ክቡር ሚኒስትር

[ለክቡር ሚኒስትሩ ሚስታቸው ስልክ ደወሉላቸው]

 • በአስቸኳይ እንድትደርስ፡፡
 • የት ነው የምደርሰው?
 • ሆስፒታል ነው ያለሁት?
 • ምነው ምን ሆንሽ?
 • ልጅህ ተፈንክቶልሃል፡፡
 • የትኛው ልጅ?
 • የመጀመርያ ልጅህ ነዋ፡፡
 • ምን ሆኖ?
 • ከሰዎች ጋር ተጣልቶ፡፡
 • የእኔ ልጅ እኮ ሰላማዊ ነው፡፡
 • ወይ ሰላማዊ?
 • ምን እያልሽ ነው?
 • ሰክሮ እኮ ነው የተጣለው፡፡
 • እያሾፍሽ ነው?
 • ቢሆን ይሻለኝ ነበር፤ ብቻ ተዋርደናል፡፡
 • የእኔ ልጅማ ሊሰክር አይችልም፡፡
 • ይኼን እኮ ነው የምልህ፤ ልጆቹን አታውቃቸውም፡፡
 • ልጆቼንማ በደንብ ነው የማውቃቸው፡፡
 • ከእነሱ ጋር መቼ ነው ጊዜ አጥፍተህ የምታውቀው?
 • እኔ እኮ አገር የማስተዳድር ሰው ነኝ፡፡
 • ቤተሰብህን ሳታስተዳደር አገር እንዴት ልታስተዳድር ትችላለህ?
 • አገሪቷማ ይኸው እየተመነደገች ነው፡፡
 • አትሳሳት፣ ውስጡን በደንብ አጢነህ መመልከት አለብህ፡፡
 • ለማንኛውም አሁን መጣሁ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ልጃቸው የተኛበት ሆስፒታል ገቡ]

 • አጅሬ፡፡
 • አቤት ዳዲ፡፡
 • ምን ሆነህ ነው?
 • ዳዲ በጣም ነው የተናደድኩት፡፡
 • ለምንድን ነው የተናደድከው?
 • ይኼ እናንተ ምንድን ነበር የምትሏቸው?
 • ምኖቹን?
 • ኪራይ ቤቶች ነው የምትሏቸው?
 • እ… ኪራይ ሰብሳቢዎች?
 • አዎ ኪራይ ሰብሳቢዎች፡፡
 • ምን ሆኑ?
 • ከእነሱ ጋር እኮ ነው የተጣላሁት፡፡
 • እንዴት?
 • በቃ ኢትዮጵያ እያደገች ነው ስላቸው ሊሰሙኝ አልቻሉም፡፡
 • እነሱ መቼ የሚሰማ ጆሮ አላቸው?
 • ከእነሱ የባሰው ደግሞ የእነዛ የደላሎች ነገር ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ለኪራይ ሰብሳቢዎቹ ተደርበው ነዋ የደበደቡኝ፡፡
 • ዛሬ አኮራሃኝ ልጄ፡፡
 • እንዴት ዳዲ?
 • ለአገሪቷ ዕድገት ስትል ከኪራይ ሰብሳቢዎችና ከደላሎች ጋር ቡጢ በመግጠምህ ተደሰትኩ፡፡
 • የአባቱ ልጅ ነኛ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ማውራት ጀመሩ]

 • አየሽ አይደል የልጃችንን ጀግንነት?
 • የምን ጀግንነት?
 • ልጃችን ምን ሆኖ ነው የተፈነከተው?
 • ሰክሮ ነዋ፡፡
 • አትሳሳቺ ሰክሮ አይደለም፡፡
 • እና ምን ሆኖ ነው?
 • ከኪራይ ሰብሳቢዎችና ከደላሎች ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጡ ነው፡፡
 • ኧረ ኡኡኡ…
 • ምን ሆነሻል?
 • ልጅህ እኮ ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ይኸው ሰካራም ሆኖ በጣም አሳፍሮኛል፡፡
 • እኔ በእጅጉ ነው የኮራሁበት፡፡
 • በምኑ ነው የኮራኸው?
 • እያፈራነው ያለው ትውልድ የእኛን አርዓያ እየተከተለ ያለ ትውልድ ነው፡፡
 • ምን አልከኝ?
 • ይህ የተባረከ ትውልድ ነው፡፡
 • የተረገመ ትውልድ ነው ያልከኝ?
 • የለም፤ ልማታዊ ትውልድ!

