናቸው፡፡ ስለዚህም እንቅስቃሴያቸው ለአገር ያለውን ጠቀሜታ ካየን ከአማካይ በታች ነው፡፡ በሌላ በኩል የመንግሥት የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ገለልተኛ አይደሉም፡፡ ለመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ለፖለቲካ ተፅዕኖ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የጥናት ውጤቶቻቸው በዋነኛነት ያለሙት የመንግሥት ድርጊትና እንቅስቃሴን ዕውቅና መስጠት ላይ ነው፤›› ያሉት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ በአንድ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በተመራማሪነት የሚሠሩ ኤክስፐርት ናቸው፡፡

በተመሳሳይ አቶ ደሳለኝ በጉዳዩ ላይ ሲናገሩ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ሥልጣን ላይ ከነበሩ መንግሥታት ልምድ ለመረዳት እንደሚቻለው ገለልተኛ አስተያየትን እንደሚያገሉ ነው፡፡ ፖሊሲ ለማርቀቅ፣ ለመቅረፅና ለመገምገም ውሳኔ ሰጪዎች መረጃ፣ ትንታኔና መሰል ሥራዎችን የሚያሠሩት በመንግሥት ኤክስፐርቶች ነው፡፡ መንግሥት የሚያወራውና የሚሰማው ራሱን ነው፡፡ በዚህም ከተለያዩ ሐሳቦችና አስተያየቶች የሚገኘውን ጠቀሜታ በራሱ ፈቃድ ያልፈዋል፡፡ በእኔ እምነት የተለያዩ ዓላማዎችን ያነገቡ በርካታ ገለልተኛ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ያስፈልጉናል፤›› ብለዋል፡፡

ከላይ የተገጸው የፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እ.ኤ.አ. በየካቲት 4 ቀን 2015 በተመድ የኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ አዲስ አበባ ላይ ይፋ ሲደረግ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ በተመሳሳይ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት  ወጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ የመንግሥት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖ ሊያደርግ እንደማይገባ አስገንዝበዋል፡፡ ገዥ የሆነውን የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም አለመቀበል እንኳን ለመንግሥታዊ ተቋማት ለግል ተቋማት እንኳን የማይቻል እየሆነ እንደመጣ የተለያዩ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ የልማት ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሙሉ ገብረየሱስ በተመሳሳይ መድረክ ተቋማቸው በመንግሥት የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖ ሥር እንዳልሆነ ተከራክረዋል፡፡ ተቋሙ በ1991 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የተቋቋመ ነው፡፡

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ‹‹ከሳይንስ አካዴሚ ውጪ ያሉት የመንግሥት የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ከፓርላማ ግልጽ የሆነ ውክልና ባልተሰጠው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ይህ ያልተለመደና ችግር ያለበት አሠራር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና ለብዙ አስተያየት ሰጪዎች የተቋማቱ ሕጋዊ መሠረት ከችግሮች ሁሉ ዝቅተኛው ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ የተቋማቱን አቅም በመገንባት ተፈላጊነታቸውን መጨመር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃና በአገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅናና የገንዘብ ድጋፍ ማግኛ መንገድ እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ይህ ለማሳካት ራሳቸው ላይ ለውጥ እያደረጉ በመጓዝ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰላምና ልማት ኢንስቲትዩት ከአገሪቱ ተቀዳሚ የመንግሥት የፖሊሲ ጥናት ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ በ1988 ዓ.ም. የተመሠረተው ይህ ኢንስቲትዩት ከሌሎች ተቋማት በተለየ መልኩ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ምርምር ይሠራ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና የውጭ ግንኙነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ‹‹ኢንስቲትዩቱ በተቋቋመበት ወቅት መሰል የመንግሥት የፖሊሲ ጥናት ተቋማት አልነበሩም፡፡ በዚህም የተነሳ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ይሠራ ነበር፡፡ ተልዕኮው ጠባብ አልነበረም፡፡ እነዚህን በርካታ ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችል በሚገባ የሠለጠነ የሰው ኃይልም አልነበረውም፡፡ እንቅስቃሴዎቹም በፍላጎት ላይ የተመሠረቱ ነበሩ ማለት አይቻልም፤›› በማለት ችግሮቹን ያስረዱት የተቋሙ ከፍተኛ የሰላምና ደኅንነት ተመራማሪ አቶ አበበ ዓይነቴ ናቸው፡፡ ተቋሙ ከዚህ በፊት ከጥናት በተጨማሪ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚመደቡ አዳዲስ ዲፕሎማቶች በመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ሥልጠና ይሰጥ ነበር፡፡ የሶማሊያ የጎሳ መሪዎችን በሶደሬ ማደራደሩም ይታወሳል፡፡ በምርጫ ወቅት የሲቪክ ትምህርትም ሰጥቷል፡፡ በሚዲያ ካውንስል ላይ ሥልጠና መስጠትና በመልካም አስተዳደር ላይ ለክልሎች ሥልጠና መስጠትም እንዲሁ ተጠቃሽ ናቸው፡፡               

