ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ጽንፈኛ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ናቸው፡፡ ቢሯቸው ተናደው ገብተው አማካሪያቸው አገኛቸው]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆንክ?
 • የተናደዱ ይመስላሉ፡፡
 • ተሸንፈን ነዋ፡፡
 • ምርጫ ነበር እንዴ?
 • የምን ምርጫ ነው የምታወራው?
 • ያው ሰሞኑን አገሪቷ ውስጥ ብጥብጥ ስለነበር ምርጫ ሳልሰማ ተካሂዶ ከሆነ ብዬ ነው፡፡
 • ቡድናችን ነው የተሸነፈው እባክህ፡፡
 • ኢሕአዴግ?
 • ኧረ እግር ኳስ ነው የምልህ?
 • ብሔራዊ ቡድናችን ጨዋታ ነበረው እንዴ?
 • የለም የለም፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፡፡
 • የማንቸስተር ደጋፊ ነዎት እንዴ?
 • ያውም ቀንደኛው ነኛ፡፡
 • የአፍሪካ ቀንድ ላይ ስላሉ ነው ቀንደኛ የሆኑት?
 • ምን ይላል ይኼ? ስለኳስ ምንም አታውቅም እንዴ?
 • ብዙም አይደለሁም፡፡
 • ለማንኛውም ችግሩን ደርሼበታለሁ፡፡
 • የምኑን ችግር?
 • የማንቸስተር ዩናይትድን ችግር ነዋ፡፡
 • ምንድን ነው ችግሩ?
 • ከፍተኛ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር አለ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • አሠልጣኙ ኪራይ ሰብሳቢ ናቸው፡፡
 • እንዴት?
 • ተጨዋች በውድ ዋጋ ይገዛሉ እንጂ ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም፡፡
 • ተጨዋች እንዴት ነው የሚገዙት?
 • በደላላ ነዋ፡፡
 • የደላላነት ችግርም አለ እያሉኝ ነው?
 • ዋነኛው ችግር እንዲያውም እሱ ነው፡፡
 • የሚገርም ነው፡፡
 • ከዚያም በላይ ግን የመልካም አስተዳደር ከፍተኛ ችግር አለ፡፡
 • ምን ዓይነት ችግር?
 • አንዳንድ አላስፈላጊ ወጪዎችን ያወጣሉ፡፡
 • ለምሳሌ ምን?
 • የተጨዋቾች የልምምድ ሜዳ ላይ የሴኪዩሪቲ ካሜራ አስገጥመዋል፡፡
 • ሀብት ያለአግባብ ያባክናሉ እያሉኝ ነው?
 • ምናልባትም በካሜራው ግዢ ኮሚሽን ያገኛሉ፡፡
 • ሌላስ ምን ችግር አለባቸው?
 • በክለቡ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት አለ፡፡
 • የምን የዋጋ ግሽበት?
 • ባለፈው 20 ፓውንድ የገዛሁት ማሊያ አሁን 100 ፓውንድ ገብቷል፡፡
 • እውነትዎትን ነው?
 • እሱ ብቻ መሰለህ?
 • እሺ ሌላ ምን አለ?
 • የትኬት ዋጋ ራሱ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡፡
 • ስታዲየማቸውም ይገባሉ እንዴ?
 • እዚያ ስሄድ ጨዋታ ሳላይ አልመጣም፡፡
 • ለስብሰባ መስሎኝ የሚሄዱት?
 • ያው ከስብሰባው ጐን መዝናናት መቼ ይቀራል?
 • ለማንኛውም አደገኛ ደጋፊ እንደሆኑ ገብቶኛል፡፡
 • ጽንፈኛ ደጋፊ ነኝ፡፡
 • አለብዎት እንዴ?
 • ምን?
 • አክራሪነት!

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ባለሀብት ደወለላቸው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • እንኳን አደረሰዎት፡፡
 • ለምኑ?
 • ለክሪስመስ፡፡
 • እኔ መቼ የእነሱን በዓል አከብራለሁ ብለህ ነው?
 • ምን አለበት ክቡር ሚኒስትር?
 • የኒዮሊብራሎች ምንም ነገር አይመቸኝም፡፡
 • ታዲያ ልጅዎትን ለምን ላኳት?
 • የት?
 • እነሱ ጋ ነዋ፡፡
 • እ…
 • ነገሩ ለትምህርት እንደላኳት አውቃለሁ፡፡
 • ምን ላድርግ ብለህ ነው?
 • ለማንኛውም ዛሬ የደወልኩት በእሷ ምክንያት ነው፡፡
 • እንዴት?
 • የትምህርት ቤት ክፍያዋ እኮ ደርሷል፡፡
 • ማን ብዬ ልጥራው ስምህን?
 • አስታዋሼ ነዋ፡፡
 • ይኼ ነው እኮ ቁም ነገሩ፡፡
 • እንዴት?
 • አንተ የእኔን ጉዳይ ስታስታውስ፣ እኔ ደግሞ የአንተን ጉዳይ አስታውሳለሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር፣ እንደ እርስዎ ዓይነት ባለሥልጣን ነው እኮ የጠፋው?
 • ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም ይላሉ፡፡
 • ልክ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ እኔ ምን ልርዳህ?
 • ያው በአዲሱ ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶች ይዤ እመጣለሁ፡፡
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • ስለዚህ ለፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልጉኝ ነገሮች እንዲጨርሱልኝ እፈልጋለሁ፡፡
 • ምንድነው የምትፈልገው?
 • በዋናነት መሬት ነው፡፡
 • ከአንተ የሚፈለገው ይኼን ያህል መሬት ብቻ ማለት ነው፡፡
 • እኔ እኮ አንዳንዴ ሳስበው ይገርመኛል፡፡
 • ምኑ ነው የሚገርምህ?
 • እርስዎ ባይኖሩ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዴት ሊቀረፍ ይችላል ብዬ ሳስብ ይገርመኛል፡፡
 • እዚህ ያለሁት እኮ እሱን ለመፍታት ነው፡፡
 • ስለዚህ የመሬቱ ጉዳይ ችግር የለውም እያሉኝ ነው?
 • የምትፈልገው ኪስ ቦታ ነው?
 • ምን አሉኝ?
 • ወይስ ግንባር ቦታ ነው የምትፈልገው?
 • ወይ ክቡር ሚኒስትር?
 • ወይስ ዓይን ቦታ ነው የምትሻው?
 • ምን ላድርግዎት?
 • ንገረኝ ወይስ ገዢ ቦታ ልስጥህ?
 • ገዢው ፓርቲ ነው ያሉኝ?
 • በእሱ አትምጣብኝ፡፡
 • ይቅርታ ስላልሰማሁዎት ነው፡፡
 • ገዢ ቦታ እሰጥሃለሁ፡፡
 • እኔም ምላሹን እሰጣለሁ፡፡
 • ምን?
 • ገዢ ገንዘብ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ልማታዊ ነው ብለው የሚያስቡት ተቃዋሚ ደወለላቸው] 

