ክቡር ሚኒስትር

[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ተበሳጭተዋል]

 • ምን ሆነሻል?
 • ምን ሆንኩ?
 • ፊትሽ የጠቋቆረው፡፡
 • ለምን አይጠቁር?
 • እኮ ምን ሆነሻል?
 • ተያዘ፡፡
 • ያ ሱቅ?
 • ክፈል ክፈል ብዬ ስንቴ ነው የነገርኩህ?
 • እና ሱቁ ተያዘ?
 • ሱቁማ ቢሆን የተሻለ ነበር፡፡
 • እና ሱቁ አልተያዘም?
 • እኔ ስለሱቁ አይደለም የማወራህ፡፡
 • እና ምኑ ነው ተያዘ የምትይው?
 • አዳራሹ ነዋ፡፡
 • የምን አዳራሽ?
 • የእህቴ ልጅ ሠርግ መድረሱን ረሳኸው?
 • ደረሰ እንዴ?
 • አንተ ምን ሐሳብ አለብህ?
 • የማላስበውን ብጠይቂኝ ይሻላል?
 • እኮ ምን ታስባለህ?
 • ስለዚች አገር ነዋ፡፡
 • ይቺን አገር ስለመቦጥቦጥ?
 • ይህቺን አገር ስለማልማት ነው እንጂ፡፡
 • ራሴን ስለማልማት ነው ያልከኝ?
 • እውነትም ተናደሻል ማለት ነው?
 • እንዴት አልናደድ?
 • አታስቢ፡፡
 • ጤንነትህን ግን መጠራጠር ጀምሬያለሁ፡፡
 • ለምንድን ነው የምትጠራጠሪው?
 • የሠርጉ ወረቀት እኮ ተበትኗል፡፡
 • ይበተና ምን ችግር አለው?
 • ወረቀቱ ላይ የተጻፈው አዳራሽ ለሌላ ተከራየ እያልኩህ እኮ ነው፡፡
 • ያ ሆቴል አይደል እንዴ?
 • አዎን ነው፡፡
 • ባለሆቴሉ እኮ ልማታዊ ነው፡፡
 • ቢሆንስ ታዲያ?
 • በአንድ ስልክ ነዋ የምጨርሰው፡፡
 • ምኑን?
 • የእኛ ሠርግ እዛ እንዲሆን፡፡
 • እኛ እኮ ስላልከፈልን ነው ለሌላ ሠርግ ያከራዩት፡፡
 • አንድ ነገር አትርሺ፡፡
 • ምን?
 • የእኛ ሠርግ ልማታዊ ነው፡፡
 • እ…
 • እኛ የተከራየነውን አዳራሽ ለመከራየት የፈለጉት ደግሞ…
 • ምን?
 • ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው፡፡
 • እኛ እኮ ስላልከፈለን ነው እነሱ የከፈሉት፡፡
 • አየሽ ኪራይ ሰብሳቢዎች መሆናቸውን የምታውቂው ቀድመው ሒሳብ በመክፈላቸው ነው፡፡
 • አንተ እውነትም ለይቶልሃል፡፡
 • ለማንኛውም አታስቢ፡፡
 • ለምን አላስብ?
 • እኔ እጨርሰዋለሁ፡፡
 • እኮ እንዴት?
 • ሆቴሉን ተቆጣጥሬዋለሁ፡፡
 • እ…
 • 100 ፐርሰንት፡፡

[አንድ ዳያስፖራ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለ]

