ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቤት ሊወጡ ሲሉ ሚስታቸው አገኙዋቸው]

 • ጊዜው እንደደረሰ ታውቃለህ አይደል?
 • ዕቁባችን ሊወጣ ነው እንዴ?
 • ወይ ዕቁብ?
 • ታዲያ የምናከራየው ሕንፃ ሒሳብ መቀበያ ጊዜ ነው?
 • ኧረ ሰውዬ ምን ሆነሃል?
 • የምን ጊዜ ነው የደረሰው ታዲያ?
 • የበዓል ነዋ፡፡
 • ታዲያ እሱ እኮ ያንቺ ጉዳይ ነው፡፡
 • ምኑ ነው የእኔ ጉዳይ?
 • በቃ የበዓል ዝግጅቱ ነዋ፡፡
 • ታዲያ ዝግጅቱ ዝም ብሎ ይካሄዳል እንዴ?
 • ምን ያስፈልጋል ታዲያ?
 • ከፍተኛ ወጪ ነው እኮ ያለው፡፡
 • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
 • ስለዚህ ወጪውን መሸፈን የአንተ ጉዳይ ነዋ፡፡
 • እና ምን ተሻለ?
 • እሱን አንተ ታውቃለህ፡፡
 • በቃ ማፈላለግ ነዋ፡፡
 • ምንድን ነው የምታፈላልገው?
 • የበዓል ዝግጅት ወጪያችን የሚሸፍን ስፖንሰር ነዋ፡፡
 • ዘዴኛ ነህ እኮ አንተ፡፡
 • እንዲያውም ሰሞኑን ከውጭ የመጡ ኢንቨስተሮች አሉ፡፡
 • ኢትዮጵያውያን ናቸው?
 • የሉም የውጭ አገር ዜጐች ናቸው፤ አንድ ትልቅ ፕሮጀክት ይዘው መጥተዋል፡፡
 • እና እነሱን ስፖንሰር እንዲሆኑ ልታደርጋቸው?
 • እህሳ፡፡
 • ሰውዬ ጤነኛ ነህ?
 • ምን ችግር አለው?
 • ትልቅ ፕሮጀክት ይዞ የመጣ የውጭ ኢንቨስተር በበዓል ስፖንሰርነት ብቻ ልታልፈው?
 • አልገባኝም?
 • የጀመርነውን ሕንፃ ሊያስጨርሱ የሚችሉ ሰዎችን በበዓል ወጪ ብቻ ልትገላግላቸው?
 • የበዓሉስ ወጪ ቀላል አይደለም እኮ፤ ከየት ይመጣል ብዬ ነው?
 • ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ዕድሉ ይሰጣቸዋ፡፡
 • ጥሩ ሐሳብ አመጣሽ፡፡
 • በዚያ ላይ ደግሞ በዓሉ የሐበሻ ስለሆነ እነሱ ጋ ነው መሄድ ያለብህ፡፡
 • ትክክል ብለሻል፡፡
 • ባይሆን የጉቦ አቀባበልህን ሥልት መቀየር አለብህ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • በዚህች የማትረባ ነገር እንዳትገመገም ማለቴ ነዋ፡፡
 • እኮ ምን ማድረግ እችላለሁ?
 • በዓሉ አሪፍነቱ እኮ ይኼ ነው፡፡
 • ምኑ ነው አሪፍነቱ?
 • የተቀበልኩት ጉቦ አይደለም ትላለሃ፡፡
 • ምንድን ነው ታዲያ?
 • ስጦታ ነዋ፡፡
 • ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡
 • ስጦታውን ግን ስትቀበል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
 • የምን ጥንቃቄ?
 • መንግሥት ሌላ ስጦታ እንዳይሰጥህ፡፡
 • ምን ዓይነት ስጦታ?
 • የስንብት ደብዳቤ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር እየሄዱ ነው]

 • ዛሬ ጃሙ ምንድን ነው?
 • ያው ደረሰ አይደል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው የደረሰው?
 • በዓሉ ነዋ፡፡
 • እየተዘጋጀህ ነው ታዲያ?
 • የዚያን ቀን ሰው እንዲጠራኝ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡
 • እኔ ጠርቼሃለሁ በቃ፡፡
 • እውነት ክቡር ሚኒስትር?
 • አዎን እኔ ቤት ታሳልፋለህ፡፡
 • ግን በዓል እንዴት ነው የሚያሳልፉት?
 • በዚህኛው በዓል እንኳን ቀለል አድርጌ ነው የማከብረው፡፡
 • እኮ ምን ምን ያደርጋሉ?
 • ያው አንድ በሬ ማረዴ አይቀርም፡፡
 • እ…
 • ግን ከአገር ቤት ዘመዶቼ የሚመጡ ከሆነ ምናልባትም ጥጃ ነገር ልጨምር እችላለሁ፡፡
 • እሺ ሌላስ?