[የክቡር ሚኒስትሩ ሁለተኛ ልጅ ትምህርት ቤት ወላጅ አምጪ ስለተባለች፣ ክቡር ሚኒስትሩ ዳይሬክተሩን ለማናገር ሄዱ]

 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምኑ ነው ይቅርታው?
 • ያው ቢዚ እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡
 • የልጄ ጉዳይ አይደል እንዴ? ምን ችግር አለው?
 • እኔም ጉዳዩ አንገብጋቢ ስለሆነብኝ ነው ያስጠራሁዎት፡፡
 • ምን ነበር ታዲያ?
 • ልጅዎት ከቁጥጥር ውጪ ሆናለች፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ትምህርት ቤቱን እየበጠበጠች ነው፡፡
 • ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ገጥማለች እያልከኝ ነው?
 • የምነግራትን ነገር አትሰማም፡፡
 • ማን አለብኝነት ሰፍኖባታል ነው የምትለኝ?
 • አዋዋሏም ጥሩ አይደለም፡፡
 • ምነው ከኪራይ ሰብሳቢዎች ጋር ገጠመች እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር ሺሻ ቤት ነው የምትውለው፡፡
 • ዋናው ጥያቄ ሺሻ ቤት ምን ልታደርግ ሄደች የሚለው ነው?
 • ያው ልታጨስ ነዋ፡፡
 • መጀመርያ ራሷን መጠየቅ አለብን፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ልጅ ተጠርታ መጣች]

 • ምንድን ነው የምሰማው?
 • ምን ሰማህ ዳዲ?
 • ከፀረ ልማት ኃይሎች ጋር ገጥመሻል አሉ?
 • ምን?
 • ማን አለብኝነት ሰፍኖብሻል ተብሏል፡፡
 • ኦ ማይ ጋድ!
 • ከኪራይ ሰብሳቢዎች ጋር ሳትገጥሚ አልቀረሽም?
 • ዳዲ እኔ እኮ የአንተ የፖለቲካ ጃርገኖች አይገቡኝም፡፡
 • ሺሻ ቤት ነው የምትውይው አሉ፡፡
 • ዳዲዬ ለሚሽን እኮ ነው የምሄደው፡፡
 • እኔም ብያለሁ፡፡
 • በየሺሻ ቤቱ ያሉት ወጣቶች እኮ ጨለምተኞች ናቸው፡፡
 • እንዴት?
 • በቃ በአገሪቱ ዕድገት ተስፋ ስለቆረጡ ነው በየሺሻ ቤቱ የሚውሉት፡፡
 • ልክ ነሽ ልጄ፡፡
 • በቃ እኔ ደግሞ አገሪቷ ውስጥ ያለውን ዕድገት ዓይናችሁን ከፍታችሁ ተመልክቱ እያልኳቸው ነው፡፡
 • ዛሬ በቃ አንጀቴ ቅቤ ጠጣ፡፡
 • የአንተ ልጅ ነኝ እኮ ዳዲ፡፡
 • እሱን ዛሬ አረጋገጥኩ፡፡

 [ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ዳይሬክተሩ ዞሩና]

 • አየህልኝ አይደል?
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • ልጄ ምን ያህል ልማታዊ እንደሆነች?
 • እ…
 • ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ?
 • በሚገባ መቆጣጠር፡፡
 • ማንን?
 • ልማታዊ ሺሻ አጫሿን!

