ክቡር ሚንስተር

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ከውጭ አይፓድ ልኮላቸዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ የተላከላቸው ዕቃ ምን እንደሆነ ስላልገባቸው አማካሪያቸውን አስጠሩት]

 

 • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • በጣም ነው እንጂ የፈለኩህ፡፡
 • ምን ፈልገው ነው?
 • አንድ ነገር እንድትረዳኝ ነው፡፡
 • ብዙ ሥራ ግን አለብኝ፡፡
 • ሥራ የምሰጥህ እኔ መሆኔን ረሳኸው እንዴ?
 • አይ ማለቴ የግል ሥራ እንዳያሠሩኝ ብዬ ነው፡፡
 • የግል ሆነ የጋራ እሱ አይመለከትህም፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • አሁን ና እዚህ አጠገቤ ቁጭ በል፡፡
 • ምን ፈልገው ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምንድን ነው ይኼ?
 • ይኼማ አይፓድ ነው፡፡
 • ምንድን ነው እሱ ደግሞ?
 • ኧረ ብዙ ጥቅም አለው፡፡
 • እኮ ምን?
 • ለምሳሌ በዚህ ኖት መያዝ ይችላሉ፡፡
 • ወረቀትና እስክሪብቶ አለ አይደል እንዴ?
 • አሁን እኮ ኢንቫሮመንት ፍሬንድሊ ሆነው ብዙ ወረቀት መጠቀም ማቆም አለብዎት፡፡
 • ሌላ ምን ጥቅም አለው?
 • ኢንተርኔትም ያስጠቅማል፡፡
 • ይኼማ ያደድብሃል ማለት ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ኢተርኔት ከተጠቀምክ ብዙ አታነብማ፡፡
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር ኢንተርኔት ላይ እኮ ብዙ የሚነበብ ነገር አለ?
 • ምን ፌስቡክና ወሬ አይደለም እንዴ ያለው?
 • ኧረ በዩ ቲዩብ ቪዲዮ ምናምን ማየት ይችላሉ፡፡
 • ቪዲዮም ማየት እችላለሁ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን ጥቁር ፍቅርንና ዛራና ቻንድራን እዛ ቲዩብ ላይ አገኘዋለሁ?
 • እሱን እንኳን የራሳቸው ዌብሳይት ላይ ነው የሚያገኙት፡፡
 • ይህቺ ነገር ጠቃሚ ሳትሆን አልቀረችም፡፡
 • ከፈለጉም ፎቶና ቪዲዮ ማንሳት ይችላሉ፡፡
 • በዚህ?
 • አዎና፡፡
 • በቃ እኔማ ምን እንደማደርግ አውቃለሁ፡፡
 • ምን ሊያደርጉ?
 • በቃ እነዛ ስሜን የሚያጠፉትን ሰዎች በዚህ ቪዲዮ ቀድቻቸው እከሳቸዋለሁ፡፡
 • እነሱ እኮ ስምዎትን እያጠፉ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ሙሰኛ ነው እያሉ ምን እያደረጉኝ ነው?
 • መረጃ እኮ አላቸው፡፡
 • መረጃውን ያቅርቡዋ፡፡
 • ኧረ ይተዉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም እስቲ ክፈተው፡፡
 • ይኸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነው የማበራው?
 • ይኸው አብርቼዋለሁ፡፡
 • ከዛ ምንድን ነው የማደርገው?
 • የፈለጉት ቦታ ሲነኩት ይሠራል፡፡
 • ይኸው ነካሁት፡፡
 • እሱ እኮ ጀርባው ነው፡፡
 • ታዲያ የፈለክበት ቦታ ንካው አላልከኝም እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር አንድ ችግር እንዳለብዎት ተረዳሁ፡፡
 • የምን ችግር?
 • የንቃተ ህሊና!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአፍሪካ አገር ከመጣ ሌላ ሚኒስትር ጋር ምሳ እየበሉ ነው] 

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ ባክህ?
 • አለን አለን፡፡
 • ለሥራ መጥተህ ነው?
 • ኧረ ለመዝናናት ነው የመጣሁት፡፡
 • ለነገሩ ኢትዮጵያ እኮ ለመዝናናት ትመቻለች፡፡
 • እንዴ በደንብ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ የት ነው ያረፍከው?
 • እዚህ እኮ ቤት ገዝቻለሁ፡፡
 • ጥሩ አድርገሃል፡፡
 • ኢንቨስትመንት ውስጥም እኮ ገብቻለሁ፡፡
 • ባለሀብት ሆነሃላ?
 • ያው እንግዲህ ተያይዘነዋል፡፡
 • ለመሆኑ ገንዘቡን ከየት አምጥተህ ነው?
 • ምን እኛ አገር ሙሰኛ ያልሆነ ባለሥልጣን አለ እንዴ?
 • የእኛው ጐራ ነሃ?
 • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለመሆኑ ምን ምን ትሠራለህ?
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር የሎጂስቲክስ ሥራው ውስጥ ታዋቂ የሆነ ድርጅት አለኝ፡፡
 • ምን እኔም እኮ እዛ ዘርፍ ውስጥ አለሁ፣ ግን የአንተን ድርጅት አላውቀውም፡፡
 • ከዛም ባሻገር በሪል ስቴት ዘርፉ እየተመነደገ ያለ ድርጅት አለኝ፡፡
 • አየህ የማላውቀው ለዛ ነዋ፣ የእኔ ድርጅት ተመንድጐ ጨርሷል፡፡
 • ሌላስ ምን ይሠራሉ?
 • አሁን ደግሞ ብራንድ ሆቴሎች አገራችን እየበዙ ስለመጡ፣ ጭስ አልባውን ኢንዱስትሪ ለመቀላቀል አስቤያለሁ፡፡
 • በነገራችን ላይ ክቡር ሚኒስትር…
 • ምንድን ነው?
 • ፕራይቬት ጄት ልገዛ ነው፡፡
 • እኔ እንኳን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው መሽቆልቆል ላይ ስላለ ያሰብኩት ሌላ ነገር ለመግዛት ነው፡፡
 • ምን ሊገዙ ነው?
 • መርከብ!

[የክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ዘመድ ከገጠር ቤታቸው መጥቷል] 

 • እንዴት ነዎት ጋሼ?
 • ምን ልታደርግ መጣህ?
 • ጋሼ ኑሮ በጣም አስቸገረኝ፡፡
 • አሁንም በቃ መጠጣት አላቆምክም አይደል?
 • ወድጄ አይደለም እኮ የምጠጣው ጋሼ፡፡
 • ለምንድን ነው የምትጠጣው?
 • በቃ የገጠር ኑሮ ጠብ የሚል ነገር የለውም፡፡
 • ለምን አትሠራም?
 • ኧረ እኔ ሥራ አስጠልቶኛል፡፡
 • ለመሆኑ ስንት ነው ዕድሜህ?
 • 31 ሞልቶኛል፡፡
 • በዚህ ዕድሜህ ነው ሥራ ያስጠላህ?
 • ምን እንዳማረኝ ያውቃሉ ጋሼ?
 • ምንድን ነው ያማረህ?
 • በቃ ሳልሠራ እንደ እርሶ እንደዚህ የተንፈላሰሰ ቤት ውስጥ መኖር፣ በቃ እሱ ነው ያማረኝ፡፡
 • መቼም የእናትህ አደራ የሚረሳ አይደለም፡፡
 • በቃ ጋሼ ተንቀባርሬ እንድኖር ያድርጉኝ፡፡
 • ስማ አሁን አንድ ሥራ እሰጥሃለሁ፡፡
 • ምንድን ነው ሥራው?
 • አንድ የሚሸጥ መሬት አለ፡፡
 • እሺ ጋሼ፡፡
 • ስለዚህ እኔ የምልክህ ገዢ ጋር ሄደህ በ50 ሚሊዮን ብር የሚሸጥ መሬት አለ ትለዋለህ፡፡
 • መሬት ነው አገር ነው በ50 ሚሊዮን ብር የሚሸጠው?
 • አንድ ቪላ ቤት ነው፡፡
 • ብሩ በዛ ብዬ ነው፡፡
 • ያልተጠየከውን አትቀባጥር፡፡
 • ይቅርታ ጋሼ፡፡
 • ከዛም መሬቱን የሚሸጠው ሰውዬ ጋ ሄደህ ቦታውን በ50 ሚሊዮን ብር የሚገዛ ሰው አግኝቼልሃለሁ ትለዋለህ፡፡
 • እሺ ጋሼ፡፡
 • ከዛ በቃ አንድ ሚሊዮን ብር የድለላ ታገኛለህ፡፡
 • ወይ ግሩም፡፡
 • ገብቶሃል?
 • ምንም አልገባኝም፡፡
 • መጀመሪያ ገዢውን ታገኛለህ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ከዛም በ50 ሚሊዮን ብር የሚሸጥ…
 • አገር አለ እለዋለሁ፡፡
 • መሬት ነው አገር አይደለም የሚሸጠው፡፡
 • እሺ ይቅርታ፡፡
 • ከዛ ከሻጭ ጋር አገናኝተህ አንድ ሚሊዮን ብርህን ትቀበላለህ፡፡
 • እሺ ጋሼ አመሰግናለሁ፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ዘመድ የመሬት ሽያጭ ኮሚሽኑን ከተቀበለ ከአራት ወራት በኋላ ቤታቸው መጣ] 

 • አሁን ደግሞ ምን ፈለክ?
 • ጋሼ አንድ ችግር ገጥሞኝ ነው፡፡
 • የድለላውን ብር አልተቀበልክም እንዴ?
 • ኧረ ተቀብያለሁ፡፡
 • እኮ የምን ችግር ነው የምታወራው ታዲያ?
 • ብሩ ጠፋብኝ፡፡
 • ምን ሆኖ?
 • በቃ የከተማ ሰው አንዱ አበድረኝ ሲለኝ፣ አንዱ ጋብዘኝ ሲለኝ ብሯን አሟጠጥኳት፡፡
 • አንድ ሚሊዮኑን በአራት ወራት ውስጥ ጨረስከው?
 • ኧረ ያጠፋሁትማ በሁለት ወራት ነው፡፡
 • ታዲያ የት ነበርክ እስካሁን?
 • ጋሼ የእርሶን ፊት የማይበት አቅም አልነበረኝምና ለዛ ነው የጠፋሁት፡፡
 • ለማንኛውም አንድ ስልክ ልደውል፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ መኪና አስመጪ ጋ ደወሉ] 

 • ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በቃ አንተ የፈለከውን ካገኘህ በኋላ ጠፋህ አይደል?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ምን እጠፋለሁ? በጣም ስፈልግዎት ነበር፡፡
 • ያን ሁሉ ውለታ አድርጌልህ በዛው ትጠፋለህ?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ምን ላድርግልዎት?
 • አምስት ሲኖ ትራኮች ፈልጌ ነበር፡፡
 • ዛሬውኑ በስሞት አዘዋውርልዎታለሁ፡፡
 • በእኔ ስም አይሆንም በሌላ ስም ነው የሚሆነው፡፡
 • በማን ስም ይደረግ?

[ክቡር ሚኒስትሩ አስመጪው ስልኩን እንዲይዘው አድርገው፣ ዘመዳቸውን ማናገር ጀመሩ] 

 • ስምህ ማን ነበር?
 • ድፋባቸው ብላባቸው፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ስልኩ ተመለሱ] 

 • ድፋባቸው ብላባቸው፡፡
 • ማን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ድፋባቸው ብላባቸው፡፡
 • ስሙ ግን ፀረ ልማታዊ ይመስላል፡፡
 • በቃ በዚህ ስም አድርጋቸው፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ዘመድ መኪኖቹን ከወሰደ በኋላ ድጋሚ ከስሮ መጣ] 

 • መቼም አሁን የመጣኸው ልትጋብዘኝ ነው?
 • አይ ጋሼ አንድ ነገር ገጥሞኝ ነው፡፡
 • መኪኖቹን አልወሰድክም እንዴ?
 • ኧረ ወስጄ ሥራም ጀምረዋል፡፡
 • ታዲያ ሥራ ከጀመሩ ምን ትፈልጋለህ?
 • ከዛ በኋላ መቼም የከተማ ሰው አንድ ክፉ ነገር አስተማረኝ፡፡
 • ምን ተማርክ?
 • ቁማር ተምሬ ጋሼ በቃ መኪኖቹን ተበላሁ፡፡
 • ምን?
 • አዎን ጋሼ በካርታ መኪኖቹን ተበላሁ፡፡
 • የሠራህበት ገንዘብስ?
 • መኪኖቹን ለማስመለስ ስጫወት እሱንም ተበላሁ፡፡
 • ወይ ጣጣ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው] 

 • ምን ሆነህ ነው የተናደድክ ትመስላለህ?
 • ምን ባክሽ አቃጥሎኝ ነዋ፡፡
 • እሳት ነው?
 • ኧረ ይኼ ድፋባቸው ነው እንጂ፡፡
 • ምን ደፋብህ?
 • ይኸው ሥራ የለኝም ብሎ በድለላ ያሰጠሁትን አንድ ሚሊዮን ብር በሁለት ወራት ውስጥ አጠፋው፡፡
 • ምን ችግር አለው አንተ አንድ ሚሊዮን ብር በወር አይደል እንዴ የምታጠፋው?
 • እኔ ታዲያ መቶ ሚሊዮን ኖሮኝ እኮ ነው አንድ ሚሊዮን የማጠፋው፣ እርሱ እንዴት አንድ ሚሊዮን ኖሮት አንዷን ያጠፋታል?
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • ከዛ ደግሞ አምስት ሲኖ ትራክ ሰጥቼው እነርሱንም በቁማር ተበላ፡፡
 • አንተ ዋነኛው የከተማው ቁማርተኛ አይደለህ እንዴ?
 • ቢሆንም እኔ ዋናዬን ይዤ ነው የምጫወተው፡፡
 • ችግሩ እኮ በአንድ ምሽት ሚሊየነሮችን መፍጠርህ ነው፡፡
 • ይኼማ የዕድገታችን መገለጫ ነው፡፡
 • የተገኘውም ገንዘብ እኮ በአንድ ምሽት እየጠፋ ነው፡፡
 • እሱ እኮ ነው ግራ ያጋባኝ፡፡
 • እሱማ የምን መገለጫ እንደሆነ እኔ ገብቶኛል፡፡
 • የምን መገለጫ ነው?
 • የጥፋታችሁ!

Leave a comment

Filtered HTML

 • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
 • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
 • Lines and paragraphs break automatically.
 • Each email address will be obfuscated in a human readable fashion or, if JavaScript is enabled, replaced with a spam resistent clickable link. Email addresses will get the default web form unless specified. If replacement text (a persons name) is required a webform is also required. Separate each part with the "|" pipe symbol. Replace spaces in names with "_".

Plain text

 • No HTML tags allowed.
 • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
 • Lines and paragraphs break automatically.