ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ከጸሐፊያቸው ጋ እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር ያው የተለመደው ጊዜ ደርሷል፡፡
 • የምን የተለመደ ጊዜ ነው?
 • እርስዎ የሚወዱት ጊዜ ነዋ፡፡
 • እኔ ደግሞ የምወደው ጊዜ የቱ ነው?
 • የበዓል ጊዜ ነዋ፡፡
 • እኔ እንደ በዓል የምጠላው ነገር የለም እኮ፡፡
 • ያው እንትኑን ይወዱታል ብዬ ነው፡፡
 • ምኑን?
 • ስጦታውን፡፡
 • ስጦታ መምጣት ጀመረ እንዴ?
 • ይኸው አሁን ያጨናነቀኝ ነገር እሱ ነው፡፡
 • በይ የተለመደው ሥራሽን እንዳትዘነጊ፡፡
 • የምን ሥራ?
 • የመለየቱን ነዋ፡፡
 • ምኑን ነው የምለየው?
 • ስጦታውን፡፡
 • እንዴት ነው የምለየው?
 • የኪራይ ሰብሳቢውን ከልማታዊው፡፡
 • እሱማ ተለይቷል፡፡
 • ስለዚህ የልማታዊውን ታስቀሪልኛለሽ፡፡
 • የኪራይ ሰብሳቢውንስ?
 • እሱን ትመልሺልኛለሽ፡፡
 • ስጦታውን ቢያዩት ግን ሐሳብዎትን የሚቀይሩ ይመስለኛል፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • የልማታዊዎቹ ስጦታ እኮ ፖስት ካርድ ብቻ ነው፡፡
 • የኪራይ ሰብሳቢዎቹስ?
 • የእነሱማ ከዶሮ እስከ በሬ ይደርሳል፡፡
 • እና የልማታዊዎቹ ስጦታ ካርድ ብቻ ነው እያልሽኝ ነው?
 • እህሳ?
 • አየሽ ልማታዊዎቹ የሚጐድላቸው እኮ ይኼ ነው፡፡
 • ምንድን ነው የሚጐድላቸው?
 • ከኪራይ ሰብሳቢዎቹ መማር ያለባቸው ነገር አለ፡፡
 • ልማታዊው ከኪራይ ሰብሳቢ ምን ሊማር ይችላል?
 • ለምሳሌ ስጦታ አሰጣጥ፡፡
 • ልማታዊ ስጦታ የሚባል ነገር የለማ፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው የሚባለው?
 • ሙስና!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው አስጠሩት]

 • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • እዚህ ጋዜጣ ላይ የወጣውን ዜና አንብበኸዋል?
 • የትኛውን ዜና?
 • የውጭ ምንዛሪ እጥረት የኤምባሲዎቻችንን ሥራ እያወከ ነው የሚለውን ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እሱ ችግር እኮ አንገብጋቢ ነው፡፡
 • እኔ ያልገባኝ እኮ አንድ ነገር ነው፡፡
 • ምንድን ነው ያልገባዎት?
 • ኤምባሲዎቻችን ንግድ ውስጥ ገብተዋል እንዴ?
 • እ…
 • ማለቴ የሚያስገቡት ዕቃ አለ?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ንግድ ውስጥ ካልገቡ የውጭ ምንዛሪ ምን ያደርግላቸዋል?
 • የገባዎት አልመሰለኝም፡፡
 • ምኑ?
 • ኤምባሲዎች የሥራ ማስኬጃዎችን ጨምሮ ለሠራተኞቻቸው በውጭ ምንዛሪ ነው የሚከፍሉት፡፡
 • ለምን በብር አይጠቀሙም?
 • ያው ብር ውጭ አገር ስለማይሠራ ነዋ፡፡
 • አሁን እኛም መደራደር አለብና፡፡
 • ምን ብለን?
 • ብር ውጭ አገር ካልሠራ ዶላር እዚህም አገር አይሠራም ብለን ነዋ፡፡
 • እየቀለዱ ነው?
 • በአገር ቀልድ የለም፡፡
 • እኛ እኮ ኢኮኖሚያችን ገና ታዳጊ ነው፡፡
 • ይኸው ዓለም ላይ ኢኮኖሚው እንደ እኛ እያደገ ያለ አገር እኮ የለም፡፡
 • ቢሆንም ያደጉት አገሮች ላይ ለመድረስ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡
 • ሌላው የገረመኝ የኤምባሲ ሠራተኞቹ የመንግሥት ሠራተኛ ሆነው እንዴት በውጭ ምንዛሪ ደመወዝ ይከፈላቸዋል?
 • ታዲያ በምን ይከፈላቸው?
 • ሌላው ሠራተኛ እንደሚከፈለው በብር ነዋ፡፡
 • ውጭ እየኖሩ?
 • እኔም እኮ በውጭ ምንዛሪ እንዲከፈለኝ እፈልጋለሁ፡፡
 • እዚህ እየኖሩ?
 • ምን አለበት?
 • አይቻልማ፡፡
 • ስለዚህ መፍትሔው አንድ ነው፡፡
 • ምንድን ነው?
 • ሥራዬን ውጭ አገር ሆኜ መሥራት፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ሚኒስትር ደወሉላቸውና ተገናኙ]

