ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ለብሔር ብሔረሰቦች በዓል ዝግጅት የሚያስፈልጉትን የኅትመት ሥራዎች በሚስታቸው ስም ላለው ማተሚያ ቤት ሰጥተዋል፡፡ ሥራዎቹ ለበዓሉ ቀን እንደሚደርሱ ለማረጋገጥም ሚስታቸው ጋ ደወሉ]

 

 • ሄሎ!
 • አቤት!
 • እንዴት እየሄደልሽ ነው?
 • ምኑ?
 • ሥራዎቹ ናቸዋ፡፡
 • ጥሩ እየሄዱ ነው፡፡
 • ዋናው ጥያቄ ለበዓሉ ይደርሳሉ ወይ የሚለው ነው?
 • እንግዲህ የቻልነውን እያደረግን ነው፡፡
 • እንዲህ ዓይነት ነገር መስማት አልፈልግም፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ሥራውን እንዴት እንዳመጣሁት ታውቂያለሽ አይደል?
 • እንዴት ነው ያመጣኸው?
 • ከስንት ደላላና ኪራይ ሰብሳቢ ጉሮሮ ፈልቅቄ ያመጣሁት ሥራ ነው፡፡
 • የመጣው ግን ዘግይቶ መሆኑን ታውቃለህ?
 • አንቺ ሴትዮ ምን ሆነሻል?
 • ምን ሆንኩኝ?
 • ሥራ ጠፍቷል፤ ማሽኖቹ አፋቸውን ከፍተው ነው የሚውሉት ስትይኝ አልነበር እንዴ?
 • አልተሳሳትክም፤ እውነት ነው፡፡
 • አሁን ታዲያ ሥራ ሲመጣ የምን ወደኋላ ማፈግፈግ ነው?
 • እንግዲህ የቻልነውን እያደረግን ነው፡፡
 • አሁን ይደርሳል አይደርስም?
 • ይደርሳል ብዬ በአፌ ሙሉ መናገር አልችልም፡፡
 • እናንተ ጋ ግን ትልቅ ችግር አለ ልበል?
 • የምን ችግር?
 • የመልካም አስተዳደር ነዋ፡፡
 • ምን እያወራህ ነው?
 • በስንት ትግል ባመጣሁልሽ ሥራ እኔኑ ልታዋርጂኝ?
 • ለምንድን ነው የምትዋረደው?
 • ይኼን በዓል እኮ አገር ነው የሚጠብቀው፡፡
 • አሁን መፍትሔው ላይ ማተኮር ነው የሚያዋጣው፡፡
 • እኮ ይደርሳል ወይስ አይደርስም ንገሪኝ?
 • ይኸውልህ ሥራው ይደርሳል ግን በዓሉ የሚከበርበት ቦታ ሩቅ ስለሆነ እዚያ የሚወስድልን ትራንስፖርት ነው ችግሩ፡፡
 • ስለዚህ በአጭሩ አይደርስልኝም እያልሽኝ ነው?
 • ነገርኩህ እኮ ሥራውን እንጨርሰዋለን፤ ትራንስፖርት ነው ችግሩ፡፡
 • በቃ አዋረድሽኝ፤ ሥራውን አይነጥቀኝም ብለሽ ነው አይደል?
 • ምን እያወራህ ነው?
 • አንዴ ሥራውን ስለሰጠኝ አይወስድብኝም ብለሽ ነው?
 • ከራስህ ላይ ራስህ ልትነጥቅ?
 • እ…
 • አሁን ወደ መፍትሔው ብንሄድ ይሻላል፡፡
 • ምንድን ነው መፍትሔው?
 • መፍትሔውማ እጅህ ላይ ነው፡፡
 • እኮ ምንድን ነው?
 • አንድ ስልክ መደወል ነዋ፡፡
 • ማን ጋ?
 • ሥራው እንዳለቀ ቦታው የሚያደርስልን ሔሊኮፕተር ወይም አውሮፕላን አዘጋጅ፡፡
 • እንደዚያ ከሆነ ሊደርስ ይችላል?
 • በሚገባ፡፡
 • አንቺን እኮ ከሌሎቹ ሴቶች ለይቼ የመረጥኩበት ዋናው ምክንያት ይኼ አስተሳሰብሽ ነው፡፡
 • የቱ አስተሳሰቤ?
 • ይኼ ልማታዊ አስተሳሰብሽ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት እየሄደላችሁ ነው?
 • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • የበዓሉ ዝግጅት ነዋ፡፡
 • በዕቅዳችን መሠረት እየተከናወነ ነው፡፡
 • አንድም ችግር መስማት አልፈልግም፡፡
 • ግን ክቡር ሚኒስትር …
 • የምን ግን ነው?
 • አንዳንድ ሰዎች እየተቹን ነው፡፡
 • ምን ብለው?
 • ከደርግ ጋር እያመሳሰሉ፡፡
 • በምንድን ነው የሚያመሳስሉን?
 • ያው ደርግም 10ኛ የአብዮቱን በዓል አክብሯል፤ እኛም አሁን የምናከብረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል 10ኛ ዓመቱ ነው፡፡
 • ሚዲያ አትከታተልም ልበል?
 • ኧረ እከታተላለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሺ አገሪቱ በስንት ፐርሰንት እያደገች ነው?
 • ከአሥር በመቶ በላይ፡፡
 • ደርግ እያለ አገሪቷ በስንት ፐርሰንት ነበር የምታድገው?
 • ከዜሮ በመቶ በታች፡፡
 • አየህ ልዩነቱ እሱ ነው፡፡
 • የሚገርም ዕውቀት ነው እኮ ያለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ባክህ? እዚህ ቦታ ላይ ስትቀመጥ እኮ ተራ አስተሳሰብ ሊኖርህ አይችልም፡፡
 • ምጡቅ የሆኑ ሰው ነዎት፡፡
 • ለመሆኑ እንግዶቹ እየተጠሩ ነው?
 • ሰሞኑን የተያያዝነው እሱን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሱ ሥራችን ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡
 • ምን ዓይነት ጥንቃቄ?
 • ምንም ዓይነት ኪራይ ሰብሳቢ እዚያ ስብሰባ ላይ ማየት አልፈልግም፡፡
 • የቻልነውን እናደርጋለን ክቡር ሚኒስትር፣ በአብዛኛው የሚጠሩት ባለፈው ዓመት የመጡት ናቸው፡፡
 • እሱ ነው እኮ ችግሩ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ባለፈው ዓመት በርካታ ኪራይ ሰብሳቢና ደላላ ነበር የሞላው፡፡
 • ምን ዓይነት ሰው ይጠራ ታዲያ?
 • ልማታዊ ብቻ፡፡
 • አሁን ኪራይ ሰብሳቢውንና ልማታዊውን እንዴት መለየት ይቻላል?
 • ይህን የሚሠራ አንድ ተቋም ያስፈልገናል፡፡
 • የምን ተቋም?
 • ኪራይ ሰብሳቢን ከልማታዊ የሚለይ፡፡
 • ሌላው ክቡር ሚኒስትር፣ ለበዓሉ እያወጣን ያለው ወጪ ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል፡፡
 • እሱ አይመለከትህም ብዬ ስንቴ ነው የነገርኩህ?
 • አይ እንዳንተች ብዬ ነው?
 • ለመሆኑ ዋነኛ ወጪያችን ምንድነው?
 • የኅትመት ወጪ ነው፡፡
 • ይኸው ለዚያ ብዬ ነው በቅናሽ የሚታተምበት ቦታ ሥራውን የሰጠሁት፡፡
 • ለነገሩ ተባብረውናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ እንዲያውም ለዚህ ሥራዬ ሰርተፊኬት እፈልጋለሁ፡፡
 • የምን ሰርተፊኬት?
 • ልማታዊ ሰርተፊኬት፡፡
 • ልማታዊ ባለሀብት ነዎት ልበል?
 • ምን አልከኝ?
 • ማለቴ ልማታዊ ባለሥልጣን፡፡
 • እህሳ፡፡
 • ለማንኛውም ከሠራተኛው ጋር ስብሰባ ማድረግ አለብን፡፡
 • የምን ስብሰባ?
 • የሩብ ዓመት አፈጻጸማችንን አስመልክቶ መሰብሰብ አለብን፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ የመሥሪያ ቤታቸውን የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሠራተኞች ጋር ስብሰባ እያደረጉ ነው]

 • የዛሬው ስብሰባችን ዋነኛ ትኩረት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ይመለከታል፡፡ አስተያየት ያለው ይቀጥል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ አስተያየት አለኝ፡፡
 • የሥራ መደብሽን ንገሪኝ፡፡
 • እኔ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባል ነኝ፡፡
 • ምንድነው አስተያየትሽ?
