ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ አረፋፍደው ቢሮ ሲገቡ ጸሐፊያቸውን አገኟት]

 • ክቡር ሚኒስትር ምነው አረፈዱ?
 • ብለሽ ብለሽ እኔን መቆጣጠር አማረሽ?
 • አይ ልቆጣጠርዎት ፈልጌ እንኳን አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምን ፈልገሽ ነው?
 • እንግዶች ነበሩዎት ብዬ ነው፡፡
 • የምን እንግዳ?
 • የውጭ ኢንቨስተሮች፡፡
 • ቀጠሮ ነበራቸው?
 • ቀጠሮ እንኳን አልነበራቸውም፡፡
 • ታዲያ ምን ፈልገው መጡ?
 • አይ አገራቸው ሊሄዱ ስለሆነ ነው፡፡
 • እና እኔ ቪዛ ሰጪ ነኝ አሏቸው?
 • የለም ስጦታ ይዘው መጥተው ነው፡፡
 • የምን ስጦታ?
 • የገና ስጦታ፡፡
 • ገና ደረሰ እንዴ?
 • የፈረንጆች ገና ደርሷል፡፡
 • እና እኔ ምን አገባኝ?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ የኒዮሊበራሎችን ገና ምን ቆርጦኝ ነው የማከብረው?
 • ያው በዚህ በዓል ስጦታ የመስጠት ባህል ስላላቸው ነው፡፡
 • ነገርኩሽ እኮ እኔ የኒዮሊብራሎችን ባህል አላከብርም፡፡
 • ስለዚህ ስጦታው ይመለስ?
 • እ…
 • ስጦታውን ልመልስላቸው ወይ?
 • ለመሆኑ ምንድነው ያመጡት?
 • ወይን ነው፡፡
 • የምን አገር ወይን?
 • የፈረንሣይ ወይን ነው፡፡
 • እኮ እኔ የኒዮሊብራሎችን ወይን ልጠጣ?
 • ምን አለበት?
 • እኔ ኪራይ ሰብሳቢ አይደለሁማ፡፡
 • የአገራችን ቢሆን ይጠጡት ነበር?
 • አዎና፡፡
 • ለምን?
 • የአገራችን ልማታዊ ወይን ነዋ፡፡
 • ለማንኛውም ኬክም አምጥተዋል፡፡
 • እሱንም አልፈልግም፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ነገርኩሽ እኮ እኔ የኒዮሊብራሎችን ኬክ አልበላም፡፡
 • እሱም የኪራይ ሰብሳቢዎች ነው?
 • አዎና፡፡
 • ልማታዊው ታዲያ ምንድነው?
 • ድፎ ዳቦ ነዋ፡፡
 • ባለሥልጣን ግን ስጦታ መቀበል ይችላል?
 • ዋናው ስጦታው አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምኑ ነው?
 • ሰጪው ማን ነው? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰጪው ልማታዊ ነው ወይስ ኪራይ ሰብሳቢ የሚለው ነው ነጥቡ፡፡
 • ስለዚህ ልማታዊና ኪራይ ሰብሳቢ ስጦታም አለ ነው የሚሉኝ?
 • በሚገባ፡፡
 • ስለዚህ ኬክና ወይን የኪራይ ሰብሳቢ ስጦታዎች ናቸው?
 • እህሳ፡፡
 • እኔ የምለው ቤት፣ መኪናና ቼክ የመሳሰሉት ስጦታዎች ምን ዓይነት ስጦታዎች ናቸው?
 • ልማታዊ ስጦታዎች፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ዳያስፖራ ደወለላቸው]

 • እንዴት ነህ ልማታዊው ዳያስፖራ?
 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔማ እየለማሁ ነው፡፡
 • በስንት ፐርሰንት እየለሙ ነው?
 • የእኔ እንኳን ከአሥር ፐርሰንትም ሳይበልጥ አልቀረም፡፡
 • ኧረ አሥር ፐርሰንት ሲያንስብዎት ነው፡፡
 • ያው ከአገሪቷ በላይ ማደጌ ጥያቄ እንዳያስነሳብኝ ነው፡፡
 • እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ቢነሳብዎትም ችግር የለውም፡፡
 • እንዴት የለውም?
 • ጥያቄው ልማታዊ ነዋ፡፡
 • ልማታዊ ዳያስፖራ ይሉሃል እንዲህ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቷ ሰላም ናት ግን?
