ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ የተለያዩ የሹም ሽር ወሬዎችን ሰምተው ተደናግጠዋል፡፡ በሰሙት ወሬም ተደናግጠው አማካሪያቸውን ቢሯቸው ለማነጋገር አስጠሩት]
- ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ሥራ ይዘሃል እንዴ?
- ኧረ አልያዝኩም፡፡
- ምን አዲስ ነገር አለ?
- ስለምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- በአጠቃላይ ከተማ ውስጥ ምን ይወራል?
- አሁን እኮ ስለአንድ ነገር ነው የሚወራው፡፡
- እ…
- ምነው ደነገጡ?
- ኧረ አልደነገጥኩም፡፡
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለምንድነው የሚወራው አልከኝ?
- ስለምርጫ ነዋ፡፡
- እፎይ፡፡
- ምነው እፎይ አሉ?
- ያው ምርጫው የታወቀ ነው ብዬ ነዋ፡፡
- እንዴት?
- ምን ነካህ?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- አሁን ለዚህ ሕዝብ ከእኛ በላይ የሚያስብ ይኖራል ብለህ ነው?
- እንዴታ ክቡር ሚኒስትር?
- ሥራችን እኮ ይናገራል፡፡
- ከሥራችንም ያለፉት አራት ዓመታት ሥራ ይበቃል፡፡
- ይህን ነው እኮ የምልህ?
- ለነገሩ እኔ ትንሽ ፈርቼ ነው፡፡
- ምንድነው የሚያስፈራህ?
- መቼም ውድድር እንደ መሆኑ መጠን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፈርቻቸው ነው፡፡
- ምን ነካህ?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እንዲያው የፈለገው ውድድር ቢሆን አሁን የእኛ ሥራ ከእነሱ ጋር ለውድድር የሚቀርብ ነው?
- ለነገሩ እውነትዎን ነው፡፡
- ባቡር ብትል፣ ቤት ብትል፣ ግድብ ብትል ኧረ ምኑ ቅጡ?
- እሱንማ መቼ ዘነጋሁት፤ ብቻ ቢሆንም…
- የሕዝቡ ልብ ከእኛ ጋር ነው፡፡
- እ…
- እውነቴን ነው የምልህ፡፡
- ኧረ የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም፡፡
- እንዴት?
- በምርጫ 97 እኮ ሕዝቡ ከእኛ ጋር ነው ብለን ነበር፡፡
- እ…
- እሱን አስቤ ነው፡፡
- ያ ሌላ ይኼ ሌላ፡፡
- እንዴት?
- አሁን ግድብ አለ፣ ባቡር አለ፣ ቤት አለ፡፡
- ለነገሩ ብዙ ነገር አለ፡፡
- ስለዚህ ብዙ አትሸበር፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ሌላ ምን ወሬ አለ?
- ሌላ ምን አለ ብለው ነው?
- ምንም አልሰማህም?
- አንድ የሰማሁት ወሬ አለ፡፡
- ምን?
- አንዳንድ ሰዎች ከሥልጣን እየተወገዱ ነው፡፡
- እ…
- ሌሎችም የሚባረሩ ሳይኖሩ አይቀርም፡፡
- ወይ ጣጣ፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ስለእኔ ምን ሰምተሃል?
- ምንም?
- እንዲያው በቀጣዩ ካቢኔ ውስጥ የምኖር ይመስልሃል?
- ማን እርስዎ?
- አዎና፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር? ያለእርስዎ ይህቺ አገር ምንድናት?
- እ…
- ማሰብዎት ራሱ ያስገርማል፡፡
- ያው መጠርጠር አይከፋም ብዬ ነው፡፡
- ስንት ሙሰኛ፣ ስንት ደካማ እያለ እርስዎማ ሊባረሩ አይችሉም፡፡
- እንዲያው ፈርቼ ነው፡፡
- ኧረ አያስቡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሺ በቃ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሚኒስትር ጓደኛቸው ዘንድ ደወሉ]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ እባክህ?
- ደህና ነኝ፡፡
- ምን አዲስ ነገር አለ?
- ኧረ ብዙም አዲስ ነገር የለም፡፡
- ካቢኔ አካባቢ ወሬ ሰምቼ፡፡
- የምን ወሬ?
- ማለቴ ስለቀጣዩ ካቢኔ ምርጫ፡፡
- የምን ምርጫ ነው የሚያወሩት?
- እኔ ግን በሚቀጥለው ካቢኔ ውስጥ እኖራለሁ?
- ክቡር ሚኒስትር ምን እያሉ ነው?
- አንተ ቅርብ ሰው ስለሆንክ ንገረኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከፊታችን እኮ ብዙ ነገር አለ፡፡
- አውቃለሁ፡፡
- አሁን ጊዜው ስለምርጫው የምናስብበት እንጂ የሹም ሽር ጊዜ አይደለም፡፡
- ይኼው ሰዎች ከኃላፊነታቸው እየተነሱ አይደል እንዴ?