 • ክቡር ሚኒስትር የሰው ምሬት ብሷል፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው በየጊዜው የሚመጣው ቅሬታ እጅጉን እየጨመረ ነው፡፡
 • ቅሬታው ምንድነው?
 • በዋናነት የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡
 • ምንድን ነው የሚሻለው?
 • ቅሬታዎቹ በአብዛኛው የሚያጠነጥኑት፣ ወሬ ብቻ ምን ያደርጋል ተግባር ላይ ዜሮ ናችሁ የሚሉ ናቸው፡፡
 • በቃ አሁን ወደ ተግባር መሄድ አለብን፤ ምን ይሻላል?
 • እኔማ ምን አውቃለሁ?
 • ያ ያቆምነውን ነገር መቀጠል አለብን፡፡
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • ጣት መቁረጡን፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተባባሰ ነው፡፡
 • እሱማ አፋጣኝ መፍትሔ የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡
 • መፍትሔውማ መቁረጥ ነው፡፡
 • ተስፋ መቁረጥ ክቡር ሚኒስትር?
 • ጣት መቁረጥ ነው እንጂ፡፡
 • ይሻላል ክቡር ሚኒስትር?
 • አዲሱ አቅጣጫችን እሱ ነው መሆን ያለበት፡፡
 • ምን ይደረግ ታዲያ?
 • ጨረታ ይውጣ፡፡
 • የምን ጨረታ?
 • ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ጨረታ ነው መሆን ያለበት፡፡
 • እኮ የምን ጨረታ ነው?
 • የጣት ቆራጮች ጨረታ፡፡
 • ያው እንደለመዱት ጨረታ ከሚወጣ እርስዎ ቢያመጧቸው አይሻልም?
 • መመርያውን መከተል አለብን፡፡
 • ሌላ ጊዜ ያለጨረታ እርስዎ ስለሚያመጡልን ብዬ ነው፡፡
 • እዚህ ላይ ልምድ ስለሌለን እንዳንሳሳት መጠንቀቅ አለብን፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ያው ጣት የሚቆርጥ ብለን እጅ የሚቆርጥ እንዳይመጣ ብዬ ነው፡፡
 • ለነገሩ እውነትዎትን ነው፡፡
 • ስለዚህ በአፋጣኝ ጨረታው ይውጣ፡፡
 • ከየት አገር ግን ልናገኝ እንችላለን?
 • ያው ከወዳጃችን ቻይና ነዋ፡፡
 • ለነገሩ እነሱ የማይሳተፉበት ዘርፍ የለም፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ሚኒስትር ደወሉ]

 • ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ሥራው እንዴት ይዟችኋል?
 • ይኸው ቀና ደፋ እያልን ነው፡፡
 • መቼም አሪፍ በዓል እናከብራለን ብዬ እጠብቃለሁ?
 • ለዚህ እኮ ነው ሌት ተቀን እየለፋን ያለነው፡፡
 • የልፋታችሁን ፍሬ በቅርቡ እንበላዋለና፡፡
 • ምን እያሳሰበኝ እንደሆነ ታውቃለህ?
 • ምን ያሳስብዎታል ክቡር ሚኒስትር?
 • እዚህ በዓል ላይ ደላላና ኪራይ ሰብሳቢ እንዳይገኝ እፈልጋለሁ፡፡
 • እሱን ማድረግ ይቻላል ብለው ነው?
 • ለምን አይቻልም?
 • ደላላ ያልገባበት ቦታ የለማ፡፡
 • እንዴት?
 • ባለሥልጣኑ ጋ፣ ባለሀብቱ ጋ በቃ ሁሉም ጋ ነው ያለው፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የሚሻለው?
 • ማደራጀት ነዋ፡፡
 • በምን?
 • በአንድ ለአምስት፡፡
 • ምኖቹን?
 • ደላሎቹን ነዋ፡፡
 • ምን ለማድረግ?
 • ልማታዊ ደላላ፡፡
 • ይሻላል ብለህ ነው?
 • ሌላ ምንም መፍትሔ የለውማ፡፡
 • ለነገሩ ልማታዊ ሆነው ደላላም ቢሆኑ ችግር የለውም፡፡
 • እሱን እኮ ነው የምልዎት፡፡
 • ልማታዊ ከሆኑ በኋላ ደግሞ እንዲመሠርቱ እናደርጋለን፡፡
 • ምን?
 • የደላሎች ፎረም፡፡