ክቡር ሚኒስትር

[የገና በዓል ደርሷል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሮ የመጡት ሥራ ለመሥራት ሳይሆን የመጣላቸውን ስጦታ ለመቀበል ነው፡፡ ቢሮ እንደገቡ ጸሐፊያቸውን ጠሯት]
- እንኳን አደረሰዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንኳን አደረሰሽ፡፡
- ይህ ለእርስዎ የመጣ ነው፡፡
- ምንድን ነው ይህ ሁላ የወረቀት ክምር?
- ስጦታ ነው፡፡
- የምን ስጦታ?
- የበዓል ስጦታ ነዋ፡፡
- ፖስት ካርድ ብቻ ምን ያደርጋል? ሌላ ስጦታ አልመጣልኝም?
- አንድ ድርጅት ወይን ልኮልዎታል፡፡
- አንድ ብቻ?
- አዎን፡፡
- ሰው ምን ሆኗል?
- ፖስት ካርድ ብቻ ሆነብዎት አይደል?
- እኔ ፍቅረኛቸው አይደለሁ ይህንን ሁሉ ፖስት ካርድ የሚልኩልኝ፡፡
- ለነገሩ ፖስት ካርድ ቢከመር ኪስ አይሞላ፡፡
- ምን?
- አይ ማለቴ ከፖስት ካርድ ይልቅ የሚጠቅም ነገር ቢልኩ ይሻላል ብዬ ነው፡፡
- በጣም የሚገርም ጊዜ ላይ ነው የደረስነው፡፡
- ለነገሩ በእነዚህ ፖስት ካርዶች አንድ ነገር ማድረግ ይችላሉ፡፡
- ምን ማድረግ?
- የጊፍት ሾፕ መክፈት፡፡
- መቀለዱ ነው፡፡
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እስቲ አማካሪዬን ጥሪው፡፡
- እሺ፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
- ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- አገሪቷ ወዴት እየሄደች ነው?
- ምን?
- ማለቴ ሕዝቡ ወዴት እየሄደ ነው?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ባህላችን ተረሳ እንዴ?
- የምን ባህል?
- የስጦታ ባህላችን፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ይህን ክምር ታየዋለህ?
- የምን ክምር ነው?
- የፖስት ካርድ ክምር፡፡
- የበዓል ስጦታ መሆኑ ነው?
- ግራ እኮ ነው የገባኝ፡፡
- ስጦታ በመቀነሱ ነው?
- ሰው ስግብግብ ሆነ እንዴ?
- ሐሳብዎት ይገባኛል፡፡
- እንዴት?
- አገሪቱ በ11 በመቶ እያደገች በመሆኑ ስጦታውም በዚያው መጠን ማደግ ነበረበት እያሉ ነው አይደል?
- አሽሙርኛ ነገር ነህ፡፡
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ ያልኩህ የገና በዓል የስጦታ መስጫ በዓል በመሆኑ ስጦታው ስለቀነሰ፣ ሰው ምን ነካው ብዬ ነው፡፡
- ለነገሩ ክቡር ሚኒስትር ስጦታው እኮ ብዙ ነው፤ ያነሰው የስጦታው ዋጋ ነው፡፡
- ከተማው ውስጥ ቢዝነስ ተቀዛቅዟል እንዴ?
- እሱም ሌላኛው ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
- እኔ እኮ የማይገባኝ አንድ ካሬ ሜትር 305 ሺሕ ብር እየተሸጠ ቢዝነስ ተቀዛቅዟል ሊባል ነው?
- ለዚህማ ተጠያቂው መንግሥት ነው፡፡
- እንዴት?
- ቢዝነሱ ሲቀዘቅዝበት ለማሞቅ የሚያደርገው አካሄድ ነው፡፡
- መልስ አታጣ መቼም?
- አይ ያው ሲያወሩ የሰማሁትን ነው የነገርኩዎት፡፡
- ወሬኛ፡፡
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ አንድ ወዳጅ ከውጭ ደወለላቸው]
- እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንኳን አደረሰህ ወዳጄ፡፡
- በዓል እንዴት ነው?
- በዓል ጥሩ ነው፤ እናንተስ ጋ እንዴት ነው?
- እዚህማ ምን አለ ብለው ነው? የአገር ቤቱ ነው ደስ የሚለው፡፡
- እሱስ ልክ ነህ፤ አንዳንዴ ግን የእናንተም ደስ ይላል፡፡
- እንዴት?
- በቃ ምንም ጣጣ የለብህማ፡፡
- የምን ጣጣ?
- በግ፣ በሬ፣ ዶሮ፣ ስጦታ ምናምን፡፡
- እኛ ግን እሱ ነው የሚናፍቀን፡፡
- ይህማ የሰው ባህሪ ነው፡፡
- እንዴት?
- ሁሌም የሌለንን ነው የምንፈልገው፡፡
- ለማንኛውም ስጦታ ልኬልዎታለሁ፡፡
- ምን ፖስት ካርድ?