 • ምን ትሆናለች ብለህ ነው?
 • አይ አንዳንድ ብጥብጦች አሉ ሲባል ሰምቼ ነው፡፡
 • ኧረ በጣም ሰላም ነን፡፡
 • ሁሉም ነገር ሰላም ነው?
 • ይኸው እኔ እንግዲህ ቢሮዬ ነኝ፣ ሕዝቡም መንገድ ላይ በሰላም እየተንቀሳቀሰ ነው፣ መኪኖችም በሰላም እየተጓዙ ነው፣ በአጠቃላይ ሁሉም ሰላም ነው፡፡
 • ሰላም ከሆነ ደስ ይላል፡፡
 • እንዲያውም አሁን በመስኮቴ ምን እያየሁ እንደሆነ ታውቃለህ?
 • ምን እያዩ ነው?
 • ነጭ እርግብ፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር እኔም አረጋግጫለሁ፡፡
 • ምን አረጋገጥክ?
 • አገሪቷ ሰላም መሆኗን፡፡
 • እሱ ነው የምልህ እኮ፡፡
 • ታዲያ የእንግሊዝ መንግሥት ያወጣው ምንድነው?
 • ምን አወጣ?
 • ትራቭል አለርት፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ያው ወደ ኢትዮጵያ ዜጐቻቸው እንዳይጓዙ የሚል መግለጫ ነው፡፡
 • ለምንድነው እንዳይጓዙ ያሉት?
 • ብጥብጥ ስላለ፡፡
 • ወሬኞች በላቸው፡፡ እኔ እኮ የሚገርመኝ አንድ ነገር ነው፡፡
 • ምንድነው የሚገርምዎት?
 • ሰላም ሲኖር ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ብለው ለምን መግለጫ አያወጡም?
 • በጣም የሚያስገርም ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም የማደርገውን እኔ አውቃለሁ፡፡
 • ምን ሊያደርጉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ተመጣጣኝ የሆነ ዕርምጃ እኛም እንወስዳለን፡፡
 • ምን ዓይነት ዕርምጃ?
 • ትራቭል አለርት እናወጣለን፡፡
 • የምን ትራቭል አለርት?
 • ዜጐቻችን ወደ ምዕራቡ ዓለም እንዳይጓዙ ነዋ፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • እዛ ባለው ብጥብጥ እንዳይጐዱ፡፡
 • ይሻላል?
 • ተረቱ እንደዛ ነዋ የሚለው፡፡
 • ምን ይላል?
 • እሾህን በሾህ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ወዳጃቸው ሚኒስትር ጋ ደወሉ]

 • ሰማኸልኝ አይደለ ያወጡትን መግለጫ?
 • የምን መግለጫ ክቡር ሚኒስትር?
 • እነዚህ ኒዮሊብራሎች ያወጡት መግለጫ ነዋ፡፡
 • ምን አሉ ደግሞ?
 • ኢትዮጵያ ውስጥ ብጥብጥ ስላለ ወደዛ እንዳትሄዱ ብለው ዜጐቻቸውን ከለከሏቸው፡፡
 • በቃ አንድ ነገር ኮሽ ሲል ለማራገብ ማን ብሏቸው?
 • አንዳንዴ ደግ መሆን ግን ጥሩ አይደለም ልበል?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኛ ፈረንሣይ እንደዚያ ስትታመስ አንድ ነገር ብለናል?
 • በጭራሽ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዲያውም ለአየር ንብረት ለውጡ ስብሰባ ሄደናል አይደል እንዴ?
 • በሚገባ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ ለዚህ ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ መስጠት አለብን፡፡
 • ለነገሩ እኛ ተመጣጣኝ ሳይሆን ከፍ ያለ ምላሽ በመስጠት ነው የምንታወቀው፡፡
 • ስለዚህ ተመጣጣኝ ሳይሆን ላቅ ያለ ምላሽ እንስጥ ነው የምትለኝ?
 • እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በምን እንጀምር?