 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ እንዴት ናት?
 • እየተመነደገች ነው፡፡
 • ኧረ የምሰማው ነገር አሳስቦኛል፡፡
 • ምን ሰማህ?
 • ይኸው ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ተከስቷል፡፡
 • እኛ ምን እናድርግ ታዲያ?
 • ሐዋሳ ላይም መሬት መንቀጥቀጥ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡
 • ይህ እንግዲህ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፡፡
 • ሰሞኑን ደግሞ በማኅበራዊ ድረ ገጽ የምሰማው ጉድ ነው፡፡
 • በየማኅበር ቤቱ አለመሄድ ነዋ፡፡
 • ኧረ እኔ ፌስቡክን ማለቴ ነው፡፡
 • ፌስቡክ እኮ የወሬኞችና የሥራ ፈቶች ነው፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር አሁን አሁን እኮ ጥሩ የመረጃ ምንጭ ሆኗል፡፡
 • ለመሆኑ ምን ሰምተህ ነው?
 • ይኸው ድሬዳዋ ዓሳ ዘነበ እየተባለ ነው፡፡
 • ለምን ይመስልሃል የዓሳ ሚኒስቴር ያቋቋምነው?
 • እ…
 • ይኼ እንደሚመጣ ቀድመን አውቀን ነበር፡፡
 • እየቀለዱ ነው?
 • የምን ቀልድ ነው? በዕድገት ቀልድ የለም፡፡
 • የምን ዕድገት?
 • ይኼ የህዳሴያችንና የዕድገታችን ውጤት ነው፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ገና ወርቅ ይዘንባል፡፡
 • ወርቃችንማ ተጠርጐ እየተወሰደ ነው፡፡
 • ምን አልክ አንተ?
 • ሰምተዋል፡፡
 • ለማንኛውም ይኼ ዜና ሊያስደስትህ ይገባ ነበር፡፡
 • የእግዚአብሔር ቁጣ ነው እኮ ይኼ፡፡
 • ይኼማ ቁጣ ሳይሆን ደስታ ነው እንጂ፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • መጽሐፍ ቅዱስ አታነብም እንዴ?
 • አነባለሁ ኧረ፡፡
 • ታዲያ እግዚአብሔር ለእስራኤሎች በየቀኑ መና ያዘንብላቸው ነበር እኮ፡፡
 • አዎን እሱን አውቃለሁ፡፡
 • መና የሚያዘንብላቸው ስለሚወዳቸው ነበር፡፡
 • ልክ ነው፡፡
 • ይኸው በእኛም ዕድገት በጣም በመገረሙ ዓሳ ማዝነብ ጀመረ፡፡
 • እና እግዚአብሔር ዓሳ ያዘነበው በዕድገቱ ተገርሞ ነው፡፡
 • በእኛ ዕድገት ብዙ ነገር ይዘንባል፡፡
 • ብዙ ነገር መዝነቡንማ አውቃለሁ፡፡
 • ማለት?
 • የወጣቶች ሊግ፣ የሴቶች ሊግ…
 • እ…
 • የወጣቶች ፎረም፣ የሴቶች ፎረም፣ የባለሀብቶች ፎረም…
 • እያሽሟጠጥክ ነው፡፡
 • በእናንተ ጊዜ ያዘነባችኋቸውን ነገሮች እየነገርኩዎት ነው እንጂ፡፡
 • ወሬኛ ነገር ነህ፡፡
 • ይኸው ሰሞኑን ደግሞ ሌላ ነገር ማዝነቡን ተያይዛችሁታል፡፡
 • ምን?
 • ደላላ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ስብሰባው አለቀ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
 • የምኑ ስብሰባ?
 • የመሪዎቹ ስብሰባ፡፡
 • ተሸኙ እኮ ወደ አገራቸው፡፡
 • መቼም ጥሩ መዝናኛ ነው፡፡
 • ምኑ ነው መዝናኛው?
 • ስብሰባው ነዋ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ያው በዓመት አንዴ ለሳምንት በደንብ ተዝናንተው ይሄዳሉ፡፡
 • አትሳሳት፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሲጀመር ስብሰባው በዓመት አንዴ ሳይሆን ሁለቴ ነው፡፡
 • ያው ሁሌ በዚህ ሰሞን ነው የሚመጡት ብዬ ነው፡፡
 • ሁለተኛው ደግሞ አንዱ የአፍሪካ አገር ነዋ የሚካሄደው፡፡
 • እናንተም በተራችሁ እንድትዝናኑ?
 • ምን ይላል ይኼ? መዝናናት ሳይሆን ሥራ ነው፡፡
 • እሱን እንኳን ተውት፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ሰሞኑን አይደል እንዴ ጉዱን ያወቅኩት?
 • አልገባኝም፡፡
 • ለሳምንት ዕረፍት የወጣሁት የአንዱ ዲፕሎማት ሾፌር ለመሆን ነበር፡፡
 • እሺ፡፡
 • በቃ የአዲስ አበባ ጭፈራ ቤት አንድ አልቀረኝም፡፡
 • እ…
 • ክቡር ሚኒስትር አዲስ አበባን አውቃታለሁ ብለው ያስባሉ አይደል?
 • በሚገባ እንጂ፡፡
 • እኔ ግን እንደማያውቋት እነግርዎታለሁ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ክቡር ሚኒስትሩ ማሳጅ ቤቱ ቢሉ፣ ሺሻ ቤቱ ቢሉ፣ ገስት ሃውሱ ቢሉ ኧረ ስንቱ፡፡
 • ምንድን ነው የምታወራው?
 • ብቻ ይኼ የስብሰባ ተሳታፊ ነኝ የሚል ሁሉ የሚገኘው እኮ እዛ ነው፡፡
 • እ…
 • እንዲያውም አንዳንዴ የስብሰባው ቦታ የተቀየረ ነው የሚመስለው፡፡
 • ማለት?
 • በቃ ሁሉም ተሳታፊዎች ያሉት በየማሳጅ ቤቱ፣ በየሺሻ ቤቱና በየጭፈራ ቤቱ ነዋ፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ለማንኛውም እርስዎም ሲሄዱ ይዘውኝ ቢሄዱ ደስ ይለኛል፡፡
 • የት?
 • ስብሰባ ሲሄዱ፡፡
 • ሞላጫ!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]    