 • ያው ፋሲካ ስለሆነ አንድ ሁለት ፍየል የግድ ነው፡፡
 • እስቲ እውነት በሉ?
 • እንግዲህ ይኼ ባለቤቴ በግ ይቅር ካለች ነው፡፡
 • ሌላስ ክቡር ሚኒስትር?
 • የሚጠጣ ደግሞ ሁለት ካርቶን ጐልድ ሌብል አዘጋጃለሁ፡፡
 • ምን አሉኝ? ጎልድ ሌብል?
 • አሁን እኮ ቢራ በላት፡፡
 • ኧረ እንዳልበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ኬክ እንኳን ሰው ራሱ የሚያመጣው ይደፋል፡፡
 • ኧረ እኔን በደፋኝ፡፡
 • ድፎ ዳቦ እያለ አንተ ምን በወጣህ?
 • አይ እንዲያው ገርሞኝ ነው፡፡
 • በዚህች ላይ ሁለት በርሜል ጠጅ ይጣላል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ኧረ እኔን የሚጥል በሽታ እንዳያሲዙኝ?
 • ለመሆኑ አንተ እንዴት ነው የምታከብረው?
 • ማን? እኔ?
 • አዎና፡፡
 • እኔ እንኳን እንደ እርስዎ ቀለል አድርጌ ሳይሆን አካብጄ ነው የማከብረው፡፡
 • እውነት? ምን ታዘጋጃለህ?
 • ከሚጠጣው ልጀምርልዎታ?
 • እሺ ቀጥል፡፡
 • አራት ጋን ፊሊተር አስጠምቃለሁ፡፡
 • እሺ፡፡
 • አንድ ዋይትና ብላክ አስጋግራለሁ፡፡
 • ዋይትና ብላክ ፎረስት?
 • ኧረ ጥቁርና ነጭ የስንዴ ድፎ ነው እንጂ፡፡
 • እሺ ሌላስ?
 • ያው ዶሮ መግዛት ስለማልችል ከበዓሉ በፊት የሥራ ፈቃድ ይሰጡኛል፡፡
 • የምን ፈቃድ ነው?
 • ከቀናኝ እርግብ አጥምጄ ለበዓሉ ለማረድ ነዋ፡፡
 • ቀልደኛ ነህ ልበል?
 • ያው ከእርስዎ አንፃር ሲታል ኑሮዬ ራሱ ቀልድ ነው፡፡
 • እና ፆሙን በምንድን ነው የምትፈታው?
 • እኔ እኮ ፆም ሳይሆን ሌላ ነገር ነው የምፈታው፡፡
 • ምንድን ነው የምትፈታው?
 • ሕልም!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ እንደገቡ ጸሐፊያቸውን ጠሯት]

 • ለምን እንደጠራሁሽ ገብቶሻል መቼም?
 • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ተዘጋጅተሻል ታዲያ?
 • ይኸው ሪፖርቱን ጽፌ ስጨርስ ነው የጠሩኝ፡፡
 • ቀጥይ፡፡
 • የበዓል ስጦታ አቀባበላችን አመርቂ ውጤት ተመዝግቦበታል፡፡
 • አፈጻጸሙ እንዴት ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር አጠቃላይ አቀባበላችን ከዕቅዳችን በላይ ነው፡፡
 • ምን ያህል ተቀበልን?
 • እንግዲህ በዚህ በዓል ለመቀበል ከአቀድነው ስጦታ ከ140 በመቶ በላይ መቀበል ችለናል፡፡
 • በጣም ደስ የሚል ሪፖርት ነው፡፡
 • የስጦታ አቀባበላችንን በዘርፍ ልከፋፍልልዎት፡፡
 • ቀጥይ እሺ፡፡
 • በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የፈርኒቸር ዘርፍ ነው፡፡
 • እሺ፡፡
 • በዚህ ዘርፍ ሙሉ የቤት ዕቃ ስጦታ በመቀበል የዕቅዳችንን 120 በመቶ አሳክተናል፡፡
 • እየሰማሁሽ ነው፡፡
 • በዚህ ዘርፍ የተገኘው ውጤት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ የበዓል ስጦታ ጋር ሲነፃፀር የ110 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
 • ግሩም፡፡
 • በሁለተኛነት የተቀመጠው የኤሌክትሮኒክስ ስጦታ ነው፡፡
 • እሱስ እንዴት ነው?
 • በዚህ ዘርፍ የዕቅዳችንን 115 በመቶ ማሳካት ችለናል፡፡
 • ይህም አመርቂ ውጤት ነው፡፡
 • በዚህ ዘርፍ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ የበዓል ስጦታ ጋር ሲነፃፀር የ112 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
 • ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የትኛው ዘርፍ ነው?
 • በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የከብት ስጦታ ነው፡፡
 • ምን ያህል ነው የተመዘገበው?
 • በዚህ ዘርፍ የዕቅዳችንን 85 በመቶ ብቻ ነው ማግኘት የቻልነው፡፡
 • ለምንድን ነው በዚህ ዘርፍ ያቀድነውን ማግኘት የቻልነው?
 • ይህ በእርግጥ መንግሥት የሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነፀብራቅ ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ያው እንደሚታወቀው ኢኮኖሚያችን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር መቀየር አለበት ተብሏል፡፡
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • እንግዲህ ሪፖርቴን እንደሰሙት በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢንዱስትሪ ውጤቶች ናቸው፡፡
 • እውነትሽን ነው እባክሽ፡፡
 • ስለዚህ የግብርና ዘርፉ ስጦታ ሦስተኛ መሆኑ የሚያሳየን ነገር አለ፡፡
 • ምንድን ነው የሚያሳየን?
 • በኢኮኖሚው ላይ የመዋቅር ሽግግር መኖሩን ያመለክታል፡፡
 • ድሮውንስ የምንለፋው ለዚህ አይደል እንዴ?
 • ሆኖም ግን በዚህ ዘርፍ የተገኘው ውጤት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ የበዓል ስጦታ ጋር ሲነፃፀር የ100 ፐርሰንት ጭማሪ አሳይቷል፡፡
 • እሺ ቀጥይ፡፡
 • የመጠጥ ስጦታው ላይ ግን የታዩ ችግሮች አሉ፡፡
 • ምን ዓይነት ችግሮች?
 • ዘርፉ ከታሰበው በታች ዝቅተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
 • በዘርፉ የተመዘገበው ውጤት ምን ይመስላል?
 • በዚህ ዘርፍ ያገኘነው ስጦታ የዕቅዳችንን 38 በመቶ ነው፡፡
 • የዕቅዳችን 50 በመቶ እንኳን አልተሰበሰበም?
 • ክቡር ሚኒስትር በዚህ ዘርፍ የተገኘው ውጤት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ የበዓል ስጦታ ጋር ሲነፃፀር ራሱ በ20 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡
 • ለምንድን ነው ዘርፉ እንደዚህ የወረደው?
 • እንግዲህ ለዘርፉ እንዲህ መውረድ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡
 • ምንድን ናቸው ምክንያቶቹ?
 • የመጀመሪያው በዓለም ላይ የነዳጅ መውረድ ያስከተለው ተፅዕኖ ነው፡፡
 • መጠጥና ነዳጅን ምን አገናኛቸው?
 • ሁለቱም ፈሳሾች መሆናቸው ዋናው የሚገናኙበት ነገር ነው፡፡
 • አንቺ አላስተዋልኩትም ነበር፤ ልክ ነሽ እባክሽ፡፡
 • በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ ያለው የዶላር እጥረት ዘርፉ ያስመዘገበው ውጤት እንዲቀንስ ሌላኛው መንስዔ ነው፡፡
 • ይኼ ዶላር እኮ ስጦታችንን ራሱ እየጐዳው ነው ማለት ነው?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ የዶላር ጉዳይ በጊዜ መፍትሔ ካልተሰጠው በቀጣይ ያሉ በዓሎች ላይ ራሱ ተፅዕኖ ማሳደሩን ይቀጥላል፡፡
 • ሌላውስ ምክንያት ምንድን ነው?
 • ሌላው በዘርፉ ላይ ኪራይ ሰብሳቢነት ተንሰራፍቶ ታይቷል፡፡
 • ይኼን ትንሽ ብታብራሪው?
 • ሰዎች መጠጥን በስጦታ ከመስጠት ይልቅ ራሳቸው የመጠጣት ዝንባሌ ታይቶባቸዋል፡፡
 • ይኼማ አደገኛ የመጠጥ ሰብሳቢነት ፀባይ ነው፡፡
 • ሰዎች መጠጥ መጠጣት ያበዙትም በኑሯቸው ላይ እየደረሰ ባሉ የተለያዩ ጫናዎች ቢሆንም፣ ይህ ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ካልተገኘለት አሁንም በቀጣይ በዓሎች ላይ ተመሳሳይ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡
 • ስለዚህ ይህን የኪራይ ሰብሳቢነት ፀባይ አጥብቀን መዋጋት አለብን፡፡
 • አዎን፣ በዘርፉ ላይም የግንዛቤ ማስጨበጫ በሰፊው መሰጠት አለበት፡፡
 • በቀጣይ ግን ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ዕቅዳችንን ማስተካከል አለብን፡፡
 • ዕቅዳችንን ምን ማድረግ አለብን?
 • መለጠጥ!