ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ገብተው የተለያዩ የዓለማችንን ዜናዎች እየተከታተሉ ነው፡፡ ቢሯቸው ያለው አዲሱ ቴሌቪዥን እጅጉን ስለመሰጣቸው ከቴሌቪዥኑ ላይ ዓይናቸውን መንቀል አልቻሉም፡፡ አማካሪያቸው ለአንድ ጉዳይ ፈልጓቸው ቢሯቸው ገባ]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር?
- ምን አዲስ ነገር አለ?
- ለአንድ ጉዳይ ፈልጌዎት ነበር፡፡
- የምን ጉዳይ ነበር?
- ስለጨረታ ላወራዎት ፈልጌ ነበር፡፡
- የምን ጨረታ ነው?
- በዚህ ወር ማውጣት ስላለብን ትልቁ ጨረታ ነዋ፡፡
- አሁን አልችልም፡፡
- ለምን?
- ምን አልከኝ?
- አይ ሥራ ላይ ነዎት ወይ ነው ያልኩት?
- የሰሞኑን አስገራሚ ዜና እየተመለከትኩ ነኝ፡፡
- ምንድነው እሱ?
- የሻርሊ ኤቢዶን ጉዳይ፡፡
- ሻርሊ ኮሜዲያኑን ነው የሚሉኝ?
- ምን ይላል ይኼ?
- ምነው?
- መጽሔቱን ነው እንጂ የምልህ፡፡
- ኦ የፈረንሳይ ጥቃቱን ነው የሚሉኝ?
- በሚገባ፡፡
- በጣም አሳዛኝ ነው፡፡
- ይህን ጥቃት አጥብቀን ልንቃወም ይገባል፡፡
- ሽብርንማ መቼም ቢሆን አጥብቀን ልንቃወም ይገባል፡፡
- ይህ ጥቃት ከሽብርም ያለፈ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት?
- ሐሳብን በነፃት የመግለጽ መብትንም ተጋፍቷላ፡፡
- ጥቃቱ ድርብ ነው ማለት ይቻላል፡፡
- ምን እየተባለ ነው ታዲያ?
- የዓለም መሪዎች ከፈረንሳይ ጐን መቆማቸውን እያሳዩ ነው፡፡
- እኛም ከጐናቸው መሆናችንን ማሳየት አለብን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔማ በግሌ ለፈረንሳይ አምባሳደር ስልክ ደውያለሁ፡፡
- ጥሩ አደረጉ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ግን…
- ግን ምን?
- የናይጄሪያ አምባሳደር ዘንድሮስ ደወሉ ወይ ብዬ ነው?
- ለምንድነው እዚያ ደግሞ የምደውለው?
- ሰሞኑን እኮ ከ2,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ብዬ ነው፡፡
- በዚህ ዓይነትማ ሁሉም አምባሳደሮች ጋ ስደውል ልውል ነው፡፡
- እንዴት?
- ሁሉም ጋ ነዋ ጥቃት ያለው፡፡
- በነገራችን ላይ አዲሱ ቴሌቪዥንዎ ያምራል፡፡
- ሌላ ችግር የሆነብኝ ይኼ ነው፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ዜና ስትመለከት እዚያው ያለህ ነው የሚመስልህ እኮ፡፡
- እጅግ ግዙፍ ቲቪ ነው፡፡
- የድምፅና የምሥል ጥራቱ ደግሞ አይጣል ነው፡፡
- ለመሆኑ ዋጋው ስንት ነው?
- ሁለት መቶ ሺሕ ብር አካባቢ ነው፡፡
- እ…
- ያንሰዋል አይደል?
- በጣም ያንስዎታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እውነትህን ነው፡፡ እኔማ ሌላም ልጨምር ነው፡፡
- ሌላ?
- አዎ ለቤቴም አንድ ሌላ እፈልጋለሁ፡፡
- አንድ ፕሮጀክት እኮ ይሠራል፡፡
- ፕሮጀክተር ነው ያልከኝ?
- እ….
- ለነገሩ እውነትህን ነው ፕሮጀክተርም ብገዛ ከጓደኞቼ ጋር ኳስ ማየት እንችላለን፡፡
- ኧረ እንደሱ አይደለም ያልኩት፡፡
- ምን አልክ ታዲያ?
- ዋጋው እጅግ ውድ ነው፡፡
- እ…
- ቴሌቪዥንዎ ምን ሆነ?
- ምንም፡፡
- ታዲያ ለምን አዲስ መግዛት አሰቡ ብዬ ነው፡፡
- ከዘመኑ ጋር መሄድ አለብህ፡፡
- እ…
- ለሕዝቡ እኮ በሁሉም ነገር ነው አርዓያ መሆን ያለብህ፡፡
- እንዴት?
- አዲስ ነገር በማስተዋወቅም አርዓያ መሆን አለብህ፡፡
- እሺ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ወዲያው ባለቤታቸው ጋ ደወሉ]
- ደህና ዋልክ?
- ደህና፡፡
- እሺ ምን ልታዘዝ?
- አንድ ነገር አጣሪ እስቲ?
- ምን ላጣራ?
- የቲቪ ዋጋ፡፡
- ስንት ኢንች?
- በቃ የመጨረሻ ትልቁን፡፡
- ልታንበሻብሸን ነው?
- ለቤትም ያስፈልገናል ብዬ ነው፡፡
- በቃ እሺ፡፡
- ቻው፡፡
- ቻው፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
- ክቡር ሚኒስትር እንግዶች አሉ፡፡
- የምን እንግዳ?
- ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡
- የምን ተቃዋሚ?
- ማለቴ ከተቃዋሚ ፓርቲ ነው የመጡት፡፡
- ምን ፈልገው ነው?
- እርስዎን በአስቸኳይ ሊያናግርዎት ይፈልጋሉ፡፡
- እኮ ስለምን?
- ጉዳዩን አልነገሩኝም፡፡
- ወይ ጣጣ፤ እሺ አስገቢያቸው፡፡
[እንግዶቹ ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገቡ]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጤና ይስጥልኝ፡፡
- ምን እየተደረገ ነው?
- ምን ተደረገ ደግሞ?
- ክቡር ሚኒስትር እንግልት እያደረሱብን ነው፡፡
- እነማን?
- የእናንተው ካድሬዎች ናቸዋ፡፡
- ምን አደረጉ?
- አባሎቻችን ከፍተኛ ማስፈራሪያ እየደረሳቸው ነው፡፡
- እሺ፡፡
- ከከተማ ውጪ ያሉ አባሎቻችንም እየታሰሩ ነው፡፡
- ምን?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር ከፍተኛ ጫና እየደረሰብን ነው፡፡
- ይኼማ ሊሆን አይችልም፡፡
- እንዴት?
- እኛ እኮ የታገልነው ለዚህ አይደለም፡፡
- ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እኛ የታገልነው በአገሪቱ ዲሞክራሲ ለማስፈን ነው፡፡
- እሱንማ ሁሌም ትላላችሁ፡፡
- የስንቱ ሕይወት መስዋዕት የተደረገው ለዚሁ ዓላማ ነው፡፡
- ለየቱ ዓላማ?
- የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ነዋ፡፡
- የእናንተ ካድሬዎች ግን የሚሠሩት ለሌላ ዓላማ ነው የሚመስለው፡፡
- ለምን ዓላማ?
- የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማጥበብ፡፡
- ይህ በአጠቃላይ ተቀባይነት የለውም፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እንዲህ የሚያደርጉትን አሁኑኑ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው እናደርጋለን፡፡
- እኛም የመጣነው ለዚሁ ነው፡፡
- ምንም ቢሆን አንድ ነገር መረሳት የለበትም፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ብትቃወሙም እናንተም እኮ ዜጐች ናችሁ፡፡
- እግዚአብሔር ይስጥዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እናንተም ብትሆኑ በራሳችሁ መንገድ አገሪቷን ለማቃናት ነው የምትደክሙት፡፡
- ምናለ ሁሉም እንደርስዎ ቢያስብ?
- ስለዚህ አታስቡ፡፡
- እናመሰግናለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ጠሩት]
- ምን ልታዘዝ ክቡር ሚኒስትር?
- ተቃዋሚዎች መጥተው ነበር፡፡
- ምን አሉ?
- ሮሮዋቸውን አሰምተው ሄዱ፡፡
- እነሱ ልማዳቸው ነው፡፡
- እሱንማ አውቃለሁ አዲስ ነገር ካለ ብዬ ነው፡፡
- ምንም የለም፡፡ በነገራችን ላይ አንድ ነገር ሳስብ ነበር፡፡
- ምን አሰብክ?
- ለምን መጽሐፍ አይጽፉም ክቡር ሚኒስትር?
- መጻፌማ አይቀርም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይህን ጉዳይ በደንብ ያስቡበት፡፡
- በየቀኑ ማታ ማታ እኮ ሁሌም ማስታወሻ እይዛለሁ፡፡
- እሱን ነው የምልዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ የምጽፈው መጽሐፍ እኮ እንደ ዲክሽነሪ አርባና ሃምሳ ጊዜ ነው የሚታተመው፡፡
- ለዚያ እኮ ነው ጻፉ የምልዎት፤ በዚያ ላይ ብዙ ታሪክ ነው የሚያውቁት፡፡
- እሱስ ልክ ነህ፡፡
- አሁን ደግሞ ሁሉም እየጻፈ ነው፡፡
- አንድ ቀን አይቀርም፡፡
- ኧረ ሳይቀደሙ መቅደም ነው፡፡
- እስቲ አስብበታለሁ፡፡
- በዚያ ላይ ገቢውም ቀላል አይደለም፡፡ የቅድሙን ነገርም መግዛት ያስችልዎታል፡፡
- ምኑን?
- ቴሌቪዥኑን ነዋ፡፡
- አሽሙር መሆኑ ነው?
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የካድሬዎች አስተባባሪ ጋር ደወሉ]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ባክህ?
- ይኸው ተያይዘነዋል፡፡
- ምኑን?
- የምርጫውን እንቅስቃሴ ነዋ፡፡
- ምን አዲስ ነገር አለ?
- በቃ ተቃዋሚዎችን ለማሸነፍ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ተያይዘነዋል፡፡
- እሱንማ ሰማሁ፡፡
- እናንተ ጋ መጥተው ነበር እንዴ?
- አዎ፣ በጥበብ ይቀጥል፡፡
- ለሰከንድ አንዘናጋም፡፡ የባለፈው ውጤታችን ይደገማል፡፡
- ይህ ነው የሚፈለገው፡፡
- እኔማ እየተወራረድኩ ነው፡፡
- ምን ብለህ?
- እንደፍነዋለን ብዬ!