 • መቼም የሙጋቤን ንግግር ተከታትለኸዋል?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ልክ ልካቸውን እኮ ነው የነገረልኝ፡፡
 • እነ ማንን?
 • ኒዮሊብራሎቹን ነዋ፡፡
 • እሱ እኮ ሁሌም ነው የሚናገረው፡፡
 • ከእንግዲህ ግን ቀልድ የለም ብሏል፡፡
 • የምን ቀልድ?
 • የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤቱ ውስጥ መግባት አለብን፡፡
 • እንዲህ በቀላሉ፡፡
 • እኮ አሁን መዘጋጀት አለብን፡፡
 • ለምኑ?
 • ምክር ቤቱ እኛ እንድንገባ ኒዮሊብራሎቹ አይፈልጉም፡፡
 • እሱማ የታወቀ ነው፡፡
 • ስለዚህ በራሳችን እናቋቁማለን፡፡
 • ምንድን ነው የምናቋቁመው?
 • የራሳችንን የተባበሩት መንግሥታት፡፡
 • እየቀለዱ ነው?
 • በዚህ ቀልድ የለም፡፡
 • እና ምን ይደረግ?
 • ኮሚቴ ይቋቋም፡፡
 • የምን ኮሚቴ?
 • የራሳችንን የተባበሩት መንግሥታት የሚያቋቁም ኮሚቴ፡፡
 • ኮሚቴ ግን አልበዛም?
 • አየህ ኮሚቴ ሲኖር ግልጽነትና ተጠያቂነት ይኖራል፡፡
 • ስለዚህ ኮሚቴው እንዴት ይዋቀር?
 • ያው እንደተለመደው ከሴቶች ፎረም፣ ከወጣቶች ፎረም፣ ከነጋዴዎች ፎረም … የተውጣጡ ይሁኑ፡፡
 • የብሔር ተዋፅኦስ?
 • እሱማ ጥያቄ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡
 • የኮሚቴው ሥራ ምንድን ነው የሚሆነው?
 • ኮሚቴው በአዲሰ አበባ ያሉ ዲፕሎማቶችን የማሳመን ሥራ ይሠራል፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይህን ለማድረግ ደግሞ ዲፕሎማቶችን እናደራጃቸዋለን፡፡
 • በምን?
 • በአንድ ለአምስት!