- ለገና እኮ ፖስት ካርድ የግድ ነው፡፡
- እና ፖስት ካርድ ነው የላክልኝ?
- አይ እንዲያው የበግ መግዣ እንድትሆን አንድ ሺሕ ዶላር ልኬልዎታለሁ፡፡
- ስንት አልከኝ?
- አንድ ሺሕ ዶላር፡፡
- ታዲያ የበሬ መግዣ ነዋ?
- በሬ ትገዛለች ብለው? ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ ኑሮ ተወዷል ይባላል?
- ቢሆንም ይኼ እንኳን በሬ ሳይገዛ አይቀርም፡፡
- ለማንኛውም ባለቤትዎን ሰላም በሉልኝ፡፡
- በጣም አመሰግናለሁ፡፡
- መልካም በዓል፡፡
- ለአንተም መልካም በዓል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ባለቤታቸው ጋ ደወሉ]
- ደህና ዋልክ?
- መልዕክት አለሽ፡፡
- የምን መልዕክት?
- ያ ወዳጃችን ደውሎ ነበር?
- ምን አለ?
- እንኳን አደረሰሽ ብሎሻል፡፡
- ብቻ?
- የበግ መግዣም ልኳል፡፡
- እውነት?
- አዎ፡፡
- ስንት ላከ?
- አንድ ሺሕ ዶላር፡፡
- እግዚአብሔር ይስጠው፡፡
- የት ነው ያለሽው?
- ገበያ ነኝ፡፡
- ምን ልታደርጊ?
- የልጆቹን ስጦታ ልገዛ ነዋ፡፡
- ምሳ እኮ ቤት እመጣለሁ፡፡
- እኔም እደርስብሃለሁ፡፡
- በይ ጥሩ ስጦታ ግዥላቸው፡፡
- እሺ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እየሄዱ ነው]
- እንዴት ነው በዓሉ?
- የምን በዓል ክቡር ሚኒስትር?
- የገና ነዋ፡፡
- በዓል ድሮ ቀረ፡፡
- እንዴት?
- አሁንስ ይህ በዓል የሚባለው ነገር ባይመጣ ይሻላል፡፡
- ለምን?
- ክቡር ሚኒስትር ወጪው እኮ አይቻልም፡፡
- እሱስ ልክ ነህ፡፡
- መለስተኛ በግ እኮ ሁለት ሺሕ ብር ነው፡፡
- እርካሽ ነው ማለት ነው፡፡
- ለእርስዎ እርካሽ ሊሆን ይችላል፡፡
- እ…
- ሁለት ሺሕ ብር የልጆቼን የትምህርት ቤት ይሸፍናል፡፡
- ለነገሩ በዓል እኮ ትርፉ ወጪ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የደመወዛችን ነገር ይታሰብበት፡፡
- እንዴት ማለት?
- ጭማሪ ይደረግልና፡፡
- ለበዓል ተብሎ?
- ኧረ በአጠቃላይ ኑሮ ከብዷል፡፡
- ኑሮ መወደዱን እንኳን እኔም እያየሁት ነው፡፡
- እርስዎስ ጋ በዓል እንዴት ነው?
- ወጪ በዛ፡፡
- ገቢውስ?
- እ…
- ይተውት፡፡
- ልጆቼ ራሳቸው ስጦታ ይፈልጋሉ፡፡
- የምን ስጦታ?
- የበዓል ነዋ፡፡
- ምንድን ነው የሚሰጧቸው?
- ለትንሿ ልጄ ሳይክል፡፡
- እ…
- ለትልቁ ደግሞ ምን ስቴሽን ነው የሚሉት?
- ጋዝ ስቴሽን፡፡
- ምን አልከኝ?
- ፕሌይ ስቴሽን፡፡
- አዎ፡፡ አንተ ለልጆችህ ስጦታ አትሰጣቸውም እንዴ?
- እኔማ አንዴ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ሰጥቼ ጨርሻለሁ፡፡
- ምን ሰጠኸቸው?
- ደርዘን ደብተርና ዩኒፎርም፡፡
- ታዲያ ለበዓል ምን አስበሃል?
- ቅርጫ እገባለሁ፡፡
- የበሬ ቅርጫ?
- ኧረ አይደለም፡፡
- ታዲያ የምን ቅርጫ ነው?
- የበግ?
- የበግ?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እየቀለድክ ነው?
- ይኼንንም በግ ፀድቆብኝ ነው አለ፡፡
- የበግ ቅርጫ አለ እንዴ?
- ኧረ ከዚያም የባሰ አለ?
- ከዚህ የባሰ ደግሞ ምን?
- የዶሮም አለ፡፡
- እ…
- ኑሮ ከብዷል እኮ?
- እኔ ግን ቅርጫ መግባት እፈልግ ነበር፡፡
- ተጨማሪ ቅርጫ?
- መቼ ገባው ብለህ ነው?
- ትልቁን ቅርጫ ረሱት እንዴ?
- የቱን?
- የአገር ቅርጫውን፡፡