- ድካም ያለባቸው ሰዎችማ አሁንም መነሳታቸው አይቀርም፡፡
- እኮ እኔን ታነሱኛላችሁ?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር እኔ ምንም አላውቅም፡፡
- እሺ ቻው፡፡
- ቻው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሚኒስትር ጋ ደወሉ]
- ሰምተሃል ወሬውን?
- የቱን ክቡር ሚኒስትር?
- ሰዎች እየተሻሩ ነው እኮ አሉ፡፡
- የቀጣይ የካቢኔ አባላት ጉዳይም እየተወራ ነው አሉ፡፡
- ስለእኛ ምን ሰማህ?
- እያወቁት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በቃ ተጠቅመው ሊጥሉን ነው አይደል?
- እ…
- ለእኛ ይኼ ነው የሚገባን?
- መውደቂያችንን ማመቻቸት ነው የሚጠቅመን፡፡
- በል ቻው፡፡
- ቻው፡፡
[ክቡር ሚኒስትር ቤታቸው ከባለቤታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ለእኔ ይኼ ነው የሚገባው?
- ስለምንድነው የምታወራው?
- በቃ ሊቀር ነው፡፡
- ምኑ ነው የሚቀረው?
- ተንቀባሮ መኖር ሊቀር ነው፡፡
- ምንድነው የምታወራው?
- ሊያባርሩኝ ነው፡፡
- ምን?
- አዎን፡፡
- ደብዳቤ ሰጡህ?
- ደብዳቤው እንኳን ገና ነው፡፡
- ታዲያ በምን አወቅህ?
- ቀልቤ ነገረኝ፡፡
- ተው ተጠንቀቅ እያልኩ ነበር፡፡
- እኔ እኮ የሚገርመኝ አንድ ነገር ነው፡፡
- ምንድነው የሚገርምህ?
- እኔ በሕዝብ የተወደድኩ ነኝ፡፡
- ብትሆንስ?
- እንዴት እባረራለሁ?
- መቼ ተባረርክ?
- ሊያባርሩኝ መሆኑ ገብቶኛል፡፡
- ብቻ መውደቂያህን አዘጋጅ፡፡
- አታስቢ፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ የሆነ አንድ ነጋዴ ደወለላቸው]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- ጠፉ እኮ ክቡር ሚኒስትር?
- ያው የእኛ ነገር እያወቅከው?
- ሥራ እንዴት ነው?
- አሁንስ ደከመኝ፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- በቃ ዕረፍት ጠፋ፡፡
- ዕረፍትማ እንደሌለዎት አውቃለሁ፡፡
- ቀን የለ ማታ፣ ቅዳሜ የለ እሑድ የለ፣ ታከተኝ፡፡
- አይዞዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በእውነት ደከመኝ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ ይህቺ አገር ያለ እርስዎ ማን አላት?
- ማረፍ ነው የምፈልገው፡፡
- እርስዎ ካረፉማ አገሪቷም አብራ ታርፋለች፡፡
- መቼም አልሞት እንግዲህ?
- ክቡር ሚኒስትር…
- አቤት፡፡
- ማረፍ ካሰቡ አንድ ነገር ቃል ይግቡልኝ፡፡
- ምን?
- ወደ እኔ እንዲመጡ እፈልጋለሁ፡፡
- እ…
- እንደ እርስዎ ያለ ሰው ከእጄ እንዲወጣ አልፈልግም፡፡
- እስቲ አስብበታለሁ፡፡
- ታዲያ ምን አሰቡ?
- ምንም አላውቅም፡፡
- አምባሳደር ሊሆኑ ነው?
- ያደርጉኛል ብለህ ነው?
- ለምን አይሆኑም?
- ብቃት ይጠይቃላ፡፡
- ሌሎቹ የሚሾሙት በብቃት ነው ብለው ነው?
- እ…
- ያው እንደ ጡረታ ነገር ነው እኮ፡፡
- እስቲ ተወኝ፡፡
- ካልሆነም አንዱ የውጭ ድርጅት ውስጥ የኢትዮጵያ ተወካይ ያድርጉዎት፡፡
- አግኝቼው ነው?
- ካልሆነ ግን ያስቡበት፡፡
- ምኑን?
- እኔ ጋ መምጣቱን፡፡
- አስብበታለሁ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ማታ ከባለቤታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ብዬሽ ነበር፡፡
- ምኑን?
- ሕዝቡ በጣም ነው የሚወደኝ፡፡
- ምን ተገኘ?
- ሁሉም ነገር ተገኘ፡፡
- ምንድነው ያገኘኸው?
- በፊትም ቢሆን እኔ አውቀዋለሁ፡፡
- ምኑን ነው የምታውቀው?
- ሕዝቡ እንደሚወደኝ፡፡
- ተሾምክ እንዴ?
- አዎና፡፡
- በማን? በመንግሥት?
- የለም በባለሀብቱ!