እንደ አቶ አበበ ገለጻ፣ ተቋሙም ሆነ መንግሥት ይህን ክፍተት በመረዳታቸው በአካሄዱ ላይ በቅርቡ ለውጥ ተደርጓል፡፡ ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. ባፀደቀው ደንብ ኢንስቲትዩቱ አሁን የውጭ ጉዳይና ስትራቴጂክ ጥናቶች ኢንስቲትዩት በሚል ተቀይሯል፡፡ አሁን የትኩረት አቅጣጫው በውጭ ግንኙነት፣ በሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲወሰን ተደርጓል፤›› በማለት አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡

በ1990 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 22 የተቋቋመው ሌላኛው የመንግሥት የፖሊሲ ጥናት ተቋም የፍትሕና የሕግ ሥርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት በተመሳሳይ የተለያዩ ለውጦችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ተጠሪነቱ ሲቀያየር የነበረው ይህ ተቋም በአሁኑ ጊዜ ተጠሪነቱ ለሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሆኗል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለ ሚካኤል መላኩ የተጠያቂነት ጉዳይ ለተቋሙ ሥጋት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለተቋሙ ዋናው ነገር ለመሥራት የሚያስችል ከባቢ ሁኔታ መኖሩና ተቋሙ ነፃና ውጤታማ የመሆኑ ጉዳይ ነው ብለዋል፤›› ብለዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዓላማ የተለያዩ ጥናቶችና ምርምሮችን በማድረግ የፍትሕና የሕግ ሥርዓቱን ማዘመንና ማጠናከር ነው፡፡ ተቋሙ በሕግና በፍትሕ ጉዳዮች መንግሥትን ያማክራል፡፡ በተጨማሪም በሥራ ላይ የነበሩ ሕጎችን ሕገ መንግሥቱን በተሟላ ሁኔታ ሥራ ላይ ለማዋል፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማፋጠንና መልካም አስተዳደርን ወይም የሕግ የበላይነትን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ማሻሻሉን አቶ ኃይለ ሚካኤል ይጠቅሳሉ፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ውጤታማ እንዲሆኑ የማገዝ ኃላፊነትም ተሰጥቶታል፡፡ ‹‹ኢንስቲትዩቱ ሕጎችን ከማሻሻል በተጨማሪ አዳዲስ ሕጎች እንዲወጡ አድርጓል፡፡ በሕግ ትምህርትና ሥልጠና ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያግዙ ጥናቶችን አድርጓል፡፡ ሕጎችን በጥናትና ምርምር ተመርኩዞ ለማሻሻል ባደረገው ጥረት 18 ሕጎች ተረቀዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተሻሻለው የወንጀል ሕግ፣ የቤተሰብ ሕግ፣ የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ሕግ፣ የግብርና ታክስ ሕግ ፀድቀው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ ሌሎች ጠቃሚ የሆኑና ውሳኔ የሚጠበቁ ሕጎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግንና የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግን መጥቀስ ይቻላል፤›› በማለት አቶ ኃይለ ሚካኤል አብራርተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራሙን በበላይነት ይመራ ነበር፡፡ ‹‹ፕሮግራሙ ወደ ፍትሕ ማኒስቴር እስኪዘዋወር ድረስ የፍትሕ አካላትን ከበጀት ጀምሮ በሰው ኃይልና በቴክኒክ ድጋፍ ያደርግ ነበር፡፡ ለሕግ ትምህርት ቤቶችም ተመሳሳይ ድጋፍ ይሰጥ ነበር፡፡ የመማሪያ ሰነዶችን፣ የኮርስ ፕሮግራሞችንና የተለያዩ መመርያዎችን ያዘጋጅ ነበር፡፡ በማስተማር ዘዴና በአስተዳደር ላይ ሥልጠና ይሰጥ ነበር፤›› በማለትም በአሠራሩ ላይ ለውጥ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ የሕግ መረጃዎችን እንዲያሳትምና እንዲያሠራጭም ይጠበቃል፡፡ ‹‹ከሠራናቸው የምርምር ሥራዎች ጋር ሲነፃፀር ያሳተምነው በጣም ጥቂቶቹን ብቻ ነው፡፡ እርግጥ የመንግሥት ተቋም እንደመሆኑ የእኛ ጥናትና ምርምር በዋነኛነት ለመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔ የሚረዳ ነው፡፡ በደንቡም የተጣለብን ኃላፊነት ይኼው ነው፡፡ በ2007 ዓ.ም. ብቻ 45 ጥናቶችን አድርገናል፡፡ በልማት፣ በሰብዓዊ መብት፣ በመልካም አስተዳደር በተለይ በሙስና ላይ ጥናቶችን አድርገናል፤›› በማለት ዳይሬክተሩ ያክላሉ፡፡ ከሃርቫርድ የኬኔዲ የመንግሥት ጥናት ትምህርት ቤት የወንጀል አስተዳደር ትምህርት ክፍል ጋር በትብብር የፍትሕ አካላት አፈጻጸም መለኪያ እያዘጋጁ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ተቋሙ ከራሱ ተነሳሽነት በተጨማሪ ጥያቄ ሲቀርብለት የተለያዩ ጥናቶችን ያደርጋል፡፡ ለአብነትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኢንስቲትዩቱ ጥናት እንዲያደርግላቸው አድርገዋል፡፡ ተቋሙ ወደፊትም ተጨማሪ ደንበኞችና ኤክስፐርቶችን ለመሳብ የሚያስችል አዲስ መዋቅር መሥራቱን አቶ ኃይለ ሚካኤል ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አቅም እየገነባን ነው፡፡ አዲሱ መዋቅር በሚገባ የሠለጠኑ ኤክስፐርቶችን ለመሳብና ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችለን ነው ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡

ከ2001 ዓ.ም. በፊት በጣም ንቁ ከነበረው ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ በመቀጠል በሥራዎቹ በግልጽ የሚታየው መንግሥታዊ ያልሆነ የፖሊሲ ጥናት ተቋም የማኅበራዊ ጥናት መድረክ ነው፡፡ በልማትና ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚሠራውና በተለያዩ ፖሊሲዎች ላይ አተኩሮ የሚሠራው ይህ ተቋም የተለያዩ ፖሊሲዎች ላይ የሠራው ትንተና ታትሞ ገበያ ላይ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ይገኛል፡፡

የማኅበራዊ ጥናት መድረክ በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የሕዝቡን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ ሲሆን፣ የፖሊሲ ውሳኔ ሰጪዎች በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ አሳታፊ እንዲያደርጉ ለማገዝ የሚያስችሉ ምርምሮችን እንደሚሠራ ይገልጻል፡፡ በአጠቃላይ በልማትና በዴሞክራሲ ላይ የሚያተኩረው ይህ መድረክ በድህነት፣ በአካባቢ ጥበቃና በሲቪል ማኅበራት ላይ የተለየ ትኩረት ያደርጋል፡፡ የተቋሙ መሥራቾች ሰፊ ልምድ ካላቸውና ከሥራ ከተገለሉ የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሙያዎች ዕውቀትን ለአዲሱ ትውልድ ለማሸጋገርም የተለያዩ መድረኮችን ይፈጥራሉ፡፡ ይህ በኢትዮጵያ የማይታወቀውን የፖሊሲ ቀጣይነት ባህል ለማሳደግ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ታይቷል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት የምርምር ጉዳዮችን ከመለየት፣ ኤክስፐርቶችን ከመመልመልና ከማቆየት እንዲሁም ከመንግሥትና ከለጋሾች ተፅዕኖ ነፃ ከመሆን አኳያ ተግዳሮቶች አሉባቸው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ተቋማትም የሚሠራ ችግር ነው፡፡ ይሁንና የነፃነቱ ጉዳይ ከሁሉም የላቀ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ እየተበራከተ የመጣውን አስተያየት ተኮር የኅትመት ባህልና ያለ ተጨባጭ መረጃና ማስረጃ የአገሪቱ ወጣቶች በተለያዩ መድረኮች (ማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ) ልዩነታቸውን ለማጥበብ ሌት ተቀን ደፋ ቀና በሚሉበት በዚህ ጊዜ፣ የሰከነና የሠለጠነ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ሳይንሳዊ ዕውቀት ላይ አተኩረው የሚሠሩ የጥናት ተቋማት የዚህ ችግር መውጫ ቀዳዳም ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