 • ክቡር ሚኒስትር ሥራ እንዴት ነው?
 • ይኸው ተያይዘነዋል፡፡
 • የዚህ የመልካም አስተዳደር ችግር ግን አንገብጋቢ እየሆነ ነው፡፡
 • አንገብጋቢ መሆኑንማ በየጊዜው እየገለጽን ነው፡፡
 • አሁን ሰው የሰለቸው አሱ ነው፡፡
 • ምንድን ነው የሰለቸው?
 • ወሬ ብቻ ሆነ፡፡
 • እና ምን ይደረግ?
 • ዕርምጃ መውሰድ ነዋ፡፡
 • እየወሰድን አይደል እንዴ?
 • ማን ላይ ነው ዕርምጃ የተወሰደው?
 • የፀረ ልማት ኃይሎች ላይ ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ችግሩ እኮ የመልካም አስተዳደር ነው፡፡
 • እሱማ አውቃለሁ፡፡
 • ስለዚህ ማላከኩን ማቆም አለብን፡፡
 • የምን ማላከክ?
 • የችግሩን መንስዔ፡፡
 • ፀረ ልማቶችን ግን አንታገሳቸውም፡፡
 • ራሳችንን ግን እንመርምር፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ካድሬዎቻችን ምን እያደረጉ እንደሆነ አያውቁም እንዴ?
 • ምን እያደረጉ ነው?
 • በአጭር መንገድ እየከበሩ ነው፡፡
 • እኔ የሚገርመኝ ሰው ሲያድግ ግን ሰው አይወድም ማለት ነው?
 • ማደጉ እኮ አይደለም ችግሩ፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው ችግሩ?
 • የሚያድጉበት መንገድና ፍጥነት ነዋ፡፡
 • አገራችንም በፈጣን ዕድገት ውስጥ መሆኗ ችግር አለው እያልከኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ያ ሌላ ይኼ ሌላ፡፡
 • እሺ ምን ይደረግ?
 • መጠየቅ ያለበት ይጠየቅ፡፡
 • እ…
 • መቀጣት ያለበት ይቀጣ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ጋ አንድ ደላላ ባለሀብት ደወለ]

 • ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ልታዘዝ?
 • አንድ ሐሳብ አለኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • ሙሉ አዲስ አበባን ለምን አትሰጡኝም?
 • ምን ልታደርጋት?
 • ላለማት ነዋ፡፡
 • እየቀለድክ ነው?
 • ኧረ እውነቴን ነው፡፡
 • ሙሉ አዲስ አበባን ለአንድ ሰው ልንሰጥ?
 • ምን አለበት?
 • ለአንድ ሰው እንዴት ይኼ ሁሉ ቦታ ይሰጣል?
 • ስንተዋወቅ አንተናነቃ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ይኸው ለህንዱ ኩባንያ ሁለት አዲስ አበባን የሚያክል ቦታ አይደል እንዴ የሰጣችሁት?
 • የተሰጠው እኮ 100 ሺሕ ሔክታር ነው፡፡
 • ያ ማለት እኮ ሁለት አዲስ አበባን ለመሆን ስምንት ሺሕ ሔክታር የጐደለው ማለት ነው?
 • ታዲያ ፈረንጆቹ እውነታቸውን ነዋ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ኢትዮጵያ ውስጥ የመሬት ወረራ አለ የሚሉት?
 • እሱን እርስዎ አሉ፡፡
 • እንዲህ አስቤው ስለማላውቅ ነው፡፡
 • ለእኔ ግን አንድ አዲስ አበባን ቢሰጡኝ አለማታለሁ፡፡
 • እሱስ ታለማለህ፡፡
 • ይህን ካደረጉ ሌላም አለማለሁ፡፡
 • ሌላ ምን ልታለማ?
 • እርስዎን!

[አንድ የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ከውጭ ደወለ]

 • ክቡር ሚኒስትር የህንዱ ባለሀብት ላይ የወሰዳችሁት ዕርምጃ አስደስቶኛል፡፡
 • ጊዜው የሥራ ነው፡፡
 • ለነገሩ ታግሳችሁታል፡፡
 • ስድስት ዓመት ታገስን፡፡
 • እና አሁን ትግስታችሁ አለቀ፡፡
 • ከስድስት ዓመት በላይ መታገስ አንችልም፡፡
 • ግን እኮ አሥራ ምናምን ዓመታት የታገሳችኋቸው አሉ፡፡
 • እ…
 • ወይስ ትግስታችሁም ይከፈላል?
 • ምን ተብሎ?
 • ልማታዊና ኪራይ ሰብሳቢ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸው አገኟቸው]

 • ግቢው እኮ እንዲሁ ሲበጠበጥ ዋለ፡፡
 • በምንድን ነው የተበጠበጠው?
 • በላካቸው ከብቶች ነዋ፡፡
 • እኮ ምን አበጣበጣቸው?
 • ቦታ ነዋ፡፡
 • እንዴት?
 • እንደምታየው በሬ ሰፊ ቦታ ይፈልጋል፡፡
 • እሺ፡፡
 • ፍየሎቹ ደግሞ ቦታ ጠበበን ብለው ከበሬው ጋር ሁከት ገጠሙ፡፡
 • በጐቹስ?
 • በጐቹማ በሬው ሰፊ ቦታ ይዟል በሚል ፍየሎቹ ከበሬው ጋ እንዲጋጩ የሚያነሳሱት እነሱ ነበሩ፡፡
 • ዶሮዎቹስ?
 • እነሱ ደግሞ ሌሎቹ ሲጋጩ እየተንጫጩ ግቢውን ሲያምሱት ነበር፡፡
 • የሚገርም ተንታኝ ሆነሽልኛል፡፡
 • ምን ላድርግ?
 • ለዚህ ሥራሽ የሚገባሽን አውቃለሁ፡፡
 • ምንድን ነው የሚገባኝ?
 • ሽልማት፡፡
 • ማን ይሸልመኛል?
 • የሽልማት ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት!