ክቡር ሚኒስትር

[የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ቀን በመሆኑ ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ከባለቤታቸው ጋር ናቸው]
- እንዴት አምሮብሻል እባክሽ?
- እኔ የአንተ ሚስት አሁንም እኮ ቆንጆ ነኝ፡፡
- የሐበሻ ቀሚስ ስትለብሺ ደግሞ ውበትሽ በእጅጉ ጨመረ፡፡
- ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ ሲባል አልሰማህም?
- ወዴት ልትሄጂ ነው ታዲያ?
- ታቦት ልሸኝ ነዋ፡፡
- እንዲህ ውብ ሆነሽ?
- ምነው ፈራህ እንዴ?
- አንዱ ሎሚ እንዳይወረውርብሽ ብዬ ነው፡፡
- ሎሚ እኮ ድሮ ቀረ፡፡
- ታዲያ ምንድን ነው የሚወረወረው?
- የቪትዝ ቁልፍ ነዋ፡፡
- የጥምቀት ስጦታ በእጅጉ ተመንድጓላ?
- እንደ አገራችን ዕድገት በ11 በመቶ ብቻ ያደገ መስሎህ ነበር?
- እስቲ አሽሙርሽን ተይው፡፡
- ተነስተህ ታቦት እንሸኝ እንጂ?
- እኔ እባክሽ ከቤት አልወጣም፡፡
- ምን ታደርጋለህ?
- ቁጭ ብዬ ዜና እከታተላለሁ፡፡
- እሺ ቢያንስ ነጭ ልብስ እንኳን ልበስ፡፡
- አሁን ነጭ ልብስ መልበስ አይቻልም፡፡
- ለጥምቀት ካልለበሰ መቼ ልትለብስ ነው ታዲያ?
- እኔ ነጭ ልብስ የምለብሰው…
- መቼ ነው?
- የባቡር መንገዳችን ሲያልቅ፡፡
- እ…
- የህዳሴ ግድባችን ሲጠናቀቅ፡፡
- እሺ፡፡
- ቀጣዩን ምርጫ ስናሸንፍ፡፡
- ሌላስ?
- መልካም አስተዳደር በአገሪቱ ሲሰፍን፡፡
- እሺ፡፡
- ድህነት ከታሪካችን ሲወገድ፡፡
- ወገኛ ነህ፡፡
- ያኔ ነው እኔ ነጭ ልብስ የምለብሰው፡፡
- ምኞትህን ያሳካልህ፡፡
- ይህ ምኞት ሳይሆን ህልሜ ነው፡፡
- እሺ፣ ህልምህ እውን ይሁንልህ፡፡
- አሜን፡፡
- ግን ጠንክሮ መሥራቱን አትዘንጋው፡፡
- እንግዲህ እንደምታይኝ ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- እንቅልፍ እኮ የለኝም፡፡
- እሱማ እንቅልፍ እንቢ ብሎህ ነው፡፡
- እንቅልፍ እንቢ ያለኝ በአገሬ ምክንያት ነው፡፡
- እንዴት?
- በዚህ ጋ ግድቡ፣ በዚህ ጋ ባቡሩ እያሉ እንቅልፍ ከየት ይመጣል?
- እኔ የምለው አንተ ባቡር ሐዲድ ላይ አትተኛ?
- እ…
- ወይስ ሳላውቀው ግድቡ ላይ ማደር ጀምረሃል?
- ምን እያልሽ ነው?
- አይ ባቡርና ግድብ ስትለኝ ከእንቅልፍ ጋር ምን አገናኘው ብዬ ነው?
- እንዴት አይገናኝ?
- እኮ አስረዳኝ?
- እነዚህ ፕሮጀክቶች እኮ ሕዝቡ በጉጉት የሚጠብቃቸው ናቸው፡፡
- እሱንማ አውቃለሁ፡፡
- ታዲያ ካወቅሽ ለምን ትጠይቂኛለሽ?
