ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ የሚያስገቡት ዕቃ ኬላ ላይ ተይዞባቸዋል፡፡ ሚስታቸው ደወሉላቸው]

 • ሰላም ዋልሽ?
 • ምን ሰላም አለ?
 • ምን ሆንሽ ደግሞ?
 • ምን የማልሆነው ነገር አለ?
 • ጠዋት ሰላም አልነበርሽ እንዴ?
 • የዚህ አገር ሰላም እኮ እንደ ስቶክ ኤክስቼንጅ ይወጣል ይወርዳል፡፡
 • ሴትዮ አትሳሳቺ፡፡
 • እንዴት ባክህ?
 • በአሁኑ ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት አገር የትም የለም፡፡
 • አትቀልድ ባክህ፡፡
 • እውነቴን ነው፡፡
 • አሁን የምነግርህ ዜና ሰላምህን ይነሳህ የለ እንዴ?
 • ምንድን ነው እሱ?
 • ዕቃው ተወረሰ?
 • ልጆቼ እያሉ ማን ነው የሚወርሰኝ?
 • መንግሥት ነዋ፡፡
 • መንግሥት እኮ እኔ ነኝ፡፡
 • ለማንኛውም አሁን ስልክ ተደውሎልኝ ነበር፡፡
 • ማን ነው የደወለልሽ?
 • ዕቃው ተወረሰ ብለው ነው የደወሉልኝ፡፡
 • የትኛው ዕቃ?
 • ሳሙናና ዲተርጀንት የጫኑት መኪኖች ተይዘዋል፡፡
 • ብረት የጫኑትስ?
 • እነሱ አልተያዙም፡፡
 • ሞባይል የጫኑትስ?
 • እነሱም እስካሁን አልተያዙም፡፡
 • እፎይ፡፡
 • እፎይ ትላለህ እንዴ?
 • እነዚህስ ተይዘው ቢሆን ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር ብዬ ነዋ፡፡
 • ቂሊንጦ ነበራ የሚውጥህ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ የኬላው ኃላፊ ጋ ደወሉ]

 • ማን ልበል?
 • ጭራሽ ማን ልበል ትለኛለህ?
 • የደወልከው እኮ አንተ ነህ፤ ማን ልበል?
 • ተናንቀናል ማለት ነው፡፡
 • ምን አልከኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
 • ውይ ውይ በሞትኩት፤ ወሳኝ ሰዓት ላይ ነው የደወሉት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የምን ወሳኝ ሰዓት?
 • ይኸው ሁለት አይሱዙ ዕቃ እንደያዝኩ ነው የደወሉት፡፡
 • የምን ዕቃ ነው?
 • የሌቦች ዕቃ ነዋ፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው ታክስ ሳይከፍሉ ሊያሳልፉ ሲሉ እኮ ነው የያዝኳቸው፡፡
 • ምንድነው የጫኑት ዕቃ?
 • ዲተርጀንትና ሳሙና ነው፡፡
 • እ…
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር ይቅርታ ቅድም ሌላ ሰው መስሎኝ ነው፤ ይኸው ከመቀመጫዬ ተነስቼ ሰላምታ ሰጥቻለሁ፡፡
 • ገና ከወንበርህ ለዘለዓለም አነሳሃለሁ፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • ሰምተሃል፡፡
 • እኮ ምን አደረግኩ?
 • ያደረግከውንማ ታውቃለህ፡፡
 • ዲተርጀንትና ሳሙና ስለወረስኩ?
 • ለመሆኑ ገላህን ታጥበህ አታውቅም አይደል?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼን ሁላ ሳሙና እወርሳለሁ ስትል አታፍርም?
 • ታክስ እኮ ስላልተከፈለ ነው፡፡
 • እኔ ለሁሉም ነገር ታክስ ከፍዬ እችለዋለሁ?
 • የእርስዎ ነው እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • እና የአንተ ነው?
 • ላውንደሪ ቤት ከፈቱ እንዴ?
 • እሱን ደግሞ ማን ነገረህ?
 • አሁን ምን ይሻላል?
 • የዘራሃውን ታጭደዋለህ፡፡
 • እንዴት ማለት ክቡር ሚኒስትር?
 • ዕቃዬን እንዳሰርክ …
 • እ…
 • አንተም ትታሰራለህ፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር የተቆጡ ይመስላሉ?
 • ምን ሰይጣን ብቻ የተሰበሰበበት አገር?
 • ምን ተፈጠረ?
 • ዕቃዬን ይዘውብኝ ነዋ፡፡
 • ማን ነው የያዘብዎት?
 • ኬላ ላይ ነዋ፡፡
 • የምን ዕቃ ነው?
 • ዲተርጀንትና ሳሙና፡፡
 • የማን ዕቃ ነው?
 • የእኔ ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የድግስ ዕቃ ያከራዩ ጀመር እንዴ?
 • ምን ማለት ነው?
 • ኬላ ላይ ከተያዘብዎት በመኪና የሚገባ ነው ብዬ ነዋ፡፡ ያ ሁሉ ሳሙና ምን ያደርግልዎታል?
 • መቼም ልታጠብበት ነው አልልህም?
 • ለነገሩ እርስዎ ቢታጠቡም አይፀዱም፡፡
 • ከምን?
 • ከሙስና!