 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቷ ውስጥ ምን እየተሠራ ነው?
 • ግድብ፡፡
 • የለም የለም፡፡
 • ባቡር፡፡
 • አልገባዎትም፡፡
 • የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፡፡
 • ምን ይላሉ?
 • የከረጢትና የስኳር ፋብሪካዎች፡፡
 • ደግሞ እናንተ ስኳር መላስ እንጂ ስኳር ፋብሪካ መገንባት ታውቃላችሁ እንዴ?
 • እየተሳደብክ ነው?
 • መተንፈሻ አሳጣችሁን፡፡
 • የምን መተንፈሻ?
 • ፓርላማውን መቶ ፐርሰንት ያዛችሁት፡፡
 • ተመርጠን፡፡
 • ሚዲያውን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠራችሁት፡፡
 • የራሳችሁን ማቋቋም ነዋ፡፡
 • ለማንኛውም የሰሞኑም ብጥብጥ እኮ የተነሳው ሕዝቡ መተንፈሻ ስላጣ ነው፡፡
 • ምነው ሩጫ ጀመርክ እንዴ?
 • ለምን እንደዚያ አሉ?
 • ስለትንፋሽ ብዙ አወራህ፡፡
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር በሚገባ ይታሰብበት፡፡
 • ምኑ?
 • የመልካም አስተዳደር ችግሩ፡፡
 • እያሰብንበት ነው፡፡
 • ማሰብ ብቻ ሳይሆን መፍታትም ያስፈልጋል፡፡
 • እኔ እኮ ፖሊስ አይደለሁም የማስረው የምፈታው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እየቀለድኩ አይደለም፡፡
 • እኔ በእናትህ አታስጨንቀኝ፤ ጭንቀት አልወድም፡፡
 • እኔ አይደለሁም ያስጨነኩዎት፡፡
 • ታዲያ ማን ነው?
 • ሥራዎት!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት] 

 • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • የሰሞኑን የመንግሥት መግለጫ ተከታትለሃል?
 • የትኛውን መግለጫ?
 • በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠውን፡፡
 • አዎን ተከታትዬዋለሁ፡፡
 • ተወረናል እኮ፡፡
 • ጦርነት ተጀመረ እንዴ?
 • የለም የለም፡፡
 • ወረርሽኝ በሽታ ገባ?
 • አንተንስ የፀረ ልማት ኃይሎች ይውረሩህ፡፡
 • ማን ነው የወረረን ታዲያ?
 • ጋኔኖች፡፡
 • የምን ጋኔን?
 • የተለያዩ ዓይነት ጋኔኖች አሉ፡፡
 • እስቲ ይንገሩኝ፡፡
 • የሙስና ጋኔን አለ፡፡
 • እሺ፡፡
 • የኪራይ ሰብሳቢ ጋኔን አለ፡፡
 • ሌላስ?
 • የደላሎች ጋኔን አለ፡፡
 • ጉድ ነው፡፡
 • የጽንፈኛና የአክራሪዎች ጋኔን አለ፡፡
 • ቀጥሉ፡፡
 • የተቃዋሚዎች ጋኔን አለ፡፡
 • ስለዚህ ብዙ ዓይነት ጋኔኖች አሉ እያሉኝ ነው?
 • እሱን እኮ ነው የምልህ፡፡
 • የመንግሥትስ ጋኔን አለ?
 • አይጠፋም ሊኖር ይችላል፡፡
 • ፈርቼ እኮ ነው፡፡
 • ምንድን ነው የፈራኸው?
 • እርስዎ እንዳይኖርብዎት፡፡
 • ወሬኛ ያልተጠየከውን አታውራ፡፡
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም በሁለተኛው ጂቲፒ ውስጥ መካተተ አለበት፡፡
 • ምኑ?
 • ይኼ ጋኔን የማስወጣት ሥራው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እየቀለዱ አይደለም አይደል?
 • ስማ ጋኔን ማስወጣት ቀልድ አይደለም፡፡
 • ስለዚህ ምን ይደረግ?
 • አንድ አዲስ ዳይሬክቶሬት ይቋቋም፡፡
 • ምን የሚሉት?
 • ጋኔን አስወጪ!