- እኔ ያልኩት ከአንተ እንቅልፍ ጋር ምን አገናኘው?
- ፕሮጀክቶቹ ሳያልቁ መተኛት አልችልም፡፡
- ለጥሩ እንቅልፍ መድኃኒቱ ጥሩ ህሊና ነው እባክህ?
- ምን እያልሽ ነው?
- ምን አልኩ?
- ጥሩ ህሊና የለህም እያልሽኝ ነው?
- አልወጣኝም፡፡
- በይ እስቲ ታቦትሽን ሸኝተሽ ነይ፡፡
- በል ቻው፡፡
- ቻው፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ የሆኑ ሌላ ሚኒስትር ደወሉላቸው]
- ጤና ይስጥልኝ፡፡
- እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንኳን አደረሰህ፡፡
- በዓሉ እንዴት ነው፡፡
- ልማታዊ በዓል ነው፡፡
- ልማታዊ ሲሉኝ?
- ያው ቤቴ ሆኜ እየተዝናናሁ ነኝ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር ምን ነካዎት?
- ምን አጠፋሁ?
- አሁን እኮ የምንዝናናበት ጊዜ አይደለም፡፡
- ዛሬ የዕረፍት ቀን ነው እኮ?
- ቢሆንም ለእኛ የዕረፍታችን ቀን አይደለም፡፡
- እሱማ ልክ ነህ፡፡
- ከፊታችን እኮ እጅግ ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎብናል፡፡
- እሱማ እኔም ደፋ ቀና እያልኩ ነው፡፡
- የጂቲፒ ሁለት ሥራ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ተብሏል፡፡
- መቼ?
- አሁን የደወልኩት እኮ እርስዎ የሚመሩትን ኮሚቴ ምክረ ሐሳብ ከነገወዲያ እንዲያስገቡ ልነግርዎት ነው፡፡
- ምን?
- አዎ ጂቲፒ ሁለት በአፋጣኝ መጠናቀቅ አለበት ተብሏል፡፡
- እኔ እኮ የሚገርመኝ በየኮሪደሩ እየወሰናችሁ እኛን ለምን ታስጨንቁናላችሁ?
- ክቡር ሚኒስትር ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው፡፡
- ከላይ ከመጣማ ምን ይደረጋል?
- ስለዚህ በአፋጣኝ ተጠናቆ ይድረስ፡፡
- በቃ እሺ እሞክራለሁ፡፡
- ለሙከራ ጊዜ የለንም፡፡
- እ…
- ከነገወዲያ እንገናኝ፡፡
- እሺ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው ዘንድ ደወሉ]
- እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንኳን አደረሰህ፤ የምን ጫጫታ ነው የሚሰማኝ?
- ታቦት እየሸኘሁ ነው፡፡
- ምን አልከኝ?
- ታቦት እየሸኘሁ ነኝ፡፡
- ታቦት?
- አዎ ምነው?
- የደላው ሙቅ ያኝካል አሉ፡፡
- ምን አጠፋሁ ክቡር ሚኒስትር?
- ስንት ሥራ ተከምሮብን አንተ ትዝናናለህ?
- የምን ሥራ?
- የጂቲፒ ሁለት ፕላን በአፋጣኝ ይፈለጋል፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው፡፡
- የአገር ፕላን እኮ እንዲህ በቀላሉ አይሠራም፡፡
- ምንም አማራጭ የለንም፡፡ ፕላኑ ከነገወዲያ ይፈለጋል፡፡
- በቃ ቢሮ እንገናኝ፡፡
- እሺ በአፋጣኝ ና፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው እየጠበቃቸው ነው]
- ቆየሁብህ አይደል?
- አይ መንገዱ ሊዘጋጋ እንደሚችል ገምቼያለሁ፡፡
- አንተ እንዴት ቶሎ ደረስክ?