 • ያው የእኛ ዜጐች በአብዛኛው የሚወጡት በድንበር ነው፡፡
 • ስለዚህ እነሱ ‘Vigilant’ ሁኑ እንዳሉት ሁሉ እኛም ዜጐቻችን ድንበር ሲሻገሩ እንደ ቆቅ ‘Vigilant’ ሁሉ ማለት አለብን፡፡
 • ያው ‘Crowd’ ያለበትን ቦታ ‘Avoid’ አድርጉ ብለዋል፡፡
 • ስለዚህ የእኛም ዜጐች ድንበር ሲያቋርጡ በቡድን ሳይሆን ነጠላ ነጠላ እየሆኑ ማቋረጥ አለባቸው ማለት አለብን፡፡
 • ለእንግሊዞቹስ ምን ዓይነት ምላሽ እንስጥ?
 • አሁን የእነሱ አገር የጐርፍ ችግር አለ አይደል?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ ለዜጐቻችን ሕይወት ጐርፉ ስለሚያሠጋ እንዳይጓዙ መግለጫ እናውጣ፡፡
 • እምቢ ብለው የሚሄዱ ካሉስ?
 • ቢያንስ ታንኳ ይዘው እንዲሄዱ እንንገራቸው፡፡
 • እ…
 • ያልቻሉት ደግሞ ላይፍ ሴቨር ይዘው ይሂዱ ማለት አለብን፡፡
 • ግን የእኛ ዜጐች ወደዛ ባይጓዙ እነሱ ምን ይጐዳሉ?
 • በአፍጢሙ ሲወድቅ ይመለከታሉ፡፡
 • ምኑ?
 • ኢኮኖሚያቸው፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሰዓት በኋላ ቢሮ ከገቡ በኋላ አማካሪያቸው አርፍዶ ሲገባ አገኙት]

 • ምን ሆነህ ነው ያረፈድከው?
 • ክቡር ሚኒስትር በአገሪቱ ችግር ነው ያረፈድኩት፡፡
 • አገሪቷ እየተመነደገች ባለችበት ወቅት የምን የማርፈድ ችግር ነው የምታወራው?
 • አገር አቀፍ ችግር ነው ልልዎት ፈልጌ ነው፡፡
 • ከፀረ ልማት ኃይሎች ጋር እያበርክልኝ ነዋ፡፡
 • አልገባዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው ያልገባኝ?
 • ለነገርዎ እርስዎ ቤትዎም ጀነሬተር አለ፤ ቢሮዎም ጀነሬተር አለ፡፡
 • ስለእሱ ማውራት ትተህ ባቡር እኮ የተገጠመው እንዲህ ዓይነት የማርፈድ ሰበብ ላለመስማት ነው፡፡
 • ባቡሩ እኮ ነው ችግሩ፡፡
 • ጭራሽ ባቡሩ ነው ችግሩ ትለኛለህ?
 • አዎን ኤሌክትሪክ ተቋርጦ መሀል ላይ ቆመ፡፡
 • ምን?
 • አዎን፣ ከዛም ታክሲ ማግኘት ስላልቻልኩ በእግሬ ነው የመጣሁት፡፡
 • እና ባቡሩ ቆሟል እያልከኝ ነው?
 • ኤሌክትሪክ ከሌለ ታዲያ በምን ይሠራል?
 • ለምን በከሰል አይሠራም?
 • በምን ከሰል?
 • አገር ምድሪቷ ከሰል አይደለች እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር ባቡር የሚሠራበት ከሰል ግን ይለያል፡፡
 • ምን ዓይነት ከሰል ነው?
 • የድንጋይ ከሰል ነው፡፡
 • እኮ ይኼን ሁሉ ድንጋይ ማክሰል ነዋ፡፡
 • የቱን ድንጋይ?
 • በየመንገዱ የፈጠጠውን ድንጋይ ነዋ፡፡
 • ነገሩ በደንብ የገባዎት አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው ያልገባኝ?
 • ከሰል ተጠቅመን ባቡሩን ማንቀሳቀስ አንችልማ፡፡
 • ለምን አንችልም?
 • አየሩን ይበክለዋላ፡፡
 • ነዳጅስ መጠቀም አንችልም?
 • እሱን ደግሞ ዋጋውን አንችለውም፡፡
 • እንዲያውም ሐሳብ መጣልኝ፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • ለወጣቱ አዲስ ሥራ መፍጠር አለብን፡፡
 • እሱማ የሁልጊዜ ዕቅዳችን ነው፡፡
 • ስለዚህ በወጣት ክንፍ ውስጥ አዲስ ክንፍ መመሥረት አለብን፡፡
 • ምን ዓይነት ክንፍ?
 • የባቡር ገፊ ክንፍ!