ኮብራ እባብ

በመርዛማነታቸው የሚታወቁት ኮብራ እባቦች ‹‹ንጉሥ ኮብራ›› በመባልም ይታወቃሉ፡፡ በብዛት የሚገኙት በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ነው፡፡ በጫካና በረግረጋማ ስፍራ መኖርን ይመርጣሉ፡፡ ከ5.6 ሜትር እስከ 5.7 ሜትር ድረስ ይረዝማሉ፡፡ የአንድ ኮብራ ንድፊያም አንድ ዝሆን የመግደል አቅም አለው፡፡

ኮብራዎች ትናንሽ አጥቢ እንስሳትን፣ እንሽላሊትና ወፎችን ይመገባሉ፡፡ በአፍሪካና በደቡብ እስያ የሚገኙት ማንጎሲ የተባሉ አጥቢ እንስሳት ግን የኮብራ ጠላት ናቸው፡፡ ቀን ሲያድን የዋለ ኮብራ ማታ ላይ የማጎሲ እራት ሊሆን ይችላል፡፡

ናሽናል ጂኦግራፊ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ ኮብራዎች ከእባብ ዝርያዎች በተለየ መልኩ እንቁላላቸውን የሚያስቀምጡት ጎጆ ሠርተው ነው፡፡

ራሳቸውን በመከላከል ጊዜ፣ ሁልጊዜም ጠንካራ ሆነው መታየትን ይመርጣሉ፡፡ ጠላት ሲጠጋቸው አንገታቸውን በማቅናት ከጭንቅላታቸው ሥር በሁለቱም ጎን ያሉትን ጡንቻዎች ይወጣጥራሉ፣ ሰውነታቸውንም ያተልቃሉ፡፡

ኮብራዎች ሲቆጡ፣ ሲርባቸውና አደጋ ውስጥ መሆናቸውን ሲገነዘቡ ቤተሰቦቻቸውን እንዴት ማረጋጋት እንዳለባቸውም ያውቃሉ፡፡

በባህሪያቸው ፀብን አይወዱም፡፡ ከጠላቶቻቸው ጋርም ቢሆን ግጭትን ማስወገድ ይመርጣሉ፡፡ ጠላት ሲቀርባቸው ቶሎ የሚሸሹ ቢሆንም፣ ሆን ብሎ ለሚያጠቃቸውና ለሚተናካላቸው ግን አደገኞች ናቸው፡፡