- እዚሁ አካባቢ ስለነበርኩ ነው፡፡
- በል ማስታወሻ ያዝ፡፡
- የምን ማስታወሻ?
- የፕላኑን ዋና ሐሳቦች ልንገርሃ?
- ሁሉም እዚህ ፍላሽ ዲስክ ውስጥ አለልዎት፡፡
- የአገር ፕላን የሚያህል ነገር እዚች ፍላሽ ዲስክ ውስጥ?
- 64 ጂቢ ፍላሽ ዲስክ ነው፡፡
- አንተ እኮ ጀግና ነህ፡፡
- ራምዎት ግን 32 ኬቢ ነው ልበል?
- ምን አልከኝ?
- ሁሉም ነገር እዚህ ውስጥ አለልዎት፡፡
- ስለዚህ እኔ ማየት አይጠበቅብኝም?
- አያስቡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በቃ አመሰግናለሁ፤ ነገ እንገናኝ፡፡
- መልካም በዓል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ሲመለሱ ከባለቤታቸው ጋር ተገናኙ]
- ሸኝተሽ መጣሽ?
- በጣም ደስ የሚል በዓል ነበር፡፡
- እንዴት?
- በቃ ኢትዮጵያ በባህል ሀብታም አገር መሆኗን የሚያሳይ በዓል ነው፡፡
- እኔ የምልሽ?
- አቤት?
- በግ ገዝተሽ ነው?
- ኧረ አልገዛሁም፡፡
- ታዲያ ግቢው ውስጥ ያለው በግ ማን አምጥቶት ነው?
- አንድ የአንተ ወዳጅ ነው ያመጣው፡፡
- እውነት?
- ብቻ ተጠንቀቅ፡፡
- ከምኑ ነው የምጠነቀቀው?
- ከእንዲህ ዓይነት ስጦታ፡፡
- ምን ላድርግ እኔ?
- እንዴት ምን ላድርግ ስትል?
- ሰው ይወደኛል፡፡
- እ…
- አገሬን እኮ በቅንነት የማገለግል ሰው ስለሆንኩ ነው፡፡
- እሱ ጥሩ ነው፡፡
- እንቅልፍ አጥቼ ሌት ተቀን ስለምሠራ ነው፡፡
- ጥሩ፡፡
- ታዲያ ሰው ባይወደኝ አይገርምሽም?
- ቢሆንም?
- ይኸው ጂቲፒ ሁለት እየቀረፅን ነው፡፡
- እኔ የምልህ ሰው የሚለውን ሰምተሃል ግን?
- ምን እየተባለ ነው?
- የምርጫው ውጤት ተረጋገጠ ወይ እያለ ነው፡፡
- እንዴት?
- ከአሁኑ ጂቲፒ ሁለት የምትቀርፁት ምርጫውን አረጋግጣችሁ ነው እየተባለ ነው፡፡
- ያ ሌላ ይኼ ሌላ፡፡
- እንዴት?
- ይህ እኮ የአገር ጉዳይ ነው፡፡
- ያኛውስ?
- እሱ የፓርቲ ጉዳይ ነው፡፡
- አሁን መጀመሪያ ያነሳሁትን ሐሳብ አታረሳሳኝ፡፡
- የትኛውን?
- የስጦታውን ጉዳይ፡፡
- እኮ ምን ላድርግ?
- ስጦታ አትቀበል?
- አሁን በግ ምን አላት?
- በኋላ ለአሽሟጣጭ እንዳትዳርገኝ፡፡
- እቺ እኮ ትንሽ ስጦታ ናት፡፡
- የስጦታ ትንሽ የለውም ሲባል አልሰማህም?
- ታዲያ ስጦታ ሲመጣ እንቢ ይባላል?
- አዎ?
- ለምን?
- ከስጦታው በስተጀርባ ያለው ፍላጎት ኃፍረት ውስጥ ይከታል! ያዋርዳል!