[አንድ ባለሀብት ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለላቸው]

 • ሰላም ወዳጄ፡፡
 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • አለሁ አንተ እንዴት ነህ?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር እጅግ እኮ እየተማረርኩ ነው፡፡
 • ምን አማረረህ?
 • ምን የማያማርር ነገር አለ ብለው ነው?
 • አንተ እኮ ደረጃ አንድ ግብር ከፋይ ነህ፡፡
 • ለዛውም ዋንጫ ተሸላሚ እንጂ፡፡
 • በዚህኛውም ዓመት ደግመህ ዋንጫውን ከወሰድከው እኮ ሐትሪክ ነው የምትሠራው፡፡
 • ምን ዋጋ አለው ክቡር ሚኒስትር?
 • ዋንጫውን ታስቀረዋለሃ፡፡
 • አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ሆነሃል?
 • እኔ በቃ የመልካም አስተዳደር ችግሩን አልቻልኩትም፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ሠራተኞቼ አቅተውኛል፡፡
 • ምን አደረጉህ?
 • ግብር አይከፍልም ብለው ይጠቁማሉ፡፡
 • ለምን?
 • ምቀኝነት ይዟቸው ነዋ፡፡
 • እሺ፡፡
 • በዛ በኩል የእናንተ ሰዎች ኪራይ ሰብሳቢ ነህ ይሉኛል፡፡
 • ምቀኞች በላቸው፡፡
 • በጐን ሠራተኞቼ ፍርድ ቤት ሲያመላልሱኝ ነው የሚውሉት፡፡
 • ምን ሆንኩ ብለው?
 • እየተበደልን ነው ብለው ነዋ፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • እና ክቡር ሚኒስትር እኔ በጣም ተማርሬያለሁ፡፡
 • ቆይ ተረጋጋ፡፡
 • ፍትሕ አጥቻለሁ ነው የምልዎት፡፡
 • መላ አለው ስልህ፡፡
 • እኔ ፍርድ ቤትም መመላለስ ሰልችቶኛል፡፡
 • እኔ አሪፍ መፍትሔ አለኝ፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • በራስ ለምን አታቋቁምም?
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • እስር ቤቱንና ፍርድ ቤቱን!

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]

 • ሰው ይፈልግዎታል፡፡
 • የምን ሰው?
 • አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው ይላል፡፡
 • ተራ ሰው አደረግሽኝ እንዴ መንገደኛው ሁሉ የሚያገኘኝ?
 • አይ ክቡር ሚኒስትር አጣዳፊ ጉዳይ ገጥሞዎት ነው፡፡
 • ሴትዮ ሥራ ላይ ነው ብለሽ አባሪልኝ፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ባለጉዳዩ መግባት እንደማይችል ብትነግረውም አልፏት ገባ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ፈልገህ ነው?
 • መግባት አትችልም ብላኝ ነበር፣ ግን ጉዳዬ አጣዳፊ ስለሆነብኝ ነው፡፡
 • በጥበቃ እንዳስወጣህ ፈልገህ ነው ታዲያ?
 • አይደለም ክቡር ሚኒስትር አንዴ ያድምጡኝ፡፡
 • ምንም አላዳምጥም፡፡
 • ችግር እየፈጠረ ያለው እኮ አለማዳመጥዎት ነው፡፡
 • እሺ ምንድን ነው ችግርህ?
 • እኔ ሳሙና አስመጪ ነኝ፡፡
 • አንተ ነሃ ተፎካካሪዬ፡፡
 • አንዳንድ ነጋዴዎች ታክስ ሳይከፍሉ እያስገቡ ከገበያ እያስወጡን ነው፡፡
 • እና ምን ላድርግልህ እኔ?
 • መንግሥት ጣልቃ ይግባልንና ይቆጣጠራ፡፡
 • ሰውዬ ታመሃል፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼ እኮ ነፃ ገበያ ነው፡፡
 • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
 • ስለዚህ መንግሥት ጣልቃ አይገባም፡፡
 • ለነገሩ እርስዎ በደንብ ጠልቀው መግባትዎን ሰምቻለሁ፡፡
 • ምን ውስጥ?
 • ኮንትሮባንዱ ውስጥ!

[የክቡር ሚኒስትሩ የእህት ልጅ ደወለላቸው]

 • ሄሎ ጋሼ፡፡
 • እንዴት ነህ ታዳጊው ባለሀብት?
 • ኧረ ጋሼ አላሠራ አሉኝ እኮ?
 • እነማን?
 • የእናንተው ሰዎች ናቸዋ፡፡
 • ምን አደረጉህ?
 • ይኸው ሱቄን አሸጉት፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • ሕገወጥ ነህ ብለው ነዋ፡፡
 • የሱቪኒር ዕቃ መሸጥ ማን ነው ሕገወጥ ያደረገው?
 • አይ ያው በጐን ዶላር እሸጥ አይደል?
 • ዶላር እጥረት ስላለ አይደል እንዴ የምትሸጠው? ማን ነው እሱንስ ቢሆን ሕገወጥ ያደረገው?
 • እሱማ ጋሼ ለባንክ ብቻ የተፈቀደ ሥራ ነው፡፡
 • አንተ ካደግህ እኮ ባንክ መሆን የምትችል ልጅ ነህ፡፡
 • ብቻ ጋሼ እኔን ያሳሰበኝ የልጆቼ ጉዳይ ነው፡፡
 • እነሱማ ምን ይሆናሉ?
 • እንዴት አይሆኑ?
 • በስማቸው ያስቀመጥክላቸው ገንዘብ እኮ እነሱንም ባንክ መሆን ያስችላቸዋል፡፡
 • እ…
 • እንደውም ባንኮች መዋሀድ አለባቸው እየተባለ ስለሆነ አንድ ላይ ተዋህዳችሁ ትልቅ ባንክ መመሥረት ነው፡፡
 • እዚህ አገር ግን ሠርቶ ማደግ ቀረ ማለት ነው?
 • እሱ ቀርቶ እኮ ሌላ ስትራቴጂ መጥቷል፡፡
 • ምን የሚሉት?
 • ሰብስቦ መጥፋት!