[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]

 • ዛሬ ምን ያህል እንደተደሰትኩኝ አትጠይቀኝ?
 • ምን ተገኘ ክቡር ሚኒስትር?
 • ልጆቼ አኮሩኝ፡፡
 • ትምህርት ቤት አንደኛ ወጡ?
 • ትልቁ ልጄ ተፈንክቶ ሆስፒታል ነው፡፡
 • ውይ ውይ ተርፏል? ምን ሆኖ ነው?
 • ከሰዎች ጋር ተጣልቶ ነዋ፡፡
 • ታዲያ መፈንከቱ ነው ያኮራዎት?
 • ከኪራይ ሰብሳቢዎችና ከደላሎች ጋር ተጣልቶ እኮ ነው የተፈነከተው፡፡
 • የት ነው የተጣላው?
 • መጠጥ ቤት፡፡
 • በዚህ ዕድሜው ይጠጣል?
 • የተጣላው እኮ ስለአገሪቱ ዕድገት በአደባባይ በመናገሩ ነው፡፡
 • ወይ ግሩም፡፡
 • ምን እሱ ብቻ?
 • ሌላ ምን አለ?
 • ታናሽ እህቱም አኩርታኛለች፡፡
 • በምን አኮራችዎት?
 • ዛሬ ወላጅ አምጪ ተብላ ነበር፡፡
 • ለምን?
 • ሺሻ ቤት ገብታ ለጨለምተኞች ስለአገሪቷ ዕድገት በመስበኳ፡፡
 • በዚህ ዕድሜዋ ሺሻ ታጨሳለች?
 • ያጨሰችው ለአገሪቷ ዕድገት መስዋዕትነት ለመክፈል ነው፡፡
 • ለማንኛውም ዛሬ የፈለኩዎት ለአንድ ጉዳይ ነበር፡፡
 • ለምን ጉዳይ ፈለከኝ?
 • ፓርላማ የቀረበውን ሪፖርት አልሰሙም?
 • የምን ሪፖርት?
 • ፀረ ሙስና ባለሥልጣናትን እየከሰሰ አይደለም ተብሎ ተተችቷል፡፡
 • እና ሥራው መክሰስ ነው?
 • ምክር እያበዛ ነው ተብሏል፡፡
 • እኔ እንደውም ምክር አንሷል ባይ ነኝ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • መመካከር አለብን፡፡
 • የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር እኮ እየጨመረ ነው፡፡
 • አየህ ይህ ሁሉ ችግር የመጣው ካለመመካከር ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ብንመካከር ኖሮ…
 • ከዚህ በላይ ይዘረፍ ነበር?
 • ምን አልከኝ?
 • ብቻ ቢያስቡበት ብዬ ነው፡፡
 • ለመሆኑ እኔ የምከሰስ ይመስልሃል?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • ስለዚህ ምክሩን አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡
 • እና ምን ይደረግ?
 • መዋቅራችን ላይ አንድ ክንፍ መጨመር አለብን፡፡
 • ምን የሚሉት?
 • መካሪ ክንፍ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ስልክ ተደወለላቸው]

 • ክቡር ሚኒስትር በእናንተ ዕርዳታ ነው እዚህ የደረስነው፡፡
 • ሁሌም ከጎናችሁ ነን አታስብ፡፡
 • እንግዲህ 50 ዓመት ሞልቶናል፡፡
 • ገና እንደ እኛ ትደፍኑታላችሁ፡፡
 • ምኑ?
 • መቶውን ነዋ፡፡
 • አሜን ክቡር ሚኒስትር ያድርግልና፡፡
 • በእኛ እኮ ነው የወጣችሁት፡፡
 • ያው ዛሬ አደዋወሌ መቼም ገብቶዎታል?
 • ምን ፈልገህ ነው?
 • ስፖንሰር እንዲሆኑን ነው፡፡
 • ምን ችግር አለ?
 • ታንኪው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እናንተ ያለእኛ፣ እኛስ ያለእናተ ማን አለን?
 • ልክ ብለዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው ስፖንሰር የሚያደርጉን?
 • የፕላቲኒየሙን ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ነው የማመሰግነው፡፡
 • ምን ነካህ? ድጋፋችንን እኮ በተግባር መግለጽ አለብን፡፡
 • በጣም ልክ ነዎት፡፡
 • እናንተ እኮ የዕድታችን ማብሰሪያ ናችሁ፡፡
 • ልክ ብለዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ ሁሌም ከጎናችሁ ነን፡፡
 • በድጋሚ ታንኪው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንም አይደል፡፡
 • ለመሆኑ የትኛውን ፕሮግራም ነው የሚከታተሉት?
 • ማን እኔ?
 • አዎን፤ ፕሮግራማችንን አይከታተሉም እንዴ?
 • ሥራም አላጣሁ!